Telegram Web
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የምርምር ተቋማት የኢንዱስትሪ ትስስር ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና አእምሮዓዊ ንብረት አስተዳደር ስልጠና ተሰጠ
========================================================
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፣ ከኢኖቨሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና አጋር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የምርምር ተቋማት የኢንዱስትሪ ትስስር ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና አእምሮዓዊ ንብረት አስተዳደር ቁልፍ ርዕሶች ዙሪያ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮዎች እና ኢንዱስትሪዎች ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ስልጠና ሰጥቷል::

ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ በበየነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት “ሀገራችን ከኢኮኖሚው አንጻር ያስቀመጠችውን መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር የመመስረት ራዕይ እውን ለማድረግ እና እየተመዘገበ ያለውን ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ የተሟላና የተሳካ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅምን መገንባት ወሳኝ ነው” ብለዋል::

ፕ/ር አፈወርቅ አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም ለልማት የሚያስፈልጉንን ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን የማመንጨት፣ የመለየት፣ የማፈላለግ፣ የመምረጥ፣ የመጠቀም፣ የማላመድ እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር አቅማቸውን ማጎልበት እንዲሁም በቅርበት ተናበው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል::
ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የእውቀትና የቴክኖሎጂ ምንጭ በመሆን የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በንድፈ ሀሳብና በተግባር እውቀት የተገነቡ፣ በገበያ ተፈላጊነት ያላቸው፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ እና ስራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በጥብቅ ቁርኝት መስራት ሲችሉ እና የዩኒቨርሲቲዎች ስርዓተ ትምህርት ቀረጻም የኢንዱስትሪውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆን አለበት ብለዋል::

ትናንት መስከረም 14 በተጀመረዉ በዚህ ፕሮግራም የከፍተኛ ትምህርት ስልጠና ተቋማት የኢንዱስትሪ ትስስር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መመሪያ እና ረቂቅ ፖሊሲ ሰነዶች በዶ/ር ሰለሞን ቢኖር፣ የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል እና በአቶ ተሾመ ዳኒኤል፣ የተቋማት ትስስር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ቀርበዋል፡፡
በቴክኖሎጂና ኢኖቨሽን እና አእምሮአዊ ንብረት አስተዳደር ጽንሰ ሀሳቦች ላይ የኢፌዴሪ ቴክኖሎጂና ኢኖቨሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ሳህለወርቅ እና ከአእምሮአዊ ንብረት አስተዳደር ጽ/ቤት ቀርበዉ ዉይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ጉብኚት የተካሄደ ሲሆን ጉብኚቱን የሲዳማ ክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሩ ከፍተዋል፡፡
በምርምር ስነ ምግባር ላይ የተሰጠው ስልጠና ጠቃሚ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ

********************************************

(መስከረም 15/2014ዓ.ም) ለሁለት ቀናት በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ሲሰጥ የነበረዉ የምርምር ስነምግባር ስልጠና ተጠናቋል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር ሰለሞን ቢኖር በበኩላቸው የምርምር ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያስፈልጉት ቁልፍ ጉዳዮች ዉስጥ አንዱ የምርምር ስነ-ምግባር በመሆኑ ወደፊትም በተጠናከረ መልኩ መተግበር እንዳለበት ገልጸው ስልጠናው በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ ጉልህ ሚና የተጫወቱትን የሐረማያ ዩኒቨርስቲ አመራሮችን እና ሰራተኞችን አመስግነዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ከማስተባበር በተጨማሪ ሳይንስንና የተቋማት ትስስርን በሀገር-አቀፍ ደረጃ እንደሚያስተባብር ገልጸዉ መሰል የምርምር ስነ-ምግባር ስልጠና በሁሉም የከፍተኛና ምርምር ተቋማት ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠልና መተግበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የሐረማያ ዩኒቨርስቲ የምርምር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ለማ እንደተናገሩት በሃገር-አቀፍ ደረጃ በእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ የምርምር ተገቢነት፣ ጥራትና ፍትሃዊነት ትልቅ ጉዳይና ስትራቴጅ ስለሆነ የበለጠ መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ሐረማያ ዩኒቨርስቲም የምርምር ተገቢነትና ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ተስፋዬ በጤና ሳይንስ ዘርፍ የተቋቋመ የምርምር ስነምግባር በስራ ላይ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ተመሳሳይ አደረጃጀቶች በሌሎች ኮሌጆች እንደሚቋቋሙ ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የነበረዉ ስልጠና ትናንት ማምሻዉን ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቅቋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት›› ህዝባዊ ንቅናቄ ተቀላቀሉ
======================================
(መስከረም 19/2014ዓ.ም) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት›› ህዝባዊ ንቅናቄ ፕሮግራም በዛሬዉ እለት አካሂደዋል።
“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ሃሳብ የአሸባሪውን ሕወሓት ሀገር የማፍረስ እቅድ ለማጋለጥ እንደ ሃገር ከመስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ንቅናቄዉ እየተካሄደ ይገኛል።
የዚህ ንቅናቄ ዋና ዋና ዓላማዎች በአገራችን ኢትዮጵያ ላይ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰ ያለውን ያልተገባ አሉታዊ ጫና ለመመከት፣ የኢትዮጵያውያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ፣ የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ወረራ ለማጋለጥ እና በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሸባሪው ህወሓት የፈጸመውን ግፍ ማሳየት ሲሆን ይህ ፕሮግራም እንደአገር እየተካሄደ ባለዉ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ዘመቻ አጋርነታችንን የምንገልጽበት እና በአገራዊ ጉዳይም ያለንን ድጋፍ በፊርማ የምናረጋግጥበት መሆኑ በተሳታፊ ሰራተኞች ተገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተካሄደውን መርሃ ግብር ጨምሮ በዘመቻው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተር ጀኔራሎች ፣ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች ከ210 በላይ ሰራተኞች ተሳትፈዋል።
2024/10/02 08:20:18
Back to Top
HTML Embed Code: