Telegram Web
#ትጾማለህን?
#በቅዱስ #ዮሐንስ #አፈወርቅ


ትጾማለህን? እንግዲያውስ በሥራህ አረጋግጥልኝ!
በምን ዓይነት ሥራ ካልከኝ?
*ደሃውን ካየህ እዘንለት (ቸርነትን አድርግለት)!
*የተጣላኸውን ካየህ ታረቀው!
*ጓደኛህ ክብርን ሲያገኝ ካየህ አትቅናበት!
*መልከኛ ሴት ካየህ እለፋት!
*አፍህ ብቻ ከምግብ አይከልከል፤ አይንህም፣ ጆሮህም፣ እግርህም፣ እጆችህም፣ ሁሉም የሰውነትህ ክፍሎች ይጹሙ።
እጆችህ ከንጥቂያና ስግብግብነት (ንፉግነት) ይጹሙ። እግሮችህ የማይገቡ ትእይንቶችን ለመመልከት ከመንደርደር ይጹሙ። አይኖችህ ውብ መልኮች ላይ ያልተገቡ እይታዎችን መቼም መች ከማሳረፍ መከልከልን ይማሩ እና ቁንጅና ላይ ከመጠመድ ይጹሙ። ማየት ለዐይን ምግብ ስለሆነ ያልተገባ እና የተከለከለን እይታ ካደረግህ ጾምህን ያፈርሰዋል፣ የነፍስህንም ሙሉ ደህንነት ያነዋውጣል፤ ነገር ግን የተገባና ጥንቁቅ ከሆነ ጾምህን ያስጌጣታል። የተከለከለውን በዓይን እየነካህ ነገር ግን በጾም ምክንያት ከማያረክስ ምግብ መጾሙ ከንቱ ከሆኑ ነገሮች መካከል ይቆጠራል። ሥጋን አትበላም አይደል? ስለዚህ በዐይኖችህ አማካኝነት ፍትወትን አትመገብ። ጆሮም ይጹም። የጆሮ ጾም ክፉ ወሬን እና ሐሜትን አለመቀበልን ያካትታል። “ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል” እንዲል። (ዘጸ. 23፥1) አፍም እንዲሁ ከመጥፎ እና ከጥላቻ ንግግሮች ይጹም። ከአዕዋፋትና አሳዎች ብንከለከል ነገር ግን ወንድማችንን ብንበላው ምን ይጠቅመናል? ክፉ ተናጋሪ የወንድሙን ሥጋ ይበላል የባልንጀራውንም ሰውነት ይነክሳልና።

ምንጭ፦
St. John Chrysostom; The Homilies on the Statues to the People of Antioch, Homily lll: 11-12, NPNF Series 1 Volume 9, Page 359/503

ትርጉም፦
መ/ር እሱእንዳለ ሽመልስ
@memhrochachn
"አልጠቅምም አትበል"

ስለ ሌሎች መዳን ከማይጨነቅ ክርስቲያን በላይ ሰነፍ ሰው የለም፡፡ ወዳጄ “እኔ ድኻ ነኝና ይህን ማድረግ አልችልም” የምትል አትኹን፤ ባለ ኹለት ዲናሯ ሴት ትወቅስሃለችና፡፡ ዳግመኛም “ወርቅም ብርም የለኝም” ብሎ የተናገረ ጴጥሮስ ይወቅሰሃልና፡፡

"ምናምንቴ ነኝ" አትበል፤ እንዲህ ስትል ምናምንቴዎቹ ሐዋርያት እንዳይሰሙህ! "እኔ በሽተኛ ነኝ" አትበል፤ በሽተኛው ጢሞቲዎስ ይታዘብሃልና፡፡ ፈጽመህ “እኔ ሌሎች ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማምጣት አይሆንልኝም” አትበል፡፡ በእውነት ክርስቲያን ከኾንክ ይህን ከማድረግ ይልቅ አለማድረጉ ይከብዳልና፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ እንድትኾን አድርጎ ፈጥሮሃልና ተፈጥሮህን መካድ አይቻልህም፡፡ ክርስቲያን በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ወንድሞቹ ብርሃኑን ከሚከለክል ይልቅ ፀሐይ ብርሃኗን ብትከለክል ይቀላልና ስለዚህ አልጠቅምም አትበል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
@memhrochachn
ተወዳጅ ሆይ! ክርስቶስ ኢየሱስ እንዲህ ይልሃል፦

✟ አንተ ግን ለድኾች ምጽዋትን ትሰጣለህ፤ እኔም እጄን ዘርግቼ ካንተ እቀበላለሁ፡፡
✟ የታረዙትን በምታለብሳቸው ጊዜ እኔን ታለብሰኛለህ፡፡
✟ የታሰሩትን በምታረጋጋቸው ጊዜ በመካከላቸው ኾኜ በዚያ ታገኘኛለህ፡፡
✟ በሽተኛውንም በምትጎበኘው ጊዜ ከእርሱ ጋር በአልጋው ላይ ኾኜ ዳግመኛ ታገኘኛለህ፡፡
✟ በቦታው ኹሉ የራቅሁ አይደለሁም፡፡ ትእዛዜን በምትፈጽምበት ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር እኖራለሁና ችግረኞችን የምረዳቸው እኔ ነኝና፤ ለድኾች የምታደርገው ኹሉ ለእኔ ማድረግህ ነው፡፡ እኔም በእርሱ ፈንታ በጎ ዋጋ እከፍልሃለሁና፡፡
✟ በቤትህ ውስጥ እንግዳ በአሳደርክ ጊዜ እነሆ ከእንግዳው ጋር በማደሪያህ አስገባኸኝ፡፡
✟ እንደዚህ ለሚያደርግ ቁጣዬ ከእርሱ ይርቃል፤ ወደ ሕይወት ወደብም አደርሰዋለሁ፡፡ ከክፉ ነገር ኹሉ እጠብቀዋለሁ፡፡ እባርከዋለሁ፡፡ ዘሩንም አበዛለሁ፡፡ ዋጋውንም በሰማይ ባለው በአባቴ ዘንድ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡ ዘለዓለማዊ ዕረፍትንም እሰጠዋለሁ፡፡"

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
@memhrochachn
"ቁጡ ሰው ከመኾን ገር ሰው ወደ መኾን ከተለወጥህ፣ ጨካኝ ሰው ከመኾን ቸር ሰው ወደ መኾን ከተቀየርህ [በተግባር] አሳየኝ እንጂ 'ለአያሌ ቀናት ጾምሁ፤ ይህን ወይም ያን አልበላሁም፤ ወይን አልቀመስሁም፤ መሻቴን ገትቻለሁ' እያልህ አትንገረኝ፡፡ [እስከ አሁን] ቁጣን የተሞላህ ከኾነ ለምን ሥጋህን ታስጨንቃለህ? ቂምና በቀል በልቡናህ ውስጥ ካሉ፥ [ወይንን ሳይኾን] ውኃ የምትጠጣው ለምንድን ነው? ረብ ጥቅም የሌለውን ጾም አትጹም፤ ጾም ብቻዋን ወደ ላይ አታርግምና፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
@memhrochachn
" አጋንትን የሚያስጮኹ ሰዎች🤔"

በዘመናችን አጋንትን እናስወጣለን የሚሉ ስዎች ግን ምን አስበው ነው የሰይጣንን ምስክርነት ከሰይጣን እየጠየቁ የሚነግሩን የሰይጣንን ምስክርነት አመነን እንድንቀበል ነውን ሰይጣንን ዝም ብለው ማስወጣት ሲገባ ሰይጣንን እየጠየቁ ማድጮኽ ምን የሚሉት ነው ለሠይጣንን ሥራውን እያገዙት ይኾን እንዴ😁😁😁
እንዴት ያዝከው የት አገኘኸው እያሉ እየጠይቁ የሰይጣንን ጩኸት እና ከአጋንት ጋር ተባባሪ ሊያደርጉን ፈልገው ነውን 🤔
ሰይጣን ምስክርነቱ ሀሰት እንደው አየታወቀ መጠየቅ ለምን አስፈለገው
ነገሩ አብረው ካልሠሩ ሠይጣኑ ወጣው ብሎ አይጮኽም መሰል በሕብረት እንደሚሠሩ እየነገሩን አይመስላችሁም😁
ለማንኛው አንድ ወንድሜ የጻፋትን ላካፍላችኹ


📖 "ኢየሱስም ዝም በል ከርሱ ውጣ ብሎ ገሰፀው::" ማር 1:25

➡️ ወንጌላዊው እንደገለጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅፍር ናሆም (የናሆም መንደር) ወረደ፡፡ በቅፍርናሆምም በክፉ መንፈስ የተያዘ ሰውን አገኘ፡፡ ከርሱም ክፉውን መንፈስ አወጣለት፡፡ "ቅፍርናሆም" የቃሉ ትርጉም "የመጽናናት ቦታ" ማለት ነው፡፡ ጌታም ወደዚያ በገባ ጊዜ ቅፍርናሆም በእውነትም የመጽናናት ቦታ ሆነች በዚያ ከክፉ መንፈስ ሰዎችን አድኖበታልና፡፡ ርኩስ መንፈስ ያለበት ሰው "ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደሆንህ አውቄያለሁ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ፡፡" ማር 1:24 በዚህን ጊዜ ክርስቶስ "ዝም ብለህ ከእርሱ ውጣ፡፡" በማለት ገስፆታል፡፡ በዚህም ሐብተ ፈውስ ተሰጥቷቸው አጋንንትን ለሚያወጡ ሰዎች ፍኖቱን ይከተሉ ዘንድ አብነት ሆኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያንም አጋንንትን ማስለፍለፍ የሚፈቀድ አይደለም፡፡ የአጋንንትአባት ምስክርነታቸውም ተቀባይነት የለውም፡፡ ዲያብሎስ ተንኮልን የተሞላ ሐሰተኛ የሐሰት ነው፡፡ ዮሐ 8:44
ስለዚህ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች አስተምረውበታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል:- "አጋንንት እንኳ የእግዚአብሔርን ስም ይጠራሉ፡፡ ነገር ግን አጋንንት ከመሆን አይለወጡም፡፡ ጌታም እነርሱን ይገስፃቸውና ያስወጣቸው ነበር፡፡ እኔም ይህን ክፉ ነገር ታስወግዱ ዘንድ እለምናችኀለሁ፡፡ ይሀውም የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ነው፡፡" በማለት በከንቱ ስሙን መጥራት ከአጋንንት ጋር እንደ መተባበር መሆኑን ይገልፃል፡፡ በሌላም ክፍል ሊቁ እንዲህ ብሏል፦ "እውነት በርኩሳን መናፍስት ምስክርነት አይመካም፡፡ አጋንንትን እውነትን ቢናገሩ እንኳ ማመን አይገባም፡፡" ብሏል፡፡ ምክንያቱም ጨለማ በብርሃን ይገለጣል እንጂ ብርሃን በጨለማ አይገለጥምና፡፡ "ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?" 2ኛ ቆሮ 6:14 እንዳለ ሐዋርያው፡፡ የአጋንንትን ምስክርነት ስንመለከት ተንኮል የተመላበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጌታ በጌርጌሴኖን ተገኝቶ ሌጌዎን አጋንንት ያደረበትን ሰው ከተገናኘው በኋላ አጋንንቱ "ታወጣንስ እንደሆነ ወደ እርያ መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት፡፡ ሂዱም አላቸው፡፡" ማቴ 8:31 ወደ እርያዎቹም ሄዱ እርያዎቹም ሞቱ፡፡ በዚህም ጊዜ ሕዝቡ ከከተማው እንዲሄድላቸው ለመኑት፡፡ በእርያዎቹ እንዲህ ካደረገ የኛን ኃጠአታችንንማ ምንኛ ቆጥሮ ይፈርድብን ይሆን ብለው ከከተማው እንዲሄድ ለመኑት፡፡ የአጋንንትን ክፉ ስራ አስተዋላችሁን? ጌታችን የአጋንንትን ተንኮል ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም ይልቁኑ ትምህርት ሊሰጠን እንጂ፡፡ ለዚህም ነው ጌታ ከሰዎች ርኩስ መንፈስን ሲያወጣ "ዝም ብለህ ውጣ" ብሎ የተናገረው፡፡ የአጋንንት ምስክርነት ተቀባይነት የለውም፡፡

◾️ሊቁ አውግስጢኖስም እንዲህ ይላል፦ " 'የእግዚአብሔር ልጅ' ተብሎ በቅዱስ ጴጥሮስ የተጠራው (ማቴ 16:16) በአጋንንትም ተጠርቷል፡፡ ( ማቴ 8:29፤ ማር1:24) ቃላቱ ተመሳሳይ ቢሆንም ሃሳባቸው ግን ልዩ ነው፡፡ ...የክርስቲያን እምነት መሠረት ማድረግ ያለበት ፍቅር ላይ ነው፡፡ አጋንንት ግን ከፍቅር የተራቆቱ (የራቁ) ናቸው፡፡ ጴጥሮስ 'የእግዚአብሔር ልጅ' ያለው በፍቅር የሆነ እምነቱን ሲገልጥ ነው አጋንንት ግን ይጠሩት የነበረው ክርስቶስ እንዲተዋቸው ነው፡፡" ሊቁ ይቀጥልና
" 'አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል' ያዕ 2:19:: እምነት ኃይል አለው ያለ ፍቅር ግን ትርጉም የለውም፡፡ አጋንንት ስለ ክርስቶስ መስክረዋል ምስክርነታቸው ግን ያለ ፍቅር በእምነት ብቻ ነው፡፡... ስለዚህ ፍቅር የሌለበት እንደ አጋንንት የሆነ እምነት ከያዝን በዚህ ልንኮራ አይገባም፡፡"

@memhrochachn
በስመአብ ወ ወልድ ወ መንፈስቅዱስ ፩ አምላክ አሜን
ክርስቶስ ተንስዐ እሙታን
በዐብይ ኃይል ወስልጣን
አሰሮ ለሰይጣን
አግአዞ ለአዳም
ሰላም
እም እዝየሰ
ኮነ
ፍስሀ ወ ሰላም
"ከሲዖል እጅ እታደጋቸዋለሁ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ ሞትሆይ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሞትሆይ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርህራሄ ከዓይኔ ተሰወረች" ሆሴ ፲፫፡፲፬

"እንደተናገረ ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም" ማቴ ፳፰ እስከ ፍፃሜው ይነበብ

"እርሱ ግን አትደንግጡ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ ተነስቶአል በዚህ የለም" ማር ፲፮ እስከ ፍፃሜው ይነበብ

"ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ እንዲህ አሉአቸው ሕያውን ከሙታን ስለምን ትፈልጋላችሁ? ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም" ሉቃ ፳፬ እስከ ፍፃሜው ይነበብ

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርት ውድስት ቅድስት በዓለ ትንሳዔው በሰላም በጤና አደረሳችሁ አደረሰን

"ለመስቀልከ ንሰግድ ወለ ትንሳዔከ ቅድስት ንሴብህ ኩልነ ይእዜኒ ወዘልፈኒ"

ጌታዬ ሆይ ክቡር የሚሆን የመቃብርህ ጠባቂዎች ከድንጋፄ የተነሳ የትንሳዔህ ግርማ የገለባበጣቸው በሦሥተኛው ቀን ከሙታን ተለይተህ ለተነሳኽው ትንሳዔህ ሰላምታ ይገባል" (መልክዐ ኢየሱስ ለትንሳዔከ ቀዳማይ)

"ስለፍፁም ሃይማኖት በክብር ለሞቱ ቅዱሳን ሁሉ የትንሳዔያቸው መተማመኛ ለሆነው ትንሳዔህ ሰላምታ ይገባል"(መልክዐ ኢየሱስ ለትንሳዔከ ካልዕ)

"በአርብ ሙታን እና ህያዋን በድኅነታቸው ተደሰቱ በእኁድ ደግሞ በህይወት ያሉ አረጋገጡ እናም ትንሳዔያቸው በክርስቶስ ስጋ እንደሆነ አወቁ" (የኮፕቲክ ቤተክርስቲያ የመጋቢት፳፱ ስንክሳር )

"በእውነት እኛ ኦርቶዶክሳውያን የዘመናት ንጉስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ ብለን እናምናለን ከእኛ ንጉስ አማኑኤል ከሞት መነሳት በኋላ ሁሉን ደስታ እና ሀሴት እግዚአብሔር"(የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን የበዓለ ሃምሳ የሌሊት ምስጋንና)

"የእኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እና ጥበቡን እኛ ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ ብለን እናመሰግነዋለን እናም እሱ እንደተናገረው ነብያትም እንደተናገሩት በመቃብር ተቀበረ ከሦስት ቀንም በኋላ ተነሳ" (የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን የበዓለ ሃምሳ የሌሊት ምስጋና)

"የደስታ እናት ድንግል ማርያም ተደሰቺ በእውነት ያንቺ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቷልና ዛሬ ሁላችን እንደሰት ደስተኛም እንሁን ምክንያቱም የንጉሦች ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቷልና"(የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን የበዓለ ሃምሳ የሌሊት ምስጋና)

"ጥበበኛው ሉቃስ እና ተወዳጁ ዮሐንስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቷልና በእውነቱ ወንጌልን ስበኩ ክርስቶስ ሆይ የማጠልቅ ፀሀይ ሆይ ና እኛም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቷል ብለን እናመስግንህ"(የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን የበዓለ ሃምሳ የሌሊት ምስጋና)

" ሞት በሞት ተያዘ ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ እሱ በመቃብር ሆኖ ህይወትን ሰጠ"(የምስራቅ ኦርቶዶክሳውያን ስንክሳር የፋሲካ ስንክሳር)

"ይሄ የትንሳዔ ቀን ነው ሁላችንም በበዓሉ እናብራ(እንድመቅ) ሁላችንም እርስ በእርስ እንተቃቀፍ ሁላችንም የጠላነውንም ቢሆን እንኳ በትንሳዔው ይቅር እንበል ወንድሞቼ ተባብለንምእንጠራራ"(የምስራቅ ኦርቶዶክሳውያን ስንክሳር የፋሲካ ስንክሳር)

"ሞትሆይ መያዝህ የትአለ? መቃብር ሆይ ድል መንሳትህ የትአለ? ክርስቶስ ሲነሳ እና ሲነግስ ከስልጣንህ ተሻርክ፣ክርስቶስ ሲነሳ አጋንንት ወደቁ፣ ክርስቶስ ሲነሳ መላዕክት ተደሰቱ"
(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

"ትላንት ከእርሱጋ ተሰቅዬ ነበር ዛሬ ከእርሱጋ እከብራለሁ ትላንት ከእርሱጋ ሞቼ ነበር ዛሬ ከእርሱጋ ህያው እሆናለሁ ትላንት ከእርሱ ጋ ተቀብሬ ነበር ዛሬ ከእርሱ ጋር እነሳለሁ"
(ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ

"ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባለችና ፋስካን ታደርጋለች"
(ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ)
ለሁላችሁም መልካም የፋሲካ በዓል ወንድሞቼ እኅቶቼ።
@APOSTOLICsuccession
“ተወዳጆች ሆይ! ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ብቻ የምትሰሙ አትሁኑ፡፡ እነርሱን ለመምሰልም ተጣጣሩ እንጂ፡፡ ለጊዜው ብቻ የምታደንቋቸው አትሁኑ፡፡ ወደ ቤታችሁ ብቻ ሳይሆን ወደ ልቡናችሁ ውሳጤም ዘልቀው እንዲገቡ አድርጉ፡፡ ዘወትር አስቧቸው፡፡ በልቡናችሁ ጓዳ እንዲገቡ አድርጓቸው፡፡ እናንተን ትተው ይሔዱ ዘንድ አትፍቀዱላቸው፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደሆነ ዘወትር እያያችኋቸው ትበረታላችሁ፡፡ በእምነት ትጸናላችሁ፡፡ የለበሱትን የጽድቅ ጥሩር፣ የያዙትን ምግባረ ወንጌል፣ የእምነት ጋሻ፣ የመዳን ራስ ቁር፣ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ እየተመለከታችሁ ትበረታላችሁ፡፡”

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
"አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ምስጉን ነው።"

መዝ 96(94)፥12-13
"ጋብቻ ለመመስረት ያሰበ አንድ ወጣት ከቤተሰብና ከጓደኞቹ ጋር ተማክሮ ከጨረሰ በኋላ የመንፈስ አባቱ ዘንድ በመሔድ ይህንን ውሳኔውን አስረዳቸው፡፡ ጥበበኛውም አባት ለማግባት ያለውን ጉጉት በልጁ ፊት ላይ እያስተዋሉ አሳቡ መልካም እንደሆነ ገልጸው ማስታወሻና ብዕራቸውን በማውጣት “ስለ ልጅቷ ትንሽ ነገር ንገረኝ” በማለት ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ እርሱም እንዲህ አለ “ትውልዷ ከነገስታት ዘር እድገቷም በምቾት መሐል ነው” አለ፡፡ እኚህም አባት በሙሉ ልብ ሆነው በያዙት ማስታወሻ ላይ ዜሮ ጻፉ፡፡
ወጣቱም ስለ ልጅቷ ማብራራቱን ቀጠለ፡- “በጣም ውብ ናት” አለ፡፡ እርሳቸውም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡ “በጣም ዝነኛ ናት” አለ፡፡ ደግመው ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡ “በጣም ሀብታም ናት” አለ፡፡ ጥበበኛውም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ምሁር ናት” አለ፡፡ አሁንም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ዘመናዊ ናት” አለ፡፡ ተጨማሪ ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡ በመጨረሻ ግን የረሳውን አንድ ነገር ነገራቸው “ልባም እንዲሁም ሕይወቷ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የተሰጠ ነው” አላቸው፡፡ ጥበበኛውም አባት ፊታቸው ላይ ፈገግታ እየተነበበባቸው አስቀድሞ ከጻፉአቸው ስድስት ዜሮዎች ፊት አንድ ቁጥርን ጽፈው “በል ሂድና አግባት” አሉት፡፡ ወጣቱም በደስታ ከፊታቸው ሄደ፡፡

ጋብቻ ብዙ ጊዜም በሌላው ሰው አካላዊ ገጽታና ውጫዊ አቋም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአካላዊ ውበት መማረክ ወደ ፍቅር የሚመራ አንደኛው መንገድ ቢሆን እውነተኛ ፍቅር ግን በአካላዊ ውበት፣ በአፋዊ መስፈርት ከመሸነፍ ያለፈ ነው፡፡ አካላዊ ውበት የጊዜያዊ ጉጉት መገለጫ ሲሆን ፍቅር ግን በሌላው ውስጥ ያለውን መልካሙን ነገር በመሻት ትዕግስትን መሰረት የሚያደረግ ነው፡፡ይህም የትኛውንም ልብ የመንካት፣ በላቀና በጠለቀ መንገድ የመግዛት ጉልበት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በዘመኑ የሚያሳልፋቸው ትልልቅም ይሁን ትንን ውሳኔዎች አሉ፡፡ ሕይወትም በዚህ የዕለት ተዕለት ቋሚ የመምረጥና የመወሰን ተግባር ላይ የተመሰረተች ናት፡፡ ጋብቻ የእኛን ትልልቅ ውሳኔ ከሚፈልጉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ የምናመልከውን እንመርጣለን፣ የምንኖርበትን አካባቢ እንመርጣለን፣ የልባችንን የምናካፍለው ባልንጀራ እንመርጣለን፣ በትዳር አጋር የሚሆነንን እንመርጣለን፣ በአጠቃላይ መሆን የምንፈልገውን እንመርጣለን፡፡ በእርግጥ ምርጫችንን ከምንኖረው በላይ ተጽእኖ ወደ ኑሮአችን የሚያመጣውን መኖራችን ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህም ውስጥ ከእውነት ጋር ያለን ትስስር ሊደበዝዝ አይገባም፡፡ ምርጫችን ውስጥ ሞትም ሕይወትም፣ ደስታም ሀዘንም፣ ክብርም ውርደትም አለ፡፡ መርጠን ዘመናችንን የእንባ ልናደርገው መብቱ የእኛ ነው፡፡"
"አንድ ወንድና አንዲት ሴት የተጋቡት (የሚጋቡት) መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ አብረው እየተጋገዙ ለመሔድ ከኾነ፥ ትዳራቸው ታላቅ የኾነ ደስታን ያመጣላቸዋል፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
አራት በህሪዎች!!

.

ቀኑ ሲነጋ ሲመሽ ወርና አመቱ ጊዜውን ጠብቆ ሲቀያየር እኛ የጊዜው ተጠቃሚዎችን ፈቃድ አይጠይቅም ጠይቆም አያውቅም… ጊዜ የራሱን ስራ እየሰራ ውቅቱን ጠብቆ ሳይዛነፍ ይጓዛል የሰው ልጅ ደሞ በዚህ አዙሪት ውስጥ ሆኖ ዛሬ ያጣውን ነገ ለማግኘት ይመኛል… ነገ ግን የዛሬው አይነት ቀን ነው የአንተን የትላንት ድክመት ሊያርም ከትላንት ዛሬ አይነጋም… ለአንተ በትላንትናና በዛሬ ማሐል ያለው ልዩነት የቀን ቁጥር ብቻ ነው።

አመት ስለተለወጠ በደፈናው ህይዎትህ አይለወጥም ከቀኑ ጋር አብረህ የምትለውጠው ህይዎት ካላኖርክ በቀር… ጎዶሎህን ጠንቅቀህ አውቀህ ለራስህ መስመር ብታበጅ ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።

የሰራሀውንና ያልሰራሀውን ለይተህ ለማረም ያግዝሃልና ለዚህም አራት መስመሮችን እነግርሃለው ታሰምራለህ።

እኛ ሰዎች ከጊዜው ጋር አብረን ብንጓዝም ባንጓዝም የጊዜ መሮጥ አይቆምም ይቀጥላል።
ብዙ ጊዜ ትቶን ሄዶዋል ሮጠን የደረስንበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም አይኖርምም… እናም ከጊዜ ጋር መሮጥህን ትተህ የሰው ልጆችን አራት የባህሪ መገለጫዎችን በራስህ ህይዎት ላይ ለመጨመር ሞክር እነዚህ አራት የባህሪ መገላጫዎች አንተን ከራስህ፣ ከእግዚአብሔር ፣ ከሰዎችና ከአለም ጋር ፍጥጥ አድርገው ያገናኙሃል በውስጣቸው ሰባት የባህሪ መገለጫዎችን አጭቀዋል በጥንቃቄ እያቸው።

1… ከራስህ ጋር… አንድ ሰው ከራሱ ጋር የሚኖሩት ሰባት የባህሪ መገላጫዎች ጥሩ ነው ይላሉ።

1… ፍርሃትን ማሶገድ
2… ለበጎ ነገር መጣር
3… ክፉን መቋቋም
4… ለመንፈሳዊ ህግጋት መገዛት
5… ሐቅና ቅንነትን መከተል
6… ራስ ወዳድነትን መራቅና
7_በድህነትም ቢሆን እነዚህን ጠብቆ መኖር።

2… ከእግዚአብሔር ጋር… ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖርህ ሰባት መገለጫዎች……

1… መስገድ፣ መፀለይ
2… ልኩን ማወቅ (አለማነፃፀር)
3… ሰለስጦታው ማመስገን
4… ሕጉን መቀበል
5… በፈተናው መታጋስ
6… ታላቅነቱን ማሰብ
7… እሱን መሻት።

3… ከሰዎች ጋር ሊኖርህ የሚገባ ሰባት የባህሪ መገለጫ መንገዶች እነዚህ ናቸው።

1… ቻይነት
2… ይቅር ባይነት
3… ትህትና
4… ለጋስነት
5… ርህራሄ
6… መልካም ምክር
7… ፍቅርና ሚዛናዊነት ናቸው።

4… ከአለም ጋር የሚኖርህ ባህሪያት ደሞ።

1… ኑሮዬ ያለኝ በቂዬ ነው
2… ከማገኘው የምናገኘውን መምረጥ
3… አስቀያሚ የምንለውን ነገር መጣል
4… የተርረፈረፈ ነገር መጥላት
5… መታቀብ መምረጥ
6… በአለም ክፉ የሆነውን ነገር ማወቅና መሻቱን መጥላት
7… ክፉ ነገር እንዳይሰለጥን መቃውም ናቸው።

በሰው ልጅ ህይዎት ውስጥ ባህሪ ወሳኝ ቦታ አለው የተስተካከለ ባህሪ ከሌለህ የተስተካከለ ህይዎት ይኖረኝ ብለህ ማሰብህ ሞኝ ያሰኝሃል።
ከራስህ ጋር ጥሩ ባህሪ ካለህ ከውጥህ ጋር ከተግባባህ ከህሊናህ ካልተጣላህ… ለእግዚአብሔር በአግባቡ ከተገዛህ… ከሰዎች ጋር ጥሩ መግባባት ካለህ… የአለም ትርጉም ከገባህ እመነኝ አመቱ ቢለወጥም ባይለወጥም ምንም አትሆንም እነዚህ ቀላል ነገሮች በራስህ ህይዎት ለመተግባር ጣር።
@memhrochachn
“ላገቡት” የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር

ባልና ሚስት አንድ መኾናቸውን ብዙ ጊዜ ስለ ተማራችሁት እርሱን አልደግምላችሁም፡፡ ከዚህ ተነሥቼ ግን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፦ ከሰውነታችሁ ውስጥ አንዱ ሕዋስ ቢታመም ቆርጣችሁ ትጥሉታላችሁን? ከሕመሙ ይፈወስ ዘንድ የምትጥሩ አይደላችሁምን? ለትዳር አጋራችሁም እንደዚህ መኾን አለባችሁ፡፡ እንደዉም'ኮ፥ ከሰውነታችሁ ሕዋስ ውስጥ ያለው በሽታ አንዳንዴ ላይድን ይችላል፡፡ የትዳር አጋራችሁ ግን፥ ምንም ክፉ ቢኾንም ሊለወጥ ይችላል፡፡ በሰውነታችን ላይ የሚኖረው አንዳንዱ ችግር ለምሳሌ ልምሾ እጅ ወይም እግር ሥራ መሥራትን ሊከለክለን፣ በሌላዉ የሰውነታችን ክፍል ላይ ጫና ሊያሳድርብን ይችላል፤ ነገር ግን ይበልጥ እንክብካቤ እናደርግለታለን እንጂ ቆርጠን አንጥለዉም፡፡ ታዲያ መዳን ለማይችለው ሰውነታችን ይህን ያህል እንብካቤ እያደረግንለት ሳለ፥ የመዳን (የመለወጥ) ዕድል ያለው አካላችንን (ባለ ትዳራችንን) መቁረጥ (መፍታት) እንደ አማራጭ ማስቀመጣችን እንዴት ብናብድ ነው?
"የብርሃናት ንጉሥ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውለድ ዛሬ የብርሃን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነት ተወለደች። ከሊባኖስ ተራሮች ርግብ ጸዐዳ ተወለደች፤ በሔዋን ምክንያት የተዘጋው የሕይወት መንገድ ይከፈትልን ዘንድ የሕይወት እናት ዛሬ ተወለደች፡፡ የዓለም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ከእርሷ ይወለድ ዘንድ እመብርሃን ዛሬ ተወለደች፡፡

ኢያቄምና ሐና ዳግሚት ሰማይ ተብላ የተጠራችውን ድንግልን ወለዱ፤ እውነተኛው ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ይወለድ ዘንድ እመ ፀሐይ (የፀሐይ እናት) ቅድስት ድንግል ዛሬ ተወለደች፤ ብርሃንን ለማስገኘት መወለድ መታደል ነው፤ ከሰው ልጆችም መካከል መመረጥ ዕፁብ ድንቅ ነው፤ የመድኃኔዓለም እናት ለመሆን መወለድ ሰማያዊ ፀጋ ነው።

በእውነት እመብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ስጦታ ናት። ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን እመብርሃን ዛሬ ተወልዳልናለችና ደስ ይበለን እልልም እንበል።"

የአለሙን ሁሉ መድኃኒት ለወለደች ለብርሃናት ጌታ እናት በቀራንዮ በመስቀሉ ስር እናት ትሆነን ዘንድ ለተሠጠችን ለመመኪያችን ዘውድ ለተወዳጇ ለቅድስተ ቅዱሳን እናታችን ልደት በዓል እንኳን አደረሰን
“በቤት ውስጥ በሚስትህ ምክንያት አንድ ደስ የማያሰኝ ስሕተት ቢፈጠር ‘አይዞሽ’ ልትላት ይገባል እንጂ ኀዘኗን ልታባብሰው አይገባህም፡፡ ኹሉንም ነገር ብታጣም እንኳን ከጎኗ ኹን፡፡ እርግጥ ነው ለባልዋ ደንታ ከሌላት ሚስት በላይ ምንም አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ በእናንተ መካከል ጸብ ክርክር ከሚፈጥር የሚስትህ ጥፋት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ስለዚሁ ዋና ምክንያት ግን ለእርስዋ ያለህ ፍቅር እጅግ ጽኑዕ ሊኾን ይገባዋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች አንዳችን የሌላችንን ሸክም እንድንሸከም የታዘዝን ከኾነ፥ ከዚህ በላይ ደግሞ አንተ የሚስትህን ሸክም ልትሸከም ይገባሃል፡፡ በመኾኑም ድኻ ብትኾን ስለዚሁ ምክንያት በፍጹም አትናቃት፡፡ ሰነፍ ብትኾን ስለዚሁ ምክንያት አስተካክላት እንጂ አታዋርዳት፡፡ እርስዋ አካልህ ነችና፤ አንተም አካልዋ ነህና፤ አንድ አካል ናችሁና፡፡ ‘ክፉ ነች፤ ቁጡ ነች፤ ራስዋን መቈጣጠር የማትችል ግልፍተኛ ነች’ ልትለኝ ትችላለህ፡፡ ስለዚሁ ጠባይዋ እጅግ ልታዝን ይገባሃል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን ጠባይ ያርቅላት ዘንድ ጸልይላት እንጂ አንተም መልሰህ አትቈጣት፡፡ ልታሳምናት ሞክር እንጂ ወደ ሙግት አትግባ፡፡ እነዚህን ክፍተቶችዋን ከእርስዋ ለማራቅ ኹሉንም ዓይነት በጎ ዘዴዎችን ተጠቀም፡፡”

“ይህን እንደማድረግ ሚስትህን የምትመታትና የምታሠቃያት ከኾነ ግን እነዚህ ሕመሞችዋ እንዲድኑ አታደርጋቸውም፡፡ ኃይለኝነት የሚወገደው በጭካኔ ሥራ ሳይኾን በየውሃት ነውና፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም ሚስትህ በየውሃት ስትይዛት ከእግዚአብሔር ዘንድ ሹመት ሽልማት እንደምታገኝ አስታውስ፡፡ ከአሕዛብ ፈላስፎች አንዱ ክፉ፣ መራራና ሥርዓት የለሽ ሚስት ነበረችው ይባላል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለምን ከእርስዋ ጋር እንደሚኖር (ለምን እንደማይፈታት) በተጠየቀ ጊዜ ጠቢቡ ሰው በገዛ ቤቱ ውስጥ የፍልስፍና ትምህርት ቤት እንዳለው ነበር የመለሰው፡፡ ‘ዕለት ዕለት በዚህ ትምህርት ቤት የምማር ከኾነ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ታጋሽ እኾናለሁ’ ነበር ያለው፡፡ በዚህ ተደነቅህን? እኔ ግን መላእክትን እንዲያውም ከእነርሱም በላይ የዋሃን ኾነን እግዚአብሔርን እንድንመስለው ከታዘዝነው ከእኛ ይልቅ አረማውያን ሰዎች ጠቢባን ኾነው ስመለከታቸው ፈጽሜ አለቅሳለሁ፡፡ ያ ፈላስፋ ሚስቱን እንዳይፈታት ምክንያት የኾነው የእርስዋ ክፉ ጠባይ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ‘ይህ ፈላስፋ ይህቺን ሴት ሚስት ትኾነው ዘንድ ያገባት ይህን ለማግኘት ብሎ ነው’ ይላሉ፡፡ አንተም ዕጮኛ ስትመርጥ በምርጫህ ተሳስተህ ክፉ ሚስት አግብተህ ከኾነ (ብታገባ) ቢያንስ ቢያንስ ይህን አረማዊ ፈላስፋ አብነት አድርገው፡፡ ሚስትህን ለማስተካከል የተቻለህን አድርግ፡፡ ክፋትዋን በሌላ ክፋት አትመልስላት፡፡ ከእርስዋ ጋር ኾነህ የትዳርን ቀንበር የምትሸከም ከኾነ ሌሎች ብዙ ረብ ጥቅሞችንም ታገኛለህና፤ መንፈሳዊ ተግባራትን ለመተግበር ቀላል ይኾንልሃልና፡፡”

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
@memhrochachn
“ደጋግመህ ኃጢአት ብትሠራም ደጋግመህ ንስሐ ግባ፡፡ ቤተክርስቲያን ሐኪም ቤት እንጂ ፍርድ ቤት አይደለችምና፡፡”

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"እየጠላን የምናደርገው"

ብዙ ሰው ‹‹እኔ ሐሜት አልወድም፡፡ ግን ማማት የሚወዱ ጓደኞች አሉኝ›› ይላል፡፡ አሁን እርሱ ምን እያደረገ ነው? ‹‹ወዳጆቼ ሐሜተኞች ናቸው›› ሲል እያማቸው አይደለምን? ወይስ ለእርሱ ሲሆን ሐሜቱ ተለውጦ የመረጃ ቅብብል ይሆናል?! በነገራችን ላይ ይህ የዚህ ጽሑፍ መግቢያ ራሱ ሐሜት ነው።

የማንወደው ነገር ግን እየጠላንም ቢሆን የምናደርገው ኃጢአት ሐሜት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሜተኛ ሆኖ የተጠቀሰው በእባብ ያደረው ሰይጣን ነው፡፡ በመጀመሪያ የታማው ደግሞ እግዚአብሔር ሲሆን፣ ሐሜቱን ሰምታ ሳትመረምር የተቀበለችውና ለስሕተት የቸኮለችው ሴት ሔዋን ነበረች፡፡(ዘፍ 3፥1-5)

የሰይጣን ሐሜት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንደኛ "አትሞቱም፤ እንደ እርሱ እንዳትሆኑ ነው የከለከላችሁ" በሚለው ንግግሩ "እግዚአብሔር ዋሽቷችኋል" እያለ ፍቅሩን እንድትጠራጠር እያደረገ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ከዛፉ ብትበሉ እንደ እርሱ ትሆናላችሁ በማለት የእግዚአብሔር አምላክነት "የዛፍ ፍሬ" በመብላት የተገኘ መሆኑንና እርሱም እንደ እነርሱ የነበረበት ጊዜ እንዳለ እንድታስብ እየገፋፋት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ስም ማጥፋት (Character assassination) ከየት ሊገኝ ይችላል? ሰይጣን በነገር ሁሉ ፍጹም የሆነን አምላክ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ሐሰት ፈጥሮ ለማማት ወደ ኋላ ካላለ፣ አንዳች ጉድለት የማያጣብን እኛማ ከሐሜቱ ጅራፍ ልናመልጥ እንደማንችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

በተለይ በአሁን ጊዜ ሐሜት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ሥሩን ሰድዷል። እንደውም ባልንጀራን ማማት እንደ ምግብ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቻችን በዚህች ደሃ አገር ከመጠን በላይ ወፍረን እንቸገር ነበር። ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን የሐሜት አውድማዎች ሆነዋል። በየገጾቻችን ከሽነን የምናቀርባቸው ጽሑፎች ጠረናቸው የሰው ሥጋ የሰው ሥጋ ይላሉ። ፊታችን በሐሜት ወይቦ ሁለት መልክ ካወጣን ቆየን። ይኸው ሳንባችን በማማት አየር ተመርዞ ሳሉ ከበረታብን ሰነባብተናል። ወዳጃችንን የማናማበት ብቸኛው ጊዜ ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ሰዓት ነው። ያውም ደግሞ ያንኑ ጊዜ ሌላኛውን ሰው ለማማት ካልተጠቀምንበት ማለቴ ነው።

ሊቁ ዮሐንስ ካዝያን እንደሚናገረው ሰው ከሚጠቅመው ቃለ እግዚአብሔር ይልቅ የማይጠቅመው ሐሜት ያጓጓዋል። የአምላክ ቃል ሲነገር እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለው ሁሉ፣ የሐሜት ነገር ሲሆን ግን እንደ እርሱ ንቁ የሚሆን የለም። በጥፍሩ ቆሞ ይሰማል። ሌሊቱን ሁሉ ሳይተኛ ቢያድር ደስ ይለዋል።

ለመሆኑ ባልንጀራችንን ስለ ምን በቀስታ እናማዋለን? የወዳጃችንንስ ውድቀት በማውራት በእኛ ላይ የምንጨምረው ምን በጎ ነገር አለ? በሰው ፊት መልካም እየመሰልን ከኋላው ግን ስለ እርሱ ውድቀት በማውራት የራሳችንን ደረጃ ከፍ ማድረግ አይቻልም። ስለ ሌሎች በማውራት የምናጠፋውን ሰዓት ራሳችንን ለማሳደግ ብንጠቀምበት ኖሮ "መኖራችንን ትርጉም እንዲኖረው" ማድረግ ይቻለን ነበር።

"ንጹሕ ወዳጅነት" ሐሜትና ማሾክሾክ የሌለባት የታማኞች ጌጥ ናት። የሐሜት ስለታቸውን ያልጣሉ ሰዎች "እውነተኛ ባልንጀርነት"ን አያውቋትም። አንተ በፍቅር ወዳጅ አድርገህ ከፊትህ ስታቀርባቸው እነርሱ ከኋላህ ሆነው የሚያሙህን አትጥላቸው፤ አትጣላቸው። ነገር ግን የሐሜቱ እርሾ እንዳያገኝህ ቶሎ ተለያቸው። ከፊትህም አድርገህ አታሰቃያቸው። የእነርሱ ቦታ ከኋላህ መሆን ነው።

ሐሜት የሰይጣን ነው። ሰውን የሚያማ በገዛ ፈቃዱ አንደበቱን ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠ ነው። ማማት በቤተ ክርስቲያን መለያየትን ያመጣል፣ ቤተሰብ ይበትናል፣ ወንድሞችን ያጣላል። ብንችል ስለ ሰው የምናውቀውን ጥሩውን እናውራ። የምናወራው ጥሩነት ከሌለው ደግሞ ቢያንስ ምንም አንበል።

ሔዋን ልክ እንደ አዳም እባብን "ሂጅልኝ" ብላ ብታባራት ኖሮ እነርሱም ከፈጣሪ ባልተጣሉ ሐሜትም ወደ ዓለም ባልገባ ነበር። ሐሜትን ማጥፋት ከፈለግን ሐሜተኛን እሺ አንበል። ማር ይስሐቅም "ወዳጁን በፊትህ የሚያንኳስሰውን ሰው አፉን መዝጋት ባትችል እንኳን ቢያንስ ሐሜቱን ከመስማት ተቆጠብ" ይላል። ሐሜትን ደስ ብሎህ ካልሰማኸው ደስ ብሎት የሚያማን ሰው ልትፈጥር አትችልም።

"ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" ገላ 5፥15

(Dn Abel Kassahun Mekuria)
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፦
፩ኛ. ትዕቢተኛ ዓይን፥
፪ኛ. ሐሰተኛ ምላስ፥
፫ኛ. ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥
፬ኛ. ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥
፭ኛ. ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥
፮ኛ. በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር
፯ኛ. በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።

ምሳሌ 6÷16-19
"ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ልጆቿን ትጣራለች፦ ሁላችሁም ስሟት በሩቁ አትሳለሟት ይልቅስ ቀርባችሁ ተማሯት ከእውቀት የጎደለች የመሰላችሁ በጥበብ ሞልታ ታይዋታላችሁና፤ ከወንጌል የሽሽች የመሰላችሁ ወንጌልን ለብሳ ታዩዋታላችሁና፤ ከክርስቶስ የራቀች የመሰላችሁ ክርስቶስን ስታነግስ ታይዋታላችሁና።

ኑ እናንተ የክርስቶስ ወዳጆች ወደ ክርስቶስ ቅረቡ ኑ ኦርቶዶክሳዊነታችሁን በስም ብቻ አታድርጉት ይልቅስ የህይወት መንገድ እንደሆነች እወቁና በዚህች መንገድ ላይ ተጓዙ፡፡

ኑና ተዋህዶን ግለጧት አንብቧት እዩዋት መርምሯት ፈትሿት፤ የክርስቶስን ምስጢረ ተዋህዶ ታሳያለች፣ የክርስቶስ የአምላክነት ክብር ታስረዳለች፣ የክርስቶስን ሞትና መከራ ታሳስባለች፣ የክርስቶስን ትንሳኤና እርገት ታሳውቃለች፣ የክርስቶስን ዳግም ምፅአት ታመላክታለች።

ተዋህዶን አንብቧት ክርስቶስን ታዩታላችሁ፤ ነገር ግን በትእቢት አይደለም በትህትና ነው እንጂ፤ ራስን ከፍ ከፍ በማድረግ አይደለም በማሳነስ ነው እንጂ፤ በአፍ አይደለም በህይወት በመኖር እንጂ፤ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ልጆቿን አሁንም ኑ ልጆቼ እያለች ትጣራለችና ቀርበን ፍቅሯን እንቅመስ፤ ማንም ይህንን ፍቅር ቀምሶ ያተረፈ እንጂ የከሰረ፣ ቀና ያለ እንጂ አንገቱን የደፋ፣ የተደሰተ እንጂ የተከፋ፣ ዘለዓለማዊ ህይወትን ያገኘ እንጂ የሞት ሞትን የሞተ የለምና፡፡"
@memhrochachn
“ለሞቱት ብቻ አናልቅስ። በቆሙት ብቻም አንደሰት። ታዲያ ምን እናድርግ? ለኃጢአተኞች በሞቱ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቁማቸውም እናልቅስ። ስለ ጻድቃን ደግሞ በቁማቸው ብቻ ሳይሆን በሞቱም ጊዜ ደስ ይበለን። ምክንያቱም ኃጢአተኞች ቆመውም ሞተዋል። ጻድቃን ግን ሞተውም ሕያዋን ናቸው።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ከአምላክህ ተጣበቅ!

መጨረሻህን የሚያሳምረው ከፈጣሪህ ጋር ያለህ ግንኙነት ነው፤ ፈጣሪህን እንደ ልብ ጓደኛህ እንደ አባትህ ካልቀረብከው ወደ ህይወትህ ካላስገባኸው የፈለገ ብትሮጥ የልብህ አይሞላም፣ አጊንተህ አትረካም፣ ለሰዎች ሙሉ ትመስላለህ ውስጥህ ግን ባዶ ነው፤ ወዳጄ ከአምላክህ ስትገናኝ ከእርሱ ጋር ስትጣበቅ ከምትፈልገው ነገር የሚያቆምህ ምድራዊ ሀይል የለም!
2025/03/13 12:13:56
Back to Top
HTML Embed Code: