Telegram Web
ስለ ለምፅ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

ሊያ ያዕቆብ ለምፅ የጀማመራት ገና በለጋነቷ ነበር። ለምፁን ተከትሎ ድብርት መጣ። ራሷን መጥላት ጀመረች። "መስታወት ማየት አልፈልግም" ትል ነበር። ምክኒያቷ የገዛ መልኳን ማየት አለመፈለጓ ነበር።

አንዳንድ ሰዎች ስነልቦናዊ ጉዳት የሚያደርስ ነገሮችን አድርገውባት ያውቃሉ። ለምፅ ስላለባት ብቻ ከታክሲ አስወርደዋት ያውቃሉ።

ሊያ ድብርት አንገላቷታል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ችግሮች ተደራርበውባታል።

ገና በለጋነቷ የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ለማድረግ ተገዳለች።

ለምፅ ፥ ድብርት ፥ መገለል ፥ የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ያለፈችበት መንገድ ነው።

አሁን ችግሮቿን ተጋፍጣ መርታት ጀምራለች።

የዛሬው ደርዘን ጥያቄ እንግዳዬ ሊያ ያዕቆብ ናት። ተከታተሉ ፥ ለሌሎች አጋሩ ፥ አስተያየት አስፍሩ።

ሊንክ 👇

https://youtu.be/Tii72h4iwTc
ማነው ባለአደራ
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ብርሃነ መስቀል ረዳ የቀኝ ጌታ ልጅ ነው። በደሴ ከተማ በድሎት እና ምቾት ነበር ያደገው። የጎደለው የለም። ተንቀባሮ ኖሯል፥ ተንቀባሮ ተምሯል። የፊውዳል ስርኣት ቢቀጥል የሚያጣው ነገር የለም። ምናልባትም ባለስልጣን የመሆን ተስፋ ነበረው። ምናልባትም እጅግ ባለጠጋ ሆኖ መኖር ይችል ነበር። ነገር ግን በስርኣቱ ላይ አመፀ። "መሬት ለአራሹ" አለ።

ብርሃነ መስቀል መሬት ለጭሰኛው እንዲሰጥ ሲጠይቅ የገዛ ሃብቱ ላይ እያመፀ ነበር። ከቀኝ ጌታ ረዳ ላይ ሊወርስ የሚችለው ሰፊ ጋሻ መሬት ተስፋ ነበረው። "የኔ የሃብት ተስፋ ይቅርብኝ" ብሎ አመፀ። "መሬት ለአራሹ፥ ተዋጉለት አትሽሹ" አለ። ለተበዳይ ወግኖ ሊፋለም ወሰነ።

"መሬት ለአራሹ" የሚለው ጉዳይ ላይ መሰረታዊ ጥያቄ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይገባኛል። የደርግ የመሬት ፖሊሲ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የሚናገሩ አሉ። ያ ትውልድ ላይ ቅሬታ ያላቸው ብዙ ናቸው። ተማሪዎች ንጉሡን መገርሰሳቸው አግባብነቱን የሚጠራጠሩ አሉ። ኢህአፓ ፥ መኢሶን ፥ ደርግ... ወዘተ የዛሬ ችግራችን ሰበቦች እንደሆኑ የሚያምኑ ጥቂት አይደለም።የኔ ነጥብ ሌላ ነው።

ነጥቤን ላስረዳ...

በያ ትውልድ ዘመን መደብ የሸጡ የሚባሉ ሰዎች ነበሩ። ከደህና ወገን ሆነው ሳለ ለሌሎች መብት የጠየቁ ሰዎች ናቸው። የባላባት ልጆች ሆነው ሳለ ለጭሰኛው መብት ታገለዋል። እነሱ ባይጨቆኑም ለተጨቋኝ መብት ሲሉ በረሃ ወርደዋል። እኚህ ሰዎች መደብ የሸጡ ይባላሉ።

ብርሃነ-መስቀል ረዳ ትልቅ ማሳያ ነው። የገዛ ምቾቱ ላይ አምፆ ለተበዳይ ድምፅ አሰማ። ድምፅ ማሰማት ብቻ አይደለም ፥ ታገለ። የብርሃነ መንገድ በመጨረሻም የገዛ ህይወቱን አስከፈለው።

ለጊዜው የርዕየተ አለም ጉዳይን እንዘንጋ። ሶሻሊዚም ፥ አሊያም ካፒታሊዝም ወይም ፊውዳሊዝም የሚለውን እንርሳው። የነብርሃነ መነሻ ነጥብ ላይ እናተኩር። መነሻ ነጥባቸው ለተበዳይ ማዘን ፥ ሀገርን መውደድ ፥ ለውጥን መፈለግ ነው። ከግል ጥቅም ይልቅ የወገንን ክብር ማስቀደም ነው መደብ መሸጥ....

ዛሬ የተወሳሰበ ችግር ባለባት ሐገር ውስጥ እንንራለን። ሚሊዮን ወጣቶች ስራ አጥ ናቸው። ባለ ስራዎቹ ደሞዛቸው አያኖራቸውም። ዜጎች ከባርነ**ት የሚስተካከል ኑሮን ይገፋሉ። ለኒህ ወገኖች ድምፅ የሚሆን ማነው?

አባይነህ ሸለሞ "ማነው ባለ አደራ" የሚል መዝሙር አለው።

"ትውልድ ወድቆ በመከራ
ወገን ሲያለቅስ በየስፍራ
አይቶ የሚመለስ ፥ ሰምቶ የሚራራ
ማነው ባላደራ ፥ የሚቆም ከተጎዱት ጋራ
" ይላል።

ማነው ባለ አደራ? እርግጥ ሁሉም ሰው ለራሱ መብት መቆም አለበት። ይህ ብቻ ግን አይበቃም። እንደነ ብርሃነ መስቀል መደቡን የሚሸጥ ያስፈልጋል።

የገንዘብ ችግር የሌለበት ፥ ነገር ግን ለድሆች የሚራራ
የሚባለውን ያላጣ ሆኖ ሳለ ለተራቡት የሚያስብ
ባለ ስልጣን ሆኖ ለተርታ ዜጎች የሚጨነቅ...

ብርሃነ መስቀል የባላባት ልጅ ሆኖ ሳለ ለጭሰኛው ራርቷል። የዘመናችን ብርሃነመስቀል ማን ይሆን?
ማነው ባለ አደራ?

"ትውልድ ወድቆ በመከራ
ወገን ሲያለቅስ በየስፍራ
አይቶ የሚመለስ ፥ ሰምቶ የሚራራ
ማነው ባላደራ ፥ የሚቆም ከተጎዱት ጋራ"

ይሄ ነገር ረዘመ መሰለኝ


@Tfanos
በቅርቡ አንድ ሰውን ዋሸሁኝ። የታቀደበት አይነት ውሸት ነበር የዋሸሁት።

ከቀናት በኋላ ራሴን ታዘብኹት። ውስጤ የተሸሸገውን ክፉውን እኔነቴን ተዋወቅኹት።

ለመዋሸቴ ይቅርታ በመጠየቅ ፋንታ ሌላ ማብራሪያ መፍጠር ቃጣኝ። "ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የዋሸሁት። ያ ሰው ሊረዳኝ ይገባል" አልኹ።

ሌላ ሰው እኔን የመረዳት ግዴታው ምን ድረስ ነው? ለጥፋቴ ቀላሉ መፍትሔ ይቅርታ መጠየቅ አይደል? "እንዲህና እንዲያ አይነት ምክኒያት ስላለኝ" የሚል ምክኒያት ምን የሚሉት ነገር ነው?

የትኛውም ሰው ከቀላል እስከ ትልቅ ጥፋት ከፈፀመ በኋላ "ለምን?" ተብሎ ቢጠየቅ ማቅረብ የሚችለው ሰበብ ይኖረዋል። ገፊ ምክኒያቱን ያብራራል። ነብሰ ያጠፋ እንኳን "ተረዱኝ" ብሎ የሚናገረው የራሱ "እውነት" ይኖረዋል።

ሰበብ ውጤቱን ይቀይረዋል?

እልፍ ምክኒያቶች የጥፋት ማካካሻ አይሁንም። ሰዎችን ያሳዘነ ፥ ሌላውን የበደለ፥ የዋሸ፥ ያጠፋ ሰው... ሰበብ መደርደር አይኖርበትም። "እንዲህና እንዲያ ስለሆነ ተረዱኝ" የሚል ተማፅኖ ማስቀደም አይጠበቅበትም። የሚቀድመው አሻሚ ባልሆነ መንገድ ይቅርታ መጠየቅ ነው። ቀጥሎ ካሳ ካስፈለገ መካስ ፥ መቀጣት ካለም ቅጣቱን በፀጋ መቀበል ነው።

በእርግጥ የልብ ዝንባሌን ማስረዳት ፥ ገፊ ምክኒያትን ማሳወቅ ፥ እንዲረዱን መጠየቅ አግባብ ነው። ግን ደግሞ ከዛ የሚቀድመው ጥፋትን ማመን ነው።

አውቃለሁ ፥ ይህ ፅሁፍ ከእናንተ ህይወት ጋር አይገናኝም።

የታዘብኩት ራሴን ነው። የሚገስፀውም ራሴን ነው። የሚወቅሰው ራሴኑ ነው። ተስፋአብን እወቅሰዋለሁ!

ጥፋቴን በማመን ፋንታ "ያጠፋኹት በዚህና በዚያ ምክንያት ነው" የሚል ማስተባበሪያ ለመፍጠር ስታገል ራሴን አገኘሁት። ሌሎችን በሚወቅሱበት ጥፋት መመላለስ አያስደነግጥም? አያናድም? እንዲያ ነው የሆነው።

ይህ ፅሁፍ ከእናንተ ህይወት ጋር እንደማይገናኝ አውቃለሁ ...


@Tfanos
"ኢትዮጵያ ደሃ ስለሆነች ደሞዛችሁ ይበቃችኋል"
* * *

የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ።

"ኢትዮጵያ ደሃ ናት። ከሐገራችን ኢኮኖሚ አንፃር ለሐገራቸው መስዋዕትነት ይክፈሉ" የሚሉ ሰዎች አሉ።

ጥሩ።

የጤና ባለሞያዎች የሐገሪቱ ብቸኛ ባለቤት አይደሉም። በልዩነት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ አይገደዱም።

ከሁሉ በፊት፥

የመንግስት ሹማምንት መስዋዕትነት ከፍለው አረዓያ ይሁኑ። በዝቅተኛ ደሞዝ ሕዝብን ያገልግሉ። ጥቅማቅሞችን ይተው። የሚያሽከረክሩትን ቅንጡ መኪና ያቁሙ። ሐገራችን ደሃ ስለሆነች በዝቅተኛ ደሞዝ ያገልግሉ!

(መሪ ለተመሪው አርዓያ ሲሆን ጥሩ ነው)

የዲጂታል ሚሊሻው ነገር አጃዒብ ነው

አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት ያስተዋወቁ ይመስል "ሐገራችን ደሃ ናት" ይላሉ ዲጂታል ሚሊሻዎች። የማናውቀውን ስላሳወቁን እናመስግናቸው። እነርሱ ባይነግሩን ኖሮ ሐገራች ሐብታም ትመስለን ነበር።

እንግዲያውስ ካድሬዎች ለሌላው የመከሩትን እነሱው ይተግብሩት። ለአጨብጫቢነቸው ከመንግሥት ካዝና የሚፈስላቸውን የሕዝብ ገንዘብ መቀበል ያቁሙ።

ዜጎች ኑሮ ሲወደድባቸው "ሐገራችን ደሃ ስለሆነች በጥቂት ገንዘብ አገልግሉ" የሚሉ ግብዞች እነርሱም ተመሳሳዩን ያድርጉ። ሐገራችን ደሃ ስለሆነች በጥቂት ደሞዝ ብቻ ያገልግሉ፥ ጥቅማጥቅም አይቀበሉ። ቅንጡ ኑሯቸውን ይተውት! (መሰረታዊ ኑሮን በማያሟላ ገቢ ህይወታቸውን ደጉመው ያሳዩ)

በተረፈ "እኔ በድሎት እየኖርኩ አንተ ግን በችጋር አለንጋ ተገረፍ" ማለት ሚዛናዊ አለመሆን ብቻ አይደለም። ስር የሰደደ ክፋት ጭምር እንጂ!


@Tfanos
አንዳንድ ነገሮች....

ልደቱ በትላንትናው እለት ለBbc በሰጠው ቃለ መጠይቅ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦች እየተዘዋወሩ ነው። አንዳንዱ ወቀሳ በጣም ያስቃል። ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ቃለ መጠይቁን ሳያነቡት ነው ትችት እያወረዱ ያሉት።

ልደቱን አትውደደው ፥ በሃሳቡ አትስማማ ፥ መንገዱ ስህተት ነው ብለህ እመን። መብትህ ነው። ግን ደግሞ ለራስህ ክብር ይኑርህ!

ራሱን የሚያከብር ሰው ለትችት ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት የተፃፈውን ያነባል።

ልደቱ በ97ቱ ምርጫ "ህዝቡን ክጃለሁ" ብሎ እንደተናገረ አስመስለው የሚፅፉ ሰዎች አሉ። እንዲህ አይነት ፅሁፍ የፃፉ ሰዎች በአጭሩ ቃለ መጠይቁን አላነበቡም። (አለማንበብ መብት ነው። ግን ደግሞ ባላነበቡት ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ራስን ትዝብት ላይ ይጥላል)

ልደቱ ያለው ነገር ግልፅ ነው። በ97 ምርጫ እንደ ፓርቲ ህዝቡን ክደናል ነው ያለው። "ህዝቡ መርጦን ሳለ ፓርላማ አንገባም በማለት ካድነው" ነው ያለው። ይህን ደግሞ ድንገት ዛሬ የተናገረው አይደለም። ደጋግሞ ተናግሮታል። አዲስ ጉዳይ አይደለም። "ፓርላማ አለመግባት የመረጠንን ህዝብ ድምፅ አለማክበር ነው" ብሎ ሲያምን ፥ ያመነውንም ሲናገር ኖሯል።
በ5 ደቂቃ ተነቦ የሚያልቅ ቃለመጠይቅ ሳያነቡ ለወቀሳ አደባባይ መውጣት ምን ይባላል?

ልደቱ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ የተናገረው ያስቆጣቸውም አሉ።

ከእውነት ጋር መደባደብ ካልፈለግን ፥ በተረት ራሳችንን መሸንገል ካልወደድን በቀር የተናገረው ሐቅ ነው።

እንደ ህዝብ ለራሳችን የተጋነነ ግምት አለን። ፃድቃን እንደሆንን ማመን ይቃጣናል። እግዚአብሔር ከሌላው በተለየ በሚያደላላት ሐገር እንደሚኖሩ የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን ቁጥራቸው ቀላል አይሉም። ግን ደግሞ እውነታው ሌላ ነው።

መራራውን እውነት መቀበል ይኖርብናል። በሽታውን የካደ አይድንም። ከእውነት እየተጣሉ ለውጥ አይመጣም። በብዙ ኋላቀር አስተሳሰብ የተተበተብን ነን። እንደ ህዝብ ብዙ ጎዶሎዎች አሉብን። በዚህ ወቅት ከተረት ይልቅ የሚጠቅመን መራሩን እውነት መጋፈጥ ብቻ ነው።
የሸሸነው እውነት ፥ ልንቀበለው ያልወደድነው ጥፋታችን ያደቀናል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ምናብ ወለድ መመፃደቃችን ወቅት እየጠበቀ ይቀጣናል።

ሐገር መውደድ ምንድነው?

ሐገር መውደድ ማለት ከእውነት ጋር ፀብ መግጠም ማለት አይደለም። እንደ ሐገር ያለብንን ሕፀፅ መካድ ፥ እንደ ህዝብ ያለብንን ደካማ ጎን አለመቀበል ሐገር መውደድ አይደለም። ይህ ተራ አድርባይነት ወይም ደግሞ አጓጉል ቅዠታምነት ነው!

የህዝብን ስህተት እየነቀሰ የሚተች ሰው ህዝብን የሚንቅ አሊያም ከማንም እበልጣለሁ ባይ አይደለም።

"ህዝብ አይወቀስም" የሚል ደፋር ሰው ዛሬም ይኖር ይሆናል። ግን ደግሞ ህዝብ በደንብ ይወቀሳል። "ህዝብ አይሳሳትም" የሚለው አባባል ለጆሮ ደስ ይል ይሆናል። ግን ደግሞ ፈርጠም ያለ ስህተት ነው። ህዝብ በደንብ ይሳሳታል። ሲሳሳት ደግሞ ይወቀሳል።

ለማንኛውም ልደቱ አያሌው 5 መፅሐፎች እና ከ30 በላይ መጣጥፎችን ፅፏል። የፖሊሲ አማራጭ ፥ የሕገመንግስት ማሻሻያ ፥ወዘተ ፅፏል። ስለሆነም ፖለቲካዊ ሃሳቦቹን አንብቦ መተቸት ለሐገር ፖለቲካ ጭምር ጥቅም ስላለው እሱ ላይ ማተኮሩ ይሻላል።


@Tfanos
የጤና ባለሞያዎችን መደገፍ ለምን....
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ዜጎች የሃኪሞችን ጥያቄ መደገፍ የውዴታ ግዴታችን ነው።

ላስረዳ

ምክኒያት አንድ፥

እውቀት ሊከበር ይገባል። ታታሪነት ተገቢውን እውቅና ማግኘት ይኖርበታል። ታታሪዎች ሲገፋ፥ አዋቂዎች ሲዋረዱ መጥፎ መልእክት ይተላለፋል።

አንድ ዶክተር የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በብዙ መትጋት ግዴታው ነው። ደግሞም ጎበዝ ተማሪ መሆን ይጠበቅበታል። እኩዮቹ በሸነና ሲሉ አንገቱን ቀብሮ ለማንበብ ይገደዳል። ከዚህ ሁሉ በኋላ መሰረታዊ ፍላጎቱን ማሟላት የማይችል ሲሆን ሌሎች እውቀትን እንዲንቁ ይገደዳሉ።

"ጠንክሬ ብማር ፥ ታታሪ ብሆን ፥ ሰቃይ ተማሪ ሆኜ ብገኝ ምን ጥቅም?" የሚል ትውልድ ይበዛል። ትምህርትን የማያከብር ዜጋ በበዛ ቁጥር የሀገር ነገ ፥ የማህበረሰብ እጣ ፋንታ ይኮላሻል።

የሃኪሞችን ጥያቄ መደገፍ ለእውቀት እና ታታሪነት ተገቢውን ክብር መስጠት ነው

ምክኒያት ሁለት

"የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመፅ በሮች ይከፈታሉ" ይባላል። እንዳለመታደል የሐገራችን ፖለቲካ ከአመፅ የተጋባ ነው። የመብት ጥያቄዎች በአመፅ ይታጀባሉ። መንግስት ሃይል ካልተጠቀመ ሐገር ያስተዳደረ አይመስለውም። ይህ ዋጋ ሲያስከፍለን ኖሯል።

የጤና ባለሞያዎች የመብት ጥያቄ አንስተዋል። ጥያቄያቸው እጅግ ተገቢ ነው። ተገቢ ብቻ ሳይሆን እስከአሁን አለመመለሱ እንደ ሐገር ያሳፍራል። ሐኪሞች ተገቢ ጥያቄ በማንሳት ብቻ አልተገደቡም። ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት መንገድ ስልጡን ነው። ይህ ብዙ ያስተምራል።

ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄ ማቅረብ ፥ በብዙ የሚያስፈልገን ባህል ነው። ሃኪሞች የተከተሉት መንገድ አረዓያነት ያለው በመሆኑ የተነሳ ከጎናቸው መቆም ይኖርብናል።

ምክኒያት ሦስት፥

ከአጀንዳ ፖለቲካ ጋር ፀበኞች ነን። እንደ ህዝብ መሰረታዊ የሆኑ አጀንዳዎች ቢኖሩንም ትኩረታችን ሌላ ነው። በብሔር እና በሃይማኖት ተከፋፍለናል። ከጋራ ጉዳያችን ይልቅ ከፋፋይ ነገሮች ይስቡናል።

በቡድን መከፋፈላችን ሐገራዊ አንድነትን ጭምር ለአደጋ የሚዳርግ ሆኗል።

ዶክተሮች ድጋሚ አርዓያ ሆነውናል።

ብሔር ዘለል መተባበር ፥ ሃይማኖት ተሻጋሪ ግኑኝነት ማድረግ እንደሚቻል አሳይተውናል። የጋራ አጀንዳን በሃይማኖት አሊያም በብሔር ሳይከፋፈሉ ማቅረብ እንደሚቻል አስተምረውናል።

ፖለቲካችን አጀንዳ ተኮር እንዲሆን ፥ የመብት ጥያቄዎቻችንም በመተባበር መከወን እንደሚችል ላሳዩት አረዓነት ሲባል ሊደገፉ ይገባል።

ምክኒያት አራት፥

"ትውልዱ ሐገሩን አይወድም" የሚል ወቀሳ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይሰነዘራል። ሐገር መውደድ የፖሊሲ ውጤት ጭምር ነው።

ዜጋ ሐገሩን እንዲጠላ ከሚያደርጉት የተለያዩ ምክኒያቶች መካከል አንዱ በሐገር የመገፋት ስሜት ነው። "ያገለገልኳት ሐገር ገፍታኛለች" ብሎ የሚያስብ ሰው በልቡ ጥላቻ ሊወለድበት ይችላል። በእርግጥ አንዳንድ ሰው ሐገር እና መንግስትን ለዩ የሚል ክርክር እንደሚገጥም ይገባኛል። ነገር ግን ይህ ንግግር መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይቀይረውም።

ሰዎች በአገዛዝ ሲበደሉ ፥ ሐገር አገልግለው ሲያበቁ ተገቢውን ክብር ሳያገኙ ሲቀሩ ለሐገራቸው ያላቸው ፍቅር ይሸረሸራል። ይባስ ብሎ ለሌላው መጥፎ ምሳሌ ይሆናል። ሌሎች ሰዎች ጭምር "ሐገራችንን ብናገለግል አንመሰገንም" የሚል አደገኛ ስሜት ይፈጥርባቸዋል። ይህ ስሜት ሲጎለብት የገዛ ሐገራቸውን የሚመዘብሩ ፥ ለወገናቸው ርህራሄ የሌላቸው ሰዎች ይበዛሉ። ይህ ምን እንደሚያስከትል ማብራራት አይጠበቅብኝም።

ለሃኪሞች ጥያቄ ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት ከምንገደድበት ምክኒያቶች መካከል አንዱ ብሔራዊ ስሜትን መጠበቅ ነው። ሃኪሞች ለህዝብ ላደረጉት አገልግሎት የሚመጥን ክፍያ ይሰጣቸው ማለት ዜጎች የሐገር ፍቅር ስሜታቸው እንዳይሸረሸር መታገል ጭምር ነው።

ምክኒያት አምስት፥

የነገ መብታችን በዛሬው የሃኪሞች ጥያቄ ውስጥ ተሸሽጓል። ዛሬ የጤና ባለሞያዎች ያቀረቡትን ተገቢ ጥያቄ መንግስት በሃይል ሊደፈጥጠው ይችላል። "ዶክተሮች እንደጀመሩት እነሱው ይወጡት" ብለን ዝም ብንል እና ጥያቄው በመንግሥት ቢደፈጠጥ የነገ እጣፈንታችን ለከፋ አደጋ ይጋለጣል።

ነገም በተራችን መሰረታዊ የመብት ጥያቄ ብናነሳ የድፍጠጣ ትምህርት ይሆናል። "ትላንት ዶክተሮችን እንደደፈጠጥኩት ዛሬም ሌላውን እደፈጥጣለሁ" የሚል መንግስታዊ ትምክህት ይፈጠራል።

ይህ ነገረ ረዘመ፥ እዚህጋ እናብቃ።

ከጤና ባለሞያች ጥያቄ ጋር መተባበር የውዴታ ግዴታችን ነው!


@Tfanos
"የዮናታን ወንጌል"
* * *

ዛሬ የኢየሱስ ስም መነገጃ ሆኗል። መፅሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ ከመፅሐፍ ቅዱሱ ተፃሪ የሚሆኑ እልፍ ናቸው። በኢየሱስ ስም ፀረ ኢየሱስ ድርጊት ይከወናል። ኢየሱስን በቤቱ ባይተዋር ማድረግ የሚፈልጉቱ ቁጥር የሌቸውም።

ዮናታን ድሆችን በአደባባይ ተሳድቧል። ድህነትን ሳይሆን ደሃን ተሳድቧል። ድሆች ጥቁር ጉንዳኖች እንደሆኑ መናገሩ ሳያንስ ለቃ ቃሚ ብሏል።

ዮናታን ጨዋ እንዲሆን አይጠበቅበትም። "የእግዚአብሔርን ቃል እስብካለሁ እያልክ እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው ለምን ትድባለህ?" ብሎ መጠየቅ ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው።

ዮናታንና ቢጤዎቹ ድሃን ሲንቁ ልክ የላቸውም። ድሃን ለመፀየፍ የሄዱበትን ርቀት የገዛ ነውራቸውን አያዩበትም።
"ድሃ..." እያሉ ሲሳደቡ በጥረታቸው ገንዘብ ያገኙ ፥ በልፋታቸው የሀብት ማማ የወጡ ይመስላል። ዳሩ ግን የስኬታቸው ምንጭ ግልፅ ውንብድና ነው።

ዮናታን አክሊሉ እና መሰሎቹ የህዝብን ስስ ብልት ያውቁታል። የህዝብን ደካማ ጎን በመጠቀም አጭበርብረው ባለጠጋ ሆኑ። ሌላ ተአምር የለውም። ሌላውን አጭበርብሮ ገንዘብ ያከማቸ ሰው ድሃን ሲፀየፍ እንደማየት የሚያሳፍር ምን አለ?

ዶክተር ደረጀ ከበደ "የአምልኮ ነፃነት" የሚል መዝሙር አለው። "የኢየሱስ ስም ለንግድ ጨረታ ወጣበት" የምትል ስንኝ በመዝሙሩ ውስጥ ተካቷል። የዛሬ ነቢያት መንገድ ይኸው ነው። የኢየሱስን ስም መነገጃ አድርገው ገንዘብን አከማቹ። ሌላ ተአምር የለም!

የተማርነው ወንጌል ሌላ ነው። የሰማነው መፅሐፍ ቅዱስ ሌላ ነው። ዛሬ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጭምር እያመፁ በአደባባይ የሚያቀረሹ ነውረኞች ጊዜ ይቀጣቸው ይሆናል። ግን ደግሞ እኒህን ነውረኞች መቃወም በተለይ ከፕሮቴስታንቱ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።

"እኛ የምናውቀው ወንጌል ይህ አይደለም። ወንጌላችን ስለ ኢየሱስ እንጂ ስለ ገንዘብ አይደለም" ማለት ከፕሮቴስታንቱ ማህበረሰብ ይጠበቃል።

"ንፁህ ወንጌል እንዳንሰብክ መሰናክል አትሁኑ"ማለት ከወንጌላውያን አማኞች ይጠበቃል።

@Tfanos
9ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። በእለቱ የከሰአት ነበር ፈረቃችን። ለትምህርት ቤት እየተዘገጃጀሁ ሬዲዮ እሰማለሁ። ያን እለት እሰማ የነበረው ኤፍ ኤም አዲስን ነበር። የእለቱ እንግዳ ደግሞ ጌታሁን ሄራሞ ይባላል።

ጌታሁን ሄራሞ ስለ ቀለም ሳይንስ ሲተነትን ሰምቼው አጃዒብ አልኹ። እንዴት ያለ ጉደኛ ሰው ነው አልኹ። ስሙን ሲነር ላይን ደብተሬ ላይ ፃፍኩት። "ጌታሁን ሄራሞ" ብዬ ፃፍኩ።

ሲኒር ላይ ማስታሻ ደብተሮች ነበሩኝ። (ለስብሰባ ወቅት የሚሰጠው ደብተር ማለቴ ነው) ሬዲዮ ስሰማ ፥ መፅሔት ሳነብ ፥ ከሰዎችጋ ሳወራ... የሰማሁትን አዲስ ጉዳይ በዛ ማስታወሻ እፅፋለሁ። ያን ቀን የጌታሁንን እውቀት እና ጌታሁንን በማስታወሻዬ ፃፍኩት።

እንደተለመደው ለሰዎች ስለጌታሁን እውቀት አወራኹ። (እስከዛሬ ድረስ የሚከተለኝ አመል አለ። የሆነ ሰውን ከወደድኹት በዙሪያዬ ላሉ ሰዎች ስለዛ ሰው አወራለሁ)

አንዲት ልጅ "ጌታሁን ሄራሞን የማውቀው ይመስለኛል። አባቴ ይወደዋል። መዝሙር አለው" አለችኝ። ተጠራጠርኳት። በልቤ እውነቷን እንዲሆን ተመኝቼ አለፍኹ።

አንድ ቀን መንፈሳዊ መፅሔት ሳገላብጥ "ጌታሁን ሄራሞ" የሚል ስም አየሁ። ተስገብግቤ አነበብኹት። ከመጀመሪያው በላይ ወደድኹት። "ይህ ሰውዬ በጣም ደስ ይላል" አልኹ።

ሌላ ቀን፥

ኳየር ነበርኹኝ። የቸርች ዘማሪ ነበርኹ። ድምፄ ለመዝሙር ባይሆንም በህብረት እንዘምር ነበር። የመዝሙር ግጥምና ዜማ እፅፍ ነበር። ኳየር መሄዱ ደስ ያሰኘኝ ነበር። የኳዬር ልጆች መንፈሳዊ ያልሆኑ መፅሐፍትን ስለማነብ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ስለሚጠይቁኝ የእውቀት የበላይነት ይሰማኝ ነበር። ለኳዬሬ ልጆች የጌታሁንን እውቀት አጣቅሼ ነገርኳቸው። "እሱ እኮ በጌታ ነው" አሉ። ደስ አላቸው። ደስ አለኝ።

የኳዬራችን ሰብሳቢ ጥበቡ አሰፋ ይባላል። መፅሐፍ አሳየኝ። "የለማኙ ሎጂክ" ይላል ርዕሱ። "የምትወደው ሰውዬ መፅሐፍ ነው" አለኝ። የጌታሁን ሄራሞ መፅሐፍ ነው። መፅሐፉን ሳነብ ከቀደመው ይበልጥ ወደድኹት።

የዛሬ 6 አመት አከባቢ ድንገት ጌታሁን ትዝ አለኝ። "ምናልባት ፌስቡክ ይጠቀም ይሆናል" ብዬ አሰብኹ። ፌስቡክ ላይ ሳገኘው ደስ አለኝ። የጓደኝነት ጥያቄ አቀረብኹ። ተቀበለኝ። ሲቀበለኝ ኩራት ተሰማኝ።

ከእለታት በአንዱ ከቸርች ልጆች ጋር ስለ ፌስቡክ አወራን። "ፌስቡክ ላይ ብዙ ምርጥ ሰዎች አሉ" አልኹኝ። ማስረጃ እንዲሆነኝ ስለ ጌታሁን ሄራሞ አወራሁ።

ፍቅሬ ቡንጤ የሚባል ሰው ከጌታሁን ጋር ተምሬያለሁ አለን። ፍቅሬ ቡንጤ የሻሸመኔ ሸዋበር ቃለህይወት ቤተክርስቲያን ሰዎች ታውቁታላችሁ አይደል? አዎ እሱ ነው።

ፍቅሬ ከጌታሁን ጋር መማሩን ነገረኝ።
"ምን አይነት ተማሪ ነበር" አልኩት። "ጎበዝ ተማሪ አልነበረም" አለኝ። ግር አለኝ። "ጌታሁን ጎበዝ አልነበረም?" አልኩት።

"ጎበዝ አልነበረም። እሱ ከጎበዞች በላይ ነው። የእሱን ጉብዝና በቃል አይገለጥም። በሁሉም ትምህርት የላቀ ተማሪ ነበር። ማንም የማይሰተካከለው ሰው ነው። እንደሱ አይነት አእምሮ ያለው ሰው አይቼ አላውቅም" አለኝ

"ደግሞ ጉብዝናው በትምህርት ብቻ አይደለም። ኳስ ሲጫወትም ጎበዝ ነው። የእጅ ኳስም ይጫወት ነበር። ደግሞ በጣም ትሁት ነበር" አለን።

መቼስ "ታድሎ" ከማለት ውጭ ምን ይባላል?

እኔ ጌታሁን ካለው አቅም ሩቡ ቢኖረኝ ትሁት አልሆንም። በትዕቢት አገር አተራምስ ነበር።

በኢኮኖሚ ተሳክቶለታል። እውቀቱን ነው ወደ ገንዘብ የመነዘረው። ይህ በጣም ጥቂቶች ብቻ ያሳኩት ነገር ነው።

አዋቂ ነው ሲባል የእውነት አዋቂ ነው። ፍቅሬ ቡንጤ እንደመሰከረለት ከልጅነቱ ጀምሮ ሰቃይ ተማሪ ነበር።

ሰው ሲያከብር ከልቡ ነው። ታናናሾቹን ጭምር ያከብራል። ወደ ታናናሾቹ ዝቅ ማለት ያውቅበታል።

ከልቡ ትሁት ነው።

መንፈሳዊ ነው።

እኔ ጉራ ከምነፋባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ "ከጌታሁን ጋር እተዋወቃለሁ" የሚል ነው። በጣም ለብዙ ሰዎች ከጌታሁን ጋር ምሳ በልተን እንደምናውቅ አውርቻለሁ። ሲቪ በሉት።

ለመጀመሪያ ጊዜ ስሙን በሬዲዮ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ሳከብረው ኖሬያለሁ።

መከበርም ፥ መወደድም ፥ መደነቅም እኩል የሚገባው ሰው ነው። ሶስቱንም እኩል የምንሰጠው በጣም ለጥቂት ሰዎች ነው። ከነኚያ መካከል አንዱ ጌታሁን ሄራሞ ነው


@Tfanos
ጊዜን ማስተዳደር
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ነብስ ካወቅንበት ጀምሮ ያለውን ዘመን እናስላው። ጊዜው እንደሸማኔ መወርወሪያ ይሮጣል። በአይን ጥቅሻ ዘመን ይከንፋል። እድሜ ይጣደፋል።

ቅርብ ጊዜ አይደል ልጆች የነበርን?

ጊዜን እንዳይባክን የሚያደርገው ምን ይሆን?

ጊዜ የላቀው ሀብት ነው። አያያዙን ላወቁበት በስኬት የሚመነዘር፥ ላላወቁበት የነገ ውድቀትን የሚያዋልድ ነው።... ጊዜን እንዴት እናስተዳድር?

ርዕሱን የዘነጋሁት ፀሐፊ ራስን ማስተዳደር የሚል መፅሐፍ አለው። ጊዜ አጠቃቀምን በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርት አስፍሮ አንብቤ ነበር። (መፅሐፉን 2010 አከባቢ ነው ያነበብኩት)

ጊዜያችንን የሚበለው ድርጊታችን ነው። ድርጊታችንን ደግሞ በአራት መደብ መክፈል እንችላለን።

በወፍ በረር እንያቸው።

ሀ፥ አጣዳፊ ያልሆነ ፥ ደግሞም የማያስፈልግ።
ይህን በተመከተ ማብራሪያ ያስፈልግ ይሆን? አንድ ጉዳይ አስፈላጊም አስቸኳይም ካልሆነ ጉልበታችንን ልናባክንት እንደማይገባ ነጋሪ አያስፈልገንም። ይልቅ ወደ ቀጣዩ..

ለ፥ አጣዳፊ የሚመስል ዳሩ ግን የማያስፈልግ

እንዲህ ያለው ነገር የብዙ ወጣቶችን ጉልበት ይበላል። ጊዜን ያበክናል። ሱስ አይነተኛው ምሳሌ ነው። አስፈላጊነቱ ምንም ነው። ነገር ግን ያጣድፋል፥ ያቻኩላል። "አሁን ካልሆነ" ይላል። ለእንዲህ አይነቱ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው እድሜን ያበክናል። እርጅናን የምሬት ያደርጋል።

ሐ፥ አጣዳፊ ደግሞም አስፈላጊ

ይህች ጉዳይ ሁሉንም የምትሸውድ ናት። ጊዜን ለማስተዳደር የላቀው መንገድ እንዲህ ባለው ጉዳይ ላይ ማተኮር ይመስላል። አስገራሚው ነገር ግን አጣዳፊ ጉዳዮች ጊዜን አባካኝ መሆናቸው ነው።

አጣዳፊ እና አስቸኳይ ጉዳዮች በእለት ተዕለት ጉዳዮች ቢዚ ያደርጉናል። በጥቃቅን ነገሮች እንድንወጠር ያስገድዱናል። ጊዜያችንን የሩጫ ያደርጉታል። እንደባከንን ዘመናችንን ሊጨርሱት ይችላሉ።

መ፥ አጣዳፊ ያልሆነ ነገር ግን የሚያስፈልግ

በዚህ ነጥብ ላይ ማተኮር የሚችሉ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። አስተዋዮች ዋነኛ ትኩረታቸው አጣዳፊ ያልሆኑ ነገር ግን አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ነው። ይህ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል። ደግሞም ስኬታማ ያደርጋቸዋል።

የመጨረሻዎቹን ሁለት ነጥቦች (ሐ እና መ) ግልፅ የሚያደርግ ምሳሌ እናምጣ

በትምህርት መጀመሪያ ለፈተና መዘጋጀት አስፈላጊ ነገር ነው። ነገር ግን አጣዳፊ አይደለም። በአመቱ መጨረሻ ላይ ለሚደረግ ፈተና መስከረም ላይ መዘጋጀት አስቸኳይ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን አስፈላጊ ነው። (አጣዳፊ ያልሆነ ነገር ግን አስፈላጊ)

በአመቱ መጨረሻ ለፈተና መዘጋጀት አስፈላጊ ነው። ደግሞም አጣዳፊ ነው። (አስፈላጊና አጣዳፊ)

ከላይ እንዳነሳነው ለስኬት የሚረዳው እና የተሻለ የጊዜ መጠቀሚያ መንገድ አጣዳፊ ያልሆነ ነገር ግን አስፈላጊው ላይ ማተኮር ነው።

የላቀው ተማሪ በአመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ለፈተና ይዘጋጃል። የፈተናው ወቅት ሲደርስ ለክለሳ የሚሆን የተትረፈረፈ ጊዜ ይኖረዋል። ራሱን ጫና ውስጥ አይከትም። ተረጋግቶ ለፈተና ይቀመጣል።

ፈተና ሲደርስ የሚያጠናውስ? ሩጫ ይበዛበታል። ለክለሳ የሚሆይ ጊዜ አይኖረውም። ውጥረት ውስጥ ስለሚገባ መረጋጋት ሊቸገር ይችላል።

(በእርግጥ ልዩ ሁኔታዎች ከግምት ይገባሉ)

ብዙ ሰው አጣዳፊ እና አስፈላጊ በሆነው ጉዳይ ላይ ሲዳክር ጊዜ ያመልጠዋል። አጣዳፊ እና አስፈላጊ ነገሮች ደግሞ ያደረ የቤት ስራ ውጤት የመሆን እድላቸው ቀላል አይደለም። አስፈላጊ ነገር ግን የማያስቸኩሉ በሆኑበት ወቅት ላይ "ጊዜ አለኝ" በሚል መዘናጋት ሳይሰሩ ይቀራሉ። በመጨረሻም ሩጫ ያስከትላሉ።

ተጨማሪ ምሳሌ፥

ስፖርት መስራት ለጤና አስፈላጊ ነው። ግን ደግሞ አጣዳፊ አይደለም።

አንድ ወጣት ዛሬ ስፖርት ሳይሰራ ቢቀር በማግስቱ ደም ግፊት አይዘውም። ስለዚህ አስቸኳይ አይደለም።

አንድ ወጣት ስፖርት ሳይሰራ ፥ እንቅስቃሴ ሳያደርግ እድሜውን ቢገፋ እና ለአላስፈላጊ ውፍረት ቢዳረግስ? ከዛጋር ተያይዞ የጤና መታወክ ቢከተልስ? ያኔ ስፖርት መስራት አጣዳፊም አስፈላጊም ጭምር ይሆናል ማለት ነው። ብዙ ጫና ተከትሎ ይመጣል። ምናልባትም ኢኮኖሚ ይናጋል።

ወጣቱ ቀድሞ ስፖርት የሚሰራ ቢሆን ቀጥሎ የሚመጣውን ቀድሞ ያግደዋል። ጊዜውም በአግባቡ ተጠቀመ ማለትም አይደል?

የፃፍኩት ግልፅ ነው? ዝም ብዬ ዘበዘብኩ ወይስ ሃሳቤን በትክክል ገለፅሁ?

ማለት የፈለግሁት በአጭሩ ልድገመው።

ጥሩ ጊዜ ማስተዳደሪያው መንገድ አስቸዃይ እና አስፈላጊ የሆነው ላይ ማተኮር አይደለም። የተሻለው መንገድ አስፈላጊ ነገር ግን አስቸኳይ ያልሆነውን በአግባቡ መስራት ነው። ያኔ አስፈላጊ እና አጣዳፊ በሆኑ ነገሮች የመዳከር እድል ይቀንሳል


@Tfanos
መንጌ፥ ሐገር ወዳዱ...
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ጓድ መንግስቱ ሃይለማርያም ልደታቸው ተከበረ። "ቆራጡ መሪ" ተብለው ሲወደሱ ከርመው ሐገር ጥለው የሸሹት መንጌ ልደታቸው ተከበረ።

ስለመንግሥቱ ሲወራ "ሐገር ወዳዱ" ይባላል። ሐገር ምንድነው? የመንግስቱን ስርኣት የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች እንምዘዝ። (ሐገር ወዳድ ተብዬው ሰው ሐገር አፍራሽ ስርኣት መገንባቱን በጥቂት ምሳሌ...

1፥ መንግስቱ ወልዴ የተባለ አንድ መፅሐፍ ነጋዴ ነበር። መንግስትን የሚቃወም ፅሁፎች ትበትናለህ ተብሎ በቁጥጥር ስር ዋለ። ቀጥሎ አንድ አብዮት ጠባቂ ከላይ እስከታች በጋዜጣ አስጠቅለለው። ከዛም ነዳጅ አርከፍክፎ አቃጠለው፡፡ አዎን ሰው በእሳት ተቃጥሎ ተገደለ። መንግስቱ ሀይለማርያም መራሹን መንግስት የሚቃወም ፅሁፍ ይበትናል ስለተባለ ይህን ቅጣት ተቀበለ

2፥ አብነት ሰፈር አከባቢ አንድ አስር አለቃ እንደልቡ ይፈነጭ ነበር፡፡ አካም ቡልቲ በሚል ቅፅል ስም የሚጠራ ሰውን ገደለው። በመግደል አላበቃም (በወቅቱ ደርግን ይቀወማሉ የሚባሉ ሰዎችን መግደል ተአምር አይደለም)። የሟች አስከሬን ቤተሰቦቹ ደጅ ላይ ተቀበረ። መውጫ መግቢያ በራቸው ላይ የልጃቸው አስከሬን ተቀበረ! ከዚህም የተነሳ የሟች አባት አበደ፡፡ ጨርቁን ጣለ፡፡ የአእምሮ ህመም ገጠመው
(ሁለቱም ታሪኮች ማዕቀብ በሚለው የእንዳለጌታ መፅሐፍ ላይ ተካተዋል-

3፥ ሻለቃ መላኩ ተፈራ ከዝነኛ የደርግ ሹማምንት መካከል አንዱ ነው። የስመጥርነቱ መንስኤ የአመራር ብቃቱ ሳይሆን የጭካኔ ደረጃው ነው።
ጎንደርን ሲያስተዳድር የጭካኔ መዋቅር ዘረጋ። ልዩ እስር ቤት አቋቋመ፥ ተጠርጣሪዎች የሚሰቃዩበት የምርመራ ክፍል አደራጀ፡፡
ደግሞ ከእርሱ ትዕዛዝን የሚቀበል መቺ ኃይል መሰረተ፡፡

'ፀረ-አብዮት' ተብለው የሚፈረጁ ሰዎች ቅጣታቸው ግልፅ ነው። ይገደላሉ! በቂ የወንጀል ማስረጃ እንደሌለባቸው እየታወቀ እንኳ ያለ ርህራሄ ይገደላሉ።

የገጠር ነዋሪዎች ወደ ከተማ ያለ ልዩ ፈቃድ ወደ ከተማ እንዳይገቡ እገዳ የጣለ ሰው ነው።

'ደርግን ተቃውመዋል' የተባሉ ዜጎችን ሲለው 'በእስራት ይቀጡ' ይላል። ካሻው የጅራፍ ግርፋትን ይወስናል። ሲፈልግ ደግሞ በስቅላት ያስገድላል። ስቅላት ሲሰለቸው በጥይት ያስደበድባል።

ሻለቃው ጭካኔው ድንበር የለሽ ቢሆንም የደርግ መንግስት "ቆራጥ፥ ታጋይ ፥ አብዮተኛ ወዘተ " በማለት በ1980 አ.ም ሸልሞታል። ሽልማቱን የቸረው ደግሞ መንግስቱ ሃይለማርያም ነበር። (ሽልማቱ ለጭካኔህ አመሰግናለሁ ማለት መሆኑ ነው)

4፥ በዘመነ-ደርግ ሕዳር 14 ቀን 1967 አ.ም በተለምዶ 60ዎቹ የሚባሉት እና በአንድ ጀንበር የተገደሉ ሰዎች አሉ።

ደርግ ያለ በቂ ምክኒያት ሰዎችን ከመረሸኑ በፊት ስለ-ሰዎቹ እጣ ፈንታ ስሜት የተጫነው ውይይት ያደረገ ሲሆን መገደላቸውን ብርሃኑ ባየህ ብቻ መቃወሙን ፍቅረስላሴ ወግደረስ ፅፏል። ብርሃኑ ባየህ "ግድ የላችሁም ሕጋዊ መንገድ እንጓዝ፥ ፍርድ ቤት ይወስን፥ ሕግ ነፃ ካደረገ ነፃ ይሆኑ፥ ከቀጣቸው ይቀጡ። እኛ ግን ስልጣናችንን ተጠቅመን መወሰን የለብንም" ብሎ የነበረ ቢሆንም ሰሚ አላገኘም። ሰዎቹ ተረሸኑ።

ጎህ መፅሔት ቆየት ባለ እትሙ ያልተለመደ ጉዳይ ስለሟቾቹ አስነብቦ ነበር። አስር አለቃ ደሳለኝ 'ሰዎቹን የገደልኩት እኔ ነኝ' ካለ በኋላ ዝርዝሩን አብራርቷል።
ጓድ መንግስቱ "ልዩ ተልእኮ አለ፥ ይህን በአግባቡ ከፈፀማችሁ ሽልማት አላችሁ ካለን በኋላ እኔና ጓደኛዬ ለተልእኮ ተሰማራን" ብሏል። መንግስቱ ሰዎቹ በቀጥታ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲገደሉ አስደረገ።

"ሐገር ወዳዱ" የሚባለው መንግስቱ በስልጣን ዘመኑ አንድ ትውልድ ፈጅቷል። ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣቶችን ፥ የሐገር ባለ ውለታ አባቶችን ፥ ባለ ተስፋ ተማሪዎችን በመደዳ ያስገደለ ሰው ነው።

ሐገር መውደድ ምንድነው?

አንባገነኖችን የማወደስ ባህል እስካለ ድረስ እስመጨረሻው ከጭቆና ነፃ አንወጣም!


@Tfanos
@Tfanos
የዛሬ ስምንት ዓመት አከባቢ ሻሸመኔ የጋዜጠኝነት ስልጠና ተሰጠ። ጣምራ ለማህበራዊ ልማት ድርጅት ነው የስልጠናው አዘጋጅ። ጣምራ "ዘመነ-ሃሊዮ" በተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራሙ ለሚሳተፉ ልጆች ፥ በኪነጥበብ ውስጥ ተሳትፎ ላላቸው ፥ የጋዜጠኝነት አቅሙ ላላቸው ወጣቶች ነበር ስልጠናውን ያዘጋጀው። (ስለጣምራ በተለይም ስለ ስራ አስኪያጁ ብሩክ ሌላ ጊዜ እፅፋለሁ)

አሰልጣኛችን ጋዜጠኛ አዳነ አረጋ ነበር። አዳነ ጥያቄ ጠየቀ። "የምትወዱት ጋዜጠኛ ማን ነው?" አለ። ሁሉም የሚወደውን ስም ጠቀሰ። የመአዛ ብሩ፥ የመንሱር አብዱልቀኒ እና የደረጀ ሀይሌ ስም በደንብ ተጠቀሰ። የኔ ተራ ደረሰ። አልዓዛር አስግዶም አልኩ። ለአዳነ አረጋ ቃል በቃል "ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጋዜጠኛ የሚባለው አልዓዛር ነው " አልኩት።

አዳነ ስለ አልዓዛር ነገረን። "በጣም ትሁት ሰው ነው። ስራውን ይወዳል። ያነባል። ጠቅላላ እውቀቱ የሚገርም ነው። ስለየትኛውም ጉዳይ በእኩል አቅም ያስረዳል" አለ። የአልዓዛርን ስልክ ሰጠኝ። በስንተኛው ቀን ለአሊዝ ደውዬለት ጥቂት አወራን። (ጥቂት ሲባል ሰላሳ ደቂቃ ገደማ ነው😀)
የደወልኩለት ቀን ስፖርት 365 ላይ ከአዩ ወልደሚካኤል ጋር በቬንገር ጉዳይ ተጨቃጭቀው ነበር። አሊዝ በጣም ስሜታዊ ሲሆን ያስታውቅበት ነበር። ለቬንገር ተገቢው ክብር አለመሰጠቱ አበሳጭቶት ነበር።

ከአእምሮዬ የማይጠፉ የአልዓዛር ስራዎች አሉ።

"ፋና ዳሰሳ" ከምወዳቸው የሬዲዮ ፕሮግራሞች መካከል ነው። በተለይ ተስፋዬ አለነ የሚሰራቸው ዳሰሳዎች ደስ ይሉኝ ነበር።አርብ በደረሰ ቁጥር በጉጉት የፋናን ዳሰሳ እሰማለሁ። ማጀቢያው ጭምር ደስ ይለኛል። አንድ ቀን አልዓዛር ዳሰሳ ሰራ። ከዛ በፊት በዳሰሳ ሰምቼው አላውቅም። የሰራው ስለ ፊፋ ቅሌት ነበር። ገረመኝ። የርዕሰ ጉዳይ ምርጫው አስገረመኝ። አለም አቀፍ ፖለቲካ በሚተነተንበት ፕሮግራም የእግርኳስን ፖለቲካ በውብ አቀራረብ ተነተነው። እግር ኳስ ከእግርኳስም በላይ እንደሆነ አሳየ። ከዛን ጊዜ በኋላ የአሊዝን ዳሰሳ በጉጉት የማደምጥ ሆንኹ።

ባርሳ ከ ፒ ኤስጂ ጋር ተጫውቶ ውጤት የቀለበሰበትን ቀን የትኛውም የእግር ኳስ ተመልካች አይዘነጋውም። ከጨዋታው እኩል የማይዘነጋ ፕሮግራም አልዓዛር ሰርቷል።

የፕሮግራሙ መግቢያ.. 👇

"ሰው እሱ ማንም ቢሆን 22 ተጫዋቾች ቅሪላ የሚላፉበት ዋዘኛ ጨዋታ ነው ቢላችሁ አትስሙ፥ ስራ ፈቶች ዝርጉን አረንጓዴ ንጣፍ በሺ ስፍር በከንቱ ይከቡታል ቢሉ እሱም እውነት አይደለም። ቢሊየን ሰዎች በሁሉም የኑሮ መደብ ያሉ እግርኳስን አቅልን በመሳት ወሰን ሆነው ቢወዱ፥ በሃሴት እና በስብራት ጊዜ ለምን የእንባ ዶፍ እንደሚያዘንቡ ግራ ቢገባቸው የትላንቱን የጨዋታ ምስል ስጧቸው።.... እኔ እግርኳስን ስለትላንቱ ምሽት እወዳለሁ" ብሎ ይጀምራል ዘገባው። ይህ ዘገባ ከተሰራ ሰባት ወይ ስምንት አመት ቢሆነውም አይረሴ የአሊዝ ስራዎች መካከል ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስልጣን ሲመጣ (የዛሬ 9 አመት) አልዓዛር በፋና መፅሔት ዳሰሳ ሰርቷል። ከዛ በፊትም ሆነ ከዛ በኋላ አልዓዛር በ90 ደቂቃ እና በ120 ደቂቃ ዝግጅቶች እንጂ በምሳ ሰአት ዜና ሰምቼው አላውቅም ነበር። ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠበት ቀን ልዩ ክስተት ነበር። በዛ ልዩ ክስተት አልዓዛር የምሳ ሰአት ትንታኔ ሰራ። (ምናልባት ለልዩ ቀን ልዩ ሰው ተመርጦ ይሆናል)

በፋና ኤፍ ኤም ስፖርት 365 ን ረጅም ጊዜ እከታተል ነበር። ሁሴን አብዱልቀኒ ፥ አዩ ወልደሚካኤል ፥ ዳዊት ንጉሴ በጋራ ፕሮግራሙን ያደምቁታል።... በሂደት ግን ሁለቱ አዘጋጆች ከሐገር ወጡ። ሁሴን እና ዳዊት ከፕሮግራሙ ጎደሉ። ያኔ ሁለቱን የሚተካ አንድ ሰው ተከሰተ... አልዓዛር አስግዶም!

አልዓዛር በቀለም ከሁለቱም የተለየ ሆኖ ሳለ ሁለቱ የፈጠሩትን ጉድለት አስረሳ። ወዲያው ደምቆ ታየ።

ስፖርት 365 ላይ የተገኘ የመጀመሪያ ቀን የነበረው አስተያየት በሙሉ ስለ አልዓዛር ነበር። ሁሉም አድማጮች ለአልዓዛር ያላቸውን አድናቆት እና ፍቅር ይገልፁ ነበር። "ደጋግመን ልናገኝህ እንፈልጋለን ፥ እንወድሃለን ፥ የራስህ አየር ሰዓት ይኑርህ...." ወዘተ። የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ አዩ ወልደሚካኤል ከአድማጭ የተላኩ በርካታ የአድናቆት መልክቶችን ለአዓዘር ሲያቀርብ አሊዝ በትህትና "አመሰግናለሁ" ይል ነበር።

አልዓዛር አስግዶም የእርግር ኳስ ተጫዋች ቢሆን እንደ አንድሬስ ኢኒየስታ የሚሆን ይመስለኛል።

ረጋ ብሎ የሚጫወት ፥ ኳስን የሚያሾር ፥ አከባቢውን በደንብ የሚቀኝ ፥ አርቲስት ፥ ራስ ወዳድ ያልሆነ ፥ ኳስ በነካ ቁጥር ውበት የሚጨምር....

አሊዝ የጋዜጠኞች ኢኒዬስታ ነው።


@Tfanos
በፈረንጆች 2014 ብራዚል በጀርመን ሰባት ለአንድ ተሸነፈች። በማግስቱ ዮናስ አዘዘ በሬዲዮ ውጤቱን ሲገልፅ "ብራዚል ሰባት ለአንድ ተሸነፈች። አድማጮች እናቴ ትሙት ከልቤ ነው" አለ።

ጨዋታውን ያላየ ሰው ብራዚል ሰባት ገባባት ሲባል አያምንምና መሓላ ያስፈልጋል።

የዛሬውን ጨዋታ ላላየ ሰው "የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ አምስት ለምንም ተጠናቀቀ። እናቴ ትሙት በፍፃሜ ጨዋታ ፥ ያውም በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ አምስት ጎል ገባ" ተብሎ ይነገራቸዋል።

ሊዊስ ኤኔሪኬ እንኳን ደስ ያለው
የብልፅግና ካድሬዎች ጀዋር መሐመድ እንዳበቃለት ይነግሩናል። "ከዚህ በኋላ ተፅዕኖ አይፈጥርም፥ ምንም አያመጣም" ይላሉ።

ደግሞ ጀዋርን ሲረግሙት ፥ ሲሳለቁበት ፥ ሲያብጠለጥሉት ፥ በኮሜንት ሲዘልፉት ይውላሉ።

ምንም አያመጣም ካሉ ለምን ንቀው አይተውትም?

የማይፈሩት ከሆነ እየደጋገሙ አንፈራህም ማለት ለምን አስፈለጋቸው?

@Tfanos
መንግስት "ጠመንጃ አስቀምጣችሁ በሃሳብ ሞግቱኝ" ይላል። የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ደግሞ ያስራቸዋል።

የመንግስት አካሄድ "በሃሳብ አትሞግቱኝ ፥ ጠመንጃም አታንሱብኝ የሚል ነው"


@Tfanos
"ሰው ማለት"

ቀን ብርሃን ሳለ
አብሮህ እየዋለ
አብረህ የምትውለው
ሰው ማለት ጥላ ነው።

አዎ - ጥላ
አጅቦህ የሚውል ከፊትና ኋላ
ኋላም ላይ 'ሚሰወር ፈፅሞ የሚሸሽ
ዙሪያህ ሲጨላልም ቀኑ ደግሞ ሲመሽ

ደግሞህ ከሸሸበት መልሶ 'ሚመጣ
ጨለማው ሲገፈፍ ፀሐይ ስትወጣ

ሰው ማለት ጥላ ነው
አዎ........ ጥላ

(ዘሪሁን ገብረጊዮርጊስ "ሳቅ ያፈናቸው ስንኞች" ገፅ 54)


@Tfanos
ቴዲ ፀጋዬ ልደቱ ነው። እንኳን ተወለደ። እኔ ከEbs ጀምሮ ተከታታዩ ነበርኩ። የማይረሱ ብዙ ፕሮግራሞችን ሰርቷል። (ለወደፊት ስለሱ እፅፋለሁ

አማርኛን የሚያዝበት መንገድ ደስ ይላል። በሐገራችን በጣም ጥቂት ምርጥ ገጣሚያንን ከጠራን አንዱ ቴዎድርስ ፀጋዬ ነው። ምርጥ የግጥም መድብል ከጠራን የቴዲ ፀጋዬን መድብል መዝለል አንችልም።

ቴዲ የተለዩ እና አይረሴ አገላለፆች አሉት።

ጥቂቶቹን እናስታውስ...

"ዶክተር ደብረፂዮን ማለት የችግር አንቴና ነው"

"ህወሃት ማለት ከድል ማህፀን ሽንፈት የሚያዋልድ ፓርቲ ነው"

"ህወሃት ሀይማኖት ነው። መሪዎቹ የሀይማኖቱ መሪዎች ናቸው። መለስ ዜናዊ ደግሞ የሀይማኖቱ አምላክ ነው። ህወሃት አሁን አምላኩ የሞተበት ሀይማኖት ነው"

"የዶክተር አብይን ድምፅ መስማት የስነልቦና ጥቃት ማስተናገድ ነው"

"ለኢያስፒድ ተስፋዬ ስራ ካገኘልኝ ሲቪዬን እልክለታለሁ። ስራው ግን የጀዋር መሀመድ ጫት ቀንጣሽነት መሆን የለበትም"

"ተመልካቾች ከዚህ ቀጥሎ አስፈሪ ነገር ልናሳያችሁ ስለሆነ ይቅርታ። መጥፎ ነገር ማየት የማትፈልጉ አሳልፉት።... የአብይ አህመድን ንግግር ልናሰማችሁ ስለሆነ ይቅርታ"

....
😎


@Tfanos
የድሬዳዋ ከንቲባ የትግራይን ህዝብ "ከሰይጣን የባሱ ናቸው" ብሎ ነበር። ያውም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርቦ።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጃኒን እንደከሰሳት ሁሉ የድሬዳዋው ከንቲባም መከሰስ ነበረበት። ነገር ግን እስከአሁን ምንም አልተባልም። በስልጣኑም ቀጥሏል።

ምን ማለት ነው?

1፥ ባለሥላናት ያሻቸውን ማድረግ ፥ የፈለጉትን ህዝብ መስደብ መብታቸው ነው። ወገኔ የሚሉት ሲነካ ግን የመክሰስ ሰልጣን አላቸው።

2፥ መንግስት ትኩረት የሚሰጠው መርጦ ነው። አንዱ ወገን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ሲሰደብ ዝም ይላል። ሌላው ሲሆን ደግሞ በቲክቶክ ለተሳደበው ይጠየቃል።

3፥ ሕግ የሚሰራው ቲክቶከር ላይ እንጂ በቴሌቪዥን አይተገበርም።

4፥ ሁሉም መልስ ነው


@Tfanos
ጆርዲ እና ተድላ ሰሞኑን ክርክር ለማለት የሚከብድ ክርክር አድርገው ነበር።

በሙግታቸው ካነሱት ውስጥ ትኩረቴን የሳበው በትዳር ውስጥ ያለ መደፈር ነው። በትዳር ውስጥ "መደፈር" የሚለው አገላለፅ ብዙ ሰዎች ምቾት አይሰጣቸውም። ምክኒያታቸውን እረዳዋለሁ።

መደፈር የሚለውን ቃል ሚስት ሳትፈልግ የሚደረግ ወሲብ ብለን እንያዘውና አንድ ታሪክ እናንሳ። እውነተኛ ታሪክ ነው።

አንዲት ባለትዳር ሴት አለች። ከሆነ ጊዜ በኋላ ከባሏጋ ወሲብ ለመፈፀም መቸገር ጀመረች። ግኑኝነቱን ማሰብ ጭምር ያስጨንቃታል። ገና ወሲቡ ሲጀመር መቀመጫዋ አከባቢ ሀይለኛ ህመም ይሰማታል። ወገቧን ያማታል። ወሲብ በራሱ ስቃይ ይሆንባታል።

ነገሩ ግራ ሲያጋባት ወደ ጤና ተቋማት አመራች። ህመም የለብሽም ተባለች። በተደጋጋሚ ትመረመራለች ህመም የለብሽም ትባላለች።

በመጨረሻም የስነልቦና ባለሞያ ዘንድ ሄደች። ህመሟ ተገኘ። የልጅነት ጠባሳ ነበር።

በልጅነቷ እድሜ አያቷ አስገድዶ ሊደፈራት ይሞክር ነበር። አያቷ በመቀመጫ በኩል ሊገናኛት በተደጋጋሚ ሞክሯል። ያ ተደጋጋሚ ጥቃት የስነልቦና ጠባሳ ፈጠረባት።

አድጋ ቤተሰብ ከመሰረተች በኋላ የተዳፈነው የስነልቦና ችግር ተቀሰቀሰ። ህመሟ አገረሸ። ወሲብ ማለት ህመም ሆነባት።

ሰዎች በተለያየ ምክኒያት የወሲብ ፍላጎታቸውን ያጡታል። አንዱ ምክኒያት የስነልቦና ችግር ነው። አንዳንዶች በወር አበባ ወቅት እና በአካላዊ የጤና ችግር ወቅት ካልሆነ በቀር ሚስት ለወሲብ ፈቃደኛ መሆን አለባት ይላሉ።

እርግጥ የስነልቦና ችግርን እንደ ጤና ችግር አንረዳውም። ብዙ ሰው ህመም የሚመስለው አካላዊ ህመም ብቻ ነው። ሴቷ በህመም ወቅት ልንረዳት ይገባል የሚል ሰው ስነልቦናዊ ጉዳይን ለመረዳት ፈቃደኝነት ሊኖረው ይገባ ነበር።

"በትዳር ውስጥ መደፈር የለም" የሚል መሟጓቻ ያላችሁ ሰዎች ምን እያላችሁ እንደሆነ እረዳለሁ። ነገር ግን በትዳር ውስጥ መደፈር አለ የሚሉ ሰዎች ምን እያሉ እንደሆነ ልትረዱ ይገባል። ባልተወሳሰበ አማርኛ "ሴቷን ተረዱ" እያሉ ነው።

በሰው ህይወት ብዙ ውስብስብ ገጠመኞች ይኖራሉ። ወሰብሳቤ ገጠመኞች ስነልቦናችን ላይ የራሳቸውን አሻራ ያኖራሉ። ያን ለመረዳት መሞከር ጥሩ ነው።

ሴቶች ባል ካገቡ በኋላ ለወሲብ ፍላጎት ቢያጡ መፍትሄው "ወሲብ ግዴታሽ ነው" ማለት አይመስለኝም። ሁኔታዋን ለመረዳት መሞከር እና በጋራ መፍትሔ መፈለግ ነው።

የሴቶች አጀንዳ ወደ አደባባይ መውጣቱ ጥሩ ነው። በብሽሽቅ እና ለመሸናነፍ በመሞከር ነገሩን ማወሳሰብ አይበጅም። ወንዶች ሴቶች ምን እያሉ እንደሆነ ለመረዳት በመሞከር ከፊል ችግሩን ማቅለል እንችላለን

Via ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
@Tfanos
2025/06/13 11:47:57
Back to Top
HTML Embed Code: