tgoop.com/Enatachn_mareyam/16327
Last Update:
🕊
[ † እንኳን ለጻድቅ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †
🕊 † አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን † 🕊
† በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን [ በተለይ ከ፲፫ኛው [13ኛው] እስከ ፲፭ኛው [15ኛው] መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው] የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ
- ክርስትና ያበበበት::
- መጻሕፍት የተደረሱበት::
- ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
- ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::
ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ :-
¤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
¤ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
¤ አባ ሰላማ ካልዕ::
¤ አቡነ ያዕቆብ::
¤ ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
¤ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
¤ አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::
በተጨማሪም :-
¤ ፲፪ቱ [ 12ቱ ] ንቡራነ ዕድ::
¤ ፯ቱ [ 7ቱ ] ከዋክብት::
¤ ፵፯ [ 47ቱ ] ከዋክብት::
¤ ፭ቱ [ 5ቱ ] ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ፯ቱ [7ቱ] እና የ፵፯ቱ [47ቱ] ከዋክብት አስተማሪ: የአበው ፫ቱ [3ቱ] ሳሙኤሎች [ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ] : የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::
ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ::
ከእነዚህ ቅዱሳን የጻድቁ ፍሬዎች አንዱ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ናቸው:: ጻድቁ አንዳንዴ "አፍቀረነ እግዚእ" እየተባሉም ይጠራሉ:: ትርጉሙም "ጌታ ወደደን" እንደ ማለት ነው::
ያፍቅረነ እግዚእ የነበሩት በ፲፬ኛው [14ኛው] መቶ ክ/ዘ ሲሆን ቁጥራቸው ከ፯ቱ [7ቱ] ከዋክብት ነው:: ጻድቁ ከልጅነት ጀምሮ በሥርዓቱ ከማደጋቸው ባሻገር እጅግ የተማሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል::
ለምናኔ ከወጡ በሁዋላ ከኖሩባቸው ቦታዎችም ፫ቱ [3ቱ] ተጠቃሽ ናቸው:: የመጀመሪያውና ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ደግሞ ደብረ በንኮል ነው:: ጻድቁ በዚህ ገዳም ከታላቁ ቅዱስ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሥርዓተ ገዳምን : ትኅርምተ አበውን : ተጋድሎተ ቅዱሳንን አጥንተው ለመዓርገ ምንኩስና በቅተዋል::
በገዳሙም ለተወሰነ ጊዜ አገልግለው ወደ ጣና አካባቢ ከአቡነ ያሳይና ከአባ ሳሙኤል ዘዋሊ ጋር መጥተዋል:: የመምጣታቸው ምክንያትም ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስና ገዳማትን ለመመሥረት ነው::
ሶስቱ ቅዱሳን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በሁዋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ ደግሞ ማንዳባን አቀኑ:: ያፍቅረነ እግዚእም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ ገዳም አቅንተው ኑረዋል:: ይህ ገዳማቸው ዛሬም ድረስ በስማቸው ይጠራል::
ጻድቁ አፍቀረነ እግዚእ ፫ኛው [3ኛው] የሚታወቁበት ገዳም ማኅበረ ዴጌ [ጻድቃነ ዴጌ] ሲሆን ገዳሙ በአክሱም ዙሪያ ይገኛል:: እርሳቸው ፫ሺ [3ሺ] ቅዱሳን የተሠወሩበትን ገዳም በማገልገላቸውም ዛሬም ድረስ በአካባቢው የታወቁ ሆነዋል::
በተረፈም አክሱም አካባቢ ሌሎች ገዳማትን እንዳቀኑም ይነገርላቸዋል:: ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌልና ገዳማትን በማስፋፋት ከኖሩ በሁዋላ በዚህች ቀን ዐርፈው ለክብሩ : ለርስቱ በቅተዋል::
† አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ይቅር ብሎ በረከታቸውን ያሳድርብን::
🕊
[ † ጥር ፲፱ [ 19 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ [አፍቀረነ እግዚእ ዘጉጉቤ - ጣና ውስጥ - ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ]
፪. አባ ባሱራ
፫. ቅድስት ኔራ
፬. ቅድስት በርስጢና
፭. አባ ዝሑራ
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላዕክት
፪. ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫. አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ [ታቦታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ 09 አካባቢ ይገኛል]
፬. አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭. አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
† ቅዱሳንን ታስቡ ዘንድ ቸል አትበሉ::
† " እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና:: ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና:: ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ:: በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ:: የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል:: አንደበቱም ፍርድን ይናገራል:: የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው:: በእርምጃውም አይሰናከልም::" †
[መዝ.፴፮፥፳፰-፴፩]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16327