Telegram Web
TIKVAH-ETHIOPIA
" ከተለጠፈዉ ማስታወቂያ በዘለለ የአፍ ዛቻና ማስፈራሪዎችም ስላሉ በርካታ ኢንተርን ሃኪሞች ግቢውን ለቀን ወጥተናል " - ኢንተርን ሃኪሞች በሰሞነኛዉ የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ሰፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ከድንገተኛና ማዋለጃ ክፍል ሃኪሞች በስተቀር ላለፉት ሶስት ቀናት የሆስፒታሉ ሬዝደንት እና ኢንተርን ሃኪሞች ስራ ማቆማቸዉን ለመረዳት ተችሏል። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ…
" ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢለጠፉም የተመለሰ ባለሙያ የለም " - የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ሪፈራል ሆስፒታል ሬዝደት እና ኢንተርን ሐኪሞች

ከቀናት በፊት በሰሞነኛዉ የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ ምክንያት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ሪፈራል ሆስፒታል ሬዝደንትና ኢንተርን ሐኪሞች በከፊል ስራ ማቆማቸዉን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዉ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያዎችን ያወጣ ቢሆንም የወጡ ሐኪሞች አለመመለሳቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

" ማስጠንቀቂያዉ የሙያ ክብራችንንና አገልግሎታችንን የማይመጥን ከመሆኑም በላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የታከለበትና የሬዝደንት እስር ያስከተለ ስለነበር ካሳለፍነዉ ሐሙስ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ስራ ለማቆም ተገደናል " ብለዋል።

" እስከ ትናንት ድረስ አንድ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ታካሚን ከሚከታተል ሬዝደንት ሐኪም በስተቀር ሁሉም ኢንተርንና ሬዝደንት ሐኪሞች ሆስፒታሉን ለቀዉ መወጣታቸውን የሚያስረዱት ሐኪሞቹ በአካዳሚክና ብቃት ማነስ የተባረሩ ሬዝደንት ሐኪሞችን ለመመለስ የመሞከር አዝማሚያዎችን ዉስጥ ካሉ ተማሪዎች ሰምተናል " ሲሉ ገልፀዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀዋሳ ዩንቨርሲቲ የሴኔት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በትምህርት / በስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ኢንተርንና ሬዚደንቶች ዛሬ ሰኞ ወደ ትምህርታቸውን እማ ስራቸው በመመለስ በየትምህርት ክፍሎቻቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ በጥብቅ አሳስቧል።

ወደ ትምህርት/ስራ ገበታቸው የማይመለሱ ከሆነ ከግንቦት 12/2017 ዓ/ም እስከ ሀሙስ ግንቦት 14/2017 ዓ/ም ድረስ ብቻ የይቅርታ ደብዳቤ በማስገባት ወደ ትምህርታቸው /ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ፈቅዷል።

በተጠቀሱት ቀናት ወደ ትምህርታቸው/ስራ ገበታቸው በማይመሱ ተማሪዎች ላይ የሴኔት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የመጨረሻውን ህጋዊ አርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ማኔጅንግ ዳይሬክተር ዝናዉ ሳርምሶ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፥ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች ሀገራዊ እንደምታ እንዳላቸዉና በፌዴራል መንግስት የሚመለሱ እንዳሉ ሆነዉ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ መመለስ የሚችሉ ጉዳዮችን ለመመለስ ዩኒቨርሲቲው ስራዎችን እየሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ካሳለፍነዉ ሐሙስ ጀምሮ በሆስፒታሉ የሬዚደንት እና ኢንተርን ሀኪሞች ስራ ማቆማቸውን ያረጋገጡት አቶ ዝናዉ " ይቅርታ ጠይቀዉ እንዲመለሱ የወሰነው ሴኔት ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሃዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
" የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል " - ማኅበሩ

የኢትዮስፕየ ነርሶች ማህበር ፥ የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ገለጸ። ጥያቄ ስለጠየቁ የታሰሩ ባለሙያዎች እንዲፈቱ እንዲሁም ዛቻና ማስፈራሪያዎች እንዲቆሙ ጠይቋል።

ማህበሩ ይህን ያለው በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እየተካሄደ ባለዉ የጤና ባለሙያዎች ወቅታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ በላከው መግለጫ ነው።

ማህበሩ ፤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለደረሰው የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል።

ማህበሩ ምን አለ ?

