tgoop.com/Gazetaw/4164
Last Update:
..የቀጠለ ማስታወሻ
✨የወታደሩ ሚስት....
የልጅነት ባሏ ነዉ፨ገና ነፍስ ሳታዉቅ ቤተሰቦቻቸዉ ልጅህን ለልጄ ተባብለዉ የዳሩለት ሚስቱ ነች፨የብረት መዝጊያ የሆነ ባል ነዉ ያላት፨ጎጇቸዉን ከቀለሱ በኋላ በፍሬ ተባርከዋል፨ሦስት ሴቶች ልጆች አሏቸዉ፨
ባለሙያነቷ ያስደምመኛል፨ምግቧን ላደነቀ ሁሉ መልሷ አንድ ነዉ፨
እርሱ ነዉ ያስተማረኝ!!
ለመጀመሪያ ጊዜ እንጀራ መጋገርና:ዶሮ መስራት ያስተማራት እርሱ መሆኑን ስትነግረኝ መገረም ያጀበዉ ሳቄን ማቆም አልቻልኩም፨
"አንቺ ሳቂ ምን አለብሽ፨እኔ አዲስ ቀሚስ ተገዝቶልኝ ስቦርቅ የዋልኩበት ቀን ሰርጌ መሆኑን ሳላዉቅ ተድሬ ነዉ" ነበር ያለችኝ፨
ባሏ በሰፈሩ የተከበረ አባወራ ነዉ፨አራሽና ተኳሽ!!ክላሽንማ እርሱ ይያዛት ተብሎ የሚሞካሽ ወንድ!!ከቀናት መሃል በአንዱ ሃገር ጥሪዋን በሰፊዉ አስተጋባች፨ልብ ሰባሪ ጥሪ ነበር!!እንደ አድዋ ለሃገራችሁና ለሃይማኖታችሁ ስትሉ ተዋጉ ተብሎ ነጋሪት አይጎሰም:ሕዝበ አቢሲኒያ ሁሉ በአንድ ቃል ሆ ብሎ ወረኢሉ አይከት ነገር ጦርነቱ አድዋ ላይ አብረዉን ከዘመቱ ወንድሞቻችን ጋር ነዉ፨ከፍቶታል፨ክላሹን ወልዉሎ የሚሄድበት ጦር ሜዳም አይደለም፨
መሳሪያ ለታጠቁ ሰዎች ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፏል፨መዝመት አልያም ትጥቃቸዉን ማስረከብ፨በጦርነቱ ባያምንበትም በተከበረበት ሃገር መሳሪያዉን አስረክቦ የፈሪ ተረት እየተተረተበት ሴት ልጆቹ ፊት እንደማይቆም ያዉቀዋል፨የልጆቹን ጉንጭ ስሞ ሚስቱን አቅፎ ተሰናበታት፨
አኬልዳማ!!
ሄደ፨ረጅም የስቃይ ወራት በብዙ የተተራመሱ ወሬዎች ተሞልተዉ አለፉ፨ጥቂት ጊዜ ብቻ ደዉሎላታል፨ጦር ሜዳ መድረሱን ሲነገራት የመጨረሻ ወሬያቸዉ ነበር፨ ከጊዜያት በኋላ እልፍ አዕላፍ ነፍሳት ረግፈዉ ከመንግስት ቴሌቭዥኖች የፕሪቶራያ ስምምነት ጉዳይ ተሰማ፨
...
የሄዱ ወታደሮች ተመለሱ ተባለ፨የሞት ዜና:አካላቸዉ የጎደለ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸዉ:እንደ አካል ደኅና እንደ መንፈስ የተሰበሩ ወታደሮች ተመለሱ ተባለ፨ፈለገችዉ ከእነርሱ መኃል የለም፨
የት ሄደ ሞ...ቷ..ል ??አለቻቸዉ፨
አላየነዉም፨ ካምፕ እንደገባን ነበር የተለያየንዉ ከዛ በኋላ ስለእርሱ የምናዉቀዉ ነገር የለም አሏት፨
አጠገቧ ከቆመ ታጣቂ መሳሪያዉን ነጥቃዉ አስርት ጥይቶችን ወደሰማይ አከታተለች፨ጩኸቷን በጥይት ድምጽ አጀበችዉ፨የሞቱ ወታደሮች ለቅሶ ላይ ተገኘች፨ቁስለኞቹን ጠይቃለች፨ሃዘንተኞችን ለማጽናናትም ነበረች፨
ዓመታት አለፉ፨ጉድ የተባለላቸዉ እልቂቶች እየደበዘዙ ሰዎች ወደየእለት ኑሮቸዉ ተመለሱ፨"አባዬስ? እያሉ ከሚጠይቋት ልጆቿ ጋር ብቻዋን ቀረች፨ሞቱም ኑሮዉም አልተሰማም፨ዓመታት ሲደራረቡ በሕይወት ቢኖር ኖሮ እንዴት እስከዛሬ ?ትላለች፨ቁርጡን አልሰማችምና ደግሞ ጭላንጭል ተስፋ ታባብላታለች፨
እሳት ከሚነድበት ምድጃ አጠገብ ተቀምጣ በሃሳብ ሄዳ ነበር ያገኘኋት፨የማዉቀዉ ቀይ ፊቷ ማዲያት ወርሶታል፨ቢነግሩኝ የማላምነዉ አይነት መጎሳቆል ገጿ ላይ ይነበባል፨ሁለተኛዋ ልጇ ታናሿን አዝላ ከወዲያ ወዲህ ትላለች፨
እንዴት ነሽ ?ብቻ ነበር ማለት የቻልኩት፨
"ተይኝ እስኪ የእኔን መኖር ኑሮ ብለሽዉ ነዉ፨
እንደዉ ለልጆቼ ቆሜያለሁ አ"ለችኝ
የዚች ሴት ጎጆና ልብ ዛሬም ክፍት ሆኖ ይጠብቃል፨ብዙ የሃገሬ እናቶች ጎጆዎች የቀሩ ልጆቻቸዉን ጥበቃ ክፍት ናቸዉ፨ለነገሩ ሃገርስ ጥበቃ ላይ አይደለችምን....ምድሯን ከሚፈስባት የልጆቿ ደም የሚታደጉላት ልጆች፨
አንቺ ምስጢራዊት ምድር ለትንሳኤሽ ያብቃሽ ብዬ ተመኝቻለሁ፨
✍️አንቺንአየሁ ገብሬ (𝓮𝓶𝓾𝔂𝓮𝓮)
https://www.tgoop.com/yeesua_queen
BY እዚህ ቤት

Share with your friend now:
tgoop.com/Gazetaw/4164