tgoop.com/husseyn_y_abdery_wedaj/4007
Last Update:
[ስሟ መስጅድ ላይ የተፃፈው የአሮጊት ሴትዮ ታሪክ]
በድሮ ጊዜ ከነግስታት መካከል አንድ ንጉስ በከተማው ላይ መስጂድ ለመስራት ፈልጎ በዚህም መስጅድ ስራ በገንዘብም ሆነ በሌላ ነገር ማንም ሰው እንዳይሳተፍ አዘዘ።
በእርግጥም ንጉሱ በፈለገው መልኩ ያለምንም የሌላላ ሰው እገዛ የመስጅዱ ግንባታ ተጠናቆ በበሩ ላይም ስሙ እንዲፃፍ አዘዘ።
አንድ ቀን ሌሊት ንጉሱ በህልሙ ከሰማይ መላኢካ ወርዶ የሱን ስም ከመስጂዱ ደጃፍ ላይ ሰርዞ በስፍራው ላይም የሴት ስም ሲጽፍ ተመለከተ።
ታዲያ ንጉሱ ከእንቅልፉ በፍርሐት በመንቃት በመስጂዱ በር ላይ ስሙ መኖሩን ለማረጋገጥ ወታደሮቹን ላከ፤ ወታደሮቹ ተመልሰው ስሙ እንዳለ ነገሩት።
በሁለተኛው ሌሊት ንጉሱ ያንኑ ህልም አይቶ ከእንቅልፉ በተነሳ ጊዜ ስሙ መኖሩን ለማረጋገጥ ወታደሮቹን ለሁለተኛ ጊዜ ላካቸው፤ እነርሱም ሄደው ተመልሰው ስሙ እንዳለ ነገሩት፤ ንጉሡም በጣም ተገረመ።
በሦስተኛው ሌሊትም ያንኑ ህልም ተደጋገመበት..... ንጉሡ ከእንቅልፉ በነቃ በሕልሙ መስጅዱ ላይ ስሟ የተጻፈላትን ሴትዮ ሥሟን ሸምድዶ ስለ ነበር ወታደሮቹ እሷን ፈልገው ወደሱ እንዲያመጧት አዘዘ።
ወታደሮቹም እስኪያገኟት ድረስ ተበታተነው ፈልገው ወደ ንጉሡም አቀረቧት ፤ ሴትዮዋ ሚስኪን አሮጊት ነበረች፤ ወደ ንጉሱ ስትቀርብ በፍርሃት ተንቀጠቀጠች።
በመቀጠልም ንጉሱም «እኔ በሰራሁት መስጅድ ላይ ረድተሻል?» በማለት ጠየቃት። እሷም፡- «ንጉሥ ሆይ! እኔ ምስኪን አሮጊት ነኝ፣ በምትሰራው መስጅድ ላይ ማንም በምንም ነገር እንዳይረዳህ ስትከለክል ሰምቻለሁ» አለች።
እሱም፦ «በአሏህ እጠይቅሻለሁ ይህን መስጅድ ለመስራት ምን አስተዋፅኦ አድርገሻል?» አላት።
እሷም፦«ከዕለታት አንድ ቀን በመስጅዱ ጎን ሳልፍ ለመስጅ ስራ የሚውል እንጨትና የግንባታ መሳሪያ የተሸከመች እንስሳ ውሃ ተጠምታ ተመለከትኩ፤ የታሰረችበት ገመድ አጭር በመሆኑ ምክንያት በአቀራቢያዋ ከነበረ የውሃ ባልዲ ደርሳ መጠጣት አልቻለችም። በዚህ ሰኣት ለአሏህ ብዬ ውሃው ወደሷ አስጠግቸላት እስክትጠግ ጠጥታ ከሞት ተረፈች፤ እኔ ያደረኩት ይህ ብቻ ነው አለች።
ንጉሱም በመገረም «ሱብሐን አሏህ! አንቺ ለአሏህ ብለሽ በመስራት ተቀባይነት አገኘሽ፣ እኔ ግን የሰራሁት የንጉሱ መስጊድ ተብሎ እንዲጠራ ስለነበር አሏህም ሳይቀበለው ቀረ»አለ።
በመቀጠልም ንጉሱ ተውባ አደረገ፤ የአሮጊቷ ስምም በመስጅዱ በር ላይ እንዲፃፍ ካደረገ በኃላ እስከ መጨረሻው እድሜዋ በድሎት ምትኖርበትን ገንዘብ ሰጦ ሸኛት።
<ማንኛውም መልካም ስራ ከአሏህ ዘንድ ተቀባይነት ሚያገኘው በኒያ ልክ ነው>
አሏህ መልካም ስራቸው ለሱ ከሆኑ ባሮች ያድርገን!
:¨·.·¨: ❀
`·. ሑሰይን የዐብደሪይ ወዳጅ
T.me/husseyn_y_abdery_wedaj
BY ሑሰይን የዐብደሪይ ወዳጅ - official
Share with your friend now:
tgoop.com/husseyn_y_abdery_wedaj/4007