tgoop.com/MedinaTube/612
Last Update:
የዙህር ሰላት ደርሶ ቢላል አዛን እያደረገ ነው። ነቢም ሰ ዐ ወ እያደመጡ ነበር። የቢላልን አዛን እየተከተለ እዛን የሚል ሰው ድምፅ ከርቀት ይሰማል።
ቢላል አዛኑን ካጠናቀቀ በኋላ ረሱል ሰዐወ፦‹‹ማን ነው አዛን ሚለው ከወደ ውጭ በኩል? ›› ሲሉ ጠየቁ። አባ መሕዙራ የተባለ እረኛ በማላገጥ ስሜት አዛን እያለ ግመሎቹን እንደሚያግድ ነገሯቸው።
ረሱልም ሰዐወ በተረጋጋ ስሜት ይህ ሰው ተይዞ እሳቸው ዘንድ እንዲቀርብ ዐሊይን እና ዙበይርን ላኳቸው። ሁለቱም ወደተላኩበት ሂደው አላጋጩን ከነ ግብረ-አበሮቹ ጠፍረው አመጧቸው።
ሁሉም አቀርቅረው ረሱል ሰዐወ ፊት ቆሙ።
‹‹ ከናንተ ውስጥ ማን ነበር አዛን ሲል የነበረው?›› ረሱል ስዐወ ጠየቋቸው።
ፍርሀት ስላደረባቸው ሁሉም ዝም አሉ።
ዝምታቸውን ያስተዋሉት ነቢይም፦‹‹እንግድያ ማን አዛን እንዳለ ለመለየት እያንዳንዳችሁ በየተራ አዛን በሉ›› አሏቸው። ሁሉም አዛን ካሉ በኋላ የአባ መሕዙራ ተራ ደርሶ አዛን ሲል እሱ መሆኑ ታወቀበት።
‹‹ስምህ ማን ነው?›› አሉት ነቢ ወደሱ ጠጋ ብለው።
‹‹አባ መሕዙራ እባላለሁ›› አለ ፈራ ተባ እያለ።
‹‹የመልአክ ድምፅ ይመስል እየተጠበብክ አዛን ትል የነበርከው አንተ ነህ?›› ነቢ ጠየቁት።
ቅጣቱን ለመቀበል ሲዘጋጅ የነበረው ሙሽሪክ በቅጠቱ ፈንታ ይህንን ልብ የሚማርክ ንግግር ሲሰማ ውስጡ ተናወጠ። ረሱል ሰዐወ ከአላጋጩ እረኛ ፊት ቁመው በጭንቅላቱ የጠመጠመውን ፎጣ ከጭንቅላቱ ላይ አውልቀው ፀጉሩን እየዳበሱ፦‹‹አላህ በረካ ያድርግህ፣ ወደ እስልምናም ልብህን ይምራልህ›› አሉት።
በስብዕናቸው የተማረከው አላጋጩ እረኛም የመልዕክተኛው እጅ ከራስ ቅሉ ሳይወርድ ጓደኞቹ እየተመለከቱ ሸሀዳውን ያዘ።
የድምፁን ውበት የመሰከሩለት ይህን እረኛም ረሱል ሰዐወ ወደ መካ ሂዶ አዛን እንዲል ሾሙት።ከዝያች ቀን አንስቶ ወደ መካ የተመመው ይህ እረኛም የመካ ሙአዚን ሁኖ‹‹ነቢ የዳበሱትን ፀጉር መቼም አልላጨውም›› ሲል ስለት ተሳለ።
መካ ላይ ቁጭ ብሎም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የነቢን ሰዐወ ትዕዛዝ እየፈፀመ ከረመ። ከሱ ህልፈት በኋላም ልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ ለ300 አመታት ያህል መካ ላይ አዛን ይሉም ነበር።
Sefwan Ahmedin
ምንጭ፦
سنن النسائي
سنن ابو داود
مسند أمام احمد
@Medinatube
BY Medina Tube || መዲና ቲዩብ
Share with your friend now:
tgoop.com/MedinaTube/612