tgoop.com/Dagmele19/658
Last Update:
"እንኳን ለጾመ ነብያት አደረሳችሁ"
ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነውን ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ድረስ በአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ እንጾማለን!
እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን ሲል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከንጽሕተ ንጹሓን፣ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም መወለዱን፣ ወደ ግብጽ መሰደዱን፣ በዮርዳኖስ መጠመቁን፣ በትምህርተ ወንጌልን ማስታማሩን፣ በመጨረሻም በሞቱ ሞትን ማጥፋቱን፣ ትንሣኤውንና ዕርገቱን ሁሉ አስቀድመው የተነሡ ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ትንቢት በተናገሩት መሠረት ተፈጽሟል፡፡ ነቢያቱም ትንቢታቸው እንዲፈጸም ‹‹አንሥእ ኀይለከ ፈኑ እዴከ፤ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው መምጫውን በጊዜ እየለኩ ሲጠባበቁ ኑረዋል። ትንቢቱም ጊዜው ሲደርስ ተፈጽሟል፡፡ እኛም ከዚህ በመነሣት ቤተ ክርስቲያናችን በሠራችልን ሥርዓት መሠረት ልንጾም ይገባናል፡፡
ጾሙ የሚጠራባቸው ስያሜዎች
፩.ጾመ ነቢያት
ይህ ጾም ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው ሁሉ ነቢያት የእግዚአብሔርን ሰው መሆንና ዓለሙን የሚያድነበትን ጊዜ እየተጠባበቁ የጾሙት በመሆኑ ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም) ተብሏል።
፪. ጾመ አዳም
ለአዳም የተነገረው የድኅነት ተስፋ ስለመፈጸሙ የተሰጠው ስያሜ ነው።
፫. ጾመ ስብከት
ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት በመሆኑ ጾመ ስብከትም እየተባለ ይጠራል።
፬. ጾመ ሐዋርያት
ሐዋርያት በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እንፈታለን፤ በዓለ ልደትንም ይህን ጾም ጾመን እንፍታ ብለው ሲጾሙት ስለነበር ጾመ ሐዋርያት ይባላል።
፭. ጾመ ፊልጶስ
ሐዋርያው ፊልጶስ በአፍራካ አውራጃዎች በመዘዋወር ወንጌልን እየሰበከና ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ያመኑትን እያጸና፣ ያላመኑትን እየመለሰ ቆይቶ በሰማዕትነት ዐረፈ። ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ቢሹ አጡት፤ ተሰውሮባቸው ነበርና። እግዚአብሔር እንዲገልጥላቸው ሱባኤ ይዘው በጾም በጸሎት ቢለምኑት በሦስተኛው ቀን ተገልጦላቸዋል። እነሱም በክብር አሳረፉት። ጾሙን ግን እስከ ጌታ ልደት ቀን ድረስ ጹመውታል። በዚህም ምክንያት ጾመ ፊልጶስ እየተባለ ይጠራል።
፮. ጾመ ማርያም
እመ አምላክ፣ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ወልደ እግዚአቤሔርን እንደምትወልደው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቢያበሥራት ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ፀንሼ፣ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ›› በማለት በትሕትና ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጹማ ነበርና ጾመ ማርያም ተብሏል።
እንግዲህ ከላይ ያየናቸው ቀደምት ቅዱሳን በዚህ ጾም ተጠቅመውበታል። እኛም አምላካችን ምሕረት ይሰጠን ዘንድ እንዲሁም ከቅዱሳኑም በረከት እናገኝ ዘንድ ልንጾመው ግድ ነው።
ተወዳጆች ሆይ! ስንጾም እነዚህን ነገሮች ልብ ማለት ይገባል።
ሀ. በእምነት ሁነን መጾም፦ እግዚአብሔር ይሰማኛል፤ ዋጋ አገኝበታለሁ ብለን እያመንን መሆኑን ማስተዋል ይገባል።
ለ. በፍቅር መጾም፦ ከወንድሞችና ከእኅቶች ጋር በመስማማትና በአጠቃላይ ክፋት በማይታሰብበት ልቡና ሆኖ መጾም ያስፈልጋል።
ሐ. ንስሓን፣ ጸሎትን፣ ምጽዋትን፣ ይቅርታን ገንዘብ በማድረግ መጾምን አለብን።
መ. ከክፉ ነገር ሕዋሳቶቻችንን ዐቅበን (ጠብቀን) መጾም፦ ዐይን፣ ጆሮ፣ እጅ፣ እግር፣ አፍ ይጹም ብሎ እንደነገረን ቅዱስ ያሬድ እኛም ከክፉ ሁሉ ተከልክለን እንዲህ ባለው አኳኋን ከጾምን ቸሩ አምላካችን ምሕረቱን ይልክልናል።
በመጨረሻም ስንጾም በመከራ ውስጥ ስላሉት ወገኖቻችን እያሰብን እንዲሁም ሁሉም ነገር መልካም የሚሆነው ሀገር ሰላም ሲሆን ነውና ለሀገራችን ሰላምን፣ ለሕዝቦቿም ፍቅር፣ አንድነትን እያሰብን አምላካችንን እንለምነው።
የራሔልን ዕንባ የተቀበለ አምላካችን ጾማችንን ይቀበልልን፤ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
www.tgoop.com/Dagmele19
BY ዳግም ምጽዓት
Share with your friend now:
tgoop.com/Dagmele19/658