tgoop.com/TarikuAbera/3168
Last Update:
"የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። "ኤር 3፥16
መ/ ር ታሪኩ አበራ
ሰላም ለሁላችሁ ይሁን አንዳንድ ወገኖች ይህንን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ በመምዘዝ ብቻ ቃሉ የተነገረበትን ምክንያትና ዘመን ባለማስተዋል ታቦት አያስፈልግም፣ ታቦት ተሽሯል እያሉ ራሳቸውን አስተው የእምነትና የሥርዓት ቤት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ሲነቅፋ ይሰማል።አለማስተዋል ነው እንጂ ኤርምያስ 3፥16 ላይ የተቀመጠው ቃል የተነገረው በኤርምያስ ዘመን ለነበሩ ቤተ እስራኤል ነው ።ቃሉ የተነገረበትም ምክንያት የእስራኤል ልጆች ከጣዖት አምልኮ ተመልሰው እግዚአብሔርን ብቻ ቢያመልኩ፣ከአመጽና ከርኩሰት ተለይተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቢመላለሱ ጠላት እንደ ማይነሳባቸው በምድራቸውም ረሀብና ችግር እንደ ማይመጣባቸው የተነገረና እነዚህ መከራዎች ከራቁላቸው ደግሞ የቃልኪዳኑን ታቦት አውጡልንና ወደ ጦርነት እንሂድ ብለው እንዳለፋ ዘመኖቻቸው እንደ ማይሹት የተነገረ ነው እንጂ የታቦትን ክብር ለማናናቅ አይደለም።ሙሉ ቃሉን
በማስተዋል ካነበብነው ሐሳቡ በግልጽ ተቀምጧል።
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕ. 3)
----------
16፤ በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም።
17፤ በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም።
18፤ በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።"
አንባብያን በጣም አስተውሉ !! እስራኤላውያን በተለያየ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ስንመለከታቸው ካህናትና ሌዋውያኑን ታቦቱን አምጡልን የሚሉት ረሃብ፣በሽታ ፣ጦርነት እና መከራ ሲደርስባቸው እንደ ነበር በግልጽ ተጽፏል። በኤርምያስ ዘመን ግን እግዚአብሔር በእውነተኛው ነቢይ በኩል ያስተላለፈላቸው መልዕክት ከቁጥር 12 ጀምሮ ስናነበው በፍጹም ልባቸው ወደ እግዚአብሔር ቢመለሱ በምድራቸው ላይ ሰላም እንደሚሆንላቸው፣ ምድራቸውም እንደ ምትባረክ ይናገርና እንዲህ ዓይነቱን ሰላምና በረከት ካገኙ ደግሞ ካህናቱን ታቦቱን አውጡልን ብለው በጭንቀት እንደማይሹት ይገልጻል። እስራኤላውያን በመከራቸው ዘመን ከፍልስጥኤም ጋር ለመዋጋት ታቦቱን ተሸክመው እንደሄዱ ሁሉ ከእንግዲህ ግን ጦርነት እንደማይሆንባቸው የተገለጸ ቃል ነው።ይህም በኤርምያስ ዘመን ተፈጽሟል።
ታቦቱንማ ራሱ እግዚአብሔር ክብሩን በሕዝቡ መሐል ይገልጥበት ዘንድ ወዶ ፈቅዶ ለሙሴ ይሰራ ዘንድ ያዘዘው የሕጉ ማደሪያ ነው እንጂ ዛሬ ሰዎች ባለመረዳትና በጥራዝ ነጠቅ እውቀት እንደ ሚናገሩት ታቦት ጣዖት አይደለም።
ታቦትን ጣዖት ብሎ መናገር ይሰራ ዘንድ ያዘዘውን ራሱ እግዚአብሔርን እንደ መስደብ ነው ሎቱ ስብሐት።ዘጸአት 25፥8- 22 ላይ እንዲህ ሲል እግዚአብሔር አዟል ፦
"በመካከላቸውም፡ዐድር፡ዘንድ፡መቅደስ፡ይሥሩልኝ...ከግራር፡እንጨትም፡ታቦትን፡ይሥሩ...የስርየት፡መክደኛውንም፡በታቦቱ፡ላይ፡ታደርገዋለኽ፤እኔም፡የምሰጥኽን፡ምስክር፡በታቦቱ፡ውስጥ፡ታኖረ ዋለኽ።በዚያም፡ከአንተ፡ጋራ፡እገናኛለኹ፤የእስራኤልንም፡ልጆች፡ታዝ፟፡ዘንድ፡የምሰጥኽን፡ነገር፡ዅሉ፥በምስክሩ፡ታቦት፡ላይ፡ባለው፡በኹለት፡ኪሩቤል፡መካከል፥በስርየት፡መክደኛውም፡ላይ፡ኾኜ፡እነጋገርኻለኹ።"
ይህ ከላይ የገለጽኩት እንግዲህ በብሉይ ኪዳን የነበረው የታቦት ዓላማና አገልግሎት ነው።ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ ።እግዚአብሔር በመከራችን ጊዜ ሰላም እንድናገኝ በችግርና በስቃያችን ሰዓት መማጸኛ እንዲሆነን የሰጠን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ነው ።ምክንያቱም እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን የተሻለውን ማዳንና ክብሩን የገለጸው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።ስለዚህ ዛሬ መማጸኛችን በመከራ ሰዓት ይዘን የምናወጣው ጋሻና ክብራችን ኢየሱስ የሚለው ስም ነው።ይህ የከበረ ኃያል ስም ዛሬ በቅዱስ ታቦቱ ላይ ተጽፏል።
ታዲያ አሁን ታቦት ምን ያደርጋል? ቢባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንት ሌላው ዓለም ጣዖት አቁሞ ሲያመልክ ኢትዮጵያውያን ግን በታቦት እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንዲኖሩ አድርጋለችና የማንነት መገለጫ /identity /ስለሆነ አክብራ ይዛ ትውልድ ሁሉ የአባቶቹን ታሪክና መንፈሳዊ ባህሉን እንዲጠብቅ እያደረገች ነው።በታቦቱ ዛሬ ክርስቶስ ከብሮበታል አማናዊ ሥጋውና ደሙ ይፈተትበታል።
የማንነት መገለጫ የሆነ መንፈሳዊ ትውፊትን ይዞ ማቆየት ደግሞ ለትውልድ በጣም ጠቃሚ ነው።ዛሬ ላይ እንደ ምንመለከተው አውሮፓውያንና ሌሎችም ምዕራባውያን ክርስትናን ይዞ መጓዝ ሲከብዳቸውና ከሃይማኖት መስመር ሲወጡ ወደ ጥንቱ ማንነታቸው ማለትም ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ወደነበረው አይደንቲቲያቸው ነው የተመለሱት ።ይኽውም ወደ ሰይጣን አምልኮ፣ወደ ሰዶማዊነት፣ወደ ዘመናዊ ጥንቆላ ወዘተ፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን መንፈሳዊ ትውፊት ይዛ ምድሪቱ ላይ ማቆየቷ ትውልዱን በሃይማኖት ጥላ ሥር ይዞ ለመቆየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪም ዛሬ ታቦት በቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጽፎበት በቅዳሴ ሰዓት ሥጋ ወ ደሙ መፈተቻ ነው እንጂ ታቦቱ ራሱ አምላክ ነው ብለን እያመለክነው አይደለም።ታሪካችንን ትውፊታችንን እምነታችንን ይበልጥ አጠንክረን ልንይዝና ለትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል። ዛሬ ሰለጠንን ያለው ትውልድ ሃይማኖት የለሽና ሰይጣኒዝምን ተከታይ እየሆነ ያለው ይህንን የመሰለ መንፈሳዊ ዕሴት፣የከበረ የእምነት መገለጫ ትውፊት ስለሌለው ነው።
ዛሬ በሃገራችን እንደ አሸን የፈሉ ሐሰተኛ ነቢያትና ፀረ ኦርቶዶክስ የእምነት ድርጅቶች ቅዱስ ታቦቱን ሲነቅፉ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ሲተቹ የሚውሉት በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ስለሌላቸውና መስራቾቻቸው ምዕራባውያን የሚጭኑባቸውን የወደቀ አስተሳሰብ ተሸክመው ስለሚዞሩ ነው ።
አንዳንድ ወፍ ዘራሽ የሆኑ አሳዳጊ የበደላቸው ወጣቶች በየመንደሩ በታቦተ እግዚአብሔር ለመሳለቅ የሚያሳዩት ርካሽ ተግባር በ80 ሚሊየን ኦርቶዶክሳዊ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ለማፌዝ የሚደረግ የትዕቢት ተግባር በመሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እነዚህን ውርጋጦች ልክ ማስገባት ግዴታችሁ ነው። ይህንን ለማስቆም ፓሊስ፣ሲኖዶስ፣ቤተክህነት ይወጣው ብሎ እጅን አጣምሮ መቀመጥ አሳፋሪ ድንዛዜ ነው።
ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኩራት የዓለም ብርሃን ናት።
ለሌሎችም ሼር አድርጉት
BY Tariku Abera
Share with your friend now:
tgoop.com/TarikuAbera/3168