tgoop.com/sratebetkrstyane/7591
Last Update:
D#ነገረ #ክርስቶስ #ክፍል #፵
ጌታ ክርስቶስ በባሕርይው ፍቅር ነው። ይህ ማለት ጥላቻ አይስማማውም ማለት ነው። አይሁድ እርሱን ጌታን ከኃጢአተኞችና ከቀራጮች ጋር ሲበላ አይተውት ነቅፈውት ነበር። "የቀራጮችና የኃጢአተኛዎች ወዳጅ" ብለውታል (ማቴ. ፲፩፣፲፱)። ኢየሱስ ኃጢኣታችን እንደ ምድር አሸዋ የበዛ ቢሆን እንኳ ንስሓ ብንገባ ይቅር የሚል አምላክ ስለሆነ ኃጥአንን ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ ምክንያት ለመሆን አብሯቸው ይበላ ይጠጣ ነበር።
ጌታ ሰዎች ተአምራቱን አይተው፣ ትምህርቱን ሰምተው ከኃጢአታቸው ተመልሰው መልካም ሥራን ይሠሩ ዘንድ በከተማዎችና በመንደሮች እየተመላለሰ ያስተምር ነበር። ነገር ግን ይህ ሁሉ ተደርጎላቸው ከኃጢአታቸው ያልተመለሱ ሀገሮች ስለነበሩ ወዮልሽ ኮራዚ ወዮልሽ ቤተሳይዳ እያለ ወቅሷቸዋል። በፍርድ ቀን መከራ እንደሚበዛባቸውም ነግሯቸዋል (ማቴ. ፲፩፣፳-፳፭)። ጌታ ኃጥአንን እንጂ ኃጢአታቸውን አይወድም። ኃጥአንን ከኃጢአታቸው ለመለየት ብዙ ተአምራትን አሳይቷል። ነገር ግን በባሕርይው ፍቅር የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርይው በትክክል የሚፈርድ (ፈታሒ በርትዕ) ስለሆነ ለሁሉም እንደየሥራው ይከፍለዋል። ፍቅሩና ፍርዱ የተስማማለት ጌታ ነው።
ስለዚህ ኢየሱስ የኃጢአተኞች ወዳጅ ነው እያልን ኃጥአን እንሁን ማለት ትልቅ በደል ነው። ጌታ ኃጥአንን በባሕርያቸው ይወዳቸዋል በግብራቸው ግን ይጠላቸዋል። ጻድቃንን ደግሞ በባሕርያቸውም በግብራቸውም ይወዳቸዋል። ስለዚህ እንደ ጻድቃን በግብርም ለመወደድ መልካም ሥራን መሥራት ይገባናል።
BY ✝️ስርዓተ ቤተክርስቲያን መመሪያ ✝️
Share with your friend now:
tgoop.com/sratebetkrstyane/7591