tgoop.com/Enatachn_mareyam/16311
Last Update:
🕊
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡
† ጥር ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †
🕊 † ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ † 🕊
መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው : አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ፯ ዓመታት
ስቃይ በኋላ ተሰይፏል:: ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ :-
- ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ [ አንስጣስዮስ ] እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም [ ልዳ ] ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::
- ቅዱስ ጊዮርጊስ ፳ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት [ የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ ] ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::
- ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ፸ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ [ ዐውደ ስምዕ ] ደረሰ::
- ከዚያም ለተከታታይ ፯ ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: ፫ ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል::
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ:
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::
- ከ፯ ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: ፯ አክሊላትም ወርደውለታል::
† ዝርወተ ዓጽሙ †
- ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ 'ዝርወተ አጽሙ' ትባላለች:: በቁሙ 'አጥንቱ የተበተነበት' እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: ፸ ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ [ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ] አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::
- በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው: በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::
- በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ [ ደብረ ይድራስ ] ወጥተውም በነፋስ በተኑት:: "ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል:: [ ምቅናይ ]
- እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው::
- ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ: አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: ፹ው ነገሥታት ግን አፈሩ::
🕊 † ቅዱስ ባኮስ ጃንደረባው † 🕊
- 'ጃንደረባ' የሚለው ቃል በግዕዙ 'ሕጽው' ተብሏል:: ይህ ስም በቤተ ክርስቲያን የተለመደ እንጂ እንግዳ አይደለም:: መድኃኒታችን እንዳለው በተፈጥሮ የሆኑ: ሰዎች እንዲያ ያደረጉዋቸውና ራሳቸውን ስለ ጽድቅ ጃንደረባ ያደረጉ ብዙዎች ናቸውና::
- ኢትዮዽያዊው ጃንደረባ ቅዱስ ባኮስም [ አንዳንዴ አቤላክ / አቤሜሌክም ይባላል] :-
- በ፩ኛው መቶ ክ/ዘመን በሃገራችን ኢትዮዽያ ተወልዶ ያደገ
- ነገሥታቱንና ሃገሩን በሙያው ያገለገለ
- በተለይ ከ፴፬ እስከ ፵፮ ዓ/ም ለነገሠችው ንግሥት ሕንደኬ ገርስሞት በገንዘብ ሚንስትርነት ያገለገለ
- በገንዘቧ ላይ ሁሉ አዛዥ [ ታማኝ ] የነበረ
- ጃንደረባ በመሆኑ ለንግሥቲቱና ቤተሰቧ ቅርብ የነበረ
- መጻሕፍትን የሚያነብና የሚመረምር
- ዘወትር ወደ ኢየሩሳሌም እየሔደ ከቅዱሳት መካናት የሚሳለም በጐ ሰው ነበር::
- በግብረ ሐዋርያት ምዕ.፰፥፳፮ ላይ እንደ ተጠቀሰው ቅዱሱ ከኢየሩሳሌም ለፋሲካና ለእሸት በዓል ነበር የሔደው:: ሲመለስ መንፈስ ቅዱስ ከፊልዾስ ጋር በጋዛ አገናኝቶታል:: በዚያም ምሥጢረ ክርስትናን ተምሮ: በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት አምኖ ተጠምቁዋል::
- ክርስትናን ለኢትዮዽያ በ፴፬ ዓ/ም አምጥቷል:: "ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ" ሲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደ ተናገረው ወደ ሃገራችን ተመልሶ: ስለ ክርስቶስ ሰብኮ በርካቶችን አሳምኗል::
- ቀጥሎም ሃብቱን ንቆ [ መንኖ ] : ከኢትዮዽያ እስከ ሕንድ ወንጌልን ሰብኮ በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ዐርፏል:: [ ተሰውሯል የሚሉም አሉ ]
" በእውነት ለቅዱስ ባኮስ ክብር ይገባል:: "
🕊 † ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን † 🕊
+ ይህ ቅዱስ ሰው :--
- እጅግ የተመሠከረለት ሊቅ
- በፍጹም ትሕርምት የኖረ ገዳማዊ
- በርካቶችን ወደ ክርስትና ያመጣ ሐዋርያዊ
- ለአእላፍ ምዕመናን እረኛ የሆነ የንጽቢን [ ሶርያ ] ዻዻስ
- ለጀሮ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሠራ ገባሬ መንክራት
- ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንትን ያፈራ ታላቅ መምሕር
- ለክርስቶስና ለእመቤታችን ታጥቆ የተገዛ የፍቅር ሰው
- እጣቶቹ እንደ ፋና የሚያበሩለት ማኅቶት
- ራሱን ዝቅ አድርጐ በቆሸሸ ልብስ የሚኖር የትህትና ሰው ነው::
- በ፫፻፳፭ [፫፻፲፰] 325 (318) ዓ/ም: በኒቅያ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡና አርዮስን ሲያወግዙ እርሱ አንዱ ነበር:: በሥፍራውም ሙት አስነስቶ ሕዝቡን አስደምሟል:: በዚያም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ሠርቶ ወደ ሃገሩ ተመልሶ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::
🕊 † ደናግል ማርያ ወማርታ † 🕊
- በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት-ባለ ሽቱ' ተብለው የሚጠሩ ፪ እናቶች ነበሩ:: 2ቱም ስማቸው ማርያም ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት- ከኃጢአት የተመለሰች': ፪ኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ አልዓዛር-በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል::
- በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል ፲፪፥፩ ላይ ያለችው የአልዓዛር እህት [ ድንግሊቱ ] ናት:: ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው::
- ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት:: ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል::
- በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው:: አልዓዛርን ከ፸፪ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል:: ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር::
- ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ:: በ፬ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ
"እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ-አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች:: [ ዮሐ.፲፩ ]
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16311