tgoop.com/Re_ya_zan/2320
Last Update:
ነገሮችን ያለ ቦታቸው ፈልገህ ታውቃለህ?.... እኔ አውቃለሁ። አባቴን ብዙ ጊዜ ልጅ እያለን አንጠልጥሏቸው በሚገባቸው ፌስታሎች ውስጥ ፈልጌ አጥቼዋለሁ። አባትነት እንደዛ አይነት ነገር ነው.... ሁሉም የዩሱፉ ያዕቁብ አይሆንም፤ ስስቱን ቶሎ አታውቅበትም። አልያም ደግሞ... ፊቱን ያን ያህል የምትመረምርበት ጊዜም አይኖርህም... ምክኒያቱም ብዙ ራቶችህ ላይ ሳትተኛ ባለመድረሱ አትተዋወቁም። ወሳኝ ቀኖችህ ላይ እንኳን በታዳሚያን መሃል ፈልገህ አታገኘውም። ግን ልክ.... የህይወት ናዳ ላይህ ላይ ሊከመር ሲሞክር የሆነ የሚጠብቅህ ዳመና ነገር እንዳለ ልብ ብለህ ቀና ያልክ ቀን... ያኔ የተሳሳተ ቦታ ላይ ስትፈልግ እንደኖርክ ይገባሃል። ሆኖም ማስተዋል እስኪመጣ አንተም ሳታውቀው ሌላ ጎጆ ውስጥ ሌላ ተፈላጊ ሆነሃልና አሁንም የጋራ ጊዜ ማሳለፍ ቀጠሮ ላይ ይቀራል። ግን ተራ ተቀያይራቹ.... ከሱ ይልቅ ባንተ ጊዜ ማጣት መገናኘታቹ ሲቀንስ፣ ደግህን ሲያዩ በኩራት ትከሻህን የደገፉ እኚያ ክንዶች እገዛህን መሻት ሲጀምሩ፣ ጉዳትህን ሲያዩ የሚከስሉ እኚያ ቆዳዎች ከተሸበሸቡ መሰንበታቸውን ስታስተውል... ያኔ ነገሮች ወደ ማረፋፈዱ ከዞሩ ቆይተዋል።
.....እኔን ከጠየቅከኝ.... አባትህን በፍቅር ቃላት ጎርፍ መሃል አቅፎ የሚያባብል ክንድ የመጠበቅ አይነት እየፈለግከው ከሆነ ብዙ ትጠብቃለህ። አባትነት ዱዳ ነው... ቋንቋውን እንድታውቅለት ይፈልጋል። ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ እውር ነው... እናትነትን በመረዳትህ ብቻ ይረካል። አባትነት... ስለመከበሩ ነው፣ በዙሪያህ ያሉት እንዲያከብሩት ባደረግከው ልክ ያስከብርሃል። እንዲፈሩት ባደረግከው ልክ ያስጠብቅሃል። ብስጩነቱ መብዛቱን አትቁጠርበት እልሃለው.... ከጎንህ አለመገኘቱን አትይበት። ፍላጎቶቹን በድርቅናህ አትፎካከርበት። በእጁ ላይ ከምንም የማትቆጠር ደካማ ነገር ቢያመጣም ውደድለት። የከለለህ ዳመና በህይወትህ ሙሉ ሊከተልህ የታደለ ዘላቂ እንዳልሆነ ስትረዳ.... ያኔ እስከዛሬ ከምንም የቆጠርከው ትንሹም ትልቁም የሚናፈቅ የፍለጋህ መልስ እንደነበር ይገለፅልሃል። መልካም እድል።
@Re_Ya_zan
BY TEAM HUDA
Share with your friend now:
tgoop.com/Re_ya_zan/2320