tgoop.com/TIBEBnegni/2497
Last Update:
🕰ሰዎች ስለወቀሱን የማይርድ፤ ስለኮነኑን የማይወድቅ፤ ስለፈረዱብን የማይሞት፤ ስለጠሉን የማይፈራ፤ ስለተዉን የማይደክም መንፈስ በውስጣችን ሊኖር ግድ ይለናል። ከፈጣሪ የተሰጠን እውነተኛው ማንነታች ይህ ነው። ብዙዎቻችን ደካማ ስለተባልን ደክመናል፤ ሃጥያተኛ ስለተባልን ቆሽሸናል፤ ወንጀለኛ ስለተባልን ታስረናል።የሌሎች ሰዎች አስተያየትና መስፈርት ከእውነተኛው ማንነታችን አርቆናል፤ ሰላም ካለበት ስፍራ አውጥቶ የይሉኝታ ሰፈር ኗሪ አድርጎናል።
⏰እውነት ነው ማናችንም ከተጽዕኖ ማምለጥ አንችልም። በመልካምም ሆነ በመጥፎ ሞርደ በየእለቱ መሞረዳችን አይቀርም። ማንነታችን የቤተሰባችን፤ የጓደኞቻችን፤ የአካባቢያችን የባህልና የእምነታችን ውጤት ነው። ሁሉም ነገራችን ላይ የአካባቢያችን ተጽዕኖ ያርፍበታል፤ ልክ ጣሪያ እንደሌለው ቤት በውጪ ያለው ሙቀትና ቅዝቃዜ፤ ዝናብና ንፋሱ፤ አቧራና ሽታው የራሳቸውን አሻራ ያኖሩበታል። በሌሎች ሰዎች ጉንፋን እኛ እናስነጥሳለን፤ በማህበረሰብ በሽታ እኛ የአልጋ ቁራኛ እንሆናለን፤ በሌሎች የእምነት ጥበት እኛ እንጨነቃለን፤። ለዚህ ነው ደስታችን በብዙ ነገሮች ተጽዕኖ ስር የሚወድቀው።
🕰ብዙ ውጫዊ ነገሮች አስደሳች ቢሆኑም ከጊዜ ጋር የተሳሰሩና ሃላፊ ናቸው። ዛሬ ያስደሰተን ጓደኛ ነገ ላይኖር ይችላል፤ ዛሬ ያጌጥንበት ውበት ነገ ይረግፋል፤ ዛሬ የተመካንበት አስተሳሰብ ነገ በቆመበት አይጸናም። ከውጪ የምናገኘው ማንኛውም አይነት ደስታ በመጣበት እግሩ ጥሎን መሄዱ አይቀርም። ከዛም አልፎ ዋጋ ያስከፍለናል። ከጊዜ ጋር የማይለዋወጥ ደስታን ለማግኘት ብቸኛ መፍትሄው ደስታና ሰላምን በውስጣችን መፈለግ ነው። እንደ ኩሬ ውሃ ያነሰች፤ እንደ ኩራዝ መብራት የቀጨጨች፤ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት የደቀቀችም ብትሆንም እንኳን ውስጣዊ ደስታን በልባችን መትከል ነው። ይህ ነው ማንም ሊነካውና ሊደፍረው የማይገባው ስፍራ።
❤️በዚህ ስፍራ ውስጥ ሙሉ ነን፤ እውነተኛ እኛነታችን የሚታየው በዚህ ስፍራ ነው። ወደ ውስጣችን ዘልቀን በዚህ ስፍራ ላይ ቆመን ህይወታችንን ብናየው፤ እንደምናስበው ደካማ አይደለንም፤ የሚጎድለን ብዙ አይደለም፤ ከምንም በላይ በፈጠረን አይን ውስጥ ውብና ንጹህ ነን። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አለ? ደስታና ሰላማችን በሰው እጅ ፤ ፍርድና ቅጣታችን በሰው ወንበር ፈጽሞ አይሁን!!!
💚💚💚💚💚💚💚💚💚💚💚💚💚
ሌሎች እንዲማሩና እንዲለወጡ ምክንያት እንሁን።በፍቅር እንኑር!!!
💙💙💙💙💙💙💙💙💙💙💙💙💙
@TIBEBnegni
@TIBEBnegni
@TIBEBnegni
BY ሰው መሆን...
Share with your friend now:
tgoop.com/TIBEBnegni/2497