Warning: Undefined array key 0 in /var/www/tgoop/function.php on line 65

Warning: Trying to access array offset on value of type null in /var/www/tgoop/function.php on line 65
- Telegram Web
Telegram Web
ታክሲ ውስጥ የኋላ ወንበር ላይ ተቀምጬ አጠገቤ ያሉ ሰዎች ስለመቸገር እያወሩ ነበር። በተለይ አንደኛው "እቸገር ነበር" ብሎ ስለጀመረ ጆሮዬን ወደጨዋታቸው ጣልኩኝ። ያው ችግርን "ነበር" ብሎ እንደመግለጽ ደስ የሚል ነገር የለም። ሁሉም ሰው "ነበር" እያለ የሚያወራበት ዘመኑ ላይ ያድርሰው።

"የምሬን ነው የምልህ በልጄ ፊት እንዴት እንደምሳቀቅ ሃሳቡ የለህም"

"ማለት እንዴት?"

"ከስራ ስወጣ ትደውልና 'አባዬ እንትን ይዘህ ና፣ እንትን ግዛልኝ ትላለች"

"ሳትገዛ ገብተህ 'ረሳሁት' ትላት ነበር?"

"ኧረ እሱማ ቢሆን ባልከፋ!"

"እና ምን ታደርግ ነበር?"

"ከባለቤቴ ጋር በስልክ ውስጥ በቃላት እንጠቃቀስና ወደቤት ልገባ ያልኩት ሰውዬ ሰፈር ያለ ድዳ ማስጫ ላይ ተቀምጬ አመሻለሁ"

"እንዴ፣ ለምን?"

"ባለቤቴ ደውላ፣ ልጃችን መተኛቷን እስክትነግረኝ"

............🤔
እንዳልኩት ነው፣ ሁሉም ሰው "ነበር" እያለ ለሚያወራበት ዘመኑ ያድርሰው።

@gere_perspective
በዘንድሮው ዓመት ከሮበርት ኦፐንሄሚየር ቀጥሎ በሲኒማ ስክሪን በደንብ የተዋወቅነው ሰው ናፖሊዮን ቦናፓርቲ ነው። በናፖሊዮን ፊልም ላይ ከ9ኛ ክፍል ጀምረን በነበረን የታሪክ ንባባችን የምናውቀውን ሰው ፍንትው ተደርጎ ተስሏል። ያው ጎበዝ አይደሉ? ለዚህ ለዚህ! የጦርነትን ትዕይንት ራሱ ከትራጀዲነት ወደ Fantasy አሸጋግረውታል፣ ብቻ ከሽነውታል።
በናፖሊዮን ታሪክ ውስጥ ግን በሰው ልጅ አፈጣጠር ጅማሮ ላይ አንድ አረዳድ (Understanding) ይጨምርልናል። በናፖሊዮን ታሪክ ሴት የተፈጠረቺው ኦሪት ዘፍጥረት ላይ "ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም" በሚለው መነሻ ለረዳትነት ብቻ አለመሆኑን ያሳየናል። ይልቁንስ ሴት የተፈጠረቺው ወንድነት ውስጥ ያለውን የበዛ ጦረኝነት፣ ግልፍተኝነትና ትኩሳታምነት ላይ ማቀዝቀዣ ለመሆንም ይመስላል። አለ አይደል ለሁሉም ገዢ ሃይል እንዳለው፣ የጫካው ጌታ አንበሳ ለቀበሮ እንደሚሸነፍ ሁሉ ወንድም ለሴት እንዲያጎነብስና ትኩሳቱም ጦረኝነቱም በሴት ፊት አቅም አጥቶ ኑባሬው Balanced እንዲሆን ሴት እንደተፈጠረችለት አድርገን ልንረዳ እንችላለን፤ ከጀብደኛው ናፖሊዮን ቦናፓርቲ ታሪክ።

"France......Army.........Josephine"

A must watch movie. #moviestowatch

@gere_perspective
Movies to Watch | Land of Bad

This is Us ላይ የማውቀው ጃክ (Milo Ventimglia) እንደሚተውንበት ሳውቅ ተሯሩጬ ነው ያየሁት። (You all knew already, am obsessed with that show)

Action Film እዩ ብዬ ጋብዣችሁ አላውቅም። አለ አይደል፣ የድመት ነፍስ የያዘ አክተር በእሳቱም በውሃውም ላይ እየተረማመደ፣ ባገኘው ላይ ክንዱን ሲያሳይ፣ ወይም የሆነ በቀለኛ በጠላቶቹ ላይ ሲረማመድ ወዘተ አይነት ትዕይንት በማይበት ሰዓት At a moment ዘና ለማለት ካልሆነ በቀር፣ ተነክተንበት ልናወራለት የሚያስችል ሃይል የለውምና ደመነፍሴ የመራኝን ባይም ለሰው Recommend አላደርግም። Land of Bad ሲጀምር አካባቢ የአሜሪካ ወታደሮች ተልእኮ መሆኑን ስረዳ፣ ያው የሸለቸንን የሚሊተሪ አቅም ሊያሳዩን ስለመሰለኝ እየደበረኝ ነበር። But they have a story and they know how to tell in a suspense. እና ደግሞ በአክተር ዙሪያ የሚያጠነጥን ፊልም አይደለም። በፊልሙ ላይ የሚታዩት ሰዎች በሙሉ ዓለምን የሚመለከቱበትን Perspective ለተመልካች ያጋባሉ። በ Cause and Effect የበለጸጉ ድንቅ ትዕይንቶችን ያካተት፣ ያለማጋነን Just Worthy ፊልም ነው።

ለቅዳሜ ከሰዓትዎ!

@gere_perspective
ሃበሻ በቋንቋው ተራቅቆ ያስነገራቸው አያሌ ተረትና ምሳሌያዊ ንግግሮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ እንከን ያለባቸውና ዘመንን የማይዋጁ መኖራቸው እሙን ነው። ነፍሴን አስይዤ የምወራረድበት ሃቅ ቢኖር ግን፣ አንዳቸውም ቢሆኑ ያለምክንያት አለመባልና አለመነገራቸውን ነው። እደግመዋለሁ፣ በርካታ ጊዜና ቦታን የማይዋጁ አባባሎች ግን አሉ፤ እነሱን እንተዋቸው።

ብዙ ጊዜ ከሚገጥሙኝ ጠያቂዎች መካከል "ችግር በቂቤ ያስበላል" የሚለው ምሳሌያዊ ንግግር እንደማይገባቸው ነው። በርግጥ አንዳንዴ ራሴም ላስረዳ ስጀምር አወሳስበዋለሁ። ሰው እንዴት ተቸግሮ ቂቤ ይበላል? የሆነ መጣረስ ያለው ይመስላል አይደል?!🤔

የዚህን ምሳሌያዊ ንግግር ጭብጥ በአሁንኛ ምሳሌ ላስረዳ። ድሮ ጊዜ "በአይሮፕላን ሄጄ አቃለሁ" ተብሎ ሁላ ጉራ ይነገር ነበር። ከጉራ የተቆጠረው ሲበዛ የቅንጦትና ብርቅ ስለነበር ነው። እነሆ አሁንስ? አሁንማ እድሜ ለችግር(...) "በአይሮፕላን ሄጄ የማላቀው እኔ ብቻ ነኝ" ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የተለመደና የተመረጠ መጓጓዣ ሆኗል። በርግጥ እኔም ሃዋሳ የሚሄድ Plane ውስጥ ገብቼ አቃለሁ። "ሊነሳ ነው፣ ቀበቷችሁን እሰሩ" የሚለውን አረፍተ ነገር አራት ነጥብ ሳያደርግበት በድርብ ሰረዝ አያያዥነት "፤ እናም በዚሁ ሊያርፍ ስለሆነ ያሰራችሁ እንዳትፈቱ" ስለተባልን፣ ሄድኩኝ ብዬ ለመጎረር በቂ አልነበረም። 🤣

ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ፣ ያው ሰው ሁሉ ኬንያ ደርሶ በሚያስመልስ ገንዘብ፣ ጎንደር የሚመላለሰው አልፎለትና አቅሙ ስለፈቀደ አለመሆኑን ሁላችንም እረዳለን። ታዲያ ሃበሻ ጎበዝ አይደል፣ "ችግር በቂቤ ያስበላል" ይልሃል!🤔

@gere_perspective
ጠንቋይ ነኝ የምትል አንዲት ፈረንጅ Inbox አደረገቺልኝ።

ምን አለቺህ?

ስለእጣፋንታህ ማወቅ ከፈለግህ የልደት ቀንህንና ፍቶህን ላክ አለቺኝ።

እና ላክላት?

አዎ እስኪ ጉዷን ልየው ብዬ።

ከዚያስ?

Breakup ላይ መሆኔን፣ የተጣላነው በኔ ጥፋት እንደሆነና ሌላም ሌላም ነገር ነገረቺኝ።

እና ምን ያህሉ ልክ ሆነ?

ያው እሱማ አብዛኛውን ልክ ነች፣ ግን ተጨማሪ እንድነግርህ ከፈለክ መዳፍህን ፎቶ አንሳና ላክልኝ አለቺኝ።

እና አንተም ጉዷን ልየው ብለህ ላክላት?

አዋ! ከዚያ ግን ምን ያለቺኝ ይመስልሃል?

እሺ ምን አለቺህ?

ብዙ በህይወትህ ዋጋ የምትሰጣቸው ሁነቶች በቅርቡ ሲከናወኑ ይታዩኛል። አስደሳቹም አስጨናቂውም የህይወትህ ክፍል መዳፍህ ላይ ይነበባል። በዝርዝር ማወቅ ከፈለግህ በሚከተለው Paypal አካውንት $30 አስገባልኝ።

🤣እና መክፈያ መንገድ ቸገረህ ወይስ ምን አልካት?

ምን እላታለሁ ያው 'አካውንቴ ላይ ያለው 74 ብርስ መዳፌ ላይ አይነበብምን?' ነዋ! ሆ!

————ስራ ቦታ አንዱ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ጨዋታ ነው።

@gere_perspective
ታክሲ ውስጥ የምሰማው የአንዱ Real Estate ማስታወቂያ

"ይፍጠኑ በመኪና ዋጋ ቤትዎን ይሸምቱ!"

እንዴ በBugatti ነው ወይስ በSuzuki ዋጋ ብዬ ልወዛገብ አሰብኩና፣ ለካ ሳይክልም የለኝም!🤣 አስተያየት ለመስጠት እንኳን የማንችልበትን ማስታወቂያ የሚያስነግሩት ታክሲ ውስጥ ተዘውትሮ በሚሰማ የሬዲዮ ጣቢያ ነው።

እንዲህ ነው መጣረስ!🤔

@gere_perspective
፬ ኪሎ አካባቢ የCBE ATM እየተጠቀምኩኝ ድንገት ቀና ስል ፎቷቸው በፖስተር ተሰርቶ የተደረደሩ ፈገግታ የበዛባቸው ተባዕት ፊቶችን አስተዋልኩ። ስማቸውን እያነበብኩ ከስር እንዲህ የሚል ቃል ስፈልግ ነበር።

"ONLY GOD CAN JUDGE ME, THANKS MOM"

😂

@gere_perspective
This browsing era of the world is just a madness. በዚህ ዘመን አንዳንዶች ገንዘብ የሚያገኙበትን መንገድ ስንመለከተው ያስደነግጣል። Accidental Billionaires ከምንላቸው የኢንተርኔት መተግበሪያ (Facebook, YouTube, X ወዘተ) ፈጣሪዎችን ወደጎን ትተናቸው መተግበሪያዎቹን የሚጠቀሙ ነቄ ሰዎች ድንገት ሳያስቡት በነፃ ሁሉ ሚሊዮን ዶላሮችን ይዝቃሉ። ከዚህ በታች ያያዝኩት በሚሊዮን ዶላሮች የተሸጡ የቴሌግራም Usernames ናቸው። በቀዳሚነት ላይ የሚገኘው news የተሸጠው ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። ከመጀመሪያዎቹ 20ዎቹ መካከል potus የሚለው የጆ ባይደን አካውንት ይገኝበታል። ethiopia ራሱ ተሸጣለች፣ በ3ሺህ ዶላር። 😂

ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ምንም! ለምክር የሚበቃ የምለው ቢኖረኝማ ራሴን እመክርበት ነበር። ለማንኛውም ግን ሰዎች ሊፈልጓቸው ይችላሉ ብላችሁ የምትገምቷቸው Usernames ካላችሁ አሁንም ለሽያጭ ማቅረብ ትችላላችሁ።

@gere_perspective
እያዩ ፈንገስ፣ ፍራሽ አዳሽና እብደት በህብረት የተሰኙት የመድረክ ገጸባህሪያት የሚመሳሰሉበት አንዱ ነገር ሶስቱም ከመንጋው የሚለዩበት ተቀጥያ ስም ስላላቸው ነው። እብዱ ወይም ሰካራሙ የሚል። ሌላው ደግሞ ነጻ ትዝብቶቻቸውን በሚናገሩበት ጊዜ ለሃገር ይበጃል ያሉትን ፖሊሲ ይቀርጻሉ፤ ይተነትናሉ። ማህበራዊ ህጸጾቻችንን በደፋርና ታዛቢ አንደበቶቻቸው ለይተው ያቀርባሉ። እና ፖሊሲ ከማቅረባቸውና ወፈፍም አለፍም ከሚያደርገው ባህሪያቸው አንጻር ለሃገራችን ፖለቲካ እንደ ብርቱ ተፎካካሪ ፓርቲ ልንቆጥራቸው እንችላለን🤣

So, ለዚያ ነው።

አማን አውለኝ!

@gere_perspective
የገረመው መነፅር📗📒📕
Photo
MEL GIBSON 🤝 ገ/ክርስቶስ ደስታ 🤝 ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

ቁሳዊ በሆነው ዓለም በሰው ልጅ የዕለት ከዕለት ህይወት ውስጥ የኪነጥበብ ሚና እየቀነሰ መምጣቱ ይታወቃል። እንደዛም ሆኖ ግን አልፎ አልፎም ቢሆን ተጽዕኗቸው እጅጉን የገነኑ የጥበብ ውጤቶችን እንመለከታል። ከነዚህም ውስጥ ከክርስቶስ ብርሃነ ስቅለት ጋር የተገናኙትን ሶስት ድንቅ የጥበብ ውጤቶች እንመለከታለን።

የመጀመሪያው የክርስቶስን ጥልቅ ፍቅር ያየንበትና በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን፤ ምናባችን ያልደረሰበት የክርስቶስን መከራ አይተን በእንባ የተራጨንበት The Passion of The Christ ፊልም አንዱ ነው። የክርስቶስን የመስቀል ላይ መከራ ስናስብ ሁሉ ይህ ፊልም ወደምናባችን ይመጣል። የፊልሙን ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ለማስረዳት ቀላሉ መንገድ የፊልሙ ፖስተር በራሱ እጅግ ICONIC ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ሰው ኃይማኖታዊ ፋይዳ ካለው ስዕለ አድህን ጋር ሲምታታበት ማየት በቂ ነው። በዚህም የተነሳ ዳይሬክተሩን MEL GIBSON 'እንጀራ ይውጣልህ' ብለን እንመርቀዋለን፣ በሃበሽኛ። ውይ ለካ ወጥቶለታል🤣፤ በቃ እንጀራውን የሚበላበት እድሜና ጤና ይስጠው።

ሁለተኛው ድንቅ ART ደግሞ የገጣሚና ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ በቀይ ቀለም ብቻ የተሳለው የክርስቶስን የመስቀል ላይ ውሎ የምናይበት ጎሎጎታ/ስነ-ስቅለት የተሰኘው ስዕል ነው። ሰዓሊው ገብረክርስቶስ ደስታ የሥዕል ት/ቤት መምህር ሳለ አንዱ ተማሪው ስነቅለቱን በጥቁር ሰው መልክ አድርጎ በመሳሉ፣ ክርስቶስ በደም እንጂ በመልክ አለመሰቀሉን ለማመልከት ይህንን ስዕል እንደሳለው ይነገራል። በዚህ ስዕል ዙሪያ ሌላው ጠቢብ ቴዲ አፍሮ "ክርስቶስ ወ ገብረክርስቶስ" የተሰኘ ዘመን አይሽሬ ግጥምን ገጥሞበታል። እነሆ ጥቂት ስንኞች።
............
ከቀናት ባንዱ ዕለት፣
ሰዎች ሲሟገቱ፥ በቀለሙ ጉዳይ ሲከራከሩበት
በተመፃዳቂ የምሁር አንደበት፣
በአንዱ አፍ ሲጠቁር፥ ባንዱ አፍ ሲነጣ
መታገስ አቃተው፥ ሰዓሊው ተቆጣ
ስሜቱ ገንፍሎ፥ በቡርሽ ጫፍ ወጣ።
ሀሳቡን የሚገልፅ ቀለም እስከሚያጣ፣
ሸራ ላይ ሰቀለው፥ እንጨት አመሳቅሎ
አልወጣልህ አለው፥ ፍቅርን ስሎ ስሎ።

ስሎ ስሎ ስሎ፥ ፍቅርን ስሎ ስሎ
በሳለው እየወጋ በደማው እየቀባ፣
'ክርስቶስ ደሙ እንጂ ዘሩ አልተሰቀለም፣
እንጨቱ ላይ ያለው እውነት ይሄ አይደለም።'
እያለ እስኪናገር፥ የስዕሉ አንደበት
ገብረክርስቶስም ለክርስቶስ የሚሆን፥ ቀለም እስኪያልቅበት
በነጩ ሸራ ላይ፥ እስከአሁን የሚወርድ ደም አፈሰሰበት።
ቀለም፣ ቀይ ቀለም! የደም ቀለም።
የሁሉም ነው እንጂ የማንም አይደለም፣
ፍቅር ዘር አይደለም። ©ቴዲ አፍሮ

ሶስተኛው የጥበብ ውጤት ደግሞ የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ "ሕማማት" የተሰኘው መጽሐፍ ነው። በክርስቶስ ሕማማት ዙሪያ የተሰነዱ በርካታ መዛግብትና የህትመት ውጤቶች አሉ ። በግል ንባቤ በሕማማት ልክ ወደ ሰው ልጆች የሚጋባን Narration ይዞ ያገኘሁት የለም። ሕማማትን የእምነቱ ተከታዮች ብቻ እንዲያነቡት የሚተው መጽሐፍ አይመስለኝም። ክርስትናን እና ክርስቲያኖችን መረዳት የፈለገ ሁሉ ቢያነበው የሚያተርፍበት ውብ መጽሐፍ ነው።

ብርሃነ ስቅለቱን በማስመልከት የጥበብን ዋጋ ከፍ ካደረጉ ስራዎች መሃል በግሌ የመረጥኳቸው እነዚህን ነው። በርግጥ በሌላ Scenario ደግሞ ብንመለከት አንጸባራቂ ኮከብ መሆን የቻሉ የተመረጡ የጥበብ ውጤቶች መኖራቸው እሙን ነው። ሰምና ወርቅ አንዱ የማህበረሰብ ኪነጥበባዊ ሃብት ነውና በዚች ሰምና ወርቅ ጽሁፌን ልቋጨው።

የየሩሳሌም ሴት፣
ጎልጎታ ላይ ሠርታ ቤት፣
እግዚአብሔር ያጥናሽ አልናት ወይ፣
ወልዳ አልሞታትም ወይ!

እንኳን ለብርሃነ ስቅለቱ በሰላም አደረሰን!

@gere_perspective
አሁን አመሻሹ ላይ ኳስ እያየን አንዱ በጭንቀት ከኋላችን ጮክ ብሎ "ውደቅ" ሲል ነበር። ደሜ ውስጥ ካለው የሃበሻ እምቢተኛ መንፈስ አንጣር በርግጥ እንድሰማው የጠበቅሁት ቃል "ተነስ" የሚለውን ነበር። መቼም ያው ሁሌ የጠበቁት አይሆንምና፣ ይሁን!

እንዲያም ሆኖ ግን ኳስ ማየት ቆንጆ ነገር ነው። አለ አይደል "ሙዚቃ እሰማለሁ"፣ "ፊልም አያለሁ"፣ "መጽሐፍ አነባለሁ" ተብሎ በኩራት እንደሚነገረው ሁሉ "ኳስ አያለሁ" ቢባልም መጥፎ ነገር የለውም። የሁሉም ትርጉም Physically Audit ተደርጎ እስከማይሰላና ግንኙነታቸው emotionally እስከሆነ ድረስ፣ ዋጋ የሰጠነው ነገር ሁሉ ዋጋ እንደሚኖረው ይታመናል።

በዚህ ሁሉ መሃል ታዲያ "የመርቆሪዎስን ነገር ሳስበው በጣም ይገርመኛል" ስትለው "እውነትህን ነው ለአንድ ክለብ ይሄን ያህል ታማኝነት ይገርማል፣ ዘንድሮ ዋንጫ ቢበላ ደስ ይለኛል" ብሎ የሚቀጥልልህ ሰው አይነት Obsession ግን ደግም አይደል። ይታረም🤔

@gere_perspective
"ምሳ ምን አለ" አላት አስተናጋጇን በችኮላ።

ብዙ ነገሮችን 'በስጋ' እያለች ስትጠራ ቆይታ 'ድንች በስጋ' ላይ ስትደርስ አስቆማትና "አዎ፣ እሱ ይሁንልኝ" አለ። ከሆነ አፍታ በኋላ ድንች በስጋው በሠፊ ትሪ ላይ ከተዘረጋ እንጀራ መሃል በአነስተኛ ጣባ መሳይ ሳህን ከፊቱ ቀረበለት።

"ተሰርቶ የቆየ ነው እንዴ!?" አለ እጅግ በከፍተኛ የድንገጤም የቁጣም በሆነ ድምጽ። ምናልባትም የድንጋጤ ድምጹን ምግብ ቤት ውስጥ ለማውጣት መኮረኒ አዛችሁ ውስጡ የሆነ የሚንቀሳቀስ ቁምቡርስ ማየት ሊጠበቅባችሁ ይችላል።

አስተናጋጇ ግን እጅግ በተረጋጋ ድምጽ፣ "የለ የለ፣ እንዴት ሲደረግ? አሁን እያየኸኝ? ድንቹን ላጥ ላጥ ከተፍ ከተፍ፣ ሽንኩርቱን ቆላ ቆላ፣ ስጋውን ቆረጥ ቆረጥ አድርጌ አንተክትኬ እያቀረብኩልህ¡!🤔 አላየኸኝም እንዴ"

"እ..እ...እ"

"ግዴለህም፣ የማይናገረውን ብላ!" ብላው ውሃ በብርጭቆ ሞልታለት፣ እንደተወዛገበ ትታው ሄደች።

@gere_perspective
ሲኒማ ቤት የምትሄዱ የአርሰናልና የዩናይትድ ደጋፊዎች አድቡ! ለአተኳኮስ ጭብጨባ፣ ለአገዳደል ጭብጨብ፣ ለአለቃቀስ ጭብጨባ፣ ጭራሽ ለአሳሳም ፉጨት! ኧረ ተው እንዴ!🤔

ለማንኛውም ትናንት የተመረቀው "ትዝታ" ፊልም እንደኳስ በጭብጨባና በፉጨት ታጅቦ ነበር የታየው። አንዱማ ጭራሽ "አቦ ይቻምህ!" ሲል ነበር፤ አክተሩ አክተሪትን ስሞ ሲመለስ😂

ምን ለማለት ፈልጌ ነው፣ ደራሲና ዳይሬክተሩን ዳንኤል አንማውን ላመሰግን ነው። ከፉጨቱም ከጭብጨባው መለስ ብለን ላየነው ሰዎች በጥንቃቄ የተሰራና ጥም ቆራጭ ፊልም እንደሆነ እንረዳለን። ያው ወትሮም የኢትዮጵያ ሲኒማ ጎበዝ ተዋናይ አጥቶ አልተቸገረምና፣ ስለትወናቸው ምንም አልልም። ዳኒ አንተ ግን ይቻምህ!🤔

@gere_perspective
ብቅል እና ብሶት መቼም እጅና ጓንት ናቸው። እና ደግሞ  የትውልዱ የብሶት ጉዳይ ሄዶ ሄዶ "ይች ሃገር" የሚል ሃረግ ላይ ይቆማል። እና "አሁንስ ከዚቺ ሃገር ነቅሎ የሚወስደኝ" ብዬ ላማርር ስል ፓስፖርት ራሱ የለኝም።

በነገራችን ላይ ፖስፖርት የለኝም ስላችሁ፣ ሳላወጣ ቀርቼ አደለም። ከአራት ዓመት በፊት አጠር ካለች 8 ወር ጥበቃ በኋላ ያወጣሁት ፓስፖርት ነበረኝ። እናስ፣ አትሉኝም። እናስ ማለት ጥሩ ነገር ነው። ይሄ በጥበቃ የመጣ ፓስፖርት ከዛሬ ነገ ዓለም ያሳየኛል ብሎ ሲያስብ አራት ዓመት ሞላው። ይሄኔ ተስፋ ቆረጠ። ተስፋ ቆርጦም ዝም አላለ። አንዱን መርከበኛ ጓደኛዬን ተከትሎ ኮበለለ። በአሁኑ ሰዓት ሜዲትራኒያን ባህርን እያቋረጠ ነው። ከተሳሳተ ሻንጣ ጋር ተዳብሎ ከድቶኝ ቢኮበልልም፣ ቢያንስ ቢያንስ ከሰፊው ህዝብ በተለየ ሁናቴ ፎቶና አሻራዬ ዓለምን እየዞረ በመሆኑ ኩራት ሊሰማኝ ይዳዳል። ማን ያውቃል አንድ ቀን ዋስ ሆኖ ሊወስደኝ ይችላል።

ጠላ እየጠጣሁ ነው ለማለት ያህል ነው፣ ሰናይ ቅዳሜ!

@gere_perspective
የአከራይ ተከራይ ውል ለመያዝ በጠዋቱ ቀበሌ ተገኝቼ ነበር። እናም አንድ ነገር ተገንዝቤያለሁ፤ በእዚያ ከተገኘነው ተዋዋዮች መካከል አከራይ የሆኑት በሙሉ በሚባል ደረጃ ወገባቸው የጎበጡ ሽማግሊቶች ናቸው። የወጣትነት ዘመናቸውን ውለታ ውለውለት እየካሳቸው ይመስላል። የዘመኔን ወጣትነት ሳስበው ታዲያ ድብርት ተጫጫነኝ፣ ቡና ጠማኝ። በርግጥ እንኳን የሽምግልና ወቅት ሃብት ይቅርና ራሱ ሽምግልና የሎተሪ ያህል ሩቅ በሆነበት ትውልድ ውስጥ መሆኔን ሳስበው፣ የምጠጣው ቡና የደበዘዘ ቀኔን ቦግ ለማድረግ አቅም ያገኛል። Its not my fault ብለህ መሸብለል ነው።

ወደ ውል መዋዋሉ ልመልሳችሁ። ከፊቴ ከነበሩት ተረኞች መሃል አንድ ምዕራብ አፍሪካዊ ጎረምሳ እና በነጭ ሽበታቸው ላይ ያለፈ ማሰሪያ ያለው ክብ መነጽር የለበሱ ቀይ(ከኔም ይቀ'ላሉ😂) ሴትዮ ነበሩ። እናም ተራ ደርሷቸው ጉዳያቸውን ማስረዳት ጀመሩ።

"እንደምታየው የኔ ተከራይ የውጪ ዜጋ ነው። እናም ያው በአማርኛ የተጻፈ ውል ላይ ስለማይፈርም፣ የሰጣችሁኝን ውል ወደ እንግሊዝኛ ቀይሬ ተፈራርመናል። እሱን እንድታጸድቁልኝ ነበር"

ተቀብሎ ለአፍታ ከአየው በኋላ "ተተርጉሞ መምጣት አለበት" አላቸው።

"እህ፣ እኮ ተርጉሜ ያመጣሁት እንግሊዝኛ ነው አይታይህም"

"አየሁት እሱማ፣ ትርጉሙ በህጋዊ ተርጓሚ ጸድቆ ማህተም ተመትቶበት መቅረብ አለበት"

"የምን ህጋዊ ተርጓሚ ነው? ያው እያየኸው ስም የሚለውን Name፣ ፆታ የሚለውን Gender ብዬ ለመተርጎም ነው አስተርጓሚ የምሄደው?"

"እንግዲህ መፍትሄውን ተናግሬያለሁ፣ ስታድየም አካባቢ ሄደው አስተርጉመው ያምጡ"

"አንተ ራሱ አታነብም መሰለኝ፣ ከየት ነው አንስተው ያመጡህ፣ እንጂም Name ስም መሆኑን ማረጋገጫ አምጪ አትለኝም ነበር"

ከዚህ በኋላ የነበረው ቃለ ምልልስ አብዛኛው"አይ ይች ሃገር" የሚል ሃረግ የበዛበት እልህ፣ ንዴት፣ ድካም የበዛበት ነበር።
አብሯቸው የነበረው ጎረምሳ ሃገር አማን ብሎ ስልኩን እየነካካ ያያቸው ነበር። ሴትዮዋን ሌሎች ተገልጋዮች መክረውና ጠቁመው ካረጋጓቸው በኋላ "ይሁና..." ብለው በረጅሙ ተንፍሰው ተከራያቸውን ለማስረዳት እጁን እየሳቡ ከተሰበሰበው ሰው መሃል ይዘው ወጡ።

በከተማይቱ እልፍ የውጪ ዜጎችና ድርጅቶች የመኖራቸውን ያህል ይሄ ከላይ ያነበባችሁት ቃለምልልስ በየቀበሌው ከሚሰሙ ድምጾች መሃል እንደሆነ ይሰማኛል። እንደ መፍትሄ ፎርሙን በእንግሊዘኛም አዘጋጅቶ በአማራጭነት ቢቀርብ በቀላሉ መፈታት ይችላል።

ሰናይ ቅዳሜ!

@gere_perspective
ዩንቨርስቲ እያለን የምንወደው አርባምንጭ ማለታችን ነው፣ INFOKEN - ኢንፎክን የሚባል የመጻሕፍት ማዕከል ነበረን። ነበረን ያልኳችሁ፣ ስለ ቀደመ ጊዜ ለማውራት ያህል ነው እንጂ ማዕከሉ አሁንም በንባብ የነቃ ትውልድ ለማፍራት በትጋት ላይ የሚገኝ ነው። ማዕከሉ ከሚሰራቸው ስራዎች መሃል ዋነኛው ሁለገብ መጻሐፍትን ለዩንቨርስቲው ማህበረሰብ በቅናሽ ዋጋ ማከራየት ነው። ከኪራይ በሚገኘው ገንዘብም ሌሎች መጻሕፍትን በመግዛት ራሱን ያደራጃል። የማዕከሉ አባላትም ዋነኛ ሚናቸው እነዚህን መጻሕፍት ማከራየትና በሰዓቱ ተመላሽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

ታዲያ በስራችን ወቅት ዋነኛው ፈተና፣ ተማሪዎች ለንባብ የተዋሱትን መጽሐፍ ሳይመልሱ ይጠፋሉ። በተለይ ይሄ ነገር ተመራቂ ተማሪዎች ላይ ይበረታል። በዓመቱ ከተከራዩት መጻሕፍት መካከል ቢያንስ 30% የሚሆኑት አይመለሱም። ይሄ ድርጊት የማዕከሉን የመጻሕፍት ክምችት ቢያመነምነውም እኛ ኢንፎክናውያን ግን ብዙም አንደነግጥም። ምክንያቱም በአንድም በሌላም መንገድ ማዕከሉ የተቋቋመበትን ዓላማ እንደማይስት ስለምናምን ነው። ማለትም መጻሕፍት የትም ሄዱ የትም ለንባብ ጥቅም ብቻ እንደሚውሉ እናምናለን። አንድ ተመራቂ ተማሪ የተዋሰውን መጽሐፍ ሳይመልስ ይዞት ከጊቢ ቢወጣም፣ መጽሐፉ ግን በሄደበት ሁሉ ስራውን መስራቱን አያቆምም። ስለዚህ ኢንፎክን አይከስርም ማለት ነው።

ይሄንን ለመጻፍ ያነሳሳኝ ባለፈው ሳምንት ያጋጠመኝን ገጠመኝ ልነግራችሁ በመሻቴ ነው። አንዲት ሴት ስልክ ደወላ ስሜን ካረጋገጠች በኋላ፣ በቴሌግራም የመጻሕፍት ውይይት ላይ ለተጠየቀ ጥያቄ ምላሽ መመለሴን እንዳረጋግጥላት ጠየቀችኝ። "አይ በፍጹም እኔ ቴሌግራም ውይይት ተካፍዬ አላውቅም" አልኩ። የውይይቱን አይነትና ርዕስ ነግራኝ በድጋሜ እንዳስታውስ አሳሰበችኝ። 100% አስረግጬ አለመሳተፌን ተናገርኩ። የስም ስህተት ሊሆን ስለሚችል ድጋሜ አመሳክራ እንደምትደውል ነግራኝ ስልኩ ተዘጋ።

በሁለተኛው ቀን ያችው ሴት ደወለች። "መጽሐፉ ከጀርመን  ሃገር በቅርቡ እንደገባና አድርሺ ለተባልኩት ሰዎች ሁሉ እያቀበልኩኝ ነው፣ እናም ለአንተ የት ላቀብልህ" የሚል ጥያቄ ጠየቀችኝ።  አሁንስ ይቺ ሴትዮ ለምን በመጽሐፍ ትፈታተነኛለች ብዬ "በቃ እኔ  በመጽሐፍ አልጨክንም፣ ሜክሲኮ ከሆንሽ ሀሁ መጻሕፍት ጋር አስቀምጪልኝ አልኳት።

ከአፍታ በኋላ ደውላ "ስምህን ጽፌ አስቀምጬልሃለሁ!" አለቺኝ። እኔም "እሺ አመሰግናለሁ!" ብዬ ስልኩን ዘጋሁ። በመሃል ረስቼው ነበርና ዛሬ ትዝ ሲለኝ ሜክሲኮ አካባቢ ስለነበርኩ "ሀሁ" ጋር ጎራ አልኩኝ። ጉዳዩን ስነግረው ከትንሽ ፍለጋ በኋላ "ቀዩ ባሐር፣ ኀዘንተኛው ባሕር" የሚል መጽሐፍ አቀበለኝ። እውነትም ስሜ ተጽፎበታል።

እናም ለማለት የፈለኩት የስም ስህተትም ከሆነ "ለኔ ነው የተላከው" የሚል ወገን ካለ አንብቤ የማቀብለው እንደሆነ ለማሳወቅ ነው። የኔ እንዳልሆነ እያወቅሁም የተቀበልኩት ከላይ በጠቀስኩላችሁ የኢንፎክን መርህ መሰረት ነው። መጽሐፍት የትም ይሁኑ የትም እስከተነበቡ ድረስ አይጠፉም፣ አይከስሩም። አይሰረቁም! በቀጣይ ደግሞ ከመጽሐፉ ላይ ሃሳብ አጋራችኋለሁ። ወደ ንባብ!

@gere_perspective
እንደዋዛ የነበረን ሁሉም ነገር መትነን ጀምሯል። የማንመለሰውን መንገድ ብዙ ርቀት ተጉዘናል። "ለይስሙላ ነው" እያልን የምንኮንነው ማህበራዊ ወገንተኝነትና እዝነታችን ሳይቀር አሁን ቢጠሩት አይሰማም። ለካ ባለ ነገር ላይ ነው ኩነኔ፣ ትችትና ወቀሳ። የሰብአዊነት ወዛችንን ደጋግመን አጠብነው። ማጠባችን ሳያንስ ርዝራዥ እንዳይቀር ጨምቀንና ጠምዝዘን አሰጣነው። "ሃገሬን በሃዘን" የተሰኘው የሱራፌል ወንድሙ ግጥም ላይ በባዕድ ሃገር የሚኖር ሰው ሃዘን በገጠመው ጊዜ "ኡኡ" ብሎ ማልቀስ አለመቻሉ ምን ያህል ሰቀቀን እንደሆነበት የሚያሳዩ ስንኞች አሉ። አሁን ያገር ሰው በሃገሩ የለም፣ ከእዝነት ልቡ ሸሽቷል።

ሰሞነኛውን የጎፋ ህዝብ ህመም በተመለከተ በየቢሮው በየቡናው ላይ የሚሰሙ ድምጾችን ላስተዋለ፣ የወትሮው ያገር ሰው በቦታው እንደሌለ ያመላክታል።

"ኧረ በስማም አንተ የሞቱት እኮ ቁጥራቸው 150 አለፉ ተባለ"

"እንዴ የመቼህን? ገና ማታ ላይ 170 እንደደረሱ አንብቤያለሁ"

"ገበያ ነበር እንዴ፣ ይሄ ሁላ ሰው እንዴት አንድ ቦታ ላይ ተገኘ"

"በየሱስ ስም፣ 260 አለፉ የሚል ነገር ተጽፎ አየሁ"

መሰል፣ መሰል ዘገባዎች ከዚያና ከዚህ ይወራወራሉ። በአንዱም ውስጥ ሃዘኔታ የለም። በአንዱም ውስጥ "እኔን 💔" የሚል ድምጽ የለም። አስመሳይ ሃዘኔታችን ለዛ ነበረው። ለወትሮው ስንሰበር ደረት የሚደልቅልን አይቸግርም ነበር። ዛሬ እሱ ብርቅና ሩቅ ነው። እንደማህበረሰብ ሰው ሟች መሆኑን አለቅጥ አምነናል። አለቅጥ ተፅናንተናል። Trauma ሸሽቶናል። ሃዘን የሚጎዳቸውንና የሚበረታባቸውን ሰዎች ሳይ ብርቅ እየሆኑብን ነው። ሁሉም Move on ላይ ጡንቻ አውጥቷል። ይሄ ይሄ ያስፈራል ሲበዛ።

አንዱ ጓደኛዬ ምን አለኝ፣ "ከንፈር የሚመጡ እናቶች የት ገቡ"

አዎ እንዴት ነው ግን ፣ ከንፈር መምጠጥ እንኳን ብርቅ የሆነብን። አዎ ከተለማመዱት ሁሉም ነገር ይለመዳል። በሞት አለመደንገጥን ያለልክ ተለማመድን። የሞት ዜና ሰዓት የማብሰሪያ ድምጽ ያህል ትኩረት እስኪያጣ ተጋትነው።

በርግጥ ይሄ ይሄ እንደሚመጣብን ደራሲው አዳም ረታም "ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ" መጽሐፉ ላይ የሚከተለውን ከትቦልን ነበር።
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
" . . . እውነቴን ነው፤ እናቶች ተትረፍርፈዋል፡፡

ነጠላ ደርበው 'ልጄ' የሚሉ፣

መንገድ ላይ የውሸት የሚቆጡ
(መቆጣት የሚችሉ ይመስላቸዋል ግን)

ለጠማው መንገደኛ ፈልሰስ እያሉ (ስለ ወፈሩ ወይም ስለ ደከሙ) ጠላ በጣሳ የሚያቀርቡ
(ይህችን ይህችን እወዳለሁ)

ጠዋት ጎሕ ሳይቀድ ለቤተክርስቲያን የሚታጠቁ፣ ፀሎታቸው ሩቅ የሚሰማ……

ዓይኖቻቸውን ከድነው በፍቅር የሚስሙ
(ጨርቅ የለበሰ ጠበል ያቀፈ ገንቦ)……

'እሰይ የእኔ ልጅ' ሲሉ ትንፋሽ የሚያጥራቸው……

ትልልቅ ጡቶች ያላቸው
(ከአምስት በላይ ያጠቡ)

ቡና እያፈሉ ነጠላ የሚቋጩ
(ሰነፍ ይጠላሉና)

ከሽሮ ወጥ ፋሲካ የሚሠሩ
(ከፍትፍቷ ፊቷ)

በቆሎና በንፍሮ ሽር ጉድ የሚሉ፤ ጋብዘው የማይጠግቡ

የውሸት የሚቆነጥጡ

ሲደነግጡ ነጠላ ጥለው ደረት የሚመቱ

ያለ መሐረብ የሚናፈጡ (በማሽቀናጠር ስላደጉ---- ከወንዝ ወንዝ የሚወረወሩ)

በነጠላቸው ጥለት ዓይኖቻቸውን የሚያብሱ

እነኚህን ዓይነት እናቶች ይጠፉ ይሆናል
('ኋላ ቀር' ብለናቸው)

ብዙ መልካሞችና መልካምነቶች እንደጠፉ ሁሉ……
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
በቅጽበት ላጣናቸው የአንድ ቀበሌ ህዝቦች ለነፍሳቸው ምህረት ይስጥልን። የሚወዷቸውን ላጡ ሁሉ መጽናናትን በቅጡ ይስጥልን። ያጡት ይበቃልና ዳግመኛ ማጣት እንዳይጎበኛቸው በምንችለው እናቋቁማቸው።

@gere_perspective
2024/09/27 21:09:16
Back to Top
HTML Embed Code: