tgoop.com/fitse_tube/436
Last Update:
#ሰብአ_ሰገል_ወርቅ_ዕጣንና_ከርቤ_የመገበራቸው_ምስጢር፡-
የጌታችንን ልደት በኮከብ ተረድተው ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ማንቱሲማር፣ ሜልኩ በዲዳስፋ የተባሉ የፋርስ ነገሥታት ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ አምጥተው የመገበራቸው (አምሐ አድርገው የመስጠታቸው) ምስጢር እንደምንድን ነው ቢሉ፡-
#ወርቅ፡-
ወርቅ መገበራቸው ይኸን የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ነህ፤ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤ አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ እንዲሁም በአንተ ያመኑ ምዕመናንም ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው። የሃይማኖት ጽሩይነቱና ግብዝነቱ የሚታወቅ መከራ ሲቀበሉበት ነውና።
#ዕጣን፡-
ዕጣን መገበራቸው ይህንን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። አንድም ዕጣን ምዑዝ ነው፤ አንተም በባሕርይ ምዑዝ ነህ ሲሉ እንዲሁ ደግሞ በአንተም የሚያምኑ ምእመናንን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ዕጣን የተስፋ ምሳሌ ነው። ዕጣን ከሩቅ እንዲሸት ተስፋ ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩት ታደርጋለችና።
#ከርቤ፡-
ከርቤ መገበራቸው ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ በኋላም የማታልፍ ብትሆንም በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፤ አንድም ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለየውን አንድ ያደርጋል። አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ ሲሉ። አንድም በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት። ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው። በፍቅር አንድ ይሆናሉና። ከርቤ የፍቅር ምሳሌ ነው። ከርቤ አንድ እንዲያደርግ ፤ ፍቅርም አንድ ታደርጋለችና።
በአጠቃላይ ሰብአ ሰገል ወርቅ፣ እጣን ከርቤ የገበሩለት ሃይማኖት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ነው። በሌላ መልኩ ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለመለኮቱ፣ ከርቤ ለሞቱ ምሳሌ ናቸው።
BY Fitse Tube
Share with your friend now:
tgoop.com/fitse_tube/436