tgoop.com/Nuensak/1977
Last Update:
አሸንፈናል .....ግን ይርበናል::
ህመም -፪
በጦብያ ሰማይ ስር ከተጻፉ ኦቶባዮግራፊ መጽሐፍ እንደ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለማርያም የተሳካለት የለም፡፡ የርሳቸውን የዘመን ውጣ ውረድ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡ ለአሁን ግን ......
በኦቶባዮግራፊ መጽሐፋቸው ላይ ሰርክ ስለሚያስገርመኝ ነገር ላውራችሁ፡፡
ገጽ 69፡፡ የጦብያ ሌላኛው ገጽ፡፡
ከአድዋው ድል ማግስት ወደየቤቱ ወታደሩ ሲመለስ:- "....ወታደሮቻችን በሣጥን የተከተተውን ዕቃ እየበረበሩ ከውስጡ እያወጡ ሲሻሙ በሜዳው ሙሉ በየትም መነዛዘሩት፡፡ በሜዳው ላይ በየትም የተበታተነው ዕቃ ብዛቱ የአንድ የትልቅ ከተማ ዕቃ ያህላል፡፡
ተግዞ ተጭኖ የሚያልቅ አይመስልም፡፡ አይኖቼን አሰከራቸው፡፡ ስንቱ ተቆጥሮ ይዘለቃል፡፡ ጣልያኖችስ ይኸን ሁሉ ግሳንግስ በምን ጭነው አመጡት? ወይን ጠጅ -አረቄ-በያይነቱ ዱቄት-ማካሮኒ-ሱካር-ፎርማዥ-ሰርዲን-ኮንሴርቫበያይነቱ-ክብሪት-ሲጃራ-ሥዕል የተሳለበት ጋዜጣ-ብስኩት.....ይህን ሁሉ ጉድ አሞራው ወታደራችን ባንድ አፍታ አመሰቃቀለው፡፡ ይህ ሁኔታ ድል አድራጊዎቹን ፍጹም አስክሯቸዋል፡፡
ባንዲት ክብሪት ወይም ሴንጢ ወይም ብልቃጥ ጠርሙስ ወይም ሰዓት የተነሣ "እኔ ልውሰድ እኔ እብሳለሁ" በማለት እየተጣሉ ጎራዴ ይማዘዛሉ ይቋሰላሉ ይታኮሳሉ ይጋደላሉ፡፡ ባቢሎን እንደፈረሰች ጊዜ ሰዎች ቋንቋ ለቋንቋ ተሳሳቱ፡፡
ተቀምጬ ሳስተውል ብዙ ቆየሁ ከዛም መደባደቡ በረድ ሲል ጠበቅኩና እኔም የተራዬን ለመዝረፍ ተነሣሁ፡፡ ....." ይሉናል፡፡
*ከጦርነት ማግስት የተሸናፊውን ንብረት መውረስ ደንብ ቢሆንም የአድዋው ከዚህ የሚለው መጋደልም ጭምር መኖሩ ነው፡፡ (እንደፊታውራሪ አገላለፅ ከሆነ)
ከትውልድ ትውልድም የኛ መልክ ይኽው ነው፡፡ ድል በቀናን ማግስት መነጣጠቅ መዘረራረፍ፡፡ ያውም እርስበራሳችን፡፡
ድል አድርገናል በጦርነት፡፡ ድል አድርገውናል በድህነት፡፡ ችጋራችን ከዘመን ዘመን አለቀቀንም፡፡ መልካችን እስኪመስል ድረስ ተጣብቆናል፡፡ የወጣቱም ተስፋ የሽማግሌውም እርጅና የህፃናቱም መኮላተፍ ተዛንፏል፡፡
ተሰራርቀናል፡፡ ተቀማምተናል፡፡ ተነጣጥቀናል፡፡
ይሄም የኛ መልክ ነው እና እንቀበለዋለን፡፡
አሸንፈናል፡፡ ግን ይርበናል፡፡
* * * * * * * * *
Graphics:- simon
BY ኑ እንሳቅ😂😂😂
Share with your friend now:
tgoop.com/Nuensak/1977