Telegram Web
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
1• ፍቅር 1.1• ፍቅር ምንድነው? ክፍል - ፩   ✞ የሰው መልኩ ፍቅር ነው "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።" (ኦሪት ዘፍጥረት 2፥7)     አምላክ ፍጥረታትን ሁሉ በስድስት ቀን ተከታታይነት ፈጥሮ ሥራውን ካበቃ በኋላ፤ በመጨረሻው ላይ ከፈጠራቸው ፍጡራን ሁሉ ለየት ያለ አንድ ፍጡርን…
1• ፍቅር

    1.2• ፍቅር ካለ ምን አለ?

ክፍል - ፪

✞ ፍቅር ወደ እምነት፥ እምነት ወደ ተስፋ፥ ተስፋ ወደ ምሪት

   የሰው ልጅ የማንነቱ መልክ የሆነውን ፍቅር በተቀደሱ መልካም ነገሮች ሁሉ ውስጥ እየፈለገና እየገለጠ በዘመኑ ላይ መመላለስ ሲጀምር፤ የባሕሪይው መዝገብ የሆነው የአዳም ቤተሰብ በሥጋ ምኞት የተነሣ በመውደቁ ምክንያት፤ ከውጪኛው የሥጋ አካሉ ላይ ተገፍፎ የተሸጎረበትን የነፍስ ጠባይና ጸጋ በተጨባጭ በማሳየት በሙሉ የተፈጥሮ ስብእና ለመገኘት የሚችልበትን ዕድል እያሳደገ እያሳደገ ይሄዳል፡፡

    ይሄ የነፍስ አካልና መንፈሳዊ ጸጋ የሆነው ፍቅር ከኛ ጋር በሚሆንበት ጊዜ፤ በእርሱ መኖር መሠረትነት ቀጥለው የሚገነቡ ሌሎች ረቂቅ ባሕሪያት ከውስጣችን መፍለቅ ይጀምራሉ፡፡ በ1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፥13 ላይ "እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው" የሚለውን የመጽሐፍ ቃል በዚህ አንቀጽ መግቢያ ላይ ላስቀመጥነው ጭብጥ ማሳያ ሆኖ አሳባችንን እንዲያብራራልን እስቲ በሚከተለው መልኩ እንዳስሰው፡፡

           ✞ ፍቅር ወደ እምነት

   በቆርንቶሱ ቃል መዝጊያ ላይ "ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው" የሚለው ጽሕፈት የሚያስረዳው፤ ፍቅር "ከእነዚህም" የተባሉትን "እምነትንና ተስፋን" ያስገኘ ታላቅ መነሻና መድረሻ ኃይል መሆኑን ነው፡፡

   ልዑል እግዚአብሔር "አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ" በማለት ጥንት ስሌለው ቀዳማዊነቱና ፍጻሜ ስለማይገኝለት ደኀራዊነቱ አሳውቆናል፡፡ አስቀድመን ደግሞ እግዚአብሔር በራሱ ፍቅር ነው ስላልን፤ እንኪያስ "ፍቅር አልፋ ነው፥ ፍቅር ዖሜጋ ነው" ብለን ሁለቱን ጥቅሶች አሰናስለን ብናነባቸው አንሳሳትም፡፡

    ይህም ከሆነ ዘንድ፤ እምነትን ያስገኘው መጀመሪያ ወይንም ፊተኛ ፍቅር ነው የሚለው ገለጻ የታመነ እውነት ነው ማለት ነው፡፡

   በእርግጥም እኛ ሰዎች አንድን አካል ወደ ማመን እየተጠጋን የምንሄደው፤ ለዛ አንድ አካል ባለን የመወደድ ቅርበት ልክ ነው፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ሰው ሊያስብል በሚያስደፍር ደረጃ፤ ወላጆቹን፣ አሳዳጊዎቹን፣ የቤተሰብ አባላቱንና የልብ ወዳጆቹን ክብደቱ በሚያለያይ መጠነ ሚዛን ያምናል፡፡ የዚህ የእምነቱ መግቢያ በር የሆነው መግፍኤ ደግሞ እነዚያን ሰዎች መውደዱ ነው፡፡

   ለኛ ዘመን ትውልድ የሚስማማ አንድ ሌላ ቀላል ምሳሌ እንጨምር፡፡ ፍቅረኛሞች አንድ ላይ በመቆየት ሂደት ውስጥ ብዙ የኑሮ መስመሮችን እየተጋሩ የመዋደዳቸው ጉልበት እየጠነከረ ሲመጣ፤ በዛውም የመተማመናቸው አቅምም ይጎለብታል፡፡ ከተለያየ ቤተሰብ ተወልደው፥ በጊዜ መካከል ተገናኝተው፥ ከመተዋወቅ በተነሣው ሁኔታ ጀምሮ እየበረታ የሚሄደውን እምነት የሚጨምርላቸው ብቸኛው መተሳሰሪያ አሪቡን ፍቅር ነው፡፡ 
  
   ፍቅር እምነት የሚባለውን ረቂቅ ጠባይ የሚወልድ ረቂቅ ማኀፀን ነው፡፡ ብቻም ሳይሆን ፍቅር እምነትን ተንከባክቦ የሚያሳድግ ጠባቂ ሞግዚት ነው፡፡ እምነት የእርጅና ዘመንም በገጠመው ጊዜ ድጋፍ ሆኖ የሚያቆየው መቋሚያ ፍቅር ነው፡፡ አይበለውና እምነት ዕድሜው ተጠናቆ ከመቃብር በታች ቢውል እንኳ፤ ፍቅር ዳግም ነፍስ የሚዘራበት ትንሣኤው ነው፡፡ ፍቅር የማይታየውን እንደሚታይ፣ ያልተሰማውን እንደተሰማ፣ ያልተዳሰሰውን እንደተዳሰሰ፣ ያልተረጋገጠውን እንደተረጋገጠ አድርገን በውስጣችን እንድንቀበል የእርግጠኝነት ማኅተም የሚመታ መንፈሳዊ ዋስትና ነው፡፡

   የነገር ሁሉ መነሻ ፍቅር ነውና፥ እምነት ከፍቅር ሲወለድ እውነተኛ እናቱን አገኝቶ ሳይቸገር ያድጋል፡፡ ከምክንያት የተወለደ እምነት ግን በክፉ እንጀራ እናት እንደሚያድግ ልጅ በችግር እየተነጫነጨና ለመሸሽም ሰበብ እየፈለገ ጊዜውን ያሳልፋል፡፡

   የሰው ልጆች ከአምላክ ፍቅር የጀመረ እምነት በልባችን እንዳይቋጠር፤ ክፉው መንፈስ ከሆነለት በምንም ምክንያት ይሁን ብቻ በእምነት ጎዳና ላይ አለማራመድን ቀዳሚ ተልዕኮው አድርጎ ሲንቀሳቀስ፤ ካልሆነለት ግን በፍቅር አንጻር በመቆም የፍቅርን ቦታ የሚተካ አንዳች ምክንያት ለእምነት ጉዞአችን መነሻና መድረሻ እንዲሆነን ይፋለማል፡፡ (ሐሳዊ መሲሕ የተሰኘውን የዲያቢሎስ መገለጥ በዓለም ሥርዓት እንዴት እንደሚከናወን እዚህ አንቀጽ ላይ ከተጠቀሰው አሳብ ጋር አስተያየተን እግረ መንገዳችንን ማገናዘብ እንችላለን፡፡ ሐሳዊ-መሲሕ ማለት በእውነተኛው መሲሕ አንጻር በመቆም በእውነተኛው መሲሕ ስም ሐሰትን የሚሠራ ማለት ነው፡፡ ይህንን በዓለም ሥርዓት በኩል ብናየው፤ በፍቅር ስም የሚዘራ ጥላቻ፣ በእምነት ስም መንፈሳዊነትን የሚዋጋ፣ ተስፋ የሚሰጥ መስሎ ተስፋ የሚያስቆርጥ ማንኛውም ንድፈ አሳብ፣ ርዕዮት፣ ፍልስፍና፣ መርህ፣ ፖሊሲ ፣ ሕግ፣ ወዘተ... ይሆናል፡፡)

    የዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊ መልእክት ያለው እዚህ ጋር ነውና፤ እስቲ አንድ አፍታ ባለንበት ስፍራ ላይ ጥሞና ወስደን በጥልቀት እናሰላስል፡፡ "ምን አስበን ነው ሃይማኖታዊ ኑሮ ውስጥ የገባነው? ምን ሰምተን ነው ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት ገመድ የተያያዘ ሕይወት እንዲኖረን የፈቀድነው? ምን ፈልገን ነው መለኮታዊ ኃይልን ለማግኘት የመረጥነው?"

    እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች ራሳችንን ለመጠየቅ እንጀምር፡፡ ስለ ነፍስም ታማኝ ሆነን በሚገባ እንመልሳቸው፡፡ ምክንያቱም እርግጥ የሆነ ምላሽን ከሰጠንበት ስፍራ ላይ፤ እስከ ዕድሜ ዘመናችን ለሚዘልቅ ሃይማኖታዊ ጉዞ ስንቅ የሚሆንን እውነት እንቋጥራለን፡፡ (ከአልፋው የጀመረ ሰው፥ በዖሜጋው እንዴት እንደሚጨርስ ማወቅ ይችላል!)

   ዲያቢሎስ እዚህ መነሻና መድረሻ ቦታዎች ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ያሰኘን ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ፍቅር በተወለደ እምነት ከሆነ መንፈሳዊ ሕይወት የጀመርነው፤ ወደፊት የሚቀጥሉት ሰማያዊ እርምጃዎቻችን መሰናክልን የሚሻገሩ፣ ዕንቅፋትን የሚቋቋሙ፣ ጉድጓድን የሚለዩ፣ በምሪት የታገዙና ቢደክሙም የሚታደሱ እንደሆነ ጠላት አበጠርጥሮ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት የምንሳብበት ገመድ ፍቅር ሳይሆን ምክንያት እንዲሆን የአስተሳሰባችንን መዘወር ለመቆጣጠር የመጨረሻውን ሙጣጭ አቅም እየተጠቀመ ይታገላል፡፡

   አብዛኛው ቤተሰብ ልጆቹን በእግዚአብሔር ፍቅር እያነጸ አላሳደግም፡፡ መንፈሳዊ ምግባሮችንም እንደ ውዴታ ግዴታ አድርጎ ሲተገብራቸው የሚገኘው በጥሩው ሥጋዊ ምክንያት ላይ ለበዓላት፤ በመጥፎው ሥጋዊ ምክንያት ደግሞ ችግር ሲመጣ፣ መፍትሔ ሲጠፋና አቅም ሲያጥር ነው፡፡ በዚህ የአኗኗር ሁኔታ ላይ ዕድገታቸውን አሳልፈው የመጡት ልጆች፤ እግዚአብሔር በባሕሪዩ ፍቅር እንደሆነ ሳይገነዘቡ ይቆዩና፤ እነርሱም እንደ ወላጆቻቸው የእምነት ሕይወት ማለት የነፍስ ማንነት አንድ አካል ሳይሆን በሰሞን ምክንያቶች መካከል የሚ'ኖር የጊዜ ስሌት ያደርጉታል፡፡ ይሄ ለዘመናት ተንከባሎ የመጣ የቤተሰብ ልማድ፤ ዲያቢሎስ ፍቅር የሚያስገኘውን የእምነት ኃይል ልጆች እንዳያስተውሉ ካለማወቅ ጀርባ ተደበቆ አለማወቅን እንዲያበለጽግ ምሽግ አበጀለት፡፡
   ፍቅር ሲኖር እምነትም ይኖረናል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የወሰንንበት ምክንያት ፍቅር ከሆነ፤ ከእርሱ ጋር በእምነት ሰንሰለት ለመያያዝ አንቸገርም፡፡ አምላክን እንደ አባት አቅርቦ የመውደድ ዕድል በሐዲስ ኪዳን ተሰጥቶአል፡፡ "አባታችን ሆይ" የሚል ጸሎት የመጣውም የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን ሥልጣን በዳግም መወለድ በኩል ስለተካፈልን ነው፡፡ እናስ አጠገባችን አብረው እንዳሉ ሰዎቻችን [እንኳ] እግዚአብሔርን አቅርበን ስንወድድ፤ ከዚህ የፍቅር ነጥብ ወዲህ ባለው መንፈሳዊ ሕይወት ከመለኮታዊ ኃይል ጋር በእምነት ተናብቦ መቀጠል አስቸጋሪ አይሆንብንም፡፡

                 ✞ እምነት ወደ ተስፋ

    እምነት በፍቅር ከተወለደ በኋላ፤ እርሱ ደግሞ ጊዜው ሲደርስ የሚወልደው ሁለተኛ ልጅ ተስፋ ይባላል፡፡ ፍቅር የተስፋ አያት ነው፡፡

   ስለወደድን ስናምን፥ ስላመንን ደግሞ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ኋላሳ የማያምን ሰው ምንን ተስፋ ሊያደርግ ይቻለዋል?" ("እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።"
(ወደ ዕብራውያን 11፥1))

    ተስፋ ነገን በዛሬ ውስጥ የሚያስኖር የእምነት ውጤት ነው፡፡ ተስፋ በዋሻ ጫፍ ያለውን ብርሃን ሳያዩ በጨለማ የመጓዝ ብርታት ነው፡፡ ተስፋ የሚመጣውን የቃልኪዳን መገለጥ በሐሴት የሚያስጠብቅ የሕልውና ስንቅ ነው፡፡ ተስፋ የኑሮ ወዝ ደርቆ እንዳይጠወልግ ልምላሜ የሚሰጥ የነፍስ ውኃ ነው፡፡ ተስፋ አድካሚና አሰልቺ በሆነ የጊዜ ምዕራፍ ላይ ስንደርስ ቀጣዮቹን ገጾች የሚያስገለብጥ መንፈሳዊ ጉልበት ነው፡፡ ተስፋ የመከራን እስራት የሚያሳጥር በጠባይ ወረቀታችን ላይ የተጻፈ አለኝታ ነው፡፡

    ተስፋ የሚባለው ጉዳይ በባሕሪያችን ላይ የተቀረጸው ከዔድን ገነት ስንወጣ ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ አንድ ቀን እየሆኑ የተዘረዘሩት ሰድስቱ ዕለታት ፍጥረታትን ሁሉ ሲያስገኙ፤ የመጨረሻዋ ሰባተኛዋ ቀን ዕረፍት ሆናለች፡፡ በአዳም አቆጣጠር በኩል አዳም 6ተኛዋን የተፈጠረባት የቀን ሥርዓት ሳይጨርስ ነው የወደቀው፡፡ ማለትም 1000 ዓመት ሳይሞላው በ930 ዓመቱ በዛፏ ፍሬ ምክንያት ሞተ፡፡ አዳም ከገነት ሲባረር ወይንም ከፈቃደ እግዚአብሔር ሲለይ፤ እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ አስቀድሞ ያየለትና የማያውቃት ሰባተኛዋ የዕረፍት ቀን በውስጡ ተስፋ የምትባለዋን የስብእና ባሕሪይ ቋጥሯ ቀርታለች፡፡ (ወደ ዕብራውያን ሰዎች ምዕ.4)

    የተስፋ ርዝመት የሚለካው በእምነታችን ጥንካሬ ነው፡፡ የእምነት ጥንካሬ ምንጭ ደግሞ ፍቅር ነው፡፡ እነሆም ፍቅር፥ እምነትንና ተስፋን አጽንተን የምንኖርበት ድንቅ ኃይል ነው ማለት ነው፡፡

    ነገራችንን ስለ ፍቅር በማውሳት የጀመርነው ስለዚህ ነው፡፡ ምንም አይነት መንፈሳዊ አሳብ፣ ቃልና ሕይወት እንዲኖረን፤ ለመንፈሳዊው ዓለም እስትንፋስ የሆነው እምነት የግድ ያስፈልገናል፡፡ እምነት ደግሞ ወይ ከፍቅር ወይ ከምክንያት ይወለዳል፡፡ (ፍቅር ምንም ምክንያት የሌለው የመለኮት ቅዱስ ባሕሪይ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ዓለሙን "እንዲሁ" ወዶአልና የሚለው የዮሐንስ ወንጌል 3፥16 ቃል ይህንኑ ይነግረናል፡፡ ምክንያት ግን ሁልጊዜ መሥፈርት አለው፡፡ እምነት ከምክንያት ከተወለደ አስተዳደጉ የቀነጨረ ነው፡፡ ፍላጎቱ በአመንክዮ ድንበር የታጠረ ነው፡፡ ኃላፊነትን የመሸከም ጫንቃው በኵነቶች የተወሰነ ነው፡፡)

    ፍቅር ያልያዘው እምነት የተስፋ አድራሻ የለውም፡፡ ፍቅር የሌለበት እምነት የማይታየውን የሚያይበት፣ የማይጨበጠውን የሚደገፍበት፣ ያልተቀጠረውን የሚጠብቅበት የነፍስ ሕዋስ የለውም፡፡ ፍቅር የሌለበት እምነት መሥዋዕትነትን እንደ ዋጋ የሚቆጥርበት የሞራል ከፍታ የለውም፡፡ ፍቅር የሌለበት እምነት በተንገዳገደ ወቅት ይዞት የሚቆመው የመጽናኛ ግንብ የለውም፡፡ ፍቅር የሌለበት እምነት የምስጋን መባዕ በቀን ደስታም ሆነ በሐዘን ማታ የማቅረብ መሻቱ የለውም፡፡ "ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፥2)

                 ✞ ተስፋ ወደ ምሪት

    ተስፋ ካለ ወደፊት የሚቀጥል አንድ ጉዞ አለ፡፡ ጉዞ ደግሞ ምሪት ያስፈልገዋል፡፡ አቅጣጫ የሚያሳየው፣ መንገድ የሚጠቁመው፣ አካሄድ የሚያስተካክለው፣ የመጣበትን ርቀት የሚያስመዘግበው፣ የሚቀረውን ርዝመት የሚያሳውቀው ምሪት ይፈልጋል፡፡ ይሄ ምሪት ደግሞ ከእምነት ልጅ ከተስፋ ይወለዳል፡፡ አሁን ፍቅር የምሪት ቅደመ አያት ሆነ፡፡ (ፍቅር የሁሉ ነገር መጀመሪያ አልፋ ነው ብለናላ! ጌታም የትእዛዛት ሁሉ በኩር ፍቅር እንደሆነ በወንጌለ ድምፁ አሰምቶናል፡፡ የማቴዎስ ወንጌል 22፥38 ፤ የማርቆስ ወንጌል 12፥31፤ የሉቃስ ወንጌል 10፥27)

    ምሪት የዘር ግንዱ ከፍቅር የሚወጣ ከሆነ፤ ቀኛችንን ይዞ እየመራ የሚወስደን ከውጪ ወደ ውስጥ ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጪ ይሆናል፡፡

    ሰዎች ይጠይቃሉ፡፡ "ከእግዚአብሔር ጋር መኖር የምችለው እንዴት ነው? ምን ያህል ብጸልይ ነው ጥሩ የሚሆነው? ስንት ብሰግድ ነው መለኮታዊ ኃይል የሚገኘው? እንዲህ እንዲህ ያለ ስንፍና አለብኝ ምን ይሻላል? ከሥጋዊው አኗኗር መላቀቅ እየፈለኩኝ አልሆነልኝም፡፡ ምን ላድርግ? ወዘተ..." አይነት ጥያቄዎች ይጠየቃሉ፡፡ ካለማወቅ የሚመነጨው ጥያቄ መጠየቁ አግባብ ቢሆንም፤ ለእግዚአብሔር እንጥፍጣፊ ፍቅር የሌለው ማንነት ግን፤ በፍቅር መኖር ምክያትነት በራሱ መልስ ሊያገኝላቸው የሚገቡትንም ጥያቄዎች ጨምሮ ይጠይቅ ዘንድ ይገደዳል፡፡

   በምሳሌ እንየው፡፡ አንድ በጣም የምትወዱትን ሰው የአእምሮችሁ ሸራ ላይ ሳሉ፡፡ ወዳጃችሁንም ለማግኘት አስፈላጊ ቀጠሮ ኖሯችሁ በሰው መኪና እየሄዳችሁ ሳለ የትራፊኩ መንገድ ተዘጋጋ እንበል፡፡ በቃ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዞ የሚወሰነው ለግለሰቡ ባላችሁ የመወደድ ልክ ነው፡፡ ሳታዩት ማደር የማይሆንላችሁ ሰው ከሆነ በእግር ወርዳችሁም ይሁን፣ በሌላ አቋራጭ መንገድ አሳብራችሁም ይሁን ማድረግ የምትችሉትን ሁሉ ስለተዘጋጋው አስፓልት እልህ ሳይሆን ስለ ወደዳችሁት ሰው ፍቅር ስትሉ ታደርጋላችሁ፡፡ ወደ ማትወዱት ሰው እየሄዳችሁ ከሆነ ግን ወደኋላ ለመመለስ እንደ መንገድ መዘጋጋት ያለ በቂ ምክንያት ሳይሆን የጎማው የመሽከርከር ሁኔታ ራሱ ሰበብ ሊሆንላችሁ ይችላል፡፡ ሃይማኖታዊ መንገድም እንዲህ ያለ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ካለ በገደልም ውስጥ ምሪት አለ፡፡ ፍቅር ሳይሆን አንድ ሥጋዊ ምክንያት ወደ እግዚአብሔር የሚወስደን ከሆነ ግን ለጥ ያለው አውድማ ብዙ ቋጥኝ የተከመረበት ረጅም ተራራ መስሎ ይታየናል፡፡ በመሆኑም ሁሉንም ነገር በድጋፍ እየተመረኮዝን ካልሆነ በራሳችን የምንሻገረው አንድም ክፍተት አይኖረንም፡፡

