tgoop.com/MedinaTube/942
Last Update:
አባዬ ሾንኬ /ጀዉሀረል ሀይደሪ
የሀገራችን ኢትዬጵያና እስልምና የኢልም ታሪክ ስናስብ የሾንኬዉን ሸህ ጀዉሀረል ሐይደሪ መነሳታቸዉ አይቀሬ ነው ። እንዲሁም በ18ኛዉ ክ/ዘመን ኢስላም በኢትዮጵያ ካፈራቸው ሙስሊም ሙጃሂዶች መካከል አባዬ ሾንኬ ቀዳሚ ናቸው ። ይህ ብቻ ሳይሆን ገጣሚ ጸሐፊ ውብ መሪና ጦረኛ ምርጥ ተምሳሌት ነበሩ።
አላህን የመፍራት ጥግ በርሳቸው ላይ ይነበብ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብለው ነው የሚሄዱት። መንፈሳዊነታቸው እጅግ ማራኪ ነበር ። ታላላቅ የሐበሻ አሊሞችንም አግኝተዋል። አባየ ሾንኬ በዚህም ምድር ላይ ፍሬያማ ዘር ዘርተው ንፁህ እና ብፁእ ወደሆኑት ምርጥ የሙስሊሞች ስብዕና መለያ ፣ የሱፊይነት ማዕረግ መጎናጸፍያ ፣ ተላብሰዉት በተግባርም አስተምረው ወደ ዘላለማዊ እዉነተኛ የስኬት አለም የተሻገሩ፣ ከአጼ ዮሀንስ ጦረኞች ጋር በመፋለም በሰይፍ አንገት ላንገት የተሞሻለቁ የዒልሙ ንጉስ ፣ የጅሀዱም ጀግና ተቅይ ሱፍይ ናቸው። ( ረሂመሁ'ዓላህ ፣ ወነፈዓና ቢሒም )
ሸህ ጀውሀር የተወለዱት ከአባታቸው ሀይደር አሊ እና ከእናታቸው ሚስከል አምበር በ1837 አ.ል አካባቢ በድሮው ቃሉ አውራጃ በአሁኑ ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ኮምቦልቻ በልዩ ስሟ 'ጊሰር' በምትባል ስፍራ ነው። በተወለዱበት አካባቢ ቁርአንን በማንበብ ከጨረሱ በኃላ ወደ አቡልፈይድ ሰይዱል ባዕ ሸህ ገታ (ረሂመሁ'ዓላህ) ዘንድ መጡ።የፍቂህ ትምህርት በባቲ አካባቢ ልዩ ስሙ 'ጎጃም'በሚባል ሀሪማ/አምባ/ ላይ ቀርተዋል። በወሎ እና በኢፋት በሚገኙ የእስልምና ማዕከላት በመሽከርከር እውቆቶችን ገበዩ። በዚህ ወቅት በይፋት ወደሚገኙ የእስልምና ማዕከላት 'ኦሲሶ' እና 'ኸይረ ዓምባ' ላይ የዐረበኛ ሰዋሰዉ ህግ ትምህርቶችን በመከታተል እዉቀታቸውን አበልጽገዋል። በይፋት ውስጥም የቆዩበት ጊዜ በትክክል ባይታወቅም ብዙ አመታትን ቆይተው ወደ ወሎ እንደተመለሱ ይነገራል። ከተመለሱ በኃላ እንደገና ወደ ባቲ ጎጃም ተመልሰዋል። ከዚያም 'ድንስር' ተብሎ በሚጠራው አካባቢም ቀርተዋል።
ከአባዬ ሾንኬ አስተማሪዎች በጥቂቱ
- ሸህ ቡሽረል ከሪም ሰይዱል-ባዕ (ገታ)
- ሸህ ቡሽራ ከርበና
- ሸህ አማን ጊሲር/ጉሰይሪ
- ሸህ መሀመድ ሸህ
-ሸህ ሙሀመድ (ኸራምባ/ኢፋት)
-ሸህ ሙሀመድ ጀማሉዲነል አንይ
-ሸህ ኸሊል ነዚል ሞፋ/ደዌ ተጠቃሽ ናቸው።
ሸህ ጀውሃር /አባየ ሾንኬ የቃድሪያን ጦሪቃ ከታላቁ እውቅ አሊምና ሙጃሂድ ሸህ ሙሀመድ ጀማሉዲን አል አንይ 'ሰማኒያን' መዝሐብ ደግሞ ከአሚር ሁሴን አብዱልዋሂድ ኢብን ጌታው አህመድ ጦይብ ተቀብለዋል ። አባዬ ሾንኬ ደዌ ውስጥ ተቀምጠው ኪታብ በሚያቀሩበት ወቅት ወደ ሾንኬ በመምጣት በወቅቱ የሾንኬን ኢማም የነበሩትን ሸህ ዘይኑን እየዘየሩ ይመለሱ እንደነበር ይነገራል።ሸህ ጀውሀር ቢን ሀይደር (ረ.ዓ ) ወደ ሾንኬ ከመጡ በኋላም ሾንክይ፤ ሸህ ሾንኬ ፤ አባዬ ሾንኬ ፤ በሚል መለዮ ስም ይታወቃሉ።
አባዬ ሾንኬ ወደ ሾንኬ መንደር ከመጡ በኃላ በአምባቸው ላይ ከ13 በላይ ትምህርቶችን ማለትም ቁርዓን ተፍሲር፣ ተውሂድ ፣ ፊቅህ ፣ ሀዲስ ፣ ነህው ፣ ሶርፍ ፣ በላገህ ፣ አሩድ ፣ መንጢቅ ወዘተ እንደ ጉድ ያቀሩ ነበር። የቁርአንንና የሀዲስ ጥልቅ እውነታ በመተንተን በዙርያቻው ያሉትን ሁሉ በአንደበታቸው ማርከውና በስብዕናቸው ጠልፈዉ ሾንኬ ላይ አስቀርተዋል። ታላላቅ አሊሞች ከተለያዩ አከባቢ በቁዱስ ቁርዓን ዙርያ አለመግባባት ሲፈጠር የመጨረሻው መፍትሄ አባዬ ሾንኬ ነበሩ።
ኢስላማዊ የትምህርት መስኮችን በአምባቸው ማስተማር ብቻ ሳዬሆን ለጭቆና እጅ የማይሰጡ ፣ ስብዕናቸው ማራኪ አስተሳሰባቸው ምጡቅ ዛሂድ ነበሩ። @medinatube
BY Medina Tube || መዲና ቲዩብ
Share with your friend now:
tgoop.com/MedinaTube/942