tgoop.com/HakimEthio/32807
Last Update:
"ሳይነስ አለብኝ?!"
በሀገራችን በአብዛኛዉ የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ ሳይነስ እንደበሽታ ይቆጠራል። ነገር ግን ሳይነሶች (the paranasal sinuses) በተፈጥሮ በሁሉም ሰዉ የሚገኙ ከአፍንጫ ጎን እና ጎን፣ ከአፍንጫ ጀርባ እንዲሁም ከአፍንጫ ከፍ ብለው የሚገኙ በቁጥር 4 ጥንድ የሆኑ በአየር የተሞሉ አጥንቶች ናቸው።
የዉስጥ ግድግዳቸዉ በስጋ የተሸፈነ ሲሆን የሚሞላቸዉ አየር እና የሚያመርቱት ፈሳሽ ወደ ሳይነሶች የሚገባው እና የሚወጣው ከአፍንጫ ጋር በሚገናኙበት ጠባብ ቀዳዳዎች አማካኝነት ነው። አብዛኛዉን ጊዜ አፍንጫን የሚያጠቃ በሽታ (በተለይ የመቆጣት እና የኢንፌክሽን ከሆነ) አብሮ ሳይነሶችንም የማጥቃት ባህሪ አለው።
አፍንጫ እና ሳይነሶች በምን በምን አይነት በሽታ ሊጠቁ ይችላሉ (ዋና ዋናዎቹ)?
-ከአፈጣጠር ችግር ከሚመጡ ችግሮች (ምሳሌ፤ በተፈጥሮ የኋለኛዉ የአፍንጫ ክፍተት ጠባብ መሆን ወይም ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆን (choanal atresia)
-በኢንፌክሽን ሊጠቁ ይችላሉ። ይህም በቫይረስ፣ በባክቴርያ ወይም በፈንገስ ሊሆን ይችላል።
-ምክንያቱ ብዙ የሆነ የረጅም ጊዜ የመቆጣት ችግር (chronic rhinosinusitis)
-በአለርጂ ሊጠቁ ይችላሉ።
-በአደጋ ጉዳት ሊደርስባቸዉ ይችላል።
-ካንሰር በሆኑ ወይንም ካንሰር ባልሆኑ እጢዎች ሊጠቁ ይችላሉ።
ከእነዚህ ዉስጥ በተለምዶ ሳይነስ አለብኝ እየተባለ በማህበረሰባችን ዘንድ የሚጠቀሱት በአለርጂ የሚመጣን፣ በኢንፌክሽን የሚመጣን እና የረጅም ጊዜ የመቆጣት ችግርን (chronic rhinosinusitis) ነው።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸዉ?
ምልክቶቹ እንደየምክንያቱ የሚለያዩ ሲሆን ህክምናዉም እንደዛዉ እንደየምክንያቱ ይለያያል።
ለምሳሌ፦ የአፍንጫ እና የሳይነስ ኢንፌክሽን በሚኖርበት ጊዜ እንደ አፍንጫ ማፈን፣ ወፈር ያለ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ሽታ አለማሽተት ፣ ፊት ክብድ ማለት ወዘተ…።
እነዚህ ምልክቶች ሳይሻሻሉ 3 ወር እና ከዛ በላይ ሲቆዩ ደግም የረጂም ጊዜ የመቆጣት ችግር (chronic rhinosinusitis) አለ ይባላል።
የአፍንጫ እና የሳይነስ አለርጅ ዋና ዋና ምልክቶች ደግሞ በአብዛኛዉ ጊዜ ቋሚ ያልሆነ አፍንጫ ማፈን፣ ዉሃ የመሰለ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ አይን እና አፍንጫ ማሳከክ ሲሆኑ ብዙ ጊዜ ከሰው ሰው የሚለያይ አባባሽ/አስነሽ ምክንያቶች ይኖራሉ።
አፍንጫ/ሳይነስ ዉስጥ የሚወጡ ካንሰር ወይንም ካንሰር ያልሆኑ እጢዎች ብዙ ጊዜ ይሄ ነው ተብሎ የሚገለጥ ምልክት የላቸዉም። ምልክታችዉ እንደየተነሱበት ቦታ እና እንደደረጃዉ የሚለያይ ይሆናል። በአብዛኛዉ ጊዜ ግን አፍንጫ ማፈን እንደዋና ምልክት ይታያል። ከዚህ በተጨማሪም ደም የቀላቀለ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ የአይን እንባ ሳያቋርጥ መፍሰስ፣ በአንድ በኩል ብቻ ማሽተት አለመቻል ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።
ህክምናው
የአፍንጫ እና ሳይነስ አለርጂ: በዋነኝነት አባባሽ ምክንያቶችንን ማስወገድ ከተቻለ ለማስወገድ መቻል። ከዚህ በተጨማሪ ግን በሚዋጡ ወይንም አፍንጫ ዉስጥ በሚደረጉ የተለያዩ መድሃኒቶች ያሉትን ምልክቶች መቆጣጠር ይቻላል።
ምክንያቱ ብዙ የሆነ የረዝም ጊዜ የመቆጣት ችግር (chronic rhinosinusitis) በሚኖርበት ጊዜ ሁለት አይነት የህክምና አማራጮች አሉ።
-የመጀመሪያው የመድኃኒት ህክምና ሲሆን አፍንጫን በጨዉ እና ዉሃ ማጠብ (saline irrigation) , መቆጣትን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን መጠቀም(አፍንጫ ዉስጥ የሚደረጉ) እና አልፎ አልፎ ጸረ ባክቴርያ (antibiotics) መጠቀምን ያካትታል።
-ሁለተኛዉ አማራጭ በኢንዶስኮፕ የታገዘ የሳይነስ ቀዶ ህክምና (endoscopic sinus surgery) ሲሆን ይህ አማራጭ የመጀመርያው አማራጭ አልሰራ ሲል ወይም አይሰራም ተብሎ ሲገመት የሚሰጥ ህክምና ነው።
ከአፈጣጠር ችግር የሚመጡ ችግሮች፣ካንሰር የሆኑ ያልሆኑ እጢዎች፣ ከአደጋ ጋር የሚመጡ ችግሮች በአብዛኛዉ ጊዜ ቀዶ ህክምና የሚፈልጉ ናቸዉ።
Dr Asaye Nibret: ENT Surgeon
Oasis ENT center at kebena Square in front of OLA gas station EPHA building
📞 0940681111 | 0940691111
https://maps.app.goo.gl/tqVyJntu3houJRFXA
@HakimEthio
BY Hakim
Share with your friend now:
tgoop.com/HakimEthio/32807