   በተመሳሳይ ገለጻ የበለጠ ግልጽ ስናደርገው፤ የፍቅርን ምሪት ከውስጡ ያገኘ ሰው ስንት መስገድ እንደተገባው የፍቅሩ መጠን ይነግረዋል፡፡ የፍቅርን ብርሃን የሚከተል ሰው ጨለማን እየለየ የሚቃወምበትን ስልት ከእውቀቱ አያጣም፡፡ የፍቅርን ዱካ እየቆጠረ መንገዱን ያቀና አማኝ "ይህንን ባደረግ አምላኬ ይደሰታል ወይስ ያዝናል" እያለ ሁሉን የሚመዝንበት የነፍስ ልኬት ከሥጋው ማኅደር ውስጥ አለ፡፡ በፍቅር ረመጥ ልቡ ያልተቃጠለ ከሆነ ግን፤ ከውስጥ የሚደመጠው የሕሊና በጎ ሹክሹክታ ዝም ስለሚል ከውጪ የሚሰማ "ይህን ይህን አድርግ" የሚል ውትወታን ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የግድ ይፈልጋል፡፡
   በእውነት በእውነት፥ ፍቅር አልፋ ነው፡፡ ፍቅር ዖሜጋ ነው፡፡ በፍቅር የጀመረ ሰው በፍቅር ለመጨረስ የሚከፍለው ሰማዕትነት ራሱን የቻለ አምኃ ይሆንለታል፡፡ ከፍቅር የተነሣ ሰው ወደ ፍቅር መድረሻ የሚሄድበት መስመር የራሱን ዓላማና ትርጉም ይይዝለታል፡፡ ፊተኛውን ፍቅር ያደረገ ሰው ኋለኛውን ለመንካት ሲንጠራራ ወደታች የሚጎትቱ እልፍ ምክንያቶች ቁመቱን አያሳጥሩበትም፡፡

   ፍቅር ያለው ሰው በሰላማዊው ጊዜ ደስተኛ ነው፡፡ ፍቅር ያለው ሰው በመከራውም ሰሞን ያው ደስታው እንዳለ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍቅር "ይታገሣል፤ በሁሉ ይጸናል፤ ለዘወትርም አይወድቅም።" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13)

   ፍቅር ያለው ሰው ሲሞላለት ያካፍላል፡፡ ፍቅር ያለው ሰው ሲጎድልበትም ያለውን ማከፈል አያስቀርም፡፡ ምክንያቱም ፍቅር "ቸርነትንም ያደርጋል፤ የራሱንም አይፈልግም፤" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13)

   ፍቅር ያለው ሰው በጥርጣሬ ወጀብ አይታመስም፡፡ ፍቅር ያለው ሰው በዝግ በር ውስጥ ማለፍን ከምርጫ አያጎድልም፡፡ ምክንያቱም ፍቅር "ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13)

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
1• ፍቅር     1.2• ፍቅር ካለ ምን አለ? ክፍል - ፪ ✞ ፍቅር ወደ እምነት፥ እምነት ወደ ተስፋ፥ ተስፋ ወደ ምሪት    የሰው ልጅ የማንነቱ መልክ የሆነውን ፍቅር በተቀደሱ መልካም ነገሮች ሁሉ ውስጥ እየፈለገና እየገለጠ በዘመኑ ላይ መመላለስ ሲጀምር፤ የባሕሪይው መዝገብ የሆነው የአዳም ቤተሰብ በሥጋ ምኞት የተነሣ በመውደቁ ምክንያት፤ ከውጪኛው የሥጋ አካሉ ላይ ተገፍፎ የተሸጎረበትን…
1• ፍቅር

  1.2• ፍቅር ካለ ምን አለ?

ክፍል - ፫

✞ አንድ ሰው ሕዝብ ነው፥ ሕዝብም አንድ ሰው ነው ✞

"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል።" (የሉቃስ ወንጌል 15፥4-6)

   በክፍል ፩ ትምህርታችን ላይ እንደተነጋገርነው በአንደኛው የቀን ሥርዓት ውስጥ መቶ ነገድ ሆነው የተፈጠሩት መላእክት ነበሩ፡፡ ከእነርሱ የፍጥረት ቀን አስቀድሞ የተገኘ የባሕሪይ ልዕልና ያለው ሕልውና አልነበረምና ፈጣሪያቸውን ወደ ማወቅ እውቀት ገና አልደረሱም ነበረ፡፡ ከፊት ቀድሞ ያለውም መልአክ "የአምላክነት ሥልጣኑ በእኔ አለ፤ እነሆ የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ" የሚል ውሸትን ከማንነቱ ገለጠ፡፡ በኋላም ይህንን ውሸት ያመኑ ወዳጆቹን ይዞ ከሰማይ ሥርዓት ተለይቶ ወጣ፡፡

    ዘጠና ዘጠኙ ነገዶችን መቶ የሚያደርጋቸው አዲስ ፍጡር ሰማይና ምድርን በማዋሐድ ተሠራ፡፡ ሰውም ተባለ፡፡ ዓመፀኛው መንፈስ አክብሮ ያልያዘውን ርስት ሰፋ አድርጎ እንዲያስተዳድርም ተሰጠው፡፡

    ሹመት ራሱን የቻለ ልዩ ኃላፊነት ይፈልጋልና፤ አዳም ይጠብቀው ዘንድ የሚገባ አንድ ትእዛዝ ተነገረው፡፡ "ሁሉ ተፈቅዶልሃል ነገር ግን ይሄን አትንካ!" የሚልን ሕግ በስብእናው ሰማ፡፡ ይህንንም ቃል ድንበር አድርጎ በመጀመሪያ ራሱን በመግዛት በሁለተኛው ደግሞ ሌሎችን መግዛት ቀጠለ፡፡

   ሰላማዊው ሂደቱ በዚህ አልቀጠለም፡፡ ከፍታን ተመኝቶ ውድቀት የገጠመው መንፈስ፤ በክብር ማማ ላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠውን ሰው አይቶ ውስጡ በቅናት አረረ፡፡ እጅግ የጠነከረ ጥላቻም ተሰማው፡፡ ስለሆነ የወደቀበትን የቁልቁለት ጉዞ ለአዲሱ ነገድ ሊያጋራ እባብን ተጋርቶ ወደርሱ ሄደ፡፡ ተሳካለት!

   አትንካን የነካው አዳም የእውቀትን ዛፍ በመብላቱ 'ፍርሃት፣ ባዶነት፣ መራቆት፣ ጸጋ ማጣትና ብቸኝነት' የተባሉ ባሕሪያትን ከውስጡ አወቃቸው፡፡ ስለዚህ መሸሸግ ፈለገ፡፡ ወደኋላው አፈግፍጎ ወደ ገነት ዱር ገባ፡፡ በሌላ አገላለጽ ከእግዚአብሔር አሳብ ጠፋ፡፡

   ይህንንም ተከትሎ አንድ ድምፅ በገነት ውስጥ ይመላለስ ያዘ፡፡ አዳምንም ጠርቶ "ወዴት ነህ?" አለው፡፡" (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥9)

   እግዚአብሔር (አብ) መልካም አስቦ የምክሩ ማረፊያ ያደረገው ሰው ከፈቃዱ በጠፋ ጊዜ በቃሉ (በወልድ) በኩል ፈለገው፡፡ "ከወዴት ነህ" አለው፡፡ አዳምም ይህንን የእግዚአብሔር አምላክ ረቂቅ ቃል እስከ ረቂቅ ነፍሱ ድረስ አደመጣት፡፡ ወደፊት ዘሩ ምድርን እየሞላ ሲሄድ ነገዱን ለማስተዳደር ሲል ለሚያወጣቸው የ"አትንካ" ሕጎች ዳኛ ወቃሽ ልትሆን "ሕሊና" ሆና ተቀረጽችበትም፡፡ በአእምሮው ወለል ላይ እየተመላለሰች የምትጠይቀው የነፍስ አካል ሆነች፡፡

   የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ከሆነ ዘንዳ "ወዴት ነህ" ያለበት የቃል ፍለጋውም ሕያው ነው ማለት ነው፡፡ ይሄው ቃል በስድስተኛው ሺህ ዘመን ላይ "ሥጋ ሆነ"፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል 1፥14) ከአዳም ወገን እንደ አንዱ ሆነና የገነቱን ፍለጋ ተከትሎ እንደመጣ ለአዳም ልጆች   እንዲህ ሲል የአባቱን አሳብ ተናገረ "የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና፡፡ ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን? ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል። እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።" (የማቴዎስ ወንጌል 18፥11-14)

   ምንም ነገር ከርሱ የማይሰወርበት በሁሉ የመላ እግዚአብሔር፤ አዳም በስተምሥራቂቱ የዔድን ዛፎች መካከል ሳለ "በወዴት አለህ?" ሲል የፈለገው "ከእኔ ስለምን ተለየህ?" የሚልን የመሳሳት ፍቅር ሲገልጥ ነው፡፡

   ይሄ ፍቅር አካላችንን ገንዘብ አደረገውና "ሸክማችሁ በወዴት ነው? ወደኔ አምጡት" የሚል ርኅሩኅ ፈቃዱን ይገልጥልን ገባ፡፡ እንዳለውም አልቀረም፡፡ ከዘጠና ዘጠኙ ብርሃናውያን ነገደ መላእክት ተለይቶ በመጥፋት የኃጢአትን ጨለማ ተሸክሞ የወደቀው ባሕሪያችንን ሊያነሣ፤ የበደላችንን ክብደት በመስቀል ተሸክሞ ደጋግሞ ወደቀ፡፡

   እየወደቀ እየተነሣም የቀራንዮን ዳገት ወጥቶ ሲጨርስ፤ በወንበዴዎች መካከል እንደ ርኩስ ተሰቅሎ ተገኘ፡፡ በስተመጨረሻም አዳም በወደቀበት ቦታ ላይ ቆመና "አባት ሆይ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ" ብሎ ጩኸታችንን ጮኸ፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የተለየቺው ነፍሳችንን መልሶ በአብ መዳፍ አስቀመጣት፡፡

   ክርስቶስ በጠፋቺው አንዲቱ በግ ውስጥ አዳምን መስሎታል፡፡ አንዲቱ በግ አንዱ አዳምን እና ሙሉውን የአዳም ነገድ ትወክላለች፡፡ አገላለጹን ፍርጥም ስናደርገው፤ ከሁሉ የአዳም ትውልድ አንስቶ እስከ አንድ የአዳም ልጅ ድኅነተ ርቀት ድረስ የእግዚአብሔር ፍቅር ተዘርግቷል፡፡ ማለትም በገነት ውስጥ የተፈለገው የአዳም ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ከዛ ቤተሰብ የሚወለደውና በባሕሪዩ ከእግዚአብሔር ፈቃድ እየወጣ እየወጣ የሚሄደው እያንዳንዱ (የአዳም ዘር) ግለሰብ ነው፡፡

   የእግዚአብሔር ቅዱስ ዓይን አንድን ሰው እንደ ሙሉ ሕዝብ፥ ሙሉውን ሕዝብ ደግሞ እንደ አንድ ሰው ያያል፡፡ "የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" የሚለው የምሕረት ቃል በደም የሰከሩትን አይሁዳውያንንና ሮማዊ ወታደሮችን ብቻ ሳይሆን ሁላችን ሳናውቅ የምንበድለውን ሰዎች ሁሉ እየጋረደ የሚታገሠው ለዚህ እንደሆነ ያስተውሏል፡፡ እንዲሁ የአንድ ነፍሰ ወደ እግዚአብሔር አሳብ መመለስ እንደ ሙሉው የሰው ዘር መዳን ሠራዊተ መላእክትን ያስደስታል፡፡ ነገረ ተዋረዱን ስንቀጥል... እኛስ? የአንድ ሰው መዳን እንደ ሕዝብ መዳን ሁሉ ያስፈነድቀን ይሆንን?

   እኛማ የኛ መዳን እስከተፈጸመ ድረስ ስሌላው አይገደንም፡፡ ሲሆን ለኛ መዳን ሌላው አለመዳን ካለበትም ወገንን እናጠፋለን፡፡ "የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግ መጥቶአል" ብሎ የተናገረ አምላክን እያመለክን፤ እኛ "ሰዎች" እንኳን የሌሎች መጥፋት ሊያሳስበን ቀርቶ፤ አስፈላጊ ከሆነ ሰውን አጥፍተን የምንፈልገውን ልናገኝ ፍለጋ እንወጣለን፡፡

   በችግር የጠፋውን፣ በድህነት የጠፋውን፣ በሐዘን የጠፋውን፣ በደስታ የጠፋውን፣ በግፍ የጠፋውን፣ ባለመወቅ የጠፋውን፣ በማወቅ የጠፋውን፣ በሐብት የጠፋውን፣ በዝሙት የጠፋውን፣ በሱስ የጠፋውን፣ ወዘተ... መፈለግ የመለኮት ድርሻ ብቻ እንዳልሆነ ራሱን "የሰው ልጅ" ብሎ የጠራው የጌታ ንግግር ያመልክታል፡፡ የሰው ልጆች ኃያል ፍቅር መልካችን እንዲሆን የመለኮትን እፍታ በነፍሳችን አትመናልና፤ የጠፋውን ሁሉ እንደ መለኮት መፈለግ በእግዚአብሔር የተመሰልን አርአያዎቹ ስለመሆናችን ምስክር ነው፡፡

   ሆኖም አኗኗራችን ፈጽሞ እንደዛ አይደለም፡፡ በአረማዊቷ ዓለም የሚከናወነውን መጠፋፋት ተወት አድርገነው፤ መንፈሳዊ ታሪክና ሃይማኖት አለን የምንል አማኞች እንኳ ወይ የራስ መዳንን ብቻ ፈላጊዎች አሊያም ሌሎችን አጥፊዎች መሆናችን በጣም ያሳዝናል፡፡ (እግዚአብሔር ማመን ምን ማለት ነው?)
  ደግ መሆን ሁለት መሥፈርት አለው፡፡ አንደኛ ደግ ነገር ማድረግ፥ ሁለተኛ ደግ ያልሆነውን አለማድረግ የሚባሉ ሁለት መሥፈርቶች አሉ፡፡ ደግ ነገር የሚያደርግ ሰው ክፉውንም የሚያደርግ ከሆነ ደግ አይባልም፡፡ ክፉውንም ደጉንም የማያደርግ ሰው ደግነትን አልኖራትም፡፡ መብትም እንደዚሁ ሁለት መሥፈርት አለው፡፡ አንደኛ የራስን ፈቃድ መፈጸም፥ ሁለተኛ የሌሎችን ፈቃድ አለመንካት፡፡ (ለምሳሌ በዲሞክራሲው ርዕዯት ሁሉም ሰው ያለመታሰር መብት አለው፤ የሌላው ሰው ያለመታሰር መብት ከጣሰ ግን መብቱ ይገፈፋል)

   በዚህም መሠረት እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ሁለት መሥፈርቶችን አሟልቶ መያዝ ይኖርበታል፡፡ አንደኛ ራሱን ከአባቱ ፈቃድ አለመለየት፥ ሁለተኛ ወንድም እህቶቹን ሁሉ ከአባቱ አለመለየት፤ እንዳይለዩ መጠበቅ፤ ከወጡም መመለስ፡፡ እነዚህን ሁለቱንም ኩታ ገጠም አድርጎ ማንነቱን በማይገነባ ቤተመቅደስ ላይ እግዚአብሔር አያድርበትም ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ "የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፥10)

    ሰው ጽድቅን ሁሉ ፈጽሞ አንድ ሰውን እንኳ ባይወድ (ቢያማ፣ ቢሰድብ፣ ቢገፋ፣ ቢጥል፣ ቢያጎሳቁል፣ ቢቀማ፣ ቢፈርድ፣ ቢከለክል፣ ቢነጥቅ፣...) ሰውየው ከክፉው መንፈስ ጋር ነው፡፡ ጽድቅን በሚችለው እያደረገ ሁሉንም ሰው ከአንጀቱ የወደደ እርሱ ከተቀደሰው መንፈስ ነው፡፡ (ዐሥርቱ ትእዛዛት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ሰው ለምን እንደሆኑ ልብ ይሏል! "እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥21))

   አጠገብ ያለን ቤተሰብ አሊያ ወዳጅ መውደድ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለቺውን የባሕሪይ ፍቅር አትወክልም፡፡ እንስሳትም እንዲሁ ያደርጋሉና፡፡ ሰው ግን የተፈጥሮ ገጽታው ፍቅር ነውና፤ አባቶችን ሁሉ እንደ አባቱ፣ እናቶችን ሁሉ እንደ እናቱ፣ ወንድሞችን ሁሉ እንደ ወንድሙ፣ እህቶችን ሁሉ እንደ እህቱ ሲወድ በእርግጥም እርሱ የአምላክ ምሳሌ ስለመሆኑ ያስረግጣል፡፡ (ክርስቲያን አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን የመሰለበት ልጅነቱ የሚተረጎመው ሌሎችን በመወደዱ ፍቅር ውስጥ ነው፡፡ አብ በራሱ አካል ለራሱ አሳቢ ሆኖ ሳለ፥ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስም አሳባቸው እንደሆነ፤ ክርስቲያንም ለራሱና ለወገኑ ሁሉ ያስባል፡፡ ወልድ በራሱ አካል ለራሱ ተናጋሪ ሆኖ ሳለ፥ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስም ቃላቸው እንደሆነ፤ ክርስቲያንም ለራሱና ለወገኑ ሁሉ ድምፅ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በራሱ አካል ለራሱ እስትንፋስ ሆኖ ሳለ፥ ለአብና ለወልድም ሕይወታቸው እንደሆነ፤ ክርስቲያንም ለራሱና ለወገን ሁሉ ሕይወት ይኖራል፡፡)

  እግዚአብሔር ሕዝብን ሁሉ እንደ ግለሰብ፥ ግለሰብን ሁሉ እንደ ሕዝብ የወደደበት ፍጹም ፍቅሩ በልባችን ማኅደር ሳይታተም፤ መርጠን የምንወድና መርጠን የምንጠላ ከሆን የሃይማኖት መሠረታዊ ሕጎች ከውስጣችን ተንደውብናል ማለት ነው፡፡

    ሰው ሰውን [ሁሉ] ሳይወድ እልፍ ቢሰግድ፣ ሙሉ ቀን ቢጸልይ፣ አጥንቱ እስኪገለጥ ቢጦም፣ በዮርዳኖስ ባሕር ቢጠመቅ፣ ቅዱስ ቁርባንን ከሱራፌል እጅ ቢቀበል፣ ሚሊዮን ብሮችን ዐሥራት ቢያወጣ፣ ክፉ መናፍስትን ማሸነፍ ቢችል፣ መላእክት ቀርበው ቢያገለግሉት ምንም ዋጋ የለውም፡፡ (ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ ሰው ግን ዋጋው አይጠፋበትም) "ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥20)

   የልዑል አምላክ የመጨረሻው ብቸኛ ዓላማ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ ጥግ እንዲደርሱ ነው፡፡ (1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥3-4) እንኪያስ ይህንን መለኮታዊ ፍቅር የሚጋራ ማንኛውም አማኝ በፈጣሪ ፊት ልዩ ቦታና ሞገስ ይሰጠዋል፡፡ ሰውን የሚያስብ ሰው እግዚአብሔር ያስበዋል፡፡ ሰውን ያከበረ ሰው እግዚአብሔር ያከብረዋል፡፡ ሰውን የሚጠብቅ ሰው እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፡፡ ሰውን የሚያስቀድም ሰው እግዚአብሔር ያስቀድመዋል፡፡ ሰውን ያሳረፈ ሰው እግዚአብሔር እረፍት ይሆነዋል፡፡ ሰውን የተንከባከበ ሰው እግዚአብሔር ይንከባከበዋል፡፡ ሰውን ያገዘ ሰው እግዚአብሔር ያግዘዋል፡፡ ሰውን ያበረታ ሰው እግዚአብሔር ያበረታዋል፡፡ (አባባል እንዳይመስላችሁ! ስታነቡት ሳይሆን ስትኖሩት ይታወቃችኋል)

   (አልገባንም እንጂ) የመዳን አጭር መንገድ ወገንን ማዳን ነው፡፡ የመፈወስ ቀላሉ ጉዞ ለሌላው ፈውስ መሆን ነው፡፡ የመደሰት ነጻው አቅጣጫ የሌሎች ደስታ መሆን ነው፡፡ ሰላም የማግኘት ቅርቡ በር ሰላምን ለሌሎች ማስገኘት ነው፡፡ ከሕመም የመጠበቅ ትልቁ ጸሎት ለታመሙት መጸለይ ነው፡፡

(ወደ ቅዱስ ቁርባን እየሄድን ፍቅርን መነሻችን ለምን እንዳደረግን አሁን ግልጽ ነው፡፡ ፍቅር በሌለው ሥጋና ደም ውስጥ የፍቅር ሥጋውና ደሙ አይወሐድም!)
ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
1• ፍቅር   1.2• ፍቅር ካለ ምን አለ? ክፍል - ፫ ✞ አንድ ሰው ሕዝብ ነው፥ ሕዝብም አንድ ሰው ነው ✞ "መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና…
1•  ፍቅር

   1.3•  ፍቅር ከሌለ ምን የለም?

