Telegram Web
.........የኢትዮጲያ የወራቶች አሰያየም ትርጉም.........

፩ መስከረም :) ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ከሪም ከሪሞት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ነው። ትርጉሙም መክረም ማለት ነው በግዕዝ "ምሴተ ክረምት" ይለዋል። የክረምት መምሻ ወይም የክረምት ጫፍ ማለት ነው። በስነቋንቋ ጥናት ብዙ ጊዜ 'ዝ' እና 'ስ' በፀሐፊ ስህተት ይወራረሳሉ። በጥንት ጊዜ መስከረም ሳይሆን መዝከረም ነበር የሚባለው ትርጉሙም የዓመት የዓመቱ ማሰቢያ ወይም አውዳመት ማለት ነው ።

. ጥቅምት :) ይኽም ጠቂም ጠቂሞት ወይም መጥቀም ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ነው። ትርጉሙም የተሰራች ስር ማለት ነው። ከሁሉም በተለየ ይህ ወር የስራ ወር እና የፍሬ ወር ነው ።

፫. ህዳር :) በዕብራይስጥ አዳር እንደማለት ነው ሀዲር ሀዲሮት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ነው። የህዳር ወር በሀገራችን ላይ እንደምናውቀው የአዝመራ ወር ስለሆነ እና ጠባቂዎች በዱር የሚያድሩበት ጊዜ ስለሆነ ስያሜው ሊሰጠው ችሏል ።

፬. ታህሳስ :) ይኸም ሀሲስ ሀሲሶት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ነው። ትርጉሙም ምርምር ማድረግ፣መፈለግ ማለት ነው።

፭. ጥር :) ይኽም ጠይሮ ጠይሮት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ነው። ትርጉሙም ምጥቀት ርዝመት ማለት ነው በዚህ ወር ኦዘፍ 11:1-7 እና በመፅሀፈ ኩፋሌ 10:12 እንደምናገኘው በሰናኦር አካባቢ 43 ዓመት የቆየ ቁመቱ 5432 ክንድ ከ2 ስንዝር የሆነ ህንፃ ተሰርቶ ነበር ነገር ግን የከላዳዉያን ቋንቋ ተደባልቆባቸው ህንፃቸው ፈርሷል ሊቃውንቱ ርዝመት ያለው ህንፃ የፈረሰበት ሲሉ ጥር ብለውታል ።

፮. የካቲት :) ይኸም ከቲት ከቲቶት ከሚለው ንዑስ አንቀፅ የወጣ ሲሆን ትርጉሙ ማስገባት ማለት ነው ድንቅ ነው የመኸር መካተቻ የበልግ መባቻ እንደማለት ነው ።

፯. መጋቢት :) ይኽም መግቦ መግቦት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ሲሆን የሌሊቱም የመዓልቱም እኩል የሚሆኑበት ማለት ነው ይህም ቀኑም 12 ሌሊቱም 12 ሰዓት እንሚመሆን የሚያመላክት ነው ።

፰. ሚያዚያ :) ይኽም ምሂዝ ምህዞት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ሲሆን መቅረብ፣ ማጀብ፣ ማክበር ማለት ነው። የሚዛዚት ወይም የሚዜወች የሙሽሮች ወራት ማለት ነው እንደሚታወቀው በሀገራችን የሰርግ ጊዜ በዚህ ወር የሚደረገው ይሄን ተንተርሶ ነው ።

፱. ግንቦት :) ይኽም ገንቦ ገንቦት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ሲሆን የክረምት አቅራቢያ የክረምት ጎን ማለት ነው። ሊቃውንት አባቶቻችን ለምን እንደዚህ ብለው እንደሰየሙት ግልፅ ነው ።

፲. ሰኔ :) በዕብራይስጥ ቋንቋ "ሴዋን" ይባላል። ይኽም ሰንይ ሰንዮት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ነው። ይኽም ማማር፣ መቆንጀት ፣ ማበብ ማለት ነው ።

፲፩. ሐምሌ :) ይኽም ሀሚል ሀሚሎት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ሲሆን መለምለም ማለት ነው።

፩፪. ነሀሴ :) ንሂስ ንሂሶት ከሚለው አርዕስት ጥሬ ዘር ስም ንዑስ አንቀፅ አባት ዘር የወጣ ሲሆን በዘይቤው ሲፈታ "ጥብቀት" ማለት ነው። የቃሉ ትርጉም በዚህ ወር አዝርዕት ስር የሚሰዱበት በቁመት የሚያድጉበት እንደሆነ ይዋጃል ።

፩፫. ጳጉሜ ትባላለች እንዴት ጳጉሜ እንደተባለች ?
አምስት እና ስድስት እንደምትሆን እናውቃለን ነገር ግን በ600 ዓመት አንድ ጊዜ ሰባት እንደምትሆንስ ያውቃሉ ?
ከሌሎቹ ወራቶች ሰፋ ያለ ዝርዝር እና ትንተና ሰለሚፈልግ ሀሳቡን በአጭሩ ይዘን እንመለስበታለን።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777

#ሼር
📜ይኽ የምትመለከቱት ጥቅልል ጥንታዊያን አባቶቻችን አዘጋጅተውልን ያለፉት ሲሆን ‘’ማዕሠረ አጋንንት” ይባላል።
📜 ማዕሠረ አጋንንት :) ትልቅ ጥበብ ያለበት የፀሎት ብራና ሲሆን አጋንንትን እያደኑ ወደ ጥልቁ ይጥሉበት እንደነበርም ይነገራል፤ ይኽም ማዕሠረ አጋንንት በበርካታ አስማተ መለኮት ( ስመ አምላክ ) የተሞላበት ነው።


@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777

#ሼር
📚ታሪከ ጎንደር📚

"ጎንደር" ማለት "ጉንደ ሀገር" ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም "የሃገር ግንድ፣ የሀገር መሠረት፣ ርዕሰ ሀገር ወይም የሀገር ራስ ማለት ነው። ይኼውም ኖህ ከጥፋት ውሃ በኋላ የተቀመጠበት በእንተላ ፣በአይዋርካ፣ በሽሌ፣ በአይከል፣ በኩል አድርጎ ጎንደር ላይ ብዙ ዘመን ፈጣሪውን እያመሰገነ እየቀደሰ የኖረባትና የተቀበረባት ቦታ በመሆኗ የሀገር መጀመሪያ ዋና ግንድ ተባለች። በ950 ዓ.ዓ ኖህ ሲሞት መቃብሩ ላይ ምንጭ ፈልቆ በርካታ ሰዎችን ይፈውስ ነበር። ከዚያም ለኖህ መታሠቢያ ይሆን ዘንድ አምላክ በቤተመንግስት አሳቦ የኖህ የመቃብር ሐውልት እንዲታነጽ ፈቀደ። ይኽም በኋለኛው ዘመን በንጉሥ ፋሲለደስ የታነጸው የፋሲል ግንብ ነው።ዐፄ ፋሲለደስም በ1629 ዓ.ም በመሀንዲስ አባ ገብረክርስቶስ መሪነት የእደ ጥበብ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ከኖህ መቃብር ላይ የቤተመንግሥቱን ታላቅ መሰረት ጥለውታል። ግንባታውም በ7 ዓመት ውስጥ ተጠናቀቀ። ዐፄ ፋሲል በቀሐ ወንዝ አጠገብ "ማንኪት" የሚባለውን ህንጻ በ17ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ግቢ መሀል ላይ 50 ሜትር በ25 ሜትር ስፋትና 2 ሜትር ጥልቀት ያለው የባህረ ጥምቀት ገንዳ አስገነቡ፡፡ ከቀሃ ወንዝ በተቆፈረ ቦይ ውሃ ተጠልፎ እንዲገባ አደረጉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ገንዳው ለጥምቀት በዓል መጠመቂያነት የሚያገለግል ሲሆን፣ ዐፄ ፋሲል ባሰሩት ጥንታዊ ህንፃ ደግሞ የታቦታቱ ማደሪያ ሆኖ ያገለግላል። መዋኛ ገንዳው በባእሉ ሰሞን የባንዲራ መቀነት ይታጠቃል፡፡ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከሆነችበት እስከ ጎንደር ዘመን ማክተሚያ ፈፃሜ መንግሥት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ድረስ 18 ነገሥታት የነገሡ ሲሆን እነዚህም አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ 44 የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የተተከሉበትን ጨምሮ እስከ ፈፃሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ ድረስ የተተከሉትን ብቻ ሲሆን ቁጥራቸውም 44 ነው፡፡ከዘመነ መሣፍንት እስከ አሁን የተተከሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም ከ44ቱ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ አርባአራቱ ታቦታተ በጎንደር ዘመን በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙና የነበሩ 44 አብያተ ክርስቲያናት ጥቅል ስም ነው፡፡ ይኽም ማለት አሁን ባለው የጎንደር ከተማ ክልል እና ዙሪያውን በሚገኙ አዋሳኝ የገጠር ቀበሌዎች ለምሳሌ፣ ጠዳ፣ ፈንጠር፣ ብላጅግ፣ ደፈጫ እና በመሳሰሉት ቦታዎች የሚገኙ አጠቃላይ የአድባራት ቁጥር ነው፡፡

🤍የአርባ_አራቱ_ታቦታት_ስም_ዝርዝር፦

፩. አዘዞ ተ/ሃይማኖት
፪. ፊት አቦ
፫. ፊት ሚካኤል
፬. አደባባይ ኢየሱስ
፭. ግምጃ ቤት ማርያም
፮. እልፍኝ ጊዮርጊስ
፯. መ/መ/መድኃኔዓለም
፰. አቡን ቤት ገብርኤል
፱. ፋሲለደስ
፲. አባ እንጦንስ
፲፩. ጠዳ እግዚአብሔር አብ
፲፪. አርባዕቱ እንስሳ
፲፫. ቀሐ ኢየሱስ
፲፬. አበራ ጊዮርጊስ
፲፭. አደባባይ ተ/ሃይማኖት
፲፮. ደብረ ብርሃን ሥላሴ
፲፯. ዳረገንዳ ኤዎስጣቴዎስ
፲፰. አጣጣሚ ሚካኤል
፲፱. ጐንደር ሩፋኤል-
፳. ደፈጫ ኪዳነ ምህረት
፳፩. ቅ.ዮሐንስ መጥምቅ
፳፪. ጐንደር ልደታ ማርያም
፳፫. ሠለስቱ ምዕት
፳፬. ጎንደር በአታ ለማርያም
፳፭. ወ/ነጐድጓድ ዮሐንስ
፳፮. ጐንደር ቂርቆስ
፳፯. ጐንደር ሐዋርያት(ጴጥሮስ ወጳውሎስ )
፳፰. ፈንጠር ልደታ
፳፱. ሰሖር ማርያም
፴. ወራንገብ ጊዮርጊስ
፴፩. ምንዝሮ ተ/ሃይማኖት
፴፪. ደ/ፀሐይ ቊስቋም
፴፫. ደ/ምጥማቅ ማርያም
፴፬. አባ ሳሙኤል
፵፭. ጐንደሮች ማርያም
፴፮. ጐንደሮች ጊዮርጊስ
፴፯. አባ ጃሌ ተ/ሃይማኖት
፴፰. ዐቢየ እግዚእ.ኪ/ምህረት
፴፱. ብላጅግ ሚካኤል
፵. አሮጌ ልደታ
፵፩. ጫጭቁና ማርያም
፵፪. ጋና ዮሐንስ
፵፫. አይራ ሚካኤል
፵፬. ዳሞት ጊዮርጊስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
ቅዱስ ድሜጥሮስ
📚..........የድሜጥሮስ ታሪክ.........📚

📝 ባሕረ ሐሳብን ለማወቅ ብዙ አባቶች ተመኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉ የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና የመንበረ እስክንድርያ አስራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ተጸልጾለታል።
📜 ድሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው። መስታወት፦ በጥርስ ያለውን እድፍ በጸጉር ያለውን ጉድፍ እንደሚያሳይ ሁሉ ድሜጥሮስም የተሰወሩ በዓላትን እና አጽዋማትን አሳይቶናል።
📜 አንድም ድሜጥሮስ ማለት መነጽር ማለት ነው። መነጽር፦ የራቀውን አቅርቦ ፣የረቀቀውን አጉልቶ፣ የተበተነውን ሰብስቦ እንደሚያሳየው ሁሉ ድሜጥሮስም የራቁ አዝማናትን አቅርቦ፣ የተበተኑ አጽዋማትን ሰብስቧልና  መስታወት ተብሏል።

ድሜጥሮስ ባጭር ታጣቂ፣ እርፍ አራቂ፣ ዲኮ ታጣቂ፣ ነገር አዋቂ፣ ፍርድ ጠንቃቂ  መስተገብረ ምድር/ገበሬ/ ነበረ። የድሜጥሮስ ኣባት ደማስቆ ወይም አስተራኒቆስ ይባል ነበር። ይህ የድሜጥሮስ አባት አርማስቆስ ወይም አስተራኒቆስ የሚባል ወንድም ነበረው። ይኖሩበት የነበረው ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ስለነበረ ሁለቱ ወንድማማቾች ከሀገራቸው ተሰደው በባዕድ ሀገር ይኖሩ ነበር። በምድረ ዓላውያን ክርስቲያኖች ያነሱበት ዓላውያን የበዙበት ስለሆነ የድሜጥሮስ አጎት ከመሞቱ በፊት ሴት ልጁን  ለሌላ ለአሕዛብ እንዳይድርበት ለድሜጥሮስ አባት አምሎት ሞቶ ነበር። በኋላ ድሜጥሮስም ሆነ የአጎቱ ልጅ ስሟ ልዕልተ ወይን/የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሚጠሩበት ስም ነው/ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ደርሰው ስለነበር ለሌላ ለአሕዛብ ድረናቸው ሕንፃ ሃይምኖት ከሚፈርስ ዘመዳሞችን አጋብተን ሕንፃ ስጋ /የዝምድና ግንኙነት/ ቢፈርስ ይሻላል በማለት ሁቱን አጋብተዋቸዋል። በጋብቻው ዕለት ስርዓተ መርዓት ወመራዊ ይፈጽሙ ብለው መጋረጃ ጥለውባቸው ሄደዋል። በዚህን ጊዜ ልዕልተ ወይን አምራ አለቀሰች። እንዲህም ብላ ጠየቀቸው፤ እኔን ንቀህ ነው? ወይስ ተዘምዿችንን? እንዴት አህትህ /የአጎትህ ልጅ/ ስሆን እኔን ታገባለህ? አለቸው። እርሱም እኔ አንቺንም ሆነ ተዘምዿችንን ንቄ አይደለም “አላ ከመ እፈጽም ፈቃደ አቡየ- ይልቁንም የአባቴን ፈቃድ ልፈጽም ብዬ ነው’ አላት። እንግዲያውስ ፈቃድሽ ከሆነ አንቺም ሴት እኔም ወንድ እንደሆንን በአዳማዊ ሩካቤ ሳንተዋወቅ መኖር እንችላለን። ለሌላም እንዳያጋቡን ባልን ሚስት መስለን በአንድ ላይ እንኑር አላት። እርሧም ደስ ብሏት ሀሳቡን ተቀበለች። ሁለቱም አንድ ምንጣፍ አንጥፈው፣ አንድ አንሶላ ተጋፈው እያደሩ በድንግልና አርባ ስምንት ዓመት ኑረዋል። ቅዱስ ሚካኤልም እንድ ክንፉን ለእርሱ አንድ ክንፉን ለእርስዋ እየጋረደ አድሮ በጠዋት በአምሳለ ርገብ በመስኮት ወጥቶ ሲሄድ ይታይ ነበር።

~ በዚህ ዘመን የመንበረ እስክንድርያ አሰራ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ዩልያኖስ ወይም ዩልዮስ የተባለው ዕድሜው ገፍቶ አርጅቶ ስለነበር ሕዝቡን ሰብስቦ ከእኔ በኋላ የሚሾመውን ሰው ምረጡ አላቸው። ሕዝቡም ‘’አባታችን እኛ ምን እናውቃለን? አንተ ሱባዔ ገብተህ ጸልየህ ንገረን እንጂ’’ አሉት እርሱም “እናንተም ጸልዩ እኔም እጸልያለሁ” አላቸው። በሶስተኛው ቀን መልአከ እግዚአብሔር ለሊቀ ጳጳሱ ተገልጾ ያለጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ እና የስንዴ ዛላ ይዞልህ የሚመጣው  ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነውና  እርሱን ሹመው ብሎ ነገረው። በዚህም ዕለት ቅዱስ ድሜጥሮስ እርሻውን ሊያቃና ወደ አዝመራው ሲገባ ያለጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ እና የስንዴ ዛላ አገኘ፤ ወስዶም ‘ለሚስቱ’ ሰጣት። እርሷም “ይህንን እኛ ልንመገበው አይገባም ይልቁንም ወስደህ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተህ ከሊቀጳጳሱ በረከት ተቀበል’’ ብላ ላከቸው። እርሱም ይዞ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄድ ሊቀ ጳጳሱም ሕዝቡን ሰብስቦ መልአኩ የነገረውን እየነገራቸው እያለ ድሜጥሮስ ገብቶ ስጦታውን ለሊቀ ጳጳሱ አበርክቶ ወጣ። ከወጣ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ለሕዝቡ ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው እሺ አይለችሁም ነገር ግን ግድ ብላችሁ አስቀምጡት ብሎ ነገራቸው።

~ ከጥቂት ቀናትም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ አረፈ። ሕዝቡም  መንበር  ባዶውን አያድርምና ድሜጥሮስን ተሾምልን ብለው ጠየቁት። እርሱም ደንግጦ “እኔ በአንድ በኩል ምንም ያልተማርኩ /ጨዋ/ ገበሬ ነኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያገባሁ ሕጋዊ ነኝ እንዴት በንጹህ በማርቆስ ወንበር እቀመጣለሁ? አላቸው። እነርሱም አንተ እንደምትሾም አባታችን ነግሮናል! በማለት ግድ ብለው አስቀመጡት። ከዚህ በኋላ ድሜጥሮስ ሕዝቡን አባታችን ምን ምን ያስተምራችሁ ነበር? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም አላውቅም ብትለን ነው እንጂ አባታችንማ አንቀጸ ኖሎትን አንቀጸ አባግዕን ተርጉሞ ያስተምረን ነበር አሉት። በዚህን ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት/ብሉያትና ሐዲሳት ተገልጸውለት አንቀጸ ኖሎትን አንቀጸ አባግዕን  ተርጉሞ ለሕዝቡ አስተምሯቸዋል።

📚ድሜጥሮስ እጅግ የበቃ ሰው ነበርና ቀድሶ ሲያቆርብ የሰው ኃጢአት ተገልጾለት ‘’አንተ ለስጋ ወደሙ በቅተሃል ቁረብ፣ አንተ አልበቃህም ተመለስ’’ ይል ነበር። በዚህን ጊዜ ሕዝቡ ‘’በንጹሑ በማርቆስ ወንበር ላይ ከነሚስቱ መቀመጡ አንሶት እርሱ እንዳንቆርብ ይከለክለን ጀመር’’ በማለት በሐሜት ወደቁ በዚህም የሚጎዱ ሆኑ። በዚህን ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ለድሜጥሮስ ተገልጾ ‘’ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእስከ አላ ክሥት ዘሀሎ ምስሌከ ወማእከለ ብእሲትከ'' በአንተና በእርሷ መካከል ያለውን ሚስጢር ግለጽ፤ ኖላዊሰ ኄር ዘይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግዒሁ - እውነተኛ እረኛ ለበጎቹ እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነውና፤ እራስህን መግለጽ ውዳሴ ከንቱ አይሆንብህም’’ ብሎታል። ድሜጥሮስም መልአኩ እንዳዘዘው ሕዝቡን አንድ አንድ እንጨት ይዘው እንዲመጡ አዟቸዋል። በዕለተ ሰንበትም የተሰበሰበውን እንጨት እንደ መስቀል ደመራ አቃጥሎ ቅዳሴ ገባ። ከቅዳሴም ከወጣ በኋላ በሚነደው እሳት ውስጥ ገብቶ እየተመላለሰ ያጥን ጀመረ። ‘ሚስቱን’ ከምቋመ አንስት ጠርቶ ስፍሒ አጽፈኪ - ልብስሺን ዘርጊ ብሎ ከእሳቱ ፍም እየዘገነ በልብሷ ላይ አድርጎላታል። እርሷም በሕዝቡ መካከል ዞራ ብታፈሰው ከልብሷ ዘሃ አንዲት እንኳን አልጠቆረም። ሕዝቡም አባታችን ይህንን ያደረከው ለምንድን ነው? ብለው ጠየቁት። እርሱም እኔ እሾምበት እከብርበት ብዬ አይደለም ይልቁንም እናንተ በሐሜት እንዳትጎዱ በማለት መልአከ እግዚአብሔር ግለጽላቸው ስላለኝ ነው። ይህ እሳት እኔ እና እርሷን እንዳላቀጠለን ሁሉ ይህን ያህል ዘመን አንድ ምንጣፍ አንጥፈን አንድ አንሶላ ተጋፈን ስንኖር በአዳማዊ ግንኙነት /በሩካቤ / ሳንተዋወቅ እርሷ ሴት እኔም ወንድ እንደሆንን ነው የምንኖረው አላቸው። በዚህን ጊዜ ሕዝቡ “ኦ አቡነ ሥረይ ለነ ኃጢአተነ - አባታችን ሆይ ይቅር በለን” በማለት ከእግሩ ስር ወድቀዋል። እርሱም “ይፍታሕ ወይሥረይ ይኅድግ ወያንጽሕ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ብሎ ናዝዋቸዋል። ኑዛዜም በዚህ ጊዜ እንደተጀመረ አባቶቻችን ይናገራሉ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

..............ይቀጥላል


@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
የቀጠለ

📚 ቅዱስ ድሜጥሮስ ከ188 – 230 ድረስ ለአርባ ሁለት ዓመት በእስክንድርያ መንበር ላይ በሊቀ ጵጵስና ቆይቷል። በዚህ ጊዜ አንድ ታላቅ ምኞትን ይመኝ ነበር። ይኸውም ጾመ ነነዌ፣ በዓለ ዐቢይ  ጾም እና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ በዓለ ርክበ ካህናት፣ ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፤ በዓለ ዕርገት ከሐሙስ፤ በዓለ ስቅለት ከዐርብ፤ በዓለ ደብረ ዘይት፣ በዓለ ሆሣዕና ፣ በዓለ ትንሣኤ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ ባይወጡ ባይነዋወጡ በጥንት ዕለታቸው ቢውሉ በወደድኩ ነበር እያለ ይመኝ ነበር። መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾ ነገር በምኞት ይሆናልን? ሱባዔ ገብተህ አግኘው አለው። ከሌሊቱ ሃያ ሦስት ሱባዔ ገብተህ አበቅቴ ፤ ከቀኑ ሰባት ሱባዔ ገብተህ መጥቅዕ ይሁንህ ብሎ ነገረው። ምነው ቀኑን አብዝቶ ሌሊቱን አሳነሰው ቢሉ ቀን የተበደለ ሲያስክስ ፣ የተቀማ ሲያስመልስ የተራበ ሲያበላ፣ የተጠማ ሲያጠጣ፣ የታረዘ ሲያለብስ፣ የታሰረ ሲጎበኝ በአጠቃላይ ምግባረ ጽድቅ ሲሰራበት ይውላል። ስለዚህ ሌሊት ከእንቅልፉ  ቀንሶ እንዲጸልይበት አድርጎታል።

ሃያ  ሶስት ሱባዔ ማለት አንድ ሱባዔ ሰባት ቀን ነው፤ ሃያ ሶስቱ ሱባዔ /23 × 7/ = 161 ይሆናል። እዚህ ጋር የምናነሳው አንድ አዋጅ አለ።

አዋጅ፦ ማንኛውም ቁጥር ከሰላሳ ከበለጠ በአውደ ወርኅ /በሰላሳ/ ግደፈው ወይም
         አካፍለው።

ስለዚህ መቶ ስልሳ አንድን በሰላሳ ስንገድፈው /161 ÷ 30/ = 5 ጊዜ ደርሶ 11 ይቀራል። ይህ አስራ አንድ ጥንተ አበቅቴ ይባላል። አበቅቴ ማለት ስፍረ  ሌሊት፣ ቁጥረ ሌሊት ማለት ነው።

ሰባት ሱባዔ ማለት /7 × 7/ = 49 ይሆናል። አርባ ዘጠኝን በሰላሳ ስንገድፈው /49 ÷ 30/ = 1 ጊዜ ደርሶ 19 ይቀራል። ይህ አስራ ዘጠኝ ጥንተ ጥንተ መጥቅዕ ይባላል። መጥቅዕ ማለት ደወል ማለት ነው። ደወል በተመታ ጊዜ የራቁ ይቀርባሉ፣ የተበተኑ ይሰበሰባሉ፤ እንዲሁም ሁሉ ይህ መጥቅዕ የበዓላትና የአጽዋማት መሰብሰቢያ ወይንም ማውጫ ነው።

ሁለቱን ማለትም አበቅቴና መጥቅዕ በአንድ ላይ ተደምረው ከሰላሳ አይበልጡም ከሰላሳ አያንሱም። መጥቅ ሲበዛ አበቅቴ ያንሳል፤ አበቅቴ ሲበዛ መጠቅዕ ያንሳል እንጂ ከሰላሳ አይበልጡም ከሰላሳም አያንሱም። እዚህ ጋር ሁለት አዋጆች አሉ። እነርሱም፦

 አዋጅ፦ 1. አበቅቴ ወመጥቅዕ ክሌሆሙ ኢየዓርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወትረ ይከውኑ

           ፴ - አበቅቴና መጥቅዕ ከሰላሳ አይበልጡም ከሰላሳም አያንሱም ሁልጊዜ ሰላሳ  ናቸው።

          2.  ኢይኩን አሐደ ለመጥቅዕ - መጥቅዕ ምንም ያህል ቢያንስ አንድ አይሆንም።

 መጥቅዕ አንድ ሲሆን አልቦ ወይም ዜሮ አበቅቴ ይሆናል። በየአስራ ዘጠኝ ዓመቱ አበቅቴ ዜሮ ይሆናል። ምክንያቱን በተገቢው ቦታ ላይ ይብራራል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቀጥላል…  

@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
📃በመጀመሪያ በዚህ ትምህርት ላይ መታወቅ ያለባቸው ጥቂት ጥሬ ቃላቶች ከነትርጉማቸው

፩. ሰንበት => እንደ ቃሉ አገባብ ሱባዔ
፪.መጠነ ራብዒት => አንድ አራተኛ የዓመተ ዓለሙ ሩብ
፫. አበቅቴ => ተረፈ አመት
፬. መጥቅዕ =>አዋጅ መንገሪያ ደወል(ነጋሪት) እንዲሁም የበዓል እና አጽዋማት ማውጫ(የመባጃ ሐመር መገኛ)
፭. ሐሳበ ዘመን => ባህረ ሐሳብ (ተዘክሮተ አዝማን)
፮. ዐውድ => ዙሪያ |ክበብ| አደባባይ
፯. ጥንተ ቀመር => ቀመር የተጀመረበት ማግሰኞ
፰. ተውሳክ => ተጨማሪ /ማስተካከያ/ ከመባጃ ሐመር ጋር የሚታሰብ

~ በቀጣይ መርሐግብራችን ላይ ባሕረ ሓሳብን በተመለከተ ስለ መጥቅዕና አበቅቴ አገልገሎት እንዲሁም የዕለታት፣የአጽዋማት እና የበዓላት ተውሳክን የምንመለከት ይሆናል።

@yekidst_hager777
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ።
.......ጥር 10 - ጾመ ገሃድ.......

📖. ጾመ ገሃድ ማለት መገለጥ ማለት ነው። ዕለቱ ጥምቀት ስያሜ የተሰጠው ቅድመ.ዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ 5500 ዘመን ሲፈጸም በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉ ነፍሳትን ሥጋውን ተቆርሶ ደሙን አፍስሶ ለማዳን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ያለዘርዓ.ብዕሲ ሕግ መጽሐፋዊ ሕግ ጣባዕያዊ ሲፈጽም አድጎ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ፍጡር ስጋን ተዋህዷልና ዘመን እየተቆጠረለት 30 ዓመት ሲሆነው ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ክብሩን ጌትነቱን የገለጠበት በመሆኑ ነው። ዛሬም ታቦታቱ ወንዝ ወርደው ማደራቸው ጌታን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱን ለማዘከር ነው።
📖. በተጨማሪ ገሀድ የረቡዕ የዓርብ ለውጥ ነው። በዓለ ጥምቀት ረቡዕ የዋለ እንደኾነ ማግሰኞ፣ ዓርብ የዋለ እንደኾነ ሐሙስ ተለውጦ እስከ ዕርገተ መስዋዕትም ቢሉ እስከ ዕርበተ ፀሐይ ይፆማል። ስለምን ቢሉ በዘጠኙ አብይት በዓላት በሰንበተ ክርስቲያንና በዘመነ ትንሳዔ መጾም ማዘን አይገባምና ፍዳ የሚያመጣ ነውና። መጾም ማዘን ፍዳ ያመጣልን? ቢሉ አያመጣም።እኒህ ዕለታት በዓላት ግን በጾም በድካም ያይደለ በብርታት በኀዘን ያይደለ በመንፈሳዊ በደስታ ልናከብራቸው የሚገቡ ዕለታት ፍሥሕ ናቸውና።

.ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን


@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
.......ጥር 11 በዓለ.ጥምቀት.......

📚. አጥመቀ አጠመቀ /ነከረ/ ከሚል የግዕዝ ሥርወቃል የተገኘ ሲሆን ጥምቀት ማለት መነከር ማለት ነው።
📖. ጥምቀት ስምንት ወገን ነው። አምስቱ ምሣሌያውያን ሶስቱ አማናውያን ናቸው።
ምሣሌያውያኑ አጥመቃ ለምድር በማአይኅ ፤ አጥመቆሙ ሙሴ በደመና ወበባሕር 1ቆሮ 10:2፤ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት ኢያ 3:15 ያላቸው ማየ አይኀ፣ ማየ ኤርትራ፣ ማየ ኢያሪኮ፣ ጥምቀተ አይሁድና ጥምቀተ ዮሐንስ ናቸው።አማንያውያኑ ጥምቀተ ወልድ፣ ደመ ሰማዕትና አንበዐ ንስሓ ናቸው።
ጥምቀተ ወልድን ከዚህ ይናገሩታል። ጌታ ከእመቤታችን በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፤ በተወለደ በ40 ቀኑ ዕጉለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዞ ወደቤተ እግዚአብሔር በመግባት በዓመት ሦስት ጊዜ ለበዓል ኢየሩሳሌም በመውጣት ሕገ.መጽሐፋዊን ሕግ ጠባዕዋን ሲፈጽም፣''በበህቅልህቀ እንዘይትኤዝ ለአዝማዲሁ እንተ ያእቲ እሙ'' እንዲል : ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ 30 ዓመት ሲመላው ወደ ዮርዳኖስ ሄደ። ዕለቱ ሠሉስ/ማክሰኞ/ ጊዜው 10 ሰዓት ሌሊት ነው። ዮሐንስን እጥምቀኝ አለው። ጌታዬ እኔ ባንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጅ አንተ በኔ ትጠመቃለህን? አለው። ወይደልወነ ከመ.ንፈጽም ኩሎ ሕገ ሕግን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል አለው። ''እንኪያስ ሰበ አጠምት ካልዐ አጠምቅ በስምከ ወሶ አጠምቅ ኪያከ በስመ መኑ አጠምቀከ'' ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ እያልህ አጥምተኝ አለው። ከውኃው ሲገባ ዮርዳኖስ ወደኋላ ሸሸች: ባሕርኑ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኀሬሁ እንዲል መዝ 113:5 ውሆች ተናወጡ ተራሮች ሽቅብ እንደጊደር ዘለሉ። ኋላ ግን በሰውነቱ ተናግሮ በአምላክነቱ አጽንቷቸው ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ እያለ አጥምቆታል። ከውኃውም ሲወጣ አብ በደመና ሆኖ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ሎቱ ስምዕዎ ብሎ የባሕርይ ልጅነቱን መስክሮለታል መንፈስ ቅዱስም በአምሳሌርግብ ጸዓዳ ወርዶ በራሱ ላይ አርፎበታል: ማቴ 3፡13-17
ከፍ ብሎ በ31 ዝቅ ብሎ በ29 ዓመት አለመጠመቁ በ30 ዓመት መጠመቁ ስለምንድን ነው? ቢሉ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በ40 ቀን እግኝቶ ኋላ ያጣትን ልጅነት ለማስመለሰ ይሏል: ያም ቢሆን አምላክ ሲሆን በዕሩቅ ብእሲ እጅ መጠመቁ ስለምንድ ነው? ቢሉ ትሕትናውን ለመግለጽ ነው አስጠርቶ ካለበት መጠመቅ ሲችል ወደርሱ ሂዶ መጠመቁ ስርዓት ለማስተማር ነው። ስመ እግዚአብሔር ከሚጠራበት መስዋዕት ከሚሰጥበት ከቤተ ክርስቲያን ሂዳችሁ ተጠመቁ ሲል ነው። አስጠርቶ ተጠምቆ ቢሆን ዛሬ መኳንንቱ መሳፍንቱ ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር።

እስመ.ዚአየ ውእቱ ኩሉ ዓለም በምልዑ መዝ49፡12 እንዲል በማር በወተት በሽቱ መጠመቅ ሲችል በውኃ መጠመቁ ስለምንድን ነው? ቢሉ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ይሏል። ወእነዝሀክሙ በማይ ቅዱስ ወትነጽሑ እምርኩስክሙ ኢሳተብሎ ተናግሯልና። አንድም ማር ሊልሱት ወተትም ሊጠጡት እንጅ ሊታጠቡባቸው አልተፈጠሩምና። ዳግመኛም በማር በወተት ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ነዳያን አጥተው ሳይጠመቁ ይቀሩ ነበርና ጥምቀት የተሰራ ለሁሉ ነውና ሁሉ በሚያኘው በውኃ ተጠመቀ።
ብዙ ውሆችም ሳሉ ዮርዳኖስን መምረጡ መጽሓፈ ዕዳችንን ሊያጠፋ ነው። ዲያበሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ስመ ግብርናት ጽፋችሁ ብትሰጡኝ አገዛዝ ባቀለልሁላችሁ ነበር አላቸው። ''አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብለው ጽፈው ሰጡት ያን በሁለት ዕብነ ሩካም ቀርጾ አንዱን በዮርዳኖስ ሁለተኛውን በሲኦል ጥሎት ነበር። በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ረግጦ እንደአምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶታል። በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለነፍስ ወርዶ አጥፍቶላቸው ወጥቷል። ስለዚህ ነው። አንድም ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረሕያዋን ገብቷል። ዮርዳኖስ የጥምቀት ኤልያስ የምእመናን ምሣሌ ያመነ የተጠመቀ ገነት መንግሥተ ሰማያት የሚግባ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። በ10ኛው ሰዓተ ሌሊት መጠመቁም ምሥጢረ መንግሥቱን በጎላ በተረዳ ለመግለጽ ነው። በቀን ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ መንፈስ ቅዱስ በአምሳሊርግብ ሲወርድ መነኛ ርግብ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ባሉት ነበርና።


.ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን


@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
@yekidst_hager777
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን መልካም በዓል።
​​​​ዐቢይ ጾም

ዐቢይ ለምን ተባለ ቢሉ ‹‹ዐበየ›› ማለት ከፍ አለ ማለት ሲሆን ከዚህም ግስ አቢይ የሚለው ቅጽል ይገኛል፡፡ ዐቢይ ማለት ከፍ ያለ ትልቅ ማለት ነው፡፡

ዐቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት፡-

ሀ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ

ለ. በቀኑ ቁጥር ከሌሎች አጽዋማት የሚበልጥ ስለሆነ

ሐ. ሦስቱ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች ማለትም 'ትዕቢት' 'ስስት' 'ፍቅረ ነዋይ' ድል የተመቱበት ስለሆነ ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ስያሜ መሰረት በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚውሉ ሰንበታት እያንዳንዳቸው መጠሪያ ስም ሲኖራቸው እነርሱም፡-

1. ዘወረደ
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሰንበት ሲሆን ይህም ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን ፈጥሮ የሚኖር አልፋና ኦሜጋ ከሰማየ ሰማያት መውረዱንና ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንጽሕተ ንጹሐን ከድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመለክት ሥያሜ ነው፡፡

2. ቅድስት
ይህ የሁለተኛው ሰንበት ስያሜ ሲሆን የተባለበትም ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው፡፡ እንዲሁም ይህ ዕለት ዕለተ እግዚአብሔር የተባለች የሰንበት ክርስቲያን ቅድስናን ያመለክታል ምክንያቱም የዚች ዕለት ጌታ እርሱ ቅዱስ እግዚአብሔር ነውና ስለዚህም ዕለተ ሰንበት ቅድስት ተብላለች፡፡

3. ምኩራብ
ይህ የሦስተኛው ሰንበት ስያሜ ሲሆን በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡ እንዲሁም ይህች ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ገብቶ እንዳስተማረ የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ ምኩራብ ማለት የቤተ አይሁዳውያን የጸሎት ቤት ነው፡፡

4. መጻጉዕ
ይህ የአራተኛው ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱ እውራንን ማብራቱ ለምጻምን ማንጻቱ ሽባዎችን መተርተሩ የሚያነሳ መዝሙር የሚዘመርበት እንዲሁም እነዚህ ሁሉ ድንቅ ገቢራተ ታምራቶች የሚዘከሩበት ዕለት ነው፡፡

5. ደብረ ዘይት
ይህ የአምስተኛው ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ነገረ ምጽአቱን እንዳስተማረ የሚወሳበት ሰንበት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት ወይራ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡

6. ገብርኄር
ይህ የስድስተኛው ሳምንት ሰንበት ስያሜ ሲሆን ይህም ዕለት ለጌታው ታማኝና በጎ የሆነው ባርያ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ተብሎ እንደተመሰገነ የሚነገርበት ዕለት ነው፡፡

7. ኒቆዲሞስ
ይህ የሰባተኛው ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ይህም ዕለት ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ መምህር በሌሊት ወደ ጌታው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየመጣ ይማር እንደነበረ ይታሰብበታል በዚም ዕለት የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

8. ሆሳዕና
ይህ የስምንተኛው ሳምንት ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት በነቢዩ በዘካርያስ ላይ የተጻፈው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቷ እና በውርንጭላይቷ ላይ ተቀምጦ ሆሳዕና በአርያም ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ተብ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱ የሚተሰብበት ዕለት ነው፡፡ ሆሳዕና ማለት ‹‹እባክህ አሁን አድን አሁን ባርከን›› ማለት ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሃት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሃትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው::

ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን፡፡
@yekidst_hager777
​​​​ዐቢይ ጾም

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ (ፍትሃ ነገስት አንቀፅ.15) “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡

መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17 ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው። መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10

ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾመው ለአብነት፣ ለማስተማር፣ ለአርዓያ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፣ ከሰው የሥጋ ጠባይ የሚመጣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ድል የተነሱበት ነው፡፡ እኛም ይህን እያሰብን በተለያየ መንገድ የሚመጣብንን ፈተና ለማራቅ ከዚህ ታላቅ ጾም በረከት እንድናገኝ እንጾማለን፡፡ ጸልዮ ጸልዩ፣ ጾሞ ጹሙ ብሎናል፡፡ ማቴ.6-16፡፡ ስለዚህም ትእዛዙን ለማክበር እንጾማለን፡፡

የዚህ ታላቅ ጾም ስያሜዎች የሚከተሉት ናቻው ፡-

ዐቢይ ጾም
ባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል፡፡

ጾመ ሁዳዴ
በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡

የካሳ ጾም
አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡ በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ካሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ፡፡

የድል ጾም
አርዕስተ ኃጣውእ /ማቴ. 4/ ድል የተነሱበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል፡፡

የመሸጋገሪያ ጾም
ጌታችን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሊያሸጋግረን የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል፡፡

ጾመ አስተምህሮ
ጌታችን የጾመው ለትምህርት ነው፡፡ እርሱ መጾም ያለበት ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ጾም ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2

የቀድሶተ ገዳም ጾም
ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ /በገዳመ ቆሮንጦስ/ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል፡፡

የመዘጋጃ ጾም
ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡

የሥራ መጀመሪያ ጾም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ በምድር ሳለ ስብከት፣ ተዓምራት ከመጀመሩ በፊት የጾመው ጾም ነውና የሥራ መጀመሪያ ጾም ይባላል።
#ሰሙነ ሕማማት

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሳኤ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

📖ሰኞ

መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፦
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

አንጽሖተ ቤተመቅደስ ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

📖ማክሰኞ

የጥያቄ ቀን ይባላል፦
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

የትምህርት ቀን ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

📖ረቡዕ

ምክረ አይሁድ ይባላል፦
ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

የእንባ ቀን ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

📖ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፦
ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

የምስጢር ቀን ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድህነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

📖ዓርብ

የስቅለት ዓርብ ይባላል፦
ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

መልካሙ ዓርብ ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

📖ቅዳሜ

ቀዳም ስዑር ትባላለች ፦
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።
ለምለም ቅዳሜ ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።
╔═★══════════📄══╗
@Zemaryan
@Zemaryan
@Zemaryan
╚══📃══════════★═╝
🌻እንኳን በፀሐይ ከ7514 ወደ 7515 ዓመተ ዓለም በሰላም አደረሳችሁ🌼   

🌻እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ🌼 

🌻እንኳን በጨረቃ  ከ7744 ከ7 ወር ከ28 ዕለት ወደ 77445 ከ8 ወር ከ9 ዕለት በሰላም  አደረሳችሁ።🌻        

🌻መጪው ዘመን ማለትም ዘመነ ሉቃስ፦
      🌻~ የሰላም🌼
      🌻~የፍቅር 🌼
      🌻~የአንድነት🌼
      🌻~የመተሳሰብ 🌼
      🌻~የተለያዩ መዛግብትን   🌼              
     የምንመረምርበት     
     🌻~በህዋ ላይ የምንራቀቅበት🌼
     🌻~የኢትዮጵያን ትንሳኤን🌼 የምንመለከትበት ቸሩ አምላካችን የበረከት ዘመን ያድርግልን።🌻   


    🌻መልካም አዲስ አመት እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ🌼

         
             🌼እንቁ ለጣጣሽ🌻
             🌻እንቁ ለጣትሽ🌼
ጥር 22 ቀን በግብፅ አገር ከአቅማን ከተማ የከበረና የገነነ የመነኰሳት ሁሉ አባት በገዳም ለሚኖር እንደ ኮከብ የሚያበራላቸው አባት እንጦንስ የእረፍቱ መታሰቢያ ነው።

#የአባ_እንጦንስ_ምክሮች

✞ ከዕለታት በአንድ ቀን አባ ፓምቦ አባ እንጦስን "ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?" ብሎ ይጠይቃል።አባ እንጦስም እንዲህ ሲል መለሰለት "በራስህ ጽድቅ አትታመን፤ላለፈው አትጨነቅ፤ይልቁኑ አንደበትህንና ሆድህን ግዛ።"

✞ አባ እንጦስ በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፦ "በዚች ምድር ላይ ስንኖር ህይወታችንንም ሆነ ሞታችን ከባልጀራችን ጋር ነው። ወንድማችንን ገንዘብ ካደረግነው እግዚአብሔርን ገንዘብ እናደርጋለን፤ ወንድማችንን ካስቀየምነው ግን በክርስቶስ ላይ ኃጢአትን እናመጣለን።"

✞ በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አባ እንጦስን "ጸልይልኝ" በማለት ይጠይቃል። እንጦስም "አንተ ራስህ ጥረት የማታደርግና ወደ እግዚአብሔር የማትጸልይ ከሆነ እኔም ሆንሁ እግዚአብሔር ምህረት ልናደርግልህ አንችም" አለው።

✞ እግዚአብሔር ሆይ አፈርና ትቢያ ሆኜ ሳለ ጻድቅ አድርገው  ከሚቆጥሩኝ ሰዎች አድነኝ።

✞ ኃጢአታችንን እኛ እያሰብን የምንፀፀት ከሆነ እግዚአብሔር ይረሳልናል፤ ኃጥያታችንን እኛ እረስትን የምንፅናና ከሆነ እግዚአብሔር ያስብብናል።

✞ ብዙ ጊዜ ሰዎች ብልህ ነን እያሉ ይሳሳታሉ። ነገር ግን ብልህ የሚባሉት ብዙ የተማሩና ብዙ ያነበቡ ብዙ የሚናገሩ ብቻ አይደሉም። ይልቁንም ጠቢባን የሚባሉት ጥብብት መጥበቢት ብልህ ነፍስ ያላቸው፤ የእግዚአብሔርንና የሰይጣንን ለይተው ለእግዚአብሔር ሆነው የሚኖሩ ናቸው። ፍጹም ምልዓተ ኃጢአትንና ከጦር ይልቅ የሚወጉ የኃጢአት እሾሀቸውን የነቀሉ ናቸው ጠቢባን።

✞ ጠቢባንስ እግዚአብሔርን ያለጥርጥር በሙሉ ልብ የሚያምኑት፤ አምነውም እንደ ፈቃዱ የተከተሉት፤ በክንፈ ጸጋ ተመስጠው ከልብ በሚወጣ ውዳሴ ከእርሱ ጋር ተዋሕደው የሚኖሩ ናቸው። የነፍሳቸውን ረብሕ ጥቅም አውቀው ዕለት ዕለት ያንን የሚለማመዱ በእውነት ጠቢባን እነዚህ ናቸው።

✞ የጋለ ብረትን ለመቀጥቀጥ የሚነሣ ሰው አስቀድሞ በብረቱ ምን ለመሥራት እንዳሰበ መወሰን አለበት፤ መጥረቢያ፥ ሰይፍ፥ ወይስ ማጭድ? እኛም በምን ዓይነት የሕይወት መስመር ፍሬ ለማፍራት እንዳሰብን አስቀድመን ልቡናችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡

✞ ዘወትር በዐይንህ ፊት ፈሪሃ እግዚአብሔር ይኑር፤ ሕይወትና ሞት የሚሰጠውን አዘክረው፡፡ ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ ጥላው፤ ከሥጋ የሚመጣውን ደስታና ሰላም አትሻ፤ ለዚህኛው ኑሮ ሙትና ለእግዚአብሔር ሕያው ሁን፤ ለእግዚአብሔር ቃል የገባኸውን አትርሳ፤ ያም በፍርድ ቀን ካንተ ይፈለግብሃል፡፡ ረኀብን በጸጋ ተቀበለው፤ ተጠማ፥ ተራቆት፥ ንቁና በሐዘን የምትኖር ሁን፡፡ በልቡናህ አልቅስና ጩኽ፤ ለእግዚአብሔር የምትመች መሆን አለመሆንህን ፈትን፤ ሥጋህን ቀጥተህ ነፍስህን ታድናት ዘንድ፡፡

✞ የቱንም ያህል በመከራ ቢወድቅብህ የቱንም ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍ ይህንን ለጌታዬ ለመድኃኒቴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስል እቀበላለሁ በል። ቀላል ይሆንልሀል። የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ኃይል ነውና። በእርሱ ማእበሉ ፀጥ ይላል ሰይጣንም ይሸሻል።

✞ ለተወሰን ጊዜ ለሀይማኖት መከራከር፤ ጠበቃ መሆን፤ መዋጋት ብሎም መሞት አይከፋም ሁልጊዜ ለሀይማኖት መኖር ግን ከሁሉ የበለጠ መስዋእትና ክብር ያለው ህይወት ነው፡፡

(#ከተለያዩ_ጽሑፎች_የተሰበሰቡ)
2025/01/19 06:56:10
Back to Top
HTML Embed Code: