tgoop.com/EOTC2921/5291
Last Update:
#ድንቅ_ተአምር_በኪዳነ_ምሕረት
ዕለቱ ታህሳሥ 3 ቀን 2003 ዓ/ም ነበር፡፡ አንድ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረች እህት በእርኩስ መንፈስ ተጠምዳ ነበር፡፡ እናም የያዛት መንፈስ እጅግ ከባድ ነበር፤ መንፈሱ እርሷን ብቻ ሳይሆን በቤተሰቧም የተሰራጨ ነበር፤ ታዲያ ልጅቷ በዚህ ቀን ያ መንፈስ ተነሳባትና ከአለችበት ዩኒቨርሲቲ ዶርም አንስቶ በእግሯ ወደ አዲስ አበባ መስመር እስከ ባኮ ድረስ ይወስዳታል፡፡ ልጅቷ ታዲያ ስልክና መታወቂያዋን በእጇ አንቃ እንደያዘች ነበር ያ እርኩስ መንፈስ አብሮ የማይታመነውን ሩቅ መንገድ የወሰዳት፡፡
ጓደኞቿ በጣም ተጨንቀው የሚያረጉት ግራ ገባቸው ስልክ ይደውላሉ፤ አንስቶም ያስፈራራቸዋል፣ ይዝትባቸዋል ይባስ ብሎ አሁን አታገኟትም ገደል ልከታት ነው፡ አንዴ ባህር ልከታት ነው ይላቸዋል፡፡ ታዲያ የተረበሹት ልጆች ወደ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አገልጋይ ወደነበሩት ቀሲስ ሙሴ ይደውላሉ፡፡ እርሳቸውም በመገረም ስልክ ተቀብለው ሲደውሉ አያነሳም ነበር፡፡
ከዚያም እዛው ባኮ አካባቢ ጠመዝማዛ ቦታ ላይ አንድ መኪና ከነቀምቴ ወደ አዲስ አበባ ይጓዛል፡፡ ልክ ከማዞሪያው ሲደርስ የመኪናው ባውዛ/የፊት መብራት/ ተሻግሮ የሆነ ቦታ ላይ ያርፋል፡፡ ከውስጥ ያሉት ሹፌርና ጓደኞቹ የሆነ የሚረብሽ ነገር ያያሉ•••
ከመሀል ነጭ ለባሽ በዙሪያዋ ጥቋቁር ነገር ከበዋት ያያሉ፤ ለማመን የሚከብድ ነገር እየተባባሉ፡ ወረዱ ከዚያም ቀስ ብለው መጠጋት ጀመሩ፡ የእጅ መብራት አብርተው በደንብ ሲያዩ በዙሪያዋ የከበቧት ጅቦች ነበሩ፡፡ እነሱም በመጨነቅ ስሜት ማነው የሆነ የተገደለ ሰው፡ ወይም የተመታ ሰው መሆን አለበት፡ ብለው ጅቦችን አባረው መጠጋት ጀመሩ፡፡
ጠጋ ብለው ሲያዩ አይኖቿን ሳታርገበግብ እንዳፈጠጠች፡ በእጆቿ የግቢ መታወቂያ እና ስልክ የጨበጠች ልጃገረድ ነበረች፡፡
ከዚያም ለሦስት አንስተው ጋቢና አስገቧት፡፡ ጠጋ ብሎ ልብ ትርታዋን አዳመጠ አልሞተችም ልጅቷ መተንፈስ ጀመረች፡፡
ከዚያም ስልኳ ጠራ፡ ቀሲስ ነበሩ የደወሉት፡ አነሱና ያዩትን ሁሉ ነገሯቸው ይዘዋት ሊመጡ ሲሉ፡ የጓደኛቸው መኪና ከአዲስ አበባ ወደ ነቀምቴ እየከነፈ መጣ እነሱም የሆነውን ነግረዋቸው እንዲወስዷት አዝዘው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ከዚያም ቀሲስ ግቢው ድረስ ለመቀበል ሄዱ ልጆችም እንዲሁ አብረው ተቀበሏት፡፡ ጊዜውም ጨልሞ ነበር ከዚያም ልጅቷ ካህኑን ባየች ጊዜ ባሰባት ጭራሹን በድንጋይ ልጆችን ልትፈጃቸው ነበር፡፡ በስንት ትግል ይዘዋት ያ መንፈስ አልሄድ ብሎ ስለነበር በቅድስት ኪዳነ ምሕረት፤ በስላሴ ስም ገዝተው እጇን በነጠላ አስረው ወደ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ወሰዷት፡፡ ከቤተ ክርስቲያን አጥር ሲደርሱ አልሄድም አለች፡፡ ቢገፋ ሂድ ቢሉ እቢ አልሄድም ከፊት ሰው ይቅደምልኝ አለች ከዚያም አንድ ሰው ቀድሞ የእጅ መብራት ሲያበራ የአንድ ጅብ አይኖች ከርቀት መብራት ጀመሩ ያን ጅብ አባረው ወደ ውስት አስገብተው ቀሲስ ሙሴም የተለመደ ጸሎታቸውን እያረጉ ማስለፍለፍ ጀመሩ፡፡
ከዚያም ልጅቷ እንዴት እንደሄደች ሁሉን አንድ በአንድ ተናገረች፦ ከዚያ ድረስ የወሰዷትም በኪዳነ ምሕረት ጠበቃ ነበር፡፡ አንዴ ከባህር ሊከቷት ሲሉ ኪዳነ ምሕረት በጨረሯ እየወጋች ታስቀራታለች አንዴም በገደሉ፣ አንዴም በመኪና ጎማ ከተው ሊገድሏት ነበር፤ ብቻ በቅድስት ኪዳነ ምሕረት ጨጨር እየተወጉ ማድረግ ሳይችሉ ከዚያ ቦታ በጅብ ተከባም ተቀመጠች ጅቦችም እንዳይበሏት ተገዝተው ዙሪያዋን ከበው ጠበቋት እንጂ መብላት እንኳ አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡
ከዚያም አልወጣም ያለው እርኩስ መንፈስ ይባስ ብሎ ቤተሰቦቿ ካልተጠመቁ ንስሃ ካልገቡ አለቅም አለ፡፡ ለጊዜው ከልጅቷ አስለቀቁትና ወደ ማንነቷ ተመለሰች፡፡ ከዚያም ልጅቷ ዊዝድራው ሞልታ/ትምህርት ለጊዜው አቁማ ጸበል መከታተል ጀመረች፡፡ ያ እርኩስ መንፈስም በቁጥር 328 ነበር፡፡ ያ መንፈስ በሌላ ጊዜ ስልክ ለንስሐ አባቷ እንዳትደውል እንዳትገናኝ በአንድ ወንድ ልጅ አድሮ ያውም ሴቶች ዶርም ገብቶ ከፖርሳዋ ነበር ሰርቆ የወሰደው፡፡ ያ መንፈስም በኪዳነ ምሕረት ስም ስለተገዘተ ይዞት እንዲመጣ ታዘዘ እንደተባለውም ልጁ ስልኳን ይዞ መሰስ ብሎ ቤተ ክርስቲያን መጣና ሰጣት፡፡ ሁሉም ቤተሰቦቿ ተነግረው ስለነበር ሁሉም በያሉበት ተጠመቁ ንስሃ ገቡ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረዶች በኃላ ልጅቷ ለመመረቅ የቀራትን አንድ አመት ከመንፈቅ ጨርሳ በሰላም ተመረቀች፡፡
የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ጣዕምና ፍቅሯ፣ ምልጃና ጸሎቷ፣ ረድኤትና በረከቷ ከሁላችንም ጋር ለዘላለሙ ይኑር አሜን፡፡
ከቀሲስ ሙሴ የኪዳነ ምሕረት አገልጋይ ካህን የሰመሁት አስደናቂ ነገር በጥቂቱ ነበር
✍ተፃፈ፡ በገ/ስላሴ መንግስቴ ኅዳር 8/2012 ዓ/ም
🙏 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር🙏
BY የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች
Share with your friend now:
tgoop.com/EOTC2921/5291