tgoop.com/Enatachn_mareyam/16399
Last Update:
🕊
[ † እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
🕊 † ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ † 🕊
† ልደት †
† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::
በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ [ከአረማዊ ጋብቻ] አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ [24] ቀን በ፲፪፻፮ [1206] ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ [24] ቀን በ፲፪፻፯ [1207] ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
† ዕድገት †
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን [ብሉያት: ሐዲሳትን] ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::
† መጠራት †
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::
የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት [ተክለ ሥላሴ] ይሁን:: ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::
† አገልግሎት †
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ [ጽላልሽ] አካባቢ ብቻ በ፲ [10] ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ፪ [2] መልክ ነበራት::
፩ኛ. ዮዲት [ጉዲት] በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
፪ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::
ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን [ጠንቋዮችን] አጥፍተዋል::
† ገዳማዊ ሕይወት †
† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ፫ [3] ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::
እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ፲፪ [12] ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ፯ [7] ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ፯ [7] ዓመታት: በአጠቃላይ ለ፳፮ [26] ዓመታት አገልግለዋል::
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ [ዞረሬ] ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ፳፪ [22] ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም ፮ [6] ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ፯ [7] ዓመታት ጸልየዋል::
† ስድስት ክንፍ †
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::
ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::
ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ :-
- በቤተ መቅደስ ብስራቱን
- በቤተ ልሔም ልደቱን
- በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
- በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
- በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::
† በዚያም :-
- የብርሃን ዐይን ተቀብለው
- ፮ [6] ክንፍ አብቅለው
- የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
- ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
- ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
- ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
- "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
† ተአምራት †
የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
- ሙት አንስተዋል
- ድውያንን ፈውሰዋል
- አጋንንትን አሳደዋል
- እሳትን ጨብጠዋል
- በክንፍ በረዋል
- ደመናን ዙፋን አድርገዋል::
ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::
† ዕረፍት †
† ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው: መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ፺፱ [99] ዓመት: ከ፰ [8] ወር: ከ፩ [1] ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ [24] ቀን በ፩፻፮ [1306] ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: ፲ [10] ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::
† በዚህ ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለ፳፪ [22] ዓመታት የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው ለ፯ [7] ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስባለች::
[ † ጥር ፳፬ [24] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
፫. ታላቁ አባ ቢፋ
፬. አባ አብሳዲ ቀሲስ
፭. ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. አቡነ ዘዮሐንስ [ዘክብራን ገብርኤል-ጣና]
፪. ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
፫. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
፬. ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
፭. ቅዱስ አጋቢጦስ
፮. ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ
† " በድካም : አብዝቼ በመገረፍ : አብዝቼ በመታሠር : አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት : ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት : በራብና በጥም : ብዙ ጊዜም በመጦም : በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: " † [፪ቆሮ ፲፩፥፳፫]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16399