Telegram Web
#ይሄም_ለአንቺ_ነው
ልነግርሽ እማይገቡ ብዙ ሚስጥሮቼን መንገሬ ዛሬም ድርስ ቅጥል ያደርገኛል።
ለምን አባሽ ግን ነገርኩሽ?….............
የተለየሁ ነኝስ ለምን አልሺኝ?.…........
ግን እኔ ነኝ ደነዙ እንጂም አንቺ ምን አደረግሽ፤ አንዱ ጅብ ከሌላው ጅብ ቢሻልም ግን ያው ጅብ ነው።
ጅብ እያልኩሽ ደሞ እንዳይመስልሽ፣
እኔ እንደዛ አልወጣኝም….........
እኔ ያልኩሽ የሰው ጅብ ነሽ ነው።
አየሽ እኔ እኮ ቢያንስ ሰውነትሽን እኮ አልካድኩም፤ በርግጥ….........
አይ እንደውም ይቅር አልጨርሰውም።
አሁንም ድረስ ምነው ስለ እስዋ ማውራት አቆምክ ይሉኛል ወዳጆቼ።
እኔም….............
ሰይጣን እሚያስለፈልፍህ እስኪለቅ ነው እላቸዋለው፤ ይሄ ግን ስድብ ነው መሰለኝ።
ይሁና….....
ቢሆንስ…..
እኔን የሰራሺኝ ሽዋሽዋ እኮ ሰይጣንም ቢሆን አያውቀውም
በቃ ለአሁን ይህን ካልኩሽ ይበቃል…።
ትዝ ስትይኝ ደሞ ይቀጥላል…
የሆነ ቦታ የሆነች የተረጋጋች ሴት ያለች ይመስለኛል። የሰውን ትኩረት የማትፈልግ ፤ ሰዎች እንዲወዷት የተለየ ነገር የማታደርግ የራሷን ኑሮ የምትኖር...

ህይወቷ በእውነት እንጂ በፈጠራ ድራማ ያልተሞላ ፤ ሰዎች እግረመንገድ ላይ ድንገት ዋነኛዋ ሴት የምትሆን ። የተሰማትን የፈለገችውን ደስ ያሰኛትን የምታደርግ ፤ ምታደርገው የማይፀፅታት ...

ምድር ላይ ያለውን የህይወት ብሶቷን አልያም ችግሯን ለመደበቅ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ወ'ታ ከመንዘባዘብ ይልቅ ከአምላኳ ጋር የምትነጋገር። ስለራሷ እሷ እና አምላኳ ብቻ የሚያውቁ። ይህቺ ሴት ብርቱ ናት....

ለጓደኝነት ትመቻለች። ነፃነት ትሰጣለች። ለጊዜያዊ የፍቅር ግንኙነት ታስፈራለች። ወንዶች ይጠነቀቁላታል። የትኛውም ወንድ ደፍሮ ሌላዋን ሴት የሚያወራበት መልኩ ይቺን ሴት ሊያወራት አይችልም። ልባም ናት። ለዘላቂ ትዳር የምታስተማምን ሴት። የቤቱ ራስ መሆን የሚችል ፣ ሚስቱ እንድትገዛለት ሆኖ መኖር የሚችል ባል የሆነ ወንድ የሚመኛት እና የሚያገኛት ሴት ናት።

ይህቺ ሴት ብርቅ ናት ! ፀሎቷ ልኬት ያለው ይመስለኛል። ከሚያስፈልጋት በላይ እንዲሰጣት አትለምንም። ተመስገንን ታውቃለች በተሰጣት አታማርርም ።

https://www.tiktok.com/@holly_generation
ጆርጅ ኦርዌል እና የእንስሳት እርሻ (Animal Farm)
-----
አፈንዲ ሙተቂ
-----
ጆርጅ ኦርዌል ከ1903 እስከ 1950 ባለው ዘመን ብቻ ነው የኖረው። በነዚህ ዓመታት በበርማ፣ ህንድ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ብሪታኒያ ኖሯል። በኖረባቸው ሀገሮች ሁሉ ያያቸውን ማህበራዊና ፖለቲካ ምስቅልቅሎች፣ የህዝቦች አኗኗር እና የተፈጥሮ ሁኔታ የሚያትቱ መጻሕፍትን ጽፏል። እርሱን ዝነኛ ያደረጉት ግን በ1940ዎቹ የጻፋቸው ኖቬላዎች ናቸው ("ኖቬላ" በመጠኑ ከሙሉ የልብ-ወለድ ድርሰት ያንሳል። ከአጭር ልብ ወለድ ድርሰት ከፍ ይላል። ለምሳሌ አሌክስ አብረሃም በጻፈው "ዶክተር አሸብር" የተባለ መጽሐፍ ውስጥ የተካተተው "ዶክተር አሸብር" የተሰኘ ትረካ በቅርጹና አቀራረቡ "ኔቬላ" ሊባል ይችላል። ይህ ዘውግ በእንግሊዝኛም "Novela" ነው የሚባለው)።

ጆርጅ ኦርዌል ከጻፋቸው ኖቬላዎች በጣም የሚደነቁት "Animal Farm" እና "Nineteen Eighty-Four" (1984) የተሰኙት ናቸው። እነዚህ ኖቬላዎች ከጥበባዊ አስተዋጽኦዋቸው ባሻገር በሰዎች የፖለቲካ ንቃትና ግንዛቤ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የፈጠሩ ናቸው። ጆርጅ ኦርዌል "የኔ masterpiece ስራ ነው" የሚለው Nineteen Eighty-Four የተሰኘውን ድርሰት ነው። በዓለም ዙሪያ የገነነውና በብዙ ሐያሲዎች እና ደራሲዎች በጣም የተደነቀለት ስራው ግን "Animal Farm" ነው። እስቲ ይህንን ስራውን በአጭሩ እንተዋወቀው።
------
Animal Farm በአቀራረቡና በአጻጻፉ የእንስሳት ፌቡላ ይመስላል። የመጽሐፉ መቸት በደቡብ ምሥራቅ እንግሊዝ፣ ዌሊንግደን በተባለ ወረዳ የሚገኝ "የማኖን እርሻ" የተባለ እርሻ ነው። የዚህ እርሻ ባለቤት ሚስተር ጆንስ ይባላል። ሚስተር ጆንስ በይዞታው ሀብታም ቢሆንም በስራው ሰነፍና ሰካራም (alcoholic) ነው። በተለይም ንብረቱ የሆኑትና በእርሻው ዙሪያ ቤት ተሰርቶላቸው የሚኖሩት በርካታ እንስሳት በሚስተር ጆንስ አያያዝ በጣም ተማርረው ነበር። በመሆኑም ከእነርሱ በዕድሜ የሚበልጠው "Major" የተባለ አሳማ በሚስጢር እየጠራቸው ለመብታቸው እንዲታገሉ ይቀሰቅሳቸው ነበር። የእንስሳት ሁሉ መታወቂያ የሆነውን "የእንግሊዝ አራዊት" የተባለ ብሄራዊ መዝሙር ያስጠናቸው ነበር።

አረጋዊው "ማጆር" እንስሳቱን እየቀሰቀሰ ሳለ በድንገት አረፈ። እንስሳቱን የመምራቱ ስልጣንም "ስኖውቦል" እና "ናፖሊዮን" ለተባሉት ሁለት አሳማዎች ተላለፈ። ስኖውቦል እና ኖፖሊዮን የእንስሳቱን የዘመናት ሮሮ በማስተጋባት "ዛሬውኑ ለመብታችሁ ተነሱ! ነጻነታችሁን አውጁ" በማለት አብዮት ቀሰቀሱ። እንስሳቱ ሁሉ በየመንጋው ሆነው ወደ ጨቋኙ ሚስተር  ጆንስ ቤት ዘመቱ።

የእንስሳቱ አመጽ ያስፈራው ሚስተር ጆንስ እግሬ አውጭኝ ብሎ ከእርሻው ፈረጠጠ። በዚህ ድል የተደሰቱት እንስሳት ሁሉ ለስኖውቦል እና ለናፖሊዮን አመርር እውቅና ሰጡ። ሁለቱ መሪዎች እንስሳቱን ሁሉ ያሳተፈ ሸንጎ ጠሩ። ሸንጎው በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ሰባት ህግጋት ያሉት የመተዳደሪያ ደንብ አጸደቀ። በዚያ ትልቅ ማሳ መግቢያ ላይ የተተከለው "የማኖን እርሻ" የሚለው ታፔላ ተነስቶ "የእንስሳት እርሻ" (Animal Farm) የሚል ትልቅ ታፔላ ተተከለ።

እንስሳቱ ያጸደቁት ባለሰባት ነጥብ የመተዳደሪያ ደንብ በእንስሳቱ መብት፣ በነጻነታቸው እና በሰው ልጆች ጠላትነት ላይ ያተኮረ ነው። ከደንቦቹ መካከል ጎላ ብለው የሚታዩት ሁለቱ ናቸው። አንደኛው ደንብ "እንስሳት ሁሉ እኩል ናቸው" የሚለው ነው። ሌላኛው ደግሞ "ባለ አራት እግር ፍጥረት ጥሩ ነው። ባለ ሁለት እግር ፍጥረት ግን መጥፎ ነው" የሚል ነው።

እንስሳቱ አስተዳደራቸውን ካዋቀሩ እና የልማት እቅዳቸውን ካወጡ በኋላ የእርሻ ስፍራውን የሚገባ ማረስና ማልማት ጀመሩ። በመሃሉ ግን በስኖውቦል እና በናፖሊዮን መካከል የስልጣን ግብግብ ተነሳ። "ስኖውቦል" ፈላስፋ፣ አዋቂ፣ ሃሳብ አመንጪ እና ጥበበኛ ነው። ይሁንና የዋህነት ያጠቃዋል። ናፖሊዮን የራሱን ሐሳብ ማመንጨት የማይችል አለሌ ነው። በተንኮል ግን ማንም አይችለውም። ከስኖውቦል ጋር ወደ ግብግብ የገባውም በሚስጢር ያደራጃቸውን እንደ "ስኩዊርል" የመሳሰሉ ተከታዮቹን ይዞ ነው።

ስኖውቦል በግብግቡ ተሸናፊ ሆነ። ሁሉም ስልጣን በናፖሊዮን እጅ ገባ። ናፖሊዮን "ስኩሪል" በተባለ ረዳቱ እየታገዘ ስልጣኑንና ቁጥጥሩን ማጥበቅ ጀመረ። በአንድ በኩል እንስሳቱን በቡድን ከፋፍሎ በመሃላቸው የሀሰት ወሬ እያሰራጨ እርስ በራሳቸው ያባላቸው ጀመር። በሌላ በኩል ለስልጣን የሚያስፈሩትን ሁሉ "ከሚስተር ጆንስ ጋር ተሻርካችሁ እርሻችንን ልታስወስዱብን ነው" እያለ ፈጃቸው።

ታዲያ በዚህ ሁሉ መሃል እንስሳቱ መስራታቸውን አላቆሙም። በጅምሩ ላይ ምርቱ በሽበሽ በመሆኑ ምግብ ተትረፍርፎ ነበር። በስኖውቦል ሃሳብ አመንጪነት ለአካባቢው ሁሉ በክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ የነፋስ ወፍጮም መስርተዋል። ናፖሊዮን ስልጣኑን ማጥበቅ ሲጀምር ግን ወፍጮውን የራሱ ገቢ ምንጭ አደረገው። ምግብም ችግር ይሆን ጀመር። እንስሳቱ የሚበሉትን አጥተው እየተቸገሩ ሳለ ናፖሊዮንና ረዳቱ የሆነው ስኩዊርል ምርጥ የተባለውን ምግብ በድብቅ ይሸጡታል።

ናፖሊዮን "ለስልጣን ያሰጉኛል" ያላቸውን መንጥሮ ከጨረሰ በኋላ በድብቅ የሚያራምደውን አጀንዳ በገሃድ ይፈጽመው ጀመር። የተቃውሞ ጥያቄና ቅሬታ የሚያቀርብ እንስሳ ሁሉ በአደባባይ መታረድ ጀመረ። ከሰዎች ጋር የነበረው ጠላትነት ተሽሮ ከሰዎች ጋር በሽርክና መስራት ተጀመረ። በእንስሳት መካከል የነበረው ፍቅርና ህብረት ጠፍቶ እንስሳትን ከሰዎች በባሰ ሁኔታ የሚጨቁን "የአሳማ ገዥ መደብ" ተፈጠረ። "Animal Farm" የሚለው ስም ተሽሮ "Manon's Farm" የተሰኘው የድሮው ስም ተመለሰ።

በመጨረሻ ላይ በሰባቱ የመተዳደሪያ ደንቦች ላይ ለውጥ ተደረገ። በተለይ ደግሞ ከደንቦቹ መካከል ጉልህ ስፍራ በነበራቸውና ከላይ በጠቀስናቸው ሁለት ደንቦች ላይ የተደረገው ለውጥ አስገራሚ ነው። አንደኛው ደንብ የተለወጠው "አራት እግር ጥሩ ነው፣ ሁለት እግር ግን የተሻለ ነው" በሚል ነበር። ሁለተኛው ደንብ ደግሞ "እንስሳት ሁሉ እኩል ናቸው። አንዳንድ እንስሳት ደግሞ የበለጠ እኩል ናቸው" በማለት ነበር የተለወጠው።
-----
የ"Animal Farm" ይዘት ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል። ይህንን ትረካ ዝም ብሎ ያነበበ ሰው "Animal Farm የተረት መጽሐፍ ነው" ብሎ ሊመደመድም ይችላል። ይሁንና ነገሩ እንዲያ አይደለም። ጆርጅ ኦርዌል በትረካው የዘመኑ ታላቅ አምባገነን መሪ የነበረውን ጆሴፍ ስታሊንን እና አገዛዙን ነው የሸነቆጠው። እርግጥ ጆሴፍ ስታሊንን በቀጥታ የሚተቹ ብዙ ጸሐፊዎች በዚያ ዘመን ነበሩ። ጆርጅ ኦርዌልም በቀጥተኛ አጻጻፍ ስታሊንን እና አገዛዙን አምርሮ ተችቷል። ሆኖም "በኖቬላ መልክ ሆኖ "Animal Farm" ተብሎ ሲጻፍ አንባቢያን በስነ-ጽሑፋዊ ፍሰቱ እየተዝናኑ የስታሊንን የጥፋት አካሄድ በደንብ ይረዱታል" በማለት ልበ-ወለዳዊ መልክ ሰጥቶታል።
AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴🇮:
ትኩረት- ከውጪ ለተወረሱ ቃላት
------
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
የሀገራችን ቋንቋዎች ከውጪ ቋንቋዎች በርካታ ቃላትን ወርሰዋል፡፡ ይህም ከብሉይ ዘመን ጀምሮ ይታይ የነበረ ክስተት ነው፡፡ የመወራረሱ አድማስ ስፋቱን የጨመረው ግን በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቀጣዮቹ አንድ መቶ ሀያ ዓመታት ውስጥ የታዩት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ክስተቶች የሀገራችን ቋንቋዎችን ለውጪ ቋንቋዎች ተጽእኖ የበለጠ ክፍት እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል፡፡

ታዲያ ከሶስት ሺህ ከሚልቁት የውጪ ቋንቋዎች መካከል ለሀገራችን ቋንቋዎች ብዙ ቃላትን ለማውረስ የበቁት አራቱ ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና እንግሊዝኛ ናቸው፡፡ የቱርክ እና የጀርመን ቋንቋዎችም ጥቂት ቃላትን ለሀገራችን ቋንቋዎች አበርክተዋል፡፡
*
ዐረብኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር የቻለው በዋናነት የእስልምና ሀይማኖት የአምልኮና የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ከእስልምና እምነት ጋር በተያያዘ ለአምልኮና ለትምህርት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቃላት በአብዛኛው ከዐረብኛ የተገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መስጊድ/መስጂድ፣ ኢማም፣ ቃዲ፣ አዛን፣ መጅሊስ፣ መድረሳ ወዘተ… የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሂደት ደግሞ የዐረብኛ ቃላት በአምልኮ ውስጥ ካላቸው አስፈላጊነት አልፈው በተራው ሰው ንግግር ውስጥም ገብተዋል፡፡ ይህ ክስተት በስፋት የሚስተዋለው ግን አብላጫው ነዋሪ ህዝብ ሙስሊም በሆነባቸው እንደ ወሎ፣ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ጅማ፣ ሶማሊ (ኦጋዴን)፣ ቤኒሻንጉልና አፋር አካባቢዎች ነው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ከሚነገሩት ቋንቋዎች “መርሐባ”፣ “አሕለን”፣ “ፉጡር”፣ “ሀድራ”፣ “ሙሐባ”፣ “መናም”፣ “ጂስም”፣ “አዛ”፣ “ኩርሲ”፣ “ማዕና”፣ “ዒልም”፣ “አስል” እና ሌሎች በርከት ያሉ የዐረብኛ ቃላትን በቀላሉ ለይቶ ማውጣት ይቻላል፡፡

ታዲያ የዐረብኛ ቃላትን የመውረሱ ተግባር በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል ደረጃ የሚጠቀምባቸው በርከት ያሉ የዐረብኛ ቃላትንም ወርሰናል፡፡ ይህም ክስተት የተፈጠረው ከንግድ መስፋፋት ጋር ነው፡፡ በተለይ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የሀገራችንን ንግድ በበላይነት ተቆጣጥረው የነበሩት ሲራራ ነጋዴዎች ዐረብኛን በንግድ ቋንቋነት በስፋት ይጠቀሙበት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ በሀገራችን ቋንቋዎች ውስጥ መሰረት ያልነበራቸው በርካታ ቃላት እንዲወረሱ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ የአማርኛ ቃላት አድርገን የምንጠቀምባቸው እንደ ሀዋላ፣ ጉምሩክ፣ ሰንዱቅ፣ ሱቅ፣ መጋዘን፣ ሽርክና፣ ወኪል፣ ሰነድ፣ ደላላ፣ መሃለቅ ወዘተ የመሳሰሉት የአማርኛ ቃላት ምንጫቸው ዐረብኛ ነው፡፡ እንደ ሐዲድ፣ ባቡር እና መኪና የመሳሰሉ ቃላትም ከዐረብኛ ነው የተወረሱት፡፡ ይሁንና ዐረብኛና አማርኛ ሴማዊ ቋንቋዎች በመሆናቸው የሚጋሯቸውን ቃላት እንደ ውርስ ቃላት ማየት ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰላም፣ ደም፣ ቤት፣ ፎቅ፣ ክፍል፣ ዐይን፣ ፈረስ፣ ዘመን፣ ሐሩር፣ ሚዛን የመሳሰሉ ቃላት በሁለቱም ቋንቋዎች ውስጥ አሉ፡፡ ሁለቱም ቋንቋዎች ሴማዊ በመሆናቸው ነው እነዚህን ቃላት የተጋሩት፡፡ የነዚህ ቃላት መነሻ የሁሉም ሴማዊ ቋንቋዎች አባት እንደሆነ የሚታመንበት ግንደ-ሴማዊ ቋንቋ (Proto-Semetic Language) ነው፡፡
*
አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መስመር ሲሰራ ደግሞ ፈረንሳይኛ ወደ ሀገራችን ቋንቋዎች እየሰረገ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም በ1910ዎቹ ውስጥ ሲከፈት የፈረንሳይኛ ተጽእኖ በጣም ተጠናክሯል፡፡ የዘመኑ የትምህርት ካሪኩለምም ከፈረንሳይ የተቀዳ በመሆኑ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና ምሩቃኑ ፈረንሳይኛን ይናገሩ ነበር፡፡ በነዚያ ምሩቃን በተሞላው ሲቪል ሰርቪስም ሆነ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ፈረንሳይኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ለመንግሥታዊ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ሰነዶችና የስራ መመሪያዎችም ከፈረንሳይኛ ሲተረጎሙ ነው የኖሩት (የመጀመሪያው ህገ-መንግሥትም ከፈረንሳይ የተቀዳ ነው)፡፡ በዚህም ሂደት በርካታ የፈረንሳይኛ ቃላት በአማርኛ ተወርሰዋል፡፡ ከፈረንሳይኛ ከወረስናቸው ቃላት መካከል “ኦፊሴል”፣ “ሞኖፖል”፣ “ሌጋሲዮን”፣ “ኮሚስዮን”፣ “ፔኒስዮን”፣ “ዲክላራሲዮን”፣ “ኦፕራሲዮን”፣ “ካሚዮን”፣ “ፍሪሲዮን”፣ “ሬኮማንዴ”፣ “ለገሀር (ላጋር)፣ “ቡፌ”፣ “ሌሲ ፓሴ”፣ “ዴኤታ”፣ “ ካፌ”፣ “ራንዴቩ”፣ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የኢጣሊያ ወረራ ከተወልን ማስታወሻዎች መካከል ትልቁ በሀገራችን ቋንቋዎች ውስጥ የሚታየው የጣሊያንኛ ተጽእኖ ነው፡፡ በአማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጣሊያንኛ ቃላትን መቁጠር ይቻላል፡፡ በተለይም በቀድሞ ዘመናት ከተሽከርካሪ እና ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ ከሚሰራባቸው ቃላት መካከል ብዙዎቹ የጣሊያንኛ መሰረት ያላቸው ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ የነዚያ ቃላት ቅሪቶች በሀገርኛ ቋንቋዎች ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ከጣሊያንኛ ከወረስናቸው ቃላት መካከል “ፓስታ”፣ “ማካሮኒ”፣ “ላዛኛ”፣ “ስፓጌቲ”፣ “ስልስ” (ሳልሳ)፣ “አሮስቶ”፣ “ፋብሪካ”፣ “ጋዜጣ”፣ “ሊቼንሳ”፣ “ፉርኖ”፣ “ቪያጆ” (በመኪና የሚደረግ ጉዞ)፣ “ላቫጆ”፣ “ካሮሴሪያ”፣ “ካምቢዮ”፣ “ሞቶሪኖ”፣ “ፍሬን”፣ “ፊልትሮ”፣ “ሳልቫታዮ”፣ “ፖርቶ መጋላ”፣ “ፒንሳ”፣ “ቺንጊያ” ፣ “ፈረፋንጎ”፣ “ኩሽኔታ” “ኪያቤ”፣ “ካቻቢቴ” “ባሌስትራ”፣ “ቸርኬ” “ፒስታ” “ኮማርዳሬ” “ጎሚኒ” “ሮንዴላ” “ዲፍረንሻሌ” “ስፒናታ” “ሳልዳሬ” “ቡኮ”፣ “ፖምፓ” (ቧንቧ)፣ “አውታንቲ”፣ “ማኖ”፣ “ኢሊ ጎሬ”፣ “ቴስታ”፣ “ፑንቶ”፣ “ቦጦሎኒ”፣ “ካምቦ” ወዘተ…. የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
*
ጣሊያኖች ከተባረሩ በኋላ እንግሊዝኛ በሀገርኛ ቋንቋዎች ውስጥ ሰርጾ መግባት ጀመረ፡፡ በተለይ እንግሊዞች በኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩባቸው አስር ዓመታት የእንግሊዝኛ ቃላት በሀገራችን ቋንቋዎች በብዛት ተወረሱ፡፡ በዚያን ጊዜ ከተወረሱት ቃላት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ በአገልግሎት ላይ ያሉትን እንደ “ፖሊስ”፣ “ባንክ”፣ “ሚኒስቴር”፣ “ካፒታል”፣ “ኤሌክትሪክ”፣ “ኮሌጅ”፣ “አካዴሚ”፣ “ኤክስፐርት”፣ “ዲሬክተር” የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም እንደ ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ጄኔራል፣ አድሚራል፣ ኮሞዶር፣ ኮሎኔል እና ካፒቴን የመሳሰሉ የማዕረግ ስሞችም የተወረሱት ከእንግሊዝኛ ነው፡፡

በእንግሊዝኛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የተነሳ ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ የነበራቸው ተጽእኖ በፊት ከነበረበት ደረጃ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ቋንቋዎች የተወረሱት የጣሊያንኛና የፈረንሳይኛ ቃላት በዘመኑ አገልግሎት መስጠታቸውን አላቆሙም፡፡ ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመን “ኮሚሲዮን” እንጂ “ኮሚሽን” የሚባል የአማርኛ ቃል አይታወቅም፡፡ ከፈረንሳይኛና ከጣሊያንኛ የተወረሰ የሀገርና የከተማ አጠራርም ቢሆን በአማርኛ ቋንቋ አንዳች ለውጥ ሳይደረግበት ያገለግል ነበር፡፡ እንደ ምሳሌም “ቤልጅግ”፣ “ስዊስ”፣ “ሎንዶን”፣ “መስኮብ”፣ “ብሩክሴል” የመሳሰሉትን የሀገርና የከተማ ስሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት ውድቀት በኋላ ግን ከፈረንሳይኛና ከጣሊያንኛ የተገኙ የሀገርና የከተማ ስያሜዎች ከእንግሊዞች በተወረሱ ስሞች ተተክተዋል፡፡ በዚህም መሰረት “ቤልጅግ” ወደ “ቤልጅየም”፤ “ስዊስ” ወደ “ስዊትዘርላንድ.፣ “ብሩክሴል” ወደ “ብራሰልስ”፣ “መስኮብ”ም ወደ “ሞስኮ” ተለውጠዋል፡፡ በመሆኑም ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች በተገኙ የቦታ ስያሜዎችና ቃላት ተውቦ ይታይ የነበረው አማርኛ የመኮማተር ባህሪን ለማዳበር ተገዷል፡፡
ይህ ቀደምት ውርስ ስሞችን በእንግሊዝኛ አጠራሮች የመተካቱ ሂደት ሳያቋርጥ በመቀጠሉ ከሁለቱ ቋንቋዎች (ከፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ) የተወረሱ የሀገር ስሞችን ከማራገፍ አልፎ በጥንታዊው አማርኛ ውስጥ መሰረት የነበራቸውን የሀገር ስሞችንም በእንግሊዝኛ ስያሜዎች መለወጥ ተጀምሯል፡፡ ለምሳሌ የዓለም ትልቋ ሀገር ከጥንት ጀምሮ በአማርኛ ስትጠራ “ሩሲያ” ነው የምትባለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ራሽያ” የሚለው አጠራር እያየለ መጥቷል፡፡ “ስጳኝ” የሚለው ትክክለኛ የአማርኛ አጠራር “ስፔን” በሚለው የእንግሊዝኛ ቅጂ ተቀይሯል፡፡ “አርመን” የሚለው አጠራርም በ“አርሜኒያ” ተተክቷል፡፡ “ቤልጅግም” ወደ “ቤልጅየም” ተቀይሯል፡፡ “ቆጵሮስ” የሚለውን ጥንታዊ የአማርኛና የግዕዝ አጠራር “ሳይፕረስ” በሚለው አዲስ ደራሽ የቅጂ ስም የሚለውጡ ሰዎችም እየበረከቱ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኦፊሴል ያገለግሉ የነበሩት እንደ “ነምሳ” (አውስትሪያ) እና “ናርበጅ” (ኖርዌይ) የመሳሰሉ የሀገራት መጠሪያዎች በዚህ ዘመን በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት መስጠታቸውን አቁመዋል፡፡

ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ ውርስ ቃላትም ቢሆኑ የመጥፋት እጣ ደርሶአቸዋል፡፡ ለምሳሌ በዛሬው ዘመን ከፈረንሳይኛ በተወረሰው “ኮሚሲዮን” የሚገለገል ሰው የለም፡፡ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች በስፋት ሲያገለግል የነበረው “ኦፕራሲዮን”ም በዚህ ዘመን “ቀዶ ጥገና” እና “ኦፕሬሽን” በሚሉት ስሞች ተተክቷል፡፡ “ፔኒሲዮን” የሚለው ቃልም ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን አቁሟል፡፡
*
“እነዚህ ቃላት ድሮውንም የውጪ ቃላት በመሆናቸው ከአማርኛ መጥፋታቸው የሚያስነሳው አቧራ የለም” ይባል ይሆናል፡፡ ነገሩን በታሪክና በአንትሮፖሎጂ መነጽር ካየነው ግን ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ምክንያቱም የነዚህ ቃላት በቋንቋዎቻችን ውስጥ መኖር የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪካችን የተጓዘበትን መንገድና የእኛነታችንን ህብርነት የሚያሳይ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የፈረንሳይኛ ቃላት በአማርኛ ውስጥ በመኖራቸው ተገርሞ “ይህ እንዴት ተከሰተ?…” የሚል ጥያቄ ቢያቀርብ የጅቡቲው ምድር ባቡርና የተፈሪ መኮንን ትምህርት ታሪክ ይተረክለታል፡፡ በጣሊያንኛ ቃላት ላይ ጥያቄ ለሚያቀርብ ሰውም የአምስቱ ዓመቱ የኢጣሊያ ወረራና የአርበኞቻችን የተጋድሎ ታሪክ ይነገረዋል፡፡
በሌላ በኩል በአንድ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ውርስ ቃላትና ሀረጋት የታሪካዊ ምርምር መሰረቶች የሚሆኑበት አጋጣሚም ሞልቷል፤ ቃላቱና ሐረጋቱ እንደ ታሪክ ማስረጃ የሚያገለግሉበት ሁኔታም አለ፡፡ ብዙ የታሪክ እንቆቅልሾች በቃላትና በሀረጋት መነሻነት ሊፈቱ ችለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዛሬ በግዴለሽነት ከኦሮምኛና ከአማርኛ ቋንቋ ውስጥ እየተወገዱ ያሉት የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ ውርስ ቃላቶቻችን ጠሊቅ የሆኑ ኪነታዊ ስራዎች የሚወጠኑበት መሰረቶች ሆነው ሲያገለግሉ ታይተዋል፡፡ እንደምሳሌም የቴዲ አፍሮን “ሼ-መንደፈር” እና “ላምባ ዲና”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቴዲ እየረሳናቸው ያሉትን አንድ የፈረንሳይኛና አንድ የጣሊያንኛ ቃላትን ወስዶ የሁለት ውብ ዜማዎች መሰረት አድርጎአቸዋል፡፡ በመሆኑም ውርስ ቃላቱን በነበሩበት ሁኔታ ማስቀጠሉ ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የሀገራችን ሚዲያዎችና ፕሬሶች ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እያካሄዱት ያለውን አጥፊ ሚና መግታት አለባቸው፡፡ ፈረንሳይም ሆነ እንግሊዝ፣ ጣሊያንም ሆነ ጀርመን ሁሉም ባዕድ ነው፡፡ ፊት የመጣውንና በህዝቡ ውስጥ የቆየውን ቃል አስወግዶ በሌላ የባዕድ ቃል መተካት በምንም መልኩ የስኬት መለኪያ አይሆንም፡፡ በተለይ ግን በረጅም ዘመናት የታሪክ ጉዞአችን ያዳበርናቸውንና እኛ ብቻ የምንጠቀምባቸውን ጥንታዊ የሀገርና የከተማ አጠራሮች (ሩሲያ፣ ቆጵሮስ፣ አርመን፣ ደማስቆ፣ ስዊስ፣ ኡክራኒያ፣ ቱርክ፣ ኢጣሊያ፣ ሮማ፣ አቴና፣ ሶሪያ፣ ፍልስጥኤም፣ ሊባኖስ፣ ግብጽ ወዘተ.. የመሳሰሉትን) ከእንግሊዝኛ በተኮረጁ ስሞች (ራሽያ፣ ሳይፕረስ፣ ደማስከስ፣ ፓለስታይን፣ ኢጂፕት ወዘተ..) መተካት ይቅርታ የማይሰጠው ጥፋት ነው፡፡ ቴክኖሎጂንና የተቀላጠፈ አሰራርን መኮረጅ እንጂ ነባር ቃላትን ማጥፋት የእድገት መሰረት ሊሆን አይችልም፡፡ ዐረቦችም ሆኑ ፈረንጆች፣ ቱርኮችም ሆኑ ህንዶች እንዲህ ዓይነት ጥፋት ሲያጠፉ አይታዩም፡፡ እኛም ይህንኑ ፈለግ መከተል አለብን፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው ሁሉ ለጉዳዩ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡
--------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 13/2006
ሸገር-አዲስ አበባ
------
(ይህ ጽሑፍ ሰኔ 2006 በታተመ አንድ የእንቁ መጽሔት እትም ላይ ወጥቶ ነበር)።
የኒውክለር ቦምብ ዓይነቶች
-----
አፈንዲ ሙተቂ
-------
ቦምቦቹ ብዙ ዓይነት ናቸው። በጣም የታወቁት ግን ሶስት ዓይነት ቦምቦች ናቸው።

1. Fission Bombs:

ብዙ ጊዜ Atomic Bomb ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ቦምቦች nuclear fission በሚባል ሂደት ይሰራሉ። ይህም አንድን የዩራኒየም ወይንም ፕሉቶንየም አቶም ለሁለት በመክፈል ኤነርጂ ማመንጨት ማለት ነው። ክብደቱ 270kg እስከ አስር ቶን ይሆናል። በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የተጣለው ቦምብ ይህኛው ነው።

2. Fusion Bombs:

ብዙ ጊዜ "Hydrogen Bombs" ወይንም "Thermonuclear Bombs" ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ቦምቦች nuclear fusion በሚባል ሂደት ይሰራሉ። ይህም የሁለት አቶሞችን ውስጣዊ ክፍል (nuclear) በማጋጨት ከባድ ኤኔርጂ መፍጠር ማለት ነው። ይህ ቦምብ ክብደቱ ከአስር ቶን (10,000 kg) በላይ ነው። ሲፈነዳ ደግሞ 30 ሜጋ ቶን TNT (የእጅ ቦምብ) ከሚያደርሰው ውድመት የበለጠ አውዳሚ እና ሀገር አጥፊ ነው። በአውዳሚነቱ በሂሮሺማ ላይ ከነፈዳው ቦምብ በ500 እጥፍ ይበልጣል።

3. Neutron bomb:

ይህ ቦምብ በመሠረቱ Thermonuclear ቦምብ ነው። ሆኖም ለልዩ ኦፕሬሽን ተብሎ የተፈጠረ አደገኛ ቦምብ ነው። Neutron Bomb ልዩ ባሕሪው ጸረ-ሕይወት መሆኑ ነው። ሲፈነዳ ከሌሎች ቦምቦች በተለየ መልኩ ህይወት የሌለውን ነገር እየተወ ህይወት ያለውን ነገር ብቻ ይገድላል።
------
ሌሎች ብዙ የኒውክለር መሳሪያዎች ቢኖሩም በጣም የሚታወቁት ሶስቱ ናቸው።

እነዚህን የኒውክለር ቦምቦች ማፈንዳት ራሱ ከባድ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ቦምቦቹ በአንድ ቦታ ተቀምጠው ከፈነዱ አካባቢውን ሊያወድሙ ይችላል። ያ እንዳይሆን በballistic missile ላይ ይታሰሩና ወደሩቅ አካባቢ ተወርውረው እንዲፈነዱ ይደረጋል።

የኒውክሌር መሳሪያዎች እጅግ በጣም አደገኞችና አውዳሚዎች ናቸው። የሚያደርሱትን ጥፋት ያነበበ ሰው ጭንቅላቱን ይዞ ነው የሚቀረው። የሰው ልጅ በስልጣኔው የፈጠረው ፋይዳ-ቢስ እና እጅግ አውዳሚ ነገርም የኒውክለር ቦምብ ነው።

በአንጻሩ የኒውክለር ኤነርጂ ተጠቃሚ መሆን የሚበረታታ ነው። በትንሽ ግብአት ብዙ ኃይል ማመንጨት ይቻላልና። የኒውክለር ቦምብ ግን የሚመኙት ዓይነት አይደለም። በዓለም ላይ ዘጠኝ ሀገሮች ብቻ እርሱን የሰሩበት ምክንያት ሌሎቹ መስራት አቅቶአቸው ሳይሆን የሚያደርሰው ውድመት ስለዘገነናቸውና ስላስፈራቸው ነው።  እኛም እንዲህ ዓይነቱን አውዳሚ ቦምብ ከእኛ እንዲያርቀው ብንጸልይ ይመረጣል።
------
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 17/2017
🐺 ቀበሮ ለዶሮ «የአባትህ ድምፅ በጣም ደስ ይለኝ ነበር» አለው።
🐓 ዶሮም «የኔም ድምፅ እኮ እንደ አባቴ ነው» በማለት መለሰ።
🐺 ቀበሮውም «እንደዛ ከሆነማ እባክህ ልታሰማኝ ትችላለህ ??» በማለት ተማጸነው።
🐓 ዶሮው «ምን ችግር አለው !» በማለት ጩኸቱን ለማሰማት ዓይኑን ሲጨፍን ቀበሮው ይዞት አፈተለከ።

ውሾች ሁሉ ዶሮውን ከቀበሮው አፍ ለማስጣል እየጮኹ እግር በእግር ተከታተሉት።

🐓 ዶሮው ለቀበሮው «ከውሾቹ ለመዳን ከፈለግክ ዶሮው የእናንተ ሰፈር አይደለም !!» በላቸው አለው። ቀበሮውም የተባለውን ለመናገር ሲሞክር ዶሮው ከአፉ አመለጠው።
🐺 ቀበሮውም በፀፀት ተውጦ «ዝም ማለት ሲገባው የተናገረ አፉ ይረገም ፤ ይኮነን» አለ።
🐓 ዶሮም በበኩሉ «መንቃት ሲገባው የተጨፈነ አይን ፤ ይኮነን» አለ። ይባላል
የምንነቃበት ቀን ይሁንልን!
#ፖለቲካዊ_ኮንትሮባንድ😂

የሩሲያ ዜጋ ነው። አንድ ልጁን ይዞ ወደ አሜሪካ ሊጓዝ፡ ሞስኮ በሚገኘው የሼሬሜቲቮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የፍተሻ ክፍል ደረሰ። ሻንጣው ተፈተሸ ፡ በውስጡ የሌኒንን ምስል የያዘ ቅርጻ ቅርጽ ነበረው። የአየር መንገዱ የፍተሻ ሰራተኛ፡-
"ምንድን ነው ይሄ ?" በማለት ጥያቄ አቀረበ። መንገደኛው ሩስኪ፥- "ጓድ ጥያቄህን ያቀረብክበት መንገድ ስህተት ነው። «ይህ ማነው?» ብለህ እንጂ «ምንድን ነው ይሄ ?» ብለህ መጠየቅ አልነበረብህም።
ለማንኛውም ይህ ሰው ለዓለም ጭቁን ህዝቦች ሲል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የታገለ የኮሚዩኒስት ስርዓት አርበኛ ነው፡፡ ለአዲሲቷ ሩሲያ ምስረታ ደግሞ ቁልፍ ሚና የነበረው ታላቁ አብዮታዊ መሪያችን ኮምሬድ ቪላድሚር ሌኒን ነው። የእሱን ገድል ለመዘከርና በረከቱን ለመቋደስ ስል፡ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ምስሉን በእቅፌ ይዤ እዞራለሁ !" በማለት ምላሽ ሰጠው።
.
ሩሲያዊው የኢሚግሬሽን ፍተሻና ቁጥጥር መኮንን፡ አጠገቡ ቆሞ በሚናገረው የሃገሩ ዜጋ አስተሳሰብ እጅግ ተደመመ። በግለሰቡ ጽኑ የሌኒን ፍቅርና እምነትም ክልቡ ተደሰተ። እናም፡-
"መልካም ! ማለፍ ትችላለህ ጓድ !" ሲል በክብር ሸኘው።
*
ሩስኪው አሁን USA ደርሷል። የአሜሪካ አየር መንገድ ተርሚናል የፍትሻ ክፍል ውስጥ እየተፈተሸ ነው። የፍተሻ ኦፊሰሩ ሻንጣ ውስጥ ያለውን ቅርጻ ቅርጽ ተመለከተ።
.
"ምንድን ነው ይሄ ?" በማለት አሜሪካዊው የጉሙሩክ ኦፊሰር ከሩሲያዊው መኮንን ጋር ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበለት። ሩሲኪውም፡- "ይቅርታ ጌታየ ! ጥያቄህን ያቀረብክበት መንገድ
ትክክል አይደለም። «ይህ ማነው?» ብለህ እንጂ «ምንድን ነው ይሄ ?» ብለህ መጠየቅ አልነበረብህም።
.
ለማንኛውም አገሬን ለቅቄ ወደዚች ሰላማዊ ምድር
የመጣሁት፡ በዚህ ጠማማና እርኩስ ግለሰብ ምክንያት ነው። የዚህ ከይሲ ሰው ፍልስፍና ነው ዓለምን በሁለት ጎራ ክፍሎ ህዝቦችን ባላንጣ ያደረገው። በዚህም ምክንያት ለበርካታ ሃገራት የብጥብጥና የቀውስ ምንጭ ሆኗል። በዚህ ሰው ርዕዮት-ዓለም አያሌ ዜጎች አልቀዋል። ይህ ሰው የዲያቢሊስ ደቀ መዝሙር ነው። ሌኒን ይባላል ! ቅርጻ ቅርጹን በዞርኩበት ቦታ ሁሉ ከኔ አልነጥለው። ምክንያቱም ሁሌም ስመለከተው ለመርገም እንዲያመቸኝ ብዬ ነው ከጎኔ የማለየው !" ሲል ምላሽ ሰጠው።
.
አሜሪካዊው የፍተሻ ክፍል ኦፊሰር፡ በሩሲያዊው እንግዳ ቅን እና ስሜት የሚነካ ንግግር ተመሰጠ። እናም፡-
.
"ጌታየ ! እንኳን በሰላም የአሜሪካን ምድር ረገጡ። አሁን ማለፍ ይችላሉ !" አለው በክብር።
.
መንገደኛው ሩስኪ ወደ ማረፊያው አመራ። የአረፈበት ሆቴልም ቅርጻ ቅርጹን አውጥቶ አስቀመጠው። ልጁም ቅርጻቅርጹን ከተመለከተ ብኋላ፡-
.
" አባዬ ይህ ማነው ?" ሲል አባቱ በሚፈልገው መንገድ ጥያቄ አቀረበለት። ሩስኪውም፡-

" የኔ ልጅ ! «ይህ ማነው?» ብለህ ጥያቄ ማቅረብህ ስህተት ነው። መጠየቅ የነበረብህ እንደ ሩሲያዊውና አሜሪካዊው የፍተሻ ሰራተኞች «ምንድን ነው ይሄ ?» ብለህ ነበር።
ለማንኛውም ይህ የምትመለከተው ቅርጻቅርጽ፡ 10 ኪሎ ግራም ባለ 24 ካራት ወርቅ ሲሆን፡ እኔ አባትህ ያለ አንዳች ቀረጥ ነው ወደዚህ አገር በሰላም ያስገባሁት። ገባህ የኔ ልጅ !" ሲል ብልጠቱን ሳይሆን እውነቱን ለልጁ ነገረው። ፖለቲካዊ ኮንትሮባንድ !
.
ብልጥ ሰው የሚሰራውን ሳይሆን መስማት የምትፈልገውን እየነገረህ ነው ፍላጎቱን የሚፈጽመው !!
.😄😄😄😄😄
AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴🇮:
ልጅ እያሱ እና ደጃች ተፈሪ መኮንን
------
(አፈንዲ ሙተቂ)
---------
ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከበርካታ ሙስሊም ባላባቶች ጋር የተነሳቸው ፎቶግራፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሀረር ውስጥ ገራድ አብዱላሂ አሊ ሳዲቅ ከሚባል የሀረር ገዥ ቤተሰብ ጋር የተነሳው ፎቶግራፍ በብዙ ስፍራዎች ተለጥፎ አይቼዋለሁ፡፡ አንዳንድ ምንጮች ያ ፎቶግራፍ ልጅ እያሱን ለመወንጀል “montage” በሚባለው የፈጠራ ጥበብ የተሰራ ነው የሚል ታሪክ ያስነብባሉ። ለምሳሌ “የሃያኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ “ፎቶውን የሰራው ዝነኛው እንግሊዛዊ ወታደር ቶማስ ለውሬንስ (በዓለም ታሪክ መጻሕፍት Lawerence of Arabia በሚል ቅጽል ስም የሚታወቅ) ነው” በማለት ጽፈዋል።

ሆኖም የልጅ እያሱ የልጅ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ እያሱ እንደዚህ ዓይነት ፎቶዎች እርግጠኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከአስር ዓመታት በፊት “ጎህ” ለተሰኘ መጽሔት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ግርማ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት።

“ከሼኮችና ከሌሎችም ጋር የተነሱአቸው ፎቶግራፎች ብዙዎች አሉ። ስለዚህ ከቄስ ጋር መነሳትም የተለመደ ነበርና ልጅ እያሱ ሁለቱንም እኩል አድርጎ ለማየት የነበራቸው ፖሊሲ አካል ነው”። (ጎህ መጽሔት፣ ቅጽ 1፣ ቁጥር 5፣ ጥቅምት 1993፣ ገጽ 13)

በቅርብ ጊዜ ስለልጅ እያሱና የአፋሮች ግንኙነት የጻፉት አራሚስ ሁመድ ሱሌ (Aramis Houmed Soulé) የተባሉ ምሁር ልጅ እያሱ ከአፋር ባላባቶችም ጋር እኝህን መሰል ፎቶግራፎች መነሳቱን አረጋግጠዋል። ስለዚህ ፎቶው “ፎርጅድ” አልነበረም ማለት ነው። ሁለቱ ምሁራን (ፕሮፌሰር ግርማ እና አራሚስ ሁመድ ሱሌ) በትክክል እንደገለጹት ልጅ እያሱ ፎቶግራፉን የተነሳበት ዓላማ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር እኩል መሆናቸውን ለማሳየት በሚል ነው። ታዲያ ልጅ እያሱ በመናፍቅነት በተከሰሰበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ፎቶዎች እየተለቀሙ እንደማስረጃ ቀርበውበት ነበር።

ይህ የልጅ እያሱ መስለም በዘመኑ ብዙ የተባለለት ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ከአፍ ታሪክ የበለጠ ማስረጃ ሊቀርብለት አልቻለም። የእርሱ የስልጣን ባለጋራ የሆኑት ራስ ተፈሪ መኮንን (አጼ ኃይለ ሥላሴ) በጻፉት “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘው ግለ-ታሪካቸው ውስጥ የእያሱ ወንጀሎች በማለት ከዘረዘሯቸው አስራ አንድ ነጥቦች መካከል አስሩ አቀራረባቸው ቢለያይም ይዘታቸው አንድ ነው። ይኸውም የልጅ እያሱ መስለም ነው። እነዚህ ነጥቦች የልጅ እያሱን አራት ሴቶች ማግባት፣ መስጊድ ገብቶ መስገድና ቁርአን ማንበብ፣ መስጊድ ማሰራት፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ “ላኢላሃ ኢለላህ” የሚል ጽሁፍ ማስጠለፍ ወዘተ… የመሳሰሉት ናቸው።

ይሁንና የልጅ እያሱ የልጅ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ “እነዚህ ሁሉ የፈጠራ ክሶች ናቸው” ነው የሚሉት። በተለይ ከተፈሪ መኮንን ጋር ከተዋጉ በኋላ ተሸንፈው በሸሹበት የአፋር በረሃ ያስጠለሏቸው የዘመኑ የአፋር ሱልጣን አቡበከር የወንድም ልጅ የሆኑት ሀንፍሬ አሊሚራህ ስለልጅ እያሱ ፍጹም ክርስቲያን መሆን ምስክርነታቸውን እንደሰጡአቸው ይገልጻሉ። አራሚስ ሁመድ ሱሌ የተባሉት ምሁርም የፕሮፌሰር ግርማን አባባል የሚያጠናክር ምስክርነት ሰጥተዋል። እኝህ ምሁር እንደጻፉት ክርስቲያኑ ልጅ እያሱ በአፋር ምድር ሳለ በክርስትና እምነቱ ከመጽናቱም በላይ አገልጋዮቹ የሰሩለትን የማሽላ ጠላ ይጠጣ ነበር። ስለዚህ ልጅ እያሱ ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ ጋር እኩል ለማድረግ ጥረት ከማድረጉ ውጪ ለራሱ ክርስቲያን ሆኖ ነው የኖረው ማለት ነው።

ሆነም ቀረ ግን የእያሱ መስለም እርሱን ከስልጣን ለማውረድ የተደረገው ትግል ማጠንጠኛ ሆኖ ነው ያረፈው። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ክሱ በዚህ ስልት የተቀናበረው እያሱን በህዝቡና በጦር ሀይሉ ዘንድ ለማስጠላት አመቺ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነው ይላሉ። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ልጅ እያሱ ቀጨኔ መድኃኒዓለምን የመሳሰሉ ደብሮችን እንዳልተከለ ሁሉ ከፍ ብሎ የሚወራው መስጊዶችን ማሰራቱ ነው። ለክሱ ማስረጃ አምጡ በሚባልበት ጊዜ “ድሮውንስ ከሙሐመድ ዓሊ ልጅ ምን ይጠበቅ ኖሯል?!” የሚል ቃለ አጋኖ ይደሰኮር ነበር። “ይሁንና” ይላሉ ፕሮፌሰር ባህሩ “ለሸዋ መኳንንት የእያሱ አደገኛነት የፖለቲካ የበላይነታቸውን ከመፈታተኑ ላይ ነበር። ስለዚህ የመናፍቅነቱ ክስ የመነጨው ለሃይማኖት ከመጨነቅ ሳይሆን ለተፈጠረው የፖለቲካ ስጋት ርዕዮተ ዓለማዊ ሽፋን ሆኖ ለማገልገል ካለው አመቺነት ነው።” (ባህሩ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983፡ ገጽ 134-135)

በልጅ እያሱ ላይ የሚደረገው ዱለታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ልጅ እያሱ አባቱን “ንጉሥ ሚካኤል” በማለት በወሎና በትግሬ ላይ ባነገሠበት ጊዜ ነው። የሸዋ መኳንንት ራስ ሚካኤል ሰሜን ኢትዮጵያን በቀጥታ ሌላኛውን የኢትዮጵያ ክልል በልጁ በኩል መቆጣጠሩን አሰመሩበት። በመሆኑም የሸዋ መኳንንት “ይህ ወጣት ከቤተ መንግሥቱ ጠራርጎ ሳያስወጣን እንቅደመው” በማለት መሯሯጥ ጀመሩ። የዚህ አድማ ዋነኛ መሪና አቀናባሪ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ስለመሆኑ ምሁራን የሚስማሙበት ሐቅ ነው።
* * *
ከዚህ በፊት እንዳጫወትኳችሁ ልጅ እያሱ የዕድሜ ልክ ባላንጣው ሊሆን የበቃውን ደጃች ተፈሪ መኮንንን በጋብቻ ጠልፎ ዝም ሊያሰኘው ሞክሮ ነበር። ይሁንና ተፈሪ የእያሱ እህት ልጅ የሆነችውን ወ/ሮ መነን አስፋውን ቢያገባም ሁለቱ ወጣቶች ፍጹም ሊጣጣሙ አልቻሉም። ተፈሪ የዘመኑ ሀብታም ክፍለ ሀገር የነበረው ሀረርጌ የዕድሜ ልክ ግዛቴ ነው ብሎ ያስብ ነበር። እያሱ ደግሞ ተፈሪ በሀረር ሀብት መበልጸጉን አልወደደውም። በተለይም ደጃች ተፈሪ ከባቡር መስመር መዘርጋት ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱ መንግሥት ግምጃ ቤት አለኝታ ሊሆን የበቃውን የድሬዳዋ ጉምሩክ ገቢ በቀጥታ ሊቆጣጠረው መቻሉ ለልጅ እያሱ አልተዋጠለትም።

ነገር ግን ከዚህ ክስተት በላይ እያሱን በተፈሪ ላይ ያነሳሳው የልጅ እያሱን ስም የሚያጠፋ ሚስጢራዊ ደብዳቤ ለእንግሊዝ መንግሥት ተጽፎ መገኘቱ ነው። ይህንን ደብዳቤ የጻፉት የደጃች ተፈሪ መኮንን ጸሓፊና አንድ ማንነቱ በውል ያልተገለጸ ሌላ ሰው ናቸው። ደብዳቤው በማን ትዕዛዝ እንደተጻፈ ግን የታሪክ ሰነዶች በይፋ የሚገልጹት ነገር የለም። ልጅ እያሱ “ትዕዛዙን ያስተላለፈው ተፈሪ መኮንን ነው” ባይ ነው። በዚህም ወደ አዲስ አበባ አስጠርቶት ስለጉዳዩ ቢጠይቀው ደጃች ተፈሪ ከነገሩ ንጹህ መሆኑን በመሀላ ገለጸለት። ቢሆንም እያሱ አላመነውም። በመሆኑም በሁለቱ መካከል የነበረው ቅራኔ በጣም ተባባሰ።

ነገሮች በዚህ ላይ እንዳሉ ልጅ እያሱ ተፈሪ መኮንንን ወደ አዲስ አበባ አስጠርቶት እርሱን ሳያነጋግር ወደ ሀረር ወረደ። ከሀገሬው ህዝብ ጋር ከተማከረ በኋላም ደጃች ተፈሪ መኮንንን ከሀረር ገዥነቱ ሻረው። በምትኩም የከፋ ገዥ አድርጎ ሾመውና በአስቸኳይ ወደ ተሾመበት ክልል እንዲሄድ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጠው። የድሬ ዳዋ ጉምሩክንም ወዳጁ በነበረው ሶሪያዊው ሀሲብ ይዲልቢ ስር እንዲሆን አደረገው።
የልጅ እያሱ እርምጃ ተፈሪን በጣም አስደነገጠው። “ይህ መስፍን ሊውጠኝ እያመቻቸኝ ነው” በማለት እንዲያስብም አደረገው። ስለዚህ ደጃች ተፈሪ ወደ ከፋ መሄዱን ተወና አዲስ አበባ ሆኖ የሚበጀውን መንገድ ማፈላለግ ጀመረ። ልጅ እያሱ በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ ቢያዥጎደጉድለትም ደጃች ተፈሪ ልዩ ልዩ ሰበቦችን እያመካኘ በዋና ከተማይቱ ሰነበተ። የእያሱንም ልብ ለማቀዝቀዝ የስጋ ዘመዱ የሆነውን ቀኛዝማች እምሩ ኃይለ ሥላሴን (የኋለኛው ራስ እምሩ) የቃልና የጽሑፍ መልዕክት አስጨብጦ ልጅ እያሱ ወደሚገኝበት ድሬዳዋ ላከው። እያሱም የተፈሪን መልዕክት ከሰማ በኋላ እንዲህ አለ።

“ደጃች ተፈሪ አሳቡ ሁሉ ሌላ ነው። ያንዳንድ ወስላቶች ነገር እየሰማ ወዲያ ወዲህ ቢል ብርቱ ነገር ያገኘዋል። የአዲስ አበባ ወስላታ ሁሉ ፍሬ ያለው መስሎታል።” (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ”፣ በኢትኦጵ መጽሔት የቀረበ ጽሁፍ፣ ጥቅምት 1993፣ ገጽ 37)

ይህ የልጅ እያሱ አነጋገር በሁለቱ ልዑላን መካከል የነበረው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል። የእያሱ ንግግር ለደጃች ተፈሪ ጆሮ ከደረሰው በኋላ ተፈሪ በስውር ማድባቱን ትቶ እያሱን ከስልጣን ለመፈንገል የሚዶልቱትን መኳንንት በይፋ ተቀላቀለ። በአስገራሚ ፍጥነትም የዱለታውን መሪነት ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እጅ ወሰደው።
* * *
የሁለቱ ወጣቶች መገፋፋት ይፋ ሆኗል። ቀጣዩ ነገር “ማን ቀድሞ አጥቅቶ የአሸናፊነቱን ዘውድ ይቀዳጃል” የሚለው ብቻ ነበር። የሸዋና የምዕራብ ኢትዮጵያ ባላባቶች በተፈሪ ዙሪያ ተሰልፈዋል። የወሎ፣ የአፋር፣ የኦጋዴንና የሀረርጌ ባላባቶች የእያሱን ጎራ ተቀላቅለዋል። ቢሆንም ሁለቱ ጎራዎች በራሳቸው ወኔ ፍልሚያውን መጀመር አልቻሉም። የመጨረሻውን ፍልሚያ ለማስጀመር ሌላ ስውር እጅ አስፈልጓል። የዘመኑ ታላላቅ ቅኝ ገዥዎች እጅ!

እንግሊዝ፣ ኢጣሊያና ፈረንሳይ ሁለቱ ልዑላን ሲጣሉ መጀመሪያ ላይ አይተው እንዳላዩ ሆነው ስራቸውን ማከናወኑን ነበር የመረጡት። ከቆይታ በኋላ ግን የልጅ እያሱ የእኩልነት ፖሊሲ (በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መካከል እኩልነትን ለማስፈን በሚል የሚወስዳቸው እርምጃዎች) የነርሱን ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ተገነዘቡ። የጠረፍ አካባቢ ገዥዎች ከቅኝ ገዥዎች ጋር ለሚያደርጉት ውጊያ የሞራል ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ አስቀየማቸው። በተለይ እንግሊዝ ሶማሌላንድን ከብሪታኒያ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ለ30 ዓመታት ሲዋጋ ለኖረው ሰይድ አብዱሌ ሐሰን የተሰኘ የኦጋዴን ሶማሊዎች ብሔራዊ ጀግና የመሳሪያ ድጋፍ በገፍ ማቅረቡ ቅኝ ገዥዎቹን በጣም አስበረገጋቸው። “ይህ ወጣት ዝም ተብሎ ከተተወ ከዚህ አካባቢ ሊያስነቅለን ነው” እንዲሉም አደረጋቸው። አልፎ ተርፎም ልጅ እያሱ በዘመኑ ከነዚህ ቅኝ ገዥዎች ጋር በአንደኛው የዓለም ጦርነት የሚዋጉትን ጀርመንና ቱርክን የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየቱ ሶስቱ ሀያላን እርሱን ከስልጣን ለመንቀል በሚደረገው ትግል በቀጥታ እንዲሳተፉ አነቃነቃቸው።

በመሆኑም ሀያላኑ ጳጉሜ 1908 የእያሱን የጠላትነት እርምጃ በማስመልከት በጻፉት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አድማውን መቀላቀላቸው ይፋ ሆነ። ከመጋረጃ ጀርባ ኩዴታ ጠንስሰው ወደ ተግባር መለወጥ ላቃታቸው የሸዋ መኳንንት ኩዴታው ወደ ተግባር የሚለወጥበትንም ስልት አስጨበጧቸው። በተለይ በእያሱ ላይ የቀረበው የመናፍቅነት ክስ ትክክል መሆኑን ለማስረገጥ የእያሱን መስለም የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን እያባዙ በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች አሰራጩ።
* * *
ይህ ውጥረት በተፈጠረበት ወቅት ልጅ እያሱ ኦጋዴን ነበር። ከበረሃ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በቤቱ ላይ የተለኮሰውን እሳት እንዲያጠፋ ወዳጆቹ መልዕክት ቢሰዱለት “የሸዋን መኳንንት በአፉ ላይ ብሸናበት የሚናገረኝ የለም” የሚል የንቀት መልስ መለሰላቸው። በዚህም የስልጣን ፍጻሜውን አቃረበው። ታዲያ እያሱ የጠላቶቹን አሰላለፍ በደንብ የተገነዘበው አይመስልም። በርሱ ሐሳብ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማመጣጠን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች የሚቃወሙት የሸዋ መኳንንት ብቻ ነበሩ።

ነገሩ ግን እንዲያ አልነበረም። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉት ልጅ እያሱ ፖሊሲውን በግልጽ ባለማብራራቱ ተራው ህዝብ እንኳ ሀገሩን ለማስለም ሌት ተቀን የሚደክም አድርጎ ነው የወሰደው። በዚህ ላይ እነ ደጃች ተፈሪ በቆንስሎቹ ድጋፍ እያሱ የሚገለበጥበትን የሀሰት ክስ ቀምመው ሲያቀርቡለት ህዝቡም እንደ መኳንንቱ “ድሮስ ከሙሐመድ ዓሊ ልጅ” አለና አረፈው። በመሆኑም ሰፊው ህዝበ ክርስቲያን ለዱለታው ድጋፉን ሰጥቷል። የእያሱ እጣ አሳዛኝ የሚሆነው ድሮ የሚገብሩለት ሁሉ በዚህ ቀውጢ ጊዜ ሲከዱት ነው። በተለይ በስልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ በወሰዳቸው ተራማጅ እርምጃዎች ተደስተው በርሱ ዙሪያ የተሰለፉት ለውጥ ናፋቂ ምሁራን በዚህ የፈተና ወቅት የገቡበት ሳይታወቅ ከጎኑ ጠፍተዋል። አንዳንዶቹ ጭራሽ ከርሱ ጎራ ተነጥለው እርሱን ወደ መንቀፍ ገብተዋል። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው የነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ነገር ነው። ነጋድራስ አፈወርቅ ልጅ እያሱን በስልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ተስፋና የለውጥ ሀዋሪያ አድርገው እንዳላንቆለጳጰሱት ሁሉ በዚህ የመከራ ወቅት እንዲህ የሚል ስንኝ መቋጠራቸውን ታሪክ አዋቂዎች በትውስታቸው መዝግበዋል።

ሙሐመድ እያሱ
ለገመ በራሱ
እያሱ ሙሐመድ
አልጋ ሲሉት አመድ።
(ብርሃኑ ድንቄ፣ ቄሳርና አብዮት፣ 1986፣ ገጽ 30)

እንግዲህ የልጅ እያሱ ውድቀት እውን ሆነ። ለሶስት ዓመታት የነገሠበትን አልጋ ከውጪና ከውስጥ በተሸረበበት ሴራ አጣ። መስከረም 17/1909 ዓ.ል. ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብላ ዙፋኑ ላይ ስትቀመጥ ደጃች ተፈሪ መኮንን “ራስ” ተብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ሆነ። ይህ ሁሉ ሲከናወን ኢላማ የሌለው ተኩስ አልፎ አልፎ ከመሰማቱ በስተቀር አዲስ አበባ ሰላም ነበረች (አንዳንዶች 17 ሰዎች ሞተዋል በማለት ጽፈዋል)።
* * *
የልጅ እያሱ ከስልጣን መውረድ ዜና የተሰማው እያሱ ጅጅጋ እያለ ነው። የዜናውን መሰማት ተከትሎ የእያሱ ደጋፊዎች በሚበዙባቸው ሀረርና ድሬ ዳዋ ታላቅ ረብሻ ተነሳ። የደጃች ተፈሪ መኮንን ደጋፊዎች የተባሉት እየተሳደዱ ተፈጁ። እያሱ በከተሞቹ ደርሶ ሁኔታውን ካረጋጋ በኋላ በአሻጥር የተወሰደበትን ዙፋን ለማስመለስ ከከተሞቹ ነዋሪዎች ጋር ተማከረ። በዚህም የህዝቡን ድጋፍ ካገኝ በኋላ በሸዋ ላይ ለመዝመት መዘጋጀት ጀመረ። ይሁንና ዝግጅቱን ሳያጠናቅቅ እነ ራስ ተፈሪ የላኩት 15,000 ጦር ወደ ሀረርጌ እየመጣ መሆኑ ታወቀ። ልጅ እያሱም የሸዋውን ጦር ለመግጠም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ገሠገሠ። ሁለቱ ሀይሎች ሚኤሶ አጠገብ ተገናኙ። ትልቅ ውጊያም አደረጉ። በጦርነቱ የሸዋው ሀይል ድል ስለቀናው ልጅ እያሱ ወደ አፋር በረሃ ሸሸ። የልጅ እያሱ አባት (ራስ ሚካኤል) የልጁን ስልጣን ለማስመለስ 100,00 ጦር አስከትቶ ወደ ሸዋ ዘመተ። ነገር ግን እርሱም እንደ ልጁ ሰገሌ ላይ ተሸነፈ።

* * *
ልጅ እያሱ የሰገሌውን መርዶ ከሰማ በኋላ በሽሽት ነው የኖረው ለማለት ይቻላል። በመቅደላና በደሴ አነስተኛ ውጊያዎችን ቢያደርግም በለስ ሊቀናው አልቻለም። ከዚያም ወደ አውሳ በረሃ ሄዶ ከወዳጁ ከሱልጣን አቡበከር ጋር ለጥቂት ዓመታት ኖረ። ነገር ግን ጠላቶቹ እዚያም እንዲቆይ አልፈቀዱለትም። ከሀረርጌና ከወሎ ትልቅ ጦር ቢያዘምቱበት ወደ ትግራይ ሸሸ። በትግራይ ውስጥ ለጥቂት ወራት ከቆየ በኋላ በ1915 ተያዘና ፍቼ ታሰረ። እዚያ እያለ የጎጃሙ ራስ ሀይሉ ተክለሀይማኖት እስር ቤቱን
ሰብሮ ሊያስወስደው መሆኑ ስለተወራ ሌላ ቦታ እንዲዛወር ተወሰነ። በመሆኑም ወደ ሀረርጌ ተወስዶ ጋራ ሙለታ አምባ ላይ በተሰራለት እስር ቤት እንዲታሰር ተደረገ። በዚህ አምባ ላይም ለአስር ዓመታት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ ጥቅምት 1928 መሞቱ ይፋ ሆነ።
* * *
ልጅ እያሱ ሚካኤል የስልጣን ዘመኑ በእንቆቅልሽ የተመላ ነው። መንግሥቱን ያስተዳደረበት ዘይቤ፣ ከስልጣን የወረደበት ሁኔታ፣ በእስር ላይ ያሳለፈው ህይወትና የሞተበትም ሁኔታ እንቆቅልሽ ነው። ሌላው ይቅርና የተቀበረት ቦታ እንኳ እስከ አሁን ድረስ በትክክል አይታወቅም። እንቆቅልሽ በእንቆቅልሽ!

ተሸዋረጋ የሚወለድ ልጅ
እምብዛም አይከፋ እምብዛም አይበጅ
ትንሽ ወደኋላ ይቀረዋል እንጅ።
ባሽከሮቹ ክፋት ደግሞም ባጋፋሪ
ዘውዱ ሲዞር አየን ወደ ልጅ ተፈሪ።
እያሱ የሚባል አንድ ልጅ ተወልዶ
የአባቶቹን መሬት አደረገው ባዶ።
መች ባንተ ይሆናል ምኒልክ ንጉሡ
አንተ አስበህ ነበር ልትሰጠው ለእያሱ
እንኳን ሊነግሥና ይያዛል ለነፍሱ
በራስ መኮንን ልጅ ትጠፋለች ነፍሱ
ተጌታ ተፈርዷል ዘውዲቱ ሊነግሱ።
የልጅ እያሱ ሰው የአባሻንቆ ሎሌ
ተለቀለቀለት መወቂያው ሰገሌ።
ሰገሌ ሜዳ ላይ የመጣብን መርዶ
በቀኝ እጁ ካራ በግራው ብርንዶ።
(የወሎው ሼኽ ሑሴን ጂብሪል ስለልጅ እያሱ ተናግረውታል ከተባለው ትንቢት: ምንጭ፣ ቦጋለ ተፈሪ በዙ፡ “ትንቢተ ሼኽ ሑሴን ጅብሪል”፣ አዲስ አበባ፣ 1985)
* * *
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 15/2005
በሀረር ከተማ ተጻፈ።
"
@hollypoem
ጋዛ የኢማሙ ሻፊዒይ ሀገር ናት!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
-----
በጋዛ የተወለዱት የአህሉ ሱንና ወል ጀመዓ ኢማም ሙሐመድ ኢብን ኢድሪስ አሽ-ሻፊዒይ እንዲህ ብለው ነበር።

"ከቁርአን ውስጥ አንዲት አያት አለች። በበዳዮች (ለዟሊሞች) ላይ አውዳሚ ቀስት ስትሆን፣ ለተበዳዮች ደግሞ ተስፋ ናት"

"ያቺ አያት (አንቀጽ) የትኛዋ ናት?" ተብለው ሲጠየቁ የሚከተለው አንቀጽ መሆኑን ተናገሩ።
” ﻭﻣﺎ ﻛﺎﻥ ﺭﺑﻚ ﻧﺴﻴﺎ “
“ጌታህም ረሺ (ዘንጊ) አይደለም”
(መርየም 64)
-------
አዎን! ጌታችን በዳዮች የሚሰሩትን እያንዳንዱን ግፍ እየተመለከተ ነው። ደግሞም በዳዮች ከሰሩት ግፍ አንዱንም አይረሳም። ሁሉም ነገር በእርሱ ዘንድ እየተመዘገበ ነው። እርሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ለግፈኞችና ለበዳዮች የእጃቸውን ይሰጣቸዋል።

አብሽር! አብሽር!
-----
Stop the Genocide in Gaza.
Free Palestine.
Free Gaza.
End the Occupation
------
የቴሌግራም ቻናሌ የሚከተለው ነው።
You may join my telegram channel here

https://www.tgoop.com/hollypoem
-----
ተማም። እናመሰግናለን። Galatoomaa
Hanan Al- Niel is blind but she is a Queen of Nubia
---
ሐናን አል-ኒል  (ዐይነ ስውሯ የኑቢያ ንግሥት)
---
ሀረር ጌይ የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፌን በማስታወሻነት ከሰጠኋቸው ስብእናዎች መካከል አንዷ ይህቺ ውብ እና ድምጸ መረዋ የሆነችው የኑቢያ ንግሥት ናት። በመጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ብዬ ነው ማስታወሻዬን የጻፍኩላት።
                                                                
  "ሐኒ! ሐኒዬ! “አነ ቢሒብበኪ ያሐኒ!” ነፍሲያዬ ያንቺ ወዳጅ ናት፡፡ አንቺ እኮ ከፈጣሪ የተላክሽልኝ የብርታት መድሀኒቴ ነሽ፡፡

  ሐኒዬ! ካንቺ የተማርኩትን የጽናት መመሪያ ስከተል ኖሬአለሁ።  ዛሬ እዚህ ደርሻለሁኝ፡፡ አልሐምዱሊላህ!  የወደፊቱንም  ወደፊት እናየዋለን። ኢንሻአላህ!

   ሐኒ! አላህ ዪጠዊል ዑምረኪ! እድሜ፣ ሰላምና ጤና ላንቺ ይሁን ያ ቢንተ ኒል!
---
(አፈንዲ ሙተቂ፤ “ሀረር ጌይ- የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች” ፤ 2004፤ ገጽ 9 )
        *  *  *
ለሐናን አል-ኒል ከዚህ በላይም ቢሆን ይገባታል፡፡ አንድ ቀን እርሷን መውደዴን እንዴት እንደምገልጽላት ይታየኛል፡፡ ኢንሻ አላህ!! እድሜና አጋጣሚውን ይስጥህ በሉኝ ብቻ!!
---
ሐናን በቀድሞ ዘመን ትዘፍን ነበር። አሁን ዘፈኑን እርግፍ አድርጋ ትታ ነሺዳ ላይ ተሰማርታለች።
-------
የቴሌግራም ቻናሌ የሚከተለው ነው።

You may join my telegram channel here.

https://www.tgoop.com/hollypoem
ፔተርሆፍ ቤተመንግሥት፣ ሩሲያ
------
የሩሲያ መዲና ሆነው ካገለገሉት መካከል አንደኛዋ በብዙ ነገሮቿ የሩሲያ ኢምፓየር መስራች ከሆነው ታላቁ ጴጥሮስ ጋር የተሳሰረች ናት። ከተማዋ ራሷ በታላቁ ጴጥሮስ ስም Saint Petersburg እየተባለች ትጠራለች። ታላቁ ጴጥሮስ በከተማዋ ካሰራቸው በርካታ ግንባታዎች መካከል አንደኛው በፎቶው ላይ የሚታየው የ"ፔተርሆፍ" ቤተመንግሥት ነው። ይህንን ውብ ቤተ መንግሥት እና ሌሎች የከተዋማን ማራኪ ሕንጻዎች ለመጎብኘት በየዓመቱ አስር ሚሊዮን ቱሪስቶች ወደዚያ ይጎርፋሉ።
--------
"ሴንት ፒተርስበርግ" በተለያየ ጊዜ ስሟ ተቀይሮ ነበር። በመሆኑም በ1905-1924 ባሉት ዓመታት "Petrograd" የተባለች ሲሆን ከ1924-1992 ደግሞ "ሌኒን ግራድ" የሚል ስም ነበራት። የሶቪየት ህብረት በ1992 ስትፈርስ ግን ስሟ እንደ ድሮው "Saint Petersburg" ሆኗል። ከተማዋ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆና ተመዝግባለች።
ፍልስጥኤም እና የኛ ሀገር በዘበዛዎች
(አፈንዲ ሙተቂ)
------
የእስራኤል-ፍልስጥኤም ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የኛ ሀገር በዘበዛዎች ነገሩን የክርስቲያንና የሙስሊም ንትርክ እያስመሰሉ ረድፋቸውን የሚያሰማምሩበት አኳኋን በጣም ይገርማል። ዓለም በተራቀቀበት በዚህ ዘመን እንኳ በአደራ እንዳስቀመጡት ድንጋይ በአንድ ቦታ ተቸክለው በራሳቸው ምናብ በፈጠሩት ተረት ልክ ነገሩን ሊሰፍሩ መሞከራቸው በጣም ያስደንቃል።
-----
እውነታው  ግልጽ ነው። በተረት የተሸፋፈነ ሳይሆን በማስረጃ እና በመረጃ የተደገፈ ዓለም አቀፍ ሐቅ ነው።

ፍልስጥኤም ከ1949—1967 ባለው ጊዜ በጉልበት የተያዘች ቅኝ ግዛት ናት። የዓለም ሰላም ወዳድ ማኅበረሰብ "ፍልስጥኤም ነፃ ትውጣ" በማለት ነው የሚጮኸው። ኸላስ! አለቀ! አበቃ!

የኛ ሀገር በዘበዛዎች አረዳድ ግን ሁልጊዜ በተቃራኒው ነው። ፍልስጥኤምና እስራኤል ሲጋጩ ነገሩን የሀይማኖት ውዝግብ ያስመስሉታል።  ግብፅና ኮንጎ በእግር ኳስ በሚጋጠሙበት ጊዜም የሀይማኖት ውዝግብ ያስመስሉታል ዘይገርም!!
---
ሐቁ በአጭሩ የሚከተለው ነው።

የፍልስጥኤም ጥያቄ የነፃነት እና የፍትሕ ጥያቄ ነው። ፍልስጥኤማዊያን ደግሞ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ናቸው። በተለያዩ የፍልስጥኤም የፖለቲካ ድርጅቶች ዙሪያ ተሰባስበው ለሀገራቸው ነፃነት የሚታገሉት አርበኞች የሁለቱም ሀይማኖት ተከታዮች ናቸው። እነ ጆርጅ ሐበሽ፣ ለይላ ኻሊድ፣ ዋዲ ሀዳድ፣ ናይፍ ሃዋትማ እና ሀናን አሽረዊን የመሳሰሉት ታጋዮች ክርስቲያኖች ሲሆኑ እንደ ያሲር አረፋት፣ ሳኢብ ኢርቃት፣ አሕመድ ቁሬ፣ ማህሙድ አባስ፣ ማህሙድ ዳርዊሽ፣ ዒስማኢል ሐኒያ፣ አሕመድ ጂብሪል የመሳሰሉት ደግሞ ሙስሊሞች ናቸው።
---
እኛ እየተቃወምን ያለነው ግፈኞች በፍልስጥኤማዊያን ላይ የወሰዱትንና እየወሰዱት ያሉትን ህገ ወጥ እርምጃ ነው። ይህንን ድርጊት የክርስቲያን—ሙስሊም ግጭት አድርጎ መረዳት ከባድ ስህተት ነው።
------
በዘበዛዎቻችን ሆይ!

ክርስቲያን እና ሙስሊም እየተጋጨ አይደለም። እስራኤል የምትባል እብሪተኛ እና "ብቸኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን" ባይ ዘረኛ መንግሥት የፍልስጥኤማዊያንን ሀገር በጉልበት ቀምታለች። ፍልስጥኤማዊያን ደግሞ ለተቀሙት ሀገራቸውና ለነፃነታቸው እየታገሉ ነው። ዓለም በሙሉ "ፍልስጥኤም ነፃ ትውጣ" ሲል አሜሪካ የምትባል ሌባ እና ማጅራት መቺ የአውሮጳ እና የሰሜን አሜሪካ ቡችሎቿን አስተባብራ "እስራኤል እንደፈለገችው ትጨፍር! እንደፈለገችው ሕዝብ ይጨርስ" ብላ ቆማ እየተሟገተችላት ነው። በመሳሪያ እና በገንዘብ እየረዳቻት ነው። "ምንድነው ጉዱ!" ተብላ ስትጠየቅ "እስራኤልን መደገፍ ለኔ ጂኦ-ፖለቲካ በጣም ያስፈልገኛል" በማለት ታላግጣለች።
--------
ግፍና ግፈኛ ይጥፋ!!
ፍልስጥኤም ነፃ ትውጣ!!
የፍልስጥኤማዊያን የዘመናት እምባ ይታበስ!!
-------
አፈንዲ ሙተቂ
October 9/2023
›የት ያደርሰን ይሆን?›
ዘመነኛ ፍቺ ዘመነኛ ትርጉም፤
ዘመነኛ እይታን ዘመነኛን ግጥም፤
ዘመነኛን ጥበብ የኋሊት ጎትቶ፤
ጭብጡን ሳይረዱ መሮጥ ልጓም ፈቶ፤
ከስጋት ተዳርቶ፤
ለሰው ስም አውጥቶ፤
በክፋት እስትንፋስ ሻማውን አጥፍቶ፡፡
ምን ይጠቅመን ይሆን?
የት ያደርሰን ይሆን?
ግብዝ ስጋታችን፤
ምክር መከራ ሆኖ ሲራቆት ቤታችን፡፡
June 2016

https://joinluvlive.com/FrP842
የጣሊባን መስራችን በጨረፍታ
----
አፈንዲ ሙተቂ
----
ሙላህ ሙሐመድ ዑመር ይባላል። የጣሊባን ንቅናቄ አባላት  "አሚሩል ሙእሚኒን" ይሉታል። "የምእመናን አዛዥ" ማለት ነው። "ሙላህ" የሚለውም የማዕረግ ስሙ ሲሆን የትውልድ ስሙ "ሙሐመድ ዑመር ጉላም ነቢ አኹንድ" ነው።

ሙሐመድ ዑመር በደቡብ አፍጋኒስታን በምትገኘው የካንዳሃር ከተማ አቅራቢያ ነው የተወለደው። የልደት ዘመኑ እ.ኤ. አ. 1960 እንደሆነም በጣሊባን ተገልጿል። ቁመቱ ከሁለት ሜትር የሚበልጥ ረጅም ሰው መሆኑም ይወሳል።

ሙሐመድ ዑመር በወጣትነቱ "ዳሩል ዑሉም ሐቃኒያ" ከሚባለው የትምህርት ተቋም ገብቶ እስላማዊውን የሸሪዓ ህግ አጥንቷል። ሶቪየት ህብረት ጦሯን  ወደ አፍጋኒስታን ባስገባችበት ዘመን ደግሞ የሙጃሂዲን ተዋጊዎችን ተቀላቅሎ ተዋግቷል። በጦርነቱም የቀኝ ዐይኑን አጥቷል (በግራ በኩል ያለውን ፎቶ ተመልከቱት)። በዚያ ጦርነት ከእርሱ ጋር የተሰለፉ የሙጃሂዲን ሸማቂዎች "በጣም ደፋርና ጀግና ተዋጊ ነበር" ይሉታል። 
-----
ሙሐመድ ዑመር ሶቪየት ህብረት ጦሯን ከአፍጋኒስታን ማውጣቷን ተከትሎ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት አልተሳተፈም። ከ1989 ጀምሮ በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ድንበር አካባቢ ባሉት የስደተኛ ካምፖች ማስተማርን ነው የመረጠው። በ1993 የትውልድ ቀዬውን ለመጎብኘት በሄደበት ጊዜ ግን ያየው ነገር ናላውን አዞረው።

በዚያን ጊዜ አፍጋኒስታን በጦር አበጋዞች ተበጣጥሳ ሁሉም በአካባቢው የየራሱ መንግሥት ሆኗል።  ፍትሕ ጠፍቷል። ጉቦ በሀገሩ ሰፍኗል። ሀብታሙ ደሃውን ይበድላል። ጠመንዣ የታጠቀ ሰው የሌሎችን ቤት በጉልበት እየሰበረ ይዘርፋል። ሴቶች በብዛት ይደፈራሉ። የመንግስት ቢሮዎች በሙስና ተጥለቅለዋል። በሰላም መጥቶ መግባት ከባድ ነው። በኮሚኒስቱ የነጂቡላህ ዘመን ጠፍቶ የነበረው ኦፕየም የማምራት ተግባር ዳግም አንሰራርቶ አፍጋኒስታን የአደንዛዥ እጽ ዋነኛ መነሻ ሆናለች።

ከሁሉ በላይ ሙሐመድ ዑመርን ያበሳጨው "ባቻ ባዚ" የሚባለው ኋላቀር እና አስቀያሚ ባህል በጦር አበጋዞቹ ዘመን እንደገና መመለሱ ነው። ይህ ባህል ህጻናት ወንዶች የታላላቅ ሰዎችን ወሲባዊ ጥማት እንዲያረኩ ተብለው ከቤተሰቦቻቸው የሚነጠቁበት ነው (ወንዶች ብቻ ናቸው የሚሳተፉበት። አንዱ የጦር አበጋዝ ህጻናቱን "አጫዋች" እያለ በቤቱ ያስቀምጥና የወሲብ መገልገያ ያደርጋቸዋል)። ድርጊቱ በኮሚኒስታዊው መንግሥት ዘመን በህግ የሚያስቀጣ ሲሆን የዶክተር ሙሐመድ ነጂቡላህ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። 
-----
ሙላህ ሙሐመድ ዑመር ከካንዳሃር ጉዞው ሲመለስ በዝምታ አልተቀመጠም። ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች መካከል ሀምሳ ያህሉን መልምሎ "ሀገራችን ተበላሽታለች፣ መከራው እያየለ ነው፣ ህዝባችንን ከጥፋት ለማዳን አንድ ነገር ማድረግ አለብን" በማለት አማከራቸው። በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት በሙሉ ሃሳቡን ደገፉት። በውይይቱ በተደረሰበት ስምምነት መሠረትም ከአፍጋኒስታን አልፎ የዓለምን የታሪክ ጉዞ የቀየረ አዲስ ንቅናቄ ተወለደ። ንቅናቄውም "ጣሊባን" ተባለ። ፍቺው "ተማሪዎች" ማለት ነው።
-----
በዚህ መንገድ ነበር የጣሊባን ንቅናቄ የተወለደው። ያ ንቅናቄም ነው እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ዙሪያ አነጋጋሪ፣ አወዛጋቢ እና አከራካሪ ሆኖ የዘለቀው። የንቅናቄው መሥራች ደግሞ ሙላህ ሙሐመድ ዑመር ነው። ይህ ሰው በአሜሪካዊያን "እጅግ ጽንፈኛ፣ ነውጠኛ እና የአሸባሪዎች አስጠጊ" ተብሎ ነው የተፈረጀው። ደጋፊዎቹ ግን በተቃራኒው "እውተኛ የአላህ ባሪያ" እያሉ ነው የሚገልጹት።
----
ጽሑፌን ከማብቃቴ በፊት ስለነዚህ ሁለት ፎቶዎች በጥቂቱ ልናገር።

ሙላህ ሙሐመድ ዑመር በህይወት ሳለ ወደ ቪዲዮ እና የፎቶ ካሜራ ብዙ አይቀርብም ነበር። እስከ ዛሬ ድረስ የእርሱ መሆናቸው በትክክል የታወቁት ፎቶዎች እነዚህ ብቻ ናቸው። አንደኛው ፎቶ በሶቪየት-አፍጋን ጦርነት ዐይኑን ካጣ በኋላ (በ1989 ገደማ) የተነሳ ሲሆን በኢንተርኔትና በፕሬስ በሰፊው ተሰራጭቶ ይገኛል። ብዙዎቻችንም የምናውቀው ይህንን ፎቶግራፍ ነው። ይህኛውን ፎቶ ማን እንዳነሳው አይታወቅም።

ሁለተኛው ፎቶ እርሱ ካረፈ በኋላ የጣሊባን የፕሬስ ክፍል የለቀቀው ነው። ይህኛው ፎቶ ሙሐመድ ዑመር ሶቪየቶችን ለመዋጋት ከመውጣቱ በፊት የተነሳ መሆኑን ጣሊባን በወቅቱ ገልጾ ነበር።
------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 17/2013
© Afendi Muteki, 2021
------
የቴሌግራም ቻናሌ የሚከተለው ነው።

You may join my telegram channel here.
ብሕማቕ ጓሳ ላም ትዉቃዕ፣
ብሕማቕ ዳኛ ቅኑዕ ይርታዕ
ፍቅረ ማርቆስ ደስታ- ኢትኖግራፈሩ ደራሲ
-----
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
-------
ዛሬ የዓለም የመጻሕፍት ቀን ነው ብለናል። በዚህ ቀን ብዙ መጻሕፍት ያበረተልንን አንድ ባለ ከባድ ሚዛን ደራሲያችንን በድጋሚ ብንዘክረው መልካም ነው።
------
የኢትዮጵያ የልብ-ወለድ ድርሰት (creative writing) ከሚታዩበት ድክመቶች አንዱ እንደ ሌሎች ሀገራት ድርሰት ፈርጀ ብዙ አለመሆኑ ነው። ደራሲዎቹ በአብዛኛው የሚያተኩሩት በሁለት ጭብጦች ላይ ነው- ፍቅር እና ወንጀል። ከዚያ ወጣ ብለው ሌሎች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሲሞክሩ አይታዩም።

ይሁን እንጂ ከተለመደው የድርሰቶቻችን አጻጻፍ ዘውግ ወጣ ብለው የራሳቸውን ልዩ የስነ-ጽሑፍ ዘይቤ እና የአትኩሮት ፈርጅ ለማስተዋወቅ የደከሙ ጥቂት ደራሲያን አሉ። ከእነዚያ ጥቂቶችም አንዱ በፎቶው ላይ የምትመለከቱት የብዕር ገበሬ ነው። ይህ ደራሲ ለየት የሚለው በርካታ ሰዎች (በተለይም ከተሜዎች) ብዙም ትኩረት የማይሰጡትን የብሄረሰብ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ተንተርሶ ግማሽ ደርዘን ያህል መጻሕፍትን ለተደራሲያን በማበርከቱ ነው።
-----
ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ይባላል። በ1955 በጎጃም ክፍለ ሀገር ነው የተወለደው። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ዲፓርትመንት በዲግሪ ተመረቀ። በተመሳሳይ ጊዜ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ በደቡብ ኦሞ ዞን፣ ጂንካ ከተማ ተመደበ። እዚያ መኖር ሲጀምርም በዞኑ ባሉት አስራ ስድስት ብሄረሰቦች ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጌጣ ጌጥ፣ የኢኮኖሚ ስምሪት፣ ባህላዊ ዳኝነት፣ ማህበራዊ ህይወት፣ ሙዚቃ፣ ዳንኪራ፣ አፈ-ታሪክ፣ ስነ-ቃል ወዘተ ተማረከ።
  
ፍቅረ ማርቆስ ያየውን ነገር በማድነቅ ብቻ አልታቀበም። ከመምህርነት ሙያው ጎን ለጎን ያየውንና የሰማውን ነገር በጥልቀት አጥንቶ ለመክተብ ወሰነ። በዚህም መሠረት ከብሄረሰቦቹ መካከል እርሱ ላለበት አካባቢ ቀረብ የሚለውን የሀመርን ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ኪነ-ጥበብ እና ትውፊት በማጥናት ያገኘውን ውጤት እንደ ግብአት ተጠቅሞ ኢትኖግራፊያዊ የፈጠራ ጽሑፎችን መጻፍ ጀመረ። በ1987 የመጀመሪያ ድርሰቱ የሆነውን "ከቡስካ በስተጀርባ"ን ለህትመት አበቃ።
----
ፍቅረ ማርቆስ መጽሐፉን ለህትመት ሲያበቃ ይዞት የተነሳው ጭብጥ ስለፍቅር እና ወንጀል መጻፍ በለመዱት ደራሲዎች እና በዚህ ዐውድ የተጻፉትን ድርሰቶች ማንበብ በለመደው ተደራሲ ዘንድ አጓጊ እና አነጋጋሪ መሆን አልቻለም ነበር። በአንትሮፖሎጂ እና ታሪክ ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን ግን ስራውን በጣም ነው ያደነቁለት። አንዳንዶቹም በዘመኑ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ የተለያዩ ግምገማዎችን ጽፈውበታል። ከዓመት በኋላ ደግሞ መጽሐፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም "ፍኩይ" የተሰኘ ሽልማት ተሸልሟል።

በዚህ የተነቃቃው ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ በ1990 በብዙዎች ዘንድ የሚወደደውንና የእርሱ masterpiece ስራ ለመሆን የበቃውን "ኢቫንጋዲ"ን ለአንባቢያን አበረከተ። በተከታዮቹ ዓመታትም " የዘርሲዎች ፍቅር"፣ "አቻሜ" እና "የንስር ዐይን" የተሰኙትን መጻሕፍት አሳተመ። በ1995 ገደማ አምስቱንም መጻሕፍት በአንድ ላይ አጠቃልሎ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ ሲያበቃ መጽሐፉን "Land of the Yellew Bull" በሚል ርእስ ለህትመት አበቃ።
-------
ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ በመጽሐፎቹ የሀመርን ህዝብ በማስተዋወቅ ብቻ አልቆመም። በብሄረሰቡ ደንብ መሠረት የሀመሮች አካል ሆኖ ከእነርሱ ጋር ኖሯል። ሀመሮች ደራሲው በብዕሩ የዋለላቸውን ውለታ በደንብ በመገንዘባቸው እንደ አንጋፋ ልጃቸው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ በ2004 "እሄዳለሁ" ብሎ ሳያስታውቃቸው ወደ አሜሪካ በመሻገሩ በጣም ተናደውበት ነበር።
 
ፍቅረ ማርቆስ በአሜሪካ ለአስር ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ አምና ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ታዲያ ደራሲው ወደ ሀመሮች ዘንድ ሲደርስ በዝምታ አልታለፈም። "በባህላችን መሠረት ጠፍቶ የመጣ ሰው ወደ ህዝቡ የሚቀላቀለው ከተገረፈ በኋላ ነው" ሲሉት ለመገረፍ አላቅማማም። ቅጣቱን ከተቀበለ በኋላም ከሚወዳቸው የሀመር ብሄረሰብ አባላት ጋር ተቀላቅሏል።
-------
ሀመር የሚባለው ኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ ብሄረሰብ በኢትዮጵያ ምድር ለረጅም ጊዜ ነው የኖረው። በቀድሞ ዘመናት ስለዚህ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ እና ትውፊት የነበረን እውቀት በጣም ውስን ነው። የሀመር ማንነት ወለል ብሎ የታየን ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ባደረገው የብዕር ተጋድሎ ነው። ደራሲው ብዙ የለፋበት ብሄረሰቡን የማስተዋወቅ ስራ ውጤት ማምጣቱንም በራሱ ዐይን ለማየት ችሏል።

ለምሳሌ በድሮ ዘመን የ"ኢቫንጋዲ"ን ምንነት የሚያውቅ ሰው እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ባለፉት ሀያ ዓመታት ግን "ኢቫንጋዲ" በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ጽንሰ ሐሳብ ለመሆን ከመብቃቱ ባሻገር ለብዙ የፈጠራ ስራዎች መነሻ ሲሆን አይተናል። በዚህ ረገድ ጎሳዬ ተስፋዬ የተጫወተው "ኢቫንጋዲ" የተሰኘው ተወዳጅ ዘፈን እንደ አብነት ሆኖ ሊነሳ ይችላል።
-----------
ኢትዮጵያ ውብ ናት!  በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የውበቷ ፈርጦች መካከል አንዱ ብሄርና ብሄረሰቦቻችን፣ ቋንቋዎቻችን፣ የብሄሮቻችን ቱባ ባህል፣ ትውፊት፣ ኪነ-ጥበብ እና ታሪክ ነው። በዚህ በኩል እንደ ኢትዮጵያ የታደሉት ጥቂት ሀገሮች ብቻ ናቸው። እነዚህ በፈጣሪ የተሰጡንን ውበቶች እንደ ትልቅ ጸጋ ቆጥረን በደንብ ከያዝናቸውና ከተጠቀምንባቸው የፍቅር ማጎልበቻ ከማድረግ አልፈን ከፍተኛ ገቢ ልንዝቅባቸው እንችላለን። 

ይህንን ለመረዳት ካሻን አሁንም የደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታን ስራዎች እንደ ምሳሌ ማንሳት ይበቃል። ፍቅረ ማርቆስ የደረሳቸው ስራዎች በኪናዊ ውበታቸው ከማማር አልፈው ብዙ ቱሪስቶች የሀመርን አካባቢ እንዲጎበኙ በማነሳሳት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እኛም ካወቅንበት የብሄረሰቦቻችንን ባህል፣ ቋንቋ፣ ትውፊት እና ታሪክ የወንድማማችነት ማጠናከሪያ፣ የእርስ በራስ መማማሪያ እና የውብ ኢትዮጵያዊነት ማጎልበቻ ከማድረግ አልፈን ትልቅ የሀገር ገቢ ማመንጫ አውታሮች ልናደርጋቸው እንችላለን።
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 3/2014 ተጻፈ።
-----
©Afendi Muteki, September 2021
-----
2025/07/08 11:38:30
Back to Top
HTML Embed Code: