Telegram Web
"የሰው ቁስል"

ሰው ልክ እንደራሱ - ለሌላው አንብቶ፣
ከልብ ሚያዝን ጠፋ - የሰው ቁስል አይቶ።
እንደ "ኢቢኤስ" ዓይነት - አዘናጊ ከፍቶ፣
አብዛኛው በእውሸት - ይዝናናል ቤት ገብቶ።
....
እያየ ከሚያለቅስ - ከሚቀር ውስጡ አሮ፣
አልሰማሁም ብሎ - ውድቀት ውስጡ ቀብሮ።
ሰላም ነው እያለ - ወጥቶ ቁርጥ ይቆርጣል፣
ወገኑ እያለቀ - ዝምታን ይመርጣል።
....
ሩቅ ያለው እሳት - ሲፋጅ እየሰማ፣
የብዙ ሰው ሕይወት - ሳለ እየቀማ።
ከሚኖርበት ቤት - ነገ ይደርሳል ብሎ፣
ማሰብ ሰው ተስኖት - ነገር አስተውሎ።
የወገኑን ስቃይ - በዝምታ ጥሎት፣
እራሱን ያጽናናል - ምን አገባህ ብሎት።
....
ባለበት ግቢ ውስጥ - እሳት ተቀጣጥሎ፣
እርሱ በዋናው ቤት - ተቀመጥኩኝ ብሎ።
በግቢው ዙሪያ ያሉት - ሰዎች በእሳቱ፣
ቤታቸው ተቃጥሎ - ሳሉ እየሞቱ።
አልደረሰም ብሎ - ካለሁበት ቦታ፣
እንዳልሰማ መስሎ - ሳይወርድ ከመኝታ።
እግር ኳስ እያየ - አልጋው ላይ ተጋድሞ፣
ጨዋታው አሳሰበው - ከወገኑ ቀድሞ።
....
የዘር የኃይማኖት - ሳጥን አበጅተው፣
በሚኖሩበት ቤት - እርስ በእርስ ተጣልተው።
የሚያስገርም ጊዜ - የሚያሳዝን መጥቷል፣
አማራ ለኦሮሞ - ማዘን ማልቀስ ትቷል።
ኦሮሞም እንዲሁ - አማራ ሲታረድ፣
በዝምታው ብቻ - ያቀብላል ሞረድ።
....
ትኩሱ ደም ሳይደርቅ - ሰሜን የፈሰሰው፣
የምዕራቡም ምድር - ልክፍቱ ደረሰው።
ይህን እርኩስ መንፈስ - የሚያስቆመው ጠፍቶ፣
ይበልጥ በጥላቻ - ተያያዘ ሰፍቶ።
ልክ እንደ ሰሜኑ - አቅልለው እያዩት፣
ህዝቡን በሞት ሜዳ - አጋልጠው አቆዩት።
....
የሰው ልጅን እልቂት - እንደ ማገዶ አይተው፣
ይቆማል እያሉ - መጠላላት ሲተው።
ባከማቹት በደል - በሠሩት ግፍና፣
በአጉል አስተሳሰብ - በአጉል ፍልስፍና።
ብሔራዊ ውርደት - አንቆ ሀገሪቷን
የአኬልዳማ መንፈስ - አፋጠነው ሞቷን።
....
ሁሉም ተሰብስቦ - በአንድነት ሱባኤ፣
መጸለይ ሲገባው - ለኢትዮጵያ ትንሣኤ።
ያም ይሄም የራሱን - አጀንዳውን ይዞ፣
መካሰስ ሲያበዛ - በእሳት ተያይዞ።
የጸጸት እሮሮ - አርጎን እስረኛ፣
እንዳንቀር ፈራሁ - ተበታትነን እኛ።

መወ
December 04, 2022
የዘንድሮ እግር ኳስ

የዘንድሮ ውድድር - እግር ኳስ ጨዋታ፣
ሳውዲ አርጀንቲናን - ጎብዞ ሲረታ።
ወዲያው ነው የገባኝ - ጊዜ ተገልብጦ፣
ጎበዝ የተባለው - ቦታው ተለውጦ።
ባልጠበቀው መንገድ - ጥበብ ተለይቶት፣
ያልታሰበ ቡድን - በጨዋታ ረትቶት።
አየሁ ተመለከትኩ - ጎበዝ የተባሉ፣
እንደሚሸነፉ - በጣም በቀላሉ።
.....
ጎበዝም ጠንክሮ - ሁልጊዜ ጎበዞ፣
ካልተገኘ ቦታው - ችሎታውን ይዞ።
አይቀርም በዝና - አንደኛ በመውጣት፣
ባላሰበው ቡድን - ያገኘዋል ቅጣት።
...
በሕይወትም እንዲህ ነው - ሁልጊዜ ጎብዘው፣
ካልተገኙ ሠርተው - በመሻል ተጉዘው።
ሰነፍ የተባለው - አንድ ቀን ጎብዞ፣
እራሱን ሲለውጥ - ማስተዋልን ይዞ።
ከፍ ብሎ ሲታይ - ሲደርስ ካሰበበት፣
ሰዎች ይሆናሉ - የሚገረሙበት።

መወ
December 09, 2022
እግር ኳስና ዓለም

ለመዝናናት ብዬ - የማየውን ነገር፣
የማሰስ ልምድ አለኝ - ያለውን ቁምነገር።
ለዚህ ነው እግር ኳስ - ጨዋታ አይቼ፣
ትርጉም የምሰጠው - በዚህ ዓለም ፈትቼ።
......
ሰዎች ተሰብስበው - የዓለም ዋንጫን አዩ፣
አሁን ተበታትነው - ሁሉም ተለያዩ።
የእኔ ግን ጥያቄ - በእያንዳንዱ ግጥሚያ፣
ባደረጉት ትግል - የጨዋታ ፍልሚያ።
ብዙ ይኖር ይሆን - እንደ እኔ ተዝናንቶ፣
ትምህርት ያገኘበት - በቅኔ ዓለም ፈቶ?
.....
ሰዎች ጨዋታ አዩ - እኔ ተማርኩበት፣
የትናንቱን ስህተት - ማረም የቻለበት።
ይችላል ሽንፈቱን - መለወጥ ለዋንጫ፣
እንደ አርጀንቲና ቡድን - አሳይቶ ብልጫ።
......
ቀረሁ ተሸንፌ - አበቃልኝ በቃ፣
በማለት አትቅር - በነጋታው ንቃ።
ችሎታህን አውጣው - ለውጥ ጨዋታህን፣
እንድታገኝ ኋላ - የድል አክሊልህን።
......
ሜሲ ሜሲ እያሉ - ይከራከሩኛል፣
እኔ በጨዋታው - የሠራው ማርኮኛል።
ተስፋ ባለመቁረጥ - ባደረገው ጉዞ፣
ተደስቶ ሳየው - የዓለም ዋንጫን ይዞ።
እሱ ነው የማረከኝ - ለካ የበረታ፣
እራሱን አግዝፎ - ይወጣል ጡረታ።
......
መወ
December 19, 2022
ሙስና ሲበረታታ

በሙስና ሳንጃ - ጀምረው ሊዋጉ፣
ተያይዘው መውደቅ - እንዳይመጣ ሰጉ።
የሁሉም አለቃ - መፍትሄ ነው ብሎ፣
በብልጽግና ሀሳብ - ሙስናን ወክሎ።
የልምምጥ ስሜት - በሚመስል ሁኔታ፣
ለሁሉ አቀረበ - ተስማሚ ገበታ።
የደበቃችሁትን - በግልጽ አውጥታችሁ፣
ዳቦ ስለሌ - ዶቦ ቤት ከፍታችሁ።
ሥራ የሌለውን - ሥራ ሰጥታችሁት፣
የሥራ አጡን ቁጥር - ከቀነሳችሁት።
እናንተና እኛ - አንፈላለግም፣
ሠርቆ ሚያሠራ እንጂ - ሚያሸሽ አንፈልግም።
....
ምንም የማያውቁት - እጅግ ተገረሙ፣
እነሱም ሊዘርፉ - ድፍረት ተሸከሙ።
በተራው ብልጽግና - የአባቱን እጅ ነካ፣
ብሶበት ወደቀ - አቅሙ ተለካ።
ልክ እንደ ወያኔ - ታሪክን ደገመ፣
ለሙስና ቱጃር - ማዕረግ ሸለመ።
በስልጣን ብልግና - ንብረትን ያፈራ፣
ባለሀብት ተብሎ - በክብር ተጠራ።
......
መፍረድ ሲገባቸው - ፍትህ እየሰጡ፣
መለማመጥ ያዙ - ስልጣን እንዳያጡ።

መወ
December 23, 2022
የስድብ ትምህርት

ስንጥርና ፊደል - አንዱንም ሳይዙ፣
ባሉበት ተቀምጠው - ሰምተው ሲታዘዙ።
በሉ የተባሉትን - ብለው በመጨረስ፣
ሁሉንም ሚረዱ - እስኪመስሉ ድረስ። 
ወያኔ የቀን ጅብ - ተብሎ ሲቀባ፣
ህዝቡ ተቀብሎት - ድምፁ አስተጋባ፣
ይህም ብዙ አልቆየም - ጁንታ ተከትሎ፣
አዲስ ስም ሆነና - የቀን ጅብን ጥሎ።
ጊዜ አልፈጀበትም - ተጉዞ በዜና፣
ጁንታ የሚለው ቃል - በህዝቡ ልቦና።
ቦታውን አገኘ - ባያውቁም ትርጉሙን፣
ወያኔን ለመስደብ - ተቀበሉ ስሙን።
ይህ የስድብ ዱላን - ሁሉም ሰው አወቀ፣
በወያኔ አናት ላይ - ከላይ ተለቀቀ።
ከዚህ ሁሉ ስድብ - ከዱላው አምልጦ፣
ወያኔ ግን ታየ - አብሮ ተቀምጦ።
...
አሁንም ድጋሚ - መጡና መምህሩ፣
ስድብ የመሰለ - ሌላ አስተማሩ፣
ይህም ቃል ይመስላል - ከስድብ የራቀ፣
ውስጠ ወይራ የሆነ - ህዝቡንም የናቀ።
የወያኔ ሩጫ - ለጊዜው ቢገታም፣
የኦሮሞ ሸኔ - ምንም ሥራ አልፈታም።
መምህሩ ግን ዛሬ - እያደናገሩ፣
የአማራ ሸኔ አለ - ብለው አስተማሩ።
እንግዲህ ይሄ ነው - የስድብ ተረኛ፣
የአማራ ሸኔ ያሉት - ማን ይሆን ጦረኛ?
የቤት ሥራ እኮ ነው - አንድነት እያሉ፣
ስድብን ማስተማር - ህዝቡን ሊያባሉ።
የእነሱ አሸቃባጭ - ስድብ ተከታዮች፣
እኛ ነን ሞኞቹ - የሚሉትን ባዮች።
....
ምንድነው ያገኘነው - ልባችን ተማርኮ?
የገደል ማሚቱ - ሆነን ቀረን እኮ።

መወ
December 26, 2022
ይድረስልን

የዙሪያችን እሳት - ብዙ ሰው ጨርሶ፣
መንደሩን ቀየውን - ሁሉንም አፍርሶ።
እየነደደ ነው - አልቆመም ግለቱ፣
ቅዱስ ገብርኤል - ደርሶ ቀዝቅዞ እሳቱ።
እንድንወጣ ያድርገን - አምላክ ካለንበት፣
በህይታችን ላይ - ታሪክን ይሥራበት።
..
አምላክን በማመን - ያደረግነው ጉዞ፣
ያምጣልን በዚህ ቀን - በረከትን ይዞ።
ቅዱስ ገብርኤል ዛሬ - አንተ የመጣኸው፣
እሳቱ ውስጥ ገብተህ - አብረህ የታየኸው።
የእነ አናንያንን ታሪክ - በእኛ ላይ ድገመው፣
በምትሠራው ሥራ - ሁሉን አስገርመው።
...
እንዴት ከእሳት ወጡ - ብለው ይደነቁ?
ዛሬ እንደ ድሮው - እንዳለህ ይወቁ።
ከመሞት አምልጠን - ስንተርፍ በሕወታችን፣
መበሳጨቱ አይቀር - ክፉ ጠላታችን።
እኛ ግን በዚህ ቀን - የጠላንንም ሰው፣
ማየት ስለምንሻ - ፍቅርን ሲቀምሰው።
በዚህ ቀን ስምህን - ስናስበው ጎልቶ፣
ፈጣሪ የእኛን ሀሳብ - በግልጽ ተመልክቶ።
ያውርድልን ሰላም - በቅተን ለንስሃ፣
አምላክ ከእኛ ጋር ሁን - አንተ ነህ የሕይወት ውሃ።

መወ
December 28, 2022
ሥራና ችሎታ

አላምን ብሎ እንጂ - መንግስት በእውነቱ፣
ውስጡ ያጎረው ቢታይ - ችሎታና እውቀቱ።
ባዶ ቀፎ ይበዛል - በልቡ አደርባይ፣
የሰዎች ስብስብ - ሁሉን አውቃለሁ ባይ።
ወንበር ሲያገኙ - ቦታውን ሲይዙት፣
በፍትህ አይደለም - ህዝቡን የሚገዙት።
ሰዉም በተማረው - ወይንም በችሎታው፣
ሲሠራ አይታይም - ጎሳው ነው ስጦታው።
ለዚህ ነው በብዛት - በገዛ ቤታችን፣
ባክኖ የሚቀረው - እምቁ አቅማችን።
....
አናጢው ጸሐፊ - ጸሐፊው ግንበኛ፣
ገበሬው ነጋዴ - ነጋዴው አንጥረኛ።
ያልተሰጣቸውን - ለመሆን ሲጥሩ፣
እንደ አባቶቻቸው - ታሪክን ሳይሠሩ።
ባላቸው ችሎታ - ጎበዝ በሆኑበት፣
ከመሬት ከፍ ሳይሉ - የትም ሳይበሩበት።
ትንሹም ትልቁም - በአቋራጭ ይጓዛል፣
ቁጭ ብሎ የሚበላው - ከአምራቹ ይበዛል።
ብዙ አፎች ይዘናል - ሁልጊዜ ክፍቶች፣
ጥቂት ሠሪ እጆች - የማይሞሉ ሆዶች።
ያጣነው ብልሃት ነው - መተማመን ይዘን፣
ክፍት አፍን ማዘጋት - የእውቀት ኃይልን መዘን።
ምንፈልገው ሰው ነው - ሁሉን አሠርቶ፣
ህዝቡን የሚያሳድግ - በእኩልነት መርቶ።

መወ
January 10, 2023
ተገለጠ

ህዝቡ ተደስቶ - ነፃነት አግኝቶ፣
መንገድ ሲለቁለት - በአንድነት ወጥቶ።
አምሮ ነው የታየው - በፈጸመው ተግባር፣
ከባለስልጣናት ነው - የጎደለው ምግባር።
.....
በቂ ምስክር ነው - ህዝቡ ካልተነካ፣
በዘረኝነት መንፈስ - ልቡ ካልተለካ።
ሁሉን ነገር ትቶ - ሁሉም በያለበት፣
በፍቅር ተባብሮ - ሠርቶ ካሳየበት።
መንግስት ለጥቅሙ - ጣልቃ ካልገባበት፣
ያለበትን ድርሻ - ማድረግ ከቻለበት።
ጥምቀት አሳይቷል - ህዝቡ እራሱን ችሎ፣
ማምለክ እንደሚችል - መብቱን ተቀብሎ።
...
ብናምንም ባናምንም - ኢትዮጵያ ያጣችው፣
ሰላም መሆን ስትችል - እንዲህ የተቀጣችው።
ከላይ ሰው አጥታ ነው - ህዝቡን ተመልክቶ፣
ወደፊት ሚመራት - በእኩልነት ዳኝቶ።
....
አሁን ግን ለጊዜው - በዓለም መድረክ ወጥቶ፣
የሚታይ ነውና - ጥምቀት በዓል ጎልቶ።
ለስማቸው ሲሉ - ይሆናል ዝም ያሉት፣
በዓሉ ሲያልፍ ነው - ሤራ ሚቀጥሉት።
ህዝቡም በመዘንጋት - የያዘውን ለቆ፣
ሲገኝ ነው ሚሞተው - በሤራቸው ወድቆ።
...
በጥምቀቱ መንፈስ - ሁላችን በንቃት፣
በአንድነት ካልታየን - ለፍሬ ለመብቃት።
አይቀር መሆናችን - የመንግስት መጫወቻ፣
እኛ የሚያዛልቀን - አብሮ መኖር ብቻ።
ስለዚህ ህዝቤ ሆይ - አጉላው ውበትህን፣
ከጥምቀትም አልፎ - አቆየው መብትህን።
ልክ እንደ ቤት መብራት - ሲያሰኘው አብርቶ፣
የሚያጠፋህ አትሁን - መንግስት አስፈራርቶ።
ብርሃንህን ሳትለቅ - የአንድነትህን ማማ፣
ኢትዮጵያን ዝቅ አድርግ - ሚሉህን አትስማ።

መወ
January 20, 2023
ዝምታ

 አይቶ እንዳላየ - ሰምቶ እንዳልሰማ
- ማለፍ በዝምታ፣
አቅሙ ብርቱ ነው - ድንጋይን ይበሳል
- እንደ ውሃ ጠብታ።
አይታይ ሲፈላ - ከውስጥ ሲንተከተክ - በሙቀት ታጅሎ፣
እንደ እሳተ ገሞራ - እስኪወጣ ድረስ
- መሬቱን ፈንቅሎ።
ያልተመቸ ሸክም - ያልተመቸ ግለት
- ያልተመቸ ጫና - የበዛበት ነገር፣
ከመጠኑ ሲያልፍ - በተለየ እርምጃ
- የበቃው መሆኑን - ማሳየቱም አይቀር።
ሰውም እንደዚህ ነው - ጫና ሲበዛበት - ዝምታውን ይዞ - አይቀር ተደብቆ፣
ፈንቅሎ በመውጣት - ያወርዳል ሸክሙን
- መብቱን አስጠብቆ።
ስለዚህ እናንተ - የሰዎች ዝምታን - ያልተረዳችሁት - ጫናን ምታበዙ፣
ዝምታ መልስ ነው - የተሰጠ ጊዜ
- ልብን እንድትገዙ።

መወ
January 28, 2023
ኢትዮጵያና ነነዌ

ጀምበር ስትገባ - መልሳ ስትወጣ፣
ለደቂቃም ቢሆን - እግዚአብሔር ሳይመጣ።
ያለፈ ቀን የለም - ያላስተማረበት፣
ችግሩ ከሰው ነው - ልቡ ደንድኖበት።
አሁን በዚህ ቀናት - እንባችን ታብሶ፣
ጌታ እንዲያሳየን - ሰላም ቤቷ ነግሶ።
ልክ እንደ ነነዌ ህዝብ - በያዝነው ምህላ፣
ተገፎ ለማየት - ያንዣበበው ጥላ።
አምላክ ተመልከታት - ኢትዮጵያን አስባት፣
አንተ ነህ እስከዛሬ - የጠበቅሃት አባት።
የመጣውን ክፋት - በኃይልህ አርቀው፣
ህዝብህ እንዲጸና - በአንድነት መርቀው።
የተጫነው ቀንበር - እንዲቀል ሸክሙ፣
ህዝብህ በምህረትህ - በአንተ እንዲታከሙ።
ከቤትህ መጥተዋል - ሲጠሩህ በጸሎት፣
ጥፋቱን ያርቀው - ዲያብሎስን ጥሎት።

አሜን!
መወ
Feb. 5, 2023
ምኒልክ

ምኒልክ ሳይጠራው - አድዋ የተገኘ፣
ማንም ጀግና የለም - በዝና የናኘ።

ምኒልክ ስምህን - ከአድዋ ነጥዬ፣
እንዴት አከብራለሁ - ድሉን የእኔ ብዬ?
አንተ ብትኖር ነው - አንተ ብትመራው፣
የአንድነት ኃይላችን - የድል ፍሬ ያፈራው።

ምኒልክ ተነስቶ - ባይመራው ቀስቅሶ፣
አይገኝም ነበር - ባልቻ አባ ነፍሶ።

ምኒልክን ትቶ - የአድዋን ድል ማንሳት፣
ከሃዲ መሆን ነው - ውለታውን መርሳት።

ምኒልክን ትቶ - የአድዋን ድል ማሰብ፣
እምዬን ዘንግቶ - ለመብላት መሰብሰብ፣
ሀቅን መቃወም ነው - ክህደትን መሰብሰብ።

መክብብ
የማይካዱ እውነታዎች

ምኒልክ ስምህን - ከአድዋ ነጥዬ፣
እንዴት አከብራለሁ - ድሉን የእኔ ብዬ?
አንተ ብትኖር ነው - አንተ ብትመራው፣
የአንድነት ኃይላችን - የድል ፍሬ ያፈራው።
........
ምኒልክ ተጽፏል - በማይጠፋ ቀለም፣
አድዋን የሚውጥ - የጥቁር ታሪክ የለም።
........
የሠራኸው ሥራ - ገዝፎ ሲታያቸው፣
እንዳንተ እምዬ - መባል ሲያቅታቸው።
ከመሬት ከፍ ብለው - ምንም ሳይታዩ፣
ስምህን በማጥፋት - መስሏቸው ሚቆዩ።
የአንተን ፎቶ አንስተው - የእነሱን በማድረግ፣
ታሪክ አይፍቀውም - የምንሊክን ማዕረግ።
.........
ጊዜ ያነሳው ሰው - ትናንትን አስታውሶ፣
ቢቀጣ በዳዩን - ልቡ ቂምን ለብሶ።
መሆኑን ያሳያል - የሌለው ችሎታ፣
መያዝ ማይገባው - ከፍ ያለውን ቦታ።
............
ባለው አቅም ጠንክሮ - ሠርቶ እንደማሳየት፣
ሰነፍ ከጎበዝ ጋር - አይችልም መቆየት። 
ሁልጊዜ ሰነፍ ሰው - ለራሱ ሲፈራ፣
ይጥራል ሊደብቅ - የጎበዙን ሥራ።
.........
ጎበዝ ሰው ምንጊዜም - ሠርቶ እያሳየ፣
በችሎታው ልቆ - ሆኖ የተለየ።
ሀገርና ስሙን - ከፍ አድርጎ ያስጠራል፣
ሰነፍ ግን ሁልጊዜ - በማፍረስ ይቀብራል።
..........
ከታች ሆነው አልቅሰው - ከላይ ሆነው አልቅሰው፣
መኖር ከሚያምራቸው - ያለፈውን ወቅሰው።
ለምን ያላቸውን - ችሎታ በማውጣት፣
ተሽለው አይገኙም - ሰላምን በማምጣት?
..........
የያዘውን ትቶ - ህፃን ሌላ ያነሳል፣
የእኔ ነው እያለ - በሰው ዕቃ ያለቅሳል።
አዋቂ ሰው አየን - በቂ ማዕረግ ይዞ፣
ጀግና በሉኝ የሚል - ታሪክ አደብዝዞ።
..........
ሰውን አታታልል - በሰው ዝና አትቅና፣
ያልሆንከውን ሆነህ - አትጠብቅ እውቅና።
እንደ እምዬ ደምቀህ - ከፍ ብለህ እንድትታይ፣
ጀግና ነኝ የምትል - ጀግና ሆነህ አሳይ።
..........

መክብብ
February 28, 2023
የምኒልክ ሀቆች


ቅዳሴ ያለአሀዱ - ተቀድሶ አያውቅም፣
አድዋ ያለምኒልክ - በዓሉ አይደምቅም።
...........
እምዬ ተብሎ - እስከ ዛሬ ይጠራል፣
ምኒልክን ማንሳት - ባንዳ ብቻ ይፈራል። 
...........
ህዝቡን አንድ አድራጊ - እምዬን እርቀው፣
መደመር ይላሉ - በማካፈል ወድቀው።
............
አንድ የሚያደርጉንን - ነገሮች በመጥላት፣
የወደዱን መስለው - ሚሆኑብን ጠላት።
በሩቅም በቅርብም - አሉ ይገኛሉ፣
ሁሌ የኛን ውድቀት - ከልብ ይመኛሉ።
እኛ ግን ምንጊዜም - ከሰው ተለይተን፣
እንገኝ ከፍ ብለን - ወደ አድዋ ዘምተን።
............
አድዋ ታሪክ ነው - ለጥቁሮች ሲሳይ፣
በምስራቅ የወጣ - የነፃነት ፀሐይ።
ጥቁር ሕዝብ በሙሉ - ወጥቶ ይሞቀዋል፣
ምኒልክ በዓሉን - ይበልጥ ያደምቀዋል።
............
ምኒልክ ባለበት - ጣይቱም ተገኝታ፣
ጣልያንን ጉድ ሠራች - በጥበብ አሞኝታ።
ወንዶች ከምኒልክ - ሴቶች ከጣይቱ - ሚማሩትን ይዘው፣
ሊታዩ ይገባል - ውድ እናታቸውን - ለማንሳት ጎብዘው።
...........
የካቲት ሃያ ሶስት - ጣልያን ወደቀ፣
በአድዋ ጦርነት - ነፃነት ደመቀ።
ሁሌ በየዓመቱ - እኛ በሀገራችን፣
የድል ቀን አረግነው - በማክበር ሁላችን።
............
ብዙ ዓይነት በዓሎች - ሲከበሩ አይቼ፣
ብፈልግ አድዋን - ውጭ ሀገር ቆይቼ።
አጣሁ እንደ አድዋ - በጥቁር የተመራ፣
ድል አድራጊ ሆኖ - ታሪክን የሠራ።
.............
እናንተ ውብ ሴቶች - የማህፀናችሁን ፍሬ፣
በምጥ ስትወልዱ - ወንድ ልጅን ዛሬ።
እስቲ ምኒልክን - በስሙ አባዙት፣
የጠላትን ደባ - ሤራውን ሠርዙት።
.............
አውራ የሌላቸው - ንቦችን ማን አውቆ?
አድዋ ያለምኒልክ - አይታይም ደምቆ።
............
የምኒልክ ፀጋ - በባንዳ ተጋርዶ፣
ፍጹም አይታይም - ከከፍታው ወርዶ።
በእሱ ልክ ለመቆም - እምዬ ለመባል፣
እንደ እሱ አመራር - ማሳየት ይገባል።
...........

መክብብ

March 1, 2023
የእኛ ነገር

ተስፋ የማጣት ስሜት - ከውስጥ ተደብቆ፣
ሰው አታሎ እራሱን - አንዱ በአንዱ ስቆ።
በሱሶች መደበቅ - አድርጎት ምርጥ ዋሻ፣
ለጊዜው ፈልጎ - እውነትን መሸሻ።
ወጣት ሽማግሌው - ነፍስ ያወቀ ሁሉ፣
የሚያስለቅስ በዝቶ - የግድ ይስቃሉ።
እኔ ግን እላለሁ - ማስመሰሉን ትተን፣
ለነገ እንሳቅ - ለእውነት ዛሬ አንብተን።
ኧረ ሰዎች በቃን - በእውሸት እየሳቅን፣
አለን እኮ እያልን - ቀስ በቀስ አለቅን።

መክብብ

March 12, 2023
የጥፋት ቅስቀሳ

ምንድነው እኛ ላይ - ያልተሞከረብን?
ምን ዓይነት ድንጋይ ነው - እኛ ያልተጫነብን?
መቼ ነው ያቆሙት - ድሃውን ከመግደል?
ማንን ነው ያላገኘው - የሚሠሩት በደል?
አይተን ማናውቀው ግፍ - እንደ ዝናብ ወርዶ፣
ሀገር አበስብሶ - መሬቱም ደም ለምዶ። 
ወጥተው በቀሩበት - አፈር የለበሱት፣
በማንነታቸው - ሞትን የቀመሱት።
ይመስክሩ እነሱ - ባሳለፉት ስቃይ፣
ማን ደረሰላቸው - በመሆን ተበቃይ?
ሁሉም ተረድቶታል - በሁሉም አቅጣጫ፣
ጥፋት ቅስቀሳ ነው - የሚታየው ሩጫ።
እንደውም ይመስላል - እኛን ማበላላት፣
ትልቅ ሕልማቸው ነው - መፍጠር ብዙ ጠላት።
እኛ ግን ምንጊዜም - በእግዚአብሔር ኃይል ችለን፣
እየሞትን አለን - አንባላም ብለን።
.....
ለእኛ የሚያቅዱት - ሳይሳካ ቀርቶ፣
በእነሱ ላይ ይበልጥ - መበላላት ሠርቶ።
እንደ ዛፍ ገዝግዞ - ሲጥላቸው ማየት፣
አይቀርም ይታያል - ደግ ነው መቆየት።

መክብብ
Apeil 2, 2023
መርዘኞች

ገድለውን - ሚያለቅሱ፣
የአዞ እንባ - ሚያፈሱ።
ስንሠራ - ሚያሾፉ፣
ስንደኸይ - ሚያተርፉ።
ስንወድቅ - ሚደሰቱ፣
ሲያመን - የሚስቁ፣
ስንሞት - ሚቦርቁ።
አብረው - እየሳቁ፣
ተንኮል -  የሚጠምቁ።
በቤትህ - ነግሰዋል፣
ከትናንትናው ጅብ - እነዚህ ብሰዋል።

መክብብ
April 22, 2023
የሾምካቸው

ነግሬህ ነበረ - ባለማዳመጥህ፣
 ያጎረስከው ነክሶህ - ጥላቻ ሲሰጥህ።
እኔ አልገረመኝም - አንተ ግን ገርሞሃል፣
አምኖ ለመቀበል - አሁንም ከብዶሃል።
ተግባባሁት ያልከው - ከልቤ ቀረብኩት፣
ታማኝ ሰው አይደለም - አትመነው ያልኩት።
አንተ ግን አምነኸው - አቅፈህ ስታስጠጋው፣
ከጀርባህም አልፎ - ልብህን ሲወጋው።
እያቃሰትክ ሳለ - ጣርህን ሰምቼ፣
ለመድረስ ብሞክር - ከቤትህ መጥቼ።
ወዳጅ ያደረግኸው - የጣለህ ሰው ሰግቶ፣
ጠበቀው ሠፈርህን - መግቢያውን ዘጋግቶ።
አንተም የጊዜውን - እንጀራህን በልተህ፣
ለመኖር ስትሞክር - ለራስህ በርትተህ።
ለምንድነው እንዲህ - በቅናት በማበድ፣
እረፍት ማያገኙት - አንተን በማሳደድ?
መቼ ነው በታሪክ - በእውቀት ጎብዘው፣
ሚጠሉህ ሚነሱት - አዋቂነት ይዘው?
ቤቴ ሞልቷል ካሉ - ታታሪ ገበሬ፣
ለምን አይቀይሩም - ወሬን ወደ ፍሬ።
ምንም ግልጽ አይደለም - በፍጹም ጥላቻ፣
ሁልጊዜ በማንሳት - የትግል ዘመቻ።
ዛሬም ይወዳሉ - ህዝብን አሸብረው፣
አላዋቂ መሆን - አዋቂውን ቀብረው።
ስለዚህ አትሞኝ - አባብለው ሚያስጠጉ፣
ወዳጅ ሰው በመምሰል - ጀርባህን ሚወጉ።
"ማኪቬሌዎቹ" - ቤትህን ስለሞሉት፣
እውነት ስታወራ - አንተን ነው ሚጠሉት።
በሀሳብ ተሟግተው - ስልጣንን ከመያዝ፣
ማንሳት ይወዳሉ - አንገት ሚቆርጥ መጋዝ።
እንዲህ ዓይነቶች ናቸው - በሱፍ ተሸፋፍነው፣
ቅኖች የሚመስሉት - ሰውን አራጅ ሆነው።

መክብብ
April 26, 2023
በጣም የሚመች ጓደኛዬ ያካፈለችኝ ግጥም 

ደጉም አላማረ - መከራችን ላቀ፣
ከልማቱ ይልቅ - ሞታችን ደመቀ፣
ተመስገን እያለ - አማራው አለቀ።
ስንቶቻችን ይህን ግጥም እናስታውሳለን? ድራማው ቀድሞ በግጥም በመነገሩ ካመነው ይልቅ ያላመነው ነበር የበዛው።


አብይና ጸዲ

አንድ ዓይነት ባይሆንም - ለእኛ የሚያወሩት፣
ሲደዋወሉ ነው - ግልጹን ሚናገሩት።
እኛጋ ባይደርስም - በድንገት ተጠልፎ፣
አገኘን ወሬውን - በግጥም ተጽፎ።

ጸዲ ተማጸነ - አብይን ፈልጎ፣
ከኢትዮጵያ ጣቢያ - ደብቆ ሸሽጎ።
የላከው ደብዳቤ - ተሽሎ ካለፈው፣
ለስለስ አድርጎ ነው - መልዕክቱን የጻፈው።
እስቲ ላካፍላችሁ - የተባባሉትን፣
ድንገት ተልኮልኝ - እኔ ያነበብኩትን።

ጸዲ፡  አይበቃም ወይ ዱላው - እየተዋወቅን?
         ለሁለት ተያይዘን - በትግል አለቅን።

አብይ፡ ቆየ ከነገርኩህ - እጅህን ስጥና፣
          መቃወምን አቁም - የእኔን ብልጽግና።

ጸዲ፡   የአንተ ብልጽግና - ሥልጣኔን ወስዶታል፣
          ህገ መንግስቱን ግን - አለቅም ብሎታል።
                  
አብይ፡  ሥልጣን በቃኝ ብላ - ወደ እኔ መጥታለች፣
           አታያትም በቃ - ከእጅህ አምልጣለች።
           የያዝኩት አጥብቄ - ከወያኔ ወስጄ፤
           ህገ መንግስቱን ነው - ማየው እንደ ልጄ።
           በእሱ የተነሳ ነው - እዚህ የደረስኩት፣
           እኔም ተራዬ ነው - መፍታት እንደቻልኩት።

ጸዲ፡    እኛው አሳድገን - በገዛ ቤታችን፣
           ተወረሰ በአንተ - ሁሉ ንብረታችን።
           አንተን ለማስወጣት - ከቤታችን ቶሎ፣
            አይቀር እንመጣለን - እዛው አራት ኪሎ።

አብይ፡  ሞክራችሁ ነበር - ደርሳችሁ ደርሳችሁ፣
            ቡና ሳትጠጡ - ምንድን መለሳችሁ?
            እንደው በድጋሚ - ከምትለፉ ብዬ፣
            መጣሁ ወደ እናንተ - ጦሬን አስከትዬ።
            በሰላም አስገቡኝ - ብዬ ስነግራችሁ፣
            አራት ዓመት ሞላኝ - እምቢ እንዳላችሁ።
            በቀረበ እርቀት - መቀሌ ይታየኛል፣
            እዛ መደበቂያ - ዋሻ የት ያገኛል?

ጸዲ፡      "አወይ አንተ ግደፍ" - ልቤን አታስቆጣ፣
             ከተደበቅኹበት - ወጥቼ እንዳልመጣ።

አብይ፡    ከተደበቀበት - ጸዲን ወጥቶ ካየሁ፣
             እኔ በበኩሌ - እጅግ በጣም ቆየሁ።
             ይልቅ እጅህን ስጥ - አቁም ጦርነቱን፣
             በቃን ማለት እወቅ - ተቀበል ሽንፈቱን።

ጸዲ፡      ቦታ ካላገኘን - ካልተጋራን ሥልጣን፣
             እንታገላለን - ናና አንተ አስወጣን።
             
አብይ፡    አይቀርም ይሆናል - ወንበሬን የሚሻ፣
             እኔ አሳጣዋለሁ - መግቢያና መድረሻ።
             በአንተ ካላሳየሁ - ሌላው አንተን አይቶ፣
             ይኮርጅ ይሆናል - ትዕቢትህን ቆይቶ።

ጸዲ፡      ዝም ያልካቸው ሰዎች - የተማሩት ከእኔ፣
             ይባሉ አይደለም ወይ - ዛሬ ኦነግ ሸኔ።
             
አብይ፡    ከሃዲዎች ናቸው - አይቀርም ለእነሱ፣
             ምቀጣበት በትር - በፍጥነት መድረሱ።

ጸዲ፡      እሱን እንኳን ተወው - በእነሱ ጭፍጨፋ፣
             የስንቱ አማራ - ምስኪን ሕይወት ጠፋ።

አብይ፡    አስመሳይ ነህ አንተ - አማራን ገለኸው፣
             ሌላ ታወራለህ - የአንተን ሸፍነኸው።

ጸዲ፡     ሁለታችንም ነን - አማራን ምንጠላው፣
            ሥልጣን እንዳይቀማን - ቀድመን የምንበላው።
            አንተም ልክ እንደ እኛ - አማራን ጥለሃል፣
            ባስተማርንህ መንገድ - ማስወገድ ይዘሃል።

እየተባባሉ - ክርክር ቢያበዙም፣
መፍትሄ የሚሆን - ምንም ፈርጥ አልያዙም።
በአማራ የተነሳ - ምስጢር ሳያወጡ፣
ከመገናኛቸው - ከመስመሩ ወጡ።

መክብብ
September 27, 2022            
2024/10/09 04:35:12
Back to Top
HTML Embed Code: