Telegram Web
ነፍስ ይማር  !!

… መነሻቸውን ከጂቡቱ ወደብ አድርገው በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በጀልባ ተሳፍረው ጉዞ እንደጀመሩ የተነገረላቸው ኢትዮጵያውያን የተሳፈሩበት ጀልባ በመስጠሟ ምክንያት በአንድ ጊዜ በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩት 300 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሰጥመው መሞታቸው ተነግሯል።

… የመን በዕድል የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በየመን የሚጠብቃቸው እስር፣ እንግልት፣ ራብ እና ስቃይ ነው። የመን ጦርነት ላይ ናት። በጦርነቱ መሃል ከሳዑዲ በሚጣሉ ቦንቦች ተቃጥለው የሚሞቱትም የትየለሌ ናቸው። በራብ የሚሞቱትም የትየለሌ ናቸው።

… በእሳቱ… በዐውሎና በወጀቡ… የበረሃውን እሳተ ገሞራ የመሰለ አሰቃቂ የሞት መንገድ አልፈው እንደ ዕድል ሆኖ ሳዑዲ የሚገቡትም ቢሆን በሳዑዲ የሚገጥማቸው እና የሚጠብቃቸውም አማሰለ ሲኦል ወደሚሆን ዘብጥያ፣ ወኅኒ ቤት መወርወር፣ ጀርባቸው እስኪላጥ መደብደብ እና መገረፍ፣ ነው።

… ይሄ ሁሉ ሞት ከፊቱ ተደቅኖ ኢትዮጵያውያን ግን ወደሞት ከመትመም ወደ ኋላ ሲመለሱ አይታይም። በሃገር ውስጥ ስደት ሶርያን የበለጥን እኛ ይህ የሞት ዜና እየተሰማ እንኳ ሺዎች ወደ ሶማሊ፣ ወደ ኬንያ፣ ወደ ሱዳን ሊቢያ፣ ወደ ጂቡቲ፣ በመሰደድ የበረሃ ጉዞ ላይ ናቸው። የ300 ኢትዮጵያውያንን በባህር ላይ መስመጥና መሞት የሰሙ ቀሪ ስደተኞችም ሌላ ጀልባ በመጠባበቅ እና ወደ የመን ለመሰደድ በተስፋ የጅቡቲ ወደብ ላይ ተቀምጠው ስደቱን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የውኃ ላይ ሞት ደግሞ እጅግ አስጨናቂ ነው።

… ነፍስ ይማር … በሰላም እረፉ።
"ሰኔ ፆም ሰኞ ይጀምራል"

ጾም መድኃኒት ናት አወሰዷን በትክክል ያላወቁባት ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒት የሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱና በምን ያህል መጠን እንደምትወሰድ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው አከባቢና የአየር ኹናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚኼዱና የማይኼዱ ምግቦችን እንዲሁም ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ሌሎች ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብቶ የማይወስዳት ሰው ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ታመዝንበታለች፡፡ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ዘሥጋ መድኃኒት እንዲያሽለን ስንፈልግ በጥንቃቄ ልንወስደው ያስፈልጋል፤ የነፍሳችንን ደዌና በአእምሮአችን ውስጥ ያሉ ቁስሎችን ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ የበለጠ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/ ማለት ሐዋርያቶች የጾሙት ጾም ማለት ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ለስብከት ከመሰማራታቸው በፊት አገልግሎታቸው የተሳካ ይሆን ዘንድ ፈጣሪያቸውን በጾም በጸሎት ተወስነው የጠየቁበት ጾም ነው። /ግብረ ሐዋ. 2፥1፣ 27፥9/
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ይህንን ጾም ሐዋርያት እንደሚፆሙት ተናግሮ ነበር። ️/ማቴ. 9፥14️/ ከዚህ በኋላ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ እንጾማለን ደቀመዛሙርትህ ስለምን አይጾሙም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላቸው “የሙሸራው ሚዜዎች ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል ያን ጊዜ ይፆማሉ።” በማለት የፆምን አስፈላጊነት አስረግጦ አስተምሯል። ጾም ባያስፈልግ ኖሮ ለደቀመዛሙርቱ እኔ ጾምኩላቸው ብሎ በተናገረ ነበር። መወሰድ የተባለው ደግሞ ዕርገቱ ነው።

ካረገ በኋላ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ጾምን ጀምረዋል ይህም ጾም ሁል ጊዜ በየዓመቱ ከበዓለ ሃምሳ ማግስት ጀምሮ ይጾማል። የፍስኩም ዕለት የማይለወጥ ሲሆን ሁል ጊዜ ርዕሰ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ብርሃነ ዓለምና ማኀቶተ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ በሚታሰቡበት ሐምሌ 5 ዕለት ይሆናል። የጾሙ ቀን ግን ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል። ሲያጥር 15 ቀን ይሆናል። ሲረዝምም ደግሞ 49 ቀን ይሆናል። ይህም ማለት የጾሙ መባቻ ከግንቦት 16 እስከ ሰኔ 20 ባሉት ቀናት ውስጥ ይለያያል። የጾሙ መባቻ ግንቦት 16 ከሆነ የጾሙ ዕለታት ብዛት 49፣ ሰኔ 20 ከሆነ የጾሙ ዕለታት 15 ይሆናሉ። በዚህ ዓመት ደግሞ መባቻው ሰኔ 14 ቀን ስለሆነ የጾሙ ዕለታት 21 /ሦስት ሳምንታት/ ይሆናሉ ማለት ነው።
በወርኃ ሰኔ ስለሚጾምም የሰኔ ጾም ተባለ እኔ ሳለሁ አይጾሙም ማለቱ እርሱ ካልሞተና ካላረገ መንፈስ ቅዱስም ካልተሰጣቸው በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ሆኖ ሰይጣንን ድል መንሳት ስለማይችሉ ይህንን አለ። ይህንንም አባባል ሲያብራራው “ባረጀ ልብስ ልብስ ላይ አዲስ ቁራጭ/እራፊ/ የሚለጥፍ የለም ምክንያቱም የአዲስ ቁራጭ ልብስ ኃይል ቀዳዳውን ያሰፋዋልና አዲሱንም ወይን ባረጀ አቁማዳ /ረዋት የሚጨምር የለም ቢጨምሩት ግን ጋኑ ይፈነዳል ወይም ያፈሳል።

በአዲስ ረዋት ቢጨምሩት ግን ምንም የሚያመጣው ችግር የለም።”/ማቴ.9፥16-17/ በማለት ምክንያቱን በምሳሌ አስተምሯል። ሐዋርያትም በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት መጾም ስለማይገባቸው መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን መጾም እንዳለባቸው ሲነግራቸው ነው። አንድም የኦሪቱ የጾም ሥርዓት ከሐዲሱ የጾም ሥርዓት የተለየ መሆኑን ሊያስረዳቸው ስለፈለገ ነው።
ይህንን ጾም የምንጾመው ሐዋርያት ጾመው ጸልየው ድል ያደረጉትን ዓለም እኛም የምናሸንፍበትን ኃይል እንዲሰጠን ፈጣሪያችንን አምላከ ሐዋርያት ተለመነን እያልን ለመማፀን ነው። በተጨማሪም ቅዱሳን ሐዋርያትን አርአያ አድርገን የበረከታቸው ተካፋይ እንሆን ዘንድ እንጾማለን። ጾሙም በሥርዓተ ጾም መሰረት እንደ ሁሉም አጽዋማት እስከ ዘጠኝ ሰዓት መጾም አለበት። ይህንን የሐዋርያት ጾም አንዳንድ ሰዎች ሐዋርያት ጾሙት ሲባል የቄስ ጾም ነው በማለት ላለመጾም ምክንያት ሲደረድሩ ታያላችሁ አስቀድመን እንደተናገርነው የቄስ ጾም የሚባል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ የለንም። አባቶቻችን ሠልስቱ ምእትም ይህን ጾም እንጾመው ዘንድ ሥርዐት ሠርተዋል።
ረቡዕ እና አርብ የምንጾመው ጾመ ድኀነት /የመዳን ጾም/ ይባላል። ረቡዕ የምንጾመው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምክረ ሞቱ የተፈፀመበት ዕለት በመሆኑ እንጾመዋለን። /ማቴ 26፥1/

አርብ ደግሞ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ሲፈፀም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የገባለትን ቃልኪዳን ለመፈፀም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል የተቀበለበት፣ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በዘጠኝ ሰዓት ሲኦል ወድቀው በእግረ አጋንንት ተቀጥቅጠው ለዘመናት ሲሰቃዩ የነበሩ ነፍሳት የነበሩትን ነፍሳት በደሙ ፈዋሽነት ያወጣበት ዕለትና ወደ መንግስተ ሰማያት ያሸጋገረበት ዕለት በመሆኑ የክርስቶስን ውለታ የማትዘነጋ ቤተክርስቲያን ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ የመከራው ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ እንዲጾሙ አዛለች። ጾመ ድኀነት ብለንም እንጾመዋለን። የምንጾመውም እስከ ዘጠኝ ሰዓት መሆን አለበት ምክንያቱም ነፍሳት ከሲኦል የወጡት በዘጠኝ ሰዓት በመሆኑ ያንን ለማሰብ ነው።

ጾሙ የሚጀመረው ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/ በገባ በሶስተኛው ቀን ማለትም ጾመ ሐዋርያት ሰኞ ገብቶ ጾመ ድኀነት ደግሞ ረቡዕ ይጀምራል። ሁሌም በየዓመቱ ሁለቱ አጽዋማት ተከታትለው ይገባሉ። በበዓለ ሃምሳና በአጋጣሚ የልደትና የጥምቀት በዓል ረቡዕና አርብ ካልዋለ በስተቀር ዓመቱን ሙሉ ጾመ ድኀነት ይጾማል። በአጋጣሚ ግን የገና በዓል ወይም የጥምቀት በዓል ረቡዕ ወይም አርብ ቢውል ሁለቱ ዕለታት የፍስክ ዕለታት ሆነው ያልፋሉ። ፍትሃ ነገሥቱም ስለሚያዝ በአንቀጽ 15 ቁ.565 “ዳግመኛ በየሳምንቱ ሁሌ ረቡዕና አርብ መጾም ነው፤ የጥምቀት የገና በዓል የተባበሩባቸው ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይፁሟቸው” በማለት ያዛል። አባቶቻችን ሠለስቱ ምእትም “ከበዓለ ኅምሳ በስተቀር የረቡዕ እና የአርብ ጾም በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን” ብለው አስተምረውናል።
ለጾም የበረታ ሰውነት፣ ለጸሎት የሚተጋ ልብ፣ በጎ የሚያደርግ ሕሊና፣ መልካም የሚያይ ዓይን፣ በደልን የሚረሳ አዕምሮ፣ ይቅርታ የሚጠይቅ አንደበት፣ ለተቸገሩ የሚመጸውት እጅ፣ እንዲኖረን ቅዱስ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን።
እንኳን ለሊቀ መላእክት፡ አኃዜ መንጦላዕት፣
መልአከ ኃይል ፡ ሰዳዴ ሳጥናኤል ፣
መዝገበ ርህራሄ ወሳህል ፡ መልአከ ምክሩ ለልዑል…

ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ።

🍁 ሚካኤል ፩ እምነ መላእክት ቅዱሳን እስመ በዲበ ሠናይቱ ለሰብእ ተአዛዚ ዲበ ሕዝብ ።

⇨ ለሰው ባደረገው በጎነት ላይ ለሕዝቡ ታዛኝ ነውና ከነበሩ ከመላእክት አንዱ ሚካኤል ነው።

⇨ Michael, one of the Holy Angels, namely the one put in charge of the best part of humankind, in charge of the nation.

. 🌴 [ሔኖ ፮፥፭]

🍁 ወውእቱ ቀዳማዊ ርኁቀ መዓት ወብዙኀ ምሕረት ሚካኤል ውእቱ

⇨ እሱም የመጀመርያው ይቅር የሚል ከመዓትም የራቀ ቅዱስ ሚካኤል ነው"

⇨ This first is Michael, the merciful and long-suffering without an urge to harm.

. 🌴 [ሔኖ ፲፥፲፪]

“ለእውነት ነገር የሚላክ ሚካኤልም በውነት አመስጋኝ ነው እውቀቱን የሚገልጥልኝ ጻድቃን እስከ ገቡባቸው ድረስ የእውነት በሮቹን የሚከፍትልኝ እሱ ነው።” [ተረፈ ባሮክ ፭፥፴፭]
"ሰኔ ፳ ሕንጸታ ቤተክርስቲያን "
በዚሕች ቀን በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአምላክ እናት ስም ታንጻለች።
ከመጀመርያው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን "ሑሩ ወመሐሩ ኩሎ አሕዛበ" (አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ) ማቴ. 28:19 ባላቸው ቃል መሠረት ዓለምን በወንጌል ያርሷት ዘንድ በዕጣ ተካፍለዋታል::

የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና (ዮሐ. 6:56) አበው ሐዋርያት ቁርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው ያቆርቡ ነበር::

በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲሕ ይከናወን ነበር:: ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኩራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር:: እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቁጥር እጅጉን በዛ::

በተለይ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ:: በዚሕ ምክንያት መምሕራን ሕዝቡን "ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?" ቢሏቸው "እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት እንደሆን የለን" ሲሉ መለሱላቸው::

ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ጳውሎስና በርናባስ ደረሰ:: ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች "ለምን አናንጽም" ብለው ነበር:: ቅዱስ ጳውሎስ ግን "ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም" አለ:: (ለዚሕ ነው ዛሬም ሊቀ ጳጳስ ካልፈቀደ ቤተ ክርስቲያን የማይታነጸው::)

ከዚያ ቅዱሳን ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ጴጥሮስ አስረዱ:: ሊቀ ሐዋርያቱም "የጌታችን ፈቃዱ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባዔ እንግባ" ብሎ አዋጅ ነገረ::

በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ልብ ሱባዔ ገቡ። በሱባዔአቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ::

ሁሉንም ሐዋርያት በደመና ጭኖ ፊልጵስዩስ አደረሳቸው:: ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ መሬት ላይም "ቤተ ክርስቲያንን በእናቴ ስም አንጹ" ብሎ አዘዛቸው:: ለቅዱስ ጴጥሮስም ሦስት ዓለቶችን ሰጠው::

እነዚያን መሬት ላይ ተክሎ ጌታችን ቆሞለት ሐዋርያቱ እየተራዱት ግርምት የምትሆን ሦስት ክፍል ያላትን የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን በ52 ዓ/ም በዚህች ቀን አንጿል::

ቤተ ክርስቲያኗን ነገ ጌታችን ቀደሳት የምንል ነንና ይቆየን::
አምላካችን የድንግል እናቱን ፍቅር : የተቀደሰች ቤቱን ጸጋ : የቡሩካን ሐዋርያቱን በረከት ያሳድርብን::

ሰኔ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ (ዕረፍቱ)

ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
4.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
5.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
6.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

"በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::"
(፪ቆሮ. ፲፩፥፳፫-፳፰)

ዜና ቅዱሳን (ታሪክ)
"ሰኔ ፳ እና ፳፩"
ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው ህንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል።

የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የታነጸው በዛሬዋ ቀን ነው አናጺውም እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው።

ጴጥሮስ፤ ዮሐንስ በርናባስና ሌሎችም ሐዋርያት በፊልጰስዩስ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ 3 ድንጋዮችን አንስቶ ጎተታቸው እንደ ሰም ተለጠጡ እንደ ግድግዳም ሆኑ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ እየሩሳሌም አምሳያ አድረጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፤ ዳግመኛ በበነጋው ሰኔ 21 ቀን እመቤታችንን እና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል ቅዳሴ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቆረባቸው ፍጹም ደስታም ሆነ።

ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታ እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የነሶሎሞን ቤተ መቅደስ የአይሁድ ምኩራብ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ስርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፤ ታዲያ ሐዋርያት የት ነበር ህዝቡን የሚያጠምቁት የሚያቆርቡት ካሉ በየሰው ቤት ነበር።

ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ታላቁ ነብይ ኤልሳዕ አረፈ። ይህ ነብይ በ 12 ጥማድ በሬ ሲያርስ ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ ተከተለኝ አለው ምንም ሳያቅማማ ሀብት ንብረቱን ትቶ ተከተለው፤ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከማረጉ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ ይለዋል ባንተ ላይ ያደረ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደርቢኝ ይለዋል፤ እንደ ቃሉ ሆነለት ተደረገለት፤ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሳ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነስቷል፤ ኤልያስ አንድ ጊዜ ባህር ሲከፍል ኤልሳዕ ሁለት ጊዜ ባህር ከፍሏል።

የእምቤታችንን የኤልሳዕ ጋን ይላታል ኤልሳ የመረረውን ውኃ እንዳጣፈጠ እመቤታችንም ይህን መራራ ዓለም ጌታን በመውለዷ አጣፍጣዋለች፤ የዚህ ነብይ ድንቅ ታሪኩ 2ኛ ነገስት ላይ በስፋት ተጽፏል ሰኔ 20 ቀን እረፍቱ ነው ቤተክርስቲያን የዛሬውን ቀን እመቤታችንን እና ነብዩን አስባ ትውላለች።

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን የእመቤታችን ምልጃና ረዳትነት አይለየን!
ክፉን በመልካም እንዴት መቃወም ይቻላል?

የምታስፈራዋን የፍርድ ቀን እንባህን በማፍሰስ አስብ። ተስፋህ በእርሱ ዘንድ የቀና የጸና ይሆን ዘንድ የፈጣሪህን መልካም ተስፋውን ስበክና መስክር።
መቀባጠር የሚያበዙትን በአርምሞ ጸጥ አርጋቸው።ሐሜተኞችን በትዕግሥትህ ገሥጻቸው እንቅልፋሞችን በትጋትህ አንቃቸው ኃጥኣንን አጽናናቸው የተዋረዱትን ራስህን በማዋረድ በትህትና አረጋጋቸው ገንዘብ በማጠራቀም የበለጸጉትን ናቃቸው። ከዓለም የተለየህ ሁን የዓለም ፍቅሯና ትርፏ ፍርድን እንዲያመጣ እወቅ። ከዚህች ዓለም ትሸሽ ዘንድ ፍጠን ተሽቀዳድም። ነፍስህንም ከመቀባጠር ጥቅም ከሌለው ከንቱ ጨዋታና ዋዛ ፈዛዛ አሳርፋት። ይልቁንም የተሰወረውን ለሚያውቅ እግዚአብሔር ምስጋና አቅርብ እንጅ ድኽነትን እንደ ወርቅ ውደዳት።
(መጽሐፈ ወግሪስ ገጽ 34)
ዝክረ ሰማዕታት በሻሸመኔ ፩ኛ ዓመት

"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም።
ወከዓው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር
ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት።
ተሣሃለነ በከመ ዕበየ ሳህልከ።
ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤
ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ።
ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ።
እንደ ይቅርታህ ብዛት ይቅር በለን።"
(የሐሙስ ውዳሴ ማርያም)

በኦሮሚያ የተጨፈጨፉ ሰማዕታት አንደኛ ዓመት ሲታሰብ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡
“ተወዳጆች ሆይ!
ስለ ሰማዕታቱ ብቻ የምትሰሙ አትሁኑ፡፡ እነርሱን ለመምሰልም ተጣጣሩ እንጂ፡፡ ለጊዜው ብቻ የምታደንቋቸው አትሁኑ፡፡ ወደ ቤታችሁ ብቻ ሳይሆን ወደ ልቡናችሁ ውሳጤም ዘልቀው እንዲገቡ አድርጉ፡፡ ዘወትር አስቧቸው፡፡ በልቡናችኁ ጓዳ እንዲገቡ አድርጓቸው፡፡ እናንተን ትተው ይሔዱ ዘንድ አትፍቀዱላቸው፡፡ ይኽን ያደረጋችሁ እንደሆነ ዘወትር እያያችኋቸው ትበረታላችሁ፡፡ በእምነት ትጸናላችሁ፡፡ የለበሱትን የጽድቅ ጥሩር፣ የያዙትን ምግባረ ወንጌል፣ የእምነት ጋሻ፣ የመዳን ራስ ቁር፣ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ እየተመለከታችሁ ትበረታላችሁ፡፡”

በረከታቸው ይድረሰን!
ደብተራነት ለዘልአለም ይኑር!
2025/07/14 03:12:04
Back to Top
HTML Embed Code: