Telegram Web
እነዚህ አጋጣሚዎች ለእኔ እጅግ አስተማሪዎች ነበሩ። እውነት ለመናገር ስለሌሎች ከመናገር በፊት እነዚያ አካላት የሚሉትን በትክክል ማወቅ በእጂጉ አስፈላጊ መሆኑንና ስለተለያዩ ብቻ እያነሡ መለጠፍ፣ እንደ ልብ መናገር በጣም አደገኛ መሆኑን የተማርሁት ይህን ከመሰሉ ስለእኛ ከተነገሩ እጂግ የተሳሳቱ ትምህርቶች ፣ ጽሑፎች እና አመለካከቶች ነው። ከዚያም ወዲህ ትላልቅ የሚባሉት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ሊቃውንት ጽሑፎች ውስጥ ሳይቀር ይህን የመሰለውን ስለእኛ ያላቸውን የተሳሳተ እምነታቸውን ሳይ በእጂጉ አዝናለሁ፤ በዚያ ምክንያትም የሥራዎቻቸውን ደኅና ነገር ሁሉ በዚያው ዓይን እያየሁ እንድጠራጠራቸው እሆናለሁ።

ይህን ሁኔታ በሌሎችም አይቻለሁ። በተለይ በእስልምናው ሐዲዝ ላይ እኛን መነኮሳቶቻቸውንና ሊቃውንቶቻቸውን ያመልካሉ ብለው የጻፉት ሁልጊዜ ሲያስቀኝ እና ሲያስገርመኝ ይኖራል። እንዲህ ያለው ችግር በርግጥ በእኛም ዘንድ አለ። በተለይ ካቶሊኮች እመቤታችንን ኃይል አርያማዊት ናት ይላሉ የሚለው አሳፋሪ ነገር እስካሁንም የሚናገሩት ሞኞች አሉ። በነገራችን ላይ ለእመቤታችን ወላጆች በተለይም ለቅድስት ሀና ብዙ ቤተ ክርስቲያን በመሰየም የካቶሊኮችን ያህል የሚኖር አይመስለኝም። ተመልከቱ እንግዲህ ይህ ሁሉ ባለበት ነው እመቤታችንን ኃይል አርያማዊት ናት ይላሉ የሚል የስሚ ስሚ ወሬን በአደባባይ ሳይቀር በድፍረት እንናገር የነበረው።

ዋናው የፈለግሁት ነገር ሌሎች እኛ ያልሆንነውን ብለዋል ሲሉ እኛን የሚሰማንን ያህል ወይም ከዚያም በላይ የናም የግምት ንግግር ሌሎቹንም ልክ እንደእኛ እንዲሰማቸው ያደርጋል። በግሌ ስለሌሎች በድፍረት መናገር ምን ያህል ስሐተት እንደሆነ እና እኔን የእነርሱ ደጋግሞ እንደሚያሳዝነኝ እነርሱንም የእኛ እንዲህ ሊያደርጋቸው እንደሚችል እና ስለማንኛውም አካል ስለምንናገረው ነገር በእጂጉ መጠንቀቅ እንዳለብኝ የተማርኩት ከእነዚህ አጋጣሚዎች ነበር።
የሚያሳዝነው ግን አሁንም እየሆነ ያለው እንደዚያው መሆኑ ነው። አሁንም ሰዎች ራሳቸው ስለሚያምኑት ነገር ከሰዎቹ በላይ ሆነው እንዲህ ነው የሚያምኑት እያሉ መናግር እጂግ በጣም አደገኛ ስሕተት ነው። የተጠራጠረ ሰው ማድረግ ያለበት መጠየቅ ነው። ከዚያ ራሳቸው የተጠየቁት አካላት እምነታቸውን አስተሳሰባቸውን አረዳዳቸውን በግልጽ ያስረዱ። እዚይ ላይ ምን ለማለት እንደፈለጉ ደጋግሞ እየጠየቁ ማጣራት እና በትክክል መረዳት መቅደም አለበት ። ካለበለዚያ ዲዮስቆሮስ አውጣኪያዊ ነው ብለው እስካሁን በስሕተት እንደሚያምኑት እና ስለማናምነው ነገር ከእኛ በላይ ሆነው እንዲህ ነው የምታምኑት እንደሚሉን አንዳንድ ምሥራቃውያን ከመሆን የዘለለ ጠቀሜታ የለውም።
©ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ዕውቀትን በተመለከተ

አንድ ወንድም ከቲክታክ ውይይት ሰማሁት ብሎ የጠየቅኝ ጆሮጅዬን ጭው ነው ያደረገኝ። አንዳንድ ተወያዮች እድገት ያመጡ እና ከፍ ያለ ዕውቀት ላይ የደረሱ እየመሰላቸው ነው መሰል በአብና በወልድ መካከል ገብተው ሁሉ አስተያየት እየሰጡ መሆኑን (የጠየቀኝ ሰው ያለኝን ቃለ በቃል መድገም አልፈለግሁም) ከጥያቄው ተረድቻለሁ። ኪሩቤል ቀና ብለው ወደማያዩት ዙፋን፣ ሱራፌል በሁለት ክንፎቻቸው እግራቸውን በሁለት ክንፎቻቸው ፊታቸውን ሸፍነው ሁለት ክንፎቻቸውን ደግሞ ዘርግተው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ከማመስገን ውጭ ወደ ማይደፍሯት ዙፋን ወይም ገናንነት መግባት የሚፈልግ ሕሊና በፍጥነት በንስሐ መመለስ አለበት ብዬ አምናለሁ።

አንድ ወንድም አንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር ገጥሞት ነበር። ከጓደኛው ጋር ወደ ጎንደር በሔዱበት ወቅት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራን ሰላም ለማለት በገቡበት ጥያቄ አነሣ። ምሥራቅ ኦርቶዶክሶች በአንድ አካል ሁለት ባሕርይ የሚሉት ባሕርየ ትስብእት ከባሕርየ መለኮት ጋር ከተዋሐደ ፣ ወልድ ደጎሞ በባሕርይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ስለሆነ እንዴት ሊይድርገው ነው ይላሉ ብሎ ይጠይቃል፤ እንደማስታውሰው ነው። ሊቀ ሊቃውንትም እርሱ ከበደኝ አላለ እናንተን ምን አስጨነቃችሁ ብለው መለሱለት ብሎ የነገረኝን ባስታወስኩ ቁጥር እደነቃለሁ። (በአጻጻፍ የሳትኩት ካለ ሓላፊነቱ የእኔ ነው)። መልሱ ሁልጊዜ ያስደስተኛል። ምክንያቱም በሥላሴ አንድነት ውስጥ ገብታ ቦታ ለማካፈል የምትደፍር ኅሊና እንዴት ያለች ደፋር እና አላዋቂ ናት በእውነት ። ሙሴ እንኳ ወደ ዕፀ ጳጦስ ለመጠጋት ጫማውን እንዲያውልቅ ታዝዞ ነበር። የቀረበውም በረዓድ እና በመንቀጥቀጥ ነበር። ምሳሌው ለተመረጠው ለሙሴ እንኳ እንዲያ የሚያስፈራ ከሆነ አማናዊው የተዋሕዶ ምሥጢርም ይልቁን ምን ያህል ትሕትና እና ጥንቃቄ ይፈልግ ይሆን?

የተገለጠና እና በትክክል የምናውቀው እንኳ ቢሆን እንዲህ ያለው ይዘት በፍጹም ለማኅበራዊ ሚዲያ የሚሆን አይደለም። እውነቱን ለመናገር “የተቀደሰውን ለውሾች አት ስጡን” ለምን አንጠብቀውም የሚለውን እጠይቅና የተቀደሰውን ስለማናውቀው ይሆናል በሚል መልስ እንደገና እቆማለሁ። በርግጥም የምናውቀው አይመስለኝም። ይህ ሁሉ እንግዲህ ኦርቶዶክሳዊውን ነገረ ዕውቀት በመጠቆም ለማሳሰብ እንደ መግቢያ ያነሣሁት ነው።

ሴባስቲያን ብሮክ የሚባለው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የኦሬንታል በተለይም የሶርያ ኦርቶዶክስ አባቶችን ጽሑፎች በተመለከተ ብዙ ካጠና በኋላ ሀሳቦቹን ካጋራባቸው መጻሕፍት አንዱ ሰሞኑን በሕሊና በለጠ ብርህት ዓይን ተብሎ የተተረጎመውን The luminous Eye የተባለ መጸሐፍ ጽፏል። ብሮክ በዚህ መጽሐፉ ካነሳቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የምሥራቃውያን (ኦሬንታል) አባቶች ትምህርታቸውን እንደ ምዕራቡ በነገረ ጉዳይ የተደራጀ (Systematic) ለምን አላዳረጉትም የሚለው ይገኝበታል። (ይህን ስጽፍ መጽሐፉን እያየሁ ስላልሆነ በትክክል ባልገልጸውም አሁን) እርሱ የሚለው የኦሬንታል ሊቃውንት የምዕራብ ሊቃውንት ያደረጉትን ማድረግ ስለማይችሉ ወይም አቅም ስለሌላቸው ሳይሆን ስለኦርቶዶክስ ነገረ ዕውቀት ባላቸው መረዳት ምክንያት ነው። ለምሳሌ የምዕራብ ሊቃውንት አንድን ጉዳይ ብያኔ (definition) ሰጥተው ይጽፋሉ። ለምሥራቃውያን ደግሞ ብያኔ ችግር ያመጣል።

ምክንያቱም መበየን ማለት ለነገሮች ድንበር መሥራት፣ መከለል፣ መለየት፣ መወሰን ማለት ነው። ነገረ ሃይማኖት ደግሞ ለሰው ልጅ አእምሮ በሚመጥን ከእግዚአብሔር የተገለጠ መለኮታዊ ሀሳብ ነው። ያን መልኮታዊ ሀሳብ ደግሞ ጥልቀቱን መወሰን እና ለዚያም ድንበር ማበጀት አይቻልም። የሰው ቋንቋም ለሰው ማስረዳት ቢችልም ነገረ አምላክን ወስኖ መያዝ ግን አይችልም። ስለዚህ እግዚአብሔር በገለጠልን መጠን እናብራራዋለን (እንተረጉመዋለን) እንጂ ልንወስነው ወይም በብያኔ ልንዘጋው አንችልም የሚል እምነት ወይም አረዳድ ስላላቸው ብያኔ እና ብያኔያዊ አካሔድ አይጠቀሙም የሚል ማብራሪያ ይሰጣል። ይህን ሀሳብ በየንታ እሸቱ ርጢን መጽሐፍ መቅድም ላይ ለመጠቆም ሙከራ አድርጊያለሁና ያንንም ማየት ይቻላል።ይህን እውነታ ከእኛም ሆነ ከሌሎች የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት ይቻላል።

ኦሬንታሎቹን ብቻ ሳይሆን እኔ እስካየሁት ድረስ ምሥራቅ ኦርቶዶክሶችን ከምዕራቡ (ከካቶሊክም ከሮቴስታንትም) ከሚለዩን መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ይህን የሚመለከት ነው።
ሌላውና መሠረታዊው የኦርቶቶዶክስ ነገረ ዕውቀት የሚያጠነጥነው ደግሞ መገለጥ ላይ ነው። መገለጥ በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም በሮማ ካቶሊክ በተለይም ደግሞ ከቶማስ አኲናስ መምጣት በኋላ (በእምነት መግለጫዋ ላይም እንዳለው) የሰው አእምሮ ወይም የመረዳት ችሎታ (reason) ብቻውን እግዚአብሔርን በርግጠኝነት ለማወቅ በአጠቃላይ ሃይማኖትን ለማወቅ በቂ ነው ብለው ያምናሉ። (ይህን ሀሳብ Thinking Orthodox እና የመሳሰሉትን መጻሕፍት አንብቦ የበለጠ መረዳት ይቻላል።)

በሁለቱም ኦርቶዶክሶች ግን ይህ ሀሳብ ተቀባይነት የለውም። እንደዚህ ከሆነ ሃይማኖት ከሳይንስ የሚለይበት መሠረታዊ ነገር ይጠፋል ወይም ያንሣል። ይህን ጉዳይ አሁንም በስፋት መግባት ባልፈልግም ኦርቶዶክሳዊው ነገረ ዕውቀት ከዚህ በጅጉ የራቀ እና የተለየ መንገድ ያለው ነው። ምንም እንኳ ሲስተማቲክ ቲዖሎጂ በእኛም ተቋማት እየተሰጠ እና በዚሁ መንገድ መጻሕፍት እየተጻፉና እየተዘጋጁ ቢሆንም መሠርታዊ ጥንቃቄ እና ኦርቶዶክሳዊውን ድነበር መጠበቅ ግን በብዙ የምሥራቅ ሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ብቻ ሳይሆን የተለመደም ጭምር ነው።

በኦርቶዶክሳዊያን ዘንድ ደግሞ በሰው አእምሮ አድሮ የሚናገረው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ይህም በጥልቅ መግቦቱ ለሰው ልጆች በመግለጥ የሚያሳየው ነው። ሰዎች በቅጥነተ ኅሊና ማለትም አእምሮአቸውን በማራቀቅ ብቻ ሊደርሱበት የሚቻላቸውም አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን “እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤” /1ኛ ቆሮ 3 ፤ 1 – 2/ የሚላቸው በክርስትና ለመንፈሳዊ ሕይወት ሕጻናት ስለሆኑ እንጂ ለእውቀት ለፍልስፍና እና ለአመክንዮ ሕጻናት ሆነው አልነበረም ባዮች ናቸው። ስለዚህ በመንፈሳዊ ሕይወት በተጋድሎ ውስጥ በምትገኝ የማትቋረጥ መገለጥ የሚሰጥ እንጂ የሰው አእምሮ የማሰብ ችሎታ ብቻውን ይደርስበት ዘንድ አይቻልም ብለው ያምናሉ። በተለይም ደግሞ መጀመሪያ ቅዱስ ወግሪስ እንደተናገረው የሚታመነው “እውነተኛ የነገረ ሃይማኖት ዐዋቂ የሚጸልይ ሰው ነው” የሚለው አባባል የሰው የሃይማኖት ዕውቀት የመረዳት ችሎታ ላይ እንዳያርፍ መጠበቂያ አጥራቸው ነው።

የኦርቶዶክሳዊ ነገረ ዕውቀት ሦስተኛው መሠረታዊ መለያ ደግሞ ሃይማኖታዊ ዕውቀት በመሠርቱ ለሰዎች ድኅነት ቅድሚያ የሰጠ (Pastoral) መሆኑ ነው። ይህም ማለት ጉዳዮች የሚብራሩት የሚተረጎሙት የሚሰበኩት የሰውን ድኅነት ቅድሚያ ሰጥተው እንጂ ለዕውቀት እና ለርቃቄ ተብለው አይደለም። ከዚህ የተነሣ ለድኅነት ከሚጠቅመው ውጭ እንኳን እንዳሁኑ ማንም ሊያየው በሚችል ሚዲያ ይቅርና ለኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን የጉባኤ ቀለም ለመናገር እና ለማራቀቅ የሚደክም የለም፣ ሲያጋጥምም አይመሰገንም። ምክንያቱም ለድኅነታቸው
ሳይሆን ለመመስገን፣ ለምደነቅ ወይም ለመከበር ተብሎ ስለሚሆን እና እነዚህም ጠባያት ደግሞ የሥጋ ጠባዮች ስለሆኑ እነዚህ መግቢያ አድርጎ ሰይጣን እንዳያስተውም ስለሚፈራ ነው።

ሁልጊዜም ቢሆን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ችግሮች የሚፈጠሩት ቲኦሎጂን ወይም ነገረ እምነትን ለአማኞች ድኅነት ቅድሚያ ሰጥቶ ማስተማር ቀርቶ የራስን ፍላጎት ለማርካት በሚደረግ አላስፈልጊ ዕውቀት መሰል ክርክር ውስጥ ነው። ይህ ጉዳይ ከዚህም አልፎ ክርክር በማያስነሡ ጉዳዮች እንኳን የሚነሣው የተለየ ነገር ተናግሮ ማስደነቅና መከበርንም ሆነ ሌላ ነገር ሲፈለግ የሚያጋጥም ስለሆነ ነው።

እንዲያውም ከዚህም አልፎ አሁንም ብዙ ገዳማዊያን ሊቃውንት አንድ መሠረታዊ ሥጋታቸውን ደጋግመው ሲያነሡ አይቻለሁ። ይህም አሁን አሁን ኦርቶዶክሳዊያን ክርስትናን ወደ ዕውቀትነት እያወረዱት ነው የሚል ሥጋት ነው። ይህ ሥጋታቸው ደግሞ ተራ ሥጋት አይደለም። በአሁኑ ጊዜ በርከት ያሉ ኦርቶዶክሳዊያን ክርስትናን ያጠኑታል፣ ለማወቅ ይጥሩለታል፣ ይወድዱታል፤ በዚያም ደስተኞች ይሆናሉ። ከዚህም የተነሣ ወደ እውነተኛው የመዳን ዕውቅት ሳይሸጋገሩ ልክ እንደ አካዳሚክ ዕውቀት በጥናት ላይ ብቻ ተመሥርተው ይቀራሉ። ይህ ባሕል እየሆነና እየተለመደ ስለሔደ ክርስቲያናዊው እውነተኛው ሕይወታዊውን ዕውቀት አካዳሚያዊ ዕውቀት እየተካው ስለሆነ ክርስትና አደጋ ላይ ነው ያለው ይላሉ። ይህን የሚሉበት ምክንያት ክርስቲያናዊ ዕውቀት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት በማድረግ ከመነገር በላይ ወደ ሆነው ወደ ሚኖረው ዕውቀት ካልተሸጋገረ አካዳሚያዊ ዕውቀት ይሆናል። ከዚህም የተነሣ እንደማንኛውም አካዳሚያዊ ነገር በሰው አእምሮ መረዳት (reasoning) ላይ ይወሰንና ስፉሕ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ሲመጡ ያንን የሚያሻሽሉት የሚያስፋፉት፣ ጠባብ አእምሮ ያላቸው ሲይዙት ደግሞ እንደዚያው የሚያጠብቡት ይሆንና በመጨረሻም በሒደት የመበረዝ ፣ የመለወጥ ፣ የመጥፋት አደጋ ይገጥመዋል የሚል ተጨባጭ ሥጋት አላቸው።

የእኛ ዘመን ተሟጋች ትውልድ ደግሞ አብዛኛው መጀመሪያ የተማረው ዘመናዊውን ወይም ምዕራባዊውን ትምህርት ነው። ይህን አስቀድሞ መማር በራሱ ችግር አይደለም፤ ( ሊሆንም አይችልም። እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ባስልዮስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮ ዘእንዚናዙ እና ሊሎችም ጭምር መጀመሪያ የተማሩት የዓለሙን ፍልስፍና ነውና። የእኛ ትውልድ ግን ከመጠን በላይ ሲስተማቲክ በሆነው አካዳሚክስ ውስጥ ከማለፉ የተነሣ ነገሮችን ሳያውቀው በዚያ መጠን የመበየን፣ ጨርሶ የማወቅ እና አቋም መያዝ ድረስ መድረሱ ችግሩ ብቅ እያለ መሆኑን ያመለክታል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ክርስትናን ከትምህርት ከሚገኝ መጠነኛ ዕውቀት በሕይወት ወደሚደረስበት የመረዳት ዕውቀት ካልተሸጋገረ ችግር መግጠሙ አይቀሬ ነው። በሰሚዕ የሚገኝ ዕውቀት እና እምነት መግቢያ በር እንጂ መድረሻ አዳራሽ ወይም ቤት አይደለምና።

ይህ ጉዳይ ራሱን የቻለ ብዙ እንድንማማር የሚያደርግ ስለሆነ ጊዜውና ችሎታው ያላችሁ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ሰፋ ያለ ዕውቀት ብታካፍሉን ብዙዎቻቸን መንገዳችንን ለማቃናት ብዙ ይጠቅመናል፤ ጉዳዮችን በአካዳሚ መንገድ እና ዓይን ከማየት፣ አለፍ ሲልም እንደ ፖለቲካ አቋምን ከመለካካት ሊያተርፉን ይችላሉ፤ ሲሆን ሲሆን ደግሞ ወደ መንፈሳዊው ዓለም እንድንገባ እና መንገዳችንን ወደዚያ እንድናደርግ ሊረዱን ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።

ከሰሞኑ ውይይቶች በተለይ አስተያየት መስጫ ላይ የማያቸው ጥያቄዎች እና መልሶች ብዙዎቹ ትውልዱ ወደዚህ አካዳሚያዊ የነገረ መለኮት ዕውቀት ሳያውቀውም ቢሆን እያደላ መሆኑን የሚጠቁሙ ይመስለኛል። በእኔ መረዳት ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ዕውቀት አቀራረብ ቀርቶ ምዕራባዊ የምነለውንና የራሱ ሥነ ሥርዓት ያለውንም ያንን እንኳ የማያሟሉ፣ የነገሮቹን መቅድማቸውን እንኳ በውል ሳናገኘው አንኳር ጉዳዩ ላይ ገብተን እንደዚያ ያለ አስተያየቶች መወራወራችን በእጂጉ ያስፈራል። ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው በእጂጉ ያስፈራል። እኔን እስከገባኝ ደርሰ ከፍተኛ ድፍረት የተሞላው የአላዋቂ ክርክር ወስጥ መሆናችንን በታላቅ ትሕትና (ነገሩ እንኳ ሳስበው ድፍረትም ጭምር ነው) መጠቆም እፈልጋለሁ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ልናደርጋቸው የሚገቡንን ውይይቶች እና ትምህርቶች በተመለከተ እኔ ከጠቆምኳቸው እና ከሌሎቹም መሠረታዊ ትውፊቶቻችን አንጻር በማየት በውስጥ መወያየት እና አቀራረቦችን ማስተካከል ይቻላል፤ ይገባለም ብዬ አምናለሁ። አበቃሁ። መልካም ጾም ይሁንልን።

©ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
«ዝክረ ኒቅያ» ሀገር አቀፍ የሊቃውንት ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው!

የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ /አዲስ አበባ)

<<የሊቃውንት ብዛት ለዓለም መድኃኒት ነው>>

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ታሪካዊና በዓይነቱ ልዩ የሆነ <<ዝክረ ኒቂያ>> የተሰኘ ሀገር አቀፍ የሊቃውንት የምክክር ጉባኤ ከሚያዚያ 20 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለማካሔድ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ የጉባኤውን ዓላማ እና ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሕዝብ ግኑኝነት ጽ/ቤት መግለጫ በሊቃውንት ጉባኤ ተሰጥቷል፡፡

በቀደምት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥያቄዎችና የኑፋቄ ትምህርቶች ሲነሱ መልስ ለመስጠት ሊቃውንቱ ተሰባስበው ምላሽ የሚሰጡ መሆኑንና አሁንም በቤተ ክርስቲያን ላይ በነገረ ሃይማኖት እንዲሁም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተለያዩ ኑፋቄና ቀኖናዊ ጥያቄዎች እየተነሱ በመሆኑ የሊቃውንት መሰባሰብ አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ 

ጉባኤው ከጥር 26-29 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለማካሄድ ታቅዶ እንቅስቃሴ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፡-

1ኛ) ጉባኤው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የጉባኤ ቤት መምህራንና ሊቃውንት የሚታደሙበት እንደመሆኑ፥ በተለይ በጠረፉ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ መምህራንን በበቂ ቊጥር ለማካተት እንዲቻል ፥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተጨማሪ ጊዜ በማስፈለጉ ፤

2ኛ) በጥር ወር በርካታ ሀገራዊ ክንውኖችና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት በየአካባቢው የሚካሄዱ በመሆናቸው የጉባኤው መካሄጃ ጊዜ እንዲስተካከል ከአንዳንድ አህጉረ ስብከት በተደጋጋሚ አስተያየት በመሰጠቱ ፤

3ኛ) ጉባኤው ከዘመናት ቆይታ በኋላ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድና በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ውይይቶችን በማካሄድ ፥ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚጠቅም የውሳኔ ሐሳብና አስተያየት የሚያቀርብ ፥ አልፎም የአቋም መግለጫ የሚያወጣ መሆኑን  ከግምት ውስጥ በማስገባት የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፥ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፥ የጉባኤ ቤት መምህራንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፥ የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት ከሚያዝያ 20-25 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚካሄድ ይሆናል።

በጉባኤው፡- ያለውን ማጽናት፣ የጠመመውን ማቅናት፣ የጠፋውን መፈለግ፣ ሊቃውንቱን እርስ በእርስ ማስተዋወቅና ቤተክርስቲያን ያለችበትን ችግር ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ እና ብፁዓን አበው በተገኙበት ለምልአተ ጉባኤው ጥያቄ የሚቀርብ እና ምላሽ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ ግቡን ማድረጉ ተገልጧል፡፡

ከመላው የሀገሪቱ ክፍል ከተቻለም ከውጭው ዓለም ያሉ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የሚሰባሰቡ ሲሆን በጊዜው በኒቂያ እንደተደረገው በዚህ ጉባኤም 318 ሊቃውንት የሚታደሙ እንደሆነ በመግለጫው ተገልጧል፡፡

በብፁዕ  አቡነ እንድርያስ ሰብሳስቢነት የሚመራው የሊቃውንት ጉባኤ ከ 15 በላይ አባላት ያለው መሆኑ በመግለጫው ላይ ለማስታወስ ተሞክሯል፡፡

@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
በቤተክርስቲያን የአገልግሎት ሰዓት አገልጋዮች የእጅ ስልካቸውን ይዘው እንዳይገቡ መከልከሉን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስታወቀ !

የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]

ሀገረ ስብከቱ የዐቢይ ጾምን አስመልክቶ አገልግሎቱ እንዴት መከናወን እንዳለበት ከሁሉም ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ጸሐፍትና ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም ቄሰ ገበዞች ጋር ባደረገው ውይይትና ስምምነት መነሻነት የተለያዩ መመሪያዎች መተላለፋቸው ተገልጿል።

ከመመሪያዎች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚከናወኑ የጸሎተ ቅዳሴና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ወቅት የእጅ ሞባይል ስልክ ይዞ መግባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ለሁሉም ገዳማትና አድባራት በተላከው የመመሪያ ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ቅዳሴ የሁሉም ጸሎታት ማጠናቀቂያ ፣ ቀራንዮ ላይ የምንገኝበት ፣ የበጉ ሰርግ ላይ የምንታደምበት፣ የጌታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በአንድነት ለኃጢአት ሥርየት፣ ለነፍስ ሕይወት ፣ ለሃይማኖት ጽንዐትና ለመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ይሆነን ዘንድ የምንቀበልበት ታላቅ የጸሎት ሰዓት ነው።

በመሆኑም አላስፈላጊ የእጅ ስልክ አጠቃቀም ጎልጎታን ከሚያስረሱ በረከትን ከሚያሳጡና ጸጋን ከሚያስወስዱ ድርጊቶች መካከል አንዱ በመሆኑ እንደተከለከለም ተገልጿል።

ይህንን መመሪያም ለየገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰበካ ጉባኤያት ጥብቅ ክትትል በማድረግ እንዲያስፈጽሙ መታዘዛቸውን በተጻፈ ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

@EotcLibilery
EOTC ቤተ መጻሕፍት pinned ««ዝክረ ኒቅያ» ሀገር አቀፍ የሊቃውንት ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው! የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ /አዲስ አበባ) <<የሊቃውንት ብዛት ለዓለም መድኃኒት ነው>> በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ታሪካዊና በዓይነቱ ልዩ የሆነ <<ዝክረ ኒቂያ>> የተሰኘ ሀገር አቀፍ የሊቃውንት የምክክር ጉባኤ ከሚያዚያ 20 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለማካሔድ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ…»
🔴 ዐቢይ ጾም || የጾም መግቢያ || ...
Enqo silassie
ዐቢይ ጾም || የጾም መግቢያ
             
Size:-42MB
Length:-45:22

    በርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ከማቴዎስ ወንጌል ጀምሮ እስከ ራእየ ዮሐንስ መጨረሻ፣ ትርጓሜ ፍትሐ ነገሥትን በእጃቸው የጻፉት ሊቀ ጳጳስ

<<የተሾምነው ምእመናንን ልንጠብቅ ነው እንጂ ልንበትን አይደለም፤ በቤተክርስቲያን ላይ ማንም ሊያዝዝ አይችልም ስለቤተክርስቲያን ኃላፊነቱ የእኛ ነው>> በሚለው ጽኑዕ አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡ ትምህርትን አብዝተው የሚወድዱ እና ሰዎችም እንዲማሩ በብርቱ የሚደግፉ፤ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ቅኔ፣ የዜማ፣ የአቋቋም፣ የብሉይ ኪዳንና ዐራቱን ብሔረ ኦሪት፣ የዳዊት ትርጓሜን ፣ ሐዲሳትን፣ ቅዳሴ ማርያምና ውዳሴ ማርያም፣ ኪዳን፣  ትምህርተ ኅቡዓት፣ ፍትሐ ነገሥት፣ በሀገር ውስጥ ከተማሯቸው ጥቂቱ ነው፡፡
ከትግራይ እስከ አርሲ ሀገረ ስብከት ጠባቂነት በጵጵስና ደረጃ ቤተክርስቲያንን ያገለገሉበት ከፍተኛ እርከን ቢሆንም በመምህርነትም ብዙ ዓመታትን ቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግለዋል፤ በተለይ በብሥራተ ወንጌል የሬዲዮ አገልግሎታቸውን በእጅጉ ይወድዱታል ይኮሩበታልም፡፡ ከሊቃውንት ወገን የሚመደቡት፣ በአስተዳደር ዘመናቸውም ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ አስማምተው፣ አዋድደውና አፋቅረው መርተዋል፤ የቀድሞ አባ መዐዛ ቅዱሳን የኋላው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ካረፉ ዛሬ የካቲት 21/2017 ዓ.ም ዘጠኝ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡

ትውልዳቸው በምሥራቅ ትግራይ ክለተ አውላሎ አውራጃ አውዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጥቢያ ከአባታቸው አቶ ገብረ ሕይወት ፀዓዱ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወለተ ክርስቶስ ቢሻው ግንቦት 12 ቀን 1923 ዓ.ም ነው፡፡ ወላጆቻቸው ልጆችን እየወለዱ በተደጋጋሚ ይሞቱባቸው ስለነበር በጭንቀት ውስጥ ሳሉ ነው ብፁዕነታቸው የተወለዱት፡፡

አባታቸው ገና በጨቅላነታቸው በመሞታቸው በእናታቸው ዘንድ በስስት እየታዩ ነው ያደጉት፡፡ ከዚህም የተነሣ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ያጡት እናትም የሁሉም ምትክ የሆኑት ልጃቸውን ካሣዬ ብለው ስም አወጡላቸው፡፡ ትንሹ ካሣዬም የእናታቸውን ፍቅር ሳይጠግቡ፤ እናትም በስስት የሚመለከቱትን የልጃቸውን ስም ጠርተው በዐይናቸው አይተው ሳይጠግቡ በለጋነት ዕድሜያቸው እናታቸውን በሞት ተነጠቁ፡፡ እናታቸው በልጅነታቸው በማረፋቸው ምክንያትም ከእኅታቸው ጋራ መኖር ጀመሩ፡፡ የእኅታቸው ፍላጎት ከብት እንዲጠብቁ፣ ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ሲደርስም በሕግ በትዳር ተወስነው እንዲኖሩና እያረሱ በግብርና ኑሮአቸውን እንዲገፉ ነበር፡፡

የካሣዬ ሐሳብ ደግሞ ከአድማስ ባሻገር ነበር፡፡ ይኸውም በአካባቢያቸው ባሉት አብያተ ክርስቲያናት እንደሚመለከቱት ሁሉ ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር፣ ቤተክርስቲያንን ማገልገል፣ ጉባኤ አስፍቶ  ወንበር ዘርግቶ ማስተማር ነበር ::

ብፁዕነታቸው አባቴ <<በጣም መንፈሳዊ ሰው ነበሩ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ አባታችን እያሉ ይጠሩኛል ስለእኔ ግን ትንቢት ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ትልቅ አባት ይሆናል ብለው ይናገሩ እንደነበረ ነግረውኛል፡፡ በወቅቱ እኔ ልጅ ስለነበርኩ ይናገሩት የነበረውን አላስታውሰውም>> በማለት ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ፍላጎታቸውን ለመወጣት ወደ አለቃ መብራቴ ዘንድ በመሔድ በአቡነ አሳይ ቤተክርስቲያን ንባብና የቃል ትምህርት ጀመሩ፡፡ የኔታ ሰሎሞን የሚባሉ የአቋቋም መምህራቸው ያላቸውን የትምህርት ፍላጎት በመረዳት፤ ነገ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅሙ ሆነው ስለታዩአቸው ወደ ሌላ ሔደው እንዳይሰናከሉ በማሰብ ከእርሳቸው ዘንድ እንዲማሩ ስለሚፈልጉ ርቀው ወደ ቆሎ ትምህርት ቤት እንዳይሔዱ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ሦስት ዋስ አስጠርተዋቸው በዚያው እንዲቆዩ አደረጓቸው፡፡

በልጅነታቸው አባትና እናታቸውን ያጡት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ግን ልባቸው ለትምህርት አድልቷልና ቤተክርስቲያንን እናት፣ እግዚአብሔርን አባት አድርገው ከተወለዱበትና ከአደጉበት ወላጆቻቸውንም ካጡበት ቀዬአቸው ትምህርትን ፍለጋ ለመኮብለል ወሰኑ፡፡ ስለዚህም ተጨማሪ ትምህርት ለመቅሰም ከመምህራንና ከቤተሰቦቻቸው ተደብቀው በጥንቱ ቆሎ ተማሪ ልማድ ስማቸውን ቀይረው ጎጃም (በጌምድር) ትምህርት ፍለጋ ተሰደዱ፡፡ በቆሎ ትምህርት ቤትም መዓዛ ቅዱሳን ተብለው ተጠሩ፡፡

ወደ ጎንደር እና ጎጃም ተሻግረው ከየኔታ ኃይሉ ስሜ በየላ ኢየሱስ፣ ከየኔታ መኰንን ላስታ አመራ ማርያም ከእነዚህ ከሁለቱም ጾመ ድጓና ምዕራፍ ከተማሩ በኋላ እንደገና ወደ ቅኔ ቤት ገቡ፡፡ ክህነት የተቀበሉትም ሁለት ጊዜ ምዕራፍና ጾመ ድጓ ዘልቀው ቅኔ እስከ ዘእይዜ ከቆጠሩ በኋላ ነበር፡፡ በደቡብ ጎንደር እና ወሎ ተዘዋውረውም በጉባኤ ቤቶች የዜማ፣ የአቋቋም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ ደረስጌ ማርያም አቅንተውም ከየኔታ መንበሩ ዘንድ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ የቅኔ ዕውቀታቸውን ለማስፋፋትም ከአዲስ አበባ ስማዳ ወረዳ ደብረ ዕንቁ በማምራት ከታላቁ ሊቅ ከየኔታ ጌጡ ዘንድ ተምረዋል፡፡ የብሉይ ኪዳንና ዐራቱን ብሔረ ኦሪትና ዳዊት ትርጓሜን ተምረዋል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመማር አዲስ አበባ በሚገኘው ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ገብተው ሐዲሳትን በመጀመሪያ ከመጋቤ ሐዲስ ወ/ሚካኤል፣ ከመ/ር ገብረ ማርያም ዓለሙ፣ ቅዳሴ ማርያምና ውዳሴ ማርያም ከመምህር ይኄይስ፣ ኪዳን ትምህርተ ኅቡዓት ከመምህር ከየኔታ ገብረ ማርያም፣ ከመምህርገብረ ሕይወት ፍትሐ ነገሥት ተምረዋል፡፡

ለራሳቸው እየተማሩ ከቤታቸው ያሉትን ተማሪዎች እያስተማሩ ቆይተዋል፡፡ የመጻሕፍት ተማሪ ሆነው መጻሕፍተ ሐዲሳትን እየተማሩ ሌሊት ከማቴዎስ ወንጌል ጀምሮ እስከ ራእየ ዮሐንስ መጨረሻ ድረስ እንዲሁም ትርጓሜ ፍትሐ ነገሥትን በእጃቸው ጽፈዋል፡፡ መዝሙረ ዳዊት ትርጓሜን በቀዳማይ ኃይለ ሥላሴ ፊት እንዲተረጉሙ ተፈቅዶላቸው በሚገባ በመወጣታቸው ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
ዓላማቸው በተመረቁበት በሐዲሱ ተማሪ አብዝተው ጉባኤ አስፍተው ማስተማር ነበር፡፡ ነገር ግን በቅድስት ሥላሴ መምህራን ማሠልጠኛ እድል አግኝተው ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

ቅኔ ቤት ገብተው ከየኔታ መንበሩ ደረስጌ ስሜን ጃና አሞራ ገብተው ሲማሩ አንድ ዘመዳቸው “ምሰሶ ታቃፊ ሆነህ እንዳትቀር ዲቁና ተቀበል" ያላቸው ትዝ እያላቸው ዲቁና የተቀበሉት ካደጉና ከተማሩ በኋላ ነው፡፡ ይኸውም ከጎንደር ሸዋ (አዲስ አበባ) ድረስ በእግራቸው ተጉዘው በመምጣት በሚያዝያ ወር በ1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ከአቡነ ይስሐቅ ዲቁና ተቀብለዋል፡፡
አቡነ ባስልዮስ በጸመ ፍልሰታ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይዘዋቸው በመሔድም ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም እየተረጎሙ እዚያው ከርመው ሦስቱን ታላላቅ መዓርጋት ቅስና፣ ምንኲስና ቁምስና በ1953 ዓ.ም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተቀብለዋል፡፡

ጵጵስና ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ለኤጲስ ቆጶስነት ከተመረጡት 13 አባቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ የትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ በትግራይ ሀገረ ስብከትም እስከ 1975 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡

ዘመናዊ ትምህርት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወደፊት ጵጵስና የሚሾሙ ሰዎች ውጭ ሀገር ሔደው የውጭውን ትምህርትና ልምድ እንዲቀስሙ ያስፈልጋል በማለት ለአቡነ ባስልዮስ አሳሰቧቸው፡፡ ሊቃውንት ሲመረጡም በንጉሡ አማካይነት ተጠቁመው ውጪ ሀገር ከሚሔዱት መካከል አንዱ ሆኑ፡፡
አባ መዓዛ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ትምህርት በቂ ችሎታ አላቸው ከሚባሉ መምህራን አንዱ ናቸው፡፡ እኒህ የቤተክርስቲያን ሊቅ ዕውቀታቸውን በበለጠ በዓለም ዐቀፍ ቋንቋ ለማሻሻል ባላቸው ፍላጎት መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም አንግሊካን ቤተክርስቲያን ሴንት ጆርጅ ኮሌጅ ተላኩ፡፡ ወደፊት ጵጵስና የሚሾም ብለው ጃንሆይ በተናገሩት መሠረት የኤጲስ ቆጶስነት ትምህርት እንዲሠለጥኑ ነበር የተላኩት፡፡ ሁለት ዓመት ተኩል የቤተክርስቲያን አስተዳደር (Church History and Administration) ተምረው ተመለሱ፡፡ ከውጭ ሀገር እንደተመለሱ ከ1951-1960 ዓ.ም በተማሩት ትምህርት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካህናት አስተዳደሪ ሆነው ቤተክርስቲያንን በማገልገል ምእመናንን በማስተማር ሐዋርያዊ ግዴታቸውን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

በዚሁ መካከል በ1958 ዓ.ም የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው እንኳን በበጎ ፈቃደኝነት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም እየተመላለሱ ያስተምሩ ነበር፡፡ በኋላም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ወደ እንግሊዝ ሀገር ኦክስፎርድ ኦስሄትሮፕ የሚባል የካቶሊክ ኮሌጅ በ1961 ዓ.ም ተልከው በእንግሊዝ ሀገር ለአራት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው (Bachelor of Divinity in Basic Philosophy Super mental and Developmental Psychology) ዲግሪ ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ከሀገርና ከቤተክርስቲያን የተቀበሉትን ታላቅ አደራ አክብረው ሀገራቸውን ለማገልገል በውጭ ሀገር የቀሰሙትን ሥልጣኔና ልምድ ለሀገራቸው የሚያውሉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው ሊቃውንት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በምዕራቡ ዓለም በትምህርት ቆይታቸው በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን ዕውቀት በተግባር ላይ ለማዋል የቻሉ ምሁር ናቸው፡፡ በዚህም መነሻ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ የሰበታ ቤተ ደናግል የበላይ ኀላፊና የቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡ በባሕል ሚኒስቴርም በቋንቋ ጥናት አካዳሚ ውስጥ መርሐ ልሳን ተብሎ በሚታወቀው ክፍል በመምህርነት ሠርተዋል፡፡

በተፈሪ መኰንን ት/ቤት ውስጥ ከውጭ ሀገር በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኢየሱሳውያን ያስተምሩ ስለነበር ብዙ ጊዜ የሃይማኖት ግጭት ይፈጠር ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ተማሪዎች በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው ጠንካሮች ስለነበሩ በሚያቀርቡት ጥያቄ በተማሪዎቹና በመምህራን መካካልም በየጊዜው ግጭት ይፈጠራል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴም ጉዳዩን ሲያጣሩ የግብረ ገብነት መምህር እንደሌላቸው በተማሪዎቹ ስለተነገራቸው በአባ ሐና አቅራቢነት በዚያን ጊዜ ስማቸው አባ መዐዛ ቅዱሳን ወደ ጃንሆይ ቀርበው በግብረ ገብ መምህርነት እንዲቀጠሩ ስለፈቀዱ ለተፈሪ መኮንን ት/ቤት የግብረ ገብ መምህር ሆነው ተቀጥረው ከ1949 ዓ.ም እስከ 1954ዓ.ም ድረስ በግብረ ገብነት አስተማሪነታቸው አገልግለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በተፈሪ መኮንን ት/ቤት እያስተማሩ የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም በተጓዳኝ በትምህርት ቤቱ ግብረ ገብ የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች ሰፋ ያለ የሃይማኖት ትምህርት የሚቀስሙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሉ በምስካዬ ኅዙናን መድኃ ኔዓለም ገዳም ወጣቶችን ስለሃይማኖት ማስተማር ጀመሩ፡፡ የዚህ አገልግሎት ፍጻሜም አንጋፋውን የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት ለመመሥረት አብቅቶታል፡፡ ብፁዕነታቸውም የዚህ ሰንበት ት/ቤት ከመሥራቾቹ አባላት አንዱ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በወቅቱ ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ቋሚ ሰባኬ ወንጌል በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን በሬዲዮ ትምህርት በምታስተምርበት ወቅት፤ አባ መዐዛ ቅዱሳን (በኋላ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል) በርቱዕ አንደበታቸው በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ “ማኅበራዊ ኑሮ በቤተክርስቲያን'' እና “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” በተሰኙ አርእስተ ትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው በሕይወት ዘመናቸው ካከናወኗቸው ተግባራት ለምእመናን በሬዲዮ ስብከተ ወንጌልን በማስተላለፍ የሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ይናገሩ ነበር፡፡

በአርሲ ሀገረ ስብከት ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለ33 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአርሲ ሀገረ ስብከት ቆይታቸውም በምእመናን የሚወደዱና የሚከበሩ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡ ወደ አርሲ ሀገረ ስብከት በመጡበት የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ያሉትን ዐበይት ችግሮች ካጠኑ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ አንድም የወጣቶች እንቅስቃሴ የሚደረግበት አጥቢያ አለመኖሩንና ሰንበት ት/ቤቶችም የተዘጉና ወጣቶችም በቤተክርስቲያን አካባቢ እንዳይታዩና ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግባቸው እንደነበረ ካወቁ በኋላ <<የተሾምነው ምእመናንን ልንጠብቅ ነው እንጂ ልንበትን አይደለም፤ በቤተክርስቲያን ላይ ማንም ሊያዝዝ አይችልም ስለቤተክርስቲያን ኃላፊነቱ የእኛ ነው>> በማለት አቋማቸውን በአደባባይ ከመግለጻቸውም በላይ በዘመኑ በሥልጣን ላይ ከነበሩት የደርግ ሹማምንት ፊት ለፊት በመጋፈጥ ልጆቻቸውን ከጥቃት ታድገዋል፤ ተቋርጦ የነበረው የሰንበት ትምህርት ቤት እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው የነገይቱ ቤተክርስቲያን ተረካቢ ወጣቶች መሆናቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ስለሆነ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ አድርገዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ወደ አርሲ ሀገረ ስብከት ተመድበው ሲመጡ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር 117 (አንድ መቶ አሥራ ሰባት) ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሳቸው በሕይወት በነበሩባቸው ዘመናት ከ300 (ሦስት መቶ) በላይ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በማስከተል ምእመናን በርቀት ምክንያት ሳይንገላቱ በአቅራቢያቸው ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከማድረጋቸውም በላይ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ 
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት ምክንያት ከነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተመርጠው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሆነው እስከተሾሙበት የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት ቅድስት ቤተክርስቲያን በመምራት አባታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ቀን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ዐርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም በደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ተፈጽሟል፡፡

የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን፡፡
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
የየካቲት 23 ስርዓተ መሕሌት
ክፍል ፪

ውድ የ አሐቲ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቻችን ፣ እንደምን አላችሁ! ዛሬ ደግሞ እያንዳንዳችንን ክርስቲያኖች የሚመለከቱ ሥርዓቶችን እንመለከታለን። ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ማደሪያ እንደመሆኗ ሥርዓት እንዳላት ሁሉ፣ እያንዳንዱ ክርስቲያንም የእግዚአብሔር ማደሪያ እንደመሆኑ ሥርዓት አለው።

1. ለክርስቲያኖች የተሠሩ ሥርዓቶች

ቅዱስ ቃሉ ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሁም ምእመን ሥርዓትን አስቀምጧል። ከእነዚህም መካከል፦

•  ለጳጳሳት፡- ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ መሆን፣ ማየትና መስማት የተሳናቸው ወይም ጋኔን ያደረባቸው አለመሆን፣ ምሥጢራተ መጻሕፍትን ማወቅ፣ በምእመናን መመረጥ፣ ነውር የሌለባቸው፣ ትዕግስተኞችና የማይሰክሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል። (ፍት.ነገ 1.5)
•  ለካህናት፡- 30 ዓመት ሳይሞላቸው ክህነትን አለመቀበል፣ አንድ ሚስት ብቻ ማግባት፣ አብዝቶ አለመጠጣትና አለመሰከር፣ የኃላፊነታቸውን ጥቅም አለመሻትና ለመማታት አለመፍጠን ተጠቃሽ ናቸው። (ፍት.ነገ 1.6 እና 1ኛ ጢሞ 3:1)
•  ለዲያቆናት፡- ጭምትነትን ገንዘብ ማድረግ፣ ነውርና ነቀፋ የሌለባቸው መሆን፣ እውነተኛ መሆን፣ ታዛዥነታቸው የተመሰከረላቸው መሆን፣ የማያዳሉና የማይሰክሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
•  ለምእመናን፡- መጠመቅ፣ ሥጋ ወደሙ መቀበል፣ ንስሐ መግባት፣ መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት፣ ዐሥራት በኩራት ማውጣትና ልጆችን በሥርዓት ማሳደግ ተጠቃሽ ናቸው። (ፍት.ነገ 1.11)

2. ለምእመናን አንድነት የተሠራ ሥርዓት

ቤተክርስቲያን ምእመናን በኅብረት እንዲኖሩ ሥርዓቶችን ትሠራለች። ለምሳሌ፡-

•  ካህናት ሲቀድሱ ምእመናን በኅብረት ጸሎት ያደርሳሉ።
•  በጋራ ሆነው ይጸልያሉ።
•  በዓላትን በአንድነት ያከብራሉ።
•  በሰንበት ጽዋ ማኅበር በአንድነት ይጠጣሉ።
•  የቅዱሳንን መታሰቢያ በጋራ ያደርጋሉ።

3. የምእመናን መብትና ግዴታ

•  ግዴታዎች፡- መብዓ፣ አሥራት በኩራትና የሰበካ ጉባኤ መዋጮን በወቅቱ መክፈል እንዲሁም መጻሕፍትንና አልባሳትን መለገስ ተጠቃሽ ናቸው።
•  መብቶች፡- ትምህርተ ወንጌልን ማግኘት፣ ልጅ ሲወለድ ክርስትና ማስነሳት፣ ጸሎተ ሜሮን መቀባት፣ ቁርባን መውሰድ፣ በኃጢአት ሲወድቁ ከካህን ንስሐ መግባት፣ ሲታመሙ ጸሎተ ቀንዲል መቀባት፣ ጋብቻ ሲፈጽሙ ሥርዓተ ተክሊል ማድረግና ሲሞቱ ጸሎተ ፍትሐት ማግኘት ይገኙበታል።

እነዚህን ሥርዓቶች ጠብቀን በክርስትና ሕይወታችን እንድንጸና እግዚአብሔር ይርዳን!

ይህን መልዕክት ለሌሎችም በማጋራት ያወቅንውን እንድናሳውቅና ና በረከትን እንድናገኝ እንጋብዛችኋለን እንዲሁም ማንኛውም አይነት ጥያቄ ካላችሁ ግሩፑ ላይ አሳውቁን እንመልሳለን
መቋሚያ
ብዙውን ከእንጨት የሚዘጋጅ እንደ በትር ዘለግ ያለ ከወደ ጫፉ መስቀል ቅርጽ ያለው ነው፤ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የ "ፐ" ቅርጽ ያለው አሊያም ድቡልቡል የሆነ ነው፤ ከወደ ጫፉ የሚደረገው ነገር የብር ፣የነሐስ ፣የወርቅ፣ የብረት፣ የቀንድ ና የእንጨት ሊሆን ይችላል

አገልግሎቱም
መደገፊያ ፣ መሞርኮዧ ና መዘመሚያ ሲሆን ይህም ከከበሮ እና ጸናጽል ጋር እንዲሁም ብቻውን ከማህሌት ላይ በዝማሜና በሽብሸባ ያገለግላል

ምስጢሩ
መቋሚያ የአዳም ተስፋና ከእመቤታችን ተወልዶ በዕጸ መስቀል ላይ የተሰቀለው የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው።

👉 አንድም መቋሚያ ያዕቆብ ትምህርተ መስቀል ያለበት በትር በፊቱ እያቆመ ይሰግድና ይጸልይ የነበረበት ምሳሌ ነው

👉ካህናት መቋሚያን በትከሻቸው አድርገው  ወዲህ ወዲያ ማለታቸው አይሁድ በዕለተ አርብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ መመውሰዳቸው

ዝማሜ ሚመሰለው በህማማተ ክርስቶስ ነው። መቋሚያው በመስቀል ይመሰላል።ካህናቱ መቋሚያቸው ከዜማ ጋር አስማምተው በዝማሜ ወቅት መቋሚያውን ወደ ግራ ወደ ቀኝ ማድረጋቸው አይሁድ ኢየሱስን አንዴ ወደግራ አንዴ ወደቀኝ ከነመስቀሉ ማንገላታታቸውን ለማስታወስ ነው። ከዛ ወደታች መሬቱን መምታታቸው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ግርፋቱ ሲበዛበት መሬት ላይ መውደቁን ያሳያል።

ጽናጽል
ከብር ከነሐስ-ከሌላም ብረት የሚሰራ፤ እንዲሿሿ ከብረት ቅጠል የሚደረግበት ሲሆን አገልግሎቱም ለእግዚአብሔር ክብር ይዘመርበታል። ጽናጽል ከከበሮ ጋር አብር የሚሄድ የዜማ መሳሪያ ነው

የብረት ቅጠሎቹ ሲያንሱ 5 ሲበዙ 7 ይሆናሉ። 5 ሲሆን አምስቱ አዕማደ ሚስጢር 7 ሲሆን በሰባቱ ሰማያት ይመሰላል።

👉2 የብረት ዘንጎች(የብረት ቅጠሎቹን የሚይዙት) ላይ ከታችኛው ላይ 2 የብረት ቅጠሎች የሚኖሩ ሲሆን ይህም ጌታችን ልደቶች  ማለትም ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ፤ ድህረ ዓለም ደግሞ ያለ አባት ከእመቤታችን መወለዱ ምሳሌ ነው

👉 የብረት ቅጠሎቹ 3 መሆን የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው

👉ድምጹ ያማረና መልካም መሆኑ በመላእክት ዜማ ይመሰላል (ሰብሕዎ በጽናጽል ዘሠናይ ቃሉ እንዲል መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር 150)
👉ጽናጽል ወዲህ ወዲያ ማለቱ ጌታችን የመንገላታቱ ምሳሌ ነው

ከበሮ
ከእንጨት ተዘጋጅቶ በጠፍርና በቆዳ የሚለጎም የዜማ መሳሪያ ነው።

ለክብረ በዓል ለበዓል ለበዓለ ንግሥ ዕለት ለእግዚአብሔር ክብር የሚመታ የሚመዘመርበት ነው

በከበሮ ወበመዝሙር ይዜምሩ ሎቱ እንዲል መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር 149

ምስጢሩ-
አፉ ሁለት ነው፤ ጠባብ እና ሰፊ
   ሰፊው- ቁመት ደረት ምሉዕ በኩለሄ/እግዚአብሔር በሁሉ ሙሉ መሆኑን ሲሆን

ጠባቡ- ደግሞ ወልድ በአጭር ቁመት መወሰኑን የሚያመለክት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው

እንጨቱ ከቆዳ የተለጎመበት ጠፍር- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ጊዜ የገረፉበት የግርፋቱ (የገላው ሰንበር) ምሳሌ ነው

ከበሮ የሚለብሰው ሱቲ ጌታችን የለበሰው ቀይ ግምጃ ምሳሌ ነው

የከበሮ አመታት ምስጢር
መጀመሪያ ከበሮ ተቀምጦ ቀስ እየተባለ ነው የሚመታው።

👉በመሬት መመታቱ ጌታችን አይሁድ በመሬት እየጎተቱ መምታታቸውን
👉በግራ እና በቀኝ ሲመታ ከቀኝ ሲመታ ወደ ግራ ከግራ ሲመታ ወደ ቀኝ ማዘንበሉን ለማስታወስ ነው
👉ከበሮ በትከሻ ተደርጎ ሲመታ ከወደቀበት እንደመቱት ፤በፍጥነት ሲመታ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰቀል ሲቃረብ በፍጥነት መምታታቸውን ያስታውሰናል

የማሕሌት ተወዛዋዦች

ዛሬ ለወጉ ማሕሌት አንቀርም ፣ ቸብቸቦ ይጀመራል ፣ ወጣቶች ከበሮውን ለማንሳት ሪከርድ በሚያሻሽል ፍጥነት የከበሮውን ገመድ ከጀርባቸው ያዋሕዱታል (እንዲያው ወጣቶች ስንል በእድሜ ማለታችን አይደለም ቆብ የደፉ መስቀል የጨበጡ ቀጣይ በምናየው መልኩ የሚሳተፉትንም የሚገልጽ ቃል ነው እንጅ ) : አፍታም ሳይቆይ እንደ አሎሎ ወርዋሪ መሽከርከር ይጀመራል : አንድ እጅ ተዘርግቶ እስክስታው ይቀልጣል: ሁለት እግር ከፍ እያለ መዝለል ይጀመራል : አሁን በአንደበት የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ነው መሬት ላይ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ ጭፈራ ሁኗል : ነፍስ ምን እየተካሄደ እንዳለ ዘንግታለች : ስጋ ግን እየተንቀጠቀጠ ነው : የስሜት እሳት ተቀጣጥሏል : እሽሽሽሽሽሽ የሚል ማጀቢያ መሆኑ ነው ከአንደበት አትጠፋም : የሙቀቱ መጠን ከቁጥጥር እየወጣ ነው : ወደ ሴቶች ጉዞ ይጀመራል : አሁን ሴቶች በቅርበት እየተመለከቱ ነው ከበሮው ላይ ብትሩ ይበረታል : የዝላዩ ከፍታ ይጨምራል : ጿጿጿጿጿ የሚል የጽናጽል ድምጽ የሚያሰማ ቢኖርም ፈገግ ተብሎ ታልፎ ጭፈራው ይደራል : ሊቃውንቱ ቢናገሩም የተጠሉ ይሆናሉ : ነፍስ ከተኛች ቆይታለች ከዱካካዋ ልትነቃ አልቻለችም : ከጎን ከበሮ የሚመታው ጓደኛ በመቺው ትዕዛዝ አመታቱን እየቀረጸ ነው : Tik Tok ቀጣዩ የቪዲኦው መሰራጫ መድረክ ነው : የታይታ ክርስትና ! እንደ ፈሪሳውያን ሰው እንዲያይ ብሎ መዘመር ! ተቃራኒ ጾታ እያዩ መስፈንጠር ! በከበሮ ትዳር አይፈለግም ! መዝለል ፣ መሽከርከር ፣ መስፈንጠር፣ መንቀጥቀጥ ፣ እሽሽሽሽሽ ማለት ፣ ወደ ተቃራኒ ጾታ አንጋጦ መዞር ይቁሙ !

ሁለት እጅ ስላለህ እና መምታት ስለቻልክ ብቻ ከበሮ አትሸከም ምስጢሩን ተረዳ ያኔ ሲገባህ ዕንባህ ከዐይንህ ያለማቋረጥ ጉንጮችህን መወረጃ አድርጎ ሲጎርፍ ይታወቅሀል : ያኔ ልብህ እንጅ እግርህ አይዘልም : ያኔ የምትንቀጠቀጠው እግዚአብሔርን በመፍራት ይሆናል: ያኔ ስትዘል አፍአዊ ላብ ሳይሆን ሕሊናህ ይሆናል በተመስጦ የሚያልበው : ያኔ እንደ መላእክት የሰማይ የመቅደሱ በር እስኪከፈት እንዲዘምሩ አንተም የልቦናህ በር ተከፍቶ ለምስጋና ትታትራለህ ። አየኋት : አወቅኳት : ወደድኳት ብሎ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የመላዕክትን ዝማሬ ሰምቶ መጦ ባቀናት ቤተክርስቲያን ምድራዊ ተወዛዋዦች ገብተናልና ወደ ልቦናችን እንመለስ ።

በወንዶች ብቻ የሚቆም ግብር አይደለም በአንስቶችም ተመሳሳይ ፍሬ አፍርቶ ተንዠርቅቆ እናገኘዋለን : በሰንበት ትምህርት ቤት እንዲሁ በአደባባይ በዓላት ቁጥራቸው ትቂት ያልሆኑ በከበሮ ላይ መከራ አጽንተው በመከራ ድር ተተብትበው ይኖራሉ : አንቲ ተቃራኒ ጾታሽ እንዲያይሽ ካልሆነ ምን ያሽከረክርሻል ? ምን ያዘልልሻል ? ወደ እነማን ፊትሽን ዙረሽስ ትመቻለሽ ? ወደፊት ወደ ኋላ ስትይ የክርስቶስን መገፋት ታስቢያለሽ ወይስ ወደፊት ሄደሽ ልብሽ የወደደውን ትፈቅጃለሽ ? ከንቱ ውዳሴን ሽተሽ በሰፈሩ የከበሮ አመታትሽ እንዲወራ ከሆነ እኅቴ ሆይ የገሀነም ደጃፍ ላይ ነሽና ሳትገቢ ተመለሽ! በአደባባይ ምድርን የሚያበራ እሳት ከማቀጣጠል በሕሊና መቅረዝ ትቂት መንፈሳዊ ማኅቶት ማብራት ይሻላል ! በእውነት እናስተውል ! እነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እኮ በዝማሬያቸው ሕሙም ይፈውሱ ነበር በእኛስ? ዘመርን ብለን እራሳችን ሕሙም ሆነን እንመለሳለን ! ወደ እነእንተና ለይቶልን በኅብረ ብሔራዊ ጭፈራ እግዚአብሔር ቢመለክ ምን ችግር አለው ብለን የኅብረት ዘፋኞች ከመሆናችን በፊት ለብው ! አምላከ ያሬድ ወዳዊት ወእዝራ የቀናውን መንፈስ ያድለን ! የቅዱሳኑ ዝማሬ ወላዲተ ቃል ድንግል ማርያም በረድኤት አትለየን
@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
@mezigebehayimanot
"መምሬ ካሳሁን እንግዳ በአድዋ ጦርነት ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት ይዘው በባዶ እግራቸው የዘመቱ አባታችን"

አድዋ የካቲት ፳፫ ቀን ፲፰፻፹፰ ዓ.ም በአድዋ ተራራ ላይ ጥቁር ሕዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የማይቻል የሚመስለውን የቻሉበት፣ አይሆንም የተባለው የሆነበት፣ “ነጮች” “በጥቁሮች” የተሸነፉበት፣ ታላቅ ሁነት የተፈጸመበት፣ የድል በዓል መታሰቢያ ነው።

የአድዋን ድል ልዩ ያደረገው አንድ ሕዝብ በጦር ሜዳ ተዋግቶ ያሸነፈበት ታሪክ ስለ ሆነ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ዓለምን የተቆጣጠረውን “ጥቁር ሕዝብ ተፈጥሮውም፣ ኑሮውም ነጭን ለማሸነፍ አያስችለውም” የሚልና እንኳን ገዥዎችን ተገዥዎችንም ጭምር አሳምኖ የነበረ አስተሳሰብን የሻረ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ለንጽጽር የማይገቡና ያልተመጣጠነ አሰላለፍ የነበራቸው ሕዝቦችና መንግሥታት ተዋግተው እንደ ጎልያድ በሰይፍ የመጣው ሳይሆን እንደ ዳዊት በእምነት ጠጠር የወነጨፈው ያሸነፈበት የማይታመን እውነታ በመሆኑም ነው፡፡

በአድዋ እንዴት ልናሸንፍ ቻልን?

የቤተ ክርስቲያናችን አስተዋጽኦ የሚገለጠው “እንዴት አሸነፍን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንመረምር ነው፡፡ ይህ ዓለምን በብርቱ ጠፍንጎ የያዘና አንዱን ባሪያ ሌላውን ጌታ የሚያደርግ፣ ሰውን ያህል ፍጡር እንደ ከብት ነድቶ፣ እንደ ዕቃ ጎልቶ፣ ለገበያ አቅርቦ የሚሸጥ እኩይ አስተሳሰብ ከመሠረቱ የናደ፣ ነጻነት ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ለሌሎች ያሳየ፣ የአስተሳሰቡ ሰለባ የነበሩ ነጮችንም ያስደነገጠ ድል ኢትዮጵያውያን እንዴት ሊቀዳጁ ቻሉ? ዓቅሙና ብርታቱስ ከየት ተገኘ? ምዕራባውያን ያላቸው የሠለጠነ ወታደር፣ የጦር መሣሪያ ልዩነት እና ዓለምን የተቆጣጠረው “የነጮች” የበላይነት አስተሳሰብ እያለ የመግጠምስ ሞራሉና እምነቱ ከወዴት መጣ? ኢትዮጵያውያንን ከዚህ የአስተሳሰብና የሞራል ከፍታ ያደረሳቸው ገፊ ምክንያትስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ስንጠይቅ መልሱ ቤተ ክርስቲያናችን ዘንድ ያደርሰናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብላ ያስተማረችው ትምህርት፣ በነገሥታቱ እና በሕዝቡ ላይ ያሳደረችው በጎ ተፅዕኖ፣ “የእኔም ጦርነት ነው፤ በህልውናዬ ላይ የመጣ ነው” ብላ በማሰብ ደወል ደውላ፣ ዐዋጅ ነግራ ታቦት ይዛ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆኗ ለኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብ ከፍታ የነበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔር የሚያምኑ፣ የካህናትን ትእዛዝ የሚቀበሉ፣ እግዚአብሔርን መፍራትንና ንጉሥ ማክበርን የሚያውቁ፣ መመካት ቢገባቸውም ምሕረትን፣ ፍርድንና ጽድቅንም በምድር ላይ በሚያደርገው በእግዚአብሔር እንጂ በጉልበት፣ በሠራዊት ብዛት፣ በመሣሪያ ጥራት እንዳልሆነ ሲሰበኩ የኖሩ፣ ይህን እውነትም በልባቸው የጻፉ ስለ ነበሩ ነው፡፡ (ኤር.፱፥፳፬)

የአድዋ አርበኞች “እኛኮ ዘመናዊ ትጥቅ የለንም፤ እኛኮ “ጥቁሮች” ነን፤ “ነጭን” ማሸነፍ አንችልም፤ እኛኮ እንበርበት አውሮፕላን፣ እንሽከረከርበት አውቶሞቢል የለንም፤ እንዴት እናሸንፋለን? እንዴትስ ይቻለናል?” የሚል ጥያቄ በፍጹም አልጠየቁም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኀ ሠራዊቱ ወያርብኅኒ በብዝኀ ኃይሉ….፤ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤ ኀያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም›› የሚል ትምህርትን ያስተማረችው፣ የእምነት ስንቅም ያስቋጠረችው ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡ (መዝ.፴፪፥፲፮) ብዙዎች የሚዘነጉት ጉዳይ ጦርነትን የሚያሸንፈው የሠራዊት ብዛት፣ የመሣሪያ ጥራት ብቻ ስለሚመስላቸው ነው፡፡

ይህ የአስተሳሰብ ችግር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ፣ አሁንም ድረስ ያልተቀረፈ አስተሳሰብ ነው፡፡ ብዙ ሰው መግደል ማለት ጦርነትን ማሸነፍ ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ሠራዊት ያላቸው፣ ብዙ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሁሉ ብዙ ሰው ይገድሉ ይሆናል እንጂ ጦርነትን ያሸንፋሉ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ አሸናፊነት፣ እውነተኛ ድል የሚገኘው እግዚአብሔርን ከሚያምን ንጉሥ፣ እግዚአብሔርን ከሚያምኑ ሠራዊት ወይም ከእውነተኛ ተዋጊዎች ነውና፡፡

ድል የሚነሡት ‹‹ድል መንሣት ዕውቀትም ካንተ ይገኛል፤ ጌትነትም ያንተ ገንዘብ ነው፤ እኔም ያንተ ባሪያ ነኝ›› የሚሉ ነገሥታትና ሠራዊት ናቸውና፡፡ (ዕዝ.ካልእ ፬፥፶፱)

ጣሊያን መካናይዝድ ጦር አሰልፎ፣ የሠለጠነ ሠራዊት አሰማርቶ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን ትጥቆች ታጥቆ በባዶ እግራቸው በሚሄዱት፣ ሰይፍና ጎራዴ በታጠቁት ሊሸነፍ የቻለው ኢትዮጵያውያኑ ‹‹ድል መንሣት በእግዚአብሔር ኃይል ነው›› ብለው በመግጠማቸው ነው፡፡(፩ኛ መቃ.፳፩፥፫) ቁም ነገሩ ስለ ጣሊያን ሽንፈት ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያውያኑ አሸናፊነትና የሥነ ልቡና የበላይነት ምክንያቱን ማንሣት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን በእምነት፣ በሥነ ልቡና፣ በአብሮነት፣ የገነባችው ሰብእና አድዋ ላይ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ባለ ርእይ የነበሩ ሊቃውንቶቿ በጸሎት ተግተው፣ ራእይ አይተው፣ በቅኔያቸውና በስብከታቸው የጦርነቱን አይቀሬነት እየገለጹ፣ ዝግጅት እንዲደረግ እያሳሰቡና የሥነ ልቡና ግንባታ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ታሪክ መሥራታቸው ቤተ ክርስቲያን በአማኞቿ ላይ በሠራችው ሥራ በገነባቸው የሥነ ልቡና የበላይነትና የአሸናፊነት መንፈስ ነው፡፡

የሮም ካቶሊክ መሣሪያ ባርካ ለወረራ ልካለች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሠራዊቱን በጸሎት ባርካ ራስን፣ ሀገርን፣ ሃይማኖትን ለመከላከል ልካለች፤ ካቶሊክ በመሣሪያ ተማምናለች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በጸሎት ተማምናለች፤ እነርሱ በታንክ ሊያሸንፉ መጡ፤ እኛ በታቦት ልናሸንፍ ታቦት ተሸክመን ወጣን፤ እኛም አሸነፍን፤ እነርሱም ተሸነፉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር መታመንን አስተማረች፤ ካቶሊክ በሠራዊትና በመሣሪያ ታምኖ ለወረራ የሚሄድን ባርካ ሸኘች፡፡ እናም ምዕራባውያኑ እስከ ክፉ መሻታቸው ተሸነፉ፡፡ አሸናፊነት ከእግዚአብሔር ነውና፡፡ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ‹‹አንተ ከሠራዊታቸው ጋር በከሃሊነትህ አጠፋሃቸው፤ ቤተ መቅደስህን ያጎሳቁሉ ዘንድ የስምህ ጌትነት ማደሪያ የሆነች ደብተራ ኦሪትንም ያሳድፉ ዘንድ መክረዋልና በብረትም የመሠዊያህን ቀንዶች አፍርሰዋልና›› ይላል፡፡ (ዮዲት ፱፥፰)

ሌላኛው የአድዋ ድል ምክንያት ደግሞ ካህናቱ ዘምተዋል፤ ሊቃውንቱ ዘምተዋል፤ ታቦቱ ዘምቷል፤ በየድንኳኑ ሰዓታት እየቆሙ ቅዳሴ እየቀደሱ፣ የሚያቆርቡ ነበሩ፤ የሞቱ እየተፈቱ በጸሎትና በምሕላ፣ በሞራልና በስንቅ ንጉሡንና ሠራዊቱን እየተራዱ ብዙ ሥራ የሠሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ የጦርነቱን ፍትሐዊነት፣ ለሃይማኖት፣ ለርስት፣ ለሚስት፣ ለልጅ ተብሎ የሚከፈል መሥዋዕትነት መሆኑን እና አሸነፊነት ደግሞ ከእግዚአብሔር መሆኑን፣ ቤተ ክርስቲያን አስተምራለች፤ አበረታታለች፤ ብዙዎቹም ሊቃውንትና ካህናት ከአርበኞች ጋር በግንባር ተሠውተዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፤ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ ይህም ለተዋጊዎች ኃይልና ብርታት ሰጥቷቸዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል፤ ታሪክ አለ፡፡ ‹‹ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጎድጓድ አንጎደጎደ፤ አስደነገጣቸውም፤ በእስራኤል ፊት ድል ተመቱ›› ይላል የሚገርም ነው፡፡ (፩ኛ ሳሙ.
፯፥፲) አድዋ ላይ የሆነውም ይህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትም በጦር ግምባር በድንኳን በቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርጉ፣ ንጉሡም ቅዳሴውን ሲያስቀድሱ፣ የልዳው ኮከብ የፋርሱ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣሊያኖቹ ላይ አንጎደጎደባቸው፤ አስደነገጣቸውም፡፡ በእነዚያ ልበ ሙሉዎች ጎራዴ ይዘው በመድፍ ፊት በሚቆሙ ደፋሮች ኢትዮጵያውያን ድል ተመቱ፡፡

የአድዋ ድል ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የመንፈሳዊ ሥነ ልቡና ብርታትና ለሀገርና ለሃይማኖት እስከ ሞት የመጋደል ወኔ የተገኘ መሆኑ ከድሉ እኩል መነገር ያለበት ነው። ኢትዮጵያውያን የኢጣሊያን ወረራ በሀገረ እግዚአብሔር ላይ እንደ ተደረገ ሰይጣናዊ ጥቃት ነበር የቈጠሩት።

እነሆ ዛሬ እኛ የድል አድራጊዎች ልጆች ተባልን፤ “ነጭም” “በጥቁር” ተሸነፈ፤ የነጻነትን ጣዕም ጥቁሮች ቀመሱ፤ የነጭ ፍልስፍና ተሻረ፤ ሰውን ያህል ፍጡር ባሪያ የሚያደርገው፣ አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ የሚያስብለው የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብም ታሪኩ በጥቁር መዝገብ ተጻፈ፤ ይህም ከሆነ እነሆ ፻፳፰ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ አባቶቻችን ድል አድርገው ታሪክ ሠሩ፤ እኛ ደግሞ ድል ማድረግ፣ ታሪክ መሥራት ቀርቶ ታሪክን መሸከም ከብዶን ለመውደቅ እንፍገመገማለን፡፡

አድዋ አንድነት ነው፤ አድዋ እኩልነት ነው፤ አድዋ ነጻነት ነው፡፡ አድዋ የድሉ ባለቤቶችን መዘከር ነው፡፡ እነዚህን ዘንግቶ፣ የድሉ ፊታውራራዎችን በማንኳሰስ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ሚና በመዘንጋት የሚከበር የአድዋ በዓል ትርጉም አልባና ታሪክን የማጥፋት ሴራ ነው፡፡

ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።

ጽሑፉን ለማሰናዳት የማኅበረ ቅዱሳንን ድረገጽ እንዲሁም ሐመር መጽሔትን ተጠቅመናል።
@EotcLibilery
፯፥፲) አድዋ ላይ የሆነውም ይህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትም በጦር ግምባር በድንኳን በቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርጉ፣ ንጉሡም ቅዳሴውን ሲያስቀድሱ፣ የልዳው ኮከብ የፋርሱ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣሊያኖቹ ላይ አንጎደጎደባቸው፤ አስደነገጣቸውም፡፡ በእነዚያ ልበ ሙሉዎች ጎራዴ ይዘው በመድፍ ፊት በሚቆሙ ደፋሮች ኢትዮጵያውያን ድል ተመቱ፡፡

የአድዋ ድል ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የመንፈሳዊ ሥነ ልቡና ብርታትና ለሀገርና ለሃይማኖት እስከ ሞት የመጋደል ወኔ የተገኘ መሆኑ ከድሉ እኩል መነገር ያለበት ነው። ኢትዮጵያውያን የኢጣሊያን ወረራ በሀገረ እግዚአብሔር ላይ እንደ ተደረገ ሰይጣናዊ ጥቃት ነበር የቈጠሩት።

እነሆ ዛሬ እኛ የድል አድራጊዎች ልጆች ተባልን፤ “ነጭም” “በጥቁር” ተሸነፈ፤ የነጻነትን ጣዕም ጥቁሮች ቀመሱ፤ የነጭ ፍልስፍና ተሻረ፤ ሰውን ያህል ፍጡር ባሪያ የሚያደርገው፣ አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ የሚያስብለው የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብም ታሪኩ በጥቁር መዝገብ ተጻፈ፤ ይህም ከሆነ እነሆ ፻፳፰ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ አባቶቻችን ድል አድርገው ታሪክ ሠሩ፤ እኛ ደግሞ ድል ማድረግ፣ ታሪክ መሥራት ቀርቶ ታሪክን መሸከም ከብዶን ለመውደቅ እንፍገመገማለን፡፡

አድዋ አንድነት ነው፤ አድዋ እኩልነት ነው፤ አድዋ ነጻነት ነው፡፡ አድዋ የድሉ ባለቤቶችን መዘከር ነው፡፡ እነዚህን ዘንግቶ፣ የድሉ ፊታውራራዎችን በማንኳሰስ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ሚና በመዘንጋት የሚከበር የአድዋ በዓል ትርጉም አልባና ታሪክን የማጥፋት ሴራ ነው፡፡

ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።

ጽሑፉን ለማሰናዳት የማኅበረ ቅዱሳንን ድረገጽ እንዲሁም ሐመር መጽሔትን ተጠቅመናል።
2025/03/13 14:55:41
Back to Top
HTML Embed Code: