tgoop.com/TarikuAbera/3162
Last Update:
አንዳንድ ሰዎች ከእውቀት ማነስ የተነሳ የአዲስ ኪዳኑን ታቦት ሲያጣጥሉና ሲነቅፋ ባልተገራ አንደበትም ጣዖት ነው ሲሉ እንሰማለን ፈጽሞ ስህተት ነው።የከበረው የክርስቶስ ስም የተጻፈበት ታቦት ጣዖት አይባልም።እንኳንስ መንፈሳዊ ምግባችንን ለምንፈትትበት ቅዱስ ምስዋዕ ለሥጋዊ ምግባችን እንኳን ማዕድ የምናስቀምጥበትን ገበታ በክብር እንይዛለን ።የከበረው የክርስቶስ ደምና ሥጋ ለሚቀርብበት ቅዱስ መሰዊያማ የበለጠ ክብር ልንሰጥ ይገባል። አንዳንዶች እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው የዓለም ማኅበረሰብ ይልቅ በልዩ ሁኔታ ከታቦት ጋር ያለንን ልዩ ሕብረት በመመልከት ሌሎች ሀገሮች የማይጠቀሙትን እናንተ ኦርቶዶክሳውያን እንዴት ትጠቀማላችሁ ይሄ ወንጌልን አለመረዳት ኦሪታዊነት ነው ይላሉ በጣም ስህተት ነው።
ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን በጥልቀት ልናጠና ይገባል ሌሎች ሀገራት ክርስትናን የተከተሉትና ወንጌልን የተቀበሉት ቀድሞ ከነበሩበት ከጣዖት አምልኮ በሐዋርያት ስብከትና በብዙ ድንቅ ተአምራት ተላቀው ወጥተው ነው ።እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ወደ ሕገ ወንጌል የተሻገርነውና ክርስትናን የተቀበልነው ቀድሞ ከነበርንበት ከሕገ ኦሪት ወጥተን ነው።ታሪክ በግልጽ እንደሚያስረዳን ከእስራኤል ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን ሕግና መንፈሳዊ ሥርዓት እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረች ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ነች ።ሌላው ዓለም ጣዖት በሚያመልክበትና በየጋራውና በየወንዙ እንግዳ አማልክትን በሚከተልበት የጨለማ ዘመን የአብርሃም አምላክ እያለች እግዚአብሔርን ታመልክ የነበረች ቅድስት ሀገር ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ነች። ስለሆነም ለታቦት ክብር መስጠታችን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ከመጣው የአምልኮ ትውፊታችን ጋር የተያያዘ ነው እንጂ እንደ ውሃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነ ዘመን ላይ የተፈጠረ ክስተት አይደለም ።
ሌሎች ሀገራት ግን ከጣዖት አምልኮ የመጡ በመሆናቸው እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሥርዓት የላቸውም። ይሁን እንጂ አዲስ ኪዳንን ከተቀበሉ በኋላ በየቤተመቅደሳቸው የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚፈትቱበት እንደ ታቦት ለመሰዊያነት የሚጠቀሙበት የከበረ ንዋይ አላቸው። ልብ እንበል የክርስቶስ ሥጋና ደም መሠጠቱን የሚያምን አንድ ክርስቲያን ይህ የከበረ ሥጋና ደም እንደ ተራ ማዕድ በየቦታው ፣ በየጠረጴዛው ሊቀርብ ይችላል ብሎ ለማሰብ እጅግ ይከብደዋል፡፡
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ስደትዋ እስካበቃበት ዘመን ድረስ በሒደት እየተሻሻለ በመጣ የቤተ መቅደስ ሥርዓት የሐዲስ ኪዳኑን መሥዋዕት በክብር ለመሠዋትና ለምእመናን ለማቀበል በቅታለች፡፡ የበግና የፍየል ደም ይሠዋ በነበረበት የኦሪት ዘመን እንኳን ለብቻው ትልቅ መሠዊያ ተዘጋጅቶ ፣ መሠዊያው ተቀድሶ ሰው በማይገባበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በክብር ተቀምጦ ነበር፡፡ በድንኳኒቱ ውስጥ የሚያገለግሉት አሮንና ልጆቹም የተለየ ልብስ ለብሰው የበጉን ደም በመሠዊያው ዙሪያ ባለው ቀርነ ምሥዋዕ (የመሠዊያ ቀንድ) ላይ እየቀቡ ሥርዓቱን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ለበግና ለፍየል መሥዋዕት ይህ ሁሉ ክብር ከተሠጠ እንደ በግ ስለ ሁላችን ኃጢአት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ እንደ ሊቀ ካህናትነቱ እጁን በመስቀል ላይ ዘርግቶ የሰዋውና ዓለም እንዲድንበት እንካችሁ ብሉ ብሎ የሠጠን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብበት መሠዊያ ምንኛ የከበረ ይሆን?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥጋ ወደሙ ‹መሠዊያ› የምትለው ታቦት በቅርጽም ፣ በአገልግሎትም ፣ በክብርም በኦሪት እግዚአብሔር ለሙሴ ከሠጠው ታቦት ጋር አንድ አይደለም፡፡ የቀደመው ታቦት በአራት ካህናት የሚያዝ በውስጡ ጽላት የሚቀመጥበት ሲሆን የአሁኑ ታቦት ግን የጽላት ቅርጽ ያለው ጽሌ (ሰሌዳ) ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሐዲስ ኪዳኑን ታቦት በሦስት ስያሜ ትጠራዋለች - የቃልኪዳኑ ታቦት ፣ ጽላት እና መሠዊያ ብላ፡፡ የቃልኪዳኑ ታቦት የሚባለው እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስላደረገው ስለ ቀድሞ ቃልኪዳን ሳይሆን ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› ተብሎ ስለተሠጠው እና ‹‹ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› ብሎ ጌታችን ስለ ሠጠን አዲሱ ኪዳን ነው፡፡ (ማቴ. 26፡ 26-30) የቃልኪዳኑ ታቦት የሚባለው በሥጋ ወደሙ ስለተሠጠን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ታቦት መባሉ ደግሞእግዚአብሔር በረድኤት የሚያድርበት ፣ በሥጋ ወደሙ ደግሞ በአካል የሚገለጥበት ዙፋን ስለሆነ ነው፡፡ ጽላት (ሰሌዳ) የሚባለው ዐሠርቱ ትእዛዛት ተጽፈውበት አይደለም፡፡ የሕግ ሁሉ ፈጻሚ የሆነው የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚለው የከበረ ስሙ በታቦቱ ላይ ስለተጻፈ ነው፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን /ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ/ ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ /ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ/)
አንዳንድ ሰዎች ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ከኦሪቱ ጋር አይመሳሰልም!›› ብለው እንደ ትልቅ መከራከሪያ ሲያውጁ ማየት እጅግ ያስገርማል፡፡ አንዴ ‹ኦሪታዊት ነሽ› አንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹ለምን እንደ ኦሪቱ አልሆንሽም›› ብሎ ንትርክ ግራ ያጋባል፡፡ የኦሪቱን ያልመሰለው አሁን ያለነው ሐዲስ ኪዳን ላይ ስለሆነና የታቦቱ አገልግሎት የተለየ ስለሆነ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ ‹‹የኦሪት ጽላት እግዚአብሔር በደመና ተከናንቦ ሙሴንና አሮንን የሚያነጋግርበት ለእስራኤል ብቻ በረድኤት የሚገለጥበት ዙፋን ነበር፡፡ ይህ ግን (የሐዲስ ኪዳኑ ታቦት) የአምላክ ሥጋና ደም የሚፈተትበት ጌታችን ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ እያለ ያመኑትን የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ (መሠዊያ) ነው፡፡ ክብርና ስግደትም የሚደረግለት ለዚህ ነው፡፡›› (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 109)
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በታቦታቱ ሁሉ ላይ የተጻፈው ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚለው የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ስም ነው፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች ታቦት ላይ ይጻፋል አልፋ፣ወዖ፣ቤጣ ፣የውጣ ፣ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው የሚሉ ምሥጢራዊ ትርጉም ያላቸው ስሞች ይጻፋሉ።ታቦት ሲወጣ በአክብሮት እጅነስተን የምንበረከከው ከስሞች ሁሉ በላይ ለሆነው ታላቅ ስም ነው። ከስሙ ጋር ደግሞ በሁሉም ታቦታት ላይ የሚከተለው ጥቅስ በግእዝ ተጽፏል፡፡ ‹‹ከመ ለስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይስግድ ኲሉ ብርክ ዘበሰማያት ወዘበምድር›› ‹‹ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ›› የሚል ነው፡፡ (ፊልጵ. 2፡10) በታቦቱ ፊት የሚሰግድ ሰው ለምን እንደሚሰግድ በታቦቱ ላይ የሚጻፈው ይህ ጥቅስ ያስረዳናል፡፡ ምክንያቱ ‹‹ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይሰግዱ ዘንድ›› ስለሚገባ ነው፡፡ የክርስቶስ ሥጋ እንደሚቆረስ ደሙ እንደሚፈስስ የሚያምን ሰው በዚህ መሠዊያ ፊት በፍርሃት ለክርስቶስ ይሰግዳል፡፡ ሥጋ ወደሙን ‹‹ተራ መታሰቢያ ብቻ ነው›› የሚል ሰው ግን በመሠዊያው ፊት እንዲሰግድና መሠዊያውን እንዲያከብር አንጠብቅም፡፡
BY Tariku Abera
Share with your friend now:
tgoop.com/TarikuAbera/3162