Telegram Web
ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው ሦስቱ ወረዳዎች ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ሰብዓዊ ርዳታ እየቀረበላቸው ነው- የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

በስምጥ ሸለቆ ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው ሦስቱ ወረዳዎች ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ሰብዓዊ ርዳታ እየቀረበላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መረጃ እንዳመለከተው በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሳቢያ በተከሰተ ርዕደ መሬት የስጋት ተጋላጮችን ለመታደግ በአፋርና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ ተግባራት እየከናወኑ ነው።

በአፋር ክልል የስጋት ወረዳዎች በሆኑት አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች ከሚገኙ 18 ቀበሌዎች ሰባቱ በርዕደ - መሬት ስጋት ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ገልጿል።

በሁለቱ ወረዳዎች አስር ሺህ ቤተሰቦች እንደሚኖሩ ያሳወቅ ኮሚሽኑ ይህም በአማካይ 60 ሺህ 36 ዜጎች ለችግሩ ተጋላጭ እንደሆኑ ግምቱን አሳውቋል።

እስከአሁን ከሁለቱ ወረዳዎች የስጋት አካባቢዎችን ለማስለቀቅ በተሰራው ስራ በነፍስ ወከፍ ቁጥር 53 ሺህ 718 ሰዎች ወይም አካባቢውን መልቀቅ ከሚገባው ምጣኔ 90 በመቶ እንደሆኑ ጠቁሟል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የርዕደ-መሬቱ ስጋት በሚስተዋልበት የምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ የቅድሚያ ቅድሚያ በተሰጣቸው ቀበሌያትን 20 ሺህ 302 ዜጎች አካባቢያቸውን በመልቀቅ ሁሉም በጊዜያዊ መጠለያ እንዲጠለሉ መደረጉን ገልጿል።

ተጨማሪም የስጋት አካባቢ እየሆኑ በመምጣታቸው የተለዩ ሁለት ቀበሌያት ውስጥ የሚገኙ 7 ሺህ 200 ዜጎች ለማስለቀቅ ከማኀበረሰቡ ጋር እየተሰራ ይገኛል ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች እስከዛሬ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 80 ሺህ በላይ ዜጐች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ስለመጠለላቸው አሳውቋል።

ኮሚሽኑ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑና ከመኖሪያ ቀዬያቸው ለተነሱ ህብረተሰብ ክፍሎች ክልሎች እና ማኀበረሰቡ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ለጉዳት ተጋላጭ ወገኖች የሚውል 282 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሷል።

ከኮሚሽኑ በተጨማሪ በፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ በክልሉ መንግስት፣ አጋር አካላት፣ ማህበረሰቡና ልዩ ልዩ ማህበራት አማካኝነት ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ርዳታ ድጋፎች እየቀረቡ መሆኑን አረጋግጧል።

በተመሳሳይ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ 1 ሺህ 542 ህፃናትን በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ነው የገለጸው።

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ከርዕደ-መሬት በፊት፣ በርዕደ-መሬት ወቅትና፣ ከዕርደ-መሬት በኋላ መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የተላለፉ መልዕክቶችን በውል በመገንዘብና በማኀበረሰብ ደረጃ በመወያየት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

በማኀበረሰብ፣ በቤተሰብና በግለሰብ ደረጃ ከስጋት አካባቢ ሳያቅማሙ መልቀቅ፣ አካባቢውን ከየትኛውም ሰውና እንስሳት ንክኪ መከለል፤ በሳይንሳዊ ምክረ-ሐሳብ በተለዩ ቦታዎች ብቻ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች መቆየት እንደሚገባም እንዲሁ።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት በቀይ መስቀል አማካኝነት ተቋቋመ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰላም፣ የግጭት-አልባ እና ሰብዓዊነት መርህዎች ላይ አተኩሮ ትምርት የሚሰጥ የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት አቋቁሟል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ለተመረጡ ሰልጣኞች ትምህርት ለመስጠት የተዘጋጀው ትምህርት ቤቱ የሥነ-ምግባር እና ሰብዓዊነት ላይ ያተኮሩ ኮርሶች ተቀርጸውለታል ተብሏል።

ትምህርት ቤቱ ለጊዜው በልዩ ዲፕሎም ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን ቢያጠናቅቅም በሂደት ግን በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪም ትምህርት ለመስጠት ውጥን ስለመያዙም ተነግሯል፡፡

“ለስልጠናው ትኩረት ያደረግናቸው በመጀመሪያ ለራሳቸው ሰልጥነው ከዚህ ስወጡ ደግሞ ማህበረሰቡን ለማሰልጠን የተዘጋጁትን ወጣቶች ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት አበራ ቶላ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ሳሪስ አከባቢ በሚገኘው የማኅበሩ ማሰልጠኛ ማዕከል ትምህርቱን ለመስጠት መምህራንን ከማዘጋጀት ጀምሮ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁም የተነገረለት ሲሆን አሁን ላይ በመጀመሪያ ዙር ስልጠናው ትምህርት ቤቱ 50 ተማሪዎችን እንደሚቀበል ታውቋል፡፡

ከ1970ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስድስት ሚሊየን አባላት እና 100 ሺህ በጎ ፈቃደኞች አሉት፡፡ 

ዘገባው የዶቼቬሌ ነው።
በአማራ ክልል ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 112 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ተባለ

የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በመውደማቸው በርካቶች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸው ይታወቃል።

በመሆኑም የክልሉ ትምህርት ቢሮ  ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት 112 ቢሊየን ብር  እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡

በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት እና በሰሜኑ ጦርነት በርካታ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን የቢሮው ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር ዘመነ አበጀ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አገልግሎት ለመመለስ 112 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ቢሮው አስጠናሁት ባለው ጥናት መሠረት ይህ ገንዘብ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባትና ከመጠገን በተጨማሪም ተጓዳኝ የትምህርት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ነው ብሏል።

መረጃው የአማራ ኮምኒኬሽን ቢሮ ነው።
ይርጋለም ኮንስትራክሽን በ4.8 ቢሊዮን ብር የፊደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃን ሊገነባ ነው
〰️〰️〰️
የፊደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ4.8 ቢሊዮን ብር ህንፃ ለማስገንባት ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራሟል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ በ4.8 ቢሊዮን ብር የህንፃ ግንባታ ስምምነት በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ባለቤትነት በይርጋዓለም ኮንስትራክሽን የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የህንጻው ግንባታ እስከ መስከረም 2019 ዓም ድረስ የሚጠናቀቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ግዙፍና በሀገር ውስጥ ኮንትራክተር የሚተገበር መሆኑን ገልፀው፤ በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገት ማሳያና ማስቀጠያ ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ የህንፃ ግንባታው የፍትህ አገልግሎትን በአንድ ማዕከል በመስጠት የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

እንዲሁም ለዳኞች እና ድጋፍ ሰጪ የፍትህ ዘርፍ ሰራተኞች አመቺ የስራ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስች መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማካተት የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት ይረዳል ብለዋል። (EPA)
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል የ550 ሚሊዮን ዶላር ብድር በፓርላማ ጸደቀ
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል 550 ሚሊዮን ዶላርን ያካተተ የብድር ስምምነት፤ ዛሬ ሰኞ ጥር 19፤ 2017 በፓርላማ ጸደቀ። የካፒታል ማሳደጊያው፤ ባንኩን “የተሻለ ተወዳዳሪ” እና በቀጠናው መስራት የሚችል “ጠንካራ ባንክ እንዲሆን የሚያስችለው” ነው ተብሏል።

ለመንግስታዊው ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውለው ገንዘብ፤ ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ለኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው 700 ሚሊየን ዶላር ብድር አካል ነው።

በዓለም ባንክ ስር የሚገኘው ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ብድሩን የሰጠው፤ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከር በማሰብ ነው።

ይህንኑ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አጭር መግለጫ ያቀረቡት በፓርላማ ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ፤ በብድሩ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሶስት የመንግስት የገንዘብ ተቋማት እንደሆኑ አስታውቀዋል።

ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ብድሩን ለካፒታል ማሳደጊያነት ከማዋል በተጨማሪ “መሰረታዊ የመዋቅር ማሻሻያ ለማድረግ” “እና “የዘርፉን የስጋት አስተዳደር ከአለም አቀፍ የባንኪንግ ደረጃዎች ጋር በማጣጣም ለማጎልበት” እንዲጠቀምበት የቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአጠቃላይ የብድሩ ማዕቀፉ ውስጥ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሻሻያ፣ ማዋቀር እና መልሶ ማቋቋም የተያዘው የገንዘብ መጠን 560 ሚሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ 550 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ፤ ለባንኩ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል መሆኑን ለፓርላማ በቀረበው የማብራሪያ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ገንዘብ በፓርላማ እንዲጸድቅ ሲቀርብ፤ በአምስት ወራት ውስጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Photo
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ናኦሚ ግርማ በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመርያ የሚሊየን ዶላር ተጫዋች ሆና ቼልሲን ተቀላቅላለች፡፡

የ24 አመቷ ወጣት ካሳንዲያጎ ዌቭ በ 900 ሺህ ፓውንድ (1.1 ሚሊዮን ዶላር) የአራት አመት ተኩል ኮንትራት ለሰማያዊዎቹ ፈርማለች፡፡

ከዚህ ቀደም በሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዝውውር ክብረ ወሰኑን ይዛ የነበረችው ዛምቢያዊቷ አጥቂ ራቼል ኩንዳናንጂ ነበረች፡፡
ተጫዋቿ ባሳለፍነው አመት በ788 ሺህ ዶላር ከማድሪድ ወደ ቤይ እግር ኳስ ቡድን ስትቀላቀል የክብረ ወሰኑ ባለቤት ሆና ነበር፡፡

ናኦሚ ግርማን ጨምሮ ቼልሲ ተጫዋቾችን በማስፈረም ሪከርዱን ሲሰብር ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ፔርኒል ሃርደርን በ2020 በ355 ሺህ ዶላር እና በ2024 ሜይራ ራሚሬዝን በ542 ዶላር አስፈርሟል።
ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን 44 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈችው ናኦሚ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የወርቅ ሜዳሊያን ማሳካት ችላለች፡፡

በተጨማሪም በ2023 በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ በተካሄደው የሴቶች አለም ዋንጫ በነበራት ሚና የአሜሪካ የአመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሆና ተመርጣለች፡፡
ለሳንዲያጎ ዌቭ ክለብ በሶስት የውድድር ዘመኖች 72 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፋ መጫወት የቻለች ሲሆን በ2023 በፊፋ የምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሽልማት ውስጥ ዕጩ በመሆን ቀርባ ነበር፡፡

ወጣቷ ተጫዋች ከፊርማው በኋላ ባደረገችው ንግግር ቼልሲ የአሸናፊነት አስተሳሰብ ያለው ቡድን ነው። ከዚህ ባለፈም ለመማር እና ለማደግ ምቹ ከባቢ ያለው በመሆኑ ቡድኑን በመቀላቀሌ ደስተኛ ነኝ ብላለች፡፡
ከቼልሲ ጋር 12 አመታትን ያሳለፈችው እና ሰባት የሱፐር ሊግ ዋንጫዎችን ያነሳቸው የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኤማ ሄይስ በእድሜ ዘመኔ ካየኋቸው ምርጥ ተከላካዮች መካከል ናኦሚ አንዷ ናት ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

ቼልሲ በአሁኑ ወቅት በሴቶች ሱፐር ሊግ ከማንችስተር ዩናይትድ በ7 ነጥብ ርቆ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ (Alain)
በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ የእርዳታ አቅራቢ ድርጅት በሆነዉ ዩኤስኤይድ የሚደረጉ የእርዳታ ስራዎች እንዲቋረጡ መድረጉ ጫናዉ በሌሎች አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ላይ ሆኗል!

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅት የሆነው "ዩኤስኤይድ" የሚያደርገዉን የስራ እንቅስቃሴ በድንገት እንዲያቆም መደረጉ ከፍተኛ ክፍት መፍጠሩ የተገለፀ ሲሆን ይህም በሌሎች አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ላይ እንዲወድቅ ማድረጉን ካፒታል ከምንጮቿ መረዳት ችላለች።እነዚሁ ድርጅቶች እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ሰብአዊ ርዳታ እና የአካባቢ ጥበቃ ያሉ የተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ቢሆንም በኢትዮጵያ ዩኤስኤይድ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን እንዲጨርሱ ወይም እንዲሸፍኑ እየተደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሳምንት በፊት ባስተላለፉት ልዩ ትዕዛዝ ለዘጠና ቀናት ( ለ 3 ወር ) ያህል ማናቸውም የውጭ እርዳታዎች እንዳይሰጡ መከልከላቸውንና በእነዚህ ቀናት በአለም ላይ ያሉት የእርዳታ ስራዎች በሙሉ ግምገማ እንደሚከናወንባቸው አስረድቷል፡፡ይህን ዉሳኔዉ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን በድርጅቱ ቀድሞ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በሌሎች መሰል የእርዳታ ድርጀቶች ላይ ኃላፊነቱ ወድቋል።

እንደ አለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ ጨምሮ ዩኤንኤችአር ፣ ዩኤንኤፍፒኤ እንዲሁም ፋኦ የመሳሰሉ በርካታ አለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘርፎች እየደገፉ እንደሚገኙ ይታወቃል።

Via Capital
በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሁለት ዞኖች ታፍነው ከተወሰዱ 13 ህፃናት መካከል አንዳቸውም አለመመለሳቸው ተገለፀ

በአኙዋ ብሔረሰብ ዞን እየተወሰዱ ከነበሩ ህፃናት ውስጥ የአንደኛው ህፃን ህይወት ማለፋ ተሰምቷል።በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሁለት ዞኖች በ2016 በጀት አመት 13 ህፃናት ታፍነው መወሰዳቸውን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል።

የፍትህ ቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፍ አቶ ጎርዶን ኮንግ ሬት ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በክልሉ በ2016 ዓ/ም በደቡብ ሱዳን  ሙርሌ ብሔረሰብ ታፍነው በርካታሕፃናት ለባርነት ተወስደዋል።ከኑዌር ብሔረሰብ ዞን አምስት ህፃናት ታፍነው እንደተወሰዱ የተናገሩት ምክትል ቢሮ ሀላፊው  2ቱ ወንድ ሲሆኑ  3ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል ከአኙዋ ብሔረሰብ ዞን አምስት ወንድ እና ሶስት ሴት ህፃናት በድምሩ ስምንት ህፃናት ታፍነው ተወስደዋል ሲሉ አቶ ጎርዶን ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።አያይዘውም ከስምንቱ ሕፃናት መካከል ታፍነው እየተወሰዱ እያሉ የአንድ ሕፃን ህይወት ማለፋን ተናግረዋል ።   

ከሁለቱ ዞኖች  ታፍነው ከተወሰዱት ህፃናት ውስጥ አንዳቸውንም ከደቡብ ሱዳን ማስመለስ እንዳልተቻለ  ተገልጻል።በዚህ መልኩ ታፍነው የተወሰዱ ህፃናትን ለማስመለስ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ ባለመቻሉ ህፃናቱን ማስመለስ አልተቻለም ተብሏል።እንዲህ ባለ ሁኔታ የጠፋትን ህፃናት ለማስመለስ የክልሉ መንግስት ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን በጋራ መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል።ቢሮው በቀጣይ ለጉዳዮ መፍትሄ ለማምጣት የአካባቢው ማህበረሰቦች ልጆቻቸውን ከመሰል ድርጊቶች መታደግ እንዲችሉ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ታስቧል ነው ያለው።
በአዲስ አበባ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ሥራ በአፋጣኝ እንደሚጀመር ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ከአመራር እስከ ሰራተኛ ድረስ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ሥራ በአፋጣኝ እንደሚጀመር ገልጿል።

ቢሮው የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ስራ ለማከናወን እና የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ኢስሚስ አተገባበር ላይ ከተቋማት ከተውጣጡ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተሮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅትም በከተማ አስተዳደሩ ከ90 ሺ በላይ የሚሆነው የመንግስት ሰራተኛ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዛ በላይ የትምህርት ማስረጃ ያለው መሆኑን በቢሮው የሰው ሀብት ስራ አመራር ዘርፍ ኃላፊ አቶ መላኩ ታምሩ ገልጸዋል። #tikvahethmagazine
Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Photo
የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያስደነገጠው ዲፕሲክ ማን ነው?

"ዲፕሴክ" የተሰኘው የኤአይ መተግበሪያ የዓለማችን ተፈላጊው መተግበሪያ ሆኗል

ይህ መተግበሪያ እንደ ጎግሉ ጀሚኒ፣ እንደ ኦፕን አይ ኩባንያው ቻትጅፒቲ እና ሌሎችም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያች ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲሰጥ ተብሎ የተዘጋጀ ነው።

የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎችን ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርገው የሰሩ ቢሆንም ይህ የቻይናው ጀማሪ ኩባንያ ግን በትንሽ ወጪ መስራቱ ተገልጻል።

ዲፕሲክ መተግበሪያ በስድስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ መሰራቱ ብቻ ሳይሆን ለተጠቃሚዎች እየሰጠ ያለው አገልግሎት ፈጣን መሆኑ በብዙዎች ተመራጭ መሆን ችሏል ተብሏል።

እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ ዲፕሲክ መተግበሪያ አሁን ላይ በአፕስቶር ላይ ቁጥር አንድ ተፈላጊ ሆኗል።

ይህ መሆኑ እንደ ኦፕን አይ እና ጎግል ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል የተባለ ሲሆን የቴክኖሎጂ ምርቶችን እንዳትጠቀም በአሜሪካ ማዕቀብ ለተጣለባት ቻይና ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

አዲሱ መተግበሪያ አሁን ላይ ከቻትጅፒቲ እና ጀሚኒ በላይ ተፈላጊው መተግበሪያ ሆኗልም ተብሏል።

ዲፕሲክ መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች በውድ ዋጋ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ኩባንያዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ሊያስገድድ እንደሚችልም ተጠቅሷል።

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጸ ሲሆን ከሰሞኑ የ500 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ከኦፕን አይ ኩባንያ ጋር መፈራረሙ ይታወሳል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየዘመነ እንደሚሄድ እና በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ በሰዎች የሚከወኑ መሰረታዊ ስራዎችን ሳይቀር ይሰራል በሚል ቴክኖሎጂ ቁጥጥር እንዲደረግበት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።#አል ዐይን
የፌስቡክና ኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ "ከቲክ ቶክ" ለቀው ለሚመጡ ክሬተሮች አምስት ሺ ዶላር እንደሚሸልም ማስታወቁን ተከትሎ ተፈላጊነቱ መጨመሩ ተገልጸ፡፡ ሜታ ኩባንያ ‹‹ብሬክስሩ ቦነስ ፕሮግራም›› በሚል አዲስ ባወጣው በዚህ ማስታወቂያ ምንም እንኳ ቲክ ቶክን በስም ባይገልፅም ከሌሎች ማህበራዊ ድረገፆች ለቀው ወደራሱ ለሚቀላቀሉ ይህንን ገንዘብ እንደሚሰጥ ይፋ አድርጓል፡፡ አምስት ሺህ ዶላሩን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች በሌላ ሶስተኛ ወገን ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ ያሉ መሆን እንዳለባቸው መግለፁ ግን ቲክ ቶክን ኢላማ ያደረገ እንደሆነ ፎክስ ኒውስ ገልጿል፡፡

በሜታ ብሬክስሩ ቦነስ ፕሮግራም ላይ ለመቀላቀል አንደኛ ተጠቃሚው በአሜሪካ የሚኖር መሆን ያለበት ሲሆን ሁለተኛ እድሜው ከአስራ ስምንት አመት በላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ወደዚህ ፕሮግራም ለመግባት በሚያመለክቱበት ወቅት የሶስተኛ ወገን ማህበራዊ ሚዲያዎትን ማለትም ቲክ ቶክ አካውንትዎን ሊንክ ማሳወቅ ይጠበቅብዎታል፡፡ እንዲሁም የኢንስታግራም ፕሮፌሽናል አካውንት ወይንም የፌስ ቡክ ገፅ ሊኖርዎት የሚገባ ሲሆን ከሌለዎት ደግሞ መክፈት ግዴታ ነው፡፡

እንዲሁም በሌሎች የፌስ ቡክ ሞኒታይዜሽን ወይንም የክፍያ ፕሮግራሞች ውስጥ የሌሉ መሆን ይገባዎታል፡፡ እነዚህን መስፈርቶች አሟልተው ማመልከቻ ከላኩ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሜታ ለፕሮግራሙ ብቁ መሆንና አለመሆንዎትን የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡ ብቁ ከሆኑ መሆንዎት ከተገለፀልዎ በሚለጥፉት መረጃ ተሰልቶ ክፍያው እንደሚፈፀም ሜታ ካሰራጨው መረጃ ተመልክተናል፡፡ ይህ እስከ አምስት ሺ ዶላር የሚደርሰው ክፍያ የሚፈፀመው በሚቀጥሉት ዘጠና ቀናት ውስጥ ነው፡፡ ክፍያውን ለማግኘት በአንድ ወር ውስጥ በፌስ ቡክ ቢያንስ ሀያ ሪልና በኢንስታግራም ደግሞ ሌላ ሀያ ሪል ወይንም አጭር ቪዲዮ መለጠፍ ይጠበቅብዎታል፡፡ እንዲሁም እነዚህን ሪሎች በየአስር ቀኑ ሼር ማድረግም ይገባዎታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቲክ ቶክ በአሜሪካ ውስጥ መታገዱ የሚታወቅ ሲሆን በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ ትእዛዝ ይህ እገዳው ለሰባ አምስት ቀናት የተራዘመለት መሆኑ ይታወቃል፡፡
Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Photo
"1,713 ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያንን ከሃገሬ አሜሪካ ላባርር ነው" - ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

በዶናልድ ትራንፕ አስተዳደር ዉሳኔ ምክንያት ወደ ሀገራቸዉ ከሚመለሱ ሰነድ አልባ ዜጎች መካከል 1,713 ኢትዮጵያዊያን የተለዩ ሲሆን የአሜሪካ አስተዳደር በአሁኑ ዙር ለማባረር ካዘጋጃቸው 1.4 ሚሊዮን ዶክመንት የሌላቸው ስደተኞች ውስጥ 1,713 ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል ተብሎአል።

እስካሁን ብዙ ሕገወጥ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው የላከው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ማን ነው?

ቢል ክሊንተን (1993-2001) በ8 ዓመት ስልጣን ዘመኑ 870 ሺህ አካባቢ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ልኳል (ዲፖርት አድርጓል)።

ጆርጅ ቡሽ (2001-2009) - በ8 ዓመት ስልጣን ዘመኑ 2 ሚሊዮን አካባቢ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ልኳል (ዲፖርት አድርጓል)።

ባራክ ኦባማ (2009-2017) - በ8 ዓመት ስልጣን ዘመኑ 3.2 ሚሊዮን አካባቢ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ልኳል (ዲፖርት አድርጓል)።ይህም "Deporter-in-chief" አሰኝቶታል።

ዶናልድ ትራንፕ (2017-2021) - በ4 ዓመት ስልጣን ዘመኑ 1 ሚሊዮን አካባቢ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ልኳል (ዲፖርት አድርጓል)።

ጆ ባይደን (2021-2024) - በ4 ዓመት ስልጣን ዘመኑ 1.5 ሚሊዮን አካባቢ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ልኳል (ዲፖርት አድርጓል)።
አደገኛ የማጭበርበሪያ መተግበሪያ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወረ መሆኑን ንግድ ባንክ አስታወቀ

ደምበኞች በዋትስ አፕ እና በቴልግራም የሚሠራጭ Pharma+/CBE Vacancy መተግበሪያን እንዳይጭኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሳስቧል።

ባንኩ ባስተላለፈው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፤ ባደረገው ምርመራ መሠረት አደገኛ መተግበሪያ ማግኘቱን ገልጿል።

ይህ Pharma+/CBE Vacancy የተሰኘ አሳሳች መተግበሪያ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው እየተሰራጨ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ይህ መተግበሪያ በቴሌግራም እና ዋትስአፕ ወደ ደንበኞቹ እየደረሰ መሆኑን ጠቁሟል።

መተግበሪያው በስልክ ላይ ከተጫነ ያለ ፈቃድ ገንዘብ ማስተላለፍ እንደሚችልም አሳውቋል።

ባንኩ ከዚህ አይነት የመጭበርበር አደጋ ለመጠበቅ ከቴሌግራም ወይም ከዋትስአፕ መተግበሪያዎችን አታውርዱ ብሏል።

ደንበኞች መሰል ተግባራት ሲገጥሟቸው በ951 ነጻ የስልክ መስመር ደውለው እንዲያሳውቁ አሳስቧል።
ብርጌድ ንሀመዱ ወይንም ሰማያዊው አብዮት ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች  በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባ አካሂደዋል።

በኤግዚቢሽን ማእከል በተከናወነው በዚህ ስብሰባ ላይ የንቅናቄው አመራሮችና ከተለያዩ አገራት የተወከሉ የንቅናቄው አባላት መገኘታቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡ ወደአንድ ሺ ያህል ሰዎች በተሳተፉበት በዚህ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራዊያንም ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ብርጌድ ንሀመዱ በኤርትራ ውስጥ የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ የሚንቀሳቀስ ቡድን ሲሆን በተለያዩ አገራት በኤርትራ መንግስት የሚከናወኑ ፌስቲቫሎች ላይ ተቃውሞ በማሰማት ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ ይህ ቡድን በይፋ እንቅስቃሴ ሲያደርግና ስብሰባ ሲያከናውን የትናንቱ የመጀመሪያው ነው፡፡
የቻይናው ዲፕሲክ የሳይበር ጥቃት ደረሰበት

በተለቀቀ በቀናት ውስጥ በዓለም ላይ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው የቻይናው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አጋዥ መተግበሪያ (DeepSeek) የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት ተዘግቧል::

ዲፕሲክ የአሜሪካውን ቻትጂፒት (ChatGPT) የሚፎካከር እና ተፈላጊነቱም እያደገ መሆኑ በተዘገበ በቀናት ውስጥ ነው ከፍተኛ የተባለ የሳይበር ጥቃት የደረሰበት::

ይህን ተከትሎም ዲፕሲክ በጊዜያዊነት አዳዲስ ተጠቃሚዎችን መቀበል ከማቆሙ በስተቀር ሌሎች ተጠቃሚዎች መጠቀማቸውን እንደማያስተጏጉል አስታውቋል::

በአሜሪካ አፕ ስቶር እና ጎግል ስቶር ላይ በነጻ ከሚገኙ መተግበሪያዎች ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያገኘ ሆኗል::

ይህን ተፈላጊነቱን ተከትሎም ሀገራት መተግበሪያውን መጠቀም አለመጠቀም ላይ የተለያዩ ምክረሃሳቦችን እየሰጡ ነው::

በዚህ ወቅት ዲፕሲክ የደረሰበት የሳይበር ጥቃት ከማን እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም ከተፎካካሪዎቹ ሊሆን እንደሚችል ዘጋርዲያን ዘግቧል::
2025/05/29 08:57:37
Back to Top
HTML Embed Code: