tgoop.com/Orthodoxbiblestudy/400
Last Update:
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8 ንባብ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች
📖 "አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።" ሮሜ 8፥15
👉 ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ አምነን ተጠምቀን ክርስቲያን የሆንን ካገኘናቸው ጸጋዎች አንዱ የልጅነት ጸጋ እንደሆነ ይገልጻል። የልጅነት መንፈስ የሚለውም የልጅነት ስጦታ ማለት ነው። እግዚአብሔር አምላክም በጸጋ አባታችን ሆኗል። ዮሐ.1:12። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመገለጡ በፊት የሰው ልጆቼ ኩነኔን ይፈሩ ነበር። "...በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።”ዕብ. 2፥14-15 እንዲል። ጌታችን ከተገለጠ በኋላ ግን ምዕመናን ገሃነም እንወርዳለን በእግረ አጋንንት እንረገጣለን ወይም የዲያብሎስ ባርያዎች እንሆናለን ብለው አይፈሩም። "እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።" 2ኛ ጢሞ. 1፥7 እንዲል።
👉 አንዱ ሊቅም ይህን ሲተረጉም "ጳውሎስ ይህን የሚለው መንፈስ ቅዱስን ከተቀበልን በኋላ ክፉ ሥራን ከመፍራት ነጻ ወጥተናል። አስቀድመን በፍርሃት ነበርን ምክንያቱም ሕጉ ከተሰጠ በኋላ ሁሉም በደለኛ እንደሆነ ታስቧልና። ጳውሎስ ሕጉን የፍርሃት መንፈስ ይለዋል ምክንያቱም ስለ ኃጢአታቸው [on account of their sin) የሚፈሩ አድርጓቸዋልና። የልጅነት መንፈስ የሚለው የእምነት ሕግ ደግሞ ኃጢአታችንን ይቅር በማለት ከፍርሃት ያወጣንና ደኅንነትን የሰጠን በመሆኑ ነው። በእግዚአብሔር ጸጋ ከፍርሀት ነጻ ወጥተን የልጅነትን መንፈስ ተቀብለናል። በጸጋው እግዚአብሔርን አባ ብለን ለመጥራት ድፍረትን አግኝተናል። ስለዚህም ምክንያት ጳውሎስ እምነታችን ወደ ትዕቢት እንዳይወርድ ያስጠነቅቃል። ግብራችን "አባ አባት" ብለን ከምንጮህበት ቃል የማይስማማ ከሆነ እግዚአብሔርን አባታችን በማለት መስደብ ይሆንብናል።" ይላል።
👉 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት እንደተሰጠን የልጅነት ጸጋ እንዳገኘን ተናግሯልና። በብሉይ ኪዳን "ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።" መዝሙር 51፥11 ተብሎ እንደተጠቀሰው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነበረ ወይ ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ነቢያትን ትንቢት ያናገረ ነው። 2ኛ ጴጥ.1:21። የኦሪቱና የሐዲሱ ልዩነት በኦሪት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ማንም ሰው እንዳይጠቀምበት የታሸገ የውኃ ጉድጓድ ዓይነት ሲሆን የሐዲሱ ግን ሁሉም እንዲጠቀምበት የሆነ የውኃ ፈሳሽ ዓይነት ነው። በኦሪት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ይሰጡ የነበሩት ለተወሰኑ ሰዎች ለነቢያት ለሃይማኖት አገልጋዮች ብቻ የነበረ ሲሆን በሐዲሱ ሥርዓት ግን ጌታ ባርያ ወንድ ወይም ሴት ሳይለይ ለሁሉም ይሰጣል። ስለዚህ ነው ሐዋርያው “ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።”
ሐዋ.10፥34-35 ያለው። ይህም አስቀድሞ በነቢዩ ኢዩኤል የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። ኢዩ.2:28-29።
BY ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት [The Orthodox study bible]
Share with your friend now:
tgoop.com/Orthodoxbiblestudy/400