Telegram Web
+• ምላሽዎ ምንድር ነው? •+

የጌታን መወለድ ሰምቶ የተግባር ምላሽ አለመስጠት ከባድ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጌታን መወለድ የሰሙ ሰዎች ሁሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ ምላሽ ግን በጎም ሆነ ክፉ ሊሆን ይችላል። ንጉሥ ሄሮድስ ስለ አይሁድ ንጉሥ በሰማ ጊዜ፥ በቅናት አብዶ በሕጻናት ላይ ሰይፉን አነሳ። ሰብዓ ሰገል የንጉሡን መወለድ ባወቁ ጊዜ ግን፥ ሀገር አቆራርጠው ለንጉሡ ሊሰግዱ ሄዱ።

ለንጉሡ መወለድ የእኛስ ምላሽ ምን ይሆን? ይህ ዜና ለጆሯችን የምስራች ነው ወይስ መርዶ? የምስራች ከሆነ፤ ስጦታን ይዘን መሄድ ይገባል። እንኳን ለንጉሥ ልደት ይቅርና፥ የትኛውም ሕጻን ሲወለድ ስጦታን ይዞ መሄድ ነባር ዓለምአቀፍ ባህል ነው። ባዶ እጅ መሄድም ነውር ነው።

የተወለደው ንጉሥ ከእኛ ወርቅ፥ እጣን እና ከርቤን አይጠብቅም። እርሱ ከእኛ የሚፈልገው እኛነታችንን ነው። ሐዋርያው "ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ" (ሮሜ 12፥1) ያለውን ብንሰማ፥ ሰውነታችንንም በንስሃ ንጹህ አድርገን በቅዱስ ቁርባን ጌታን ወደ ሕይወታችን ብንቀበል፥ በንጉሡ ዓይን ሞገስን እናገኛለን።

እርስዎም የጌታን መወለድ ሰምተዋል። ታዲያ ለዚህ በጎ ዜና ምላሽዎ ምን ይሆን?

እንኳን ለጌታችን ልደት በሰላም አደረሰን!

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

እንኳን አደረሳችሁ መልካም በዓል
🙏1🕊1
+ ወደ ሄሮድስ እንዳትመለሱ +

ሰብአ ሰገል ወደ ሄሮድስ ሔደው ስለተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ጠየቁ:: ከዚያም በኮከብ ተመርተው ወደ ክርስቶስ ደረሱ:: ሔደውም ሰገዱለት:: እጅ መንሻም አቀረቡ::

ከዚያ በኋላ ግን "ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ" ማቴ. 2:12

ይህ መልእክት የተነገራቸው ስለ ሁለት ነገር ነው:: የመጀመሪያው ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ስለሚፈልግ ለሄሮድስ መረጃ እንዳይሠጡ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለተወለደው የአይሁድ ንጉሥ እየመሰከሩ የመጡበትን መንገድ ትተው አየነው እያሉ በሌላ መንገድ እንዲመሰክሩና የሕፃኑ ንጉሥ ዝና እንዲሰፋ ወንጌል እንዲስፋፋ ነበር::

መልአኩ ወደ ሄሮድስ አትመለሱ አለ እንጂ "ሄሮድስ ሊገድለው ነው" አላላቸውም:: ምክንያቱም ይህን ዜና ቢሰሙ ጦር ይዘው የመጡ ነገሥታት ናቸውና "እኛ እያለን እስቲ ይሞክረን" ብለው ውጊያ ሊያነሡ ይችሉ ነበር:: የሰላም አለቃ የተባለው ህፃኑ ክርስቶስም የውጊያ መነሻ ይሆን ነበር:: ክርስቶስ ግን የምትዋጋለት ሳይሆን የሚዋጋልህ አልፎም የሚወጋልህ አምላክ ነው::

በዚህ መሠረት ሰብአ ሰገል
"ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ"

ወዳጄ ክርስቶስን ሳታገኝ በፊት ሄሮድስ ጋር ብትሔድ ችግር የለውም:: ክርስቶስን ካገኘህ በኋላ ግን ወደ ሄሮድስ መመለስ ኪሳራ ነው:: እንደ ሰብአ ሰገል ለጌታ እጅ መንሻ አቅርበህ ፣ ዘምረህ ፣ የከንፈር መሥዋዕት አቅርበህ ነፍስህ መድኃኒትዋን አግኝታ ከተደሰተች በኋላ ሕይወት እንዴት ይቀጥላል?

ወደ ሄሮድስ ልትመለስ ይሆን? እንዳታደርገው! ሄሮድስ ጋር ያለው ኃጢአት ነው:: ሄሮድስ ጋር ያለው ክፋት ነው:: እመነኝ እንደ ሰብአ ሰገል ጌታህን ካገኘህ ወዲህ ወደ ሄሮድስ አትመለስ!

ወዴት ልሒድ ካልከኝ መልሱ እዚያው ላይ አለ :-

"በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሔዱ"

እስቲ ሌላ መንገድ ሞክር! ትናንት ያልኖርክበትን ዓይነት ኑሮ ፣ ትናንት ያልሞከርከው የንስሐ መንገድ እስቲ ዛሬ ሒድበት! ሌላ መንገድ አልነግርህም "መንገድም ሕይወትም እውነትም እኔ ነኝ" ያለህ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እርሱ ነው:: በእኔ ኑሩ እንዳለ በእርሱ ኑር:: አደራ ወደ ሄሮድስ እንዳትመለስ!

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ (የመቄዶንያ አምባሳደር)
ጥር 2 2017

ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!
8161 ላይ OK ብለው በመላክ መቄዶንያን ይርዱ!
መቄዶንያን ይጎብኙ!

ማስታወሻ :- የልደቴን ቀን አስመልክታችሁ ብዙ ምርቃትና መልካም ምኞት ላዘነባችሁልኝ ሁሉ ለእኔ የተመኛችሁትን ሁሉ ለእናንተ እጥፍ ድርብ ያድርግላችሁ:: ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልገኝ ጸሎታችሁ ነውና ተክለ ማርያም ብላችሁ አስቡኝ::

የልደት ሥጦታ ልሥጥህ ካላችሁ ደግሞ 8161 ላይ OK ብለው በመላክ መቄዶንያን ይርዱልኝ::
🙏2👍1
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥር 3-ከዐለት ላይ ውኃ እያፈለቁ ድውያንን የሚፈውሱት ተአምረኛውና አባት አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኸውም የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ገዳም ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› በስማቸው የተሰየመላቸው ናቸው፡፡
አባ ሊባኖስ፡-
አባታቸው አብርሃም እናታቸው ንግሥት ይባላሉ፡፡ እነርሱም በወርቅና በብር እጅግ የበለጸጉ ሮማዊ ናቸው፡፡ ልጃቸውን አባ ሊባኖስን በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው ካሳደጓቸው በኋላ ዕድሜያቸው ሲደርስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያጋቧቸው ዘንድ ከቁስጥንጥንያ አገር ሚስት ባመጡለት ጊዜ እርሱ ግን ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ወደጫጉላቤትም መግባትን እምቢ አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤልን እንደጠራው አባታችንንም እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ተለይ አንተ የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ ነህ እንጂ የዚህ ምድራዊ ዓለም ሙሽራ አይደለህም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወዴት እሄዳለሁ? ምንስ ላድርግ?›› ባሉ ጊዜ ወዲያው የታዘዘ መልአክ በሌሊት መጥቶ ከአባታቸው ቤት አውጥቶ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስም ለአባ ሊባኖስ በዓት በመስጠት ገዳመ ሥርዓትን፣ አስኬማ መላእክትን፣ ቅናተ ዮሐንስን አስተምረዋቸው አመነኮሷቸውና ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር እንዲገናኙ አደረጓቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ያ ከአባታቸው ቤት ወስዶ አባ ጳኩሚስ ገዳም ያደረሳቸው ያ መልአክ ድጋሚ ተገለጠላቸውና ‹‹ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሂድና ተጋድሎህን በዚያ ፈጽም ዝናህ በስፋት ይነገራል፣ ለብዙዎችም አባት ትሆናቸዋለህ›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም ራሱ መልአኩ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸውና በአክሱም ተቀመጡ፡፡ በዚያም ብዙ ከተጋደሉ በኋላ ወደ ሸዋ መጡና ወንጌልን ዞረው አስተምረው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ተመልሰው አክሱም ሄዱ፡፡ በአክሱምም 7 የተለያዩ ጸበሎችን ከድንጋይ ላይ በተአምራት አፍልቀው ድውያንን ፈውሰው ዕውራንን አበሩ፡፡በዓታቸውንም ከአክሱም ጽዮን ፊት ለፊት አድርገው ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አባታችን በተአምራት ከጭንጫ ካፈለቁት ጸበል ‹‹ተራ ውሃ ነው›› ብላ አንዲት ሴት ልጇን አዝላ ልትቀዳ መጣች፡፡ ወዲውም ከቦታው ስትደርስ አድጧት ወደቀችና ልጇም አምልጧት ልቡን ድንጋይ መቶት ሞተ፡፡ ሴትዮዋም ስትጮህ አባ ሊባኖስ ፈጥነው ወጡና በልጁ ላይ ጸልየው በመስቀል ምልክት አማትበው ከሞት አስነሥተውታል፡፡ ሕፃኑ ልጅ ከሞት እንደተነሣ ‹‹አምላከ አባ ሊባኖስ›› ብሎ አመሰገነ፡፡
ይህንንም ደግ ሥራቸውንና ተአምራታቸውን ያዩ አንዳንድ እኩይ ካህናት በቅናት ተመልተው ‹‹ምትሃት ነው የሚያሳየው›› ብለው በጻድቁ ላይ ሕዝቡን አሳደሙባቸው፡፡ አባታችንም ካህናቱን ለመምከር ቢሞክሩም አላስቀምጥ አሏቸው፡፡ ይልቁንም ጦር ጦራቸውን ይዘው አሳደዷቸው፡፡ አባታችንም በዚህ እጅግ አዝነው ከአክሱም ተነሥተው ደርቃ ወደምትባል ቦታ ሄዱ፡፡ በዚያም በጾም በጸሎት እየተጋደሉ ሲኖሩ በእነዚያ በጠሏቸውና በክፋት በተነሡባቸው ካህናት አገር ግን ለ3 ዓመት ምንም ዝናብ ሳይዘንብ ቀረ፡፡ አባታችን በተሰደዱባት በደርቃ አገር ግን ብዙ ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ አባታችን በዚያችም አገር እንደልማዳቸው ከዐለት ላይ ውኃ አፍልቀው በውኃው ብዙ ድውያንን ፈውሰውበታል፡፡ በዚያም ትልቅ በዓት መሥርተው በተጋድሎ ሲኖሩ በክፉ የተነሡባቸው እኩይ የሆኑ ካህናት መጥተው ‹‹አባታችን በከንቱ አምተንሃል በድለንሃልና ይቅር በለን፣በድርቅ ማለቃችን ነውና ዝናብም እንዲዘንብልን ጸልይን›› ብለው ከእግራቸው ሥር ወደቁ፡፡አባታችንም ይቅር ብለው ከፈጣሪ አማለዷቸው፡፡ ዝናቡም ወዲያው ዘነበላቸውና በአገሪቱ ጥጋብ ሆነ፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን አስቀድመው ወዳዩአት ወደ ሸዋ ምድር ግራርያ መጡና በዓታቸውን በአሰቦት ጫካ አደረጉ፡፡ ነገር ግን መልአኩ ተገልጦላቸው ‹‹ሊባኖስ ሆይ! ከዚህ ቦታ የአንተ መኖሪያ አይደለም፣ በዚህ ቦታ ላይ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያገናኝ የሚያስታርቅ ታላቅ ጻድቅ ይወጣበታልና ይህ ቦታ የእርሱ ርስት ነው፣ የብዙ መነኮሳትም መንደር ይሆናል ነገር ግን የቦታው ስም በአንተ ስም ይጠራልሃል›› አላቸው፡፡ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተወልደው በዓታቸውን በዚያ ቦታ ላይ ሲያጸኑ ቦታው ግን ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› ተብሎ በመጀመሪያው አባት ስም ተሰየመ፡፡ መልአኩም በሌሊት እየመራ ወደ አክሱም ወሰዳቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ታሪክ ወደምትሠራበት ዕጣ ክፍልህ ወደሆነው ቦታ አደርስሃለሁ›› አላቸውና ወደ ኤርትራ አካለ ጉዛይ አውራጃ ልዩ ስሙ መጣዕ ወደተባለው ቦታ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም አባታችን ድውያንን እየፈወሱ፣ ለምፃሞችን እያዳኑ፣ ሙታንን እያስነሡ ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እየሰበኩ ‹‹ሊባኖስ ዘመጣዕ›› የሚባለውን ትልቁን ገዳማቸውን መሠረቱ፡፡ በወቅቱ የነበረው ዐፄ ገብረ መስቀልም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን አሠራላቸው፡፡
ቅዱስ ላሊበላ 23 ዓመት ሙሉ ካነጻቸው እጅግ ድንቅ 11 ቤተ መቅደሶች ውስጥ አንደኛውን በአባ ሊባኖስ ስም ሰይሞላቸዋል፡፡ በዐፄ ገብረ መስቀል ያሠራላቸው ሌላኛው ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ እጅግ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የሚታወቁት አባታችን እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ከሮም በመምጣት በሀገራችን ላይ ብርሃንን አብርተዋል፡፡ በመጨረሻም ጥቅምት 2 ቀን ተፀንሰው ሐምሌ 3 ቀን ተወለደው ጥር 3 ቀን ባታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ ቅዳሴ ቤታቸው ደግሞ ሐምሌ 3 ቀን ነው፡፡ ይኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ በዐፄ ገብረ መስቀል ጊዜ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ የተመረቀበት ዕለት ነው፡፡
የአባ ሊባኖስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
👍1
ጥር 6 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪት ሕግ የሆነውን ግዝረት የፈጸመበት ዕለት ጥር ስድስት ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ክርስቶስ በሥጋ ግዝረትን ተቀበለ፣ ለአባቶች የተሰጠውን ቃልኪዳን ይፈጽም ዘንድ›› ብሎ መስክሯል፡፡ (ሮሜ 15፥8)
መጽሐፈ ስንክሳር

እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን !!!
👍3
+• አሥራት ለምን ታወጣለህ? •+

አባ ታድሮስ ማላቲ “Stories for the Youth” በሚል ርዕስ ለወጣቶች ባዘጋጁት መጽሐፍ ላይ፥ ስለ አሥራት ጥቅም አንድ አጭር ታሪክ ጸፈዋል፤ እንደሚከተለው ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ።
--
ከሃያ ዓመት ቆይታ በኋላ፥ በካሊፎርኒያ ከተማ አንድ የመንፈስ ልጄን አገኘሁት እና ወደ ቤቱ ወሰደኝ። ቤቱ እጅግ ግዙፍ እና ውብ ነበር። አብረን ተቀምጠን ሳለም፥ “አባ፥ የዛኔ በካሊፎርኒያ መኖር ስጀምር ትዝ ይልዎታል? ኑሮን ለማሸነፍ ትግል ላይ ነበርኩ፥ አሁን ግን እግዚአብሔር ከጠየቅሁትም በላይ ሰጥቶኛል።” አለኝ።

እኔም “ይህ የእግዚአብሔር ቸርነት ነው። በእውነቱ አምላካችን ያስብልናልና እናመሰግነዋለን።” አልኩት።

እርሱም ቀጠለና፥ “እግዚአብሔር ምን ያህል ቸርነት እንዳደረገልኝ ያውቃሉ? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ጀምሮ ‘እዚህ በምድር ላይ ስኬታማ ብሆን፥ መንግሥተ ሰማያትን ግን ካጣሁ ምን እጠቀማለሁ?’ እያልኩ መብሰልሰል ጀመርኩ። ከዚያ አንድ ቀን፥ በአምላኬ ፊት ተንበርክኬ፥ ሁኔታዬ ምንም ያህል ቢከፋ፥ ከማገኘው ገቢ ላይ አሥራቴን ላለመንካት ቃል ገባሁለት። አሥራት የእግዚአብሔር ነዋ! ቀጠልኩና ‘ጌታዬ ሆይ፥ ሁሉም ያንተ ስጦታ ነውና፥ ከዘጠኝ እጁ ላይ ደግሞ በእዚህ በአሜሪካም ሆነ በግብጽ ላሉ ነዳያን እመጸውታለሁ።’ አልኩት።

“ከዚያም በልግስና መስጠት ጀመርኩ፤ የገነት በሮችም ተከፈቱልኝ! በእውነቱ እግዚአብሔር ከሚያስፈልገኝ በላይ ሰጠኝ። አንዳንዴ፥ ተንበርክኬ እያለቀስኩ፥ ‘እባክህ በቃህ አምላኬ! ከዚህ በላይ ከሰጠኸኝ የሃብት ብዛት ነፍሴን እንዳያጠፋት እፈራለሁ’ ብዬ እለምነው ነበር። እርሱ ግን እንዲህ እያልኩም የበለጠ ይሰጠኝ ነበር።”

ከ Fresenbet GY Adhanom ገጽ የተወሰደ ።
✍️ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ስለ ዘማሪት ሕይወት እንዲህ አለ

2008 ዓ.ም. ከዘማሪት ሲስተር ሕይወት ተፈሪ ጋር የተባበሩት ዐረብ ኢመሬትስ ሻርጃ ሰአሊተ ምሕረት አብረን ለማገልገል ተጠርተን ነበር:: ከሃያ ቀናት በላይ በየቀኑ በሚካሔደው በዚህ ጉባኤ ላይ ዘማሪት ሕይወት መሣሪያ በማይፈልገው የተለየ ድምፅዋ "ና ና አማኑኤል ና መድኃኒቴ" የሚል ድንቅ መዝሙር ስትዘምር ሰማሁ::

"ስሸጥህ አቀፍከኝ ስወጋህ ዓይኔ በራ" እያለ ራስን ከይሁዳና ከሌንጊኖስ ጋር በትሕትና የሚያነጻጽረው ይህን መዝሙር በጣም ስለወደድሁት አንዲት ቃል ላይ ብቻ እርማት እንድታደርግ አስተያየት ሰጥቼ አብረን በሰነበትንበት ሻርጃ ሕዝቡ በቃሉ እስኪይዘው ድረስ 14ቱንም ቀን አስዘመርኳት::

ዘማሪት ሕይወት ተፈሪ በሙያዋ ነርስ ስትሆን ቤተ ክርስቲያን ቆንጥጣ ካሳደገቻቸው ወርቅ ዘማርያን አንድዋ ናት:: ሰዓታት የምትቆም ፣ አስቀድሳ የምቆርብ ፣ መምህሩ ያስተማረውን ቁጭ ብላ ሰምታ ለትምህርቱ የሚስማማ መዝሙር የምትዘምር ፣ በጣም በትሕትናና በታዛዥነት የምታገለግል ካላት የዝማሬ ጸጋ ገና የሚገባትን ያህል ያልተሰማች (Underrated) ያወቋትና የሰሟት ደግሞ እንዴት ሳልሰማት ቀረሁ የሚሉባት የቤተ ክርስቲያን ውድ ልጅ ናት:: እግዚአብሔር ይጠብቅልንና ዘማሪት ሕይወት ከ "ረ" ፊደል በስተቀር በመዝሙር ዘርፍ ገና ለመሥራት ምንም የሚቸግራት ነገር የለም::

ሰሞኑን በአእላፋት ዝማሬ ላይ "ና ና አማኑኤል" የሚለው መዝሙር በጃን ያሬድ መዘምራን ሲዘመር የሰሙና የወደዱት ምእመናን "ይኼ መዝሙር ግጥሙ የአንተ ነው" በሚል ሲመርቁኝ ሰነበቱ:: ምርቃቱን ሳላስተባብል አሜን ብዬ ብቀበልም ይህንን በሳል መዝሙር ግጥምና ዜማ የሠራውን ሰው ግን በጸሎት እንድታስቡትና እንድትመርቁት ማሳሰብ የግድ ሆነብኝ::

የመዝሙር ርእስ :- ና ና አማኑኤል ና መድኃኒቴ
ዘማሪዋ :- ዘማሪት ሕይወት ተፈሪ
ግጥም :- ዘማሪት ሕይወት ተፈሪ
ዜማ :- ዘማሪት ሕይወት ተፈሪ

መዝሙሮችዋን ለመስማት ይኼንን ገፅ ሰብስክራይብ አድርጉ https://youtu.be/MZHegl4Wrn4?si=7NmkZ9NJFGvmklfJ

https://youtu.be/mpoTvGB3kcQ?si=bpxzCLCH42yX-Lfw
5👍4
#በዓለ_ሥሉስ_ቅዱስ (ጥር 7)

ጥር ሰባት በዚች ቀን በዓለ ሥላሴ የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::

#ሕንጻ_ሰናዖር
ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::

ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::

ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::

መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::

ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::

ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::

#ቅዳሴ_ቤት
ልክ የዛሬ 324 ዓመት አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት (በ1684 ዓ.ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::

ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን ሠራዊት መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል። በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል። ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል ደግ ጥበበኛ አስተዋይ መናኝ ንጉሥ ነውና።

ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ.ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

(ስንክሳር ዘተዋሕዶ)
👍1
የነባሕታዊ ገብረ መስቀል ውርስ (የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላለቀ የቤት ሥራ)
+ + + + +
የደርግ መንግሥት እንደወደቀ አንድ የ27 ዓመት እጅግ ቆንጆ እና ንግግር አሳማሪ ወጣት ከሆነ ቦታ ብቅ አለ፡፡ ‹‹ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከስልጣን እንደሚወርድ ነግሬው ነበር›› በሚል እና እግዚአብሔር መሐሪ ሳይሆን መቅሰፍት አውራጅ እንደሆነ በሚያስጠነቅቁ መልእክቶች ተሞልተው እጅግ በሚገርም ፍጥነት የአዲስ አበባን ብሎም የአንዳንድ የሀገራችንን ቦታዎች ምዕመናን ተቆጣጠረ፡፡ ይህ የዛን ጊዜ ወጣት ራሳቸውን ባሕታዊ ገብረ መስቀል በማለት አሳወቁ፡፡
የቡና ተክልን ጌታችን ሲሰቀል ሌሎች ሲጠወልጉ እርሱ ብቻ ለምልሞ የተገኘ ነው የሚል ምንጩ ያልታወቀ ትምሕርት በማስተማር በየሰዉ ቤት ያለ ሲኒና ጀበና አሰበሩ፣ ወጣቶችን በባዶ እግር ከአንድ ደብር ወደ አንዱ ደብር እንዲሄድ አደረጉ፡፡ የተከተላቸውን ሕዝብ ይልቁንም ወጣቱን እርሳቸው ወደፈለጉበት ቦታ ብቻ መንዳት ተያያዙት፣ ቅዱስ ፓትርያሪኩን፣ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን ሊቃውንትን እንዳይሰማ ከእጃቸው መስቀል እንዳይባረክ አደረጉ፡፡ አንድ ጊዜ በረከታቸው ይደርብንና የቅዱስ አማኑኤል ቀን አቡነ ሰላማ (የባሌው) ቀድሰው ‹‹ከኃጢአት ማሠሪያ እግዚአብሔር ይፍታ›› ሲሉ እጅግ ብዙ ሆነው ቤተ መቅደሱን የሞሉት ተከታዮቻቸው ‹‹ተክልዬ ይፍቱን›› ብለው ማስደንገጣቸውን አስታውሳለሁ፣ እንደዚሁ በወቅቱ የሆነ ንግሥ ያለበት ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ሊቃነ ጳጳሳት ሲመጡ የባሕታዊ ተከታዮች መንገድ ዘግተው አናሳልፍም ሲሉም አስታውሳለሁ፡፡
በወቅቱ ባሕታዊ ገብረ መስቀልን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ አንጻር መቃወም ከስድብ እስከ ዱላ የሚደርስ የመልስ ምት ነበረው፡፡ አንዳንዶች እንደመከራከሪያ የሚያቀርቡት ደግሞ ‹‹ወጣቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን አመጡት እንጂ ሌላ ምን አደረጉ? .. .. . ከቡና እና ከጫትና ከሲጋራ ሱሰኝነት አላቀቁት እንጂ ምን አደረጉት? .. . . እናንተ ሊቃውንት የምትሏቸው የሳቸውን ሩብ ሰርተዋል? ምቀኝነተት ነው እንጂ ድሮም ሰው ሲሠራ አይናችሁ ደም ይለብሳል›› የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ባሕታዊው ተቃውሞዎችን የሚያረግቡበት አንዳንድ በጎ ሥራዎችን በመሥራት እጅግ ሃብታም ሆኑ፣ ምዕመኑ አስራትና በኩራቱን ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለባሕታዊ መመገበር ተያዘ፡፡ ባታዊው በመሐል ሚስትም አገቡ፣ በብራቸው መጠን አሁን ድረስ የሚደግፏቸው ትላልቅ ሰዎች አሏቸው፡፡ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን መርሐ ግብርም አላቸው፡፡
ይህን የባሕታዊ ገብረ መስቀል በማር የተለወሰ ክፋት ያስታወሰኝ ትናንትና እጅግ በሚገርም የባለሙያ እና የአመራር ጥበብ ታድሶ የተመረቀውን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለማክበር እና ለማስቀደስ ስሄድ መንገድ ላይ ከተገናኘዋቸው ሰዎች ጋር የነበረኝ ውይይት ነው፡፡
አብረውኝ የሚጓዙ ምዕመናን በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጨውን ‹‹መስቀሉን ለመርገጥ አትሂዱ›› የሚለውን የአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ‹‹ተቆርቋሪዎችን›› ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ትዕዛዝ አፍርሰው የመጡ ቢሆንም ቅሬታቸውን ግን መደበቅ አልተቻላቸውም፡፡
‹‹የመስቀሉ መረገጥ ግን በጣም ያሳስባል፣ መምሕር ደረጄ ዘወይንዬ እና አንዳንድ በግልጽ የሚናገሩ የቤተ ክርስቲያን መምሕራን ቢናገሩም ለ ‹‹ሆዳቸው ያደሩና ከመንግሥት ጋር ተሻርከው ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው የሰጡ ጳጳሳት›› ለማስተካከልና መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም›› አለ፡፡
ሌላዋ ቀጥላ ‹‹መንግሥት ለምን ይመስልሃል ፈቃድና ገንዘብ የሰጠው? .. .. . መስቀሉ እንዲረገገጥ ስለሚፈልግ ነው›› አለች፡፡
ዝምታዬ ተጨማሪ ሐሜቶችን ለመስማት እንጂ ሌላ ጥቅም ስለሌለው ‹‹በወለሉ ላይ ያሉት የመስቀል ምልክቶች ዛሬ የተሠሩ ሳይሆን ከ81 ዓመትም የነበሩ ናቸው›› አልኩ፡፡
‹‹እንዴት ሊሆን ይችላል? . .. .. እኔኮ እዚህ አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግሁት ዛሬ ብቻ ነው ምንጣፍ የተነሳው ብዙ ጊዜ ተቀይሯል እና የዛን ጊዜ ሳይታይ ዛሬ እንዴት ታየ? . .. . ውሸት ነው አሁን ነው የሠሩት›› አለ፡፡
ሌላኛዋ ተለሳልሳ ‹‹ቢሆንም አሁን ሲታወቅ መነሳት አለበት፣ እ ደግሞ ለምዕመናን ጳጳሳት ይበልጥም ፓትርያሪኩና የአዲስ አበባ አቡነ ሔኖክ መግለጫ መስጠት ነበረባቸው›› አለች
‹‹በብጹዕ አቡነ ሔኖክ የሚመራው ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ላይ ስለጉዳዩ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ በመግለጫውም (ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም የተሰጠ ነው) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የእድሳት እና የማስተካከያ ሥራዎችን ለመሥራትም ጊዜ እንደሚፈልግ ገልጸዋል›› አልኩ፡፡
ተጨማሪ ውይይት ሳናደርግ ሁላችንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ገብተን ተለያየን፡፡
ግን እስከመቼ ነው እነ ደረጄ ዘወይንዬ . .. .. እነ መምሕር እገሌ፣ እነ ዲያቆን እገሌ፣ እነ ወጣት እገሌ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ባልሆነ መዋቅር የሚመሯት እስከ መቼ ነው?. .. .. የእነዚህ ሰዎች ልክና ገደብ የት ድረስ ነው? . . . በተለያየ አገጋጣሚ ቅዱስ ፓትርያሪኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳትን ‹‹ሆድ አደር . .. . መለካዊ እያሉ የሚሳደቡት እስከመቼ ነው? ሃሳባቸው ካልተሳካ ባላቸው ሚዲያና ኔትወርክ እንደፈለጉ የሚፋንኑት እስከ መቼ ነው? በእኔ ልክ ካልጮሃችሁ ተሳስታችኋል፣ ምዕመኑን አሳልፋችሁ ሰጥታችኋል እያሉ ምዕመኑን ተሳዳቢ፣ አባቶቹን የማያከብር የሚያደርጉት እስከመቼ ነው? .. . . ሲፈልጋቸው ምዕመነኑን ቤተ ክርስቲያን ሂድ ሲያሰኛቸው አትሂድ የሚሉት እስከመቼ ነው?
ከቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ መዋቅር የበለጠ ታምነው አስራትና በኩራት የሚሰበስቡት እስከመቼ ነው? .ምዕመኑ በሰጣቸው ገንዘብ የሆነ ቦታ ሄደው የሆነች ነገር አድርገው እግረ መንገዳቸውን የቤተ ክሕነተት ሰዎችን አንቋሸው የሚመለሱት እስከ መቼ ነው?

🖍 Abrham Yiheyis
👍71
2025/09/06 00:17:21
Back to Top
HTML Embed Code: