tgoop.com/MinistryoSHE/1796
Last Update:
በምርምር ስነ ምግባር ላይ የተሰጠው ስልጠና ጠቃሚ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ
********************************************
(መስከረም 15/2014ዓ.ም) ለሁለት ቀናት በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ሲሰጥ የነበረዉ የምርምር ስነምግባር ስልጠና ተጠናቋል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር ሰለሞን ቢኖር በበኩላቸው የምርምር ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያስፈልጉት ቁልፍ ጉዳዮች ዉስጥ አንዱ የምርምር ስነ-ምግባር በመሆኑ ወደፊትም በተጠናከረ መልኩ መተግበር እንዳለበት ገልጸው ስልጠናው በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ ጉልህ ሚና የተጫወቱትን የሐረማያ ዩኒቨርስቲ አመራሮችን እና ሰራተኞችን አመስግነዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ከማስተባበር በተጨማሪ ሳይንስንና የተቋማት ትስስርን በሀገር-አቀፍ ደረጃ እንደሚያስተባብር ገልጸዉ መሰል የምርምር ስነ-ምግባር ስልጠና በሁሉም የከፍተኛና ምርምር ተቋማት ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠልና መተግበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የሐረማያ ዩኒቨርስቲ የምርምር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ለማ እንደተናገሩት በሃገር-አቀፍ ደረጃ በእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ የምርምር ተገቢነት፣ ጥራትና ፍትሃዊነት ትልቅ ጉዳይና ስትራቴጅ ስለሆነ የበለጠ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ሐረማያ ዩኒቨርስቲም የምርምር ተገቢነትና ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ተስፋዬ በጤና ሳይንስ ዘርፍ የተቋቋመ የምርምር ስነምግባር በስራ ላይ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ተመሳሳይ አደረጃጀቶች በሌሎች ኮሌጆች እንደሚቋቋሙ ገልጸዋል፡፡
ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የነበረዉ ስልጠና ትናንት ማምሻዉን ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቅቋል፡፡
BY Ministry of Science and Higher Education (MoSHE)
Share with your friend now:
tgoop.com/MinistryoSHE/1796