tgoop.com/AndEmnet/13550
Last Update:
#ቅዱሳን_መክሲሞስ_ማንፍዮስ_ፊቅጦር_ፊልጶስ (ስንክሳር)
➯ዳግመኛም በዚህች ቀን ከአፍራቅያ የሆኑ ቅዱሳን መክሲሞስ፣ ማንፍዮስ፣ ፊቅጦርና፣ ፊልጶስ በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመን በሰማዕትነት አረፉ።
➯በዚህም ከሀዲ ንጉሥ ዘመን ሰባቱ ደቂቅ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት አንቀላፍተው የነቁ ከእርሱ በሸሹ ጊዜ ነው። እሊህም ቅዱሳን መስተጋድላን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ክዶ ክርስቲያኖችን ሲአሠቃይ በአዩት ጊዜ ሃይማኖታቸውን ግልጥ ያደርጉ ዘንድ በአንድ ምክር ተስማምተው በአንድነት ተሰብስበው ወደ ከሀዲው ንጉሥ ቀረቡ እኛ በእግዚአብሔር ልጅ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጥ የምናምን ክርስቲያኖች ነን ለእርሱም እንሰግዳለን እናመልከዋለንም ብለው ጮኹ።
➯ይህ ከሀዲ ዳኬዎስም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ እንዲገርፉአቸው አዘዘ አንድ ጊዜም ሁለት ጊዜም ታላቅ ግርፋትን ገረፏቸው በእሳት በአጋሉትም ከብረት በተሠሩ በትሮች ደበደቧቸው።
➯ከዚህም በኋላ በበርኖስ እላቂ ጨርቅ ከመጻጻና ከጨው ነክረው ቊስላቸውን አሹአቸው የንጉሡንም ትእዛዝ ባልሰሙ ጊዜ ሥቃዩንም ፈርተው ከበጎ ምክራቸው ባልተመለሱ ጊዜ ቁጣን በማብዛት ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸው። ከዚያ የነበሩ ብዙ ሕዝብም ትዕግሥታቸውን በአዩ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ በዚያንም ጊዜ ንጉሥ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ እንደዚህም የምስክርነታቸውን ተጋድሎ ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
➯ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።
@AndEmnet #ስንክሳር ህዳር ፩/1 ቀን
BY "፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel
Share with your friend now:
tgoop.com/AndEmnet/13550