tgoop.com/TIBEBnegni/2568
Last Update:
"ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር"
+=========================+
የመጀመሪያው ሰማዕት ዲያቆን እስጢፋኖስን በግፍ ከቤተ ሳይዳ መግቢያ ከአንበሳ በር አውጥተው በድንጋይ ወግረው በግፍ እንዴት እንደገደሉት ዝርዝር ታሪኩ በሐዋርያት ሥራ ላይ ተጽፎአል:: የታሪኩ ማብቂያ ላይ ያለው ዐረፍተ ነገር እስጢፋኖስን በጭካኔ በድንጋይ ከቀጠቀጡት ሰዎች ጋር አብሮ ባይቀጠቅጠውም የሌላ አንድ ተሳታፊ ስም ተጠቅሶአል:: "ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር" (ሐዋ. 7:60)
በዚያች የምታሳዝን ዕለት ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ፈራጅ የነበሩት ጸሐፍት በጭካኔ ታውረው ሆ ብለው በእስጢፋኖስ ላይ ተነሥተውበት ነበር:: በዚያ ባለ ብዙ ተስፋ ወጣት ላይ የድንጋይ ዶፍ ሲያወርዱ ትንሽ እንኳን አልዘገነናቸውም:: ይቅር በላቸው ከማለት ውጪ ክፉ ያልወጣውን ምስኪን ክርስቲያን ወጣት ያለ ርኅራኄ ቀጥቅጠው ገደሉት::
በዚያች ዕለት ሳውል ተሳትፎው ምን ነበር? እርግጥ ነው በእጁ ድንጋይ አልያዘም:: በእስጢፋኖስ ጭንቅላት ላይ ጉዳት ለማድረስ እጆቹን አላስወነጨፈም:: ነገር ግን አንድ እውነታ መካድ አይቻልም:: ሳውል በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ስለነበር በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ከእስጢፋኖስ ሞት ጋር ስሙ አብሮ ተነሥቶአል::
የሰው ልጅ ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ፍጹም አዛኝ መልአክ መሆን እንደሚችል ሁሉ ሁኔታው ከተመቻቸለት ፍጹም አውሬ የመሆን እምቅ ችሎታ ያለው ፍጡር ነው:: ጭካኔም ሆነ ርኅራኄ ከየትኛውም ዘር ብትወለድ ሊኖርህ የሚችል ነገር ሲሆን በሕግ በሃይማኖትና በሰብአዊነት መርሆች ካልተገታ በስተቀር የሰው ልጅ የማያደርገው ክፉ ነገር እንደሌለ የዓለም ታሪክ ያስረዳል::
በዘመናችን የምናየው የንጹሐን ግድያ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉና ብዙ እስጢፋኖሶችን በግፍ የሚገድሉ ጨካኞች አሉ:: በሕግ የሚጠየቁትም የሚቀጡትም እንደዚህ ያሉት ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ናቸው::
ሆኖም በእኛ ሀገር በቁጥር እጅግ የሚበዙት እስጢፋኖስ ላይ ድንጋይ ከወረወሩት አይሁድ ይልቅ በእስጢፋኖስ መገደል የተስማሙት ሰዎች ናቸው:: ከሩቅ ሆኖ "ተነሣ በለው" ማለት ያም ባይሆን "እዚህ ሰፈር ሰው ተገደለ" ሲባል "እዚያ ሰፈርስ ሞቶ የለ ወይ?" እያሉ ለማካካስ መሞከር : ይበለው ይበላት ብሎ መናገርም በእስጢፋኖስ መገደል መስማማት ነው::
ወዳጄ በክፋት ውስጥ በቀጥታ መሳተፍም : ከሩቅ ሆኖ ቃላት መወራወርም : ጥላቻን መዝራትም : ሌላውን እየናቁ ራስን መኮፈስም ዞሮ ዞሮ በፈጣሪ ፊት ስለ ንጹሐን ደም ማስጠየቁ አይቀርም::
እስጢፋኖስን የመሰሉ በግፍ የተገደሉ ሁሉም ሰማዕታት በፈጣሪ ዙፋን ፊት ቆመው "እስከመቼ አትፈርድም?" ማለታቸው ስለማይቀር ሳናውቀው ዕዳ በራሳችን ላይ እንዳናከማች ከየትኛውም የጥላቻ ንትርክ ራሳችንን እናውጣ::
እስጢፋኖስ ሲገደል ሳውል የተስማማ ቢሆንም በመጨረሻ ግን "ይቅር በላቸው" በሚለው የእስጢፋኖስ ጸሎት ምክንያት በክርስቲያኖች መገደል ከመስማማት ወጥቶ በክርስትናው መከራ የተቀበለ ሐዋርያ ሆነ::
በጣም የሚደንቀው የእስጢፋኖስን ቤተሰቦችም ያጠመቀው በልጃቸው መገደል ተስማምቶ የነበረው ሳውል (ጳውሎስ) ነበረ:: የልጃችን ደም አለበት ሳይሉ ይቅር ብለው የተጠመቁት ጥፋትን በጥፋት ማረም እንደማይቻል ተረድተው ነበር:: ክርስትና ዘር ቆጥሮ የእኔን ወገን እንዲህ አድርገሃል ብሎ የመበቀል ሕይወት ሳይሆን
ባለፈ የጥላቻ ቁስል ማነከስን ትቶ በይቅርታ ዛሬና ነገን መኖር ነው:: ለትውልድ ቂም ማውረስ ለልጅ መርዝ ከማጠጣት አይተናነስም : ይቅርታን ማስተማር ግን ለልጅ በሰማይም በምድርም ርስት እንዲያገኝ ማድረግ ነው::
ኢትዮጵያ እግር አውጥታ ከእኛ እንዳትሸሽ እነዚህ ሦስት ነገሮች ከእንግዲህ በሀገራችን አይኑሩ
- በግፍ የሚገደል እስጢፋኖስ
- በግፍ የሚገድሉ ፈሪሳውያን
- በእስጢፋኖስ መገደል የሚስማሙ ሳውሎች
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሐምሌ 9 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
@TIBEBnegni
@TIBEBnegni
@TIBEBnegni
BY ሰው መሆን...
Share with your friend now:
tgoop.com/TIBEBnegni/2568