Telegram Web
በአዲስ አበባና በሰፋፊ ከተሞች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሀብት አስተዳደር እንጂ በብዛት የሚታሙ አይደሉም፤ በሽያጭ የሚወገዱት ዣንጥላ፣ ጧፍ፣ ዕጣን፣ ዘቢብ እንደ ችግር የሚነሱ አይደሉም፣ ሌሎቹ ግን ለምሳሌ ልብሰ ተክሕኖ፣ ምንጣፎች፣ ጽዋ፣ ጻሕል፣ ዕርፈ መስቀል፣ መጋረጃዎች፣ አንዳንዴም መንበሮች በሽያጭ የማይወገዱ በመሆኑ ከፍተኛ የንብረት መጨናነቅ እየፈጠሩ ለብክነትና ለብልሽት ይዳረጋሉ፤ በመሆኑም በከፍተኛ የንዋየ ቅድሳት ዕጥረት የሚቸገሩ በገጠር የሚገኙ እጅግ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፤ ለእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ትርፍ ንብረቶች በሥርዓት የሚተላለፉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፣ በገንዘብ ደረጃ ከፍ ያለ ዓቅም ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ለመዘጋት የተቃረቡ አብያተ ክርስቲያናትን በቋሚነት የመርዳት ኃላፊነትም ሊሠመርበት ይገባል፡፡
+ + + + +
4. የአብነት ትምሕርት ቤቶች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በብዙ መልኩ ይበልጥ ለማገልገል፣ የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ ለመገንዘብ (ታሪካችን በአብዛኛው ተሰንዶ ያለው በግዕዝ ስለሆነ)፣ የአብነት ትምሕርት ቤቶች በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሊከፈቱ ይገባል፡፡ የአብነት ተማሪዎች ትምህርት ቤት ፍለጋ ከሀገር ሀገር መዞርም ሆነ በየመንደሩ እየዞሩ ቁራሽ መለመን (አኩሪና የበረከት ምንጭ ቢሆንም) ጊዜ ያለፈበት አሠራር ሆኗል፡፡ በመሆኑም በሁሉም አሕጉረ ስብከቶች ለዚህ አገልግሎት አብያተ ክርስቲያናት መለየት ይገባቸዋል፡፡ የመጽሐፍ መምሕር፣ የአቋቋም መምሕር፣ የድጓ መምሕር፣ የቅኔ መምሕር እየተባሉ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የተመደቡ ባለሙያዎች ሥራ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ሕጻናትና ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ካለበቂ ዕውቀት (በድምጫ ብቻ) ዲያቆን፣ ካሕን፣ መሪጌታ የሆኑ ሁሉ የሚማሩበት፣ የዓቅም ማሻሻያ የሚያገኙበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከአብነት ትምሕርት ቤቶች ሊወጡ ይገባል፡፡ ካህናት በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፎች (ሰይፍ ዘክልኤ አፉሁ) መሆን ይገባቸዋል፡፡ በዘመናዊው ዕውቀትም ሆነ በዓለማዊው ዕውቀት የበቁ ከሆኑ ጥቅማቸው ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለዓለም ይተርፋል፡፡
+ + + + +
5. ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት (ከሙዓለ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም)
በብዙ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰፋፊ መሬት (ይዞታ) ያላቸው ናቸው፡፡ ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት ረዘም ላለ ጊዜ ዘመናዊ ትምሕርት ቤት ከፍተው የማስተማር ልምድ አላቸው፡፡ በመሆኑም ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ አብያተ ክርስቲያናት ተለይተው የግንባታና መሰል ፈቃዶች በሀገረ ስብከቶች በኩል እንዲያልቁ ተደርጎ የሚያስተምሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥር በሚገኙ ትምሕርት ቤቶች የተማሩ ልጆች (ዜጎች) ሀገርን በፖለቲካው፣ በማኅበራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በቴክኖሎጂው የሚመሩና የሚያሻግሩ በምግባርና በሃይማኖት የታነጹ ይሆናሉ፡፡
+ + + +
6. የሕክምና ተቋማትን ማስፋፋት በተመለከተ
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እስከሚያውቀው ድረስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት የሚተዳደሩ የሕክምና ተቋማት፤ሲግናል አካባቢ የሚገኘው ምግባረ ሠናይ ጠቅላላ ሆስፒታልና ቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት እንኳን ለኢትዮጵያ ለአንድ አገረ ስብከትም ያንሳሉ፡፡ በመሆኑም በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚተዳደሩ ሆስፒታሎች፣ ከፍተኛ ክሊኒኮች፣ ክሊኒኮችና ኮሌጆች ሊኖሩ ይገባል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክሕነት ሥር ደግሞ ቢያንስ አንድ ቲቺንግና ሪፈራል ሆስፒታል ሊኖር ይገባል፡፡
+ + + + +
7. የጎጆ ኢንደስትሪና መካከለኛ ፋብሪካዎችን በተመለከተ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልባቸው ብዙ ንዋያተ ቅድሳት ከውጪ ሀገር የሚገቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጾር መስቀል፣ ጽዋ፣ ዘቢብ፣ መጋረጃ፣ ምንጣፍ፣ ልብሰ ተክህኖ እና የመሳሰሉት፡፡ እነዚህን ንዋያተ ቅድሳት በሀገር ውስጥ በዚያውም በአብያተ ክርስቲያናት ቢመረቱ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረው ትርጉም እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ምርቶቹን መሠረት አድርጎ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና አሕጉረ ስብከቶች የልየታ ሥራ በመሥራት የሚመረቱበትን አሠራርና የገበያ ተሥሥር እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በሕትመት በኩል ዕድሜ ጠገቡ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ድርጅት ዘመኑን የዋጀ ሊሆንና የአገልግሎት አድማሱን ሊያሰፋ ይገባል፡፡
+ + + + +
8. የፕሮጄክት አስተዳደርን በተመለከተ
በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚታዩ ፕሮጄክቶች የጠለቀ ጥናት ያልተደረገባቸው፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃም ቢሆን ስምምነት ያልተደረሰባቸው (የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሆኑ) የሚጀመሩበትና የሚጨረሱበት ጊዜ የማይታወቁ፣ ተደራራቢ (በአንድ ጊዜ ሁለት ሦስት ፕሮጄክቶች) የሆኑ፣ ኃላፊዎች ሲቀያየሩ የሚቆሙ፣ የገንዘብ አሰባሰብ፣ አወጣጥ፣ አስተዳደር ዘዴ ያልተበጀላቸው (ለምዝበራ የተጋለጡ)፣ ተገቢ የሆነ የክትትል የድጋፍ እና የቁጥጥር አሠራር ያልተበጀላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች አንድ ቀላል ፕሮጄክትን ለመፈጸም ብዙ ዓመታትን ይወስዳል፡፡ በአብያተ ቤተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉና ዓመታትን ያስቆጠሩ ብረቶች፣ ጠጠር፣ አሸዋ እና የደረቁ ሲሚንቶዎችን መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡
በመሆኑም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በክፍለ ከተማ ደረጃ በሌሎች አሕጉረ ስብከቶች ደግሞ በሀገረ ስብከት ደረጃ በባለሙያ (ቅጥርና በበጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች) የተደራጀ የሥራ ክፍል ሊያደራጅ ይገባል፡፡ የሥራ ክፍሉ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚቀርቡ ፕሮጀክቶችን የሚመረምር፣ የአካል ጉብኝት በማድረግ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሆን ፕሮጄክቶችን የሚቀርጽ፣ የሚከታተል፣ የሚደግፍና የሚቆጣጠር እንዲሁም የእርምት እርምጃ የሚወስድ ሊሆን ይገባዋል፡፡
+ + + + +
9. የሥነ ምግባር መከታተያ መምሪያ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊትና ሰማያዊት ብትሆንም በምድር ያለች፣ በምድራውያን ሰዎች የምትተዳደር ናት፡፡ ምድራውያን ሰዎች ደግሞ ሊያለሙም ሊያጠፉም ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በአብየተ ክርስቲያናትና በሌሎች መዋቅሮች የሚታዩ የአስተዳደር ብልሹነቶችን የሚመለከት፣ የሚመረምር፣ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ ቢያንስ በክፍለ ከተማ ደረጃ መዋቅርና በአጥቢያ አቤ ክርስቲያን ደረጃ አንድ ባለሙያ ሊመደብ ይገባል፡፡
+++++++
የቤተ ክርስቲያን ደጆች በምሕረትና በሃይማኖት እንዲከፈቱ ያድርግልን፡፡

ሼር በማድረግ አድርሷቸው
† የአዲስ ኪዳን ታቦት †

★ ታቦት ማክበር ወንጌል አለመረዳት ነውን?★

★ የብሉይ ኪዳን ታቦትና የአዲስ ኪዳኑ ለምን ተለያየ ?

መ/ር ታሪኩ አበራ

#ማሳሰቢያ ይህን ትምህርት ሼር በማድረግ በስህተት
ጎዳና ያሉ ወገኖትን በማስተማር አንድ ነፍስ ያድኑ።

ታቦት ቃሉ የግእዝ ሲሆን ትርጓሜውም ማደሪያ ማለትነው።ታቦት በብሉይ ኪዳን ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎትሲሰጥ የቆየ ቅዱስ ንዋይ ሲሆን በሐዲስ ኪዳንም የራሱ የሆነ አገልግሎት ያለው የከበረ መንፈሳዊ የክብር መገልገያ ነው። ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ አንዳንድ ሰዎች የብሉይ ኪዳን ታቦትንና የአዲስ ኪዳን ታቦትን አንድ አድርገው በማሰብ የአዲስ ኪዳኑ ታቦት ፍጹም ስህተት እንደሆነና መኖርም እንደሌለበት በተሳሳተ ግንዛቤ ሲተቹ ስለተመለከትኩኝ ነው።

በጣም ልናስተውለው የሚገባን የብሉይ ኪዳን ታቦትና የአዲስ ኪዳን ታቦት በቅርጽና በይዘት፣በዓላማና በአገልግሎት ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸውን ነው።የብሉይ ኪዳን ታቦት በይዘቱ ትልቅ የሆነና አራት መያዣዎች ያሉት ሲሆን በአራት ሰዎች የሚያዝ ነው።አገልግሎቱ ደግሞ አሰርቱ ትእዛዛት የተጻፈባቸውን ሁለት ጽላቶች ለማስቀመጫነት የሚጠቅም ነው።ታቦት የሚለው ቃል ማደሪያ የሚል ትርጉምንም ያገኘው ከዚሁ ይሰጥ ከነበረው የማደሪያነት አገልግሎት አንጻር የተሰጠ ስያሜ ነው።

ይህንን የከበረ የሕግ ማደሪያ(ታቦት) ይሰሩና በወርቅ ይለብጡት ዘንድ ለሙሴና ለአሮን ያዘዛቸው ራሱ እግዚአብሔር ነው።ዘፀ 25፥8 እግዚአብሔር ያለ ዓላማና ያለ ምክንያት አንዳችም ነገር ሰዎች ይሰሩ ዘንድ አያዝም።በዘመነ ብሉይ የታቦቱ መኖር ታላቁ ዓላማ እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ከነዓን ሲጓዙ መንፈስ የሆነውንና በሥጋዊ ዓይን የማይታየውን እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ ለማምለክ የእምነት ደረጃቸውና የአምልኮ ልምምዳቸው ገና ስለነበር በሚታየው ታቦት ፊት የማይታየውን እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ አዕምሯቸውን የሚያግዝ በፊታቸው የሚያልፍ ፣የሚታይና ግዘፍ ያለው ነገር መኖር ስለነበረበት እግዚአብሔር ታቦት በመካከላቸው ይኖር ዘንድ ወደደ።

የሰው ልጅ አእምሮ በሃይማኖት አድጎና በእምነት ጎልምሶ በመንፈስ ማምለክ እስካልጀመረ ድረስ ከኅሊና በላይ ረቂቅ የሆነውን እግዚአብሔርን ለማምለክ በዓይኑ ፊት የሚታዩና የሚዳሰሱ ኅሊናውን ለአምልኮ የሚያግዙ መንፈሳዊ ንዋያት ያስፈልጉታል። በዚህም ምክንያት ነበር የሕጉ ማደሪያ በሆነው በታቦት ላይ የሠራዊት ጌታ ራሱን በክብር እየገለጠ ኃልዎቱን በማሳየት ለክብር የመረጠው ሕዝብ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ እንዳለ በእርግጠኝነት እንዲያምንና ለእርሱ በፍቅር እየተንበረከከ የእጆቹን በረከት እንዲመገብ እንዲሁም ከአሕዛብ ጣዖታት ራሱን እንዲጠብቅ ያደርግ የነበረው።

" በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።" (ኦሪት ዘጸአት 25:22)

ስለዚህም የብሉይ ኪዳን ታቦት የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ዙፋንና ኃልዎቱን ማስረጃ የክብር ንዋይ ስለነበር ሕዝቡ ታቦቱ ወዳለበት ወደ መገናኛው ድንኳን እየሄደ በክብር ደመና የሚገለጠውን እግዚአብሔርን በፍቅር ያመልክ ነበር ።በሕዝቡና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ግንኙነትም እንደ አባትና ልጅ የቅርብ ነበር እንጂ እግዚአብሔር መንፈስ እንደ መሆኑ ለሕዝቡ ፈጽሞ ከሕሊናቸው የራቀ አልነበረም።

ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ የአዲስ ኪዳን ታቦት በይዘትና በመጠን በአገልግሎት እና በዓላማ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሳይሆን የከበረውን የክርስቶስ ሥጋና ደም በከበረ ቅዱስ ንዋይ ላይ ለመፈተት የምንጠቀምበት ክቡር ምስዋዕ ነው።በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን የገለጠው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዌ በኩል ነው ።መልአኩ ለቅድስት ድንግል ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ካበሰረ በኋላ ባሕርያችንን ባሕርይው አድርጎ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ በምድራችን በሥጋ የተገለጠው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ከብሉይ ኪዳኑ ታቦት በላቀ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ክብር ገልጦልናል፣በአባቱ እቅፍ ያለው የበኩር ልጅ አባቱን ተርኮልናል።

የእግዚአብሔርን መኖርና መግቦቱን በግልጽ የክርስቶስ ሰው መሆን ዓለም እንዲረዳው አድርጎታል። ዓይንና ልባችን ወዴትም እንዳያይ ፈጣሬ ፍጥረታት መጋቤ ዓለማት አንዱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ልባችንን ገልጦ አስተምሮናል። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ። " ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን።" ዕብ 1፥1

ስለዚህ የብሉይ ኪዳኑን ታቦት ክብርና ዋና ዓላማ ክርስቶስ ኢየሱስ ጠቅልሎ ወስዶታል የእግዚአብሔርን ክብርና መግቦት በልጁ በኩል የበለጠ ተገልጦልናል። " መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።" (የዮሐንስ ወንጌል 1:18) ሌላው የብሉይ ኪዳን ታቦት አገልግሎት ሕጉ ለተጻፈበት ጽላት ማደሪያ ነበር ዛሬ የአዲስ ኪዳን ታቦት ላይ በየቤተ ክርስቲያኑ ስመ እግዚአብሔር ይጻፍበታል እንጂ አስርቱ ትእዛዛት አይጻፍበትም ምክንያቱም ሕጉን በልባችን ላይ እንደ ሚጽፈው በቅዱስ ቃሉ አስረግጦ ነግሮናል።ክርስትና ደግሞ ከፊደል ሕግ በላይ በመንፈስ ሕግ የምንኖርበት የቅድስና ሕይወት ነው። " እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው።" (2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3:3)

በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔርን በእውነት እና በመንፈስ እናመልካለን ፣በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ያገኘነውን ሕይወትና ጽድቅ በልባችን እያሰብን በኅሊናችን ሕያው ሆኖ የሚኖረውን የእግዚአብሔርን ክብር ለፍጥረት ሁሉ ስናውጅ እንኖራለን።

#የአዲስ ኪዳን ታቦት አስፈላጊነት ለምንድነው?

መልሱ አጭርና ግልጽ ነው የኃጢአት ሥርየት ያገኘንበትንና ወደ ዘለዓለም ሕይወት የተሻገርንበት የከበረው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም መፈተቻ አድርገን እንጠቀምበታለን ።ዛሬ በቤተ መቅደስ የሚፈተተው ሥጋና ደም በእለተ አርብ ከፈሰሰው የኪዳን ደም ጋር በእምነት ሕብረት የምንፈጥርበት ስለሆነና ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት ያገኛል ያለውን መለኮታዊ ቃል በተግባር የምንፈጽምበት ስለሆነ ለከበረው መንፈሳዊ መስዋዕት የከበረ ቅዱስ መሰዊያ ስለሚያስፈልግ ታቦቱን በክብር እንጠቀምበታለን።
አንዳንድ ሰዎች ከእውቀት ማነስ የተነሳ የአዲስ ኪዳኑን ታቦት ሲያጣጥሉና ሲነቅፋ ባልተገራ አንደበትም ጣዖት ነው ሲሉ እንሰማለን ፈጽሞ ስህተት ነው።የከበረው የክርስቶስ ስም የተጻፈበት ታቦት ጣዖት አይባልም።እንኳንስ መንፈሳዊ ምግባችንን ለምንፈትትበት ቅዱስ ምስዋዕ ለሥጋዊ ምግባችን እንኳን ማዕድ የምናስቀምጥበትን ገበታ በክብር እንይዛለን ።የከበረው የክርስቶስ ደምና ሥጋ ለሚቀርብበት ቅዱስ መሰዊያማ የበለጠ ክብር ልንሰጥ ይገባል። አንዳንዶች እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው የዓለም ማኅበረሰብ ይልቅ በልዩ ሁኔታ ከታቦት ጋር ያለንን ልዩ ሕብረት በመመልከት ሌሎች ሀገሮች የማይጠቀሙትን እናንተ ኦርቶዶክሳውያን እንዴት ትጠቀማላችሁ ይሄ ወንጌልን አለመረዳት ኦሪታዊነት ነው ይላሉ በጣም ስህተት ነው።

ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን በጥልቀት ልናጠና ይገባል ሌሎች ሀገራት ክርስትናን የተከተሉትና ወንጌልን የተቀበሉት ቀድሞ ከነበሩበት ከጣዖት አምልኮ በሐዋርያት ስብከትና በብዙ ድንቅ ተአምራት ተላቀው ወጥተው ነው ።እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ወደ ሕገ ወንጌል የተሻገርነውና ክርስትናን የተቀበልነው ቀድሞ ከነበርንበት ከሕገ ኦሪት ወጥተን ነው።ታሪክ በግልጽ እንደሚያስረዳን ከእስራኤል ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን ሕግና መንፈሳዊ ሥርዓት እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረች ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ነች ።ሌላው ዓለም ጣዖት በሚያመልክበትና በየጋራውና በየወንዙ እንግዳ አማልክትን በሚከተልበት የጨለማ ዘመን የአብርሃም አምላክ እያለች እግዚአብሔርን ታመልክ የነበረች ቅድስት ሀገር ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ነች። ስለሆነም ለታቦት ክብር መስጠታችን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ከመጣው የአምልኮ ትውፊታችን ጋር የተያያዘ ነው እንጂ እንደ ውሃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነ ዘመን ላይ የተፈጠረ ክስተት አይደለም ።

ሌሎች ሀገራት ግን ከጣዖት አምልኮ የመጡ በመሆናቸው እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሥርዓት የላቸውም። ይሁን እንጂ አዲስ ኪዳንን ከተቀበሉ በኋላ በየቤተመቅደሳቸው የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚፈትቱበት እንደ ታቦት ለመሰዊያነት የሚጠቀሙበት የከበረ ንዋይ አላቸው። ልብ እንበል የክርስቶስ ሥጋና ደም መሠጠቱን የሚያምን አንድ ክርስቲያን ይህ የከበረ ሥጋና ደም እንደ ተራ ማዕድ በየቦታው ፣ በየጠረጴዛው ሊቀርብ ይችላል ብሎ ለማሰብ እጅግ ይከብደዋል፡፡

ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ስደትዋ እስካበቃበት ዘመን ድረስ በሒደት እየተሻሻለ በመጣ የቤተ መቅደስ ሥርዓት የሐዲስ ኪዳኑን መሥዋዕት በክብር ለመሠዋትና ለምእመናን ለማቀበል በቅታለች፡፡ የበግና የፍየል ደም ይሠዋ በነበረበት የኦሪት ዘመን እንኳን ለብቻው ትልቅ መሠዊያ ተዘጋጅቶ ፣ መሠዊያው ተቀድሶ ሰው በማይገባበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በክብር ተቀምጦ ነበር፡፡ በድንኳኒቱ ውስጥ የሚያገለግሉት አሮንና ልጆቹም የተለየ ልብስ ለብሰው የበጉን ደም በመሠዊያው ዙሪያ ባለው ቀርነ ምሥዋዕ (የመሠዊያ ቀንድ) ላይ እየቀቡ ሥርዓቱን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ለበግና ለፍየል መሥዋዕት ይህ ሁሉ ክብር ከተሠጠ እንደ በግ ስለ ሁላችን ኃጢአት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ እንደ ሊቀ ካህናትነቱ እጁን በመስቀል ላይ ዘርግቶ የሰዋውና ዓለም እንዲድንበት እንካችሁ ብሉ ብሎ የሠጠን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብበት መሠዊያ ምንኛ የከበረ ይሆን?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥጋ ወደሙ ‹መሠዊያ› የምትለው ታቦት በቅርጽም ፣ በአገልግሎትም ፣ በክብርም በኦሪት እግዚአብሔር ለሙሴ ከሠጠው ታቦት ጋር አንድ አይደለም፡፡ የቀደመው ታቦት በአራት ካህናት የሚያዝ በውስጡ ጽላት የሚቀመጥበት ሲሆን የአሁኑ ታቦት ግን የጽላት ቅርጽ ያለው ጽሌ (ሰሌዳ) ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሐዲስ ኪዳኑን ታቦት በሦስት ስያሜ ትጠራዋለች - የቃልኪዳኑ ታቦት ፣ ጽላት እና መሠዊያ ብላ፡፡ የቃልኪዳኑ ታቦት የሚባለው እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስላደረገው ስለ ቀድሞ ቃልኪዳን ሳይሆን ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› ተብሎ ስለተሠጠው እና ‹‹ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› ብሎ ጌታችን ስለ ሠጠን አዲሱ ኪዳን ነው፡፡ (ማቴ. 26፡ 26-30) የቃልኪዳኑ ታቦት የሚባለው በሥጋ ወደሙ ስለተሠጠን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ታቦት መባሉ ደግሞእግዚአብሔር በረድኤት የሚያድርበት ፣ በሥጋ ወደሙ ደግሞ በአካል የሚገለጥበት ዙፋን ስለሆነ ነው፡፡ ጽላት (ሰሌዳ) የሚባለው ዐሠርቱ ትእዛዛት ተጽፈውበት አይደለም፡፡ የሕግ ሁሉ ፈጻሚ የሆነው የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚለው የከበረ ስሙ በታቦቱ ላይ ስለተጻፈ ነው፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን /ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ/ ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ /ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ/)

አንዳንድ ሰዎች ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ከኦሪቱ ጋር አይመሳሰልም!›› ብለው እንደ ትልቅ መከራከሪያ ሲያውጁ ማየት እጅግ ያስገርማል፡፡ አንዴ ‹ኦሪታዊት ነሽ› አንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹ለምን እንደ ኦሪቱ አልሆንሽም›› ብሎ ንትርክ ግራ ያጋባል፡፡ የኦሪቱን ያልመሰለው አሁን ያለነው ሐዲስ ኪዳን ላይ ስለሆነና የታቦቱ አገልግሎት የተለየ ስለሆነ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ ‹‹የኦሪት ጽላት እግዚአብሔር በደመና ተከናንቦ ሙሴንና አሮንን የሚያነጋግርበት ለእስራኤል ብቻ በረድኤት የሚገለጥበት ዙፋን ነበር፡፡ ይህ ግን (የሐዲስ ኪዳኑ ታቦት) የአምላክ ሥጋና ደም የሚፈተትበት ጌታችን ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ እያለ ያመኑትን የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ (መሠዊያ) ነው፡፡ ክብርና ስግደትም የሚደረግለት ለዚህ ነው፡፡›› (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 109)

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በታቦታቱ ሁሉ ላይ የተጻፈው ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚለው የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ስም ነው፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች ታቦት ላይ ይጻፋል አልፋ፣ወዖ፣ቤጣ ፣የውጣ ፣ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው የሚሉ ምሥጢራዊ ትርጉም ያላቸው ስሞች ይጻፋሉ።ታቦት ሲወጣ በአክብሮት እጅነስተን የምንበረከከው ከስሞች ሁሉ በላይ ለሆነው ታላቅ ስም ነው። ከስሙ ጋር ደግሞ በሁሉም ታቦታት ላይ የሚከተለው ጥቅስ በግእዝ ተጽፏል፡፡ ‹‹ከመ ለስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይስግድ ኲሉ ብርክ ዘበሰማያት ወዘበምድር›› ‹‹ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ›› የሚል ነው፡፡ (ፊልጵ. 2፡10) በታቦቱ ፊት የሚሰግድ ሰው ለምን እንደሚሰግድ በታቦቱ ላይ የሚጻፈው ይህ ጥቅስ ያስረዳናል፡፡ ምክንያቱ ‹‹ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይሰግዱ ዘንድ›› ስለሚገባ ነው፡፡ የክርስቶስ ሥጋ እንደሚቆረስ ደሙ እንደሚፈስስ የሚያምን ሰው በዚህ መሠዊያ ፊት በፍርሃት ለክርስቶስ ይሰግዳል፡፡ ሥጋ ወደሙን ‹‹ተራ መታሰቢያ ብቻ ነው›› የሚል ሰው ግን በመሠዊያው ፊት እንዲሰግድና መሠዊያውን እንዲያከብር አንጠብቅም፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በታቦቷ ጽፋ ክብር የምትሠጥ የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ልጆች ስለሆንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ የታቦቱ ሌላ መጠሪያ የመሠዊያ ታቦት (ታቦተ ምሥዋዕ) የሚል ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ መሠዊያ ‹‹መሠዊያ አለን በድንኳኒቱ የሚያገለግሉ ከእርሱ ሊበሉ መብት የላቸውም›› በማለት ስለ ሐዲስ ኪዳኑ መሠዊያ ይነግረናል፡፡ (ዕብ. 13፡10) ይህ መሠዊያ በኦሪት ድንኳን የሚያገለግሉ የአሮን ልጆች ከእርሱ ሊበሉ መብት የሌላቸው ለእኛ ክርስቲያኖች ብቻ በመሠዊያው ያለውን ሥጋና ደም እንድንበላ የተሠጠን ታቦተ ምሥዋዕ (Christian Alter) ነው፡፡

የታቦትን የሐዲስ ኪዳን አገልግሎት ስንናገር የሚቃወሙ ሰዎች ከሚያነሡት ተደጋጋሚ ትችት አንዱ "ታቦት ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት›› የሚል ነጥሎ የመምታት ጥረት ነው፡፡ በተለይም የግብፅ ቤተ ክርስቲያንን በመጥቀስ ‹‹ግብፆች ታቦት የላቸውም›› የሚል ንግግር ይዘወተራል፡፡

ለዚህ ጉዳይ እኛ መልስ ከምንሠጥ የራሳቸው የግብፃውያንን ምላሽ ብቻ ማስቀመጥ ይቀልለናል፡፡ ግብፃውያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ጋር አቻ የሆኑ ሁለት ንዋያተ ቅድሳት አሏት፡፡ አንደኛው የመሠዊያው ጽላት (ሰሌዳ) /Alter Board/ ሲሆን ሁለተኛው ታቦት /Ark/ ነው፡፡ ቄስ ታድሮስ ማላቲ የተባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅ ጸሐፊ ‹‹Church The House of God›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ስለ የመሠዊያው ሠሌዳ (Alter Board) አሠራር ሲናገሩ ‹‹ይህ የመሠዊያ ጽላት አንድ መስቀል ወይም ብዙ መስቀሎች ይሳሉበታል ፤ አልፋና ኦሜጋ ተብሎ ይጻፍበታል ፤ ከዚያም መዝ. 86፡1 ላይ ያለው መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው የሚለው የመዝሙረ ዳዊት ቃል ይጻፍበታል፡፡›› ይሉና ስለ አሠራሩ ሲናገሩ ‹‹የግብፅ ቤተ ክርስቲያን መሠዊያው ስለሚሠራበት ቁስ የተደነገገ ሕግ የላትም ፤ እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከእንጨት ብቻ ይሠራ ነበር፡፡ ከዕብነ በረድና ከድንጋይም ሊቀረጽ ይችላል፡፡›› ይህንን ካሉ በኋላም እግረ መንገዳቸውን ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ምሥዋዕ ሲናገሩ ‹‹ከእንጨት የሚሠራ ታቦተ ምሥዋዕ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሥጠቱን ቀጥሏል›› (Wooden Alters continue in use in the Ethiopian Church at the present time) ብለው ያጠቃልላሉ፡፡

ይህ ስለ መሠዊያ እንጂ ስለ ታቦት አይናገርም፡፡ ስለ ታቦት በእኚሁ ጸሐፊና በቤተክርስቲያኒቱ በኦፊሴላዊ ድኅረ ገጽ ላይ የሚከተለው ተጽፏል።

"In the middle of the Alter, there is a wooden box, called in Coptic 'pi totc' which means 'a seat' or 'a throne', and is used as a Chalice- Stand. Usually it is cubicle in shape, about thirty centimetres high and twenty-five centimetres wide, the top is closed with high flaps. The beautiful carving is inlaid with ebony and ivory and is decorated with four small icons. It can be only the Lord in the last supper, St Mary, Archangel Michael, St. Mark and then the patron Saints. It is called 'the Throne' for it represents the presence of the Crucified Lord. Its name also corresponds to the 'Ark of the Old Testament', for it contained the Tablets of Law written with the finger of God to declare God's covenant with man. The new Ark now contains the true Blood of Christ, as the New covenant, that fulfils the Law and the prophets.››

(‹‹ከመሠዊያው መካከል የሚቀመጥ የእንጨት ሳጥን ሲኖር ይህ በኮፕት ቲቶት ተብሎ የሚሠራ ሲሆን ትርጉሙም ‹መንበር› ወይም ዙፋን ማለት ነው፡፡ ጽዋው የሚቆመውም በዚህ ላይ ነው፡፡ ቅርጹ ክበባዊ ሲሆን 13/25 ሴንቲሜትር ነው፡፡ ከላይ በጨርቅ ይሸፈናል፡፡ በጥቁርና ነጭ ኽብረ ቀለማት ያጌጠ ሲሆን አራት ሥዕላት በዙሪያው ይደረጋሉ፡፡ ሥዕላቱ የጌታችን ጸሎተ ሐሙስ ሥዕል የእመቤታችን ፣ የቅዱስ ሚካኤልና የሚታሰበው ቅዱስ ሥዕላት ናቸው፡፡ ‹ዙፋን› ተብሎ የሚጠራው የተሰቀለው ጌታ እንደሚያድርበት በማሰብ ነው፡፡ ይህ ስያሜም ‹ከብሉይ ኪዳኑ ታቦት› ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ያ ታቦት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያደረገው ቃልኪዳን የተጻፈባቸው የሕግ ጽላት ያሉበት ነበር፡፡

አሁን ያለው አዲሱ ታቦት ግን እውነተኛውን የክርስቶስ ደም የያዘ ሲሆን ክርስቶስም ሕግንና ነቢያትን ፈጽሞ አዲሱን ኪዳን የሠጠን ነው፡፡››) http://www.stmarkdc.org/ coptic-sanctuary ይህ ማብራሪያ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ስለ እኛ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ከሠጡት ማብራሪያ ጋር ምንም አይለያይም፡፡ ይህን እንደ ማሳያ ጠቀስን እንጂ ታቦቱ ዑደት ባለማድረጉ እና በሥርዓቱ ይለያያል እንጂ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሥጋ ወደሙ መሠዊያ ነው ብላ ከምታከብረው ታቦት ጋር በክብርና በአገልግሎት አቻ የሆኑ በቅብዐ ሜሮን የሚከብሩና በመንበር የሚቀመጡ ንዋያተ ቅድሳት በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡

ባለንበት ዘመን በሥጋ ወደሙ እውነተኛነት ከማያምኑ ሰዎች ጋር ስለ መሠዊያው አስፈላጊነት በመከራከር ብዙ ጊዜ ሲባክን ይታያል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጻፈበትን ታቦት ‹ጣዖት› ነው የሚሉ ‹ክርስቲያኖች› እያየን እንደነቃለን፡፡ ‹‹ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይንበርከክ›› ተብሎ የተጻፈበት ‹ጣዖት› እንዴት ይኖራል? ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚል ጣዖት አለ? ወንጌል በላዩ ላይ የተቀመጠበት ፣ በቅብዐ ሜሮን የከበረ ፣ ሥጋ ወደሙ የሚፈተትበት ታቦት እንዴት ጣዖት ተብሎ ይጠራል? አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ተብሎ በሥላሴ ስም የሚቀደስበትን ታቦት ባዕድ አምልኮ ለማለት መድፈር እንዴት ያስደነግጣል፡፡

አንዳንዶች ‹ታቦት ተሰርቆ ተሸጠ› የሚሉ ዜናዎችን በማራገብ ታቦቱ ኃይል የለውም ሊሉን ይሞክራሉ፡፡ እንኳን የክርስቶስ ስም የተጻፈበት ታቦት ቀርቶ ራሱ ክርስቶስ በሠላሳ ብር ተሸጦ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ እየተተፋበት ፣ እየተደበደበ ተጎትቶ ተሰቅሎ የለምን? ክብር ይግባውና ክርስቶስ ኃይል የለውም ሊባል ይችላል? ‹‹ታቦቱን ገልጠን እናሳያለን›› ብለው እየፎከሩ ቤተ ክርስቲያንን ያዋረዱ የሚመስላቸው ፣ በታቦቱ እግዚአብሔርን የምታመልከውን ቤተ ክርስቲያን ታቦት ታመልካለች ብለው ያላለችውን በግድ ብላለች ብለው ድርቅ የሚሉ ሰዎች ስናይ ከማዘን ውጪ ምን እንላለን? ቤተ ክርስቲያን ታቦትን የምትሸፍነው ስለሚፈተትበትና ስለሚሠዋበት የጌታችን ሥጋና ደም ክብር እንጂ ቢገለጥ የምታፍርበት ነገር ኖሮ አይደለም፡፡
ቢገለጥ የሚታየው የመድኃኔዓለም ክርስቶስና የቅዱሳኑ ስም ነው፡፡ ጌታዋ ዕርቃኑን በመሰቀሉ ያላፈረች ቤተ ክርስቲያን ስሙ በተጻፈበት ታቦት አታፍርም! የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ጽድቅና ድኅነታችን በወንጌል ነው ።በወንጌል ሕይወት እየተመላለስን መንፈሳዊ ትውፊታችንን፣ሃይማኖታዊ በዓላቶቻችንን እና የማንነት መገለጫ ቅርሳችንን አጥብቀን ልንይዝ ይገባል።ዛሬ ሰለጠንን የሚሉት ምዕራባውያን ወንጌልን ተረድተናል በሚል የጀመሩት የአምልኮ ነጻነት መንፈሳዊ ትውፊቶቻቸውን ጠራርጎ አጥፍቶ ዛሬ ላይ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ትውልዱን ሥርዓት አልባ አድርገውት መንፈሳዊ መዓዛ ተለይቷቸው በመጨረሻም አብዛኞቹ ቤተ መቅደሶች የሚያመልክባቸው ትውልድ ጠፍቶ ወደ ጭፈራ ቤት፣መጠጥ መሸጫና ቡቲክነት እንደተቀየሩ በአውሮፓና አሜሪካ ላይ ዓይናችን እያየ ነው።ትውልዱም እግዚአብሔር የለም በሚል ፍልስፍና ተጠልፎ ለሰይጣናዊ አምልኮ ተጋልጦ ይገኛል።

ስለዚህ ሁሉን በሩቅ አጥሮ መያዝ ስለሚገባ አባቶቻችን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ያቆዩልንን መንፈሳዊ ክብራችንን፣ሥርዓትና አምልኳችንን ሁሉ ጠንቅቀን ልንጠብቅ ይገባል።ክብራችንን እያቀለልን ወንጌል ገብቶኛል ማለት ፍጹም የተሳሳተ አመለካከትና ፍጻሜው የማያምር ሕይወት ነው።

አንዳንዶች አለቦታው የሚጠቀስ ጥቅስ በመጥቀስ ታቦት ተሽሯል ሲሉም እንሰማለን ።ይህ የሚያሳየው የግለሰቦቹ በዘመንና በትርጉም ተከፍሎ የሚጠናውን መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት አለማጥናታቸውን ነው። ቃሉ እንዲህ የሚል ነው።

" በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። " (ትንቢተ ኤርምያስ 3:16)

ይህንን ቃል በጣም በጥንቃቄ ልናስተውል ይገባል ነብዩ ኤርምያስ በዘመኑ ለነበሩ እስራኤላውያን ይህንን ቃል የተናገረው የሰላም ዘመን መቅረቡን ጦርነትና ስደት ከእነርሱ መራቁን ለማብሰር ነው።እስራኤላውያን በታሪካቸው እንደምናጠናው መከራና ችግር ሲመጣባቸው ታቦቱን አውጡልንና ይዘን እንጓዝ ይሉ ነበር አሁን እንደዚያ የምትጨነቁበት ዘመን አይሆንም ሲላቸው ነው ነብዩ የእግዚአብሔርን የቃልኪዳኑ ታቦት ብለው አይጠሩም ያለው እንጂ ታቦት ጭራሽ አያስፈልግም ለማለት አይደለም። ልብ ካልን ሲጀምር በበዛችሁ ጊዜ በምድር ላይም በረባችሁ ጊዜ ብሎ የሚጀምረው ዘመነ ሰላም እንደ ቀረበላቸው የሚያስረዳ ነው። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እኛ ነን ስለዚህ ታቦት ማለት ማደሪያ ስለሆነ በዚህ ዘመን አያስፈልግም ይላሉ ይህ ጥራዝ ነጥቅነት ነው።

የእኛ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነትና የሥጋወ ደሙ መፈተቻ ታቦት ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም።ነገሮችን በጥንቃቄ ልንመረምርና ክብራችንን መንፈሳዊ እሴቶቻችንን አጥብቀን ልንጠብቅ ለትውልድም ልናስተላልፍ ይገባል። መንፈስ ቅዱስ ለሁላችንም ትሑት ልቡና ያድለን። እባካችሁ ሰዎች ከተሳሳተ አመለካከት እንዲመለሱ ትምህርቱን ለሌሎችም ሼር አድርጉት።

ለበረከት ሁኑ።
መ/ር ታሪኩ አበራ
"የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። "ኤር 3፥16

መ/ ር ታሪኩ አበራ

ሰላም ለሁላችሁ ይሁን አንዳንድ ወገኖች ይህንን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ በመምዘዝ ብቻ ቃሉ የተነገረበትን ምክንያትና ዘመን ባለማስተዋል ታቦት አያስፈልግም፣ ታቦት ተሽሯል እያሉ ራሳቸውን አስተው የእምነትና የሥርዓት ቤት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ሲነቅፋ ይሰማል።አለማስተዋል ነው እንጂ ኤርምያስ 3፥16 ላይ የተቀመጠው ቃል የተነገረው በኤርምያስ ዘመን ለነበሩ ቤተ እስራኤል ነው ።ቃሉ የተነገረበትም ምክንያት የእስራኤል ልጆች ከጣዖት አምልኮ ተመልሰው እግዚአብሔርን ብቻ ቢያመልኩ፣ከአመጽና ከርኩሰት ተለይተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቢመላለሱ ጠላት እንደ ማይነሳባቸው በምድራቸውም ረሀብና ችግር እንደ ማይመጣባቸው የተነገረና እነዚህ መከራዎች ከራቁላቸው ደግሞ የቃልኪዳኑን ታቦት አውጡልንና ወደ ጦርነት እንሂድ ብለው እንዳለፋ ዘመኖቻቸው እንደ ማይሹት የተነገረ ነው እንጂ የታቦትን ክብር ለማናናቅ አይደለም።ሙሉ ቃሉን
በማስተዋል ካነበብነው ሐሳቡ በግልጽ ተቀምጧል።

(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕ. 3)
----------
16፤ በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም።

17፤ በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም።

18፤ በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።"

አንባብያን በጣም አስተውሉ !! እስራኤላውያን በተለያየ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ስንመለከታቸው ካህናትና ሌዋውያኑን ታቦቱን አምጡልን የሚሉት ረሃብ፣በሽታ ፣ጦርነት እና መከራ ሲደርስባቸው እንደ ነበር በግልጽ ተጽፏል። በኤርምያስ ዘመን ግን እግዚአብሔር በእውነተኛው ነቢይ በኩል ያስተላለፈላቸው መልዕክት ከቁጥር 12 ጀምሮ ስናነበው በፍጹም ልባቸው ወደ እግዚአብሔር ቢመለሱ በምድራቸው ላይ ሰላም እንደሚሆንላቸው፣ ምድራቸውም እንደ ምትባረክ ይናገርና እንዲህ ዓይነቱን ሰላምና በረከት ካገኙ ደግሞ ካህናቱን ታቦቱን አውጡልን ብለው በጭንቀት እንደማይሹት ይገልጻል። እስራኤላውያን በመከራቸው ዘመን ከፍልስጥኤም ጋር ለመዋጋት ታቦቱን ተሸክመው እንደሄዱ ሁሉ ከእንግዲህ ግን ጦርነት እንደማይሆንባቸው የተገለጸ ቃል ነው።ይህም በኤርምያስ ዘመን ተፈጽሟል።

ታቦቱንማ ራሱ እግዚአብሔር ክብሩን በሕዝቡ መሐል ይገልጥበት ዘንድ ወዶ ፈቅዶ ለሙሴ ይሰራ ዘንድ ያዘዘው የሕጉ ማደሪያ ነው እንጂ ዛሬ ሰዎች ባለመረዳትና በጥራዝ ነጠቅ እውቀት እንደ ሚናገሩት ታቦት ጣዖት አይደለም።

ታቦትን ጣዖት ብሎ መናገር ይሰራ ዘንድ ያዘዘውን ራሱ እግዚአብሔርን እንደ መስደብ ነው ሎቱ ስብሐት።ዘጸአት 25፥8- 22 ላይ እንዲህ ሲል እግዚአብሔር አዟል ፦

"በመካከላቸውም፡ዐድር፡ዘንድ፡መቅደስ፡ይሥሩልኝ...ከግራር፡እንጨትም፡ታቦትን፡ይሥሩ...የስርየት፡መክደኛውንም፡በታቦቱ፡ላይ፡ታደርገዋለኽ፤እኔም፡የምሰጥኽን፡ምስክር፡በታቦቱ፡ውስጥ፡ታኖረ ዋለኽ።በዚያም፡ከአንተ፡ጋራ፡እገናኛለኹ፤የእስራኤልንም፡ልጆች፡ታዝ፟፡ዘንድ፡የምሰጥኽን፡ነገር፡ዅሉ፥በምስክሩ፡ታቦት፡ላይ፡ባለው፡በኹለት፡ኪሩቤል፡መካከል፥በስርየት፡መክደኛውም፡ላይ፡ኾኜ፡እነጋገርኻለኹ።"

ይህ ከላይ የገለጽኩት እንግዲህ በብሉይ ኪዳን የነበረው የታቦት ዓላማና አገልግሎት ነው።ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ ።እግዚአብሔር በመከራችን ጊዜ ሰላም እንድናገኝ በችግርና በስቃያችን ሰዓት መማጸኛ እንዲሆነን የሰጠን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ነው ።ምክንያቱም እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን የተሻለውን ማዳንና ክብሩን የገለጸው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።ስለዚህ ዛሬ መማጸኛችን በመከራ ሰዓት ይዘን የምናወጣው ጋሻና ክብራችን ኢየሱስ የሚለው ስም ነው።ይህ የከበረ ኃያል ስም ዛሬ በቅዱስ ታቦቱ ላይ ተጽፏል።

ታዲያ አሁን ታቦት ምን ያደርጋል? ቢባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንት ሌላው ዓለም ጣዖት አቁሞ ሲያመልክ ኢትዮጵያውያን ግን በታቦት እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንዲኖሩ አድርጋለችና የማንነት መገለጫ /identity /ስለሆነ አክብራ ይዛ ትውልድ ሁሉ የአባቶቹን ታሪክና መንፈሳዊ ባህሉን እንዲጠብቅ እያደረገች ነው።በታቦቱ ዛሬ ክርስቶስ ከብሮበታል አማናዊ ሥጋውና ደሙ ይፈተትበታል።

የማንነት መገለጫ የሆነ መንፈሳዊ ትውፊትን ይዞ ማቆየት ደግሞ ለትውልድ በጣም ጠቃሚ ነው።ዛሬ ላይ እንደ ምንመለከተው አውሮፓውያንና ሌሎችም ምዕራባውያን ክርስትናን ይዞ መጓዝ ሲከብዳቸውና ከሃይማኖት መስመር ሲወጡ ወደ ጥንቱ ማንነታቸው ማለትም ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ወደነበረው አይደንቲቲያቸው ነው የተመለሱት ።ይኽውም ወደ ሰይጣን አምልኮ፣ወደ ሰዶማዊነት፣ወደ ዘመናዊ ጥንቆላ ወዘተ፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን መንፈሳዊ ትውፊት ይዛ ምድሪቱ ላይ ማቆየቷ ትውልዱን በሃይማኖት ጥላ ሥር ይዞ ለመቆየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪም ዛሬ ታቦት በቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጽፎበት በቅዳሴ ሰዓት ሥጋ ወ ደሙ መፈተቻ ነው እንጂ ታቦቱ ራሱ አምላክ ነው ብለን እያመለክነው አይደለም።ታሪካችንን ትውፊታችንን እምነታችንን ይበልጥ አጠንክረን ልንይዝና ለትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል። ዛሬ ሰለጠንን ያለው ትውልድ ሃይማኖት የለሽና ሰይጣኒዝምን ተከታይ እየሆነ ያለው ይህንን የመሰለ መንፈሳዊ ዕሴት፣የከበረ የእምነት መገለጫ ትውፊት ስለሌለው ነው።

ዛሬ በሃገራችን እንደ አሸን የፈሉ ሐሰተኛ ነቢያትና ፀረ ኦርቶዶክስ የእምነት ድርጅቶች ቅዱስ ታቦቱን ሲነቅፉ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ሲተቹ የሚውሉት በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ስለሌላቸውና መስራቾቻቸው ምዕራባውያን የሚጭኑባቸውን የወደቀ አስተሳሰብ ተሸክመው ስለሚዞሩ ነው ።

አንዳንድ ወፍ ዘራሽ የሆኑ አሳዳጊ የበደላቸው ወጣቶች በየመንደሩ በታቦተ እግዚአብሔር ለመሳለቅ የሚያሳዩት ርካሽ ተግባር በ80 ሚሊየን ኦርቶዶክሳዊ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ለማፌዝ የሚደረግ የትዕቢት ተግባር በመሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እነዚህን ውርጋጦች ልክ ማስገባት ግዴታችሁ ነው። ይህንን ለማስቆም ፓሊስ፣ሲኖዶስ፣ቤተክህነት ይወጣው ብሎ እጅን አጣምሮ መቀመጥ አሳፋሪ ድንዛዜ ነው።

ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኩራት የዓለም ብርሃን ናት።

ለሌሎችም ሼር አድርጉት
† የድንግል ማርያም ዕረፍት †

★ ሼር በማድረግ ሌሎችም እንዲማሩ እናድርግ

በክርስትና ስም ከሚጠሩ ቤተ እምነቶች በተለየ መልኩ፥ “ቀጥተኛ መንገድ” የሚል ትርጉም ያለው የኦርቶዶክስ እምነትን የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያን ለተቀደሰው ሐዋርያዊ ትውፊት (Holy Tradition) ትልቅ ቦታ አላቸው። ቅዱስ ትውፊት የምንለው ከቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ዘመን ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣውን አስተምህሮ እና ሥርዓተ አምልኮ ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስም እኛ ዘመን የደረሰው በዚሁ የተቀደሰ የትውፊት ሰንሰለት ነው። ለዚህም ነው ኦርቶዶክሳውያን አበው፦ “መጽሐፍ ቅዱስ፥ በተቀደሰው የትውፊት ዛፍ ላይ የበቀለ መልካም ፍሬ ነው” የሚሉት።

የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፥ በምድረ ፍልስጥኤም በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን በዓለ ዕረፍት ወፍልሰት ማክበር እንደጀመረች የሚጠቁሙ ታሪካዊ መረጃዎች አሉ። በዚሁ ዘመን “The Dormition and the Assumption of the body of St. Mary into Heaven” በሚል ርእስ ዙሪያ የሚያትቱ ጽሑፎች በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይጻፉ እንደነበር በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከነዚህ ጥናቶች መካከል ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ያተረፈው የሚከተለው መጽሐፍ ነው፦ Stephen Shoemaker, Ancient Traditions of the Virgin Mary’s Dormition and Assumption, Oxford University Press, 2006. በፍልስጥኤም (Palestine) የተጀመረው “በዓለ ዕረፍታ ወፍልሰታ ለማርያም” ቀስ በቀስ ወደ ምዕራቡ ዓለም ደርሶ፥ በ8ኛውና 9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዓለም አቀፋዊ በዓል ለመሆን ችሏል። ይህን በዓል ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያን August 15 ቀን ሲያከብሩት፥ ጥንታዊውን Julian Calendar የምትከተለው ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ነሐሴ 16 (August 22) ቀን በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች።

★ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ ★

ቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር” "የእግዚአብሔር፡ከተማ፡ሆይ፥ባንቺ፡የተከበረ፡ነገር፡ይባላል።" መዝ.፹፮፥፫/86፥3 እንዳለ ሊቃውንት በትርጓሜ እግዚአብሔር ማህጸንሽን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የኖረብሽ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው የተደረገው ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው እንዳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ሆና ማረፏ ይደንቃል። ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል።

★ ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር ★

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ በነገረ ማርያም አበው እንደሚያስረዱት ዕረፍቷ በጥር ፳፩ /21 እሑድ ነው ። አባቶቻችን በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም ሲተረጉሙ የእረፍቷን ነገር እንዲህ ብለው ይተርካሉ።

የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ በእሑድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት። ቅድስት ሥጋዋን ከቅድስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት፣ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት። ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር አሳርፉ አላቸው። ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ ቀድሞ ልጇን ተነሳ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሱ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። መልአክ መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት አግብቶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስን እንደምን ሆነች አሉት ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች አላቸው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ ሁለት ሱባዔ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንና አስነሺነት “ከመ ትንሳኤ ወልዳ” እንደ ልጇ ተነሥታለች። ቅዱስ ቶማስ አልነበረም ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ዛሬም ደግሞ ያንችን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁን ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ከሀዘኑ የተነሳ ሊወድቅ ወደደ እመቤታችንም አይዞህ አትዘን እሊያ ትንሳኤየን ዕርገቴን አላዩም አንተ አይተሃል ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሂዶ የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ አላቸው አግችተን ቀበርናት አሉት ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተው ይህ ነገር አይመስለኝም አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ እንጅ ልማድህ ነው አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሩ ሂዶ ቢከፍተው አጣት ደንግጦ ቆመ ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብየ እንጅ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች አላቸው የያዘውንም ሰበን ሰጣቸው ለበረከትም ተካፍለውታል። በዓመቱ ሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ጾም ጀመሩ በ፲፮ 16 ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን ዘይትራድኦ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ቤተክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሯን በልቦናችን ጣዕሟን በከንፈራችን ታሳድርብን ።

ለሌሎችም አጋሩት
2025/02/05 10:34:10
Back to Top
HTML Embed Code: