tgoop.com/EWLA1/226
Last Update:
በ23 ዓመቷ ወጣት ላይ የአሲድ ጥቃት የፈፀመዉ ግለሰብ
በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ
ሰላም ግዜው የ23 አመት ወጣት ስትሆን በፋርማሲ የት/ት ዘርፍ ዲፕሎማ አላት፡፡ ሰላም የምትኖረው በአማራ ክልል ምስ/ጎጃም ዞን ቀራኒዩ ከተማ ሲሆን ይኸነው ፈንታ የተባለ ግለሰብ ተደጋጋሚ የፍቅር ጥያቄ ያቀርብላት የነበረ ሲሆን ይህንንም እሷ እንደማትቀበለው ስትገልፅለት ቆይታለች፡፡
ይኽን ተከትሎም ታህሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በስራ ቦታዋ ሳለች ነበር ግለሰቡ ምንነቱ ያልታወቀ አሲድ ከቤንዚን ጋር በመቀላቀል ሰውነቷ ላይ በመድፋት ከባድ የአሲድ ቃጠሎ ጉዳት ያደረሰባት፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማህበር ባ/ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጉዳዩን እየተከታተለዉ የሚገኝ ሲሆን ጉዳዩ የቀረበበት የወረዳው ፍ/ቤት የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት ይኸነው ፈንታ በ14 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ዉሳኔ አስተላልፏል፡፡
ሰላም የተሻለ ህክምን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሆስፒታል ዉስጥ ህክምና እየተደረገላት ይገኛል፡፡ ማህበራችን ባህር ዳር በሚገኘዉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አማካኝነት የህግ ጉዳዩን ከመከታተሉ ጎን ለጎን የዋናዉ ጽ/ቤታችን የህግ ድጋፍ ክፍል እና የህዝብ ግንኙነት ክፍል ተወካዮች ሰላም ህክምና በምትከታተልበት ሆስፒታል ተገኝተዉ ያለችበትን ሁኔታ ማየት ችለዋል፡፡ በዚህ መመሰረት የህክምና ሂደቷን ጨምሮ በቀጣይ የሚያስፈልጉ የስነ-ልቦና ክትትሎችን እንድታገኝ ለማስቻል የሚመለከታቸዉን ተቋማት በማነጋገር ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ አጋጣሚም ሰላምን በተለያየ መንገድ ማገዝ ወይም መደገፍ የምትፈልጉ ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች በዉስጥ መስመር ብታሳዉቁን ሁኔታዎችን የምናመቻች መሆኑን እንገልፃለን፡፡
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር
BY Ethiopian Women Lawyers Association (EWLA)
Share with your friend now:
tgoop.com/EWLA1/226