Telegram Web
🕊

[  † እንኳን ለቅዱሳን ቅዱስ ኄኖክ : ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ : ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊   †  ቅዱስ ኄኖክ   †   🕊

† ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ቅዱስ ኄኖክ ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ ነው:: አዳም: ሴት: ሔኖስ: ቃይናን: መላልኤል: ያሬድ ብለን ሰባተኛው ኄኖክ ነውና::

ቅዱሱ የማቱሳላ አባትም ነው:: አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉም ሞትን ያላየ: ብሔረ ሕያዋን የገባ የመጀመሪያው ሰው ሁኗል:: ለአዳም ልጆችም ተስፋ ድኅነት እንዳለ ማሳያ ሁኗል:: "በአቤል አፍርሆሙ: ወበኄኖክ አንቅሆሙ" እንዳለ ሊቁ::

ቅዱስ ኄኖክ በ፲፬፻፹፮ [1486] ዓ/ዓ የመጀመሪያውን የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል [መጽሐፈ ኄኖክን] ከመጻፉ ባሻገር በብዙ ሥፍራ በክብር ተጠቅሶ ይገኛል::


🕊 † ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ †  🕊

† ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው:: ወደ ክርስትና የመጣው በ40ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው::

በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል:: ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር:: ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር:: በኤፌሶንም ጵጵስናን ሹሞ ፪ መልዕክታትን ልኮለታል:: ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል::
ዛሬ ሥጋው ከኤፌሶን ወደ ቁስጥንጥንያ የፈለሰበት ነው፡፡ ጊዜውም ፫፻፴ [330] ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ይታመናል፡፡

"መድኃኒታችን እግዚአብሔር: ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ: በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ:: ከእግዚአብሔር ከአባታችን: ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን: ጸጋና ምሕረት: ሰላምም ይሁን . . ." [፩ጢሞ. ፩፥፩]


🕊 † ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት † 🕊

† ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል: ገብርኤል: ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::

በሦስቱ ሰማያት ካሉት ዘጠኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ [የሥልጣናት] መሪ [አለቃ] ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብን ያሳራው: ከጥፋት ውኃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት:: ዛሬ ደግሞ የሊቀ መልአኩ ቅዳሴ ቤቱ ነው::

† የይቅርታ ጌታ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አይተወን . . . አይጣለን !

[  † ጥር ፳፯ [ 27 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ኄኖክ ነቢይ [ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረገበት]
፪. ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ [ፍልሠቱ]
፫. ቅዱስ አባ ቢፋሞን ሰማዕት
፬. ቅዱስ ሰራብዮን ሰማዕት
፭. ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት [ከሰባቱ ሊቃናት አንዱ]

[    † ወርኀዊ በዓላት    ]

፩. መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ
፪. አቡነ መባዐ ጽዮን
፫. አባ መቃርስ ርዕሰ መነኮሳት
፬. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት [ንጉሠ ኢትዮጵያ]
፭. ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
፮. ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ

" የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ:: " † [፩ጴጥ. ፪፥፳፩-፳፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#ቹሩ_መድኃኔዓለም

#አቤቱ__ጌታዬ_ሆይ ወደ አንተ ስጣራ ስማኝ የልመናዬንም ቃል አድምጥ እንደ በደለው ልጅ #በመጸጸት አቤቱ በሰማይም በፊትህም በደልሁህ እላለሁ ሉቃ 15:18 በእውነት ሰውን የምትወድ አንተ በፊትህ ተቀበለኝ #ጸሎቴንም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ተቀበለኝ እንደ ቀራጩ ሰው በንስሀ ይቅር በለኝ ጌታዬ ብዬ ለመንኩህ እኔ #ኃጢአተኛ ነኝ ባንተ ዘንድ ግን ብዙ ይቅርታና ምህረት #አለ::

#መልካም_ቀን🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
                          †                          

[    🕊    ገ ድ ለ   ቅ ዱ ሳ ን   🕊     ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[ ቅዱስ መቃርዮስ ካስተማረው ትምህርት ]

        [       ክፍል  ሰማንያ አንድ     ]

                         🕊  

[ አባ ወቅሪስን ስለ ትዕግሥትና ራስን ስለ መካድ አስተማረው ! ]

🕊

❝ ዳግመኛም አባ ወቅሪስ እንዲህ አለ ፦ “ በቀኑ ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ በሆነበት ሰዓት [ቀትር] ላይ አባ መቃርዮስን ላየው ሄድሁ፡፡ በጥም እየተቃጠልሁ ነበርና ፦ 'አባቴ ሆይ ፣ በጣም ተጠምቻለሁ' አልሁት፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ፡- “በጥላው ዐረፍ ማለት ይብቃህ ፣ በዚህ ሰዓት ላይ በመንገድ እየተቃጠሉ ጥላ እንኳ ማግኘት የማይችሉ ብዙ ሰዎች አሉና፡፡”

ከእነዚህ ቃላት በኋላ ከእርሱ ጋር ስለ መልካም ምግባር ሕይወት ተነጋገርኩ፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ ፦ “ልጄ ሆይ ፣ በእውነት ሰውነቴን በዳቦና በውኃ ሳልሞላ ፣ ትንሽ ሽለብ እስኪያደርገኝ ድረስ ከግድግዳ ጠጋ ከምል በስተቀር ዕንቅልፍ ሳላጠግብ ሃያ ዓመት አሳልፌያለሁ፡፡ ❞

🕊

የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡

ይቆየን !


💖                      🕊                      💖
                         †                        

 [       🕊    ፍኖተ ቅዱሳን    🕊      ]

[ የቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስናና የተጋድሎ ሕይወት ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

             [        ትሕትና !         ]

------------------------------------------

❝ በአፉ ዐረፋ እስኪያስደፍቀው ድረስ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው አንድን መነኵሴ ፊቱን በጥፊ መታው፡፡ መነኵሴውም ሌላኛውን ፊቱን አዙሮ ሰጠው:: በዚህ ጊዜ ጋኔኑ የመነኲሴው ትሕትናው ስላቃጠለው ወዲያውኑ ከሰውዬው ወጥቶ ጠፋ፡፡ ❞
-------------------------------------------

❝ አጋንንት ለምን ይህን ያህል አጽንተው ይዋጉናል?" ብለው አንድን አረጋዊ ጠየቁት፡፡ እርሱም ፦ "መሣሪያዎቻችንን አሽቀንጥረን ስለ ጣልናቸው ነው ፤ መሣሪያዎቻችን ማለቴም ክብርን መናቅን ፣ ትሕትናን ፣ ድህነትንና ጽናትን ማለቴ ነው" አላቸው፡፡ ❞

--------------------------------------------

🕊

የደጋግ አባቶቻችን ጸሎትና በረከት ይደርብን፡፡


†                         †                         †
💖                      🕊                      💖
💛
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊       [   ምክረ ቅዱሳን   ]        🕊

▷     "  ትእግስትና ታዛዥነት !  "

💖 አቡነ አትናቴዎስ ዘእስክንድር 💖 ] 

[                        🕊                        ]
-------------------------------------------------

❝ እነሆ ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን ፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል ፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል ፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። ❞

[   ያዕ.፭፥፲፩  ]


🕊                       💖                     🕊
🕊

[  † እንኳን ለጌታችን አማኑኤል ክርስቶስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊  † ተአምረ እግዚእ †  🕊  ]

† " ተአምር " የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል:: መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው:: ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ [በላይ] : ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ [ሲፈጸም] ተአምር ይባላል::

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው:: ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው::

እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል:: በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ [ኦሪትን ተመልከት] እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ [፩ ነገሥት] እንደ ነበር ይታወቃል::

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል:: በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል:: [ ማቴ.፲፥፰ , ፲፯፥፳ , ማር.፲፮፥፲፯, ሉቃ. ፲፥፲፯, ዮሐ.፲፬፥፲፪ ]

እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: [ሐዋ. ፫፥፮ , ፭፥፩ , ፭፥፲፪ , ፰፥፮ , ፱፥፴፫-፵፫ , ፲፬፥፰ , ፲፱፥፲፩]


🕊  † ተአምራተ እግዚእ †  🕊  ]

† ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: እያንዳንዱ ግን ቢጻፍ ዓለም ለራሷ ባልበቃች ነበር:: ከእነዚህ መካከልም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ዕለት በ፯ እንጀራ እና በጥቂት ዓሣ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር ፬ ሺህ ሰዎችን በቸርነቱ አበርክቶ አጥግቡዋል:: ደቀ መዛሙርቱም ፯ ቅርጫት ማዕድ አንስተዋል::

ጌታችን በከሃሊነቱ የተራቡትን ሲያጠግብ እንዲሁ አይደለም:: በጊዜው የነበሩ አይሁድ ጠማሞች ነበሩና እነሱን ምላሽ በሚያሳጣ መንገድ ነበር እንጂ:: አይሁድ ላለማመን ብዙ ጥረት ነበራቸውና::

በዚህ ዕለትም እንጀራውን አበርክቶ ሲያበላቸው :-

፩. ጊዜው አመሻሽ ላይ ነበር:: ምክንያት :- ጧት ላይ ቢሆን ከቤታችን የበላነው ሳይጐድል ብለው ከማመን ይርቁ ነበርና::

፪. ከውሃ ዳር አድርጐታል:: መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::

፫. ሳር የበዛበት ቦታ ላይ አድርጐታል:: ምክንያቱም መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::

፬. ከከተማ አርቆ ምድረ በዳ ላይ አድርጐታል:: ያማ ባይሆን "ፈጣን: ፈጣን ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው እየገዙ አቀረቡለት" ባሉ ነበርና::

† ለመድኃኒታችን ክርስቶስ አምልኮና ምስጋና ይሁን !

አማኑኤል አምላካችን ጣዕመ ፍቅሩን ያሳድርብን::

🕊

[  † ጥር ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት [ስለ ሃይማኖት ፯ ጊዜ ሙቶ የተነሳ , ፯ አክሊል የወረደለት ]
፪. ቅዱስ አካውህ መነኮስ
፫. ፰ መቶ "800" ሰማዕታት
፬. ቅዱስ ዮሴፍ አይሁዳዊ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፮. ቅድስት ሳቤላ

[   † ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. አባቶቻችን አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ
፪. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፫. ቅዱስ እንድራኒቆስና አትናስያ
፬. ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

" ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ :- ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ:: በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም' አላቸው::

ደቀ መዛሙርቱም :- 'ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?' አሉት:: ጌታ ኢየሱስም:- 'ስንት እንጀራ አላችሁ?' አላቸው:: እነርሱም:- 'ሰባት: ጥቂትም ትንሽ ዓሣ' አሉት::

ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ:: ሰባቱንም እንጀራ: ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ:: ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ:: ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ:: ሁሉም በሉና ጠገቡ:: የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሱ:: የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ::
"
† [ ማቴ.፲፭፥፴፪ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2025/02/05 02:53:18
Back to Top
HTML Embed Code: