tgoop.com/Terbinos/12715
Last Update:
ነቢያት በትንቢት መነጽር ያዩት እርሱን እንጂ ሌላ አይደለም፤ ሐዋርያትም የበሉት ከእርሱ ጋር እንጂ ከሌላ ጋር አይደለም፡፡ በአባቱ ዕቅፍ የነበረው እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፤ በጲላጦስ የተፈረደበትም እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም። በመስቀል ላይ በሚስማር የተቸነከረው እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፤ በዘባነ ኪሩብ ላይ የነበረውም እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ጻድቁ ዮሴፍ በጨርቅ የጠቀለለው እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፤ በእጁ መዳፍ ፍጥረታትን የያዘውም እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በመቃብር ያደረው እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ሱራፌል ያመሰገኑትም እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም። በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነስቶ ሰው የኾነውም እርሱ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡
••
እግዚአብሔር በዕልልታ ዓረገ፡፡ አምላክ በመለከት ድምፅ ዓረገ፡፡ ከዘለዓለም አንሥቶ ፈጣሪ የኾነው፣ ኹሉንም ነገር ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣው፣ አዳምን የሠራው፣ የሰው ልጆችን የፈጠረው፣ ደስ ያሰኘውን ሄኖክን ወደ ሕይወት ያሸጋገረው፣ ኖኅን ከዓለም ጋር የጠበቀው፣ አብርሃምን ከከለዳውያን ምድር የጠራው፣ ይስሐቅን የነገረ መስቀል ምሥጢር ምልክት እንዲኾን ያደረገው፣ ያዕቆብን የዐሥራ ኹለቱ አዕማድ ሥር እንዲኾን ያደረገው፣ ለኢዮብ ትዕግሥትን የሰጠው፣ ሙሴን የሕዝቡ መሪ እንዲኾን አድርጎ የሾመው፣ ሳሙኤልን ከእናቱ ማኅፀን አንሥቶ በትንቢት የሞላው፣ ከነቢያት መካከል ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ የቀባው፣ ለሰሎሞን ጥበብን የሰጠው፣ ኤልያስን በእሳት ሰረገላ የወሰደው፣ ነቢያት መጻእያትን እንዲያዩ ያደረጋቸው፣ ለሐዋሪያት ሀብተ ፈውስን የሰጣቸው፥ “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎም አሰምቶ የነገራቸው እርሱ ዛሬ በዕልልታና በመለከት ድምፅ ዓረገ፡፡
••
ወደ ሰማያት በዕልልታ ያረገው፣ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠው የክብር ጌታ ይህ ነው፡፡ መላእክትና አለቆች ኃይላትም ይገዙለታል፡፡ ቁርጥ ልመናችንን የሚቀበል፣ ወደረኞቻችንን ድል እንድንነሣቸው ኃይልን የሚሰጠንም እርሱ ነው፡፡ “እባቡን ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ እነሆ ሥልጣን ሰጠኋችሁ” እንዳለ በክፉ መናፍስት ኹሉ ሥልጣን ያለው እርሱ ነው፡፡
••
ነውር ነቀፋ የሌለብህ ንጹሃ ባሕርይ ሆይ! በነፍስ፣ በሥጋና በመንፈስ ጠብቀን፡፡ ይህን በዓል እናከብረው ዘንድ የሰበሰብከን የኹሉም አምላክ የኾንህ ጌታችን ሆይ ! በጽድቅ ፍሬ የተሞላን አድርገን፡፡ ለአንተም ከባሕርይ አባትህ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወትህ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ክብር፣ ኃይልና ስግደት ኹሉ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ይገባል፥ አሜን፡፡
••
አምላክ በእልልታ ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። መዝ ፵፮ ፡ ፭
••••
የቴሌ ግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ - https://www.tgoop.com/Terbinos
የቲክ ቶክ የገፃችን ይመልከቱ - https://www.tiktok.com/@yeamanuelljochi
የፌስቡኩ ገፃችን ይመልከቱ - https://www.facebook.com/terbinos
BY ❤️ የአማኑኤል ልጆች ❤️
Share with your friend now:
tgoop.com/Terbinos/12715