Telegram Web
#የትሩፋት_ሥራ_ጀምር

ጨክነህ ቆርጠህ የትሩፋትን ሥራ ጀምር፡፡ በትሩፋት አጠገብ እየተጠራጠርህ አትኑር፡፡ ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ከማመን ተስፋ ወጥተህ በልብህ እንኳ አትጠራጠር፡፡ ትሩፋትህ ረብህ ጥቅም የሌለው እንዳይሆን የትሩፋት ሥራ ክቡድ አይምሰልህ፡፡ መሐሪ እግዚአብሔር ለለመኑት ሰዎች ጸጋውን ፈጽሞ እንዲሰጣቸው እመን እንጂ ስጦታው እንደየሥራችን አይደለም፡፡ በትጋታችን፣ በማመናችንና በመሻታችን መጠን ነው እንጂ እንደ ሃይማኖትህ ይደረግልህ ብሏልና፡፡

የትሩፋት ሥራም ይህች ናት፣ አንዱ መተምተሚያ አዘጋጅቶ መሐል ራሱን ይተመትመዋል፡፡ በየጊዜው በሚጸልየው ጸሎት እንዳያፍር ትቀርበኛለች ብሎ ያዝናል፡፡ አንዱ አብዝቶ ይሰግዳል፣ ልጸልይ ያለውን ይጸልያል፣ ስለ ጸሎቱ ፈንታ ብዙ ያለቅሳል፣ በልቅሶው ረብህ ጥቅም ያገኝበታል፡፡ አንዱ የልቡና ሥራ የምትሆን ትሩፋትን በመዘከር ይጋደላል፣ ወደ ተወሰነለት ጸጋ ይደርሳል፣ አንዱ ምግብ ነስቶ ሰውነቱን በረኃብ ያስጨንቃታል ጸሎቱን መፈጸም የማይቻለው እስኪሆን ድረስ፣ አንዱ ተናዶ እየመላለሰ ዳዊት ይጸልያል። በመድገም ዘወትር ጸሎትን ገንዘብ ያደርጋታል፣ አንዱ መጽሐፍ ለመመልከት፣ ለመድገም ጽሙድ ሆኖ ይኖራል፣ አንዱ ከአምላክ በተገኙ መጻሕፍት ያለውን ትርጓሜ ምሥጢር ያስበዋል፣ ያስተውለዋል፣ ይመረምረዋል። ወደ ሥራው ይሳባል፤ አንዱ የዐቢይ ምዕራፉን መለያ አይቶ ምሥጢሩን ያደንቃል፣ ዝምታ ይሰለጥንበታል፡፡ በልማድ መጽሐፍ ከመመልከት በልማድ ከመድገም ይከለከላል፡፡

አንዱ ደግሞ ሁሉንም አንድ አድርጎ ይሠራቸዋል፡፡ በዚህም ይሰለቻል፡፡ ዓለማዊ ሥራ ይሠራል፣ ለሐኬት ጽሙድ ሆኖ ይኖራል። አንዱ መጽሐፍ ከመመልከት ጥቂት ምሥጢር ያገኛል፡፡ በዚህም ትዕቢት ያድርበታል፡፡ በሰው መዘበት ያድርበታል፤ ይበድላል፡፡ አንዱ የልማድ ምክንያት ይሰለጥንበታል፣ አንዱም ይህን ሁሉ ድል ይነሣል፤ ከዚህ ሁሉ ይጠበቃል፡፡ ዕንቁ ክርስቶስን ገንዘብ እስኪያደርገው ወደኋላ አይመለስም፡፡ ደስ ብሎህ እግዚአብሔር ያዘዘውን የትሩፋት ሥራ ጀምር፡፡
“እንደ እባብ ልባሞች ኹኑ” ማቴ.10÷16

እባብ ራሱን (ጭንቅላቱን) ለማዳን ሲል ሌላው ሰውነቱን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ኹሉ አንተም እንዲህ አድርግ፡፡ ሃይማኖትህን ለመጠበቅ ስትል ሀብትህን ወይም ሰውነትህን ወይም የዚህ ዓለም ሕይወትህን ወይም ያለህን ኹሉ እንኳን መስጠት ካለብህ ይህን በማድረግህ በፍጹም አትዘን!

አንተ ሃይማኖትህን ይዘህ ወደ ወዲያኛው ዓለም ስትሔድ እግዚአብሔር ደግሞ ኹሉም ነገር እጅግ ውብ አድርጎ ይመልስልሃል፤ ሰውነትህን በታላቅ ክብር ያስነሣልሃል፤ ከሀብት ከንብረት ይልቅም ከመግለጽ ኃይል በላይ የኾኑ በጎ በጎ ነገሮችን ይሰጥሃል፡፡ ኢዮብ ዕራቁቱን ኾኖ በአመድ ላይ ከሞት እልፍ ጊዜ የሚከፋ ሕይወትን እየመራ የተቀመጠ አይደለምን? ነገር ግን ሃይማኖቱን ስላልጣለ አስቀድሞ የነበረው ኹሉ እጅግ በዝቶ ተመልሶለታል፤ ጤናውና ውብ የኾነ ሰውነቱ፣ ልጆችን፣ ሀብቱን፣ ከዚህ ኹሉ የሚበልጥ ደግሞ አክሊለ ትዕግሥትን አግኝቷል፡፡

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ  -  #ገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ)
በቅርብ ቀን ይጠብቁን subscriber.በማድረግ አግዙኝ
#የሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ_ማብራሪያ

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው #“ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡
፩. በመቅድመ ወንጌል “ወአልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤ እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡ በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርም “ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ /ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡
#ሊቁ (ቅዱስ ኤፍሬም) በኦሪ. ዘፍ ፫፥፱ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕምም እንዲህ ይላል፡- “ቸር ወዳጅ የኾነው እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ወዲያው እንደተሳሳቱ ፍርዱን አላስተላለፈባቸውም፤ ታገሣቸው እንጂ፡፡ ይኸውም ምኅረት ቸርነቱን ይለምኑት ዘንድ ነው፡፡ እነርሱ ግን አልለመኑትም፡፡ እግዚአብሔርም ምንም ሳይናገራቸው በገነት ውስጥ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ አዳምና ሔዋን ግን አሁንም አልመለስ አሉ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ድምፁን ማሰማት ጀመር፡፡ ‘አዳምን ወዴት ነህ?’ ይላቸው ጀመር፡፡ አስቀድሞ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስን እንደሚልክላቸው፣ ቀጥሎ ድምፅ አሰምቶ ወዴት ነህ ብሎ መፈለጉም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ ሊያድናቸው እንደ ፈቀደ ያጠይቃል” ይላል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Genesis/፡፡
#ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኦሪት ዘልደትን በተረጐመበት በ፲፯ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን እንመለከታለን፡፡ አንድ አባት ልጁ የማይረባውን ነገር በማድረግ ከክብሩ ቢዋረድም አባቱ እጅግ እንዲወደውና ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ እንዲደክም፤ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች ጋር ይህን የመሰለ ፍቅር ሲያሳይ እናስተውላለን፡፡ አንድ ሐኪም ወደ ታማሚው አልጋ ጠጋ ብሎ በሽተኛውን እንዲጠይቀውና አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግለት፣ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ወደ አዳም ጠጋ ብሎ ሲያነጋግረው እንመለከታለን” ይላል፡፡
ዳግመኛም #በሌላ አንቀጽ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ” ማለቱ፣ ለአቅርቦት መኾኑን ሲገልጥ፡- “አዳም ሆይ! ምን ኾንክብኝ? በመልካም ቦታ አስቀምጬህ ነበር፤ አሁን ግን ቦታህ ተለወጠብኝ፡፡ ብርሃን ተጐናጽፈህ ነበር፤ አሁን ግን ጨለማ ውስጥ አይሃለሁ፡፡ ልጄ! ወዴት ነህ? ይህ ኹሉ እንደምን ደረሰብህ? በአንተ ውስጥ ያኖርኩት መልኬ ማን አበላሸብኝ? በዚህ ያህል ፍጥነት የጸጋ ልብስህን ገፎ የጽልመት ልብስ ያከናነበህ ማን ነው? ውዴ! ባለጸጋ አድርጌ ፈጥሬህ አልነበረምን? ታድያ አሁን ድኽነት ውስጥ የከተተህ ማን ነው? ያን የግርማ ልብስህን ሰርቆ ዕራቆትህ ትኾን ዘንድ ያደረገህ ማን ነው? እኮ የጸጋ ልብስህን እንድታጣ ያደረገህ ማን ነው? ይህን የመሰለ ቅጽበታዊ መለወጥ ከወዴት መጣብህ? የከበረ ዕንቁህን እንድትጥል ያደረገህ ምን ቢገጥምህ ነው? አክብሮ በተወደደ ቦታ ካስቀመጠህና ኹል ጊዜ በስስት ዐይን ሲያነጋግርህ ከነበረው አምላክህ ተደብቀህ እንድትሸሸግ ያደረገህ ምንድነው? ማንም የወቀሰህ ሳይኖር፣ እንዲህ እንዲህ አድርገህ በድለሃል ብሎ የመሰከረብህ ሳይኖር ይህን ያህል በፍርሐት መናጥ ከወዴት አገኘህ?” ይላል /Daily Readings of St. John Chrysostom/፡፡
#ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ሆይ! ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነፃ ካደረገው ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ #“ቅድስት” ማለቱ ንጽሕት፣ ጽንዕት፣ ክብርት ልዩ ሲል ነው፡፡ ይኸውም፡-
· ሌሎች ሴቶች ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሐልዮ አይነጹም፡፡ እሷ ግን የዕንቆራው #ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ቴዎዶጦስ “ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በሕሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ- ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን (በሕሊናዋም በሥጋዋም) ከድንግልናዋ አልተለወጠችም” /ሃይ.አበ.፶፫፡፳፪/ እንዲል ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ናትና፡፡
· #ጽንዕትም አለ፡፡ ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፤ ኋላ ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እሷ ግን ቅድመ ፀኒስ ጊዜ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት (ወትረ ድንግል) ናትና፡፡
· #ክብርትም አለ፡፡ ሌሎችን ሴቶች ብናከብቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን ወለዱ ብለን ነው፡፡ እሷን ግን ወላዲተ አምላክ ወልዳልናለች ብለን ነውና፡፡
· #ልዩም አለ፡፡ እናትነትን ከድንግልና፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች፤ በድንግልናም እያለች ከጡቶቿ ወተት ተገኝተው በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ መጋቤ ፍጥረታት አምላክን የወለደች፤ እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ሱራፌልም በፍርሐት በረዐድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት እሳተ መለኮት ጌታን ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በዠርባዋ ያዘለች ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡

#“ለምኚልን” ሲልም ልክ በዚህ ምድር እንደነበረው ዓይነት ልመና ከዚያ በኋላ ኖሮባት አይደለም፡፡ ስንኳን በሷና በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ፡፡ ይኸውም በቃል ኪዳኗ ማለት ነው፡፡ አንድም በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ማዘከር (ማሳሰብ) አለና፡፡
#“ሰአሊ ለነ ቅድስት” የሚለው ቅዱስ ኤፍሬም የተናገረው አይደለም፡፡ “ታድያ ይህን የጨመረው ማን ነው?” በሚለው ላይም ኹለት ዓይነት አመለካከለት አለ፡፡ “ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መከፈያ ተናግሮታል” የሚሉ አሉ፤ “የኋላ ሊቃውንት ተናግረውታል” የሚሉም አሉ፡፡
#የማክሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ_ማብራሪያ

ለምስጋና ኹለተኛ፣ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ቀንም እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ክርክር በዕለተ ሰኑይ አልቋልና “ባርክኒ” ብሎ ተባርኮ “አክሊለ ምክሕነ” ብሎ ምስጋናውን ይጀምራል፡፡

፩. ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ቢባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም /፩ኛሳሙ.፲፮፥፲፫/፡፡ ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢኾንም የደኅንነታችን መጀመሪያ መኾን አልተቻለውም፡፡ ኤልያስም ምንም ንጹሕ፣ ድንግል ቢኾንም የንጽሕናችን መሠረት መኾን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናችን መሠረት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የመመኪያችን ዘውድ “አክሊለ ሰማዕት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የደኅንነታችን መጀመርያ “ጥንተ ሕይወት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የንጽሕናችን መጀመርያም ኹሉ በእጁ የተጨበጠ፣ ዓለምንም በመዳፉ የያዘ፤ በጠፈር ላይ የሚቀመጥ ፣ ዳግመኛም መሠረቱን ከታች የሚሸከም “መሠረተ ዓለም” የሚባል ጌታችን ነው /ቅዳ.ማር. ቁ.፶፩/፡፡ እርሱም አካላዊ ቃልን በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡ እኛን ስለማዳን ሰው ኾነ፤ ሰውም ከኾነ በኋላ ግን ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ እንደ ወለደችው ኹሉ እርሱም አምላክነቱ ሳይለወጥ ሰው ኾነ፡፡ እርሷ “ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም)” ስትባል እንደምትኖር ኹሉ እርሱም “አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው)” ሲባል ይኖራል /ሃይ.አበ.፷፯፡፯/፡፡ ተፈትሖ ሳያገኛት (ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ) እንደምን እንደወለደችው ግን የማይመረመር አንድም ሊነገር የማይችል፣ ከኅሊናት ኹሉ የሚያልፍ ድንቅ ነው፡፡
በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. “ቃል ሥጋ ኾነ” እንዲል በእርሱ ፈቃድ /ዮሐ.፩፡፲፬/፣ “ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” እንዲል በአባቱ ፈቃድ /ዮሐ.፫፡፲፮/፣ “በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው” እንዲልም /ሐዋ.፲፡፴፰/ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ኾኖ አዳነን፡፡ ሊቁ እንዲህ ማለቱ “ወልድ ያለ ፈቃዱ ሰው ኾነ” የሚሉ መናፍቃን ስላሉ ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንትም፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ፈቃዱ ሰው እንደ ኾነ የሚያምን፤ የሚያስተምር፤ ወይም የአብ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የወልድ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ሌላ ነው የሚል ቢኖር፤ ፈቃዳቸው አንድ፤ መንግሥታቸውም አንድ እንደኾነ የማያምን ሰው ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ብለው አስተምረዋል /ሃይ.አበ.፻፳፫፡፪/፡፡

በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት የምትኾኚ እመቤታችን ሆይ! በድንግልና ጸንተሽ ብትገኚ ላንቺ የተሰጠሸ ጸጋ ፍጹም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይ ቢኾን አንድም በጸጋ ቢያድርብሽ ባለሟልነትን አግኝተሸልና ለአንቺ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ ይህ ከቃላት በላይ የሚያልፈው ባለሟልነቷ ቅዱስ ባስልዮስ ከሌሎች ቅዱሳን ጋር እያነጻጻረ ሲያብራራው፡- “የዚህ ዓለም ነገር ኹሉ አይመጥናትምና የሚመጥናትን ምን ዓይነት ምስጋና እናቅርብላት? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ሲናገር ዓለም አልተገባቸውም /ዕብ.፲፩፡፴፰/ ካላቸው ከከዋክብት በላይ ኾና እንደምታበራው ፀሐይ ለኾነችው ለአምላክ እናትማ ምን ልንል እንችል ይኾን?... ምን ምሥጢር እንደተከናወነ ተመልከት፤ ኅሊናን አእምሮን የሚያልፍ ነገር እንደኾነም አስተውል፡፡ ታድያ የአምላክ እናት ታላቅነት እንደምን ኹሉም ሰው አይናገር? ማንስ ነው ከቅዱሳን ኹሉ በላይ እንደኾነች ያላስተዋለ? እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ የሚልቅ ጸጋን ከሰጠና የሚነኩት ኹሉ ሰው ከበሽታው ከተፈወሰ፣ ጥላቸው ያረፈበት ተአምር ከተፈጸመለት፣ ጴጥሮስ በጥላው ካዳነ /ሐዋ.፭፡፲፭/፣ የጳውሎስ የልብሱ ዕራፊ መናፍስትን ካወጣ /ሐዋ.፲፱፡፲፩/ ለእናቱማ ምን ዐይነት ሥልጣንና ኀይል ተሰጥቷት ይኾን? በምን ዓይነትስ ሥጦታ አስጊጧት ይኾን? ጴጥሮስ፡- ክርስቶስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ስላለው ብፁዕ ነህ ከተባለና የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ከተሰጠው /ማቴ.፲፮፡፲፮-፲፱/ እርሷማ ከኹሉም ይልቅ እንዴት ብፅዕት አትኾን? /ሉቃ.፩፡፵፭/ ጳውሎስ ታላቅ ክብር ያለውን የክርስቶስን ስም በመሸከሙ ምርጥ ዕቃ ከተባለ /ሐዋ.፱፡፲፭/ የአምላክ እናትማ የምእመናን ምግብ የኾነ መናውን ሳይኾን የሕይወት ሰማያዊ እንጀራን ያስገኘች እርሷ ምን ዓይነት ልዩ ዕቃ ትኾን? … ነገር ግን ስለ እርሷ ብዙ እናገራለሁ ብዬ ስለ ክብሯ ጥቂት በመናገር ራሴን በኀፍረት ውስጥ እንዳልጨምር እፈራለኁ፡፡ ስለዚህ ከአሁን ወዲህ የንግግሬን መልሕቅ ስቤ በዝምታ ወደቤ ላይ ማረፍን መርጫለሁ”  ይላል /መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣ ገጽ ፺-፺፩ ይመልከቱ/፡፡

ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲፰-፲፱/፡፡ መተርጕማኑ ይህ ምን ማለት እንደኾነ ሲያብራሩ፡- “ከምድር እስከ ሰማይ መድረሷ የልዕልናዋ፣ በላይዋ ላይ ዙፋን ተነጽፎባት ንጉሥም ተቀምጦባት ማየቱ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀኗ ለመሸከሟ፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ማየቱ ደግሞ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ለማሳረግ አይወጡም አይወርዱም ነበር፤ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከኾነ በኋላ ግን ለተልእኮ የሚወጡ የሚወርዱ ኾነዋልና ሲል ነው”  ይላሉ /ሉቃ.፪፡፲፬፣ ሐዋ.፲፡፫-፬፣ የኦሪት ዘልደትን ትርጓሜ ይመልከቱ/፡፡

ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ በአምሳለ ንጉሥ ካየው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
#የሐሙስ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡

፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ “ወአግኃሦ ለሱራፊ ዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡

  ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰው ኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡

ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪም ያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ፣ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎ የፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡
በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላም በልጆችዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች፡፡ በዚህን ጊዜ ወንጌላዊ ዮሐንስ ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ  ከሰገደላት በኋላ ተመልሶ ወደ ምድር ወረደ፤ ሐዋርያትንም ተሰብስበው ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ፣ እንደሰማና ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንዳሳረጓት ነገራቸው፡፡

ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ፡፡ ከዚያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ‹‹የፍቅር የአንድነት ልጆች፤ ሰላም ይሁንላችሁ! ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ፡፡ እነሆ እኔ እርስዋን በሥጋ ላሳያችሁ፤ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል›› ብሏቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ሐዋርያትም ለዓመት ከቆዩ በኋላ የነሐሴ ወር በሰባት ቀን ዮሐንስ ለሐዋርያቱ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ! ይህን ሁለት ሱባዔ በጾም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው፤ በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን፡፡››

ዮሐንስም እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፤ በነሐሴ ዐሥራ ስድስትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጇ ቀኝ ተቀምጣ፣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ፣ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት፡፡ እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን ባረከቻቸው፤ በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዔ ካህን ሆነ፡፡ እስጢፋኖስም አዘጋጀ፤ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ፡፡ ሁሉም ሐዋርያት በመሰዊያው ዙሪያ ቆሙ፤ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው፡፡

ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ አላት፡፡ ‹‹በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰበኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው፡፡

መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ፡፡ የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም፤ መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ፣ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውትም ቸርነቴ ትገናኘዋለች፤ ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው፡፡››

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለቸው ‹‹ልጄ ሆይ! እነሆ በዐይኖቻቸውም አዩ፤ በጆሮዎቻቸውም ሰሙ፤ በእጆቻቸው ያዙ፤ ሌሎችም ታላላቅ ድንቆች ሥራዎችን አዩ፡፡›› እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ፡፡

የክርስቲያን ወገኖች ሆይ! እኛም በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡ እርሷ ስለ እኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይምረን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን! አሜን፡፡

ምንጭ፡-ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ
የእመቤታችን በዓለ ዕርገት

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረገችበት ዕለት ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

ሐዋርያት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ዕረፍት በኋላ ከእነርሱ በመለየቷ ባዘኑበት ወቅት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው፤ እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድም ተስፋ ሰጣቸው፡፡

በዚያን ጊዜ ወንጌላዊ ዮሐንስ እስያ በሚባል አገር እያስተማረ በነበረበት በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ዘንድ ተቀምጦ አየው፡፡

የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፤ እነርሱም ‹‹የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል›› አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት፤ ‹‹የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ! ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ፡፡›› ከዚያም በገነት ያሉ ዕፅዋት ሁሉም አዘነበሉ፤ መላእክት፣ የመላእክት አለቆች፣ ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ንግሥት እመቤታችን! ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች›› እያለ በበገና አመሰገናት፡፡
"የጽድቅን ሥራ የምንሠራበት ከኾነ አዲሱ ቀን ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመት ለእኛ መልካም ነው፡፡ ኀጢአት የምንሠራበት ከኾነ ግን ቀኑ ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመትም ክፉና መከራ የመላበት ይኾንብናል፡፡ አዲሱን ዓመት በበጐ ሥራ የምንጀምረው ከኾነ በዓመቱ በምናደርገው ማንኛውም ክንውን ላይ በጐ ተጽዕኖ ያሳድርብናል፡፡"
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

መልካም አዲስ ዓመት🙏
ጳጳሳት ደመወዝተኞች፤ ካህናትስ ለምን ፈሪዎች ሆኑ?
.
#ጳጳሳት በደመወዝ ማደራቸው ተገቢ አለመሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል! ስማቸውንም ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር እያነሳን አብዝተን እንነቅፋቸዋለን!  . . . ደመወዛቸው ቢቀር ስንል ግን እንዴት እንደሚያድሩና ሊያገለግሉን ሲወጡና ሲወርዱ ወጪዎቻቸውና አስፈላጊ ግብአቶች እንዴት ሊሟሉላቸው እንደሚችሉ አማራጭ አላስቀመጥንም!
.
ለመሆኑ ስለጳጳሳቶቻችን ምን ያህል እናውቃለን? የምናውቀውስ ምን ያህል በቂ ነው? በምናውቀውስ ምን ያህል እርግጠኞች ነን?  . . . ብዙዎቹ የቤተ ክርስቲያናችን ጳጳሳት (Exceptions are there) ረጅሙን ጊዜያቸውን በትምህርት ያሳለፉ፤ ሙሉ እነርሱነታቸውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠታቸው ቤተሰባዊና  ማኅበራዊ ትስስራቸው የተበጠሰ ወይም የላላ፤ ብዙውን የሕይወታቸውን ክፍልና ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ምንም ዓለም የሌላቸው፤ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ያለውን ዓለም ለመልመድ የማይችሉ፤ ያላቸውን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ሲሉ ያጡና የተዉ . . . ናቸው!!!
.
ለቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የምንሰጠው ለጳጳሳቱና ለካህናቱ ብለን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ብለን እንደሆነና እግዚአብሔርም አገልጋዮቹን እንድንመግብለትና ቀለባቸውን እንድንሰፍርላቸው እንዳዘዘን እንዘነጋለን! . . . ገንዘብ ስለምንሰጥ ብቻ እንጓደዳለን . . . ጳጳሳቱን እናዋርዳለን፤ ካህናቱን እንሰድባለን . . . በጣም የሚገርመው ደግሞ እንደዚህ የምናደርገው ብዙዎቻችን በሰንበት እንኳን ማስቀደስ የሚከብደን ሰነፎች ነን!!! ንስሓውና ሱታፌ ምሥጢሩማ መቼም ቅንጦት ነው ለእኛ!!!
.
ከጳጳሳት አባቶቻችን ጋር ተያይዞ አንድ እውነተኛ ታሪክ ላጋራችሁ!  . . . ሊቀ ጳጳሱ አረጋዊ ሆነው ለአገልግሎት ስለተቸገሩ ረዳት ጳጳስ ይመደብላቸዋል . . . ረዳት ጳጳስ ከተመደበላቸው በኋላ ግን የቤተ ክህነቱ ሠራተኞችም ሆኑ ምእመናኑ ትኩረት ነፈጓቸው፤ የሁሉም ትኩረት ወደ አዲሱ ጳጳስ ብቻ ሆነ፤ አረጋዊውን ሊቀ ጳጳስ ተጠቅመንባቸው ስናበቃ እንደ አሮጌ ዕቃ ወርውረን ረሳናቸው . . . በዚህ መሐል አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ቀሚሳቸው ጠልፏቸው ይወድቁና መንጋጋቸው ይሰበራል፤ ቶሎ የደረሰላቸው ሰው ግን አልነበረም . . . ከተደረሰላቸው በኋላ ደግሞ አስቸኳይ ህክምና የሚያገኙበት ዕድል አልነበረም!  . . . ወደ አዲስ አበባ በአፋጣኝ መውሰድ የሚቻልበት ምንም አይነት የተሻለ አማራጭ አልነበረም . . . ለእንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች ይሆናል ብለን ቀድመን ያሰናዳነው አውሮፕላንም ሆነ ሔሊኮፕተር አልነበረንም!!!
.
እኒህ አረጋዊ አባት ዕድሜያቸውን ሙሉ የደከሙላት ቤተ ክርስቲያንና እንደ ሰም ቀልጠው ያበሩላቸው ምእመናን በዕርግናቸው ጊዜ ፈጽመው ረስተዋቸው ነበር . . . የትናንት ድካማቸውን አስበው እንክብካቤ ሊያደርጉላቸው ሲገባና ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ድጋፍና እንክብካቤ በሚያሻቸው በዕርግናቸው ጊዜ ወጣትና ልጅ እግር ጳጳስ ፍለጋ ትተዋቸው ጠፉ፤ በልጅ እግሩ ጳጳስ ፍቅርና ውዳሴ ተጠምደው ትናንተ በጨለማው ዘመን መንገድ ጠርገው ያገለገሏቸውን አረጋዊውን አባታቸውን ፈጽመው ረሱ!!!
.
ይሔ ብቻ ሳይሆን ብጸዐን አባቶቻችንን ክብረ ክህነታቸውን በጠበቀ መልኩ የምናሳክምበት የጤና ሥርዐትና ሆስፒታል ስለሌለን እንደ ተራ ሰው በማያምኑና ክብረ ክህነት ምን እንደሆነ በማያውቁ ባለሙያዎች ያለአግባብ እንዲስተናገዱና እንዲነካኩ፤ ከምእመናን ልጆቻቸው ጋር እንዲጋፉ፤ ወረፋ ጠብቀው እንዲስተናገዱ ፈርደንባቸዋል . . . 
.
በእነዚህና እዚህ ባልተጠቀሱ መሰል ማሳያዎች የተነሳ የቤተ ክርስቲያንንና የክህነትን ክብር ለመጠበቅ ሲሉ ብጹዐን አባቶቻችን ነገን ስለሚፈሩና እኛም ደግሞ እንደ ልጅነታችን የምናኮራቸውና የምናስመካቸው ስላልሆንን ስታመም ማን ያሰክመኛል፤ ስደክም ማን ይጦረኛል፣ ስሞት ማን ይቀብረኛል  . . . በሚል ስለጵጵስና ክብር ሲሉ ብቻ ገንዘብ ወደ መሰብሰብና ወደ ማጠራቀም ይሔዳሉ (Exceptions are there)  . . . በዚህ ሁሉ ግን እኛም ወደ ላይ እያዳጠን ገንዘብ ወዳጆችና ሥጋውያን እያልን ሰድበን ለሰዳቢ እንሰጣቸዋለን!!!
.
ካህናት አባቶችም ቢሆኑ ሚስትና ልጆች ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን ለልጆቻቸውና ለሚስቶቻቸው የሚሆን ተገን ስላላዘጋጀንላቸው ስለልጆቻቸውና ስለሚስቶቻቸው ብለው ተሰቅቀው መከራንና ሰማዕትነትን ሲሸሹ ፈሪዎች፣ ምንደኞች፣ ሥጋውያን . . . እያልን ሰድበን ለሰዳቢ እንሰጣቸዋለን!!! አንድ ካህን ስለእውነትና ስለቤተ ክርስቲያን ብሎ ቢሞት ወይም ቢታሰር ግን ሚስቱንና ልጆቹን የምንደግፍበትና ወጪያቸውን የምንሸፍንበት ምንም አይነት ሥርዐት አልዘረጋንም!!!
.
ካህኑስ እሺ መንፈሳዊ ኃላፊነት አለበት እንበል፤ ሚስቱና ልጆቹ ምን ዕዳ አለባቸውና ነው ስለካህንነቱ ለሚደርስበት መከራና ሰማዕትነት እነርሱም ዋጋ ከፋዮች የሚሆኑት!!! . . . ፍርድ እኮ እንደራስ ነው . . . የካህን ክህነቱ ለእኛ እንጂ ለሚስቱ ግን ባል፤ ለልጆቹም አባት መሆኑ ለምን ይረሳል? . . . ካህናት አባቶቻችን የሰማዕትነቱን መንገድ ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን ስለሚስቶቻቸውና ስለልጆቻቸው ተሰቅቀው ነው መከራውን የሸሹት፣ ፈሪዎች እያልን ስናንጓጥጣቸውም በአኮቴት የተቀበሉት!!! የዚህ መንስኤው ደግሞ ምእመናን የአገልጋይ ሰማዕታትን ሚስቶችና ልጆች የምንደግፍበት ምንም አይነት ሥርዐት ስላልዘረጋንና ተባባሪዎችም ስላልሆንን ነው!
.
የጳጳሳቱንና የካህናቱን ችግርና ጉድለት መንቀስ ብቻ አይደለም! ወደራስም መመልከት ያስፈልጋል . . . ሃይማኖቱም ሆነ የሃይማኖቱ ሥራ የጋራችን ነው! አገልጋዮቹ ብቻ ዋጋ እንዲከፍሉና ለሰማዕትነት ጥቡዐን እንዲሆኑ አልተጻፈም!!! ሰማዕትነቱ የጋራችን ነው! ጳጳሳቱንና ካህናቱን ከመውቀሳችን በፊት እንደ ምእመን እኛም የሚጠበቁብንን የቤት ሥራዎቻችንን አድምተን እንሥራ!!! . . . የቤት ሥራዎቻችንን አድምተን የሠራን ጊዜ ግን የምንፈልገውን አይነት ጳጳሳትና ካህናት ይኖሩናል!!!
.
በተነሳው ጉዳይ ላይ ስድብና ነቀፌታውን ትተን ቢሆን ጥሩ ነው ወይም ይጠቅማል የምንለውን ሐሳብ እናዋጣ!!!
ሀሳብ አስታያየት በውስጥም መስመር ይላኩልንን @Abeln
" የመንፈሳዊነት ግቡ፤ የአገልጋይነት ልኩ፤ የክርስትናችንም ጥጉ ወደ እግዚአብሔር መድረስ፣ እግዚአብሔርን ማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ነው! "
.
“እናንተ በመጽሐፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችኹ ይመስላችኋልና፥ እነርሱን ትመረምራላችኹ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን፥ ሕይወት እንዲኾንላችኹ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” ዮሐ 5፤39-40
.
የመንፈሳዊነት ግቡ፤ የአገልጋይነት ልኩ፤ የክርስትናችንም ጥጉ ወደ እግዚአብሔር መድረስ፣ እግዚአብሔርን ማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ነው!!!
.
ክርስቲያኖች የሆንነው እግዚአብሔርን ለማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ነው!
.
መጽሐፍ ቅዱስ የምናነበውና ቅዱሳት መጽሐፍትን የምንመረምረው እግዚአብሔርን ለማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ነው!
.
ቤተ ክርስቲያን የምንሔደው፤ ቅዳሴ የምንቀድሰውና የምናስቀድሰው፣ ማኅሌት የምንቆመው፣ በሥርዐተ አምልኮው ውስጥ የምንሳተፈው . . . እግዚአብሔርን ለማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ነው!
.
የምንማረውም ሆነ የምናስተምረው፤ ጉባዔ የምንዘረጋውና በጉባዔም የምንታደመው፤ የምንዘምረውና የምናገለግለው . . . ታቦት የኖረን፣ በታቦቱ መስዋዕት የምንሰዋው፣ ታቦት አክብረን በዓለ ንግሥ የምናነግሠው . . . እግዚአብሔርን ለማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ነው!
.
መብዐ የምናገባው፣ ጳጳሳትና ከህናት ያስፈለጉን፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የኖረን፣ ገዳማትን የመሠረትነው፣ ቤተ ክህነት የሚባል መዋቅር የፈጠርነው፣ ሰበካ ጉባኤ የሚባል ሥርዓት የዘረጋነው፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ያቋቋምነው፣ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል ማኅበር እንዲኖረን የተደረገው፣ ሌሎች ማኅበራትን የፈጠርነው . . . እግዚአብሔርን ለማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ነው!
.
ባሉን ነገሮችና በምንሳተፍባቸው አገልግሎቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ማግኘት ካልቻልንና ከእግዚአብሔር ጋር ካልሆንበት ጥቅሙ ምንድን ነው? በትምህርታችንም ሆነ በሥርዐተ አምልኳችን እግአብሔርን ካልሆነ በቀር ምን ልናተርፍበት እንችላለን?
.
የትምህርታችንም ሆነ የሥርዐተ አምልኳችን ማዕከሉ ወደ እግዚአብሔር መድረስ ነው! የክርስትናችን መሠረታዊ አላማና የአገልግሎታችን ዋነኛ ተልዕኮ እግዚአብሔርን ማግኘትና ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ነው! . . . እግዚአብሔርን ካላገኘንበትና ወደ እግዚአብሔር ካልቀረብንበት፤ እግዚአብሔርንም ካላገኘንበት ክርስትናችን፣ አገልግሎታችን፣ የቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን፣ ልዩ ልዩ ተሳትፏችን . . . ፋይዳው ምንድን ነው!
.
“እናንተ በመጽሐፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችኹ ይመስላችኋልና፥ እነርሱን ትመረምራላችኹ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን፥ ሕይወት እንዲኾንላችኹ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” ዮሐ 5፤39-40 ተብሎ እንደተጻፈ ክርስትና ወደ እግዚአብሔር መምጣት፤ ወደ ክርስቶስም መድረስ ነው!!! ሕይወት እንዲሆንልን፤ እንዲበዛልንም ወደ እግዚአብሔር እንምጣ፤ ወደ ክርስቶስም እንድረስ፤ ከእግዚአብሔር ጋር እንሁን፤ እንደቃሉ እናድርግ፤ እንደተማርነው እንኑር፤ ከፈቃዱም ጋር ውለን እንደር!!!
ነገሮችን ለማስተካከል እግዚአብሔር ስንት ሰው ይበቃዋል?
.
ቤተ ክህነታችንን ለማስተካከል እግዚአብሔር ስንት ሰው ይበቃዋል?
.
የቤተ ክርስቲያናችንን ችግሮች ለመቅረፍና ለማሻሻል እግዚአብሔር ስንት ሰው ይበቃዋል?
.
የምንፈልገውን አይነት የኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት ዐውድ ለመፍጠር እግዚአብሔር ስንት ሰው ይበቃዋል?
.
ሊሠራ ከወደደ እግዚአብሔር በጥቂት ሰዎችም ይሠራል፤ ይሆን ዘንድ ከፈቀደም አንድ ሰው ይበቃዋል!!! የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ያበበችው ሐቢብ ጊዮርጊስ በሚባል አንድ ዲያቆን እኮ ነው!!!
.
እግዚአብሔር በጥቂት ሰዎችም ሊሠራ ቢወድ እኛ ከእነዚያ ጥቂት ሰዎች መካከል ለመሆን ዝግጁዎችና ፈቃደኞች እንሆን ይሆንን?
.
እግዚአብሔር በአንድ ሰው ሊሠራ ፈቃዱ ቢሆንና ያ አንድ ሰው እኛ እንድንሆን ቢወድ ከእግዚአብሔር ጋር ለመሥራትና ለመታዘዝ ፈቃደኞች እንሆን ይሆንን?
.
ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር መተው የቻልን ጊዜ እግዚአብሔር እንደወደደና እንዳሰበ በጥቂቶች ወይም በአንዳችን መሥራት እርሱን አይቸግረውም!!!
ምኵራብ
የቤተ ክርስቲያን እንዚራ ቅዱስ ያሬድ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምኵራብ መግባት አይቶ በወንጌል የተጻፈውን ተርጒሞ ሳምንቱን በዜማ ያንን ቤተ መቅደስ የገባበትንና ቤተ መቅደሱ ውስጥ ይሸጡ ይነግዱ የነበሩ ወንበዴዎችን ያባረረበት ቅጽበት አንሥቶ ለጾሙ ሳምንት ምኵራብ ብሎ አርእስት ሰጥቶታል።
ምኵራብ “ቤተ አዳራሽ፣ ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ሕንጻ፣ ሰቀላ መሰል አዳራሽ” ማለት ሲሆን ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን ወርሮ ቤተ መቅደሱን ባፈረሰበት ሰዓት እና ሕዝቡንም በምርኮ ወደ ባቢሎን በአግአዘ (በአፈለሰ) ወቅት በምርኮ ሀገር ሆነው እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት፣ ለጸሎት እና መሥዋዕት ማሳረጊያ ይሆናቸው ዘንድ ባገኙት ቦታ ድንኳን ይተክሉ (የጸሎት ቤት ይሠሩ)ነበር። (ሕዝ.፲፩፥፮፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፷)
በዚያ ምኩራብም መጻሕፍትን ያነቡ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ይማሩ፣ የአምልኮ እና የጸሎት ሥርዓት ይፈጽሙ ነበር፤ ከሕግና ከነቢያት፣ ከዳዊት መዝሙራትም ይዘምሩ ነበር፥ ስብከት እና ቡራኬም ነበር፤ሕግ ያፈረሱትን በፍርድ የሚቀጡበትም ቤት ነው። ይህም የሚሆነው በሰንበት ቀን ነበር። (ማቴ.፬፥፳፫፣ ሐዋ.፮፥፱፣ ፱፥፪፣ ዮሐ.፱፥፴፬፣ ፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፬፣ ሉቃ.፬፥፲፮)
ጌታችንም በሰንበት ቀን እየሄደ ሕዝቡን ያስተምር፣ ድውያንን ይፈውስ፣ አንካሳውን እንዲራመድ ያደርግ ነበር፤ ሽባውን ይተረትር፣ ለምጻሙንም ያነጻ ነበር። ከነቢያት መጻሕፍትን ከመዝሙርም እየጠቀሰ ያስተምራቸው ነበር። (ማቴ.፳፩፥፲፬፣ ማር.፩፥፳፩፣ ፭፥፴፭፣ ሉቃ.፬፥፲፮)
ይህን አይቶ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንዲህ አለ፤ "ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ  ቃለ ሃይማኖት ለአይሁድ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕተ፤ አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ፤ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠጾሙ ያርምሙ አንከሩ ምሕሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፤  ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖትም ቃል አስተማረ፡፡ ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ አላቸው፡፡ የአባቴን ቤት የሸቀጥ ቦታ አታድርጉት፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ ወደ ምኵራብ ገብቶ ተቈጣቸው፡፡ ዝም እንዲሉም ገሠጻቸው፡፡ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩንም ጣዕም፣ የንግግሩንም ርቱዕነት አደነቁ፡፡" (ጾመ ድጓ ዘምኩራብ ዘሰንበት)
የሊቁን ሐሳብ ይዘን ብንመረምር ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን እናገኛለን። በዋናነት ግን ሁለት ዐምድ የሆኑ ጉዳዮችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ጌታችን ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብቶ እንዳስተማረ፤  የሃይማኖትንም ቃል እንደነገራቸው ስለ ምጽዋት፣ ስለ ሰንበት ጌትነቱ፣ ስለ ምሕረት እንዳስተማራቸው የምናገኝበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አንጽሆተ ቤተ መቅደስ ያደረገበትን ቦታ እናገኛለን። ቅዱስ ያሬድም ጌታችንን ወደ ምኵራብ የገባበትን እና ቤተ መቅደሱን ያነጻበትን ምክንያት በማድረግ ሳምንቱን ምኩራብ ብሎ የጠራው። እስኪ ሁለቱን ሐሳቦች አንድ በአንድ እያነሣን እንመልከታቸው፡-
የመጀመሪያውን በተመለከተ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ምኵራብ መሄዱን እና የሄደበት ጊዜ ደግሞ ፋሲካቸው መዳረሻ አካባቢ እንደሆነ እንዲህ በማለት ይነግረናል። “ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ። የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።" (ዮሐ.፪፥፲፪-፲፫)
አይሁድ በምኵራባቸው በሰንበት ቀን እንደ ልማዳቸው መሠረት ጸሎት መጸለይ፣ ትምህርት መማር፣ መጻሕፍትን ማንበብ ያዘወትሩ ነበር። ኢየሱስም የተገኘው በዚሁ ዕለት ነው። ያን ጊዜ ደግሞ የአይሁድ ፋሲካ ነበር። ወንጌላዊው ይህን ፋሲካ ከእግዚአብሔር ፋሲካ ሲለይ የአይሁድ ፋሲካ ብሎ ጠራው። (ዘዳ.፲፪፥፲፩)
ነቢዩ ኢሳይያስ የአይሁድ ፋሲካን ከእግዚአብሔር ፋሲካ መለየቱን እና እግዚአብሔርም እንዳልተደሰተበት የሚነግረን “መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።" (ኢሳ.፩፥፲፬)
እግዚአብሔርን የኃጢአተኞች ድግስ ደስ አያሰኘውም። የእርሱን ፋሲካ የሚያርጉት ግን እግዚአብሔር ወደዚያ እንዲመለከት ያደርገዋል።  መጽሐፍ "ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው" የሚለው ለዚህ ነው። (ዘሌ.፳፫፥፪)
በዚህም አይሁድ ከተሠራላቸው ሕግ እንደራቁ፣ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ይልቅ በወግ አጥባቂ ሕግ እንደታወሩ መረዳት ይቻላል። ጌታችንም ወደ ምኵራብ በገባ ጊዜ የልቡና ዓይናቸው እንዲገለጥ፣ የዕውቀት ብርሃናቸው እንዲበራ ብሎ ያስተማረውን ትምህርት ነው፤ ቅዱስ ያሬድ "ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖትን ቃል አስተማረ" የሚለው ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ ቤተ መቅደስ የገባው በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር። ያን ጊዜ ከመምህራን ትምህርትን ሊማር፣ ሊጠይቅ እንጂ ሊያስተምር አልነበረም። (ሉቃ.፪፥፵፪-፶፪) ከዚያ በኋላም ግን ለማስተማር፣ መጻሕፍትን ያውቁ ዘንድ (ሉቃ.፬፥፲፮) የእውነትን ምሥጢር ይገልጥላቸው ዘንድ ስለ አባቱ ጌትነት፣ ስለ እራሱም የባሕርይ ልጅነት፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወትነት ሊያስተምራቸው፣ ከሃይማኖት ይልቅ በወግ አጥባቂ ሕግ ታንቀው ነበርና ያንን ያፈርስ ዘንድ፤ ጾምን፣ ምጽዋትን፣ ወንድማማችነት ሊሰብክ ወደ ምኵራብ ገባ።  እነርሱ ግን አላወቁም። የእነርሱንም ድንቁርና አልተረዱም። ይልቁንም የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕም፣ የንግግሩንም ርቱዕነት ያደንቁ ነበር እንጂ።
አይሁድ ግን የእጁን ተአምር እያዩ፣ የቃሉን ትምህርት እየሰሙ ክፉ ቅንዓት ይዟቸው ነበር። እንዲያውም የምኵራብ መሪዎች እነርሱን እና ቤተ መቅደሱን የሚያዋርድ ይመስላቸውም ነበር። (El Khoury paul Elfaghali: The Gospel of Saint John, The Writhing Syndicate, 1992, page 15)
እግዚአብሔርም ግን በፍቅሩ ስቦ ወደ ቅዱስ መቅደሱ በክብር ያቆመናል። እኛም በእርሱ፣ በአባቱም ፊት ባለሟልነትን እናተርፋለን። ለዚያም ክብር ያብቃን፤ አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር፤አሜን!
የሌሊቱ ተማሪ ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ነው። በዮሐ. 3÷1 ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው እንደነበረና እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን መጥቶ እንደተማረ ተጠቅሷል። (ዮሐ 1÷2) በአይሁድ አለቆች ፊትም ”ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተናገረ እሱ ነው ኒቆዲሞስ “መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርገ የሚችል የለምና።" በማለት ተናገረ።(ዮሐ3፥2) በዚህ ጊዜ ጌታችን የገነት በር ስለሆነው ስለ ምስጢረ ጥምቀት አስፍቶና አምልቶ በምሳሌ ጭምር አስረዳው። "እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” (ዮሐ 3፥3) በማለት መንፈሳዊ እውቀት የጎደለው መሆኑን አሳይቶ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ እንደሚሆን አስርግጦ ነገረው።

በዚህም ታላቅ ምስጢርን ሊገልጥለት ወደደ። ይህ አነጋገር ከአይሁድ አለቆች አንዱ ለሆነው ፈሪሳዊ ሰው ከባድ ነበር። ምሥጢሩም ቢጸናበት ጊዜ ጌታን እንዲህ በማለት ጠየቀው “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንደምን ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማሕጸን ተመልሶ ሊገባ ይችላልን?“። (ዮሐ 3፥4) ጌታችንም ለኒቆዲሞስ መልሶ የአዳም ልጆች ሁሉ ከውሃና ከመንፈስ ዳግም ካልተወለዱ (በመንፈስ ቅዱስ መታደስን በሚያሰጥ ጥምቀት ካልተጠመቁ) መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደማይችሉ ነገረው።

ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!
Forwarded from አቤል ታደሰ ابيل
በስመአበ ወወልድ ወመንፈስ ቅድስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
"ወደ ተራራው ውጡ እንጨትም አምጡ ቤቴልም ስሩ በእረሱም ደስ ይለኛል እኔም እመሰገንበታለሁ"
ይላል እግዚአብሔር ት.ሐጌ ምዕራፍ 1፥8
__
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዳማ ወረዳ ስር የሚገኘው ጉራጃ ፉርዳ ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ፍቃድ የተመሰረተው በ1995 ዓ.ም ሲሆን ቤተክርስቲያኑ በወቅቱ ጥንካሬ ባለው የግንባታ እቃ ስላልተሰራ ከማርጀቱ የተነሳ ቆርቆሮው በማፍሰሱ እና ግርግዳው በመሰነጣጠቁ ምክንያት ለአገልግሎት አመቺ ባለመሆኑ እስካሁን ድረስ የቃልኪዳን ታቦቱ በመቃኞ ቤት ውስጥ ይገኛል።ቤተክርስቲያኒቱ በገጠራማ አካበቢ ላይ ስላለች ብዙም ምዕመናን ስለሚያገኝበት በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ምክንያት ባለመታደሱ ምዕመኑ እና ኮሚቴው ቤተክርስቲያኗን ለመስራት አስበው እንቅስቃሴ ስለጀመሩ የተጀመረውን ቤተክርስቲያን ለማጠናቀቅ እንድንችል የገንዘብም ሆነ የግንባታ እቃዎች እርዳታ እንድታደርጉልን ስንል በአምላካችን በቅዱስ አማኑኤል ስም እንጠይቃለን።
በቤተክርስቲያኑም ሆነ በአካልም በመገኘት በአካውንት ቁጥር 1000685260135 ጉራጃ ፉርዳ አማኑኤል በሚል ገቢ እንድታደርጉልን በቤተክርስቲያን ስም እንጠይቃለን።
Forwarded from አቤል ታደሰ ابيل
የቻላቹትን ከበረከቱ ተሳተፉ screenshot lakuleng::አሐው!
2025/07/06 13:27:52
Back to Top
HTML Embed Code: