Telegram Web
† እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል †

† ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው::

ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት "ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት" ሲሉ ይገልጹታል:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር "አሮስ" የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት: እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር::

አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል: "እንስሳ ተያዘልን" ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: 2 ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር::

እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ: ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ: ወገባቸው እንደ ሰው: ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስል::

እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና:- አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው::

"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት" አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ 2ቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት::

ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ - የአብ ወዳጅ" ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን : ልጁንና 2ቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ::

አበው ካህናት እሱን "ኖኅ" : ሚስቱን "ታቦት" : ልጁን ደግሞ "መርቆሬዎስ" ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ - የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው::

ከዚያም ደስ እያላቸው: ክርስቶስን እያመለኩ: ነዳያንን እያሰቡ: ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ "ካላመጣሃቸው" አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ::

ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን 2ቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::

በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን "ላግባሽ" ስላላት የ5 ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው::

እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በሁዋላ ግን በሕጻኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ::

በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ: ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጎ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::

በጦርነትም እጅግ ኃያል: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ: የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ::

ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው::

በማግስቱም "ምን ይሻላል?" ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቋቋማቸዋለሁ" ቢል ሳቁበት::

እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ: በሰላም ሒዱ" ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ አልነበረም::

ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ "ድሉ የጣዖቶቼ የነ አድሎን ነው" በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ::

በ3ኛው ቀንም "ለጣዖት ሠዋ" የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው::

"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል:: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ:: (ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ)" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ: የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው::

ያም አልበቃ:: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት:-
"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም::
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም::
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም::" ያሉት::

ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ: በግርፋት: በእሳት: በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር 25 ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::

እርሱ ካረፈ በሁዋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ200 ዓ/ም እንደ ተወለደ: በ220 ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ225 ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::
ሰማዕቱ በዚህች ዕለት : በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል::
የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው!

††† አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን:: ከርስቱም አያናውጠን:: ከበረከቱም ይክፈለን::
ቸሩ እግዚአብሔር እድሜ ለንስሃ ዘመን ለፍሥሃ አይንሳን::
††† ጥር 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ
2.ቅዱሳን ባስልዮስና ጎርጎርዮስ
3.ብፁዕ አባ ጴጥሮስ ጽሙድ (ለምጽዋት ራሱን የሸጠ አባት)
4.ቅዱስ ሰብስትያኖስ ሰማዕት
5.ቅዱስ አስኪላ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
2.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
3.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
4.አቡነ አቢብ
5.አባ አቡፋና

† "የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና(ዕብ 11:35)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
† እንኳን ለቅዱሳን አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

አረጋውያን ሰማዕታት

† ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና::(ማቴ 5:44) ነገር ግን
ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

የእነዚህ ሰማዕታት ቁጥራቸው 49 ሲሆን አባ ቢስዱራ የሚባል ጻድቅ ሰው 50ኛ ሁኖ ይመራቸው ነበር:: መኖሪያቸው ገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) ሆኖ ዘመኑ 5ኛው መቶ ክ/ዘ ነበር::

ሃምሳውም ሙሉ ዘመናቸውን በምናኔና በቅድስና ፈጽመው በስተእርጅና ደግሞ ሰማዕትነት መጣላቸው:: በ430ዎቹ አካባቢ
የዚያን ጊዜ በርበር ይባሉ የነበሩት አረማውያኑ (የዛሬዎቹ አሕዛብ አባቶች) "ሃይማኖት ካዱ" እያሉ ሰይፍን መዘዙባቸው::

በጊዜው አባ ቢስዱራ በማረፉ ሃላፊነቱን የወሰዱት አባ ዮሐንስ ከአርባ ስምንቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ተስማምተው በበርበር እጅ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል:: ከንጉስ ቴዎዶስዮስ (ትንሹ) ተልኮ የነበረ አንድ ክርስቲያንም በፍቅረ ክርስቶስ ተስቦ ከወጣት ልጁ ጋር ተሰይፏል:: የብርሃን አክሊልም ለሃምሳ አንዱም ወርዷል::

† አምላከ ቅዱሳን ከተከፈተ ገነት  ከተነጠፈ ዕረፍት በቸርነቱ ያድርሰን::

† ጥር 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት (ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ ውስጥ)
2.ቅድስት አንስጣስያ (በ5ኛው መቶ ክ/ዘ ከቁስጥንጥንያ ወደ ግብጽ ወርዳ  ንግሥናን ንቃ በበርሃ ስትጋደል የኖረች ቅድስት
እናት ናት::)
3.ቅዱስ ዮሴፍ (መፍቀሬ ነዳያን)
4.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)

† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ኢትዮጵያዊ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::"(ሮሜ፰፥፴፭-፴፰)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2025/02/03 04:14:15
Back to Top
HTML Embed Code: