tgoop.com/SPMMC/2837
Last Update:
የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያጸደቀው የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2014 ምን ጉዳዮችን ይደስሳል?
በቅርቡየጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 ምክር ቤቱ ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን ከጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አጽድቋል።
አዋጁ በጤናው ዘርፍ በተለያዩ ሕጎች በተበታተነ እና ለአፈፃፀም ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የሚገኙ የጤና አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በአንድ ማእቀፍ ሕግ እንዲወጣ አስፈላጊነቱ ስለታመነበት እና ከእነዚሁ ድንጋጌዎች በተጨማሪም አሁን ወቅቱ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ የተጣጠመ አዳዲስ የጤና አገልግሎት ለመዘርጋት፣ የማህበረሰባችን ባህልና ሃይማኖትን፣ነባር ህጎችን በጥንቃቄና በጥልቀት በመመልከት እንደዚሁም በስራ ላይ የነበሩት ድንጋጌዎችን በማሻሻል ወጥ የሆነ እና ለአፈፃፀም ግልፅ የሆነ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተግበራዊ ለማድረግ የሚደግፍ ሲሆን የጤና ባለሙያዎችን ሙያዊ መብትንም ያካተተ አዋጅ ነው፡፡ በዋናነት የዚህ የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ዋና ዋና አላማዎቹ፡-
የጤና መመዘኛ መስፈርቶችን በማውጣት እና በመተግበር ተጠያቂነትና ጥራት ያለው እንዲሁም ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመዘርጋት፤
የሐገሪቱን የጤና አገልግሎት በማዘመን የሕብረተሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል አሰራር ተግበራዊ ለማድረግ ፤
የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች፤እንዲሁም የጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ሥርዓት ቀልጣፋ ዉጤታማና ወጥነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ፤
የጤና አገልግሎት ስርዓቱን ለማሻሻል የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚመሩበት እና የሚተገበሩበት አሰራርን ለመዘርጋት፤
የጤና መረጃ ስርዓት በመዘርጋት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥን በማረጋገጥ የጤና እና ጤና ነክ አገልግሎትን ጥራትና ደህንነት፤ ተደራሽነት እና የተገልጋይ ደህንነትን ለማሻሻል ነዉ፡፡
እነዚህን ዓላማዎች ከማሳካት አንጻር አዋጁ አጠቃላይ የጤና አገልግሎት እና ልዩ የጤና አገልግሎቶች የሚሰጡበትን ስርዓት፤ የጤናዉ ዘርፍ የሰዉ ሀብት ልማት እና አስተዳደርን የተመለከቱ፤የጤና ባለሙያዎች፣ ጤና ተቋማት፣ ጤና-ነክ ተቋማት እና የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥጥር፤ የጤና ምርምር አተገባበር፤ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓት፤የጤና ፋይናንስ እና የመንግስትና የግል አጋርነት፤ እንዲሁም ይህንን አዋጅ የሚያስፈጽሙ አካላት የሚኖራቸዉ ተግባር እና ሀላፊነትን የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡
በእነዚህ በተጠቀሱ ዋና ዋና የአዋጁ ይዘቶች ዉስጥ የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት እንደማንኛዉም የጤና አገልግሎት ሽፋን የተሰጠዉ ሲሆን አዋጁ በተለይም የእናቶች እና ህጻናት ጤናን በቀጥታ የሚመለከቱ የተለያዩ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡
ለአብነትም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መርሆች መካከል ሴቶች እና ህጻናትን ለመንከባከብ አዎንታዊ ልዩነት ሊደረግ እንደሚችል፤ ክትባትን በተመለከተ ማንኛዉም ወላጅ፣አሳዳጊ ወይም በህግ ሀላፊነት የተጣለበት ሰዉ ህጻናትን የማስከተብ ግዴታ እንዳለበት፤እንዲሁም በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ ማግኘት ወይም ወላጅ መሆን ያልቻሉና በባለሙያ የተረጋገጠ የትዳር ጥንዶች በቴክኖለጂ በታገዘ ሁኔታ ልጅ ማግኘት የሚችሉበትን አማራጭን በተመለከተ ዝርዝር ስርዓቶችን አስቀምጧል፡፡ ይህ ተግበራዊ ሲሆንም ቀደም ሲል አገልግሎቱን ለማግኘት ከሀገር ውጪ የሚደረግን ጉዞ ፣እንግልት እና ከፍተኛ ወጪ ያስቀራል ማለት ነው፡፡
አዋጁ ማንኛውም የጤና ተቋም እና የጤና ነክ ተቋማት የሚሰጠውን የአገልግሎት ጥራትና ደህንነት እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የቁጥጥር ስርዓቱ የሚጠናከርበትን ድንጋጌዎች አስቀምጧል ፡፡ ተገልጋዮች በጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲመጡ ጥራቱን የተጠበቀ ፣ፍትኃዊ የሆነ ፈጣንና የተሟላ አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተጠያቂነት ባመላከተ መልኩ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ሌላው አዋጁ በግልጽ ድንጋጌ ያስቀመጠው ጉዳይ የጤናው ዘርፍ ሰራተኛ መብትን ነው፡፡ለአብነት ፡- በሌሎች የሐገሪቱ ህጎች ስለ ስራ ቦታ ደህንነት የተደነገጉ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ የጤናው ዘርፍ ሰራተኛ በስራው ባህሪ ምክንያት ተጋላጭ ለሚሆንባቸው በሽታዎች ቅድሚያ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው ደንግጓል፡፡የጤናው ዘርፍ የመንግስት ሰራተኛ የጤና መድህን አባልነት ሙሉ መዋጮ በመንግስት እንደሚሸፈንም አስቀምጧል፡፡ ለዚህም ዝርዝር አፈጻጸም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ አማካይነት በወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም የጤና ባለሙያ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት በቁጥጥር ስር የሚውለው ባለሙያዉ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ ምክያታዊ ጥርጣሬ እንዲኖር የሚያስችል ማስረጃ ሲኖር እንደሆነም አዋጁ ይደነግጋል፡፡
ሌላው አዋጁ በዋናነት ያስቀመጠው የልብ እና የመተንፈሻ አካላት የአሰራር ሥርዓት መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ በመሳርያ ላይ የተመሰረተ የአተነፋፈስ ስርዓትን በሶስት አግባነብት ባላቸዉ ባለሙያዎች ዉሳኔ ማቋረጥ እንደሚቻል እና ይህም ቤተሰብን ለማይመለስ ነፍስ ከአላስፈላጊ እንግልትና ወጪ እንደሚታደግ ይታመናል። የዚህ ድንጋጌም ዝርዝር አፈጻጸም ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ይሆናል፡፡
ሌላው በዚህ አዋጅ ላይ ተደነገገው የደም፣ ህዋስ፣ ህብረ ህዋስ፤ የአካል ክፍል ወይም የአካል ልገሳ እና የንቅለ-ተከላ ህክምና አገልግሎትን የተመለከተ ሲሆን በዚሀም ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው አካል ፊት ቀርቦ በሚሰጠው ፈቃድ መሰረት ደም፣ ህዋሱን፣ ህብረ ህዋሱን፣ የአካል ክፍሉን፣ አካሉን መለገስ ይችላል፡፡መለገስ የሚችለውም ለዚሁ ዓላማ ሲባል ለሚቋቋመው ተቋም ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያዘዘ ማንኛውም ሰው በሽያጭ ወይም ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ደም፣ ህዋስ፣ ህብረ ህዋስን፤ የአካል ክፍል እና አካልን መለገስም ሆነ መቀበል የተከለከለ ነው፡፡ ከህጋዊ የልገሳ ስርዓት ውጭ የተገኘ አካል፤ የአካል ክፍል፤ ሕብረ ሕዋስ ወይም ሕዋስ አገልግሎት ላይ ማዋል የተከለከለ ነው፡፡
ከሞት በኋላ ተፈጻሚ ስለሚሆን ልገሳ ማንኛውም ሰው ህይወቱ ሲያልፍ ህዋሱን፣ህብረ ህዋሱን ፤ የአካል ክፍሉን ወይም አካሉን ለመለገስ ፈቃዱን አግባብነት ላለው አካል ሊለግስ ይችላል። ይህንንም በዝርዝር አዋጁ አካቷል፡፡
በአጠቃላይ አዋጁ መንግስት በህገ መንግስቱ የተጣለበትን ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት ለዜጎች የማቅረብ እና ተደራሽ የማድረግ ግዴታዉን ለመወጣት የሚያስችለዉን የተሻለ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ በቀጣይ ይህንን ሀላፊነት ከመወጣት አኳያ በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ወደ ተግባር ለማዉረድ የሚያስችሉ ዝርዝር ደንቦችና መመሪያዎች የሚወጡ፤ እንዲሁም የአሰራር ስርዓቶች የሚዘረጉ ይሆናል፡፡
(ምንጭ፡ ጤና ሚኒስቴር-ኢትዮጵያ )
BY St.Paul's Hospital Millennium Medical College
Share with your friend now:
tgoop.com/SPMMC/2837