tgoop.com/EOTC2921/5316
Last Update:
🌾✞ #ቅዱስ_ገብርኤል ✞🌾
⛪️ ታኅሣሥ 19
❖ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” መዝ.33፥7፤ ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልኮ በዙሪያቸው ሆኖ ከመከራ እንደሚያድናቸው ያስተምራል፡፡ የመላእክት አንዱ ተግባር መዳንን ይወርሱ ዘንድ ያላቸውን ሰዎች መጠበቅ መሆኑ ተጽፏል፡፡
❖ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” ዕብ.1፥14፤ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን ሁሉ ሲያስገዛለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም እወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም የሚቃወመኝም የለም፡፡” ኢሳ.10፥13-14 ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ ዱራ(አዱራን) በሚባል ስፍራ ላይ አቆመው፡፡ በግዛቱ በልዩ ልዩ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉትን ሹማምንቱንና ገዢዎችን ሰበሰባቸው፤ “የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሥ ናብከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፡፡ ወድቆም ለማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣል” ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን አዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ የመለከቱና የእንቢልታው እንዲህም የዘፈን ድምፅ በተሰማ ጊዜ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡
❖ በባቢሎን አውራጃዎች ላይ የተሾሙ አዛርያ(ሲድራቅ)፣ አናንያና(ሚሳቅ) ሚሳኤል(አብደናጎ) ግን ንጉሥ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡ ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ነገሩት፤ ንጉሥም እጅግ ተቆጥቶ ወደ እርሱ አስጠራቸው፡፡ እርሱ ላቆመው ለወርቅ ምስል ያልሰገዱ እንደሆነ እጅና እግራቸውን ታስረው ወደ እቶን እሳቱ እንደሚጣሉ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሠልስቱ ደቂቅ ግን “ናብከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፣ ከሚነደውም ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን አማልክትህን እንዳናመልክ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” ብለው መለሱለት፡፡
❖ የንጉሥ ናብከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእነ ማዕረገ ልብሳቸው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው ትእዛዝን አስተላለፈ። ትእዛዙ አስቸኳይ ነበርና ወደ እሳት ጣሏቸው። ወደ እሳቱ የጣሏቸውም ኃያላን በእሳቱ ወላፈን ተገርፈው ሞቱ፡፡ እንዲህ ሲሆን ሳለ ግን ሠልስቱ ደቂቅ ወደ አምላካቸው “በፍጹም ልባችን እናምንሃለን፣ እንፈራሃለን፣ አታሳፍረን እንጂ ገጸ ረድኤትህንም እንፈልጋለን፡፡” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ ነቢያትም በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበረባቸው መከራና ስቃይ ያድናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጮሁ ይለምኑ ነበርና። "አንስእ ኃይለከ ወነዓ አድኅነነ አምላክ ኃያላን ሚጠነ" እያሉ ለምነዋል።
❖ በብዙ ትንቢትና ኅብረ አምሳል የእግዚኣብሔርን መምጣት በትንቢት ተናግረዋል። እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታቸውን ተቀበለ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም እስራታቸውን ፈታ፤ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠልስቱ ደቂቅም መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር፤ ስምህም ለዘለዓለም የተመሰገነና የከበረ ነው” በማለት አመሰገኑት፡፡ ምስጋናውም የቀረበው ቅዱሳን መላዕክት ከሠለስቱ ደቂቅና ቅዱስ ገብርኤል ጋር በእሳቱ ውስጥ እየተመላለሱ አመስግነዋል። ሠለስቱ ደቂቅም ከእስራታቸው ተፈተዋል። ይህም በሐዲስ ኪዳን ያሉ ምዕመናን ከኃጢአት እስራት በተፈቱ ጊዜ በጌታ የልደት ወቅት ከመላዕክት ያመሰገኑት ምስጋና ምሳሌ ነው።
❖ "በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ"ሉቃ.2፥6 ይላል። ይህ የሚያስረዳን ሠለስቱ ደቂቅ የእግዚአብሔር ልጅ በአምሳለ ገብርኤል በተገለጠላቸውና ባዳናቸው ጊዜ ከመላዕክት ጋር እንዳመሰገኑ ሁሉ በጌታ ልደት ጊዜም እረኞችና መላዕክት በሰው ልጅ ድኅነት ደስ ተሰኝተው "ስብሐት ለእግዚኣብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" ብለው አመስግነዋል።
❖ የንጉሥ ናብከደነፆርም ሠልስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ከእነርሱ ጋር አራተኛውንም ተመለከተ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን ፊቱን ጸፍቶ አፉን ከፍቶ “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን” ዮሐ.11፥49 ብሎ እንዳናገረው እንዲሁ ናብከደነፆርንም “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ እንዲናገር አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅን መልክ ያለው፤ በኋላም መልአክ ብሎ የተናገረለት ቅዱስ ገብርኤልን ነበር፡፡ ምስጢሩ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃለኛው ዘመን ሰው ሆኖ እንዲወለድና የአዳም ልጆችን ሁሉ ሲያቃጥል ከነበረው የኃጢአት እሳት እንደሚያድን ለናቡከደነፆር ሲገልጥለት ነው። ❝እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?❞ አላቸው፤ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ" ማቴ 16፥16 እንዲል። እንግዲህ ይህን ለቅዱስ ጴጥሮስ የገለጠለትን ምስጢር እግዚኣብሔር በቸርነቱ ለናቡከደነፆር ገልጦለት እንደነበር ማስተዋል ያስፈልጋል።
❖ እግዚአብሔር ለሰዎች በተለያየ መልክ ይገለጥላቸዋል። በዚህ ታሪክ ላይ እንደምናየው የእግዚአብሔር ልጅ በአምሳለ ገብርኤል እንደተገለጠላቸው ያሳያል። ለዚህ ማረጋገጫ መልክዐ ማርያም በሚባለው የጸሎት መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይላል። "እግዚአብሔር ኀቤኪ ፈነዎ ቃሎ ገብርኤልሃ አስተማሲሎ። ማርያም አምላከ ዘወለድኪ በተደንግሎ። ..." ይላል። ይህም ማለት እግዚአብሔር አብ ቃል የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስን በገብርኤል አምሳል ወደ አንች ላከው አንችም ማርያም ሆይ አምላክን በድንግልና ወለድሽው ማለት ነው።
#ይቀጥል ---፪
BY የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች
Share with your friend now:
tgoop.com/EOTC2921/5316