Telegram Web
††† እንኳን ለቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት እና ቅድስት ታኦድራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት †††

††† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እንዲያውም ለዘመነ ሰማዕታት መሪና አስተማሪ እርሱ ነበር::
እስኪ በጥቂቱ ነገሩን ከሥሩ እንመልከተው::
በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች: ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር:: የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- ፋሲለደስ: ገላውዴዎስ: ፊቅጦር: መቃርስ: አባዲር: ቴዎድሮስ (3ቱም): አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: ሌሎቹም ነበሩ::

ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ:- ማርታ: ሶፍያ: ኢራኢ: ታኡክልያ: ሌሎቹም ነበሩ:: ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ: ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ /ሞተ/::

የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች:: ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር:: ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ::

በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪዻዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር:: ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪዻዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው:: ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው::

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም:: የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው:: ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው:: ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች::

ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ:: የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ:- "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው:: ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ::

ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ: ይጸልዩ ገቡ:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር:: ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው:: ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ::

አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ: አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ-ቤተክርስቲያኖች ይዘጉ: ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ" አለ:: አዽሎን: አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ::

በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ::
*ምድር በደም ታጠበች::
*ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ::
*እኩሉ ተገደለ: እኩሉ ተቃጠለ: እኩሉ ታሠረ: እኩሉም ተሰደደ:: በዚህ ጊዜ 'መራሔ ትሩፋት' ቅዱስ ፋሲለደስ ለሰማዕትነት ይበቁ ዘንድ ስለ ራሱና ስለ ወገኖቹ ጸለየ::
ቅዱስ ሚካኤልም በግርማ ወርዶ ቅዱሱን ወደ ሰማይ አወጣው:: ከቅዱሳን ጋር በገነት አስተዋውቆት: ክብረ ሰማዕታትን አሳይቶት: ከጌታ ዘንድ አስባርኮት: ከሕይወት ውሃ ምንጭም አጥምቆ መለሰው::ቅዱስ ፋሲለደስም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ በንጉሡ ፊት ቆመ::

ንጉሡ ፈራ: እርሱ ግን በፈጣሪው ስም መሞት እንደሚፈልግ ነገረው:: ሊያባብለው ሞከረ: አልተሳካም እንጂ:: ከዚያም አስሮ ወደ አፍራቅያ (አፍሪካ) ላከው:: መጽሩስ የሚባል መኮንንም ቅዱሱን አሰቃየው::

እርሱ የሁሉ የበላይ ሲሆን ስለ ክርስቶስ ሁሉን ተወ:: አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት: በምጣድ ላይ ጠበሱት: አበራዩት: በወፍጮም ፈጩት:: እርሱ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ሁሉን ታገሰ:: ሁለት ጊዜ ገድለውት ከሞት ተነሳ:: በተአምራቱ ምክንያትም ከከተማው ሕዝብ ግማሹ ያህል ከአሕዛባዊነት ተመልሶ ሰማዕት ሆነ::

በመጨረሻም በዚህ ዕለት አንገቱን ሲቆርጡት ደምና ወተት ፈሶታል:: መላእክትም እርሱን ለመቀበል ዐየሩን ሞልተውታል:: ከልዑላኑ ወገንም የቅዱስ ፋሲለደስን ሚስትና ልጆችንጨምሮ አንድም የተረፈ የለም:: ሁሉም በሰማዕትነት አልፈዋል::

††† እናታችን ቅድስት ታኦድራ †††

††† ይህች ቅድስት እናታችን የትእግስት እመቤት ናት:: ትእግስቷ: ደግነቷ ፈጽሞ ይደነቃል:: ታሪኳ ደግሞ በሆነ መንገድ ከቅድስት እንባ መሪና ጋር ይገናኛል::

ቅድስት ታኦድራ ግብጻዊት ስትሆን ተወልዳ ያደገችው በእስክንድርያ ነው:: ከሕጻንነቷ ጀምራ ቅን ነበረች:: ምንም እንኳ የምናኔ ሰው ብትሆንም ወላጆቿ ያመጡላትን ባል 'እሺ' ብላ አገባች:: ለተወሰነ ጊዜም በሥጋ ወደሙ ተወስነው ከባሏ ጋር በሥርዓቱ ኖሩ::

ለቤተ ክርስቲያን ከነበራት ፍቅር የተነሳ ጠዋት ማታ ትገሰግስ ነበር:: አንድ ቀን ግን መንገድ ላይ የሆነ ፈተና ጠበቃት::ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በመልኳ ምክንያት ለኃጢአት ተግባር ይፈልጋት የነበረ አንድ ጐረምሳ ድንገት ያዛት:: ታገለችው: ግን ከአቅሟ በላይ ነበር:: ጮኸች:የሚሰማትም አልነበረም:: ሰውየው የሚፈልገውን ፈጽሞ: ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ይህንን መቻል ለአንዲት ንጽሕት ወጣት ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ መረዳቱ አይከብድም::

እጅግ መጥፎ ሰው: በቀለኛም ለመሆን ከዚህ በላይ ምክንያት አይኖርም:: ቅድስቷ ግን ከወደቀችበት ተነስታ መሪር እንባን አለቀሰች:: ሕመሟን ችላ ወደ ቤቷ ላትመለስ ወደ በርሃ ተጓዘች:: ወደ ገዳም ገብታ በወንድ ስም 'አባ ቴዎድሮስ' ተብላ መነኮሰች:: በአካባቢው የሴቶች ገዳም አልነበረም::

የሚገርመው በገዳም ውስጥ ሆና ያንን ጨካኝ ሰው ይቅር አለችው:: ቀጥላም ስለ እርሱ ኃጢአት ንስሃን ወስዳ ከባዱን ቀኖና ተሸከመችለት:: ይሔ ነው እንግዲህ ሕይወተ ቅዱሳን ማለት: ራስን አሳልፎ ለጠላት መስጠት:: (ዮሐ. 15:13) ፈተናዋ ግን ቀጠለ::

ወንድ መስለዋት 'በአካባቢው ከምትገኝ ሴት ጸንሰሻል' ብለው ከገዳም አባረሯት:: ያልወለደቺውንም ልጅ ታሳድግ ዘንድ ሰጧት:: አሁንም በአኮቴት ተቀብላ ለ7 ዓመታት በደረቅ በርሃ ተሰቃየች:: ልጁንም አሳደገች:: ከዚያም ከባድ ንስሃ ሰጥተው ተቀበሏት:: ቅድስት ታኦድራ እንዲህ ስትጋደል ኑራ በዚህች ቀን ዐርፋለች:: በዕረፍቷም ቀን ክብሯ ተገልጧል::

††† ቸር አምላክ የቅዱሳኑን ትእግስትና መንኖ ጥሪት አይንሳን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

††† መስከረም 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
2.ቅድስት ታኦድራ እናታችን
3.ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ሐዋርያዊ (ሐዋ. 10ን ያንብቡ)
4.ቅድስት በነፍዝዝ ሰማዕት
5."3ቱ" ገበሬዎች ሰማዕታት (ሱርስ: አጤኬዎስና መስተሐድራ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄምና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?መከራ፡ ወይስ ጭንቀት፡ ወይስ ስደት፡ ወይስ ራብ፡ ወይስ ራቁትነት፡ ወይስ ፍርሃት፡ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::
(ሮሜ ፰፥፴፭)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
††† እንኳን ለቅዱሳን አባቶቻችን ሊቃውንት ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ጉባኤ ኤፌሶን †††

††† ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ያከበሩትን: እርሱም ያከበራቸውን ሰዎች 'ቅዱሳን' ትላለች:: ራሱ ባለቤቱ "ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ-እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" ብሏልና:: (ዼጥ. 1:15) እነዚህንም ቅዱሳን 'መላእክት: አበወ ብሊት: ነቢያት: ሐዋርያት: ሰማዕታት: ጻድቃን: ሊቃውንት: ደናግል: መነኮሳት: ባሕታውያን' ወዘተ. ብለን: ክፍለ ዘመን ሰጥተን በአበው ሥርዓት እናስባለን::

ከእነዚህ ቅዱሳን መካከልም አንዱንና ትልቁን ቦታ ቅዱሳን ሊቃውንት ይወስዳሉ:: 'ሊቅ' ማለት 'ምሑር: የተማረ: ያመሰጠረ: ያራቀቀ: የተፈላሰፈ: በእውቀቱ የበለጠ: የበላይ: መሪ: ሹም: ዳኛ' . . . ወዘተ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል::

ወንጌል ላይም ጌታችን መድኃኔ ዓለም ኒቆዲሞስን "አንተ ሊቆሙ ለእሥራኤል-አንተ የእሥራኤል መምሕር (አለቃ) ነህ" ብሎታል:: (ዮሐ. 3:10) ስለዚህም 'ሊቃውንት' ማለት በእውቀት ከሁሉ በላይ የሆኑ እንደ ማለት ነው::

ዘመነ ሊቃውንት ተብሎ የሚታወቀው ከ3ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 6ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን እንደ እንቁ ያበሩ: ብርሃንነታቸው በሰው ፊት የበራ ብዙ አበው ተነስተዋል:: ቅዱሳን ሊቃውንት ከሌሎች ምሑራን ቢያንስ በእነዚህ ነገሮች ይለያሉ:-
1.እንደ ማንኛውም ሰው ከተማሩ በኋላ እውቀቱ ይባረክላቸው ዘንድ ጠዋት ማታ በጾምና በጸሎት ይጋደላሉ::
2.አብዛኞቹ ቅዱሳን ሊቃውንት ገዳማዊ ሕይወትን ጠንቅቀው ያውቃሉ::
3.ምሥጢር ቢሰወርባቸው ሱባኤ ይገባሉ እንጂ በደማዊ ጭንቅላት አይፈላሰፉም::
4.ፍጹም መናንያን በመሆናቸው ሃብተ መንፈስ ቅዱስ እንጂ የሚቀይሩት ልብስ እንኳ የላቸውም::
5.እያንዳንዷን የመጽሐፍ ቃል ከማስተማራቸው በፊት በተግባር ይኖሯታል::
6.እረኞች ናቸውና ዘወትር ለመንጋው ይራራሉ::
7.ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ግፍን ተቀብለዋል::
8.በኃይለ አጋንንት የመጡ መናፍቃንን ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ለብሰው: መጻሕፍትን አልበው: ጥቅስ ጠቅሰው መክተዋል::
9.ምግብናቸውንም ፈጽመው ዛሬ በገነት ሐሴትን ያደርጋሉ::

††† የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምትቀበላቸው የቅዱሳን ጉባኤያት 3 ብቻ ናቸው::
1ኛ.በ325 (318) ዓ/ም በኒቅያ 318ቱ ሊቃውንት ያደረጉትን
2ኛ.በ381 (373) ዓ/ም በቁስጥንጥንያ 150ው ሊቃውንት ያደረጉትን: እንዲሁም
3ኛ.በ431 (424) ዓ/ም በዚህች ቀን 200ው ሊቃውንት ያደረጓቸውን ጉባኤያት ትቀበላለች::
ይሕስ እንደ ምን ነውቢሉ:-
በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን 2 አካል: ባሕርይ ነው (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት)

ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ::

ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በኋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር(ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::

የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ (የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን የአምላክ እናት: ዘላለማዊት ድንግል: ፍጽምት: ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::

እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሂዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::

††† አምላከ ሊቃውንት ዛሬም ያሉንን አባቶች ይጠብቅልን: ያንቃልን:: ከቅዱሳን ሊቃውንት በረከትም አይለየን:: የእመ ብርሃን ፍቅሯንም ያሳድርብን::

††† መስከረም 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን 200ው ሊቃውንት (በኤፌሶን የተሰበሰቡ)
2.ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
3.ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ
4.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት
5.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
6.ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

†ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
(ሐዋ ፳፥፳፰)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
🌹#እንኳን አደረሳችሁ ቤተሰብ📌

ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ - የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ - የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት መካከል) አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩። ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰
††† እንኳን ለታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ዓመታዊ የተዓምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

"በዛቲ ዕለት #እግዚአብሔር ገብረ: በእደ ባስልዮስ መንክረ::"
(በዚህች ዕለት እግዚአብሔር በባስልዮስ እጅ ድንቅን አደረገ)

††† ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ †††

††† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ #አርእስተ_ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ #ኤስድሮስ(ባስልዮስ የሚሉ አሉ): እናቱ ደግሞ #ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው 5 ወንድና 1 ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ ( #ቅድስት_ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን 5ቱም ወንዶች ዻዻሳት መሆናቸው ነው::

የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: #ቅዱስ_ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው:: ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች (websites) እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል::

††† ቅዱስ ባስልዮስ
ገዳማዊ ጻድቅ:
ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ:
የብዙ ምዕመናን አባት:
የቂሣርያ ሊቀ ዻዻሳት:
ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ያስገነባ እርሱ ነው::

እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዛሬ ይህኛውን ታስባለች::

በዘመኑ እዚያው #ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ::

እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቅዋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ" አለው::

ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ:: መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት 6 ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል" ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ: ነጥቆ ወደ ጥልቁ: የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::

ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ" አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው::

በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ" አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ::

እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ: ጸለዩ: ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ " #ቤተ_ክርስቲያን ተሳልመህ: ቆርበህ : ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ: አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው:: እርሱም "በጭራሽ አላውቅም" አላት:: "ለምን?" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት::

ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በህሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት:: "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል" አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች::

እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ: በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሺን አምጪው" አላት:: ሒዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ: ከ40 ቀን በሁዋላ ትመጫለሽ" ብሎ አሰናበታት::

በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ4 አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከ3 ቀን በሁዋላ እመጣለሁ" ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ3ኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው:: "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ" አለው:: "አይዞህ!" ብሎት ወጣ::

በ6ኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው:: "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ: ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል" አለው:: "በርታ" ብሎት ሔደ:: በ9ኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው:: "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው" አለው::

እንዲህ በ3: በ3 ቀናት እየተመላለሰ ለ13 ጊዜ ጠየቀው:: በ39ኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስ በ40ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት: ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ: ያን ሰው ከመሃል አቁሞ: "እግዚኦ በሉ" አላቸው::

ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ40 ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ::

የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር 6 ቀን ዐርፏል::

††† አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሤራ ይሰውረን:: ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን::

††† መስከረም 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
2.አባ ይስሐቅ ባሕታዊ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

እውነት እውነት እላቹሃለሁ:: በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል:: ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል:: እኔ ወደ አብ እሔዳለሁና:: አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ:: ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ::
(ዮሐ 14:12)
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/09/23 00:07:35
Back to Top
HTML Embed Code: