tgoop.com/Mgetem/4763
Last Update:
ከዳመናው መሀል ይፈልቃል ኃያል ጢስ
ድል ለሀገሬ ሊሰጥ
በፈረሱ ይነጉዳል የአራዳው ጊዮርጊስ
ይዘምታል በሰማይ አማኝ ህዝቡን ከልሎ
የአምላክ ውብ ምድር
ቅድስት ኢትዮጵያ አትደፈር ብሎ
ይጎርፋል ሰው
ጦር ጋሻውን በእጁ አንጠልጥሎ
ምንሽር አልቤኑን በጀርባው ላይ አዝሎ
በባዶ እግሩ ጋሬጣውን ረቶ
እንዴትስ ይቀራል
ከንጉሱ ከንፈር የማርያም ስም ወጥቶ
ልክ እንደ ጦር እቃ ታቦት ተሸክሞ
ልክ እንደ አዘቦት ቀን በጾም ተሸልሞ
ቅንጣት እህል ሳይጎርስ በእምነቱ ቁሞ
ቅዳሴውን ሳይሽር በሰዓቱ ተገኝቶ
‹‹አሀዱ›› ሲል በህብረት አንድነት ገንብቶ
የዋለ ገበሬ የዋለ ሰራዊት
ድል አፍሶ ቢመለስ ይደንቃል ወይ ጥቂት?
(አይደንቅም)
አቡነ ማቲዎስ እምነትን አግዝፈው
ለሰራዊት ሲባል
‹‹ጾም ይሻር›› የሚል ትእዛዝ ተላልፈው
ከንጉስ ተሟግተው
በመስቀል አሳልመው
ባርከው ተዋጊውን ቢልኩ ወደ ውጊያ
ሰው በእህል ሳይሆን
በእምነት እንደሚረታ
ምስክር ትሆን ዘንድ አሸነፈች ጦቢያ
እኔ ግን
የድል ታሪክ ይዤ
ቆሚያለሁ ፈዝዤ
ተኝቻለሁ ደንዝዤ
አልስራ ጀብድ አልፈጽም ገድል
እንዴት ያቅተኛል
መዘከር እንኳን የአባቶቼን ድል?
ቢገባኝ ኖሮ የነጻነት ክብር
የካቲት ጊዮርጊስ
ስዕለት ባስገባሁ ለመቆሜ ተአምር
በባዶ እግር ሄዶ ጫማ ያለበሰኝ
ከአራቱም አቅጣጫ
ለአንድ አላማ ዘምቶ ሀገር ያወረሰኝ
በዘር ጎጠኝነት
ተከፋፍዬ ቢያይ በእንባው በወቀሰኝ
‹‹ ከአንድነት እርካብ ቁልቁል ተፈጥፍጠህ
በቁንጽል ማንነት ራስክን ለውጠህ
የምትኖር ሁላ አድዋን አስታውሰህ
ሁን እንደ ጥንቱ ፍቅርን ተንተርሰህ
አሻፈረኝ ካልክ ግን
‹‹ማርያምን!›› እፋረድኃለው በሰማይ
በሀገሬ ጀርባ ላይ ፈልተኃል እንደ ተባይ ››
ብሎ ባወጀብኝ
ሽልብታዬን አይቶ
እብደቴን ታዝቦ ከሞቴ ባነቃኝ
ጾም ጸሎትን ትቼ
አርብ ሮብን ረስቼ
ቅዳሴ ሰዓታት
ማህሌት ኪዳንን እኒህን ዘንግቼ
ለሆዴ አድሬ ስኖር እንደ አሳማ
ይደንቃል ወይ እውነት
ተረግጬ ብቀር ልክ እንደ ቄጤማ?
ተንኜ ብቀር ልክ እንደ ጤዛ?
ተሸንፌ ብታይ ወድቄ እንደ ዋዛ?
(አይደንቅም)
ዋ ለእኔ!
ዋ እኔ!
ርግብ ጋር ዘምቼ
ለቀረሁኝ ሞቼ
#ኤልዳን
@eldan29
https://www.tgoop.com/Mgetem
https://www.tgoop.com/Mgetem
BY መንፈሳዊ ግጥም ብቻ
Share with your friend now:
tgoop.com/Mgetem/4763