tgoop.com/Dagmele19/644
Last Update:
ቅዱስ ጳውሎስ
ጳውሎስ ማለት ንዋይ ህሩይ ማለት ነው። ሐዋ. ፱፡ ፲፭ (9፡15) አንድም ብርሃን ማለት ነው። ዘዳ.፲፬፡፪ አንድም መድቅዕ ማለት ነው። ቀዳሚ ስሙ ሳዖል ነው። ሳዖል ማለት ጸጋ እግዚአብሔር የበዛለት ማለት ነው። ትውልዱ ከነገደ ቢኒያም ነው። ፊሊ. ፫፡፭ አባቱ ዮስአስ ይባላል።
የተወለደው ጌታ በተወለደ በ፭ (5) ዓመት በጠርሴስ ነው። ከ፲፭ ዓመቱ ጀምሮ ኢየሩሳሌም በታላቅ እህቱ ቤት ተቀምጦ ከመምህር ገማልያል ሕገ ኦሪትን ተምሯል። በወንጌል ያመነው ጌታ ባረገ በ፰ኛው ዓመት ነበር። ጌታም በደማቆ መብረቅ ጥሎበት ሳኦል ሳኦል ስለምን ታሳደኛለህ ብሎ ታርቆታል። ከ፸፪ (72) አርድእት አንዱ የሆነው ሐናንያ ጌታ በራዕይ ታይቶት ጳውሎን አስተምረህ አሳምነህ አጥምቀው አለው። እርሱም በእጁ ገና አይኑ በዳሰሰው ጊዜ አይኑን አሳውሮት የነበረው እንደ ቅርፊት ወድቆለታል። ሐዋ.፱፡፩-፲፱ (9፡1¬-19)
ከዚያ በኋላ በክርስቶስ እመኑ እያለ አስተምሯል። ብዙዎችንም አስተምዎ አጥምቋል። ሐዋ. ፲፬፡፰-፲፰ ብዙውንም አሳምኗል። በወይኒም ታስሮ በነበረበት ወቅት ብዙ ሰዎችን አሳምኗል። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱ፤ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎችም አቅርበው። እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ።
ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ።
የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ። ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው።
እነርሱም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት።
ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው ፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ። ሐዋ. ፲፮፡፲፰-፴፬ (16፡18-34) ሕሙማንንም ሕሙም መስሎ አስተምሯል። ፩ቆሮ.፱፡፳፪ (1ቆሮ.9፡22) ፲፬ መልዕክታትንም ጽፏል።
ከዚህ በኋላ በ69 ዓ.ም ሮም ሲያስተምር ኔሮን ቄሣር አስጠሩት ሲል በንጉሱ ፊት ሲቀርብ መስቀሉን ይዞ ቀረበ። ንጉሱ ተቆጥቶ በሰይፍ ቅጡ አለ። በመጎናጸፊያም ሸፍኖ ሰይፎታል። ደሙም ሰማየ ሰማይ ወጥቶ ቀተሉኒ በዓመጻ እያለ ተካሷቸዋል። ሲያልፍም የ72 ዓመት አረጋዊ ነበር። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የሞቱት በአንድ ቦታ በአንድ ቀን ነበር። ይህም ሐምሌ ፭ ነው።
ምንጭ፡- ገድለ ሐዋርያት፣ ዜና ሐዋርያት፣ ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ፪፣ መዝገበ ታሪክ
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!
@dagmele19
@Dagmele19
BY ዳግም ምጽዓት
Share with your friend now:
tgoop.com/Dagmele19/644