- በአሁኑ ሰዓት እየተነሱ ያሉት የባለሙዎቹ እና የማህበሩ አባላት ጥያቄዎች ማለትም፦
• የተቋማት ግብዓት እጥረት መኖር
• የደመወዝ ማነስ
• የጥቅማጥቅም አለመኖር
• የትምህርት እድል እና የደረጃ እድገት አለማግኘት
• የስራ ቦታ ደህንነት አለማግኘት ... ለረዥም ጊዜያት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለውይይት ሲቀርቡ እና አጀንዳ ሆነው የቆዩ መሆናቸውን ገልጿል። ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑም ሁኔታው የመንግስትን ትኩረት እንዲያገኝ ጠይቋል።

- " የህክምና አገልግሎት ተቋርጦ ወይንም ተስተጓጉሎ ጥያቄ ማቅረብ የጤና ተቋማቱም ሆነ ጤና ሙያተኛው ማዕከል የሆኑትን ታካሚዎች ለሞት ለእንግልት የሚዳርግ በመሆኑ የምንቀበለው አይደለም " ያለው ማህበሩ " ስራዎቹ በአስቸኳይ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሙያተኞቹ፣ የተቋማት ሃላፊዎችም ሆነ ጤና ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ውይይት እና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ " ሲል ጠይቋል።

- " ጥያቄ ጠይቃችኋል " ወይም " አስተባብራችኋል " በሚል ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች እንዲፈቱ ፤ በተቋማትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ዛቻና ማስፈራሪያዎችም እንዲቀሙ ጠይቋል።

- ጥያቄ ያላቸው ነርሶችም ሆነ ሌሎች ሙያተኞች ለውይይት በሚዘጋጁ መድረኮች በመገኘት ጥያቄአቸውን እንዲያቀርቡ እና ለመፍትሄ ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቋል።

#EthiopianNursesAssociation

@tikvahethiopia
#Tigray

ሾልኮ የወጣው ሚስጥራዊው ሰነድ ምንድነው ?

" የጊዚያዊ  አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት በመሆናቸው ብቻ ያወቁትን ሚስጥር እሰከ መጨረሻ መጠበቅ ሲገባቸው ለርካሽ ገበያ አቅርበዋል " - የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት

➡️ " ጥቂት ወንጀለኞችን ለማዳን ሲባል በህዝብ ስም መነገድ ይቁም " - አቶ ጌታቸው ረዳ


የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ፅህፈት ቤት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ  ፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የተናገሯቸውን ንግግሮች አስመልክቶ የተቃውሞ መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫው አቶ ጌታቸው ለፋና ቴሌቪዥን የሰጡትን ቃለመጠይቅ " የህግ ልዕልና ለማረጋገጥ ያለመ ሳይሆን የህዝቡን የትግል ታሪክና ቀጣይነት የሚያጎድፍና የሚያጨልም በቂም በቀል የታጨቀ ነው " ሲል ገልፆታል። 

" በስልጣን ቆይታቸው የታዩ ወድቀቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ አካል ሲያላክኩና ከሳሽ ሲሆኑ ሰንብተዋል " ያለው ፅ/ቤቱ " ይህ ወደ ሚድያ ፕሮፓጋዳ የወረደ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው " ብሏል።

የፅ/ቤቱ መግለጫ ፤ አቶ ጌታቸው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስመልክቶ በብዙ ጥረት ተጠንቶ ወደ እጃቸው የገባ ኮፒ ያልተደረገ ሰነድ በወቅቱ ተጠያቂነት ሳያረጋግጡ ቀርተው አሁን በማህበራዊ ሚድያ እንዲሰራጭ አደርገዋል ሲል ይከሳል።

" ይህ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ሊያጠቋቸው የፈለጓቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ  ያነጣጠረ ሳይሆን ፍትህና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚጎዳ በጥናቱ ተሳትፎ የነበራቸውና አካላትና ቤተሰቦቻቸው ጭምር ለአደጋ የሚያጋልጥ የነውር ነውር ነው " ሲል በምሬት ወቅሷል።

" የጊዚያዊ  አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት በመሆናቸው ብቻ ያወቁትን ሚስጥር እንደ አንድ የህዝብ ብሄራዊ ጉዳይ እሰከ መጨረሻ መጠበቅ ሲገባቸው ለርካሽ ገበያ ማቅረባቸው ማንነታቸው ያሳየ ተግባር ነው " ሲል አቶ ጌታቸው ረዳን ወርፉዋቸዋል።

የፕሬዜዳንት ፅ/ቤቱን መግለጫ ተከትለው ወድያውኑ ምላሽ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ " የተጠናው ጥናት ተተንተርሶ ወደ እርምጃ እንደማይገባ ስላወቅኩኝ ወደ ሚመለከተው የበላይ አካል መረጃውን ልኬዋለሁ " ብለዋል።

ሚንስትሩ " በጥናት ሰነዱ መሰረት ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ከሚገባ ተጠያቂዎች እንዳንዶቹ ከአገር ወጥተዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

" ' ሰው መሸጥ (slave trading in modern parlance  ) ለትግራይ ህዝብ የማይመጥን ወንጀል ነው ' የሚል አገላለፅ በፕሬዜዳንት ፅህፈት ቤት በወጣው መግለጫ የለም " ያሉት አቶ ጌታቸው " ሰነዱ ግለሰቦችን ከማጥቃት ባለፈ የህግ ልዕልና እንዲረጋገጥ ያለመ ነው " ሲሉ አብራርተዋል።  

ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ " በጥናት ሰነዱ የተቀመጠው ሃቅ ነው ጥቂት ወንጀለኞች ለማዳን ሲባል በህዝብ ስም መነገድ ይቁም " ብለዋል።

ሚስጥራዊ ሰነዱ ምንድነው ?

ከሰሞኑን አንድ ሚስጥራዊ ሰነድ ሾልኮ ወጥቶ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። በማህበራዊ ሚዲያዎችም በርካቶች እየተቀባበሉት ይገኛሉ።

ሚስጥራዊ ሰነዱ ፥ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር (በብዛት ኤርትራውያን በህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር የሚመለከት) እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተጠና ሰነድ ሲሆን በ4 ክፍሎች የተከፋፈሉ 69 ገፆች አሉት።

በሰነዱ በጥናት የተለዩ የወንጀል ተግባራት ፦
- ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም
- በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በመያዝና በማዘዋወር (መኒ ላውንደሪንግ)
- ሰው ማፈንና መሰወር
- በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ከአገር ወደ አገር ማዘዋወር
- የመንግስት ስራ ምቹ ባልሆነ መንገድ መምራት
- ሃላፊነት ባልተገባ መንገድ በመጠቀም
- ሙስና

መፈፀማቸውን ያረጋግጣል።

በሰነዱ በተጠቀሱ የወንጀል ተግባራት በሰራዊት አመራር ያሉ የነበሩ የጀነራል መዓርግ ካለቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እስከ ቀበሌ አመራር ያሉ አስተዳዳሪዎች ነጋዴዎችና ሌሎች የሚገኙባቸው 231 ተጠርጣሪዎች በስምና አድራሻቸው ተጠቅሷል።

ሰነዱ በህገ-ወጥ መንገድ የተዘዋወሩ ኤርትራውያን ስም የተዘዋወሩበት ቦታና ቀን ፣ ያረፉባቸው ሆቴሎች እንዲሁም ለህገወጥ ዝውውሩ ገንዘብ ገቢ ያደረጉባቸው የባንክ የሂሳብ ቁጥሮች ሰፍረዋል።

የጥናት ሰነዱ የሰው ማስረጃ ፣ የድምፅ ቅጂ፣ እንዲሁም በድብቅ የተቀረፀ ምስል ያካተተ እንደሆነ ይዘረዝራል።

በሰነዱ በቀንደኛ ተጠርጣሪነት ከተጠቀሱት ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ የሆኑት ተወልደ ገ/ትንሳኤ (ዕምበብ) በቅርቡ ከአገር መውጣታቸው ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከፋና ቴሌቪዥን በነበራቸው ቆይታ ጠቅሰዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle

@tikvahethiopia
#SafaricomEthiopia

በሳምንታዊ ጥቅሎች ፈታ ብለን ዳታ እንጠቀም! ከጉርሻ የሳፋሪኮም ደቂቃ ጋር 🎁
በልዩ ልዩ አማራጮች የቀረበልንን የሳፋሪኮም የኢንተርኔት ጥቅል የM-PESA Appን በመጠቀም አሁኑኑ እንግዛ! በፈጣን ዳታ እንንበሽበሽ!

🔗የM-PESA ሳፋሪኮም መተግበሪያ በዚህ ሊንክ እናዉርድ: https://play.google.com/store/apps/details?id=et.safaricom.mpesa.lifestyle

#MPESASafaricom
#1wedefit
#Furtheraheadtogether
“ በትግራይ ክልል የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለማከናወን እስካሁን አስቻይ ሁኔታዎች አልተገኙም ” - የምክክር ኮሚሽኑ

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩ እንዲሁም “ጫካ ያሉና በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ” አካላት በምክክሩ አለመሳተፋቸው ፈተና እንደሆነበት ተናገረ።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፣ “በትግራይ ክልል የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለማከናወን እስካሁን አስቻይ ሁኔታዎች አልተገኙም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ያሉት ኮሚሽኑ፣ “ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የዲጂታል ሚዲያው ሚና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከዲጂታል ሚዲያው ጋር ዛሬ በኃይሌ ግራንድ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ባደረጉት ንግግር ነው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በቅርቡ አዲስ ፕሬዜዳንት ተሹሟል፤ ይህ ሂደቱን በክልሉ ለማስጀመር አስቻይ ሁኔታን አልፈጠረም ? መሰናክሎች ምንድን ናቸው? ሲል ኮሚሽኑን ጠይቋል።

ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር) ምን መለሱ?

የኮሚሽኑ ሂደት ሲጀመር ክልሉ በጦርነት ስለነበር ኮሚሽኑ ምን እንዳደረገ የመስማት እድል ክልሉ እንዳላገኘ፣ ከጦርነቱ በኋላም በትራውማ ያለ ህዝብ ስለሆነ፣ የመሰረተ ልማትና የሰላም ጥያቄ፣ የታጠቁ ወገኖችን ማምጣትና የተለያዬ ጉዳዮች ስለነበሩ ወዲያውኑ ለማከናወን ጊዜ እንደወሰደ አስረድተዋል።

አዲስ የትግራይ አመራር ከመመረጡ በፊት ከአስተዳደሩ ጋር፣ አሁንም ለክልሉ ጊዚያዊ ፕሬዜዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ጭምሮ ደብዳቤ መፃፉን፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ኮሚሽኑ እንደተነጋገረ፣ ለTPLF ደብዳቤ እንደፃፈ፣ ተገናኝቶ ለመነጋገር ዝግጅት እንዳለ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም፣ “ጊዜ ሁሉ ተቀጥሮ ተሰጥቶ በእነርሱ ሳይሆን በኛ በኩል የቲክኒካል ጉዳይ ስላጋጠሙን ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይዘናል። ግንኙነቱ ይቀጥላል” ብለዋል።

የክልሉ ስጋቶች ምንድን ናቸው? ስንል ላቀረብነው ጥያቄ ኮሚሽነሩ፣ “ስጋታቸው የፓለቲካ አለመረጋጋት ነው፤ ሰላም ወዲያው የሚመጣ ነገር አይደለምና ‘ወደ ትላንት ውስጥ እንመለስ ይሆን?’ የሚሉ ስጋቶች አሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የትግራይ ክልልን አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ለማካሄድ ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን፣ የታጠቁ አካላት አሁንም አጀንዳዎቻቸውን ለማስገባት ዝግጁ ከሆኑ የኮሚሽኑ በር ክፍት መሆኑንም በአጽንኦት አሳስበዋል።

ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር)፣ “የትጥቅ ትግል ያዋጣናል ብለው ጫካ ውስጥ ያሉ እህት ወንድሞቻችን አሉ” ብለው፣ የዲጂታል ሚዲያው አካላት እነዚህ ወገኖች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ኢትዮጵያ #ረቂቅአዋጅ

የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ መሬትን በሊዝ በባለቤትነት መያዝ የሚያስችላቸው የአዋጅ ረቂቅ ነገ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል።

የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት " ባለቤት ' ወይም  " ባለይዞታ " የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው ይህ " የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት " ወይም " ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የሚያገኙበትን " ህጋዊ አሰራር ለመዘርጋት ነው።

ረቂቅ አዋጁ ምን ይላል ?

- ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በኢትዮጵያ መሬትን፣ የመኖሪያ ቤትን ወይም ተያያዥ ግንባታዎችን በባለቤትነት ለመያዝ፤ ቢያንስ 150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሊመድቡ እንደሚገባ ይደነግጋል።

- በውጭ ዜጋ " በሊዝ ባለይዞታነት " ወይም " ባለቤትነት " የሚያዝ መሬት ወይም የመኖሪያ ቤት፤ " የማይንቀሳቀስ ንብረት " ተደርጎ ይወሰዳል። " ሊዝ "  ማለት " አግባብነት ባለው ህግ መሰረት በጊዜ በተገደበ ውል ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ዓላማ የሚውል የከተማ ወይም የገጠር መሬት የሚገኝበት የመሬት ይዞታ ስሪት " ነው።

- ማንኛውም የውጭ ዜጋ በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ሊሆን የሚችለው በአዋጁ የተዘረዘሩ ቅደመ ሁኔታዎችን ሲያሟላ ነው።

እነዚህም ፦
° የውጭ ዜጋው ስም፣ ዜግነት እና ሌሎችን ማንነትን የሚገልጹ ህጋዊ ሰነዶችን ማቅረብ አለበት።
° የውጭ ዜጋው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብት ለመሆን የሚያስፈልግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ለማሟላት የሚያስችል በቂ አቅም ያለው መሆን አለበት።
° ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለመሆን፤ የሊዝ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ ዋጋ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግዢ የሚመድበው አነስተኛ የገንዘብ መጠን ከ150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ሊሆን አይችልም።
° የውጭ ዜጋው የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆን ይገባዋል።

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ አንድ የውጭ ዜጋ ከከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚሰጥ ፈቃድ ሊያገኝ ይገባዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ " የፈቃድ ይሰጠኝ " ማመልከቻ ላቀረበ የውጭ ዜጋ፤ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ በ15 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል።

- የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከውጭ ዜጎች የሚጠበቀውን የአነስተኛ ገንዘብ መጠን ከፍ ወይም ዝቅ የሚያደርግ የእያንዳንዱን የሊዝ ቦታ ወይም ቤት ስፋት እንዲሁም የሊዝ ይዞታዎችን ወይም ቤቶችን አጠቃላይ ቁጥር የሚወስን መመሪያ የማውጣት ስልጣን በአዋጅ ረቂቁ ተሰጥቶታል። መመሪያውን የሚያወጣው፤ የቤቶች ገበያ ወቅታዊ ሁኔታን፣ የከተሞች የማይንቀሳቀስ ንብረት አማካይ ዋጋን፣ የውጭ ዜጎች በቤቶች ገበያ ያላቸውን የተሳትፎ መጠን እና የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ሌሎች ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ነው።

- የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ፤ የተወሰኑ ሀገራት ዜጎችን ወይም ዜግነት የሌላቸው የውጭ ሀገር ሰዎችን በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዳይሆኑ #ሊከልክል ይችላል።

- ለውጭ ዜጎች የተገደቡ ልዩ ቦታዎች እና የድንበር አካባቢዎችም እንዲሁ በሚያወጣ መመሪያ ይወሰናሉ።

- በውጭ ዜጎች ላይ የተጣሉ ሌሎች ገደቦችም አሉ።
° ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ለመሆን ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ አይችልም።
° የውጭ ዜጎች ይህን ጉዳይ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ ወይም ተያያዥ የመንግስታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን መክፈል ያለባቸው በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሬ ብቻ ነው።
° ማንኛውም የውጭ ዜጋ በመንግስት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን አይችልም። ይህ ገደብ በግል እና በመንግስት አጋርነት ወይም በተመሳሳይ የቤቶች ልማት ማዕቀፍ በፌደራል ወይም በክልል መንግስታት የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችን አያካትትም። ለውጭ ዜጎች የተቀመጠው ገደብ በእነዚህ አካላት አማካኝነት ለትርፍ ዓላማ ተገንብተው ለሽያጭ የሚቀርቡ ቤቶች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ነው።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

" በክልሉ አድማ ብተናና መደበኛ ፖሊስ እየተወሰደ ያለዉ የሃይል እርምጃዉ ቀጥሎ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ 2 ንፁሃን አርሶአደሮች ተገድለዋል " - ነዋሪዎች

➡️ " ' የሃይል እርምጃ ተወስዶ ሁለት አርሶአደሮች ተገድለዋል ' የሚባለው ፍፁም የዉሸት መረጃ ነዉ። ሽፍቶችን ለመያዝ እየተደረገ ባለዉ ኦፕሬሽን እስካሁን የሞተ ሰዉ የለም " - የጋሞ ዞን ፖሊስ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዘይሴ ነዋሪዎች " ካሳለፍነዉ እሁድ ጀምሮ በአከባቢው በአድማ ብተናና የጋሞ ዞን ፖሊስ እየተወሰደ ያለው ተገቢ ያልሆነ የሃይል እርምጃ በርካታ ምስቅልቅሎችን ሲፈጥር ቆይቷል ከትላንት በስቲያ ደግሞ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ 2 አርሶአደሮች በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ተገድለዋል " ሲሉ ተናግረዋል።

በአከባቢዉ እየተንቀሳቀሱ ባሉ የታጠቁ የፀጥታ አካላት እየተወሰደ ባለዉ ድብደባና እስር ምክንያት የህብረተሰቡ እቅስቃሴ ተገድቦ መቆየቱን የገለፁት ነዋሪዎቹ " ' ቢቀሳ 'ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ ከብት በረሃብ እንዳይጎዳ አሰማርተዉ የነበሩ 2 አርሶ አደሮችን በጥይት ተመተው ተገድለዋል " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገርናቸው የአከባቢው የሃይማኖት መሪዎች እና ሽማግሌዎች " እርምጃው ፍፁም ትክክል ያልሆነ " ሲሉ ገልጸዋል።

ከሰሞኑን የሃይማኖት ተቋማትን ነፃነት የጣሰ ተግባር መፈጸሙን ጠቁመዋል።

" በኤልጎ ሙሉ ወንጌል እና ወዘቄ መካነ ኢየሱስ ቤተክርቲያናት አገልጋዮች ከመድረክ ተጎትተው ተወስደዉ የታሰሩበትና የተደበደቡበት ሁኔታ ነበር። በዚህም ምክንያት በእሁድ ዕለተ የአምልኮ ቀን ምዕመናን ወደ ቤተክርስቲያን አልመጡም " ሲሉ ተናግረዋል።

" የሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ተጥሷል ፣ የጤና ተቀማት የወታደር ከምፕ ሆነዋል፣ ትምህርትና የእርሻ ስራን ጨምሮ አጠቃላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በዘይሴ ኤሊጎ፣ ዘይሴ ዳቢሌ እና ዘይሴ ወዘቄ አከባቢዎች ወዳልተፈለ አቅጣጫ እያመራ ስለሆነ ከዚህ በላይ ቀዉስና ሞት እንዳይከሰት የክልሉ መንግስትና የፌደራል ገለልተኛ አካላት ጣልቃ ገብተዉ ያረጋጉ " ሲሉ የሃይማኖት መሪዎች እና ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

የጋሞ ዞን ፖሊስ ምን አለ ?

የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ደበበ ኦንቶ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፥ ከሳምንት በፊት በግዳጅ ላይ ለነበሩ የፀጥታ አባላት ስንቅ ሲወስዱ በነበሩ የአድማ ብተናና ፖሊስ አባላት ላይ በተፈፀመ ድንገተኛ ጥቃት አንድ የአድማ ብተና ፖሊስ ተሰውቷል ሲሉ አስታውሰዋል።

" ይህን ጥቃት ያደረሱ ሽፍቶችን ለመያዝ የፀጥታ መዋቅር አካላት ተሰማርተዋል ነገርግን ' የሃይል እርምጃ ተወስዶ ሁለት አርሶአደሮች ተገድለዋል ' የሚባለው ፍፁም የዉሸት መረጃ ነዉ " ሲሉ ገልፀዋል።

" ለአከባቢው አለመረጋጋት ዋነኛ ምክንያት የሆኑት ተደብቀዉና በሰሩት ወንጀል የሚፈለጉ አንዳንዶች ደግሞ በሌሉበት የፍርድ ዉሳኔ ተላልፎባቸዉ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ናቸው " ያሉት አዛዡ " እነዚህ ግለሰቦች ሀሰተኛ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የዉሸት መረጃ እያሰራጩ ነዉ " ብለዋል።

በአከባቢው የሚገኙት የፀጥታ አካላት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዳይወርድ በሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሃይሎች በሰላማዊ ዘጎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ በአከባቢው የሚገኙ ናቸዉ ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa

@tikvahethiopia
" በአዲስ አበባ በ7 ሺህ 521 ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎች ከዛፎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል " - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት " የኃይል መቆራረጥን ወደ ዜሮ ለማውረድ የያዝኩትን ዕቅድ ለማሳካት እየሠራው ነው " ሲል አሳውቋል።

" የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽን ወደ ዜሮ ለማውረድ የተጀመረው የ100 ቀናት እቅድ ሥራዎች ሁለት ወራትን ተሻግረዋል " ብሏል።

ተቋሙ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በላከው መግለጫ እንደገለጸው በ100 ቀን እቅዱ በቅድሚያ አዲስ አበባ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ስራዎቹን በአገር አቀፍ ደረጃም በማውረድ የኃይል መቆራረጥ መንስኤዎችን የመለየትና አስፈላጊው የማስተካከያ ሥራ እየተሰራ ነው ብሏል፡፡  

የ100 ቀናት እቅድ የቅድመ መከላከል ሥራው በጂፒኤስ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንደሆነ ተገልጿል።

ባለፉት ወራት በተደረጉ ቅኝቶች የተገኙ ውጤቶች ምን ይመስላሉ ?

" በአዲስ አበባ በ152 የመካከለኛ መሥመሮች እና እነዚህን መሥመሮች የሚሸከሙ 49 ሺህ 581 ምሰሶዎች ላይ በተደረገ ቅድመ ምርመራ 26 ሺህ 559 ከባድና ቀላል ግኝቶች ተገኝተዋል፡፡

ይህንንም ለመለየት ምርመራ ቡድኑ 1ሺህ 767 ኪሎ ሜትር ያህል በእግር ተጉዟል፡፡  

በአዲስ አበባ ፦
° በ7ሺህ 521 ቦታዎች ላይ የዛፎች ንክኪ
° 6 ሺህ 399 መቀየር የሚያስፈልጋቸው ምሰሶዎች
° 6 ሺህ 338 የረገቡ
° 2 ሺህ 427 መሥመሮች ከግንባታዎችና እርስ በእርሳቸው የተቀራረቡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ይህም ለተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ መንስኤ ከሆኑ ዋነኞቹ የግኝት ነጥቦች መካል ተጠቃሽ ናቸው።

እስካሁን 29 በመቶ ወይም ለ7 ሺህ 663 ያህሉ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጓል።

በከተማዋ በሚገኙ በ10 ሺህ 498 ትራንስፎርመሮች ላይ ምርመራ ተደርጎ በ7 ሺህ 211 ያህሉ ላይ መጠነኛ ችግሮች የተገኙ በመሆኑ ተገቢው ማስተካከያ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡  

በሌላ በኩል በከተማዋ ከፍተኛ የኃይል ጭነት ባለባቸውና በሌለባቸው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል የኃይል ማበዳደር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

በ23 ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የዋና መሥመሮች ወጪ የሚሆኑበት ጋንትሪ የማስተካከል ሥራዎችም በሂደት ላይ ናቸው፡፡

ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙት ሪጅኖች 561 የቴክኒክ ባለሙያዎችን በማሠማራት አጠቃላይ ካሉት 909 የመካከለኛ መስመሮች ውስጥ እስካሁን 192 ያህሉ ምርመራ የተጠናቀቀላቸው ሲሆን፤ ቀሪዎቹ በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

መስመሮቹ ረጅም ዘመን ያገለገሉና ረጅም ርቀት የሚጓዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እስካሁን በተሠራው የቅድመ ምርመራ ሥራ ብቻ 193 ሺህ ከባድና ቀላል የግኝት ነጥቦች ተመዝግበዋል፤ የሁሉም መስመሮች ምርመራ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ግኝቶች እንደሚኖሩ የሚጠበቅ ነው " ብሏል፡፡

ተቋሙ ያስቀመጠውን የመቶ ቀናት የሥራ እቅድ ሊጠናቀቅ የቀረው ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ብቻ እንደሆነ አመልክቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#ፍትሕ

" አያንቱ ላይ የግብረ-ስጋ ድፍረት ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በፖሊስ አዛዥ ተባባሪነት እንዲሸሽ ተደርጓል " - የአያንቱ ታላቅ ወንድም

🚨 " ፖሊስ አዛዡን ከኃላፊነት ከማዉረድ የዘለለ ደፋሪዉን ለሕግ አቅርቦ ዉሳኔ የማሰጠት ስራ አልተሰራም !! "

በሲዳማ ክልል፤ በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ሻፋሞ ወረዳ ሹሮ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ በእንጀራ አባቷ ቤት እያደገች የነበረች የ13 ዓመቷ ታዳጊ አያንቱ ቱና እሜ ለእናቷ መልዕክት ተልካ እየሄደች በነበረችበት ወቅት ባጥሶ በቀለ በተባለ ተጠርጣሪ ወጣት የግብረ-ስጋ ድፍረት ወንጀል ይፈጸምባታል።

በኋላም ተጠርጣሪዉ ተይዞ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋል ሲገባዉ በፖሊስ አዛዥ ተባባሪነት በቤተሰቦቹ አማካኝነት ወደ ሌላ ክልል እንዲሸሽ መደረጉ ተነግሯል።

በወቅቱ የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ የነበሩትና የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸመው ከተጠረጠረው ወጣት ጋር ባላቸዉ ዝምድና ምክንያት በጉዳዩ ላይ ቸልተኝነትን በማሳየት ተጠርጣሪው ከአከባቢው እንዲሸሽ ስለማስደረጋቸው የአያንቱ ታላቅ ወንድም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ከፍተኛ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባት ታዳጊዋ አያንቱ በቦና አጠቃላይ ሆስፒታል ስትታከም ቆይታ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀዋሳ ተወስዳ በጣሊታ የሕፃናት ማቆያ እንደምትገኝ የሚናገረው ወንድሟ " ፖሊስ አዛዡን ከኃላፊነት ከማዉረድ የዘለለ ደፋሪዉን ለሕግ አቅርቦ ዉሳኔ የማሰጠት ስራ አልተሰራም " ብሏል።

" አያንቱ በአካልና በስነልቦና በእጅጉ ተጎድታ ከትምህርት ገበታዋም ተለይታ ፍትሕ ሳይሰጣት በጣሊታ የሕፃናት ማቆያ ከ1 ዓመት በላይ እንድትቀመጥ መደረጉ እጅግ በጣም ጎድቷታል " ሲል ገልጿል።

" የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ' ጉዳዩን ለምን በሚዲያ አወጣህ ሚዲያ ፍትህ ያሰጥህ ' ብለዉኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋረደኝ እንጂ እኔ ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪና አባታችን በሕይወት የሌለ፤ እናታችንም ሌላ ሰዉ አግብታ የምትኖር ምስኪኖች ነን " ሲል ታላቅ ወንድሟ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

የፍትህ አካላት ምን አሉ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳይ ላይ የፍትህ አካላትን ምላሽ ለማካተት ፦
° የማዕላዊ ሲዳማ ዞን ዐቃቤ ሕግ መምሪያ
° የወረዳዉ ፍትህ ጽ/ቤት
° የወረዳና የዞኑን ፖሊስ
° የሻፋሞ ወረዳ ሴቶችና ሕፃናት ወጣቶች ጉዳይ መምሪያና የክልሉን ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን ለማነጋገር ሞክሯል።

የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ ምን አለ ?

የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሙሴ አወል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለፁት በወቅቱ የነበሩት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት መነሳታቸዉን አስታወሰዋል።

እሳቸዉ ወደ አዛዣነት ከመጡ በኋላ ተጠርጣሪዉን የማፈላለጉ ስራ በተለያዩ ቴክኒኮች እየተሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች ለምን ዉጤታማ አልሆኑም ? በሚል ትክቫህ ኢትዮጵያ ላነሳላቸዉ ጥያቄ " ፖሊስ የሚችለዉን ሁሉ እያደረገ ነው " ሲሉ መልሰዋል።

የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ፍትሕ መምሪያ ምን አለ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸዉ የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዐቃቤ ህግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደማምሰዉ ታፈሰ ፥ ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን በቀረበለት መረጃና ማስረጃ ልክ ተመልክቶ ክስ በማዘጋጀት ሂደት ላይ እያለ ተጠርጣሪዉ እንዲሸሽ መደረጉንና የቀድሞ የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን ተጠርጣሪውን አፈላልጎ ለህግ በማቅረቡ ሂደት ፖሊስ እያደረገ ያለዉን ክትትል በማጣራት በህግ አግባብ መሰረት ቀጣይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታዉቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፍፁም በላይነህን ለማግኘት መክሯል።

ኃላፊዋ በስልክ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ይህም በመሆኑ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ በአካል ቢሯቸው ተገኝቶ ኃላፊዋን ለማነጋገር ቢሞክርም ፈቃደኛ ባለመሆናቸዉ ሃሳባቸው ሳይካተት ቀርቷል።

ጉዳዩን እስከመጨረሻው ድረስ የምንከታተለው ይሆናል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa

@tikvahethiopia
2025/05/20 00:46:24
Back to Top
HTML Embed Code: