tgoop.com/Ketbeb_mender/3479
Last Update:
♥️♡:。.。 እዮሪካ 。.。:♡♥️
ክፍል ፲፬
✍ደራሲ - አብላካት
ቀጠል አድርጌም.... "ጋሼ ማይለፍ አይመጣም እንዴ በጣም ቆየ እኮ " አልኳቸው
"ቆየብሽ አይደል ትንሽ እንጠብቀው ይመጣል" ከማለታቸው ከርቀት ወደ እኛ ሲመጣ ተመለከትኩት... ምን እንደሆነ ባላውቅም በእጁ ግን ሞላ ያለ ኩርቱ ፌስታል ይዟል ወደ እኔ እየተጠጋ ...
"አንድ ነገር ላስቸግርሽ" አለኝ
"እሺ"
"ይሄንን ወደ ውስጥ አስገቢውና ምግቡን ደግም በሳህን አድርገሽ አምጪው ብሎ ፌስታሉን ሰጠኝ።ተቀብዬ ወደ ውስጥ ገባሁኝ ፌስታሉ ውስጥ የታሸጉ ሽሮ እና በርበሬ እንዲሁም ደግሞ ሽንኩር እና ቲማትሚ አሉ ለምን እንደሆነ ባላውቅም እንደዚህ ማድረጉ ገርሞኛል..ሌላ ደግሞ በጥቁር ፌስታል የታሰረ ነገር አገኘው ስፈታው ጥሬ ስጋ ነበር እሱን በሳህን አደርጌ ይዤላቸው ወጣሁኝ። ጥሬ ስጋ ብወድም ዛሬ ግን አላሰኘኝም እነሱ ግን እየተጎራረሱ በሉ ፍቅራቸው ያስቀናል ሰው የስጋ ዝምድና ሳይኖረው እንዲህ ይዋደዳል እኔ እና ቤተሰቦቼ ደግሞ የአንድ እናት ልጆች ሆነን መታረቂያው እርቆናል። መወለድ ቋንቋ ነው እሚባለው እውነት ነው።
" አሁን እንሂድ በቃ ጋሼ ሰሞኑን ደግሞ እመጣለን"
አላቸው
"በል ከዚህ በኋላ ስትመጣ እሷን ሳትይዝ ደጄን እንዳትረግጥ"
"አታስብ ጋሼ ይዣት እመጣለው"
"በይ የኔ ልጅ ቸር ቆይኝ" ብለው አቀፉኝ
"አሜን ሰላም ሁኑ" ብለናቸው መኪና ውስጥ ገብተን ሄድን። አሁንም ግን ይሄንን ያህል ከወደዳቸው ለምን ከዚህ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ አላደረጋቸውም እሚለው ጥያቄ እና ስሜን ሲሰሙ የደነገጡት ነገር ውስጤ እየተመላለሰ ነው። ለመጠየቅም ድፍረቱን አጣው
"ከቻልክ እኔን ቅርብ ያለ ቤተክርስቲያን አውርደኝ" አልኩት
"አብረሽኝ እምትቆዪ መስሎኝ ነበር"
"አይ ትንሽ እዛ ልቀመጠ እማይመችህ ከሆነ በታክሲ እሄዳለው"
"እንደዛ ሳይሆን...እሺ አብሬሽ ልግባ ?"
"እሚደብርህ መስሎኝ ነው ከፈለክ ችግር የለውም"
"እንደውም ደስ ይለኛል" ብሎ ወደ ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሄድን እዛ ፀሎታችንን አድርሰን ኣንድ ጥግ ጋር ተቀመጥን።
"ማወቅ እምትፈልጊው ነገር አለ ?"
"አይ። ግን ለምን ጠየከኝ ?"
"አይንሽ ያስታውቃል ውስጥሽ የሆነ ነገር ያለ ስለመሰለኝ ነው"
"መስሎህ ነው እንጂ ምንም የለም" ግን እኮ ብዙ መጠየቅ እምፈልገው ነገር ነበረ ለምን መጠየቅ ፈራሁኝ ..
"እርግጠኛ ነሽ ?"
"እእ ማለት..አለ አይደል መጠየቅ ይኑርብኝ አይኑርብኝ አላውቅም ለዛ ነው"
"ችግር የለውም ጠይቂኝ"
"ለምንድነው ጋሼን ይሄንን ያህል እምትወዳቸው ከሆነ ብዙ ሀብት አለህ ለምን ከዚህ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ አላደረክም ?"
"ያላሰብኩት ይመስልሻል ? ግን በተደጋጋሚ ጠይቄው በተደጋጋሚ እምቢ ስላለኝ ነው። ጋሼን ያወኩት ከሁለት አመት በፊት ነው እናቴ ኩላሊቷ ሙሉ በሙሉ መስራት እንዳቆመና ውጪ ሄዳ ብትታከም እንኳን የመትረፍ እድሏ በጣም አናሳ መሆኑን ከዶክተሮች ስምቼ እንደወጣው ዙሪያው ሁሉ ገደል ሲሆንብኝ ይሄንን ጭንቀት ለመርሳት ካለ ቅጥ ሰክሬ መንገድ ለመንገድ ስደናበር ሌቦች ሊዘርፉኝ ሲሉ ነበር ጋሼ መተው ያተረፉኝ ከዛም ወደዛች ደሳሳ ጎጇቸው ወስደው ጎኔን እንዳሳርፍ አደረጉኝ። ሲነጋም በሌለ አቅማቸው ወተት አፍልተው ፍርፍር አፈርፍረው ያበሉኝ ያጠጡኝ። ችግሬን ሁሉ ነግሬያቸው ተስፋ እንዳልቆርጥና እስከመጨረሻው እንድታገል ብርታት ሆኑኝ እሳቸው ጋር ሁለት ቀን ቆይቼ እናቴ እንደምትድንና ተስፋ እንዳላት አምኜም ወደ ቤቴ ተመለስኩኝ ከአንድ ወር በኋላም እናቴ ውጪ ሄዳ ታክማ ከሙሉ ጤና ጋር ተመለሰች። ወዲያው አዕምሮዬ ውስጥ የመጡት ጋሼ ነበሩ ለሳቸው ጥሩ ነው ያልኩትን ቤት መርጬ በስጦታ መልክ ላበረክትላቸው ወደ ቤታቸው ሄድኩኝ እሳቸው ግን አሻፈረኝ አሉ ምክንያታቸው ደግሞ ባለቤታቸው ከመሞታቸው በፊት ይኖሩባት የነበር ቤት ስለሆነ የሳቸውን ትዝታ ትቶ መሄድ አለመፈለጋቸው ነው። እኔም ስሜታቸው እየገባኝ ሲመጣ ጥያቄዬን አቆምኩኝ። እንጂ ለሳቸው ከዚህም በላይ ይገባቸው ነበር" አለኝ
እራሴን በስንቱ ልታዘበው አሁንስ አፈርኩኝ ለምን ብዬ መጠየቅ እየቻልኩኝ ዘልዬ መፍረድ ላይ ገባሁኝ።
"በጣም ይቅርታ እንደዚህ ስላልመሰለኝ ነው"
"ችግር የለውም ሌላም ሰው ባንቺ ቦታ ቢሆን ሊጠይቀው እሚችለው ጥያቄ ነው"
"ሌላም ጥያቄ ነበረኝ ቅር ካላለህ ?"
"እሺ ጠይቂኝ"
"ለምንድነው ጋሼ ስሜን ስትነግራቸው የደነገጡት ?"
"እእ አይ እሱን ሌላ ጊዜ እነግርሻለው" አለኝ
"እሺ አላስጨንቅህም" ማወቅ ብፈልግም ፊቱ ላይ ግን ጥሩ ነገር ስላላየሁኝ ደግሞ መጠየቁን አልፈለኩትም።
"እንውጣ አይደል እራት በልተን ወደ ቤት እሸኝሻለው"
"አይ ይቅርብኝ ወደ ቤት ልሂድ"
"ዛሬ እኮ ከእኔ ጋር ለማሳለፍ ፈቅደሻል ስለዚህ እምቢ ማለት አይቻልም"
"እሺ ግን ብዙ አልቆይም" ብዬው ከቤተክርስትያኑ ወጣን።
እዛው አካባቢ ካሉት ሆቴሎች ውስጥ አንዱ ጋር ገባን ወንበሩ ላይ ልቀመጥ ስል ፈጠን ብሎ መቶ ወንበሩን ስቦልኝ እንድቀመጥ ጋበዘኝ አምስግኜው ተቀመጥኩኝ። እኔም እሱም እምንፈልገውን አዘን እራሳችንን እየበላን ብዙ ነገር ተጨዋወትን ወደ 3:20 አካባቢ ከሆቴሉ ወተን ወደ ሰፈሬ ሸኘኝ እንደተለመደው መታጠፊያው ጋር ስንደርስ ከመኪናው ወረድኩኝ ያሳለፍኩት ቀን በጣም ደስ ይል እንደነበር ነግሬ አመስግኜው ሄደ። ሳቢ በጣም ናፍቃኝ ስለነበር ዛሬም ስላልተደዋወልን ቢያንስ አይቻት ልመለስ ብዬ ወደ እሷ ቤት ሄድኩኝ። በዛብህ ነበር የከፈተልኝ
"ሰላም አመሸህ በዜ ?"
"ፈጣሪ ይመስገን። እንዴት ነሽ አንቺ ?"
"ደህና ነኝ። ሳቢ አለች እንዴ ?"
"ቅድም የወጣች መች ተመለሰች አንቺ ዘንዳ የመጣች መስሎኝ እኮ ነው"
"ኧረ ከነጋ አልተገናኘንም ስልክ አልደወለችም በጣም ቆየች እንዴ ?"
"ዘመንም የላት ከወጣች እንዲያው አባባ ትንሽ አስቀየሟትና ተበሳጭታ ነበር የወጣች"
"እንዴ ከአባባ ጋር ተጣልታ ነው ምን ተፈጥሮ ?"
"ምኑን አውቄው እህቴዋ እንደው ሲጨቃጨቁ አረፈዱ በዛው ወጥታ ሄደይ ጃኬት እንኳን አልደረበች"
"ታዲያ ለምን አልደወልክልኝም በዜ ?"
"እኔማ አንቺ ጋር ትመጣለይ ብዬ ነዋ"
"በቃ እሺ እኔ እፈልጋታለው አትጨነቅ" ብለው ወደ ክፍል ገብቼ እምትደርበው ልብስ ይዤላት ወጣሁኝ። ስልኳ ላይ ስሞክር ዝግ ሆነብኝ ሳቢ ከአባባ ጋር ከተጣላች ሁሌም ቢሆን የእህቷ መቃብር ስፍራ ነው እምትሄደው በዚህ ሰዓት ወደዛ ቦታ መሄድ ቢያስፈራኝም ግን ደግሞ ሳቢን ብቻዋን መተው አልፈልግም በህይወቴ እንደ መቃብር
ስፍራ እምፈራው ነገር የለም እንኳን በጨለማ በቀን እንኳን በልመና ነው እምሄድላት ዛሬ ግን አስፈልጋታለው። እንደምንም እየተንቀጠቀጥኩኝም ቢሆን ወደ መቃብር ስፍራው ሄድኩኝ በእርግጥ ከመሸ መቃብር ስፍራ ጋር መሄድ ክልክል ነው ዘብኛውም አያስገባም ግን ሳቢ ሁሌም ስትሄድ ትንሽ ብር ሸጎጥ ስለምታደርግለት ለምዶናል። ቦታው በጣም ነው እሚያስፈራው አንዴ በአምስት ሰዓት እሷን ፍለጋ ከአቤል ጋር መተን ለሊቱን ሙሉ ስቃዥ ያደርኩት መቼም አይረሳኝም ዛሬም ልደግመው ነው መሰለኝ።
ይቀጥላል........
ቀጣዩ ክፍል እንዲለቀቅ እያነበባችሁ አስተያየታችሁን አድርሱኝ
ለአስተያየት- @Yetomah_Bot
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
@Ketbeb_Mender
@Ketbeb_Mender
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
BY የብዕር ጠብታ✍📒📖
Share with your friend now:
tgoop.com/Ketbeb_mender/3479