ክፍል - ፬

✞ ማንም የማይሠራባት ሌሊት አትነጋም ✞

    ከፀሐይ ሥርዓት በታች ለሚሆን ነገር ሁሉ የራሱ ጊዜ ይኖረዋል፡፡ ሰማይ የሚጠቁርበት፥ እንደገና የሚፈካበት፤ ክፉ የሚያይልበት፥ እንደገና የሚቀንስበት፤ ሐዘን የሚነግሥበት፥ እንደገና የሚወርድበት፤ ማጣት የሚጠነክርበት፥ እንደገና ማግኘት የሚተካበት የየራሱ ጊዜ አለ፡፡

   ሃይማኖት ጉዞ ናት፡፡ በሂደቷም ውስጥ የራሳቸውን ተራና ዑደት እየጠበቁ የሚከሰቱ ነገሮች አሏት፡፡ ከአንዱ የእምነት ምዕራፍ ወደ ሌላኛው በምንሻገርበት ከፍታ ውስጥ ቦታ ይዘው የሚጠብቁ እረከኖች ይኖራሉ፡፡ መንፈሳዊ ደረጃዎችን እየረገጥን በምንወጣበት አካሄድ ላይ የምናገኛቸው እንደየወቅታቸው የሚከሰቱ ሁነቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ መከራ ነው፡፡

   መከራ የራሱን ጊዜና ሰልፍ እየጠበቀ ብቅ የሚል የዓለም ኃይል ነው፡፡ መከራ በእያንዳንዱ የለውጥ ዛቢያ ላይ የማሻገር ወይንም የመጣል ሚናን የሚጫወት ባለ ድርሻ ነው፡፡ መከራ የአስተሳሰብ ረድፍን የመቀየር ጉልበት ያለው ባለወፍራም ክንድ ነው፡፡ መከራ ከምቾት ክልል የሚያፈናቅል ብርቱ ተዋጊ ነው፡፡ መከራ የእግዚአብሔርን ጥሪ የማድመጥ ዕድል የሚሰጥ ቁጡ መልእክተኛ ነው፡፡

    ሰዎች በእጅጉ ከሚሸሿቸውና ከሚጠሏቸው ነገሮች መካከል መከራ ግምባር ቀደሙን ይይዛል፡፡ ሁሌ እንደተዝናናን፣ እንደፈነጠዝን፣ እንደተስማማን፣ እንደተሳካልን መቀጠል የሥጋ ባሕሪይ ተፈጥሮአዊ ምኞት ስለሆነ፤ ይሄ ጠባይ በሚገንንበት እይታ ላይ የመከራ መልክ አስፈሪና አስቀያሚ ነው፡፡

   ለመከራ የምንሰጠው ሚዛን ቀለለም ከበደም፤ (ብንወድም ብንጠላም) በምድር እስካለን ድረስ መከራን የማየታችን ጊዜ ከቶውኑ አይቀርም፡፡ [በተለይ] ለእውነተኛ ክርስቲያን መከራ የአንድ ፊቱ ሌላኛው ጎን ነው፡፡ መጽሐፍ፦ "ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም" (ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1፥29)

    አንድ ወቅት ላይ መድኃኒቱ መምህር ተማሪዎቹን አስከትሎ በመንገድ እየሄደ ነው፡፡ አንድም ሰው ወደርሱ ቀረብ አለና "ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።" (የሉቃስ ወንጌል 9፥57) "ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" ብሎ መልስ ሰጠ፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 8፥20)

   "ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" ያለበት ንግግሩን እናስተውለው፡፡ በተለይ 'ለሰው ልጅ' የሚለውን ቦታ ልዩ ትኩረት እንስጠው፡፡ መሲሑ "የሰው ልጅ" ሲል ራሱን የሚጠራበት ሥጋ ከመለኮት ጋር በአንድነት ያለ ነው፡፡ እናማ "ልከተልህ እወዳለሁ" ላለው ሰው "አንተ ሥጋ ከመለኮት (ከእኔ) ጋር በአንድነት መኖርን ወድደህ ስትከተለኝ የሚመች መጠጊያ አይኖርህምና ደግመህ አስብ" እያለው ነበረ፡፡

   የሰብአዊነት ቤተመቅደስ በገነት ሳለ እንደፈረሰ ይታወቃል፡፡ ስለሆነ የጎሰቆለውን አሮጌውን ቤተመቅደስ "በሦስት ቀን አፍርሶ" ዳግም ሊሠራ የእግዚአብሔር ልጅ ሲወለድ፤ ገንዘብ ያደረገው የሰውነት ባሕሪይ ከጽደቅ ያልፈረሰውን የአዳምን አካል ነው፡፡ ወይንም በሌላ አባባል ክርስቶስ የለበሰው ሥጋ አዳም ከመሳቱ በፊት የነበረውን፥ ክፉውን የማያውቅ ሥጋን ነው፡፡

   ከእውቀት ዛፍ ያልበላው አዳም ደግሞ ዔድን ገነትን እንጂ ምድርን አያውቃትም፡፡ ወደ ተፈጠረባት መሬት ተሰድዶ ለመኖር የመጣው የጸጋው ብርሃን ከተገፈፈ በኋላ ጨለማን ለብሶ ነው፡፡ ምድሪቱም አሜኬላና እሾህ የምታበቅልበትን እንጂ ከእግዚአብሔር ያልተለየውን "አዲሱን" ሰው አታውቀውም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የመጀመሪያውን የአዳም ንጹሕ ባሕሪይ ገንዘብ አድርጎ ወደ ዓለም ሲመጣ "ዓለሙም አላወቀውም።" ስላላወቀውም ገና ሲወለድ ጀምሮ ማደሪያ አሳጣው፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል 1፥10)

   ብላቴናው አድጎ በዓለም ፊት እያስተማረ ሲመላለስም ራሱን የሚያስጠጋበት ማረፊያ አላገኘም፡፡ ምክንያቱም ዓለም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሆነውን ሥጋ አታውቀውም፡፡ ካላወቀቺው ታሳድደዋለች፡፡

   ለጻፊው (ልከተልህ እፈልጋለሁ ላለው ሰው) በተሰጠው መልስ ውስጥ ሁላችን የተነገረን አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ በሐዲስ ኪዳን ዘመን "ሰው" የተባለው ፍጡር እንደገና ከመንፈስና ከውኃ ተወልዶ፤ ክርስቶስን ወደ መምሰል የእግዚአብሔር መልክ እያደገ እያደገ የሚሄድ ከሆነ መጠጊያ?... የለውም!

   ክርስቲያኖች ዓለም ለእነርሱ በጭራሽ ቦታ እንደሌላት ማስተዋል እንዲያቅታቸው፤ አጥፊው ኃይል በአራቱም የምድር ማዕዘናት ምቹ መጠጊያዎችን አበጅቶ "እስቲ አረፍ በሉ" ይላል፡፡ "እሺ" ብለው ማረፊያ ያመቻቹ ክርስቲያኖች ሲኖሩ ታዲያ፤ ጌታ "የሰው ልጅ" ብሎ የጠራው ከእግዚአብሔር ያልተለየ ሥጋ መሆናቸው ቀርቶ የቀበሮ ወይንም የሰማይ ወፎች ሥጋ ሆኑ ማለት ነው፡፡

   በእውነትም ይህቺ ዓለም የምትመቸው እንደ እባብ ለሚናደፉ፣ እንደ ጊንጥ ለሚመርዙ፣ እንደ ጅብ ለሆድ ለሚኖሩ፣ እንደ አሳማ በቃኝ ለማያውቁ፣ እንደ ቀበሮ ጣዝማ ለሚልሱ፣ እንደ በቀቀን ወሬ ለሚወዱ፣ እንደ ጃርት ለሚዋጉ፣ እንደ ነብር ደም ለሚመጡ፣ እንደ እስስት ለሚያስመስሉ፣ እንደ ፍየል ለሚቅበዘበዙ፣ እንደ ጭልፊት ለሚነጥቁ፣ እንደ ድመት ወገናቸውን ለሚበሉ ሁሉ ነው፡፡ ክርስቶስ እንደለካው የ"ሰው" መጠን ሆነው በውድ ሕልውና የሚመላለሱት በአንጻሩ "በዓለም ሳሉ" ከመከራ የሚያርፉበት መጠጊያ አያገኙም፡፡

   ዲያቢሎስ ሰዎች ሰማያዊ መዝገባቸውን ቀደው ከእንስሳት እንደ አንዱ በመሆን በዓለም ምቾት መጠጊያ አግኝተው የጽድቅ መከራን እየነቀፉ እንዲኖሩ በማገዝ አያሌ ነፍሳትን በስውር ጥበብ እያጠፋ ይገኛል፡፡ ይሄ ወጥመዱ ላይ ጥቂቶች ነቅተው ክርስቶስን ወደ መከተል "ሰውነት" እርምጃ ሲጀምሩ ደግሞ፤ እያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸውን በፈተና ከቦ ትንፋሽ በማሳጣት፤ መንፈሳዊውን ጉዞ እንዲጠሉትና እንዲያማርሩት ያደርጋል፡፡

   አማኞች ፈጣሪያቸውን በትክክል ማምለክ ፈልገው የሆነ እንደሆነ ዓለም መቀመጫ እንደምታሳጣቸው አስቀድመው ብርቱ ግንዛቤ ማግኘት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም በዓለም ዙፋን ላይ ነግሦ ያለው ገዢ የቅድስናና የበጎ ነገር ሁሉ ተቃዋሚ ነው፡፡
   ክርስቶሳዊነት በአውሬው አስተዳደር ውስጥ ርስት የለውም፡፡ (ልብ ብላችሁ እዩ) መልካም ስብዕና ይነገድበታል እንጂ አይወደድም፡፡ ይመከራል እንጂ አይኖርም (ኖ ጠብቆ ይነበብ)፡፡ ጥሩ ነው ይባላል እንጂ አይመረጥም፡፡ አፍቃሪ ሰው፣ ለጋሽ ሰው፣ ሩኅሩኅ ሰው፣ የዋህ ሰው፣ ቀና ሰው፣ ታዣዥ ሰው፣ ድሃ ሰው፣ ሐቀኛ ሰው በሁሉም መስክ ላይ አባራሪዎች አሉበት፡፡ "በመላ ክፋት" የተያዘቺው ምድር ለክፉ እንጂ ለደግ ስብዕና ኮታ አላዘጋጀችም፡፡ አስተማሪያችን እንቅጩን ስለነገረን ግን አይገርመንም "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ" (የዮሐንስ ወንጌል 16፥33)

   ክርስቲያንነት መከራን በመቀበል ማኅተም የተዘጋ የሕይወት መጽሐፍ ከሆነ፤ በመከራ የመጽናኛ፣ መከራን የመቋቋሚያ፣ የመከራን ሚስጢር የመማሪያ፣ ከመከራ የመውጫ መንገድ ደግሞ በአንጻሩ ይኖር ዘንድ ግድ ነው፡፡ ("ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፥13)) ይሄ መንገድ እንደ መከራው አይነትና ይዘት አቅጣጫው ቢለያይም መነሻ መሠረቱ የሚነሣው ግን ከፍቅር ነው፡፡

ሐዋሪያው፦ "በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥37-39)

   እግዚአብሔርን ከልብ በመውደድ ፍቅር ውስጥ በዓለም ሳለን የምናያቸው መከራዎች ሁሉ ቀድመው የተሸነፉ ናቸው፡፡ ይሄንን ገልብጠን ብናነበው፤ መለኮታዊ ፍቅር ከማንነቱ ላይ የማይፈልቅለት ሰው በመከራዎች ሁሉ የተሸነፈ ነው፡፡

   ጌታ "ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች" ሲል እንደተናገረው በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ የመከራ ጽልመቶች ፈረቃቸውን እየጠበቁ መጥቆራቸው አይቀሬ ነው፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል 9፥4) በዛ ዙሪያ ገባው በማይታይበት ድቅድቅ ጨለማ ላይ ሳለን፤ የሚወጉ የመሬት እሾህች ቢያደሙንም፣ ወለል የመሰሉ ጉድጓዶች ወደታች ቢጥሉንም፣ ዕንቅፋቶች በየርቀቱ ተቀምጠው ቢነድሉንም፣ መቆማቸው ከማይታይ ግንዶች ጋር ብንጋጭም፤ እየዳበስንም ቢሆን መራመዳችንን የምንቀጥለው ነፍስ ውስጥ በምትበራ የፍቅር ፋኖስ ስንመራ ነው፡፡

   ማንም በማይሠራባት የቀን ስብራት፤ ውስጣችንን ጠግና የምታሠራን ፍቅር ናት፡፡ መከራውን እንደማናሸንፍ እየተሰማን እንኳ ለማሸነፍ ተስፋ የምንቀጥለው በፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ያለበት ልብ በሌሊትም ሲያይ፤ ፍቅር አልባው ደግሞ የቀን ፀሐይን እየጠበቀ ይወጣል፡፡

   ክርስቲያናዊ አኗኗር የመከራ መጋዘን እንደሆነ ተነጋግረናል፡፡ በእያንዳንዱ መንፈሳዊ ሥራ ላይ ዲያቢሎስ የመከራ ክፍልን ከጀርባ አዘጋጅቶ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም መጸለይ መከራ ነው፣ መስገድ መከራ ነው፣ ንስሐ መግባት መከራ ነው፣ መቁረብ መከራ ነው፣ መማር መከራ ነው፣ መስጠት መከራ ነው፣ መታዘዝ መከራ ነው፣ ማክበር መከራ ነው፣ የዋህ መሆን መከራ ነው፣ ሐቅን መናገር መከራ ነው፣ ሐሜትን መቃወም መከራ ነው፣ ወዘተ... (ሰማያዊ ዕሴቶች በሙሉ እንዳይገለጡ የሚታገላቸው ሌሊት አለባቸው)

   ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር የሆኑትን የነፍስ ጎዳናዎች በመከተል ላይ መከራን መቀበል ገሐድነት ያለው ዋጋ እንደማይገኝበት በማሳየት፤ ለመንፈሳዊ ምግባሮች መሥዋዕትነት መክፈል ብክነት እንደሆነ በዓለም ዜጎች አመለካከት ውስጥ አሰልጥኖ አምላካዊ ፍቅርን አጥፍቷል፡፡ ይሄንን ቃል በተጨባጩ የዘመናችን መስክ ሥጋ ለብሶ በአንድ ቅርጽ ብቻ ስናየው፤ ትውልዳችን ከአስተዳደጉ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ክብደትን የመሸከም ጫንቃው እንዳይጠነክር ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብና ትምህር ቤት ስለ ቅዱሳን፣ ስለ ጻድቃንና ስለ ሰማእታት ታሪክና ክብር አላሰተማሩትም፡፡ ልጆች የተጋድሎ ምሳሌ እንዲያደርጓቸው በአርአያነት የሚቀረጹላቸው ታላላቆች መንፈሳዊ ገድልና ሥነ ሕይወት ያላቸው አይደሉም፡፡ ስለዚህ መከራን የመታገል ኃላፊነት ግድ ሲሆን፤ ታዳጊዎች መቸገር ያለባቸው ከሰማይ ዝቅ ላሉ የእንጀራ ስኬቶች እንጂ በሳይንስና በገንዘብ የማይደረስበት እምነት ላይ አቅምና ጊዜ እንዳያባክኑ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንደ ውኃ ሲጠጡት በከረመው ምድራዊ ርዕዮት ይሞላሉ፡፡ (መሬታዊ ተክለ ቁመና ደግሞ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ያለች "ማንም የማይሠራባት ጨለማ" ላይ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን የፍቅር ኃይል፤ ሥጋዊ ጉድለቶችን የማሟያ የቁስ ፍላጎት አድርጎ ይቀይረዋል፡፡)

   ፍቅር ከሌለን ረቂቅ ጦርነቶችን የምንዋጋባቸው የእምነት ጦር ዕቃዎችን በልበ ሙሉነት አንታጠቅም፡፡ የመከራ ዶፍ በዘነበ ጊዜ የምንሸሸግበት ዋሻ የለንም፡፡ ከፈተና ገጽ ጀርባ ያለውን ትምህርት የምናስተውልበትን እርጋታ አንታደልም፡፡ ከመጸለይ ንጋት በፊት፣ ከመስገድ ጸዳል አስቀድሞ፣ ንስሐ ገብቶ ከመቁረብ ብርሃን መጀመሪያ የሚኖረውን አላሠራ የሚል ዲያቢሎሳዊ ለሊት ለማሳለፍ የምንችልበትን ጽናት አናገኝም፡፡ (እግዚአብሔርን ያላፈቀረ ሰውነት አንትኩኝ ባይ ሆደ ባሻ ነው፡፡ ራሱን በተኮሰው፣ ዓይኑን ባቃጠለው፣ ሆዱን በቆረጠው፣ እግሩን ባዳለጠው፣ ሥራው በደከመው፣ ትምህርት በከበደው፣ ምቾቱ በራቀው፣ ሌሊቶች በከበቡት ቁጥር እንዳማረረ፣ እንደተበሳጨ፤ እንዳሳበበ፣ እንደሸሸ፣ እንደተልፈሰፈሰ፣ ለምን በኔ ብቻ እንዳለ ይኖራል፡፡)

   "በወደደን በእርሱ" ብሎ የሚነሣው የሮሜው መልእክት ዓ.ነገር መዝጊያ "እንበልጣለን" ነው የሚለው፡፡ ቁመታቸው ከረዘመ፣ ግዝፈታቸው ከተለቀ፣ ጡንቻቸው ከጠነከረ፣ ርስታቸው ከሰፋ መከራዎች ሁሉ የምንበልጠው በፍቅር በኩል ነው፡፡ እንበልጣለን ከሚለው ቃል ወዲያ መደምደሚያው አራት ነጥብ (::) ነው የሚገኘው፡፡ ይሄ ደግሞ "በወደደን" ብሎ በጀመረ ድንቅ ፍቅር ባለው ሃይማኖታዊ መንገድ ላይ የመከራዎች ሁሉ መጨረሻቸው መሸነፍ (መበለጥ) ነው ማለታችንን እርግጠኛ ያደረግልናል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
   ክርስቶሳዊነት በአውሬው አስተዳደር ውስጥ ርስት የለውም፡፡ (ልብ ብላችሁ እዩ) መልካም ስብዕና ይነገድበታል እንጂ አይወደድም፡፡ ይመከራል እንጂ አይኖርም (ኖ ጠብቆ ይነበብ)፡፡ ጥሩ ነው ይባላል እንጂ አይመረጥም፡፡ አፍቃሪ ሰው፣ ለጋሽ ሰው፣ ሩኅሩኅ ሰው፣ የዋህ ሰው፣ ቀና ሰው፣ ታዣዥ ሰው፣ ድሃ ሰው፣ ሐቀኛ ሰው በሁሉም መስክ ላይ አባራሪዎች አሉበት፡፡ "በመላ ክፋት" የተያዘቺው ምድር ለክፉ እንጂ…
1•  ፍቅር

    1.3•  ፍቅር ከሌለ ምን የለም?

ክፍል - ፭

✞ ዲያቢሎስ አንዳች አለው ✞

   መንፈሳዊ ውጊያ ብለን የምንሰይመው በቅዱስና በርኩስ መንፈስ መካከል ያለ ጦርነት ከአጠራሩ ብቻ ለመገንዘብ እንደሚያስችለው የፍልሚያው አጠቃላይ ገጽታ ከዓይን የተሰወረ ረቂቅ ነው፡፡ በግዙፍ ሥጋ አእምሮና አካል የውጊያውን መልክ መረዳት በፍጹም አይቻልም፡፡

   ከመንፈሳዊና ከሥጋዊ ባሕሪያት ውሕደት የተገነባነው የሰው ልጆች ወደ ረቂቁ ዓለም "መጋደል" በገባን ጊዜ፤ መንፈሳዊ ባሕሪያቶቻችን እንጠቀምባቸው ዘንድ ያለን የውጊያ ጦር ዕቃዎቻችን ናቸው፡፡ ከነዚህ ባሕሪያት መካከል የአንበሳውን ሚና በመጫወት ለሌሎቹ መንፈሳዊ ባሕሪያት (ትሕትና፣ ለጋስነት፣ ታዛዥነት፣ የዋህነት፣ ወዘተ..) ጉልበት የሚሰጠውና መንፈሳዊ ሥራዎች ተጀምረው እንዲፈጸሙ ኃይል የሚሆነው ጥበብ ፍቅር ነው፡፡

   ፍቅር በሌለበት ቦታ ላይ ዲያቢሎስ ሁልጊዜ አቅም አለው፡፡ ምንም እንኳ መንፈሳዊ ምግባራትን (ጸሎት፣ ስግደት፣ ጾም፣ ወዘተ...) በማድረግ ክፉውን መንፈስ ለማጥቃትና ለመከላከል ብንችልም፤ ፍቅር ባልመሠረተው የእምነት ትግል ላይ ጠላት ክንዱ ቶሎ የማይዝል ፈርጣማ ነው፡፡

   መድኃኒታችን አንድ ወቅት ላይ ከሐዋሪያቱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ አላቸው፦ "ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም" (የዮሐንስ ወንጌል 14፥30)

   በርዕሳችን ልናነሣው የወደድነውን አሳብ የሚያስረዳልንን ሐረግ ትኩረት እናድርግበት፡፡ "የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም" የሚለውን፡፡

   ክርስቶስ "በእኔ ላይ" ሲል የሚጠቅሰው እርሱነቱ በፍጹም ተዋሕዶ ያለ ነው (ክፍል-፬ ላይ የሰው ልጅ የሚለው የጥቅስ ቃል የተብራራትን አንቀጽ 7 እይ)፡፡ ከሁለት ባሕሪይ አንድ ባሕሪይ፥ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነ ተዋሕዶ፡፡ ፍቅርም ተዋሕዶ ነው፡፡ ፍቅር የተለያዩ አካላት እንደ አንድ የአካልነት ተገናዝቦ የሚተሳሰሩበት ድንቅ ሰንሰለት ነው፡፡ ለምሳሌ እናትና ልጅ፣ ባልና ሚስት፣ ጓደኛና ወዳጅ፣ ወገንና ወገን ተዋድዶ የሚኖርበት ሰብአዊ ሕግ ፍቅር ለተዋሕዶ የሰጠውን ብያኔ ገንዘብ ያደረገ ነው፡፡

   እግዚአብሔርና ሰው በአማኑኤልነት ማዕቀፍ ውስጥ አንድ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ኃይል ይኸው በተዋሕዶ ያለ ፍቅር ነው፡፡ አምላክ ሰው እስኪሆን ድረስ ራሱን ባዶ አድርጎ ከፍጡራን ጋር መሆንን እንደ መተናነስ ያልቆጠረበት ብቸኛ ምክንያት ፍቅር ነው፡፡ የማይወሰነው መለኮት በሥጋ ተወስኖ ከፀሐይ በታች ባለ ሥርዓት የተመላለሰውም ስለ ፍቅር ነው፡፡

   በተዋሕዶ ያመንን ክርስቲያኖች ስንሆን፤ "አምላክ ሰው ሆነ"ን ብቻ ተርከን አንቀመጥም፡፡ እንደ እምነታችን ደግሞ ቀሪውን "ሰው አምላክ ሆነ"ን እንኖራለን፡፡ እግዚአብሔር በፍቅር ሰው ሆነ ብለን እንጀምርና፤ እኛ ደግሞ በእግዚአብሔር ውስጥ እንሆናለን ስንል ተዋሕዶን በሕይወት እንገልጻለን፡፡ ይህንንም ሕይወት "ክርስትና" እንለዋለን፡፡

   ከላይ በተቀመጠው ቃልም ላይ ጌታ የተናገረው ይህንን ነው፡፡ "በእኔ [ከአምላክ ጋር በፍቅር አንድ በሆነ ሰውነት] ላይ አንዳች የለውም" አለ፡፡ "አንዳች የለውም" ማለት ክፉው ምንም ውጊያ አይከፍትም እንዲሁ አርፎ ይቀመጣል ማለት ሳይሆን፤ ምንም አይነት ፈተናና መከራ ቢያደርስ ማሸነፌ የተረጋገጠ ነው፥ እኔ ላይ የሚያስቆጥረው አንድስ እንኳ ድል  አይኖረውም ማለት ነው፡፡ (በእኔ ላይ አንዳች የለውም የሚለውን ቃል በጥሬው በማየት፤ ሰይጣን ክርስቲያኖችን ሊያስጨንቅ ሥልጣን የለውም፤ ምንም ሊያደርገን አይችልም ብለው የሚናገሩ አሉ፡፡ እህሳ ክርስቶስ ከውልደት እስከ ሞት ያሳለፈው ስደትና ፈተና ምንድር ነው? በዚህ ምድር ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ማለቱ "የዓለሙ ገዢ" የተባለ ዲያቢሎስ ነፍስን ሁሉ ለማሳት ስለመታገሉ አይደለምን?)

   እግዚአብሔር በፍቅር ሰው የሆነበትን ተዋሕዶ፤ እኛ ደግሞ እርሱን በመምሰል ሃይማኖታዊ መንገድ በመራመድ የቃልን ሥጋ መልበስ ለዓለም እንተረጉማለን፡፡ እኛ እርሱን ወደ መምሰል አንድነት ከፍ እያልን የምንወጣበት ደረጃ ታዲያ ፍቅር ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ እኛን ለመሆን ከላይ ወደ ታች የወረደበት ደረጃ ይኸው ፍቅር ስለሆነ (አንድ መመላለሻ ነው ያለው)፡፡

   ስለዚህ በመንፈሳዊ ኑሮ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ በመሆን ሂደት ያመንነውን ተዋሕዶን የምንኖርበት ትክክለኛው መግፍኤ ፍቅር ነው፡፡ ከፍቅር ተነሥተን ከእግዚአብሔር ጋር ስለመሆን ስንጸልይ፣ ስንሰግድ፣ ስንጾም፣ ስንቆርብ እንደተነገረን ዲያቢሎስ ሊቃወም ቢመጣም፤ በኛ ላይ አንዳች የለውም፡፡

   ነባራዊ ችግርን ብቻ ማዕከል ያደረገ መፍትሔ ፍለጋ የፍቅርን ቦታ ተክቶ የያዘብን እኛ፤ እግዚአብሔርንና ሰውን ከነፍስ በመውደድ ውስጥ ሆነን መንፈሳዊ ውጊያን ስለማንጀምር፤ ዲያቢሎስን በተለያዩ የእምነት ጦር ዕቃዎች እየቀጠቀጥነውም ቢሆን በእኛ ላይ አንዳች [ውጤት] ማስመዝገቡን ቀጥሏል፡፡ (አንቀጹ ቢያንስ ሁለቴ ይነበብ!)

   ክፉው መንፈስ ከሰው ልጆች (በተለይ ከዚህ ትውልድ) በእጅጉ የተሻለ የጽናት አቅም አለው፡፡ አዳማዊያን ለ8 ቀን በርትተው ያለመነዋወጽ ጽድቅን ለመኖር በጣም ሲቸገሩ፤ መናፍስት ለ8 ሺህ ዓመታት ያለ አንዳች መወላወል ርኩሰትን ሲሠሩና ሲያሠሩ ከርመዋል፡፡ እንግዲያውስ የቱን ያህል ጠንክረን ብንፋለመው፤ ጊዜ ጊዜን በተካ ቁጥር እየላላን እየላላን መሄዳችን የሥጋ ተፈጥሮአዊ ድክመትም ጭምር ስለሆነ፤ በወደፊተኛው ቀን ላይ ከኛ የበለጠ ጉልበት ያለው ባላጋራችን ነው፡፡ የሕይወት መመሪያው እንዲል፦ "ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።" (የማቴዎስ ወንጌል 6፥34)

   ቀን የራሱን ክፋት ይሸከማል፡፡ ዛሬ ወደ ነገ ሲሻገር ከነበረበት ክፋት ላይ ሁለተኛ ይጨምራል፡፡ ይህንን ገለጻ በዲያቢሎስ የባሕሪይ በር ገብተን ብናስተውለው፤ ጠላት ብርቱ ክፋቱ የማይበርድለት አጥፊ በመሆኑ፤ ከዛሬ ነገ በክፉነቱ እያደገና እየበለጸገ ነው የሚሄደው፡፡ እናሳ ነገ የሚጠብቀን ተጨማሪ ስልቱን ያዘመነና ከስሕተቱ የተማረ የዲያቢሎስ ውጊያ ነው፡፡

   ይሄ በነገዎች ላይ እየጨመረ ጸንቶ የሚቀጥል ክፋት የሚሸነፈው፤ ክርስቶስ "በእኔ" ያለውን የተዋሕዶ ኃይል አሁን ስንኖረው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር ስንጣበቅ!

   ፍቅር የጎደለበት፥ ምክንያት የነገሠበት መንፈሳዊ ሕይወት ከነገ ወደ ነገ እየተንሸራተተ እንዲወርድ ከፍ እያሉ ዳገት የሚሠሩት የዲያቢሎስ የማያባሩ ፈተናዎች ያስገድዱታል፡፡ ፍቅር የሌለበት የጽድቅ መስመር በመናፍስት ክብ አዙሪት ተሸከርክሮ ዞሮ ከተነሣበት ነጥብ ላይ ይመለሳል (ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም የፍልሚያው ቅርጽ አንድ አይነት መስሎ እንዲታየን ሆኖ፤ በየዕለቱ ከአምላክ ኃይልና ጸጋ ጋር ለመሆን ከመጣራችን ክትትል የተነሣ ማደጋችንን፣ መለወጣችንን፣ መማራችንን ሳናጤነው እየሰለቸን እንሄዳለን)፡፡ ፍቅር የታጣበት "የሰው አምላክ ሆነ" ክርስቲያናዊ ተዋሕዶ፤ ልዩነትን የሚፈጥር እንግልት በገጠመው ቁጥር ከእግዚአብሔር አንድነት እየተሰነጠቀ ይመጣል፡፡ (ይሄ አንቀጽ ተደጋግሞ ይነበብ!)
   እዚህ ጋር ስለ አንድ የመናፍስት የጥፋት ዘዴ ስናወራ፤ "ሰው አምላክ ሆነ"ን ለመኖር (በተግባራዊ የክርስትና ሕይወት ለመመላለስ) የሚፈቅድ ስብዕና [ቢያንስ በቀላሉ] እንዳይኖረን፤ ክፉዎቹ በባሕሪያችን ውስጥ አስቀድመው ስፍራ ለመያዝ ዛር ሆነው አብረው ከማኅፀን ጀምሮ ተመሳስለው በመወለድ፤ ተዋሕዶ ማለት በምድር እርምጃ ሰማያዊ መንገድን የመሄድ የፍቅር ጉዞ መሆኑን እንዳንረዳ ይከላከላሉ፡፡ እንዴት ነው የሚከላከሉት ስንል፤ አንድ ግለሰብ ከልጅነቱ አንሥቶ የእርሱ ብቻ በመሰለው ጠባዩ ውስጥ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ነገር የሚሸሽ ሆኖ ሲያድግ፤ በሥጋዊ የሕይወት ጎን አጋድሎ የቁስ አቅጣጫዎችን ብቻ በመከተል ሃይማኖቱን ከባሕል ማክበሪያት በዘለለ ሳይጠቀምበት ረጅሙን ዕድሜ ያቃጥለዋል፡፡

   በእንዲህ አይነት የሕይወት ገጽ ታሪኩን እያሰፈረ የመጣ ሰው፤ በኋላ ላይ ስለ ክፉ መናፍስት አሠራርና ሚስጢራዊ ውጊያ መረጃ አግኝቶ ቢነቃም እንኳ፤ ማንነቱን ገንብቶ የሠራ ባሕሪው ውስጥ ያለ ልምዱ የእግዚአብሔርን ፍቅር ከማወቅ ተነጥሎ ስለቆየ፤ ስውር ባላንጣዎቹን በመዋጋት ጊዜ ሳለ ክፉዎቹ ከዛሬ ነገ እየበረቱ እርሱ ግን እየደከመ መሆኑን ሲያይ ተስፋ ቆርጦ እጅ መስጠት ሰፊ ዕድሉ ይሆናል፡፡

   ነገ የሚጨምሩ የቀን ክፋቶች በኛ ላይ አንዳች እንዳይኖራቸው ወደ ተዋሕዶ አንድነት በፍቅር በኩል ማደግ ያስፈልጋል፡፡

   ቀደም ሲል እንደተነጋገርነው "በእኔ ላይ አንዳች የለውም" ማለት "ስለ ፍቅር በፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር አንድ በሆነ ሰውነት ላይ ዲያቢሎስ ማሸነፍ አይቻለውም" ማለት ነው ተባብለናል፡፡ የማቴዎሰ ጽሕፈት እንደነገረን ደግሞ በየቀን ዘወትሮች ላይ ዲያቢሎስ በክፋት አንዳች ለማድረግ መጣሩን ጸንቶ ይቀጥላል፡፡ በሌላ አገላለጽ "እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" ወደሚለው የተዋሕዶ ከፍታ እንዳናድግ ጠላት ለደቂቃ ሳይተኛ ሴራ ይጠነስሳል፡፡ ከዚህም የተነሣ ነገ ላይ እርግጠኛ ሆኖ የሚጠብቀን ጉዳይ የክፉው መንፈስ ወጥመድ ነው፡፡

    ታዲያ መድኃኒታችን "በእኔ ላይ አንዳች የለውም" ሲለን "ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር የተሳሰረ ሕይወት እስካላችሁ ድረስ የጠላታችሁ ፈተና ባያቋርጥም፤ በእናንተ ላይ ድል ተቀዳጅቶ የአሸናፊነት ጽዋን አይጠጣትም" የሚል ውድ መልእክትን እያስተላለፈልን ነው፡፡ ጥርት ያለ ምስል እንዲኖረን አንድ ምሳሌ እንሳል፡፡

   ከእግዚአብሔር ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ቆመናል፡፡ ከጀርባችን ደግሞ ዲያቢሎስ ከኋላችን ትይዩ በሆነ አንጻር ቦታ ላይ ሆኖ ከፈጣሪ መዳፍ ሊለያየን ወደኋላ ይጎትተናል፡፡ ባላጋራው ስቦ ስቦ ከእግዚአብሔር ነጥሎ እንዳያስቀረን ልንታገልበት የምንችለው አማራጭ የጨበጥነውን እጅ አጥብቆ በኃይል መያዝ ነው፡፡ ዲያቢሎስ ዛሬ የጀርባ ጉትታው እንዳልተሳካለት ሲያይ፤ ነገ ደግሞ በግራ ጎን በኩል መጥቶ ሊለያየን መጎተቱን ይቀጥላል (ነገ ሌላ ክፋት ነው ያለው ተብሎአላ)፡፡ እኛም የያዝነውን እጅ አጥብቀን እንደጨበጥን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ከነገ ወዲያም እንዲሁ አቅጣጫ ተቀይሮ በቀኝ በኩል እንጎተታለን፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ስበት ላይ ከእግዚአብሔር ሳንለይ አያይዞ የሚያቆየን ብቸኛው ሥራችን ታዲያ፤ የያዝነውን እጅ ላለመልቀቅ ወስኖ እንደጨበጡ መቅረት ነው፡፡ (እጀ መንገዴን የምጽፈው፤ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ ሊያሳልፈን ያስፈለገበት አንዱ ጽንሰ አሳብ ይኸው ነው፡፡ መናፍስት በየቀኑ ስልት እየቀያየሩ በጎተቱን ቁጥር፤ የያዝነውን የመለኮት መዳፍ ላለመልቀቅ የምናደርገው ጥረት አዳዲስ ብርታቶችንና የፍልሚያ እውቀቶችን እያስተማረን ይሄዳል፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ናቸው በጊዜ ውስጥ ከትንሹ ወደ ትልቁ እየተሰበሰቡ "ለውጥ" የሚሆኑት)

   ስዕሉን በውጊያ ቋንቋ ስናብራራው፤ መናፍስት በየዕለቱ አዳዲስም ሆነ ነባር የውጊያ ስልቶችን እየለዋወጡ በየቀኑ አንዳች ክፋት ሊያደርጉብን ጥርስ ነክሰው ይፋለማሉ (ባሕሪያቸው በየጊዜው የርኩሰት ጽልመቱን እያደመቀ እያመደቀ እንደሚሄድ ልብ ይሏል!)፡፡ በዚህ ውስጥ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት (የምንጨባበጥበት) የመንፈሳዊ ልምምድ ኃይል የፍቅር ጉልበት ከሌለው፤ ከዛሬ ነገ በሚብስ መከራ በተፈተንን ቁጥር የጨበጥነውን እጅ እየለቀቅን፤ "ሰው አምላክ ሆነ"ን በመኖር ተዋሕዶአችን መካከል ላይ ነፍስ እየገባ፤ ክርስቶስን ለመምሰል የምንከተለው ጎዳና ዕንቅፋት የበዛበት ረጅም እየመሰለ፤ የእምነት ኑሮ ራሱን የቻለ አሰልቺና የጣር ሥራ እየሆነ፤ ይሄድ .. ይሄድና በመድረሻው ላይ ተሸንፈን ቁጭ እንላለን፡፡ አሁን ከዛ አስከትሎ የዓለሙ ገዢ "በእናንተ ላይ አንዳች አለኝ"ን በስኬት ይዘምራል፡፡

(የተሰመሩባቸውን በማስተዋል አንብቧቸው‼️ በነገራችን፥ መናፍስት አብረው ሲያነቡ የትምህርቱን ሙሉ አሳብ በሚገባ ስለሚረዱ፤ በጣም አንኳር የሆኑ መረጃዎችን ካለማጤን እንድናልፋቸው አእምሮን ያስቸኩላሉ አሊያም ይጋርዳሉ፡፡ ስለዚህ ነው አስፈላጊ ቃላት ላይ በማስመር ይህ ተንኮላቸው እንዳይሳካላቸው የሚጣረው)

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
1•  ፍቅር     1.3•  ፍቅር ከሌለ ምን የለም? ክፍል - ፭ ✞ ዲያቢሎስ አንዳች አለው ✞    መንፈሳዊ ውጊያ ብለን የምንሰይመው በቅዱስና በርኩስ መንፈስ መካከል ያለ ጦርነት ከአጠራሩ ብቻ ለመገንዘብ እንደሚያስችለው የፍልሚያው አጠቃላይ ገጽታ ከዓይን የተሰወረ ረቂቅ ነው፡፡ በግዙፍ ሥጋ አእምሮና አካል የውጊያውን መልክ መረዳት በፍጹም አይቻልም፡፡    ከመንፈሳዊና ከሥጋዊ ባሕሪያት ውሕደት…
1•  ፍቅር

   1.4•  ፍቅር እንዲኖረን ምን እናድርግ?

ክፍል - ፮

   ፍቅርን ያስጎበኘን ጉዞአችን እነሆ ወደ ማብቂያው መዳረሻ ደረሰ፡፡ ከተሳፈርንበት ልንወርድ ነው፡፡ ወደሚቀጥለው ኬላ ለመሻገር ተቃርበናል፡፡ ከፍቅር ምዕራፍ ብንወርድም፤ ከፍቅር ግን አንወርድም፡፡ ፍቅርን መነሻችን (መሠረታችን) ያደረግነው ስለዚህ ነው፡፡ ይዘነው ስለምንቀጥል፤ በሌሎቹ ውስጥ ፍቅር ስላለ፤ ሌሎቹም በፍቅር ውስጥ ስለሚኖሩ፤ ፍቅርን በሄድንበት ሁሉ ይዘነው እንዞራለን፡፡

   ፍቅር ምንድነው አልን፤ ፍቅር ካለ ምን አለን ብለን መረመርን፤ ፍቅር ከሌለን ምን የለንም ስንል የሌለንንም አየነው፡፡ አሁን በመድረሻው ቦታ ላይ ፍቅር እንዴት ይኑረን ብለን እንጠቀልላለን፡፡

                ✞ ፍቅርን ከነፍስ መሳብ ✞

   ክፍል ፩ን እናስታውስ፡፡ ፍቅር መልካችን ነው፡፡ የነፍስ ባሕሪያችን፡፡ እግዚአብሔርን የመሰልንበት መለኮታዊ ውበታችን፡፡ ፍቅርስ የት ይገኛል ቢሉ አምላክ "እፍ" ብሎ ከኛ ባሳደረብን እርሱነቱ ውስጥ ይገኛል፡፡

   እንግዲህሳ ያለን ነገር ካለበት የምናነሣው ካለበት ቦታ ላይ ነው፡፡ በሌላ አባባል ፍቅር እንዲኖረን ምን እናድርግ የሚለው ጥያቄ የሚመለሰው ወደ ነፍስ በመዝለቅ ነው፡፡ የነፍስን ሥራ በባሕሪይም በአካልም በመሥራት፡፡ መንፈሳዊነት!

   የነፍስ ባሕሪይ ወደፊተኛው ገጽ ወጥቶ በሥጋ ባሕሪይ ላይ መነበብ ሲችል፤ ፍቅርም በዛ ውስጥ መገለጥ የሚችልበትን ዕድል ያገኛል፡፡ በሥጋ ባሕሪያትና ምግባራት እውነተኛ ፍቅርን (ከፍቅር አንጻር የሚቆም ፍቅር መሳይ ጥላቻ እንዳለ አንርሳ - ሐሳዊ መሲሕ) መኖር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የፍቅር ምንነትና ኃይል ታትሞ የተቀመጠው ነፍስ ላይ ነው፡፡

   "እግዚአብሔር ፍቅር ነው" ብለናል፡፡ ስለዚህ ፍቅርን የምንኖረው ወደ እግዚአብሔር በሚያስከትሉ መንፈሳዊ አቅጣጫዎች ስንመራ ነው፡፡ በአጭሩ ነፍስ ውስጥ ያለች ፍቅርን ወደ ሕይወት ለማምጣትና ለመግለጥ፤ የነፍስ ሥራዎችን ዶማ (ሌላም መቆፈሪያ ይቻላል) አድርገን ሥጋን (ሥጋ አፈር ነው) ፍቅር እስኪወጣ ድረስ መቆፈር አለብን ነው፡፡

   ፍቅርን የማግኘት ርዕስ የያዙ መንፈሳዊ ፍለጋዎችን ማከናወን፤ ከባሕሪያችን ውስጥ ያለች ፍቅር እንድትገለጽና እንድትታወቀን የማድረጊያው ፍጹሙ መንገድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ስለማግኘት ርዕስ (ልዩ ጉዳይ) ሰጥቶ መጸለይ፣ መስገድ፣ መጾም፣ መቁረብ፣ መመጽወት፣ ወዘተ... ከሰማይ ያለው ሁለንተናው ፍቅር የሆነው የመለኮት ባሕሪይ ነፍሳችንን እንዲያነቃት ያደርጋል፡፡

   እጅግ ብዙዎቻችን ችግራችንን ስለተመለከተ ጉዳይ እንጸልያለን፡፡ "ፍቅርህን ስጠኝ" የሚል የጸሎት ርዕስ ግን የለንም፡፡ እንኪያስ ያ የጸለይልነት መሰናከል ሲያልፍ፤ ሌላኛው ደግሞ ይጠብቀናልና አሁንም ለሌላ ችግር እንጸልያለን፡፡ በዚህ አይነት መከራዎችን የመቅረፍ ዓለማ የተያዘ መንፈሳዊ ሂደታችን ታዲያ፤ ወደፊት እየነጎደ በተጓዘ ቁጥር የችግሮቹ መደራረብና የማያልቁ መሆን፤ የእምነት ኑሮ እንዲመረን ያስገድዱናል (ብዙው አማኝ ስለ እግዚአብሔር ሲያወራ ችግርን አብዝቶ ምስጋናን እንዳይቀር ያህል አስገብቶ የሚያወራው ለዚህ ነው)፡፡

   ሌሎቹንም መንፈሳዊ ሥራዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር ከማግኘት ጋር አያይዘን አንከውናቸውም፡፡ ሰይጣን እንዲቃጠል እንጂ አንጀታችን በፈጣሪ ፍቅር እንዲቃጠል አንሰግድም፡፡ የጾም ጊዜ ስለመጣ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲመጣልን አንጾምም፡፡ ከችግር እንዲያወጣን እንጂ ወደ ፍቅሩ እንዲያስገባን አንቆርብም፡፡ ዲያቢሎስ እንዲደክም እንጂ ሕልውናችን ስለ ፍቅር እንዲደክም አንበረታም፡፡ ሕመማችን እንዲፈወስ እንጂ ፍቅርን አለማፍቀራችን እንዲፈወስ አልጣርንም፡፡ በረከት ማጣታችንን እንጂ መልካችንን ማጣታችን አልታየንም፡፡

   (አስተውለን እናንብባትማ) የአምላክ ፍቅር እንዲኖረው የሚጸልይ ሰው ግን እግረ መንገዱን ስለ ችግሩ መፍትሔ እየጸለየ ነው፡፡ እንዴት?... ፍቅርን ጠይቆ የተሰጠው ምዕመን ጠንካራ እምነትን ይወልዳል፡፡ ብርቱ እምነት ያለው ሰው የማይደነግጥና የማይናወጽ ተስፋ አለው፡፡ ፍቅር፣ እምነትና ተስፋ ያለው ደግሞ ሃይማኖት አለው፡፡ ሃይማኖት ሲኖረን ደግሞ የሚሳነን?... የለም! (የማቴዎስ ወንጌል 17፥20)

   ባለፉት ክፍሎች ላይ "ፍቅር አልፋ ነው ፍቅር ዖሜጋ ነው" ስንል አንስተን ነበር፡፡ ፍቅር መነሻ ነው ፍቅር መድረሻ ነው ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትንም ለመጀመር ስንነሣ፤ በመንፈሳዊ ምግባራት በኩል ፍቅርን ለመጨበጥ ስንቀሳቀስ፤ አልፋ የሆነ ፍቅር ወደ ዖሜጋነቱ በመድረስ ባሕሪይው እየመራ ራሱን ፍቅር ለማግኘት የተጠቀምንባቸው መንፈሳዊ ምግባራቶቻችን ጸንተው እንዲቀጥሉ ኃይል የሚሆን ልዩ ጉልበትን ይሰጣል፡፡ /ፍቅርን ስለማግኘት አስቀድመን ስንጸልይ፤ በጸሎት የመጣቺው ፍቅር ደግሞ እንድትመጣ የጠራት ጸሎት እንዳይቋረጥ በማድረግ ውለታዋን ትመልሳለች ነው የአንቀጹ አሳብ/

  ስለ ፍቅር መጸለይ፣ ስለ ፍቅር ማልቀስ፣ ስለ ፍቅር መስገድ፣ ስለ ፍቅር መጾም፣ ስለ ፍቅር መ'ሳል፣ ስለ ፍቅር ሱባዔ መያዝ፣ ወዘተ... ፍቅርን በትክክለኛ ሁኔታ ገንዘብ የማድረጊያ ጎዳና ነው፡፡ ፍቅር በነፍስ ውስጥ ተቀርጻ ያለች የፈጣሪ አካል እስከሆነች ድረስ፤ ከነፍስ እንድትወጣና ኑሮአችንን እንድትመራ በር መከፍት የምንችለው በመንፈሳዊ ምግባራት በኩል ነው፡፡ ፍቅርን ስለ ማግኘት የሚያነሣ ርዕስ ለብቻው አስቀምጠን፤ የርዕሱን ሐተታ በመንፈሳዊ ሥራዎች በመታገዝ መተንተን ኃይል ከአርያም ሰማይ እየተለቀቀ ማንነታችን ውስጥ የተጻፈች ፍቅር እንድትነበብ ያደርጋል፡፡

              ✞ ቃለ እግዚአብሔርን መከታተል ✞

"ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፥5)

   ወደ ዓለም የመጣነው ከእውቀት ዛፍ በልተን ነው፡፡ ይህም ማለት ከፀሐይ ሥርዓት በታች የምንኖረው የምድር ሕይወት ወደድንም ጠላንም በማወቅና ባለማወቅ መካከል ላይ ይባትታል፡፡

   ፍቅርም በማወቅ ላይ የሚመሠረትበት ሁኔታ አለው፡፡ በአእምሮ እውቀት ግን አይደለም፡፡ አእምሮ የሥጋን ነው የሚያውቀው፡፡ የሚጨበጠውን፥ የሚረጋገጠውን ነው ሊመረምር የሚችለው፡፡ ከዚህ የተነሣ ፍቅርን በስሌት፣ በልኬትና በቀመር አይደርስበትም፡፡ ፍቅር በልብ (ልብ በነፍስ ሥራ መጠራትን አስለምዳለች) እውቀት ይታወቃል፡፡

   በልብ የምንማረውና የምንገነዘበው እውቀት ደግሞ የሚዳሰስና የሚታይ ግዙፍ አይደለም፡፡ ረቂቅ ነው፡፡ ለምሳሌ መናፈቅን በአእምሮ አንማረውም፡፡ ናፍቆት የልብ ጉዳይ ነው፡፡

   እግዚአብሔርን የምናገኘው በልብ ነው፡፡ በአእምሮ ፈልገው ያጡት "የለም" ብለው ደምድመዋል፡፡ "ከዝንጀሮ ነው የመጣነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡ መጽሐፍ ስለነርሱ ይመልሳል፦ "ጥበበኞች እንሁን ሲሉ ደንቆሮዎች ሆኑ"፡፡ በአእምሮ መሄድ እንዲህ ነው፡፡ ሐሰትም ይሁን እውነት በማስረጃ ይደገፋል፡፡ ጨብጦ በማረጋገጥ ያምናል፡፡ በአጭሩ ምክንያታዊነትን ይፈልጋል፡፡ ምክንያት ደግሞ የፍቅር ጸር ነው፡፡ ምክንያት ሚዛኖች አሉት፡፡ ሰፍሮ፣ መጥኖ፣ ለክቶና ቆጥሮ ነው የሚስማማውን የሚቀበለው፡፡ ምክንያታዊነት ውስጥ ፊቷን አዙራ የተቀመጠች ጥቅም አለች (አዟዟሯ እንደ ኵነቱ ይለያያል¡)፡፡ ፍቅር ይሄን ሒሳብ አያውቅም፡፡ መጠቀም አለመጠቀሙን አይለካም፡፡ በቃ ዓለምን "እንዲሁ" ይወዳል፡፡
   ቃለ እግዚአብሔርን በአእምሮ ያይደለ በልብ መማር ወደ ፍቅር መልክ ያደርሳል፡፡ ሰፊ ጊዜን ሰጥቶ የአምላክን ቃል ከአንጀት መማር ፍቅርን ያሳድጋል፡፡ ለምን ቢሉ..."የእግዚአብሔር ቃል" በራሱ ፍቅር ነውና፡፡ እርሱ ሥጋ ለብሶ በዓለም ላይ የፍቅር ድምፆችን (ወንጌል) እንዳሰማ ሁሉ፤ ድምፁን ከእውነት በሰማን ጊዜ ፍቅርነቱ ከውስጣችን ሥጋ ይለብሳል፡፡ በአሳብ፣ በእቅድ፣ በድርጊት፣ በአኗኗር ውስጥ ዘልቆ ይገለጻል፡፡ ቃሉ "መንፈስና ሕይወት" ነው፡፡
  
                    ✞ በሌሎች ጫማ መቆም ✞

   የእግዚአብሔርን ፍቅር ከላይ በተገለጹት ሁለቱ መንገዶች እያገኘን፤ ይሄንን ፍቅር ደግሞ ሰዎች ላይ በመተረጎም የተጨባጭነት አቅሙን ማሳደግ ግድ ይለናል፡፡ ምክንያቱም "ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥20)

   "ስጠኝ" ያለውን ፍቅር ለሌሎች "መስጠት" ፍቅርን ከነበረው ደረጃ ላይ የማሳደጊያና የማበልጸጊያ መንገድ ነው፡፡ ተወዳጁ ሲያስተምር "ስጡ ይሰጣችኋል" ብሎ ለተማሪዎቹ የነገራቸውም ጉዳይ ይህንን ነው፡፡ ፍቅርን ስጡ፥ ፍቅርም ይሰጣችኋል፡፡ (የሚሰጣችሁ ግን የሰጣችሁት አካል ላይሆን ይችላል)

   ለሌሎች መስጠት እንዲቻለን ደግሞ በሌሎች ጫማ ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ጉድለት ለመሙላት በሰው ጉድለት መጉደል ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ውድቀት ለመውደቅ "ይህ ወድቀት በኔ ደርሶ ቢሆን" ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ችግር ለመቸገር "ይህ ችግር በኔ ደርሶስ ቢሆን" ብሎ ማሰብ ያሰፈልጋል፡፡ የሰው ሐዘን ለማዘን የራስን ያለፈ ሐዘን እያሰቡ የአሁንን ስሜት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በወገኑ ቦታ ላይ ራሱን እያስገኘ የማያምሰለስል ሰው እንደምን አድርጎ ፍቅርን መስጠት ይችላል?

   ዛሬ ዛሬ ላይ ዓለማችን በተለይ በዘፈኑና በፊልሙ ላይ ያሰለጠነቺን ፍቅር ዝሙት ተኮሩን የጾታ ግንኙነት ብቻ ነው፡፡ የመዝናኛው ዘርፍ በልብ በተወከለ ሽፋን ተጽዕኖ የሚያደርሰው አእምሮ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው በቁንጅና፣ በሐብትና በቁስ የተመሠረተ የጾታ ፍቅርን ትንሽ ደግነት ለውሶ የሚያሳየው (እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ከሌሉ የመዝናኛው ኢንደስትሪ ቀጥ ይላል)፡፡

   ይሄንን የመዝናኛውን ዘርፍ እንደወረደ የጋተው ትውልዳችን፤ ፍቅር ማለት በሌሎች ጫማ ውስጥ ሆኖ መራመድ ሳይሆን በራስ ምቾት ልክ ሌላውን መስፋት አድርጎ፤ መሙላት የሚገባውን ጉድለት ሸሽቶ ሁሉም ውበት ያለውን፣ ሐብት ያለውን፣ ዝና ያለውን ይፈልጋል፡፡ ፍቅር ወደታች መውረድ ሆኖ ሳለ፤ ፍቅርን ፍለጋ ወደላይ ይወጣል፡፡ በዛ ከፍ ባለበትም ቦታም ላይ በፍቅር ስም የሚነግደውን የዓለም ሥርዓት ያገኛል፡፡ እርሱም እንዲህ ብሎ ይመክረዋል "እየመረጥክ ስጥ!"

            ✞ ፍቅርን የሚዋጋ ባሕሪይ መታገል ✞

   ዲያቢሎስን ኃያል እምነት አያስፈራውም፡፡ እርሱም ራሱ አማኝ ስለሆነ፡፡ (የያዕቆብ መልእክት 2፥19)

   ባይሆን በፍቅር ያለች ጥቂት እምነት ታስጨንቀዋለች፡፡ በሰው ልጆች ማመንና በርኩሳን መናፍስት ማመን መካከል የተሰመረው ብቸኛ ድንበር ፍቅር ነው፡፡ እኛ አፍቅረን ማመን ስንችል፤ መናፍስት ጠልተው ነው የሚያምኑት፡፡

   ስለዚህ ዲያቢሎስ ካሉት ባሕሪያችን ውስጥ አትኩሮ የሚዋጋው ፍቅርን ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ጠቅለል ያለው የፍልሚያ ይዘት ይሄ ነው፡፡ የሙሴን አምላክ የሰቀሉት አይሁዳውያን ሙሴን ያምኑ ነበረ፡፡ ፍቅር ግን ጭራሹኑ አልነበራቸውም፡፡

   ይሄ በክርስቶስና በአሳዳጆቹ መካከል ያለው ውጊያ፤ በክርስትና መንገድ ላይ በሚጓዙ ምዕመናን ላይ የዘመኑን ገጽታና ቅርጽ እየዋጀ እስከ ዕለተ ምፅዓት ይቀጥላል፡፡ እኛም በስሙ የተጠራን ክርስቶሳውያን ስንሆን፣ ይሄ ውጊያ በባሕሪያችን ተጽፎ ይቀመጣል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ በቤተመቅደስ ውስጥ ያሉ ሰዎች እውነተኛውን ቤተመቅደስ ሊያፈርሱ እንደታገሉ፤ ቤተመቅደስ የተባለ ሰውነታችን ውስጥ የሚያደፍጡ መናፍስት የቤተመቅደሳችንን መልክና መሠረት (ፍቅር) ሊያፈርሱ ይታገላሉ፡፡ ይሄ ፍትጊያ ወደ ውጪ ሲገለጥ፤ በስሙ የተጠሩ በቤቱ ያሉ ሰዎች ፈተና ይሆኑብናል፡፡ (በቤተክርስቲያንም ብናይ፥ ሴቲቱን ለማዳከም የሚሮጠው ኃይል ከውጪ ይልቅ የውስጥ ልጆቿን ይጠቀማል)

   በመሆኑም በባሕሪያችን ተመሳስሎ ገብቶ፤ ፍቅርን (የክርስቶስን ባሕሪይ) የሚዋጋ እኛነታችንን በተለየ ትኩረትና አቅም መፋለም ያስፈልገናል፡፡ ፍቅርን ለመስጠት በሞከርንባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ላይ ወደኋላ የሚስበንን ጠባይ (ክፉ መንፈስ) ለብቻው ለይተን በእምነት ጦር ዕቃዎች መቅጣት አለብን፡፡ ፍቅርን እንዳንኖር የተለያዩ የኑሮ ምክንያቶችን መደበቂያ የሚያደርገውን ጠላት ምሽግ ማፍረስ ይጠበቅብናል፡፡

-------------------
ከፍቅር የጀመርነው ዘመቻችን እዚህ ደርሷል፡፡ በቀጣይ ንስሐን የምናይበት መንገዳችንን እንጀምራለን፡፡ ለንስሐ ጉዞአችንም ፍቅር መነሻችን (አልፋ) እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ቀድሞውኑ ንስሐ ለመግባትም ፍቅር ያስፈልጋላ፡፡ በኃጢአት አጥፍቻለሁ ብሎ ለመጸጸት ምክንያት የሚሆነው ፍቅር ነው፡፡ ያለ ፍቅር ንስሐ እንግባ ብንል ኃጢአትን መዘገብ እንጂ መናዘዝ አይሆንልንም፡፡ ፍቅርን "አንድ ጊዜ አረፍ በል" ካላልነው ብዙ ያስወራናል፡፡ አስጀምሮ ላስፈጸመን ለፍቅር እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
2•  ንስሐ

   2.1•  ንስሐ ምንድነው?

ክፍል - ፩

    ✞ ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም ✞

   አዳምን ወላጅ ሆኖ ያስገኘ የሥጋ ማኅፀን የለም፡፡ ለመጀመሪያው የሰው ልጅ የመጀመሪያ እናትና አባት አልነበረውም፡፡ የአዳም እናቱም አባቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፡፡ አዳም የተጸነሰባት ማኅፀን የአምላክ ፈቃድ ነበረች፡፡

   ቀዳሚው የሰው ልጅ ከተጸነሰ በኋላ እስኪወለድ ድረስ በምቾት የኖረባት ስፍራ ዔድን ገነት ትባላለች፡፡ ልጅ ከእናት ማኅፀን ተወልዶ ዓይኑን በመግለጥ የመጣበትን ዓለም ለማወቅ እንደሚጀምር፤ የእውቀትን ዛፍ ገና ያልበላው አዳም በገነት ሳለ በእግዚአብሔር የፈቃድ ማኅፀን ውስጥ ነው የነበረው፡፡ ወይንም በቀላሉ ገነትን አዳምን አርግዛ እንዳለች አንዲት ነፍሰጡር በምናብ እንሳላት፡፡ የነፍሰጡሯ የእርግዝና ወራት (አዳም በገነት የሚቆይበት ጊዜ ማለት ነው) "በእግዚአብሔር አንድ ቀን በሰው ልጅ አንድ ሺህ ያህል ዓመት ነበር፡፡" (2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፥8)

   ሺህውም ዓመት ሲፈጸም (ስድስተኛውን ቀን ሲጨርስ) አዳም ከገነት ይወለዳል፡፡ ማለት በሰባተኛው ቀን ላይ የሰው ልጅ ከእውቀት ዛፍ በልቶ ዓይኑን በመግለጥ በወላጁ (በእግዚአብሔር) ክንድ ውስጥ ይታቀፋል፡፡ ወደ ቀጣዩ ሥርዓት ማደግ (መርቀቅ) ይጀምራል፡፡

   የቀደመው ወንዱ ልጅ በገነት መኖሩን እንደቀጠለ፤ በራእየ ዮሐንስ ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት ላይ የተጠቀሰው ዘንዶ ብዙ ነፍሳትን በልቶ ሳይወፍር በፊት "የቀደመው እባብ" ሳለ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ የቀደመቺው ሴት ፊት [አዳምን ሊበላ አስቦ] ቆመ፡፡

   ዘንዶው ከሰማይ ሥርዓት ከእግዚአብሔር እውነትና ፈቃድ በማፈንገጥ ወድቋል፡፡ በዚህም የተነሣ ውድቀት የክፉው መንፈስ ልዩ ማንነትና መገለጫ ባሕሪይ ሆኗል፡፡ ስለ መውደቅ ስናነሣ፤ ውድቀት ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ አይመለከተውም፡፡ ምክንያቱም ወደ ላይ አይወደቅም፡፡ በመሆኑም ዲያቢሎስ በመውደቅ ውስጥ ባለ ጠባይ ራሱን ስለሚገልጥ፤ የአሳቡም ሆነ የሥራው መነሻና መድረሻ ሕግ ሁልጊዜ ራሱንም ሌላውንም ወደ ታች መጣል ነው፡፡

   ከላይ በተጨዋወትነው መሠረት፤ የአዳም ሰብአዊ ባሕሪይ ከስድስተኛው ቀን ወደ ላይኛው ሰባተኛው ቀን በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ በማብራሪያ ግልጽ ለማድረግ፤ የሰው ልጅ መጀመሪያ የተፈጠረበት ሰብአዊ ተክለ ቁመና ሙሉ በሙሉ ሕያው በመሆንና ባለመሆን መካከል ቦታ ያለ ነበር፡፡ እናም የአዳም ባሕሪይ ከዚህ ከመካከል ላይ ተነሥቶ ፍጹም ሆኖ ወደ ሚቀጥለው ሥርዓት ወደ ሚረቅበት ልዕልና ለመሻገር ሺውን ዓመት በገነት ጨርሶ የሕይወትን እና የእውቀትን ዛፍ በየጊዜያቸው መብላት ያስፈልገው ነበር፡፡

   ሆኖም ውድቀትን በላዩ ይዞ የሚንቀሳቀሰው መንፈስ፤ የፍጡራን ከእግዚአብሔር ፈቃድ መውጣት ልክ እንደርሱ ወደታች መጣልን እንደሚያስከትል ከራሱ ስለተገነዘበ፤ "አትብላ!" ብሎ እግዚአብሔር ያለ ቀኑ እንዳይበላት የከለከለውን የዛፍ ፍሬ እንዲበላ "ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽ ከአጥንቴ" ባላት አካሉ በኩል አዳምን ገፋፋው (መንፈስ ከውስጥ ሲገባ ከገዛ አካላችን ጋር መፋለም የመሰለ ጦርነት ነው የሚከፍተው)፡፡ ያቀደውም ሆነለት፡፡ "አዳም ሆይ ከወላጅህ ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚስትህን ፈቃድ ለመፈጸም ወድደሃልና፤ ወደ መጣህበት መሬት ተመለስ፡፡ አፈር ነህና፤ ወደ አፈርም ትመለሳለህ" የሚል ቃል ከአምላክ ተደመጠ፡፡ የሰው ልጅ ሕልውና ወደ ሰባተኛው ቀን መርቀቅ ትቶ ወደ ኋላ ወደ አንደኛው ቀን (አፈር የተፈጠረው በመጀመሪያው ቀን ነው) በመመለሱ ምክንያት ዲያቢሎስ ውጥኑ ሰመረለት፡፡ ወደ ላይ ከማረግ ይልቅ እንደርሱ ወደታች መውደቅን አዳም በባሕሪዩ እንዲያውቀው አደረገው፡፡

   አዳም ከገነት (ከፈቃደ እግዚአብሔር) ወጥቶ ወደ መጣበት ምድር (የእግዚአብሔር አሳብ ወዳልነበረው) መሬት ሲመለስ፤ መቼም ጀርባውን ለአምላክ ፊቱን ለምድር ሰጥቶ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አዳም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ተለይቶ በመውጣት የሰው ፈቃድ ወዳመጣው ከፀሐይ ሥርዓት በታች በተወሰነ አኗኗር ውስጥ ገባ፡፡ የአዳምና የሔዋን ከገነት ተለይቶ መውጣት በአካል ብቻ የተከናወነ ሳይሆን፤ በባሕሪይም ጭምር የሚገለጥ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ በአዳም ባሕሪይ ውስጥ የተሰማው ሞት የሰውነትን ባሕሪይ በሚይዙት የአዳም ልጆች ላይ ሁሉ ይዋረሳል፡፡ በተለምዶ "የአዳም ኃጢአት" እየተባለ የሚነገረውም ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ስለዚህ አዳም በባሕሪይው ጭምር ነው ከገነት የወጣው ስንል፤ የአዳም ልጆች የሆኑት ሰዎች ሁሉ የሕይወት ገጻቸውን  ወደ መጡበት ምድር (ሥጋ) አዙረው፤ ለእግዚአብሔር ፈቃድና እውነት (ለነፍስ) ጀርባ ሰጥተው ከአምላካቸው ፈቃድ እየወጡ .. እየወጡ ይኖራሉ እያልን ነው፡፡

   ንስሐ የምንላት መንፈሳዊ ሚስጢርም የምትመጣው እዚህ አዳም ፊቱን ከእግዚአብሔር አዙሮ ከወጣባት ቅጽበት ጀምሮ ነው፡፡ የሰው ልጅ "እንደ አምላክ" በመሆን ከንቱ ምክር ተታልሎ ከፈጣሪው ከተጣላ በኋላ፤ አስታራቂ ማኅተም ሆና ከመሃል የምትገባው ረቂቅ ኃይል ንስሐ የምንላት የምሕረት ክፍል ናት፡፡

   ንስሐ የሚለው ቃል በጥሬ ትርጓሜው ጸጸት፣ ሐዘን፣ ቁጭት፣ ቅጣት፣ የኃጢአት ካሳ ማለት ነው (የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት)፡፡ ይህንንም ብያኔ ወደ አዳም ታሪክ መልሰን ስናየው፤ አዳም ከእውቀት ዛፍ በልቶ ራቁቱን መሆኑን ዓይኖቹን ገልጦ ባወቀ ጊዜ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፉ ከውስጡ ጠባይ የነቃ ፍርሃት፣ ባዶነት፣ ብቸኝነትና መገፈፍ ተሰምቶታል፡፡ እነዚህ ስሜቶች በኋላ እጅ ለእጅ ተያይዘው አዳምን ንስሐ ወደምንለው ቦታ አምጥተውታል፡፡ አዳም ባጠፋው ጥፋት ራሱን እየወቀሰ (ቁጭት)፤ ለምን በላሁት በሚል አሳብ እየተብሰከሰከ (ጸጸት)፤ ስላጣው ጸጋና ኃይል እየተከዘ (ሐዘን)፤ እግዚአብሔር ይምረው ዘንድ ለመጠየቅ ለረጅም ጊዜያት ራሱን እየገሠጸና እያለቀሰ ሱባዔ ይዟል (ቅጣትና የበደል ካሳ)፡፡

   እስከአሁን በተነጋገርነው መሠረት ላይ ሆነን ንስሐን ጠቅልለን ስናየው፤ ንስሐ ማለት የሰው ልጆች ባሕሪይ አቅጣጫውን አስተካክሎ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ጀርባውን ወደ ውድቀት የሚያዞርበት ሰማያዊ ሂደት ነው፡፡

   አንድ አማኝ ሰው ንስሐ ገባ ስንል፤ እርምጃውን ወደ እግዚአብሔር መንገድ አቀና እያልን ነው፡፡ በአዳምኛው ቋንቋ ስንናገረው፤ "ወደ መጣችሁበት ተመለሱ" ሲል ወደ ወደድነው የሥጋ ፈቃድ እንድንመለስ ምርጫችንን አክብሮ ለለቀቀን አምላክ፤ "የለም የለም ጌታ ሆይ፥ ተሳስቼ ነውና ወዳንተ (ወደ ነፍስ ፈቃድ) መመለስ እፈልጋለሁ" ብለን የምንናገርበት የተቀደሰ ድምፅ ነው፡፡

   በአንጻሩ ንስሐ አልገባንም ማለት፤ ፊታችንን ወደ ዓለም ጀርባችንን ወደ እግዚአብሔር ሰጥተን እየተጓዝን ነው ማለት ነው፡፡ ንስሐ ሳንገባ የነፍስ ፈቃድ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት እንኳ ቢኖረን፤ የእምነት አካሄዳችን ጀርባውን ለእግዚአብሔር እንደሰጠ ወደ እግዚአብሔር እንደመሄድ ያለ የኋልዮሽ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡ ፊቱን ለአውራ ጎዳናው ቀጥ አድርጎ መጓዝ ሲችል፤ ወደኋላ እየሄደ መንገዱን የሚያቋርጥ መኪናን ጥሩ ምሳሌ አድርገን ለዚህ እንጠቅሳለን፡፡

በእርግጥም ከንስሐ ራቅ ብሎ የሚገኝ ኑሮአችንን አጢነን ስናየው፤ ፍላጎቱን፣ እቅዱን፣ ሩጫውን፣ ጉልበቱንና ጊዜውን ለሥጋ ጉዳዮች አብዝቶ እያዋለ፤ ከተፈጥሮው ውስጥ ሕይወት ሆና ስለምታንቀሳቅሰው ነፍሱ ግን አጥርቶ ማስተዋል ተስኖት ይታያል፡፡ ይሄ መሬት የረገጠ እውነት ነው ፊትን ወደ ዓለም ጀርባን ወደ አምላክ የሚያሰኘው፡፡
   የሕይወት ጀርባችን ወደ እግዚአብሔር ሆኖ፤ ከአርያም መቅደስ ስለ ሰው ልጆች መዳን የሚለቀቀውን የቸርነት ብርሃን ማየት ስላቃተን፤ ታይቶ ሳይቆይ የሚጠፋውን የዓለምን ብርሃን ለመጨበጥ ስንል፥ መልሰን እናገኛቸው ብንል የማይቻል፥ ብዙ የዕድሜ ዓመታቶቻችንን አቃጥለናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ፊታችንን ያዞርንለት ብርሃን የተረጋገጠ ዋስትና አስይዞ፤ የመኖር ሕልውናችንን ሊያሳርፈውና ሊያረጋጋው አልቻለም፡፡

   እረፍት የተነፈገና መረጋጋት ያጣ ስብእና ደግሞ ሰላም የለውምውኃ ሲቀጥንም ሆነ ሲወፍር ይነጫነጫል፡፡ የሚፈልገውን አግኝቶም ሆነ አጥቶ ያኮርፋል፡፡ ከውስጣዊ አካሉ የሚደመጥ እፎይታ ተነፍጎ ዘወትር ይቅበዘበዛል፡፡ ከገንዘብ፣ ከውበት፣ ከእውቀት፣ ከሥልጣንና ከአቅም ውስጥ አደላድሎ የሚያስቀምጥ አንድ የሰላም ወንበር እየፈለገ ይኳትናል፡፡ ግን የለምአያገኝም፡፡

   ንስሐ ያልገባች ነፍስ፤ እነዛ በመጀመሪያ አዳም ጋር የተሰሙት ፍርሃት፣ ማጣት፣ ባዶነት፣ ብቸኝነት የተባሉ ስሜቶች ስለሚሰሟት፤ እነዚህን ለማፈን ሲባል በሥጋ ወከባ የሚምታታ ትንንቅ ውስጥ ትገባለች፡፡ ምንም አይነት ሥጋዊ ብልሃትና ሙከራ የነፍስን ክፍተት ይሞላ ዘንድ አይቻለውምና፤ ፍርሃቱ ወደ ጭንቀት፣ ማጣቱ ወደ ብስጭት፣ ባዶነቱ ወደ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቸኝነቱ ወደ ጣዕም አልባ ሕይወት እየተሸጋገረ፤ አድራሻ ጠፍቶት እንደሚባትት መንገደኛ ወዲህም ወዲያም እየተራወጠች ትንከራተታለች፡፡

   ነፍስ በባሕሪይዋ የእግዚአብሔር አካል ናትና፤ የሰው ልጅ ስብእና ሲፈጠር ይሄድ ወደነበረበት፥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ወደሆነው ከፍታ መርቀቅን ሁልጊዜ ትፈልገዋለች (የሞትን ነገር ውስጣችን የሚጠላብን ለዚህ ነው) ፡፡ ይህ ማለት ነፍስ ከስድስተኛው ቀን ወደ ሰባተኛው የእረፍት ቀን የመሻገር ስበት በረቂቅነቷ ውስጥ አለ፡፡ ከላይዋ ሆኖ ጀቡኖ የያዛት ሥጋ ግን ወደ መጣበት አፈር ለመመለስ ይፈጥናልና፤ ይሄ የሥጋና የነፍስ መስተቃርናዊ ሂደት የሚታረቀው፤ የሰው ልጅ ንስሐ በሚባል መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምር ብቻ ነው፡፡

   እንዲህም ከሆነ፤ ንስሐ ማለት ነፍስና ሥጋን በአንድ መንፈሳዊ ክር ሰፍቶ የሚያይዝ የምሕረት መርፌ ነው፡፡ በአካላችን ውስጥ የሚገኙ ሰማያዊና ምድራዊ ማንነቶችን አንድ ገጽ የሚሰጥ ልዩ መታወቂያ ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚጣሉ ሁለት ባሕሪያትን የሚያስማማ መለኮታዊ ሸንጎ ነው፡፡

 {ዓለም}  ☜☜ሥጋ   ነፍስ☞☞ ️ {እግዚአብሔር}
 {ዓለም} ☞☞ሥጋ  ️[ንስሐ]  ነፍስ☞☞ {እግዚአብሔር}
                 
   ሞትና ትንሣኤ ስለሚባሉትም ጉዳዮች እዚህ ጋር ማንሣት እንችላለን፡፡ ሞት በመንፈሳዊ ፍቺው ሲተነተን በአጭሩ የሥጋና የነፍስ መለያየት ማለት ነው፡፡ ከላይኛው አንቀጽ ባወጋነው አሳብ ስንመለከተው፤ የነፍስና የሥጋ የተለያየ ጉዞ የመጨረሻ ውጤት እንበለው፡፡ ከአፈር የተገኘው ሥጋ ወደ "አፈር ትመለሳለህ" የሚልን ፈቃዱን የተከተለ ውሳኔ ስለሰማ፤ ወደ ተፈጠረበት ምድር ባሕሪይው እየተጎተተ .. እየጎተተ ይሄዳል፡፡ ይሄ መቼም የማይቀር ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ሰው ሁሉ ወደ ሞት ይጓዛል፡፡

   ሰውን የቱን ያህል መንፈሳዊ ብርታትና ጽናት ይኑረው ወደ ሞት የሚገሰግሱበት የሥጋ ባሕሪያት ራሳቸውን የቻሉ ጾር እየሆኑ ያስቸግሩታል፡፡ ፍጹም የሆነው መለኮት እንኳ ሥጋ በተዋሐደው ጊዜ "መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው" ሲል የሥጋን ታላቅ መገዳደር አስታውቆአል፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 26፥41)

   በመጀመሪያው የማኅፀን ሥርዓት የሚወለደው ሥጋ ከፊቱ የሚጠብቀው ሞት ነው፡፡ ነፍስ የቱን ያህል ብትታገለውም የመፍረስን ሕያው ቃል በባሕሪዩ አንዴ ያደመጠው ሥጋ፤ በየዕለቱ ቀን በቆጠረ ቁጥር እየፈረሰ እየፈረሰ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል?

   ማኅፀኒቱ መለወጥ አለባት፡፡ የመጀመሪያቱ ሔዋን ከእባቡ ጋር በፈቃድ ተስማምታ ከእርሷ የሚወለደው ዘሯን ሁሉ ወደ ሥጋ ፈቃድ አንከባላ አስገብታዋለች፡፡ ስለዚህ ሌላ የአወላለድ ሥርዓት ያስፈልጋል .. መንፈሳዊ ማኅፀን!

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚያሳድደውን የአዳምን ባሕሪይ ገንዘብ አድርጎ በሥጋ የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ወደ ሞት እየገሰገሰ የሚሄደውን ሥጋ እስከ መጨረሻ ታግሦ ተከተለውና፤ ሥጋ በመስቀል ላይ "በቃ" ብሎ ሲጨርስ፤ መሞት የሌለበት መለኮት፥ የተዋሐደውን ሥጋ አዲስ ሥርዓት አሳየው፡፡ ከመቃብር አነሣው፡፡ ፈርሶ ከመቅረት ነጻ አወጣው፡፡

   ይህንን አዲስ የትንሣኤ ሥርዓት እኛ እንድናገኘው ደግሞ፤ ከጎኑ ደምና ውኃ ሆና ከወጣቺው አዲስቷ ሔዋን (ቤተክርስቲያን) ጋር ሰማያዊ ጋብቻ ፈጽሞ ከማይጠፋ ዘር ወለደን፡፡ አሁን ዳግም ከመንፈስና ከውኃ የሚወለድ ሥጋ፤ እንደ ቀዳሚው አዳም በሥጋ ማኅፀን ከመወለዱ የተነሣ ሞትን ቢቀምስም፤ ለሁለተኛ ጊዜ በተወለደበት ማንነቱ በኩል ግን ሞትን ድል አድርጎ ይነሣል፡፡ "አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር" ይሆናል፡፡ በትንሣኤ ነፍስና ሥጋ ስለማይለያዩ ሞት የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡

   እንኪያሳ ከዚህ ገለጻ አንጻር ደግሞ ንስሐ ማለት፤ ከሥጋ ፈቃድ የተወለደው ሥጋ ወደ ሞት እየገሰገሰ ከነፍስ ለመለያየት ሲቸኩል፤ ነፍስንም አራውጦ ይዟት እንዳይሞት (ኃጢአትን እንዳያትምባት) የሚከላከል ጠበቃ ነው፡፡ ሰው ንስሐ እየገባ ነው ማለት፤ በመሲሑ ድንቅ ሥራ አምኖ ዳግም የተወለደበት ሥርዓት እንዳይበላሽ እየጠበቀ ነው ማለት ነው፡፡

   "የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና"፤ ከፈጸመው ኃጢአት ለመላቀቅ ሲል ንስሐ የማይገባ ሰው፤ ዳግም ቢወለድም እንኳ ከፈቃደ እግዚአብሔር የመለየቱ መግፍኤ ከትንሣኤው በኋላም እንዲሞት ያደርገዋል፡፡ (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23) ስለዚህ ንስሐ የማይገባ ሰው "ሁለት ሞት" ይሞታል ማለት ነው፡፡ አንደኛ የሥጋ ባሕሪይን በመያዙ የሥጋን ሞት ይሞታል፤ ሁለተኛ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን ባለመፍቀዱ ምርጫው ተከብሮለት ቀደም ሲል አምላክን አልፈልግም ወዳለው ወደ ዲያቢሎስ ማደሪያ እንዲሄድ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ ለነፍስ ሞት ነው፡፡

   ነገሩስ ያለ ንስሐ የሚመላለስ ምዕመን፤ ሦስት ሞት ነው የሚሞተው፡፡ ንስሐ ማለት ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም አድርጎ የመጓዝ ሂደት ነው ብለን ጀምረናልና፤ ከንስሐ ሕይወት ተለይቶ የሚኖር ሰው በተገላቢጦሽ ፊቱን የሚያዞረው በቁም ወደ ምትገለዋ ዓለም ነው፡፡ በዓለም ውስጥ የመኖር ሕግ መንፈሳዊ ጠባያትን ይገላል፡፡ 'ለሥራው ዕድገት ስትል ዋሽ፣ ለትምህርት ስኬት ነውና ኮርጅ፣ ለገንዘቡ መጠራቀም ጉቦ ውሰድ፣ ብዙ ጥሪት እንዲኖር ለቸገረው አትስጥ፣ ደስታን እንዳታጣ የሰውን ችግር አትስማ፣ ካንተ ውጪ ማንም የለህምና ራስህን ብቻ ውደድ፣ ዘመኑ የፉክክር ነውና የተመኘኸውን ለመጨበጥ ሌላውን ገፍተህ እለፍ፣ ..' እያለ፤ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የተባሉትን ቅዱስ ጠባያት የማንነትህ አካል እንዳታደርግ በዓለም ውስጥ ጩኸቱ ከአድማስ ጥግ እስከ አድማስ ጥግ የሚሰማለት ክፉው መንፈስ፤ በፖሊሲ፣ በመርህ፣ በኑሮ ውድነት፣ በዘመን ለውጥ፣ በእንጀራ ጉዳይ፣ በመኖር ጥያቄ ጀርባ እየተከለለ ሰው የመሆንህን ንጹሕ ጠባያት እንዳትገለጽ በስልት አፍኖ፤ በጠባብ የርኩሰት አስፓልት ላይ ይመራሃል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን . . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
2•  ንስሐ    2.1•  ንስሐ ምንድነው? ክፍል - ፩     ✞ ፊትን ወደ እግዚአብሔር ጀርባን ወደ ዓለም ✞    አዳምን ወላጅ ሆኖ ያስገኘ የሥጋ ማኅፀን የለም፡፡ ለመጀመሪያው የሰው ልጅ የመጀመሪያ እናትና አባት አልነበረውም፡፡ የአዳም እናቱም አባቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፡፡ አዳም የተጸነሰባት ማኅፀን የአምላክ ፈቃድ ነበረች፡፡    ቀዳሚው የሰው ልጅ ከተጸነሰ በኋላ እስኪወለድ ድረስ…
2•  ንስሐ

   2.2•  ንስሐ ለምን እንግባ?

ክፍል - ፪

                ✞ የኃጢአትን ምሽግ ለማፍረስ ✞

   ኃጢአት የሚለውን ቃል በቀጥተኛ ፍቺ ስንተነትን፤ ከእግዚአብሔር ንጹሕ ፈቃድ መለየት፣ የእግዚአብሔርን ፍጹም አሳብና ባሕሪይ መሳት፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ መልካም አድርጎ ባየው ነገር ላይ ማመፅ፣ የጽድቅን በጎ ሥርዓትና ትእዛዝ መተላለፍ፣ የቅድስና አነዋወርን መቃወም አሊያ መሸሽ ብለን ማስቀመጥ ስንችል፤ በደፈናው ስንጠቀልለው ደግሞ የክፋት ሁሉ ራስና የኃጢአትም ኃይል ከሆነው ከዲያቢሎስ መንፈስ ፍላጎትና ጠባይ ጋር በስሜት፣ በአስተሳሰብ፣ በንግግርና በድርጊት መስማማት ልንለው እንችላለን፡፡ በነገራችን፥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ብየና ኃጢአት ማለት ሕገ እግዚአብሔርን በመሻር ክፉ የሆነን ሁሉ መፈጸም ብቻ ሳይሆን "በጎ ማድረግንም አውቆ አለመሥራት ጭምር ነው።" (የያዕቆብ መልእክት 4፥17)

   ስለ ኃጢአት በምንም አይነት መንገድ ከተነሳ ዘንዳ፤ ክፉ መናፍስትም አብረው ሊነሱ ግድ ይላል፡፡ የአንድ ሳንቲምን ሁለት ገጽ ፈጽሞ ለመለያየት እንዳይቻል፤ ዲያቢሎስና ኃጢአትም በጭራሽ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ ዮሐንስ በአንደኛ መልእክቱ (3፥8) ይህን አሳባችንን እንዲህ ሲል ይደግፍልናል፤ "ኃጢአትን የሚያደርግ [ሁሉ] ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።"

   በመግቢያችን ላይ ባስቀመጥነው የትንተና ፍቺ መሠረት፤ ኃጢአትን "ሀ" ብሎ በሥነ ፍጥረት ታሪክ የጀመረው ከሐዲው መንፈስ (ሳጥናኤል) እንደሆነ በብዙዎቻችን ሃይማኖታዊ ግንዛቤ ይታወቃል፡፡ በተሰጠው ልዩ ከፍታና የእውቀት ኃይል ታግዞ ፈቃደ እግዚአብሔርን መከተል ሲገባው ይልቁኑ "እኔው ነኝ አምላክ" የሚል ዓመፅን መልካም እንዲያደርግበትና እንዲከበርበት ከተሰጠው ነጻ እውቀቱ ውስጥ አጠንጥኖ አወጥቷል፡፡ በዚህም መነሻነት የፈጣሪን መለኮታዊ ክብር፣ ኃይልና ባሕሪይ ሲቃረን፤ እንደ እግዚአብሔር በመሆን ጣዖታዊ መሻቱ ባሕሪይውን አጽንቶ በመቀጠሉ፤ ከእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ የሚቃወም፣ የሚሸሽና የሚጥስ፤ የርኩሰት፣ የእርግማን፣ የጥላቻ፣ የክሕደት፣ የውሸት፣ የትዕቢት፣ የጥፋትና የስሕተት ነገር ሁሉ መነሻ፣ መድረሻና ሁለንተናዊ መገለጫ ሆኖ ቀርቷል፡፡

   ዲያቢሎስ ይህንን "ከሰማይ ስፍራ የተለየ" ማንነቱን ይዞ ወደ ሔዋን ሲመጣም፤ እርሱ አስቀድሞ የሳተበትን የዓመፃ አሳብ (ሳይጨምር ሳይቀንስ) አስከትሎት ነበር፡፡ ስለሆነ "ከእውቀት ዛፍ ፍሬ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ" በማለት "እንደ አምላክ የመሆንን" ጥብቅ ምኞቱን ለቀዳማይቱ ሴት አካፈላት፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥5) በሌላ አገላለጽ የኃጢአትን የመጀመሪያ ቃል ለሰው ልጅ ባሕሪይ አስተዋወቀ፡፡
 
   እንግዲህ ይህ የትናንት መነሻ ታሪክ ነው "ኃጢአትና ክፉ መንፈስ ያው አንድ ናቸው" እንድንል ለዛሬ መደምደሚያ እውነት የሚሆነን፡፡ ሰው በአምላክ ምሳሌነት ሲፈጠር፤ ከፈጣሪው ፍጹም ቅዱስና ንጹሕ ባሕሪይ የተነሣ እርሱም ኃጢአትን የሚባለውን የዓመፅ ውጤት ፍጹም የማያውቅ ሆኖ ነበር፡፡ ክፉ መንፈስ ወደ ሰው ልጅ ሕይወት ከመጣ በኋላ ግን፤ አዳማዊ ስብእና "ክፉን" (ኃጢአትን) እና "መልካሙን" (ጽድቅን) ለያይቶ ያውቅ (ከእውቀት ዛፍ ስለበላ) ዘንድ ዓይኖቹን ገልጧል፡፡ በአጭሩ፤ ሰዎች የትኛውንም አይነት ኃጢአት እንዲሠሩ ምክንያትና  ሂደት የሚሆነው የርኩሳን መናፍስት ሠራዊት ነው፡፡

    በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ጳውሎስ ክፉ መንፈስን በኃጢአት እየወከለ ሲነግረን እንሰማለን፦ "የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 7፥15)

  የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር ወሳኝና ልዩ ትኩረት የሚያሻው መልእክትን ይዟል፡፡ "እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ" ሲል ሐዋሪያው ጽፏል፡፡ ግርታን የሚጭር አባባል ነው፡፡ አንደኛው ላይ "እኔ አይደለሁም" አለ፡፡ ቀጠለና በሁለተኛው ሐረግ "በእኔ ያደረ ኃጢአት ነው" ይላል፡፡ ጳውሎስ አንድ ሊጠቁመን የወደደው፤ በእርሱ ያለ፥ ነገር ግን ከእርሱ ያልሆነ ኃይል በውስጡ አለ፡፡

አሁንም ጳውሎስ፦ "በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።" (2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፥7-8)

    ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ስለገመጠው ብርቱ ፈተና የጻፈበትን ሁለቱን ጥቅሶች አያይዘን ብናጤናቸው፤ የሚፈልገውን እንዳያደርግ፥ የማይፈልገውን ግን እንዲያደርግ በእርሱ አድሮ የሚገፋው የኃጢአት ኃይል ጎሳሚው ሰይጣን እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡

   ታሪካዊ ዝርዝሩ እንተወውና፤ "ከነገደ ብንያም" የሆነው የቀድሞው ሳዖል፥ የኋለኛው ታላቁ ጳውሎስ፤ የዘር ሐረጉ መነሻ መሠረትና መጠሪያ የሆነው ብንያም የተወለደው፥ እናቱ ራሔል ከአባቷ ከላባ ቤት ሰርቃና ከባሏ ከያዕቆብ ደብቃ የወሰደቺውን የተራፊም ጣዖት ይዛ በኮበለለችበት ወቅት ነበር፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 31)

   በዚህ በጣዖታዊ ባዕድ አምልኮ ውስጥ መዋቅሩን በዘር ትስስር በኩል አሳልፎ በብንያም ነገዶች ላይ ስውር ሰንሰለት በማበጀት በረጅም አድማስ የተቆጣጠረው የተራፊሙ መንፈስ፤ በእጁ አስገብቶ ከሚመራቸው ትውልዶች ወገን የሆነው ሳዖል ጋር ሲደረስ፤ ለብሉይ ኪዳን ቀናዒ የሆነ ልቡን ተገን አድርጎ ሐዲስ ኪዳንን የሚያሳድድ፣ ክርስቲያኖችን የሚጨቁንና የሚያጠፋ፣ በሐዋሪያት የወንጌል አገልግሎት ላይ ከባድ እንግልትና መከራ የሚያደርስ የፈተና ሰው እንዲሆን የራሱን ባሕሪይና ፈቃድ ከውስጥ ያጋራው ነበር፡፡ እንግዲህ ይህን ለዘመናት በሕልውናው አድፍጦ የተገዳደረውን ክፉ ኃይል ነበር "በእኔ ያደረ ኃጢአት" ሲል የገለጸው፡፡

   ዛሬ ባለንበት በኛ ጊዜ፤ ክፉ መናፍስትን እና ኃጢአትን በአንድ ክር ሰፍቶ የሚያስተውል፥ መንፈሳዊ እይታን የታደለ ንቃተ ሕሊና በጣም ጎድሏል፡፡ ምንም አድካሚ ሃይማኖታዊ ፍተሻና ውስብስብ ምርምር ሳያስፈልገው ኃጢአት ተብሎ የተፈረጀ ማንኛውንም ነገር ሁሉ የዲያቢሎስ ኃይል እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ሲገባን፤ ከኃጢአት ሥራዎች ጀርባ ረቂቅ ተፈጥሮውን (መንፈስነቱን) ተጠቅሞ የሚንቀሳቀሰውን አደገኛ ባላንጣ ፍጹም በዘነጋ ልቦና እንመላለሳለን፡፡ ነገሩን አስደንጋጭና አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ፤ እንኳን በዓለማዊው ቀርቶ በመንፈሳዊውም ስፍራ ላይ ያሉ በርካታ የቤተ-እግዚአብሔር ሰዎች፤ ኃጢአትና ዲያቢሎስ "ሥራና ሠራተኛ" ሆነው የተሰናሰሉ የጽድቅ ተፋላሚዎች ስለመሆናቸው በተገባ የሚያስረግጥ፤ በቂ፣ በሕይወት የተፈተነና በመገለጥ የተደገፈ እውቀትና ጸጋ ያለመያዛቸው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል "ንስሐ ግቡ" የሚለው ስብከትና "ንስሐ የሚገባው" ምዕመን ቁጥር ምንም ሊመጣጠን ያልቻለው፡፡
  አንድ በእግዚአብሔር ሕያው አምላክነት በእውኑ አምናለሁ የሚል ግለሰብ፤ ንስሐ በሚባል መንፈሳዊ መንገድ ላይ ለመጓዝ ሲዘጋጅ፤ በኑሮና በዕድሜው ውስጥ ከተፈጸመው የኃጢአት ሥራ ጀርባ መግፍኤ የሆነ ጉልበት ያሳደረ ክፉ መንፈስ እንዳለ ማወቅ ያስፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም ንስሐ በመግባት ከሚገኙ መሠረታዊ ሰማያዊ ትሩፋቶች መካከል አንዱና ዋነኛው፤ ኃጢአትን እንደ ምቹ ምሽግ ተጠቅሞ በባሕሪይ የሚደበቀውን ዲያቢሎስ በቀጥታ መቃወምና መጣል ስለሆነ፡፡ ባለ ራእዩ የሚለንን እንመልከት፦

"ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአል።" (የዮሐንስ ራእይ 12፥10)

   አጥፊው መንፈስ ትልቁና መድረሻ ሥራው፣ ዓላማው፣ ራእዩና ፍላጎቱ፤ በጽድቅና በኩነኔ መካከል ባለ የክስ መዝገብ ላይ ኃጢአታችንን አብዝቶ መደርደር ነው፡፡ በእያንዳንዷ ዕለት ላይ (ቀንና ለሊት) ኃጢአትን በኛ ፈቃድና ውሳኔ እንድንሠራ በተለዋዋጭና በዘርፈ ብዙ መናፍስታዊ ስልቶች በየደቂቃው በመፈተን፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚነበብ የበደልን ጽሕፈት በስማችን ይከትባል፡፡

   ይህ በእንዲህ ሳለ፤ እግዚአብሔርን በአፍ አመልካለሁ ብለን በተግባር ስንተወው፤ በአንጻሩ ሰይጣንን በአፍ ከድቻለሁ ብለን በተግባር ኃጢአትን ያለምንም ሥጋትና ቅደመ ሁኔታ በመፈጸም አብረነው ስንኖር፤ "እኔ መንፈስ የለብኝም" እያልን፤ የ'የለብኝም" ድምፃችንን እንደ ጭዳ ቆጥሮ ከማንነታችን ኋላ ይበልጥ ተሰውሮ እንዲገባ እና ራሳችን ቀድመን እንደሰየምንለት "እንደሌለ ሆኖ" የሚያደፍጥበትን ጊዜ እንዲጨምር፤ አቅሙን የምናበልጽግለት ሰዎች ጥቂቶች አይደለንም፡፡

   የመናፍስት ብቸኛ መግለጫና ኃይል የሆነውን ኃጢአት ዘወትር እንደልብ እየሠራን በእግዚአብሔር የጽድቅ ነገራት ላይ ድንዝዝ ብለን ስንቀመጥ፤ "ምንድነው ነገሩ? ለምንድነው በእምነት ሕይወቴ ውስጥ በእውነተኛ ምግባር መመላለስ ያቃተኝ? በእርግጥ የኃጢአት ራስ ከሆነው የዲያብሎስ መንፈስ የጸዳሁ ሰው ብሆን ኖሮ ፥ኑሮዬ ታዲያ ከጥፋት ገጽታዎች ስለምን ጸድቶ አይታይም? በአምላክ ላይ ያለማቋረጥ ዓመፃን እያስነሳሁ የምኖር መሆኔን በሚገባ ሳውቅ፥ የዓመፅ መሠረት የሆነው ክፉው መንፈስ የለብኝም ለማለት እንደምን ይቻለኛል?" ብለን በረጅም ጥሞና ተረጋግተን መመርመር ገና አልጀመርንም፡፡
 
    ዓለማችን በዚህ ዘመን ባለ ዕድሜዋ ኃጢአትን ሥር በሰደደ አኳኋን በብዙ ለምዳና የመኖር አንድ አካል አድርጋ፤ ከትውልዶች ፊተኛ የለውጥ ግስጋሴ ጋር አብሮ ቅርጽና ይዘት እየለወጠ በሚከተል የእርግማን፣ የርኩሰትና የክፋት ገጽታዎች የተሞላች ስትሆን፤ ይኸውና አሁን የጽድቅ እውነት ኃጢአት፥ የኃጢአት ውሸት ደግሞ ጽድቅ ሆኖ ተገላብጦ ቁጭ ብሏል፡፡
 
    አምላካዊ መሥፈርት የሆኑ የቅድስና እውነታዎች ነጻነትን እንደሚገፍፉ የባርነት እስር ቤቶች በአእምሮ ስሌት ተቆጥረው፤ በሥጋ ምቾት ላይ የተለጠፉ ኃጢአቶች የየዕለት ሽርፍራፊ ክስተቶቻችን ሆነው እንዲዛመዱን፤ በእግዚአብሔር የተቀደሱ አምባዎች ላይ መቆም በምድር የሚገባንን የቅንጦት ኑሮ እንዳንኖር የጎታችነት ቀንበር የሚያሳርፍ ተጽዕኖ እንዳለው ክፉ መናፍስቶች በቀላልና ለመቀበል በሚስማማን ጥቁር ጥበብ ካሳመኑን አያሌ ዘመናት አልፎዋል፡፡

    በተለይም በ17ተኛው ክፍለ ዘመን ከተነሳው፥ የኢንዱስትሪ ሥልጣኔን ሽፋን አድርጎ ከተቀጣጠለው የርዕዮት ሽግግር ወዲህ፤ የፉክክር መድረክ እንድትሆን አብዮታዊ ቅርጽ በወጣላት ዓለም ውስጥ አሸናፊ ለመሆን፤ የርኩሰትንና የዓመፃን ግብራት መፈጸም እንደ ተራ የተለምዶ ክብደት እየተዘመነ፤ "ሁሉም ሰው ኃጢአት ይሠራልና እኔም በዚህ ሁሉነት ውስጥ የደርሻዬን ኃጢአት ልውሰድ" በሚል ጋርዮሻዊ አኗኗር ሁላችን እየተመራን፤ የነፍሳችንን ዘላለማዊ ጩኸት አፍነን የሥጋችንን ጊዜያዊ ሹክሹክታ አድምቀን በመስማት ወደ ጨለማው ጠለል በዝግታ አንድ በአንድ ስንወርድ እንገኛለን፡፡

    በእውነት አስቸጋሪው የጥፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ኃጢአትን በመልመድ የኖርንበት ጊዜ የመልካምነትን ፍቅርና መሥዋትነት ከጠባያችን ውስጥ ደምስሶ፤ "በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም" ለሚለው የሮሜው ቃል መጽደቂያ ፍጻሜ አስገኝቷል፡፡ ኃጢአትን በመልመድ የቆየንበት ኑሮ የእግዚአብሔር ረድኤት በእጅጉ ርቆበት፤ የማይነዋወጽ ሰላም የምንለው የቅድስና አንድ መልክ "በበረሃ ውስጥ እንደሚፈልቅ ምንጭ" በጣም ውድ ሆኖብን ይገኛል፡፡ ኃጢአትን በመልመድ ያሳለፍንበት ቸልተኛ ዕድሜ በሁላችን ታሪክ ላይ ተመሳሳይ ሆኖ ሲገኝ፤ ቅዱስ መሆን ተአምር እስከሆነበት ጥግ ድረስ ርኩሰት ተላምዶን፤ ስለ ነፍስ መጨረሻ መጨነቅ እያቃተን፤ የደመወዝ ቀን መድረሻው እያስጨነቀን፣ የሥጋ ድሎት መጀመሪያው እያስጨነቀን፤ የውስጥ ሕልውናችን ባላወቅነው ደባል ጠላት በአዚምነት ግርዛዜ መካከል ተሸፍኖ እንዳለ ሳይገባን እንኖራለን፡፡

   ንስሐ፥ በኃጢአት ውስጥ የኃጢአት ኃይል ሆኖ የመሸገው ርኩስ መንፈስ በኛ ሕይወት ውስጥ የሚደበቅበትን የማድፈጫ ቦታ እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ በሚገባ ጸድቶ የተወለወለ ጠረጴዛ ላይ ቆሻሻን የምትፈልግ ዝንብ ልታርፍና ልትቆይ አትችልም፡፡ ሆኖም ጠረጴዛው በሚገባ ካልጸዳ፤ ባልጸዳው የቦታ ክፍል ላይ አንዣባ ሄዳ ታርፋለች፥ ትቀመጥማለች፡፡

   ምሳሌውን ወደ መንፈሳዊው እውነት ስናመጣው፤ ዲያቢሎስ ኑሮአችን ውስጥ ተመሳስሎ ገብቶ ራሱን ለመከለል የሚጠቀምባቸው መደበቂያዎች ንስሐ ያልገባንባቸው የኃጢአት ታሪኮቻችን በሙሉ ናቸው፡፡ (ልብ ውስጥ እስኪሰርጽ ተደጋግሞ ይነበብ)

   ከእግዚአብሔር ፈቃድ የተለየንበት፣ የእግዚአብሔርን ንጹሕ አሳብና ባሕሪይ የሳትንበት፣ በእግዚአብሔር መልካም ነገር ላይ ያመፅንበት፣ የቅድስናን ሕግ የጣስንበት ማንኛውም አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አኗኗር ሁሉ፤ ከሥጋዊ ኑሮአችን የተደበቀ የጠላት መንፈስ መጋረጃ አድርጎ የሚከለልባቸው የዲያቢሎስ መጠለያዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ንስሐ በገባን ቁጥር እያፈረስን የምንሄደው የኃጢአትን ክምር ተራራ ብቻ ሳይሆን ከተራራው (ፊትና ጀርባ) ሆኖ በተጨባጭ በማይታይ ገመድ እንዳንርቅ ጠፍንጎ ያሰረንን ኃይል ነው፡፡

   አገላለጻችንን በጳውሎስኛ አጻጻፍ መልክ ብናሲዘው፤ ንስሐ ማለት በኛ ውስጥ አድሮ እኛ ሳንፈልግ የምንሠራውን፥ ደግሞ ፈልገን የማንሠራውን ሥራ እንድንፈጽም ምክንያት የሚሆን ኃጢአትን የሚያስወግድ መለኮታዊ መሣሪያ ነው፡፡

   ወይንም ደግሞ የራእዩን ጥቅስ መግቢያ በራችን አድርገን ንስሐን ብናይ፤ ንስሐ ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሰንን የወገኖቻችን ከሳሽ፤ የኃጢአት መዝገቡን የሚያሰፍርበትን ሰነድ የሚቀድ የእግዚአብሔር መሐሪ እጅ ነው ልንል እንችላለን፡፡

   (እናስተውል!) ካለ ንስሐ በምንመራው ሕይወት ውስጥ፤ የዲያቢሎስ እርምጃ ከኛ አንድ እርምጃ የሚቀድምበትን ዕድል ያገኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ንስሐ ባልጎበኘው የዕድሜያችን ዘመናት ሁሉ ላይ መናፍስት ወደፊት ቀድመው በመጓዝ ፈቃዳቸውንና እቅዳቸውን በኛ ላይ ለመፈጸም የሚያስችል ጥንካሬና አቅም አላቸው፡፡ ምክንያት? .. የእግዚአብሔር ኃይል ጽድቅ ነው ከተባለ፤ እንኪያሳ የዲያቢሎስ ኃይል ደግሞ ኃጢአት ይሆናላ፡፡ በመሆኑም በንስሐ ያልተገረሰሱ የኃጢአት ጊዜዎቻችን ራሳቸውን የቻሉ ዲያቢሎሳዊ ጉልበቶች ሆነው ለክፉው መንፈስ ያገለግላሉ፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
+ በጾመ ፍልሰታ እንፍለስ +
+ በጾመ ፍልሰታ እንፍለስ +

እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ አስቀድሞ ጤናውና ሰላሙ ይኑራችሁ፡፡ ስለርሱም ዘወትር አመስግኑ፡፡ ሌላው ሁሉ በጊዜው ይደርሳል፡፡

ፍልሰታ በጥሬ ቃል ፍቺው መፍለስ ከሚለው ግስ የተነሣ ሲሆን፤ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መዛወር፣ መንቀሳቀስ፣ መጓዝ የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና እርገት ጋር የቃልኪዳን ትስስር ያለው ልዩ ጾም ነው፡፡

ጾመ ፍልሰታ በዐሥራ ስድስት ቀናት ውስጥ ተጀምሮ የሚያልቅ ቆይታ ሲኖረው ይኸውም መግቢያ ቀንና መውጪያ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ይሆናል፡፡ አንድ ሱባዔ ሰባት ቀን ሲሆን፤ ሁለት ከሆነ ዐሥራ አራት ቀን ይሆናል፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያው መነሻና መፈጸሚያ መድረሻ ቀናት የጾሙ መግቢያና መውጪያ ጊዜያት ይሆናሉ፡፡ ጾሙ ደቀመዛሙርቱ እንደያዙት ሱባዔ፤ ሰማያዊ መልስ፣ የመንፈሳዊ ሚስጢር መገለጥና የበረከት ስጦታ የምናገኝበት ጾም ነው፡፡ ሐዋሪያቱ ሰማያዊ መልስ ጠይቀው አግኝተውበታል፡፡ ሚስጢር የሆነባቸውን ጉዳይ በመንፈሳዊ መገለጥ ፈትተዋል፡፡ በመጨረሻው ስለ እመቤታችን ትንሣኤ የበረከት ምልክት የሚሆነውን ሰበን ሐዋሪያው ቶማስ ተቀብሎአል፡፡

እኛም መልስ ያጣንለት ጥያቄ ይኖረናል፡፡ ሚስጢር ሆኖ አልገለጥ ያለን ጉዳይ ይኖረናል፡፡ የበረከት ማነቆ በሰላቢ መናፍስት፣ በቡዳ መናፍስት፣ በመተት መናፍስት ምክንያት ደርሶብን፤ የልፋታችንን ከንቱነት እያሰብን የምንገኝ እንኖራለን፡፡ በጾመ ፍልሰታ ታዲያ፤ ከነፍስ፣ ከልብና ከአሳብ በተሰበሰበ አንድ የፍቅር ምዕራፍ ከፈለስን፤ ብዙ ቦታ ላይ አልገጥም ብሎ ያሰቃየን ጉዳይ ቅርጹን ይይዛል፡፡

ጾመ ፍልሰታን እንዴት እናሳልፍ ?

፩. በፍቅር

የመንፈሳዊ ሕይወት ግንባታ መሠረት "ፍቅር" ነው፡፡ ሃያ ዐራቱን ሰዓት ሁሉ ብንጾም፣ ከደመና በላይ ጮኸን ብንጸልይ፣ አጥንታችን እስኪሰበር ብዙ ብንሰገድ፣ ኃይል ከሰማይ እንደዝናብ ቢወርድ፣ የቱንም ያህል ደረጃ ነገሩ ቢሳካ፤ ሕይወታችን ፍቅር ከሌለበት ሁሉ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ነው (ይሄ፥ ጥሬ አባባል የሚመስለው፥ ለብዙ ሰው ነው)፡፡ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፥2) ፍቅር የሌለው መንፈሳዊነት ወግ ይሆናል፡፡ ዘልማድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ፍቅር ሲኖረው መንፈሳዊነቱ ላይ ጠንካራ እምነት ይገኝለታል፡፡ በጣም ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ ወድደን የምናደርገው እና ተገደን አሊያ ማድረግ አለብን ብለን አስበን የምንከውነው ጉዳይ መካከል የራሱ የሆነ ርቀት አለ፡፡ ዐሥራ ስድስቱ ቀናት እየጣፈጡህ ማለቃቸውን እንኳ ሳታስተውል እንድትፈልስባቸው፤ መጀመሪያ ቀን አንድ ስትል፥ ከፍቅር ጀምር፡፡ እውን የእመቤታችን ፍቅር ነፍስህን ይዞት፤ ትንሣኤዋ ልብህ ላይ ተቀምጦ፤ የሐዋሪያቱ ሱባዔ አሳብህ ውስጥ ሆኖ ክብሩን ባነገሠ ምግባረ ክርስትና መሄድ ስትጀምር፤ ቀኖቹ እንዲያልቁ ሳይሆን እንዳያልቁ በስስት እያየህ እያንዳንዷን ቀነ ደቂቃ እየነጠልክ ትጾማቸዋለህ፡፡

፪. በአምልኮትና በጸጋ ስግደት

ስግደት ጸሎት ማጽደቂያና ማሰሪያ ነው፡፡ መሥዋዕት የማቅረቢያ አንድ መንገድ ነው፡፡ የመገዛትና የማክበር መግለጫ ነው፡፡ እነሆስ፥ "ተወዳጂቱ ቤዛዊት ዓለም ሆይ፥ ቢመጣም ባይመጣም፣ ቢሠራም ባይሠራም፣ ቢከናወንልን ባይከናወንልም፣ ቢደርስም ባይደርስም በእውነትም እንወድሻለን!" የምንለው በጸጋ ስግደት በኩል ነው፡፡ የሚሰግድ ሰው የፍቅሩ ኃይል ላይ ማኅተም አለው፡፡ ማረጋገጫ አለው፡፡ ዋጋ ስለመስጠቱ መታያ ነው፡፡ እንኪያስ፥ የእመቤታችንን ስግደት በጾመ ፍልሰታ ከዘወትሩ ስግደት ጋር አስተባብራችሁ በደንብ ስገዱ፡፡

፫. በጸሎት

ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን ወደ አፀደ ሕይወት መፍለስ እያሰብን የምንጾመው ከሆነ ዘንዳ፤ እንግዲያው እኛም በመንፈሳዊ ጉዞ በኩል ወደላይ መፍለስ አለብን፡፡ መጨመር አለብን፡፡ የአምልኮት ልምምድ፤ ጊዜ፣ ብዛትና አቅም መጨመር አለብን፡፡ ሁለቴ የምትጸልየው ሦስቴ፥ ሦስቴም ከሆነ አራቴ፥ አራቴም ከሆነ አምስቴ ለማድረግ እንጀግን፡፡ በሥጋ ላይ ያለን ከፍታ ለማምጣት ዓለም ሁሉ ይሮጣል፡፡ የነፍስ ብልጽግና ግን ለተመረጡት ነው፡፡ ድምፁን ለሚሰሙት .. ለበጎቹ! (ውዳሴ ማርያምን ጸሎት በገባችሁ ልክ ብትጸልዩ ጥሩ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ቀን 6:00 መልክአ ሚካኤል ሲነበብ፤ አስቀድማችሁ ውዳሴ ማርያምን በመቀጠል የመልአኩን መልክአ መጸለይ፡፡ በሥራና ሌሎች ጉዳዮች የተወጠራችሁ ሰዎች እስከምትችሉት ያህል ጸልዩ፡፡ ከፍቅር መሠረት ላይ መነሣት የሚገባን ለዚሀ ነው፡፡ ፍቅሩ ካለ እስከ የትኛው አቅም ልክ እየሄድን መበርታት እንዳለብን ማንም ሳይጠቁመን እናውቀዋለን)

፬. ክፉውን በመዋጋት

ጥሩ ንቃተ ሕሊና የታደለ ሰው መናፍስት ብርታት የሚሆኑ የጽድቅ ጠላቶች እንደሆኑ ያውቃል፡፡ በተለያየ መንገድ ፈተና ውስጥ የሚከቱን አጥፊ ኃይሎች ባይኖሩ ኖሮ ማን ያበረታናል? .. አባቶቻችን መከራ ሲርቃቸው ተጨንቀው ያለቅሱ ነበረ፤ እግዚአብሔር የተዋቸው እየመሰላቸው፡፡ በአንክሮ ስንገንዘብ፤ ያለ ፈተናና ትግል ክርስትና ውስጥ መንፈሳዊነት ለካ አይበረታም፡፡ የተዘጋብንን ለማስከፈት በሰገድን፣ በጸለይን፣ በመቁጠሪያ በተዋጋን ቁጥር ወደ አርያም ሰማይ ምን ያህል እየፈለስን እንደሆነ ብዙዎቻችን አይገባንም (ችግር ችግሩን ስለምንቆጥር)፡፡ እስኪ ከትናንት ዛሬ የመጣንበትን በደንብ እናጢነው፡፡ ስግደት አናውቅም ነበረ አሁን እንዴት ሆነናል? ጸሎት በርትተን አንጸለይም ነበር አሁን ከምን ደርሰናል? .. መናፍስቱን በተዋጋንበት ልክ፤ የኛም መንፈሳዊ ለውጥ በዛው ልክ ከፍ ይላል፡፡

በሉ ስለዚህ በጾመ ፍልሰታ መናፍስቱ ላይ መለኮታዊ ማዕበል አውርዱ፤ ዝመቱ፤ በደንብም አድክሟቸው፡፡ በነገራችን የፍልሰታ ጊዜ የሱባዔ መልክ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ሱባዔ ደግሞ ብቸኝነት ይፈልጋል፡፡ አርምሞ ይወዳል፡፡ ከሥጋ ወከባና መዝናኛ መለየት ደስ ይለዋል፡፡ ስለዚህ .. የነፍስ ቆይታ ላይ ትኩረት እንስጥ፡፡ ከለመድናቸው የሥጋ ጉዳዮች ሸሸት እንበል፡፡ ዘፈን ከመዝሙር አናምታታ፤ ጸሎትን ከቂም አንቀላቅል፤ ዓለማዊን ከመንፈሳዊ አናወሳስብ፡፡ ምክንያቱም ተወዳጁ.. እንኳን በሰላሙ ሰዓት .. በመሰቀል ጭንቅ ሳለም .. ቀላቅለው የሰጡትን መጠጥ ሊጠጣው በፍጹም አልወደደም!

፭. በመቀደስ

ጾመ ፍልሰታ ጊዜ ውስጥ የሁለት ሳምንታት ቅዳሴዎች አሉ፡፡ በመሆኑ የምንችል ሰዎች ስናስቀደስ፤ በዛውም መቀ'ደስን እንወቅ፡፡ ንስሐ ገብታችሁ ያለ ቅዱስ ቁርባን ቁጭ ያላችሁ ወገኖቼ መቼ ልትቆርቡ ነው? ምን እየጠበቃችሁ ነው? ምንድነው'ስ አላስቆርብ ያላችሁ? ..

በነዚህ የፍልሰታ ሳምንታት መቁረብ እጅግ ታላቅ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያት ካልን፤ አንደኛ ጾሙ በራሱ የሱባዔ መልክ እንዳለው ተነጋግረናል፡፡ ሱባዔና ቅዱስ ቁርባን ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ ባልንጀሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛ፤ ፍልሰታ የቃልኪዳን በረከት ያለው ጾም ነው፡፡ ይሄ በረከት ደግሞ ስለመኖሩ ራሱ የሚታወቀን በቅዱስ ቁርባን ስንቀደስ ነው፡፡ ሦስተኛ፤ ጾሙ ውስጥ መንፈሳዊ መገለጥ ታሪካዊ መዝገብ ሆኖ ይገኛል፡፡ የዚህ የመገለጥ ቁልፍ መክፈቻ ደግሞ የመድኃኒቱ ሥጋና ደሞ ነው፡፡ እናሳ? .. እንዴት ነው ምን ወሰናችሁ?
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
+ በጾመ ፍልሰታ እንፍለስ + እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ አስቀድሞ ጤናውና ሰላሙ ይኑራችሁ፡፡ ስለርሱም ዘወትር አመስግኑ፡፡ ሌላው ሁሉ በጊዜው ይደርሳል፡፡ ፍልሰታ በጥሬ ቃል ፍቺው መፍለስ ከሚለው ግስ የተነሣ ሲሆን፤ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መዛወር፣ መንቀሳቀስ፣ መጓዝ የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና…
፮. ለአገርና ለወገን በመጸለይ

እንደምታውቁት ያለንበት ዘመን ከባድ ጊዜ ሆኖ እያለፈ ነው፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ ሰቅጣጭ ዜናዎች፣ የሞት ድምፆች፣ አስጨናቂ መረጃዎች፣ አሳዛኝ ታሪኮች በየጊዜው ሲነገርባቸው የከረሙ ዓመታትን ያቀፈ ዘመን ነው፡፡ አሁን ደግሞ መጨረሻው የዓመቱ መገባደጃ ጊዜ የነሐሴ ወር ላይ ልንገባ ነው፡፡ እነሆ የሞቱትን በአፀደ ነፍስ እንዲያሳርፋቸው፣ የታመሙት እንዲድኑ፣ በእስራት ያሉ እንዲፈቱ፣ የጨለመባቸው ብርሃን እንዲያዩ፣ ተስፋ የቆረጡ እንዲበረቱ፣ ያዘኑ እንዲጽናኑ፣ ካለ አምልኮት ሕይወት የሚኖሩ እንዲነቁ፤ አገራችንም በጽድቅና በእውነት መንፈስ የሚመራ አንድ የሆነ በጎ ወገን እንዲበዛላት ጸልዩ፡፡

ብልጥ ሆናችሁ ከሰማችሁ፥ አድምጡኝ፡፡ ለራሱ ብቻ የሚጸልይ እና ለራሱም ለሌሎችም የሚጸልይ ሰው መካከል ሰፊ ድንበር አለ፡፡ ለራሱ የጠየቀው፥ ለራሱ የጠየቀውን ያህል ይቀበላል፡፡ ለሌሎችም ጨምሮ የጠየቀው ግን፥ እርሱ ለሌሎች እንዲሰጥ የጠየቀውን አክሎ ይቀበላል፡፡

ለሰዎች ከልቡ ራርቶ የሚጸልይን ሰው እግዚአብሔር ይበልጡኑ ይከተለዋል፡፡ ለምን ሲባል፤ የራሱ የክርስቶስን ሥራ፣ የጻድቃንን ሥራ፣ የመልአክትን ሥራ የሚሠራ ሰው ስለሆነ፤ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ በኃይል ለመገለጥ ፈቃደኛ ነው፡፡ ለወገኖቻችን እንጸልይ! የበረከት ሥራ እንሥራ! የወደቁትን በምንችለው ልክ እንደግፍ! እዚህኛው ጋራ ሰዎች በምትችሉት ልክ እርዱ ሲባሉ ካላቸው ላይ ትንሹን ይሰጣሉ፡፡ መስጠቱ በራሱ ምንም ያህል ይሁን መልካም ቢሆንም፤ ወደን በእግዚአብሔር ፊት ስንሰጥ ግን በእውነተኛው አቅም ልክ ልንሰጥ ይገባል፡፡ ከምትችለው አቅም አሳንሰህ አትስጥ፡፡ መስጠትን ቃየንም አቤልም እንደሰጡ አስብ፡፡ ግን አቤል ካለው ላይ በአቅሙ ልክ መርጦ ሰጠ፡፡ ዐሥራት በኩራት አወጣ ማለት ነው፡፡ ቃየን ከሚችለው አሳንሶ አስረከበ፡፡ ዐሥራት አወጣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስንሰጥ፤ እውነት ከልባችንና ከጥጋችን ልክ የሰውን ችግር ለመቅረፍ ዓላማ አድርገን እንስጥ ብቻ .. የቀረውን ጎዶሎ ጥበበኛው አባት ይሞላል፡፡

ያለንበት ይሄ ዘመን፤ ሴቲቱ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃን ከእግሮቿ በታች አኑራ በሰማይ የተገለጠችበት ዘመን ነው፡፡ (የዮሐንስ ራእይ ምዕ.12) አበው ሴቲቱ አንድም ያመነች ነፍስ (ምዕመን) ናት ሲሉ ይተረጉማሉ፡፡ ባለራእዩ ሴቲቱን በተለያየ የዘመን መገለጥ ውስጥ ነው ያያት፡፡ የሐተታ ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ለምሳሌ ባንዱ ዘመን ላይ ሴቲቱ በድንግል ማርያም ስብእና ተመስላ ትታየዋለች፡፡ በሌላ ዘመን ደግሞ ሴቲቱ በመምህራንና በምዕመናን መልክ ትታያለች፡፡ እንጠቅልለውና እውነተኛይቱ ሃይማኖት እንበላት፡፡ ሴቲቱ በሰማያዊ ውበት አሸበርቃ ስትገለጥ ዘንዶው ልጇን ሊበላ እየተሳበ ወደርሷ ይመጣል (በድንግል ማርያም በኩል ስናይ ዘንዶው ሄሮድስ ይሆናል)፡፡ መጥቶም ከፊቷ ይቆማል፡፡ በኛ ዘመን ስናሰላ፤ እውነተኛይቱን ስብእና ይዘው የሚመላለሱ ምዕመናን ፊት፤ የሚውልዱትን የሃይማኖት ሥራ ሊበላ ዘንዶው ትይዩ የሆነ ቦታ ይዞ ይዘጋጃል፡፡

የዚህ ዓለም ሥርዓት ስብእናይቱን ያባርራታል፡፡ በእርግጥም ዘመናችንን ስናስተውል፤ መልካምነት ከሰው ሕልውና ሸሽታ ትታየናለች፡፡ ውሸት አምሮባታል፤ ወፍራለች፡፡ ግብዝነት ተለምዳለች፡፡ ገንዘብ በጭንቅላት ዙፋን ነግሣለች፡፡ ደግነት ተደብቃለች፡፡ እውነት መኖሯ እስኪያጠራጥር ድረስ ዝምታን መርጣለች፡፡ ፍቅር እንደ በረድ ቀዝቅዛለች፡፡ ጥላቻ በእያንዳንዳችን ጓዳ ተቀጣጥላ ትሞቀናለች፡፡ ዮሐንስ እንዳየው ዘንዶው ሴቲቱን ያሳድዳታል፡፡

ግን የሴቲቱ ልጅ፤ የእናታችን ልጅ፤ አህዛብን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛበትን ኃይል ይዞ ወደ አባቱ ተነጥቋል፡፡ እርሱ ብርቱ ነው፡፡ ጠፈንገው ማሰራቸውን ሳይጨርሱ ይፈታል፡፡ በር ሲዘጉበት እንደተቆለፈ ይገባል፡፡ በሥጋ ሲገድሉት በነፍስ ይሠራል፡፡ አጠፋነው ሲሉት በዝቶ ይወጣል፡፡ ሥራው ሁሉ ድንቅ መንክር ነውና የሚያደርጉት ይጠፋቸዋል፡፡ እርሱም የታመነ ነው ወደሚጠብቁት ምስክሮቹ ይገሰግሳል፡፡ ሊያዩት ወደሚጓጉት ሲሄድ ይቸኩላል፡፡ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ይወድዳቸዋል፡፡ በውስጣቸው ገብቶም ይረቅላቸዋል፡፡ የማይቻለውን ሁሉ ያስችላቸዋል፡፡ ይሄ አንባቢ ደስ እንዲለው የተጻፈ የሞራል ቃል አይደለም፡፡ በሕይወት የሚከተብ ሕያው እውነት ነው፡፡ እውነትን የምታምኑ .. አምናችሁም የምትኖሩ .. እየኖራችሁም ሐሰትን የምትታገሉ እናንተ የእናቲቱ ልጆች .. በርቱ .. "የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።" (2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፥11)

#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
ሰሙነ ፲፮
ማርያምና ኢትዮጵያ

ሰሞኑ ለተዋሕዶ ክርስትና አማኞች የፆም ወቅት ነው። የፍልሰታ ፆም! እስቲ አንዳንድ እውነታዎችን እንጨዋወትበት።

፩. የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም!

ከቶማስ ውጭ ያሉት ሌሎች ሐዋርያት የማርያምን ትንሣኤ ከእርሱ ሰምተው መንፈሳዊ ቅናት ይይዛቸውና ሱባኤ ይገባሉ። ተገለጸችላቸውም። ጾሙ የዚህ መታሰቢያ ነው። እኛ ጾሙን ለሕይወታችን እንጠቀምበታለን። ታሪኩ እንዳለ ሆኖ 'ለሐዋርያት ምስጢር ይከፈልባቸዋል ወይ? ለአንዱ ተገልጾ ለሌላው ሳይነገር የሚቀር ነገር አለ?' ብለን እንጠይቅ። እርገት በመጽሀፍ ቅዱስ ሲመሰጠር የወንድ ስርዓት ነው። የሴት አይደለም። ዝርዝሩ ይቆየን። ሐዋርያትን ሊያስደንቃቸው የሚችለውም ይሄ ነው። በተለምዶ ይሁን ለቃል ካለመጠንቀቅ ባላውቅም የድንግል ማርያም እርገት ከተወዳጁ እርገት'ጋ ተመሳስሎ ይነገራል። የማርያም እርገት ከጌታ እርገት ይለያል። የጌታ ወደአብ፣ ወደክብሩ፣ ወደ አባቱ የገባበት ነው። በሊቀ ካህንነቱ እስካሁን ነፍሳችን ትገለገላለች። ወደ አብ በመግባቱ በምልአት እንደ አባቱ ሆነ። በሰው በኩል ሲታይ “ሰው አምላክ ሆነ “። የእግዚአብሔር ሀሳብ በእኛ ለመታሰብ ቻለ። ይህ የሆነልን በተወዳጁ እርገት ምክንያት ነው። ጳውሎስም ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የሚለው ለዚህ ነው። የማርያምና የሀዋርያት ግን በትንሳኤው ቢመስሉትም በእርገት ወደ አብ አልሄዱም። በነፍስ ስርዓት ይኖራሉ። ጌታ ተነስቶ ለአርባ ቀናት በኖረው ስርዓት ይቆያሉ። እነሱ የሞትና የሕይወት ቁልፍ ያለው የእግዚአብሔር ልጅ የሰጣቸው ልጅነት አለቻቸው። ስለዚህ ሲሞቱም ፈልገውት እንጂ ሞት ገዝቷቸው አይደለም። ጳውሎስ “ቢሆንልኝ የሞቱን ጥምቀት እጠመቃለሁ” የሚለው በሞት መንገድነት የሚገኝ ታላቅ ምስጢር ስላለ ነው። ልጅነት ካለችህና ሙት ካስነሳህ አንተም ትነሳለህ ማለት ነው (ጠንቋይ ነው ለራሱ የማይሆነው)። ጌታ የኅያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እነማርያም ሕያዋን ናቸው። ጌታ እንዳለው ”አምላክ ሙሴን ሲያናግረው የአብርሃም፣ የይስሃቅ፣ የያእቆብ አምላክ ነኝ” ማለቱን በመጥቀስ የህያዋን አምላክነቱን ተናግሯል። በሞቱ እንደመሰሉት በትንሳኤውም ይመስሉታል። ሞቶ መነሳት ዋንኛ መገለጫው በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ መገኘትን ነው። አንዱ ስንዴ ሞቶ ሲነሳ ብዙ ሆኖ መውጣቱን ይመለከቷል። ጳውሎስ ስለ ትንሳኤ ሙታን ሲናገር “እኛ ህያዋን ሆነን የምንቀረው ያንቀላፉትን አንቀድምም” በማለት ነው። ታሪክ ጳውሎስ እንደሞተ ይናገራል። እርሱ ግን እስከ ምጽአት ህያው እንደሆነ ይናገራል። ጳውሎስ ትክክል ነው። እነርሱ በዙሪያችን አሉ። እንደ ደመና ከበውናል። የትንሳኤን ትምህርት ምስጢር የሚያሰኘውም እንደዚህ አይነት በመኖር ብቻ የሚታወቁ ነገሮች ስላሉት ነው። በዚህ የተነሳ ማርያምም ተነስታለች። ሁሉም ግን በራሱ ተራ ነው።

፪. ቶማስ

ሀዋርያት በቶማስ ያዩት ግን ያላወቁት አንድ ጉባኤ አለ። ይህም ከእርሱ በስተቀር ትንሣኤውን ያመኑት በቃልና በመገለጽ ነው። እንደ ቶማስ በመንካት አላመኑም። የተወዳጁን ጎን በመንካት የሚያነጋግረው ኢየሱስ እንደሆነ አውቆ አመነ። ያ ጎን በቀራንዮ ደምና ውኃ የፈሰሰበትና አባት በልጁ አምጦ እኛን የወለደበት ነው። ማየ ገቦ እንዲል መጽሀፍ። ከተወለድንበት ማህጸን ነው ማለት ነው። እናት!

የተነሳው ተወዳጅ ስጋና አጥንት ከመስቀል በፊት ከነበረው ስጋው የሚለይበት አንድ ነገር አለ። የተነሳው የሞት አገልግሎት አይከናወንበትም። ቀን በጨመረ ቁጥር ለሞት አይቀርብም እንደማለት ነው(በትንሳኤ የማያስፈልጉ የሰውነት ክፍሎችና ስርዓቶች አሉ። የሆድ እቃ ላያስፈልግ ይችላል እንደማለት ነው) እኛ ወደእርጅና እንገሰግሳለን። ጌታ ከተነሳ በኋላ ይህን አስቀርቶታል። ከክብር ወደ ክብር እየሄደ በመጨረሻም እየረቀቀ ሄዶ ወደ አባት ገብቷል። መርቀቅን ነው ማረግ የምንለው። ቶማስ ይህን አካል ነክቶት አምኗል። ይህ የነካው ስጋ ከማርያም የነሳው ስጋ ነው። ይህ ስጋ በነፍስ ስርዓት ውስጥ ያለ ነው።

፫. መቶ ሃያው ቤተሰብ

ጌታ ካረገ በኋላ ያሉት አስሩ ቀናት በሰሜኑ የመቅደሱ በር ሲለኩ 16.4 ዓመታት እንደሆኑ ከዚህ በፊት አውስተናል። ይህ የቅድስት ቅዱሳን ቁጥር አብን ይወክላል። ከአስሩ ቀን መንፈሱን ልኮ ወልዶናል። ማርያም የአብ ምሳሌ የተባለችውም በዚህ ወላጀነቷ ነው። በ16.4 ዓመቷ ወልዳዋለች። ይህ በስጋ ነው። በእነዚያ አስር ቀኖች ውስጥ 120ው ቤተሰብ እየጸለዩ ነበር። ማርያም እዚህም አለች። በስጋዋ የሆነውን ነገር የተረዳችውና ያወቀችው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነበር። የዚህ እውነት ምሳሌነቷን በሥሉስ ቅዱስ ተረጋገጠላት። ይህ የፅዮን እናትነት ነው፤ ሁሉም የሚወለድበት። 16.4 ለእርሷ ብቻ ታውቆ አልቀረም። ሁሉም ይህን እናትነት አገኙት። ተገለጸላቸው።

አጠቃላይ መቅደሱ በዘመን ሲለካ 1968 ዓመታትን ይሆናል (ፖለቲካችን ከመቅደስ የወጣበት ዘመን ነው)።መቶ ሀያው ቤተሰብ የኖራት ፲ ቀን ወይም 16.4 ዓመታት ቅድስተ ቅዱሳን ናቸው። ሁሉም ይህንን የወላጅነት ስርዓት አግኘተውታል። ተገልጾላቸዋል። በሌላ አባባል እያንዳንዳቸው 16.4 በመሆን ዓለምን ለውጠዋል። ስሌቱ ፦
1968 ÷ 120 = 16.4

በበዓለ ሀምሳ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ድምጹ ተነግሯል። ይህ ሁነት በሰሜኑ በር ለ1968 ዓመታት ክርስትና ለዓለም ሁሉ ተሰብኳል። በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተመስክሯል። እኛም ይህ እንዲገለጽልንና እንድንኖረው ያስፈልጋል። ስሌቱም የሚናገረው ይህንን ነው (በነገሬ ላይ አንድ ሰው ለመብቃት 16 ዓመት ይፈጅበታል ማለት አይደለም። ይህ በጉ በሄደበት ሁሉ ለሚሄዱት የተሰጠ ነው። ከእነሱ የተነሳ ይህን በማመን የምናገኘውን ጸጋ ሰው ሆኖ በተገለጸበት ምልዓት መጠን ለመግለጽና ምን ያህል አምላክ እየሰራ እንደሆነ ለማወቅ እንዲረዳን ነው። ሁሉ በእርሱ ሆኗል። ያለ እርሱ የሚሆን እንደሌለም እንድናይበት ነው።)
2024/10/01 12:12:34
Back to Top
HTML Embed Code: