tgoop.com/Hulaadiss/38732
Last Update:
በኢትዮጵያ ውስጥ 10 እጅግ የናጠጡ ሀብታሞች እነማን ናቸው ?
ቢሊየነርስ አፍሪካ እንደገለፀው ግብፅ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያላቸው ባለሀብቶችን ማፍራት የቻሉ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ያላት ቢሊየነር አንድ ብቻ ነው፡፡
እሳቸውም ሼክ መሀመድ አልአሙዲ ናቸው፡፡ ይሁንና እሳቸውን በመከተል ትልቅ የቢዝነስ ኤምፓየር የገነቡ፣ ለበርካቶች ስራ የፈጠሩ፣ ኢንዱስትሪዎችን የሚመሩና በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉ በርካታ ሚሊየነሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ዛሬ ለንባብ በበቃው በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልአሙዲ በቁጥር አንድነት የተቀመጡ ሲሆን የሀብታቸው መጠን 9.56 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሁለተኝነት የተቀመጡት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ናቸው፡፡ የሳንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሳሙኤል በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርተው ከአምስት ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ህንፃዎችን መገንባታቸውንና በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትር መንገዶችን መስራታቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ጨምሮም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ አገር በቀል ድርጅቶች ቀዳሚው ሰንሻይን መሆኑን ገልፆ የድርጅታቸው አመታዊ ገቢ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር እንደሚበልጥ አስረድቷል፡፡
በቢሊየነርስ አፍሪካ በዚህ ዝርዝር በሶስተኛነት የተቀመጡት አቶ በላይነህ ክንዴ ናቸው፡፡ ከአንድ ሺህ ዶላር በሚያንስ ካፒታል ቅቤና ማር በመሸጥ ስራ የጀመሩት አቶ በላይነህ በአሁኑ ወቅት በላይነህ ክንዴ ግሩፕ የተሰኘ ግዙፍ ተቋም ለመመስረት መቻላቸውን ያስረዳው ዘገባው ድርጅታቸው ባለፉት አስራ ሰባት አመታት ወደስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሷል፡፡
በአራተኛ ደረጃ የተቀመጡት ደግሞ አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ ናቸው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ከሀይል አቅርቦት እስከ ሸቀጣ ሸቀጥና ሪል ስቴት ዘርፍ ባሉ ስራዎች ላይ መሰማራታቸውን የጠቀሰው ዘገባው ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ የተሰኘ ድርጅት እንዳላቸውም አስረድቷል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳጅ የሆነው የማእድን ውሀ ማለት አምቦ ውሀ ባለቤት መሆናቸውን ያስረዳው መፅሄቱ በተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የቦርድ አባል መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡
መፅሄቱ በአምስተኛ ደረጃ ያስቀመጣቸው አቶ እዮብ ማሞ ናቸው፡፡ አቶ እዮብ በዋሽንግተን ዲሲና ኒውዮርክ ከተሞች ውስጥ በርካታ የነዳጅ ማደያዎች እንዳላቸውና በቨርጂኒያ የሪል ስቴት ዘርፍ ላይ መሰማራታቸውንም አስታውቋል፡፡ በቀጣይነት የተቀመጡት አቶ ከተማ ከበደ፣ አቶ አለማየሁ ከተማ፣ አቶ ብዙአየሁ ቢዘኑ፣ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴና አቶ ግርማ ዋቄ ናቸው፡፡
ምንጭ : ዘሃበሻ
BY Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)

Share with your friend now:
tgoop.com/Hulaadiss/38732