tgoop.com/MedinaTube/617
Last Update:
ወሎ ሠይድ ዓብዱልቃድር ጀይላኒን "ዓብዱዬ ጅላሌ" ይላቸዋል። እኔም ዓብዱዬ ለአገሩ እንግዳ ሳይሆኑ ወሎዬ ሸኽ ነው የሚመስሉኝ። እሮብ ረፈድፈድ ሲል ጀምሮ ቀልቤ ወደ መንደሬ ሽምጥ ይጋልባል። እናቴ ከሮቢት ገበያ የምትገዛው ትርንጎ መዓዛ አፍንጫዬ ሥር ይመጣል፣ የሚንቦለቦለው የአድሩስ ጭስ ከ’ነ ጋቻው ድቅን ይልብኛል። የአደስና የጠጀሳሩ ሽታ ከተጎዘጎዘው ቄጤማ ትኩስ መዓዛ ጋር ያውደኛል። የቡና ሙቀጫው ቅው ቅው የሚል ድምፅ ያቃጭልብኛል። ከርቤ የመሰለው የዓብዱዬ ቡና ወደ ፍንጃሉ ሲንቆረቆር ከ‘ነ እንፋሎቱ ይታዬኛል። ለቡና ቁርስ በጥቁር ጤፍ ተጋግሮ ቂቤና በርበሬ የሚቀባው አነባበሮ ትውስ ይለኝና ምራቄን ያስውጠኛል። የቡና ቁርሱን በእንሶስላ ቀለም በተዋቡ እጆቿ "ቢስሚላሂ የነቢ ማ‘ድ" እያለች እየቆራረሰች ከሚያምር ፈገግታዋ ጋር የምታጋራን እናቴ ትናፍቀኛለች። ከገበያ መልስ በበራችን የሚያልፉት በግና ፍየሎች ጩኸት ይሰማኛል።
አባባ በግ አይቶ አያልፍም። ስጋ ይወዳል። ኧረ ስጋ ራሱ እሱን ይወደዋል። ዝልዝል ጥብስ፣ ዱለት፣ ቋንጣና፣ ኩላሊት ጥብስ በሚጥሚጣ ደግሞ በተለዬ ይወዳል። ወጣ ወጥ ሲሠራ ስጋ እንደባከነ ነው የሚቆጥረው። ሃኪሞች አዘውትሮ ስጋ መመገብ የሚያስከትላቸውን የጤና ጉዳቶች ሲዘረዝሩ በምፀት ፈገግ ብሎ "ወግድ የሚያመውስ ማጣቱ!" ይላል። ለእንግዳ ክብሩን የሚገልፀው በግ በማረድ ነው። እንግዳ ሲመጣ ቤት ውስጥ ስጋ ቢኖር እንኳን "እንዴት ዱለት ሳይቀምስ?!" ብሎ ይወጣል። አላፊ አግዳሚ ከገጠመው ጥሩ ካልሆነም ወደ ገበያ ይፈተለካል። ወደ ሮቢት ገበያ። ሮቢት ገበያ በጦስኝ ያደጉ፣ ስጋቸው እንደ ነዓነዓ (ነጭ) ከረሜላ ምላስ ላይ የሚሟሟ፣ አጥንታቸው እንደ ሙዝ የሚላጥ በጎች ሞልተዋል። አንዱን ስቦ ይመጣል። እኔም በርሱ ወጥቼ ስጋ እወዳለሁ። ከአጥንት ጋር ስንላፋ ያዬን ጠላት የገጠምን ይመስለዋል። እሮብ ከት/ቤት ስመለስ ታርዶ መዘፍዘፊያ ላይ ጠፈፍ እያለ ያለ ስጋ ይመጣብኛል። ወዲያው እግሬ ኩሽና ያደርሰኛል። ገንፈል እንዲል ጥቂት ተቀንሶ የእንጨት ምድጃ ላይ የተጣደ ስጋ፣ እየተከተፈ ያለ ጨጓራ፣ የሚከተከት ጉበት አያለሁ ደስ ይለኛል። አባባ ሁሌም እንደሚያደርገው አንዷን ኩላሊት አስቀርቶ በከሰል ፍም ያስጠብስና ቆረጥ እያደረገ በሚጥሚጣ ያቀምሰኛል። ስበላ ደስ ይለዋል። ወደ ሳሎን ሳመራ ደግሞ እናቴ የገዛችው ትርንጎ፣ የምታጨሰው አደስ መዓዛ ይቀበለኛል። ሁሉም ነገር ከምኔው እንደሚደርስ ይገርመኝ ነበር። ሰብሰብ ብለን የደረሰውን ለሆድ አድርሰን ቡናችንን ጠጥተን ተመራርቀን ዱዓ አድራጊውም ወደ ዱዓው፣ ከስሳቢውም ወደ ከስቡ፣ እኔም ወደ አስኮላዬ!@medinatube
BY Medina Tube || መዲና ቲዩብ

Share with your friend now:
tgoop.com/MedinaTube/617