tgoop.com/Enatachn_mareyam/16447
Last Update:
🕊
[ † እንኳን ለጌታችን አማኑኤል ክርስቶስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †
[ 🕊 † ተአምረ እግዚእ † 🕊 ]
† " ተአምር " የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል:: መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው:: ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ [በላይ] : ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ [ሲፈጸም] ተአምር ይባላል::
ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው:: ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው::
እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል:: በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ [ኦሪትን ተመልከት] እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ [፩ ነገሥት] እንደ ነበር ይታወቃል::
እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል:: በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል:: [ ማቴ.፲፥፰ , ፲፯፥፳ , ማር.፲፮፥፲፯, ሉቃ. ፲፥፲፯, ዮሐ.፲፬፥፲፪ ]
እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: [ሐዋ. ፫፥፮ , ፭፥፩ , ፭፥፲፪ , ፰፥፮ , ፱፥፴፫-፵፫ , ፲፬፥፰ , ፲፱፥፲፩]
[ 🕊 † ተአምራተ እግዚእ † 🕊 ]
† ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: እያንዳንዱ ግን ቢጻፍ ዓለም ለራሷ ባልበቃች ነበር:: ከእነዚህ መካከልም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ዕለት በ፯ እንጀራ እና በጥቂት ዓሣ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር ፬ ሺህ ሰዎችን በቸርነቱ አበርክቶ አጥግቡዋል:: ደቀ መዛሙርቱም ፯ ቅርጫት ማዕድ አንስተዋል::
ጌታችን በከሃሊነቱ የተራቡትን ሲያጠግብ እንዲሁ አይደለም:: በጊዜው የነበሩ አይሁድ ጠማሞች ነበሩና እነሱን ምላሽ በሚያሳጣ መንገድ ነበር እንጂ:: አይሁድ ላለማመን ብዙ ጥረት ነበራቸውና::
በዚህ ዕለትም እንጀራውን አበርክቶ ሲያበላቸው :-
፩. ጊዜው አመሻሽ ላይ ነበር:: ምክንያት :- ጧት ላይ ቢሆን ከቤታችን የበላነው ሳይጐድል ብለው ከማመን ይርቁ ነበርና::
፪. ከውሃ ዳር አድርጐታል:: መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::
፫. ሳር የበዛበት ቦታ ላይ አድርጐታል:: ምክንያቱም መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::
፬. ከከተማ አርቆ ምድረ በዳ ላይ አድርጐታል:: ያማ ባይሆን "ፈጣን: ፈጣን ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው እየገዙ አቀረቡለት" ባሉ ነበርና::
† ለመድኃኒታችን ክርስቶስ አምልኮና ምስጋና ይሁን !
አማኑኤል አምላካችን ጣዕመ ፍቅሩን ያሳድርብን::
🕊
[ † ጥር ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት [ስለ ሃይማኖት ፯ ጊዜ ሙቶ የተነሳ , ፯ አክሊል የወረደለት ]
፪. ቅዱስ አካውህ መነኮስ
፫. ፰ መቶ "800" ሰማዕታት
፬. ቅዱስ ዮሴፍ አይሁዳዊ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፮. ቅድስት ሳቤላ
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. አባቶቻችን አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ
፪. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፫. ቅዱስ እንድራኒቆስና አትናስያ
፬. ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
† " ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ :- ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ:: በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም' አላቸው::
ደቀ መዛሙርቱም :- 'ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?' አሉት:: ጌታ ኢየሱስም:- 'ስንት እንጀራ አላችሁ?' አላቸው:: እነርሱም:- 'ሰባት: ጥቂትም ትንሽ ዓሣ' አሉት::
ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ:: ሰባቱንም እንጀራ: ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ:: ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ:: ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ:: ሁሉም በሉና ጠገቡ:: የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሱ:: የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ::" † [ ማቴ.፲፭፥፴፪ ]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16447