tgoop.com/HadithAmharic/350
Last Update:
አስሩን የዙልሒጃ ቀናት እንዴት እናሳልፍቻው?
1-እውነተኛ ተውበት ማድረግ
እነዚህንም ሆነ ሌሎች የዒባዳ ቀናትን ለመቀበል ከሰራናቸው ወንጀሎች በመጸጸት ወደ አላህ መመለስ አለብን። አላህ እንዲ ብሏል:-
{ ምእምናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ።﴿ [ሱረ አል-ኑር፣31]
2- ቀኖቹን በአግባቡ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆን
በዙልሒጃ 10 ቀናት ውስጥ ልዩ ትኩረት ሰጥተን አላህ በደነገጋቸው ኢባዳዎች ለማሳለፍ ከወዲሁ ራስን እና ያግዘናል ያልነውን ነገሮች በሙሉ ማዘጋጀ ተገቢ ነው።
አላህ እንዲ ብሏል:- {እነዚያም በኛ መንገድ የታገሉ መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፤ አላህም በእርግጥ ክበጎ ሠሪዎች ጋር ነው።﴿[ሱረቱ አል-ዐንከቡት፣69]
3- ከወንጀል መራቅ
የአላህን ተእዛዛት መፈጸም ወደርሱ እንደሚያቃርብ ሁሉ የከለከላቸውን እና እርም ያደረጋቸውን ነገሮች መዳፈር ከርሱ መራቅን እና ከእዝነቱ ለመባረር ምክንያቶች ናቸው።
🕋 አስሩ የዙልሒጃ ቀናት ያላቸው ደረጃ
1-አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ በነዚህ ቀናት ምሏል
አላህ በሆነ ነገር ሲምል የዛን ነገር ትልቅነት እና ደረጃ ያመለክታል፤ አላህ በትልቅ ነገር እንጅ አይምልም። አላህ እንዲህ ብሏል:-
﴾በጎህ እምላለሁ።በዐሥር ሌሊቶችም።﴿
[አል-ፈጅር፣1-2]
ኢብን ከሢርን ጨምሮ አብዛኞች ሙፈሲሮች እንዳሉት ‘አስሩ ሌሊቶች’ የዙልሒጃ የመጀመሪያዎቹ ናቸው።
2-አላህ በርሱ ውስጥ እሱን ማውሳትን የደነገገባት “የታወቁ ቀናት” መሆናቸው።
አላህ እንዲህ ብሏል:-
﴾በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከማለዳ እንሰሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ፣ (ይመጡሃል)﴿
[አል-ሐጅ፣28]
ኢብን ዐባስ እንዳሉት የታወቁ ቀኖች የተባሉት የዙሒጃ የመጀመሪያዎቹ አስሩ ቀኖች ናቸው።
3- ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከዱንያ ቀኖች በላጭ መሆኗን ተናግረዋል
ከዐብደላህ ቢን ዐባስ(አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) እንደተወራው ነቢዩ( ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ:-
[ከነዚህ አስርት(ከዙልሒጃ የመጀመሪያዎቹ) ቀናት ይበልጥ አላህ ዘንድ በውስጣቸው የሚሰሩ መልካም ስራዎች ተወዳጅ የሚሆኑበት ቀን የለም።] ብለው ሲናገሩ ሶሐቦች፡- ”የአላህ መልእክተኛ ሆ! በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ጂሃድም ቢሆን?“ በማለት ጠየቁ፤ ነብዩ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም):- [ (አዎን!)ነፍሱንና ንብረቱን ይዞ የወጣ፣ ከዚያም አንዱንም ይዞ ያልተመለሰ ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ጂሃድም ቢሆን(አይበልጥም።)] አሉ። (አቡ-ዳውድ ዘግበውታል።)
4- በአስሩ ቀናት ውስጥ የዐረፋ ቀን አለ።
ዐረፋ ከዙልሒጃ የዘጠነኛው ቀን ነው። አላህ ﴾ ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ። ለናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ﴿የሚለውን አያህ ያወረደበት፣ወንጀሎች የሚማሩበት፣ የአላህ ባሮች ከእሳት ነጻ የሚባሉበት ቀን ነው።
5- በአስሩ ቀናት ውስጥ የእርድ ቀን (ዒደል-አድሐ) አለ።
የዙሒጃ አስረኛው የውመነሕር(የእርድ ቀን)የዒድ ቀን ነው። ከቀናቶች ሁሉ ታላቅ ቀን ነው። ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል:-(አላህ ዘንድ ከቀናት ሁሉ ትልቁ የእርዱ(ዒደል-አድሐ) ቀን ነው።(አቡ-ዳውድ ዘግበውታል።)
6-ዋና ዋና የዒባዳ አይነቶች በነዚህ ቀናት ውስጥ ተሰብስበው ይገኛሉ።
ኢብን ሐጀር(አላህ ይዘንላቸው እና) እንዲህ አሉ:- “የዙልሒጃ አስሩ ቀናት ልዩ የሆኑበት ምክንያት ዋና ዋና የአምልኮ አይነቶች እነሱም:ሶላት፣ ጾም፣ ሶደቃ እና ሐጅ በውስጧ ስለተሰበሰቡ ነው። ይህ(ስብስብ) በሌሎቹ ውስጥ አይገኝም።”
🕋በአስሩ የዙልሒጃ ቀናት ውስጥ ከሚሰሩ ታላላቅ ዒባዳዎች:- ሐጅ እና ዑምራ፣ ጾም፣ ሶላት፣ ዚክር እና ደቃ ማብዛት ይገኙበታል።
🔖ሐዲስ በአማርኛ:-
Telegram: www.tgoop.com/HadithAmharic
Instagram: instagram.com/HadithAmharic
FB: fb.com/HadithAmharic
BY ሐዲስ በአማርኛ

Share with your friend now:
tgoop.com/HadithAmharic/350